ስንክሳር_ዘወርኅ_ኅዳር 2 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, November 16, 2022

ስንክሳር_ዘወርኅ_ኅዳር 2

 ኅዳር 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.አባ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት ሣልስ
2.አባ ሱንቱዩ ሊቀ ዻዻሳት
3.ቅድስት ሴቴንዋ ነቢይት
4.ቅድስት አንስጣስያ
ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
5.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ
7.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያ





አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ሁለት በዚህች ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ_አባት_ጴጥሮስ_ሣልሳዊ አረፈ፣ ስልሳ ሦስተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ_ሱንትዩ አረፈ።

ኅዳር ሁለት በዚህች ቀን ከአባ ጢሞቴዎስ በኋላ የተሾመ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ጴጥሮስ ሣልሳዊ አረፈ።
እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃያ ሰባተኛ ነው ይህንንም ቅዱስ እግዚአብሔር ለሊቀ ጵጵስና ሹመት መርጦ በሐዋርያ ማርቆስ ወንበር ላይ ከአስቀመጠው በኋላ የቍስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አካክዮስ እንዲህ የሚል መልእክትን ጻፈለት እንደ ቅዱሳን ቄርሎስና ዲዮስቆሮስ ሃይማኖት ልዩ ሦስት በሆነ በአንድ አምላክ እናምናለን እናሳምናለን።
ዳግመኛም በዚች መልእክት ውስጥ እንዲህ ብሎ ገለጠ የተዋሕዶ ጥቅም እንዳይሻር ከተዋሕዶ በኋላ የአካላዊ ቃልን መለኮቱን ከትስብእቱ ሊለዩት አይገባም።
ይህ አባ ጴጥሮስም እንደ ተቀበላት ገልጦ ስለ ቀናች ሃይማኖት ከራሱም ያለውን ጨምሮ ለመልእክቱ መልስ ጽፎ ከሦስት ምሁራን ኤጲስቆጶሳት ጋር ላካት። አባ አካክዮስም ተቀበላቸው በቅዳሴና በቊርባንም አንድ ሆኑ ያቺንም መልእክት በቃሉ በሚያምኑ ሕዝብ ፊት አነበባት።
ከዚህም በኋላ ሌላ መልእክትን ጻፈ በውስጧም ከቅዱሳት መጻሕፍት ብዙ ቃላትን ተርጒሞ ወደ አባ ጴጥሮስ ላካት። ይህም አባ ጴጥሮስ ኤጲስቆጶሳቱን ሰብስቦ ያቺን መልእክት በፊታቸው አነበባት እነርሱም እጅግ ደስ አላቸው ከቃሏና ከትርጓሜዋም የተነሣ አደነቁ በቀናች ሃይማኖትም ከእርሳቸው ጋር አንድነት ያላቸው መሆኑን ተማመኑ።
ይህንን አባት አባ ጴጥሮስንም ከሀድያን ከሆኑ አይሁድ ከአረማውያንም ከመንበረ ሹመቱ እስኪያሳድዱት ድረስ ስለቀናች ሃይማኖት ብዙ መከራ ደረሰበት።
ከጥቂት ወራትም በኋላ ወደ ሹመቱ ወንበር ተመለሰ መንጋውንም በቀናች ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ አዘውትሮ ያስተምራቸው ነበር ከእነርሱም ርቆ በስደት በነበረበት ጊዜ ከመናፍቃን እንዲጠበቁና በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ መልእክቶችን ጽፎ ይልክ ነበር በሹመቱ ወንበርም ዐሥር ዓመት ኑሮ በሰላም አረፈ።

በዚህችም ቀን ዳግመኛ ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ስልሳ ሦስተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሱንትዩ አረፈ።
ይህም አባት መንጋዎቹን እያስተማረ በሹመቱ ወንበር ዐሥራ አምስት ዓመት ኑሮ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages