ATRONS MEDIA INTERNET TV

ATRONS MEDIA INTERNET TV በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብ ሚዲያ ነው።


Recent Videos

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ክብረ በዓል ጎንደር ሐምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ምቅዱስ ሚካኤል ክብረ በዓል 2011 ዓ/ም ጎንደር

Megabi Tibeb Bemnet .......Sibket


ትዕግስተኛው ቅዱስ ኢዮብ - Saint Eyob Full Movie


ሐዲስ ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት?
ቅዱሳን ጻድቃን በመንፈሳዊ አርአያነታቸው፣ በጸሎታቸውና በትምህርታቸው ከከበቡን የነፍስ ጠላቶች፤ ከርኲሳን መናፍስትና ከጨለማው ልጆች፣ ከክፉ ሰዎች ሽንገላና ተንኰል ለመሰወርና ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር የተቀበሉት ሥልጣን ምን ጊዜም ይሠራል፡፡ በጻድቃን መኖር ሀገር ከጥፋት ትድናለች፡፡ የጻድቃንን ስም ጠርቶ እግዚአብሔርን በመለመን በረከትና ረድኤት ይገኛል፡፡ ስለ ጻድቃን ብሎ እግዚአብሔርም ምሕረቱን ያድላል፡፡ ጻድቃንን ማሰብ ሥራቸውን መዘከር ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ያጐለምሳል፡፡ በነፍስ በሥጋ ይታደገናል፤ ይረባናል፤ ይጠቅመናል፡፡

ስለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያናችን ጻድቃንን እንድናስባቸው፣ በስማቸውም ለድሆችና ለጦም አዳሮች እንድንመጸውት፣ መታሰቢያቸውን እንድናደርግ የምትመክረን፤ የምታስተምረን /ማቴ.፲፥፵፩-፵፪/፡፡ ቅዱሳን ጻድቃን በሕይወተ ሥጋ ሳሉም ኾነ ከሞቱ በኋላ በዐጸደ ነፍስ ኾነው በጸሎታቸው ለሚታመኑ፣ በቃል ኪዳናቸው ለሚማጸኑ ምእመናን በመጸለይና ወደ እግዚአብሔር በማማለድ ድኅነተ ሥጋ፣ የድኅነት ነፍስን የሚያስገኙልን የችግር ጊዜ አማላጆቻችንና አስታራቂዎቻን ናቸው፡፡ ከእነዚህ ቅዱሳን መካከል ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንደኛው ናቸው፡፡

‹ተክል› ማለት ፍሬያማ ዕንጨት፣ ዛፍ፣ ቅመም፣ ቅጠላ ቅጠል፣ የሚበላ፣ የሚሸተት፣ ገነታዊ ዕፅ፣ እንዲሁም ሕግ ሥርዓት ማለት ነው /ማቴ.፲፭፥፲፫/፡፡ ‹ሃይማኖት› ማለት ደግሞ በሀልዎተ እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር የዅሉ አስገኚ መኾኑን፣ በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት፣ በቅዱሳን ተራዳኢነት ማመን አምኖም መመስከር ማለት ሲኾን ተክለ ‹ሃይማኖት› የሚለው ሐረግም የሃይማኖት ተክል፣ ይኸውም የጽድቅ ፍሬን ያፈራ፣ ከኃጢአት ሐሩር ማምለጫ ዛፍ፣ ምእመናንን በቃለ ወንጌል ያጣፈጠ ቅመም፣ መዓዛ ሕይወቱ የሚማርክ፣ ቢመገቡት ረኃበ ነፍስን የሚያስወግድ ቅጠል፣ የጻድቃን መጠለያ ዕፅ የሚል ትርጕም አለው፡፡ ገድለ ተክለ ሃይማኖትም ‹‹ተክለ ሃይማኖት ማለት የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስ ተክል ማለት ነው›› ሲል የጻድቁን ስም ይተረጕመዋል፡፡

ጻድቁ አባታችን ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደ ገበሬ ታጥቀው፣ ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና በመኖራቸው፤ እርሳቸው በአሚነ ሥላሴ ጸንተው ሌሎችንም እንዲጸኑና እንዲያምኑ በማድረጋቸው፤ እንደዚሁም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ በመስበክ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሰባኬ ወንጌል በመኾናቸው ‹‹ተክለ ሃይማኖት›› ተብለው ይጠራሉ፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት በእግዚአብሔር ድንቅ ጥበብ፣ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ብሥራት፤ በኢትዮጵያ ምድር በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ልዩ ስሙ ኢቲሳ በሚባል ቦታ ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀረያ መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፲፪፻፲፪ ዓ.ም ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስተኛው ቀን እሑድ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ፤ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፤ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤ አንዱ አብ ቅዱስ ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው›› በማለት ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስም ‹‹ፍሥሐ ጽዮን›› የሚል ሲኾን ‹‹ተክለ ሃይማኖት›› ደግሞ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ያወጣላቸው ስም ነው፡፡ በተወለዱ በ፲፭ ዓመታቸው ዲቊናን፤ በ፳፪ ዓመታቸው ደግሞ ቅስናን ከግብፃዊው ጳጳስ ከአባ ጌርሎስ (ቄርሎስ) ተቀብለዋል፡፡

አንድ ቀን ወደ ጫካ ለአደን በሔዱበት ዕለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱ ክርስቶስ ተገልጦላቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱን ካሰደረባቸው፤ እንደዚሁም ‹ሐዲስ ሐዋርያ› ብሎ ወንጌል ወዳልተዳረሰበት ቦታ እንደሚልካቸው ከነገራቸው፤ ቅዱስ ሚካኤልም ከአውሬ አዳኝነት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስ እንደ ተመረጡና አጋንንትን የማውጣት፣ ተአምራትን የማድረግ ሥልጣን እንደ ተሰጣቸው፤ ስማቸውም ‹ተክለ ሃይማኖት› እንደሚባልና ትርጓሜውም ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት እንደ ኾነ ካስረዳቸው በኋላ ወደ ቤታቸው ተመልሰው ያላቸውን ንብረት ኹሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥተው ‹‹አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደ ተከፈተ ተውኩልህ›› በማለት ቤታቸውን ትተው ወንጌልን ለማስተማር ፈጥነው ወጡ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረው በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ ብዙ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም አንጸዋል፡፡ ‹ሐዲስ ሐዋርያ› የተባሉትም በዚህ ተልእኳቸው ሲኾን፣ ትርጕሙም ሐዲስ ኪዳንን ወይም ሕገ ወንጌልን እየተዘዋወረ የሚያስተምር ሰባኬ ወንጌል፤ በክርስቶስ ስም ድንቅ ድንቅ ተአምራትን የሚደርግ የክርስቶስ ተከታይ (ሐዋርያ) ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደገበሬ ታጥቀው ይህንን ዓለም ንቀው በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና ከመኖራቸው በተጨማሪ እንደቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፣ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሚታወሱባቸው በዓላት መካከልም ታኅሣሥ ፳፬ ቀን የሚከብረው በዓለ ልደታቸው አንደኛው ነው፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር ዜና ልደታቸውን ሲናገር ‹‹ብፁዕ ወቅዱስ ሐዲስ ሐዋርያ›› በማለት በክብር ጠርቷቸዋል፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፡፡ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል፡፡ ማንም ከእነዚህ ከተናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋው አይጠፋበትም፤›› /ማቴ.፲፥፵-፵፪/ በማለት የተናገረውን መለኮታዊ ቃል ኪዳን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መሠረት አድርጋ መጋቢት ፳፬ ቀን ፅንሰታቸውን፤ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ልደታቸውን፤ ጥር ፳፬ ቀን ስባረ ዐፅማቸውን፤ ግንቦት ፲፪ ቀን ፍልሰተ ዐፅማቸውን፣ ነሐሴ ፳፬ ቀን ደግሞ ዕለተ ዕረፍታቸውን በመንፈሳዊ ሥርዓት በደስታ ታከብራለች፡፡

የአቡነ ተክለ ሃይማኖትና የኹሉም ጻድቃን ጸሎትና በረከት ረድኤትና ምልጃ በመላው ሕዝበ ክርስቲያን ላይ ለዘለዓለሙ ጸንቶ ይኑር፡፡

ቅድስት አርሴማ ድንግል ማን ናት?
" ታኅሣሥ 6 "
<<< እንኩዋን "ለድንግልና ሰማዕት ቅድስት አርሴማ" : "አባ አብርሃም" እና "ቅዱስ ስምዖን ጫማ ሰፊው" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ >>>
+*" ቅድስት አርሴማ ድንግል "*+
=>እናታችን ቅድስት አርሴማን በምን እንመስላታለን? እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው:: መድኃኒታችን ክርስቶስ በወንጌል እንዳለው "በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትምና" (ማቴ. 5:11) የሰማዕቷ ሕይወት በፊታችን እንደ ብርሃን ተገልጦ ይታያል::
*ቅድስት አርሴማ እንደ ልጅ ወላጆቿን በመታዘዝ ደስ ያሰኘች ቡርክት ናት::
*ቅድስት አርሴማ ይሕ ቀረሽ የማይሏት ውብ ናት::
*ቅድስት አርሴማ ድንግል ናት::
*ቅድስት አርሴማ ባሕታዊት ጻድቅ ናት::
*ቅድስት አርሴማ ኃያል ሰማዕት ናት::
¤ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:
+አበው በትውፊት እንደ ነገሩን ከሆነ ቅዱሱ ጐርጐርዮስ የታላቁዋ ሰማዕት ቅድስት አርሴማ ትልቅ ወንድም ነው:: በዜና ሰማዕታት ተጽፎ እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሦስት ኃላፊነቶች ነበሩበት:-
1.ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት
2.ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ ማጥናት
3.የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት::
+ቅዱሱ 3ቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ መሆን ቻለ:: ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት:: መከራው ገፍቶ እስከ መጣበት ጊዜ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ሆነው ይጸልዩ: ይጾሙ: ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር::
+ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስ ጻድቃን የምንላቸው:: በሁዋላ ግን ማሕደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ በመልኩዋ ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ድንግሏን አርሴማን ጨምሮ ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ ተሰደደ::
+በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና በጸሎት ለጥቂት ጊዜ ቆዩ:: ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው:: የሚላስ የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለ መኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ወደ ከተማ ለመውጣት ተገደደ::
+በዚያም በድርጣድስ ቤተ መንግስት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ:: በሚያገኛት ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር:: መከራው ግን አለቀቃቸውም:: ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው::
+ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ ባለመቻሉ "ካላገባሁሽ" አላት:: ድንግሊቱ ግን "እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ: አይሆንም" አለችው:: ሊያስፈራራት ሞከረ:: ዐይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው::
+አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው:: እጅግ ስላፈረ አስገረፋት: አሰቃያት: ዐይኗንም አወጣ:: በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት::
+ከነገር ሁሉ በሁዋላ ድርጣድስና ባለሟሎቹ ለአደን በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት (እሪያነት) ቀየራቸው::
+የንጉሡ እንስሳ (አውሬ) መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን ፈጠረ:: የንጉሡ እህት ስታለቅስ በራዕይ "ለእመ ኢያዕረግምዎ ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን-ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት አትድኑም" አላቸው:: ወዲያውም ቆፍረው አወጡት::
+ቅዱሱ እንደ ወጣ ዕረፍትን አልፈለገም:: ለ15 ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው::
ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሒዶ ፈወሳቸው::
+የሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ አጽም በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ከሌሎች ሰማዕታት አጽም ጋር ኢትዮዽያ እንደ መጣ አባቶቻችን በትውፊት ነግረውናል:: ለዚህም ይመስላል ቡርክቷ እናታችን ከሌሎች ሃገራት ለይታ ለኢትዮዽያውያን ልዩ ፍቅር ያላት:: በዋናው ገዳሟ (ወሎ /ኩላማሶ/ : ስባ : ውስጥ የሚገኝ ነው) ጨምሮ ስሟ በተራበት ሁሉ ኃይልን ታደርጋለችና::
+ነገር ግን ወንድሞቼና እሕቶቼ በቅድስቷ እናታችን ስም የሚነግዱ ሥጋውያን ሰዎች በዝተዋልና እንጠንቀቅ:: የሰማዕቷ ክብር ብዙ ነውና በሕልም ላይ ብቻ አንታመን:: አባ እንጦንስ እንዳሉት "በሕልሙ የሚታመን ሰው ከንቱ ነውና::" (መዝ. 75:5)
+በዚህ ዕለት ከሰማዕቷ ጋር የመንፈስ እናቷን ቅድስት አጋታን ልናስባት ይገባናል:: ይህች እናት እመ-ምኔት ስትሆን ቅድስት አርሴማን ታስተምራት: ታጸናት: ከጐኗም ትቆምላት ነበር:: ረሃቧን: ጥሟን: ስደቷን: መከራዋንም ሁሉ አብራት ተሳትፋለች:: በፍጻሜውም አብራት ተሰይፋለች::
+ይህች ዕለት ለቅድስት አርሴማና ለተከታዮቿ ሰማዕታት የፍሰትና የቅዳሴ ቤት መታሰቢያ ናት:

ለብቻችን አንችለውም ዘፍ 29፤8


ቃለ መጠይቅ (በሊቁ እንደስራቸው አግማሴ እስር ጉዳይ ከአባ ሙሉ ሽታነህ ጋር )
የኢያሪኮ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አመሰራረት ከደብሩ አስተዳዳሪ ጋር 
Support : Creating Website | በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ | Atons Media Tube
Copyright © 2013. ATRONS MEDIA INTERNET TV - All Rights Reserved
Template Created by Creating Website Published by በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ
Proudly powered by Blogger