በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ጉባኤ ኤፌሶን
ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን ያከበሩትን: እርሱም ያከበራቸውን ሰዎች 'ቅዱሳን' ትላለች:: ራሱ ባለቤቱ "ኩኑ ቅዱሳነ እስመ ቅዱስ አነ-እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ" ብሏልና:: (ዼጥ. 1:15) እነዚህንም ቅዱሳን 'መላእክት: አበወ ብሊት: ነቢያት: ሐዋርያት: ሰማዕታት: ጻድቃን: ሊቃውንት: ደናግል: መነኮሳት: ባሕታውያን' ወዘተ. ብለን: ክፍለ ዘመን ሰጥተን በአበው ሥርዓት እናስባለን::
ከእነዚህ ቅዱሳን መካከልም አንዱንና ትልቁን ቦታ ቅዱሳን ሊቃውንት ይወስዳሉ:: 'ሊቅ' ማለት 'ምሑር: የተማረ: ያመሰጠረ: ያራቀቀ: የተፈላሰፈ: በእውቀቱ የበለጠ: የበላይ: መሪ: ሹም: ዳኛ' . . . ወዘተ ተብሎ ሊተረጐም ይችላል::
ወንጌል ላይም ጌታችን መድኃኔ ዓለም ኒቆዲሞስን "አንተ ሊቆሙ ለእሥራኤል-አንተ የእሥራኤል መምሕር (አለቃ) ነህ" ብሎታል:: (ዮሐ. 3:10) ስለዚህም 'ሊቃውንት' ማለት በእውቀት ከሁሉ በላይ የሆኑ እንደ ማለት ነው::
ዘመነ ሊቃውንት ተብሎ የሚታወቀው ከ3ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ እስከ 6ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ ያለው ሲሆን በዚህ ዘመን እንደ እንቁ ያበሩ: ብርሃንነታቸው በሰው ፊት የበራ ብዙ አበው ተነስተዋል:: ቅዱሳን ሊቃውንት ከሌሎች ምሑራን ቢያንስ በእነዚህ ነገሮች ይለያሉ:-
1.እንደ ማንኛውም ሰው ከተማሩ በኋላ እውቀቱ ይባረክላቸው ዘንድ ጠዋት ማታ በጾምና በጸሎት ይጋደላሉ::
2.አብዛኞቹ ቅዱሳን ሊቃውንት ገዳማዊ ሕይወትን ጠንቅቀው ያውቃሉ::
3.ምሥጢር ቢሰወርባቸው ሱባኤ ይገባሉ እንጂ በደማዊ ጭንቅላት አይፈላሰፉም::
4.ፍጹም መናንያን በመሆናቸው ሃብተ መንፈስ ቅዱስ እንጂ የሚቀይሩት ልብስ እንኳ የላቸውም::
5.እያንዳንዷን የመጽሐፍ ቃል ከማስተማራቸው በፊት በተግባር ይኖሯታል::
6.እረኞች ናቸውና ዘወትር ለመንጋው ይራራሉ::
7.ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ ግፍን ተቀብለዋል::
8.በኃይለ አጋንንት የመጡ መናፍቃንን ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ለብሰው: መጻሕፍትን አልበው: ጥቅስ ጠቅሰው መክተዋል::
9.ምግብናቸውንም ፈጽመው ዛሬ በገነት ሐሴትን ያደርጋሉ::
ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የምትቀበላቸው የቅዱሳን ጉባኤያት 3 ብቻ ናቸው::
1ኛ.በ325 (318) ዓ/ም በኒቅያ 318ቱ ሊቃውንት ያደረጉትን
2ኛ.በ381 (373) ዓ/ም በቁስጥንጥንያ 150ው ሊቃውንት ያደረጉትን: እንዲሁም
3ኛ.በ431 (424) ዓ/ም በዚህች ቀን 200ው ሊቃውንት ያደረጓቸውን ጉባኤያት ትቀበላለች::
ይሕስ እንደ ምን ነውቢሉ:-
በወቅቱ ስመ ክፉ መናፍቅ ንስጥሮስ ተነስቶ የእስያ አብያተ ክርስቲያናትን አወካቸው:: ትምሕርቱ ክርስቶስን 2 አካል: ባሕርይ ነው (ሎቱ ስብሐት!) የሚል ነበር:: በእውነት እንየው ከተባለ ግን ጠቡና ጥላቻው ከድንግል ማርያም ጋር ነበር:: ምክንያቱም ጌታችንን ወደ 2 የከፈለው እመቤታችንን የአምላክ እናት አይደለሽም ለማለት ነው:: (ላቲ ስብሐት)
ነገሩን ቅዱስ ቄርሎስ በሰማ ጊዜ ወዳለበት ሒዶ ቢመክረውም ንስጥሮስ ሊሰማ አልፈለገም:: በዚህ ምክንያት በትንሹ ቴዎዶስዮስ (የቁስጥንጥንያ ንጉሥ) ትዕዛዝ በኤፌሶን ታላቅ ጉባኤ እንዲሰበሰብ ሆነ::
ይህ ጉባዔ በቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻው የተቀደሰ ጉባዔ ነው:: በ431 ዓ/ም በኤፌሶን ከተማ የመናፍቃኑን ጥርቅም ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና 200 ቅዱሳን ሊቃውንት ተገኙ::
የሚገባው ጸሎትና ሱባዔ ከተፈጸመ በኋላ ጉባዔው ተጀመረ:: አፈ ጉባዔው ሊቀ ማሕበር ማር(ቅዱስ) ቄርሎስ ነበርና በጉባዔ ፊት ንስጥሮስን ተከራክሮ ረታው:: ምላሽም አሳጣው:: ከቅዱሳት መጻሕፍት ክርስቶስ አንድ ባሕርይ መሆኑን: ድንግል ማርያምም ወላዲተ አምላክ መሆኗን እየጠቀሰ: በምሳሌም እያሳየ አስረዳ::
የሰይጣን ማደሪያ ንስጥሮስ ግን እንቢ: አላምንም በማለቱ ተወግዞ ተለየ:: ቅዱሳን ሊቃውንቱም በቅዱስ ቄርሎስ አርቃቂነት 12 አንቀጾችን አዘጋጅተው ወደ ዓለም ሁሉ ላኩ:: እሊህ አንቀጾች ዛሬም በሊቃውንቱ እጅ አሉ:: ይነበባሉ: ይተረጎማሉ::
ከእነዚህም አንዱ ድንግል ማርያም "ታኦዶኮስ (የእግዚአብሔር እናቱ) ናት" የሚል ነው:: እመቤታችንን የአምላክ እናት: ዘላለማዊት ድንግል: ፍጽምት: ንጽሕትና አማላጅ ብሎ ማመን ለሰማያዊ ርስት የሚያበቃ በጐ ሃይማኖት ነውና::
ጉባዔው ከተጠናቀቀ በኋላ ቅዱስ ቄርሎስ ንስጥሮስን ጠርቶ "በድንግል ማርያም እመን:: እርሷ ከልጇ ታስታርቅሃለች" ቢለው በድጋሚ "እንቢ" አለው:: ያን ጊዜ ሊቁ "ለአምላክ እናት ያልታዘዘ ምላስህ ላንተም አይታዘዝህ" ብሎ ረገመው:: ወዲያው ምላሱ ተጐልጉሎ ወጥቶ ደረቱ ላይ ወደቀ::
እንደ ውሻ እየተዝረከረከ ሂዶ ከወዳጆቹ ጋር ቁሞ ሳለ መሬት ተከፍታ ውጣዋለች::
አምላከ ሊቃውንት ዛሬም ያሉንን አባቶች ይጠብቅልን: ያንቃልን:: ከቅዱሳን ሊቃውንት በረከትም አይለየን:: የእመ ብርሃን ፍቅሯንም ያሳድርብን::
Post Top Ad
Wednesday, September 21, 2022
እንኳን ለቅዱሳን አባቶቻችን ሊቃውንት ዓመታዊ የጉባኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
Post Bottom Ad
Author Details
Templatesyard is a blogger resources site is a provider of high quality blogger template with premium looking layout and robust design. The main mission of templatesyard is to provide the best quality blogger templates which are professionally designed and perfectlly seo optimized to deliver best result for your blog.
No comments:
Post a Comment