ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 17 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 17

 #ቅዱስ_መክሲሞስ እና #ቅዱስ_ዱማቴዎ

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥር ዐሥራ ሰባት በዚህች ዕለት ለለውንድዮስ ለሮም ንጉስ ልጆቹ የሆኑ የከበሩና የተመሰገኑ መክሲሞስና ዱማቴዎስ መታሰቢያቸው ሆነ። ይህም ንጉስ ሃይማኖቱ የቀና እግዚአብሔርንም የሚፈራ በእውነትም የቀና ፍርድን የሚፈርድ ነበር ስለዚህም እሊህን ሁለት ቅዱሳን እግዚአብሔር ሰጠው እነርሱም ከታናሽነታቸው ጀምሮ በንጽህና እንደ እግዚአብሔር መላእክት ሆኑ።


ትሕትናን ፈሪሀ እግዚአብሔርን በማስተማር አሳደጋቸው የሚጾሙና የሚፀልዩ በቀንና በሌሊትም የብሉይና የሐዲስ መጻህፍቶችን የሚያነቡ ሆኑ። ከዚህም በኋላ ይህን ዓለም ይተውት ዘንድ የመላእከትንም ልብስ ይለብሱ ዘንድ እርሷም የከበረች የምንኩስና ልብስ ናት ከዚያም ሐሳብ መጣባቸው ሃይማኖታቸው የቀና ሦስት መቶ አስራ ስምንት አባቶች ወደ ተሰበሰቡባት ወደ ኒቅያ ሂደው ይፀልዩ ዘንድ እንዲአስናብታቸው ለአባታቸው ምክንያት አቀረቡ።
ይህንንም ከርሳቸው በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ አለው ከብዙ አገልጋዮችና ከብዙ ሰራዊት ጋር አሰናበታቸው ከኒቅያ አገርም በደረሱ ጊዜ ከከበረ ቦታ በረከትን ተቀበሉ ሰራዊቱንም ወደ ንጉስ አባታቸው ጌታችን ንጉሥ ሆይ እኛ ከዚህ ጥቂት ቀን መቆየት እንሻለን ከሚል ጽሑፍ ጋር ጽፈው ላኩ።
ከዚህም በኃላ ለአንድ ፃድቅ መነኮስ ሐሳባቸውን ገለጡ እንዲህም አሉት ከአንተ ዘንድ የምንኩስናን ልብስ እንድንለብስ እንሻለን እርሱም እኔ ከንጉስ አባታችሁ የተነሳ እፈራለሁ ነገር ግን ወደ ሶሪያ ሂዱ ስሙ አጋብዮስ የሚባል ከዚያ ሀይማኖቱ የቀና ካህን ደግ መነኮስ አለ አላቸው። ይህንንም ሲላቸው ምክሩን ተቀብለው ወደ ሶሪያ ተጉዘው ወደ ቅዱስ አባ አጋብዮስ ደርሰው ኀሳባቸውን ገለጡለት እርሱም ተቀብሎ የምንኩስና ልብስን አለበሳቸው እስከሚአርፍበትም ቀን ከእርሱ ዘንድ ኖሩ።
ከዕረፍቱም አስቀድሞ ያየውን ራእይ ነገራቸው ታላቁ አባ መቃርስ ወደርሱ እንደመጣና ልጆችህ መክሲሞስና ዱማቴዎስ ለኔ ልጆቼ ይሆኑኝ ዘንድ ወደ እኔ ወደ አስቄጥስ ገዳም እንዲመጡ ከመሞቴ በፊት እዘዛቸው አለው።
ዳግመኛም እንዲህ አላቸው ልጆቹ እኔ ይህን ሰው አባ መቃርስን በስጋው አየው ዘንድ እመኝ ነበር እነሆ በመንፈስ አየሁት እናንተም ከሞትኩ በኃላ ወደርሱ ሒዱ።
ከአረፈም በኃላ አልሄዱም በዚያ በሶሪያ አገር ኖሩ እንጂ እግዚአብሔርም ሀብተ ፈውስ ሰጥቷቸው በሽተኞችን የሚፈውሱ ሆኑ ወሬያቸውም በሀገሮች ሁሉ ተሰማ በባህርና በየብስ ከሚነግዱ ነጋዴያንም የመርከብ መዛነቢያቸውን መስራት ተምረው ከድካም ዋጋቸው በየጥቂቱ የሚመገቡና የተረፈውን ለድሆችና ለችግረኞች የሚሰጡ ሆኑ።
እግዚአብሔርም በእጆቻቸው ከሚሰራቸው ድንቆች ተአምራቶች የተነሳ የቅዱሳን መክሲሞስንና ዱማቴዎስን ስም መናፍስት ርኩሳን በሚሰሙ ጌዜ ከሰዎች ወጥተው ይሻሻሉ ሰዎቹም ያን ጊዜ በጌታ ኃይል ይድናሉ ጤነኞችም ይሆናሉ።
እጅግ ታላቅ የሆነ በጎዳና አጠገብ የሚኖር ከይሲ ነበር ብዙዎች ሰዎች ሰዎችንም አጥፍቷል የአገር ሰዎችም ወደ ከበሩ መክሶሞስና ዱማቴዎስ መጥተው ከዚያ ከይሲ ያድኗቸው ዘንድ ለመኗቸው አባ መክሲሞስም ክርታስ አንስቶ እንዲህ ብሎ ፃፈ የብፁእ መቃርዮስ አምላክ በሆነ መንፈስ ቅዱስንም በለበሰ በአባታችን በአጋብዮስ አምላክ በህያው እግዚአብሔር አካላዊ ቃል በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ደብዳቤ ከዋሻህ ደጅ ቢደርስ አንተ ወጥተህ ሙት የሰማይ ወፎችም ይብሉህ።
አንድ ሰውም ያቺን ደብደቤ ተቀበሎ ሄደ በዚያም የዘንዶ ዋሻ ደጃፍ አኖራት በዚያንም ጊዜ ዘንዶዉ ወጥቶ ሞተ የሰማይ ወፎችም በሉት ህዝቦችም ሁሉ እጅግ አደነቁ እግዚአብሄርንም አመሰገኑት የክብር ባለቤት ጌታችንም በእሊህ ቅዱሳን በመክሲሞስና በዱማቴዎስ እጆች ብዙ ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ።
በአንዲትም ዕለት ከአባታቸው መኳንንቶች አንዱ ወደ ባህር ዳርቻ ደረሰ ከመርከቦችም በአንዱ መርከብ መዛገቢያ ላይ መክሲሞስና ዱማቴዎስ የሚል ፅሁፍ በአየ ጊዜ የመርከቡን ሹም ጠየቀው እርሱም እንዲህ አለው በፀሎታቸው ከስጥመት እግዚአብሔር ያድነኝ ዘንድ የእሊህን ሁለት ወንድማማቾች የከበሩ መነኮሳት ስማቸውን በመርከቤ ላይ ፃፍኩ መኮንኑም መልካቸው ምን ይመስላል አለው እርሱም የመልካቸውን ምልክት ነገረው የንጉሱ ልጆች እንደሆኑ አውቆ ያን ነጋዴ ወደ ንጉስ አባታቸው አደረሰው።
ንጉሡም ጠየቀው ነጋዴውም የመልካቸውን አምሳል አስረዳው ንጉሡም ልጆቹ እንደሆኑ በተረዳ ጊዜ እናታቸውንና እኅታቸውን ከብዙ ሠራዊት ጋር ወደነርሱ ላከ ደርሰውም በአዩአቸው ጊዜ ጩኸው አለቀሱ እናታቸውም ወደ ንጉስ አባታቸው ከእርሷ ጋር ይመጡ ዘንድ ለመነቻቸው።
እነርሱም ራሳችንን ስእለት አድርገን ለእግዚአብሔር ሰጥተናልና ቃል ኪዳናችንን ማፍረስ አይቻለንም ነገር ግን ሄጄ ለአንቺም ለአባታችንም ከመከራ ሁሉ እግዚአብሔር ያድናችሁ ዘንድ እንፀልይላችኋለን በዚህም አነጋገር አረጋጓት በመለየቷም ፈፅማ እያዘነች ተመለሰች።
ወደ ንጉሱም በደረሰች ጊዜ ከእነርሱ የሆነውን ነገረችው ንጉሱም ለሚስቱና ለባለሟሉቹ እንዲህ አለ በእግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የሕይወት ድልብ ይሆኑን ዘንድ እንተዋቸው ፀሎታቸውም ይጠቅመናል በዓለም ውስጥ ያለ ክብር ሁሉ እንደ ሕልም ኃላፊ ጠፊ ነውና እነርሱ ግን የማያልፍ መንግስትን አተረፉ።
በዚያም ወራት የሮሜ ሀገር ሊቀ ጳጳሳት አረፈ ስለሚሾሙትም ሊቀ ጳጳሳት ይማከሩ ዘንድ ኤጲስቆጶሳት ጳጳሳትም ተሰበሰቡ የከበረ መክሲሞስንም አሰቡትና ሁሉም ለዚች ሹመት እርሱ በእውነት ይገባል ተባባሉ።በሽተኞችን ይፈውስ ዘንድ ብዙዎች የሆኑ ድንቆች ተአምራቶችንም ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር ታላቅ ፀጋ ሰጥቶታልና በእድሜውም ወጣት ቢሆን ክርስቶስ በውስጡ ወጣት ቢሆን ክርስቶስ በውስጡ ስለአደረ በዕውቀትና በበጎ ስራ በቤተ ክርስቲያንም ህግና ስርአት ሁሉ ፍፁም ነው።
ይህንንም በሰሙ ጊዜ አባቱና እናቱ ደስ አላቸው መኳንንቶችንም ላኩ የከበሩ መክሲሞስንና ዱማቴዎስን ወደ ሮሜ ይሰዳቸው ዘንድ ወደ ሶሪያ አገረ ገዢ ደብዳቤ አብረው ላኩ። እሊህም ቅዱሳን ሰምተው እጅግ አዘኑ አባታቸው አባ አጋብዮስም ያዘዛቸውን አሰቡ በዚያንም ጊዜ ተነሱ ልብሳቸውንም ለውጠው ወደ ኤርትራ ባህር ዳርቻ ተጓዙ ወደየትም እንደሚጓዙ አያውቁም ውኃን በሚጠሙ ጊዜም እግዚአብሔር መራራውን ውኃ ለውጦ ጣፋጭ አድርጎላቸው ይጠጣሉ ከዚህም በኃላ ከእርሱ ዘንድ ረድኤትን ኃይልን ላከላቸውና ከሶሪያ አገርም ተሸክማ ወደ አስቄጥስ ገዳም አደረሰቻቸው ወደ አባ መቃርስም ገብተው በእርሱ ዘንድ መኖርን እንደሚሹ ነረጉት።
እነርሱም በፀጋ የለመለሙ እንደሆኑ በአየ ጊዜ በገዳም መኖርን የማይችሉ መስለው በገዳም ያለውን ችግር ነገራቸውና በዚህ መኖር አትችሉም አላቸው እነርሱም አባታችን ሆይ ተወን ከዚህ መኖር ካልተቻለን እንሄዳለን ብለው መለሱለት።
ከዚህም በኃላ ሰሌን መስራትን አስተማራቸው ሰሌንም የሚቆርጡበትን ወንዝ አሳያቸው ማደሪያቸውንም እስከሚሰሩ ድረስ ረዳቸው የእጅ ስረቸውንም የሚሸጥና ምግባቸውን የሚያመጣላቸውን አንድ ህዝባዊ ሰው አምጥቶ አገናኛቸው። እንዲህም ሆነው ከቶ ከሰው ሳይገናኙ ሶስት አመት ኖሩ ነገር ግን በጭልታና በዝምታ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚገቡና ሥጋውንና ደሙን ተቀብለው ወደ ማደሪያቸው የሚመለሱ ሆኑ።
ሦስት አመት ያህል ወደርሱ ስለአልመጡና ስለአልጎበኙት አባታቸው አባ መቃርስ ከስራቸው የተነሳ አደነቀ ስራቸውንም ይገልጥለት ዘንድ ወደ ጌታችን ለመነና ተነስቶ ወደ ርሳቸው ሄደ እነርሱም በመምጣቱ ደስ ተሰኙበት በዚያች ሌሊትም ከርሳቸው ጋር አደረ። ለፀሎትም በተነሱ ጊዜ የእሳት ሐብል ከአፋቸው ሲወጣና ወደ ሰማይ ሲደርስ ሰይጣናትም እንደ ዝንቦች ሲከቡት የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ሰይፍ ዝንቦቹን ሲያበርራቸው የከበሩ መክሲሞስንና ዱማቴዎስን አያቸው በነጋም ጊዜ አስኬማን አለብሳቸው ፀልዩልኝ ብሏቸውም ሊሄድ ተነሳ። እንርሱም ሰገዱለትና አባታችን ሆይ አንተ በእኛ ላይ ትፀልይ ዘንድ ትባርከንም ዘንድ የሚገባ ነው አሉት።
ተጋድሎአቸውንም በፈፀሙ ጊዜ እግዚአብሔር ከዚህ አለም ድካም ሊአሳርፋቸው ወደደ መክሲሞስም በፅኑ ህመም ታመመ ስጋውም እንደ እሳት ጋለ ወደርሱም ይመጣ ዘንድ ወደ አባ መቃርስ ላከ። አባ መቃርስም በመጣ ጊዜ በደዌ ሲሰቃይ አገኘው መክሲሞስም ፀልይልኝ ባርከኝም አለው። እርሱም በላዩ አማትቦ ይህ ደዌ ከአንተ ይርቃልና አይዞህ አለው መክሲሞስም አባቴ ሆይ በዚች ደዌ ከዚህ አለም እንደምወጣ እኔ አውቃለሁ ረድኤት አገኝ ዘንድ አንተ ፀልይልኝ አለው።
ይህንንም በተናገረ ጊዜ መሪር ልቅሶን አለቀሰ በዚያችም ጊዜ አባ መቃርስ የቅዱሳንን አንድነት ነቢያትን ሀዋርያትን መጥምቁ ዮሀንስን ንጉስ ቆስጠንጢኖስንም አያቸው። እነርሱም ነፍሱ በክብር እስከወጣች ድረስ በአባ መክሲሞስ ዙሪያ ነበሩ።
አባ መቃርስም አልቅሶ መክሲሞስ ሆይ የተመሰገንክ የከበርክ ነህ አለ። ዱማቴዎስም በውንዱሙ ላይ መራራ ልቅሶ በማልቀስ አባ መቃርስን የሚለምነው ሆነ ነፍሴን ይወስዳትና ወደ ወንድሜም ያደርሳት ዘንድ ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር ፀልይ አለው።
አባ መክሲሞስም ከተቀበረ በኃላ በሶስተኛው ቀን አባ ዱማቴዎስ ታመመ ስለርሱም ለአባ መቃርስ ነገሩት አባ መቃርስም ወደርሱ ሊሄድ ተነሳ በጉዞ ላይም ሳለ አስቀድሞ ወደ አባ መክሲሞስ የመጡትን የቅዱሳን አንድነት አየ የአባ ዱማቴዎስንም ነፍስ ተቀበለው በክብር ወደ ሰማይ አሳረጓት።
አባ መቃርስም ወደ በኣታቸው ሲደርስ ዱማቴዎስን አርፎ አገኘው ወስዶም ከወንድሙ ከመክሲሞስ ጋር በአንድ መቃብር በክብር ቀበረው። የመክሲሞስም እረፍት በዚህ ወር በአስራ አራት ነው ዳግመኛ የዱማቴዎስ እረፍት ጥር አስራ ሰባት በዚች ቀን ነው።
የከበረ አባ መቃርስም ያ ቦታ በስማቸው እንዲጣራ አዘዘ እንዲሁም ደብረ በርሞስ ተብሎ እስከ ዛሬ የሚጠራ ሆነ ለዘላለሙም መታሰቢያቸው ሆነ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ መክሲሞስና ዱማቴዎስ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages