አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ሃያ ስድስት በዚህች ዕለት ከሮሜ አገር የከበረች ቅድስት አንስጣስያ በሰማዕትነት ዐረፈች፡፡ የዚችም ቅድስት አባቷ ጣዖትን የሚያመልክ ነው እናቷ ግን ክርስቲያን ናት ይቺንም ቅድስት በወለደቻት ጊዜ አባቷ ሳያውቅ የክርስትና ጥምቀትን በሥውር አጠመቀቻት አውቆ ቢሆን ማጥመቅ ባልተቻላትም ነበር። ከዚህም በኋላ በበጎ አስተዳደግ አሳደገቻት በቀናች ሃይማኖት እስከ አጸናቻት ድረስ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተማረቻት ጠባይዋን መለወጥ ለማንም አልተቻለውም።
አድጋም አካለ መጠን በአደረሰችም ጊዜ አባቷ እንደርሱ ላለ ከሀዲ ሰው አጋባት እርሷ ግን እጅግ ጠላችው ልትገናኘውም አልፈለገችም በሴቶች ላይ በሚሆነው ግዳጅና አንዳንድ ጊዜም በደዌ የምታመካኝ ሆነች እንዲጠላትና ከእርሷ እንዲለይ ያደፈና የቆሸሸ የተጐሳቈለ ልብስ ትለብስ ነበር። ባሏም ወደ ሥራው ወጥቶ በተሰማራ ጊዜ እርሷም ስለ ቀናች ሃይማኖት የታሠሩ እስረኞችን ትጐበኝ ዘንድ ትሰማራለች ታገለግላቸውና የሚሹትን ትሰጣቸዋለች። ባሏም ይህን የምትሠራውን በአወቀ ጊዜ ወደ ውጭ እንዳትወጣ በቤት ውስጥ ዘጋባት እርሷም ከእጁ ያወጣት ዘንድ አዘውትራ በመረረ ልቅሶ ወደ እግዚአብሔር የምትለምን ሆነች ጌታችንም ልመናዋን ሰምቶ ያንን ሰው አጠፋው። እርሷም በሞቱ ደስ አላት ከዚህም በኋላ ለድኆችና ለምስኪኖች ስለ ቀናች ሃይማኖትም በመታመን ለታሠሩ እሥረኞች ገንዘቧን ሁሉ ሰጠች።
የሮሜ አገር ገዢም ዜናዋን በሰማ ጊዜ መልእክተኞችን ልኮ ወደርሱ አስመጣት ስለ ሃይማኖቷም ጠየቃት ክርስቲያን እንደሆነች በፊቱ ታመነች ቃል ኪዳን በመግባትም ተናገራት ከበጎ ምክርዋ አውጥቶ ወደ ክህደት ሊያዘነብላት አልቻለም። በዚያንም ጊዜ በብዙ በተለያየ ሥቃይ አሠቃያት።
ከዚህም በኋላ ወደ ባሕር ያሠጥሟት ዘንድ አዘዘ ባሕሩም በሕይወቷ ተፋት ዳግመኛም በአራት ካስማ መካከል አስተኝተው ዘርግተው አሥረው ታላቅና ጽኑዕ የሆነ ግርፋትን ይገርፋዋት ዘንድ አዘዘ መኰንኑም እንዳዘዘ አደረጉባት ግን ምንም ምን ጉዳት አልደረሰባትም። ከዚህም በኋላ ወደ አዘጋጁላት የእሳት ማንደጃ ውስጥ ይጨምርዋት ዘንድ አዘዘ በጨመርዋትም ጊዜ ነፍሷን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠች በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊል ተቀበለች።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት አንስጣስያ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን ።
No comments:
Post a Comment