ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 4 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 4

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር አራት በዚህች ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚወደው የሐዋርያው #ቅዱስ_ዮሐንስ የፍልሰቱ መታሰቢያ ነው፣ #አባ_ናርዶስ_ዘደብረ_ቢዘን እና #የአቡነ_መልከጼዴቅ_ዘዋሸራ የእረፍታቸው መታሰቢያ ነው።


ጥር አራት በዚህች ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚወደው የከበረና የተመሰገነ ወንጌልን የጻፈ የሐዋርያው ዮሐንስ የፍልሰቱ መታሰቢያ ሆነ።
ለዚህም ቅዱስ ወደ እስያ ሀገር ይሔድ ዘንድ ዕጣው በወጣ ጊዜ እጅግ አዝኖ አለቀሰ እነርሱ ክፉዎች ከሀዲዎች ልባቸው የደነደነ መሆናቸውን አውቋልና ግን ከጌታችን ኃይልን መጽናናትን አግኝቶ ከደቀ መዝሙሩ ከአብሮኮሮስ ጋር ወጥቶ ወደ ክፍሉ ሔደ።
ወደ ኤፌሶንም ሊሔድ ወዶ በመርከብ ላይ ተሳፈረ መርከቡም ተሰበረ እየአንዳንዱ በመርከብ ስባሪ ሠሌዳ ላይ ተንጠለጠለ ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስንም የባሕሩ ማዕበል ወደአንዲት ደሴት አደረሰው ቅዱስ ዮሐንስ ግን በባሕሩ ማዕበል መካከል አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ኖረ።
ከዚህም በኃላ ደቀ መዝሙሩ አብሮኮሮስ ወዳለበት ወደ የብስ ባሕሩ ተፋው ስለ መገናኘታቸውም እግዚአብሔርን አመሰገኑት በዚያን ጊዜም ተነሥተው ወደ ኤፌሶን ከተማ ገቡ ግን በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይሰብኩ ዘንድ አልተቻላቸውም እነዚያ ያገር ሰዎች እጅግ የከፉ ናቸውና።
ስለዚህም ምክንያት ፈጥረው ዮሐንስ ሮምና ለምትባል ሴት የውሽባ ቤት እሳትን የሚያነድ ሆነ ረድኡ አብሮኮ ሮስም አጣቢ ሆነ ያቺ ሴትም እጅግ ታሠቃያቸው ነበር መጻተኞችም ስለሆኑ ታጉሳቁላቸዋለች ትደበድባቸዋለች ትረግማቸዋለች ባሮቿም እንደሆኑ ጽፈውላታልና ለእርሷ ባሮች አደረገቻቸው በዚህ በታላቅ ጒስቊልና ውስጥ ኖሩ።
ከዚህም በኃላ በአንዲት ዕለት ይታጠብ ዘንድ የአገረ ገዥው ልጅ ገባ በዚያም የውሽባ ቤት ከተሠራ ጀምሮ የሰይጣን ኃይል አለ የመኰንኑንም ልጅ አንቆ ገደለው በዚያንም ጊዜ የአገር ሰዎች ለዚያ ለሞተው ሊያለቅሱለት ተሰበሰቡ የከበረ ዮሐንስም ከእርሳቸው ጋር መጥቶ እንደ ሰው ሁሉ ሊያይ በዚያ ቆመ።
ሮምናም በአየችው ጊዜ ረገመችው አንተስ በጌታዬ ልጅ ሞት ደስ ብሎህ ልትዝትብኝ መጣህ አለችው ቅዱሱ ግን በቅንነት አይዞሽ አትዘኝ አላት ይህንንም ብሎ ወደ ሞተው ቀረብ ብሎ በመስቀል ምልክት አማተበበት በፊቱም ላይ እፍ አለበት። በዚያንም ጊዜ ያ ሞተው ድኖ ተነሣ የአገር ሰዎችም ደነገጡ ሮምናም ወዮልኝ እግዚአብሔር የሚሉት አምላክ አንተ ነህን አለች። እርሱም አይደለሁም እኔ አገልጋይ ሐዋርያው ነኝ እንጂ አላት በእነርሱ ላይ የሠራችውን በደል ሁሉ ይቅር ይሏት ዘንድ መሪር ልቅሶ በማልቀስ ሐዋርያትን ለመነቻቸው እነርሱም አረጋጓት አጽናኗትም።
ከሀገሩም ሰዎች ብዙዎቹ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው በፊታቸውም ብዙዎች የሆኑ ድንቆች ተአምራትን አደረገ ይህንንም አይተው የሀገሩ ሰዎች ሁሉም በጌታችን አመኑ። ከጣዖታቱ አገልጋዮች በቀር እነርሱም ሰይጣን በእርሱ ላይ ስለሚያነሣሣቸው ሊገድሉት ይሹ ነበር ነገር ግን ምርጦቹን እግዚአብሔር ጠበቃቸው።
የከበረ ዮሐንስም ሁሉንም እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ እስከመለሳቸው ድረስ ታላቅ ድካምና ጭንቅ የሆነ መከራ ደረሰበት። የከበረ ሐዋርያ ጳውሎስም ስለ ልቡናቸው ደንዳናነት ጣዖታትን ስለመውደዳቸውም ስለ እነርሱ መስክሮአል። እርሱም ዮሐንስ በታላቅ ድካም ወደ ቀናች ሃይማኖት መለሳቸው። ከዚህም በኋላ ኤጲስቆጶሳትን ቀሳውስትን ዲያቆናትን ሾመላቸው።
ከዚህም በኃላ ከእስያ በዙርያዋ ወዳሉ አገሮች ሁሉ ወጥቶ አስተማረ እግዙአብሔርንም ወደማወቅ መለሳቸው።ይህም የከበረና የተመሰገነ ዮሐንስ በዚህ ዓለም ዘጠና ዓመት ኖረ እጅግም ሸመገለ ግን እንደ ባልንጀሮቹ ሐዋርያት በመሰየፍ ሞትን አልቀመሰም። ስለ ድንግልናውና ስለ ንጽሕናው ይህ ሆነ ሁሉም በክብር ይስተካከሉ ዘንድ እርሱም ወንጌልን ቀለም ሲስ የሙባለውን ራእይ ሦስት መልእክታትን የጻፈ ነው።ራት ሲበሉ በጌታ ኢየሱስ አጠገብ የተቀመጠውና አቤቱ የሚያሲዝህ ማነው ያለው ይህ እርሱ ነው።
ጌታችንም በተሰቀለ ጊዜ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር በመስቀሉ አጠገብ የቆመ እናቱንም እነሆ ልጅሽ ያላት እርሱን ደቀ መዝሙሩንም እነኋት እናትህ ያለው ነው።
ጴጥሮስም እርሱን ሲከተለው በአየው ጊዜ ስለርሱ ጌታ ኢየሱስን አቤቱ ይህስ እንዴት ነው ብሎ የተናገረ ጌታ ኢየሱስም እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ከወደዱኩ አንተ ምን አለህ አንተ ግን ተከተለኝ ያለለት ይህ ነው ።
የተመሰገነ ዮሐንስም ከዚህ ዓለም የሚወጣበት ሰዓት እንደ ቀረበ በአወቀ ጊዜ ሕዝቡን ጠራቸው ጸሎትንም ጸለየና ኅብስቱን ባርኮ ቆረሰ ይህም የጌታችን ሥጋውንና ደሙን ሰጣቸው በቀናች ሃይማኖትም እንዲጸኑ አዘዛቸው ባረካቸው አጽናናቸውም።
ከዚህም በኃላ ደቀ መዝሙሩ አብሮኮስን ከወንድሞችም ሌሎች ሁለትን መቆፈሪያ ይዘው ይከተሉት ዘንድ አዘዘ።ከኤፌሶንም ከተማ ውጭ ወጣ ጐድጓድ እንዲቆፍሩም አዘዘ ከውስጥዋም ወርዶ ቆመ ልብሱንም አስወገደ ከአንድ የበፍታ ቀሚስ በቀር አላስቀረም። እጆቹንም አንሥቶ ጸለየና ወደ ከተማ ይመለሱ ዘንድ አሰናበታቸው በክርስቶስም ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ ለሕዝቡ ይነግሩአቸው ዘንድ አዘዛቸው በጎ ሥራዎችንም ይሠሩ ዘንድ ጌታችን ለሁሉም እንደ ሥራው ይከፈለው ዘንድ አለውና።
ሁለተኛም እንዲህ አላቸው እኔ ከሁላችሁም ደም ንጹሕ ነኝ ከእግዚአብሔር ትእዛዝና ሕግ ሳልነግራችሁ የተውኩት ምንም ምን የለምና እናንተም ከእንግዲህ ከቶ ፊቴን አታዩኝም።
ይህንንም በተናገረ ጊዜ አለቀሱ እጆቹንና እግሮቹን ስመው በጒድጓዱ ውስጥ ትተውት ወደ መንገድ ተመለሱና የሆነውን ሁሉ ለሰዎች ነገሩዋቸው ሁሉም ደንግጠው መጡ ግን ልብስና ጫማ እንጂ መቃብሩን አላገኙም እጅግም አደነቁ ደቀ መዝሙሩ ዮሐንስን በዚህ በጎ ዕረፍት ያሳረፈው እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚኽች ዕለት ስንክሳሩ ‹‹ተጋዳይ የሆነ በጥላው ብቻ ከይሲን የገደለ የደብረ ቢዘኑ አባ ናርዶስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡ እርሱም እግሮቹ እስኪያብጡ ድረስ ቆሞ በመጸለይ የተጋደለ ነው›› በማለት በአጭሩ የገለጸው ጻድቁ አባ ናርዶስ ዕረፍቱ ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
መርሐቤቴ ያሉት ማለትም በደጃቸው የተቀበረውን ሰው ዐፈር የማስበሉት ጻዲቅ የሚዳው አቡነ መልከጼዴቅና የዋሸራው አቡነ መልከጼዴቅ ሁለቱ የተለያዩ ናቸው፡፡ እኚህኛው የዋሸራው አቡነ መልከጼዴቅ ከአባታቸው ከዘካርያስና ከእናታቸው ስነ ክርስቶስ የተወለዱት አቡነ መልከጼዴቅ ዘዋሸራ ትውልድ ሀገራቸው ጎጃም ዋሸራ ሲሆን በታላቅ ተጋድሎና በሹመት ያገለገሉትም በዚሁ ነው፡፡
ዲቁናንና ቅስናን ከግብፅ ተቀብለው በዋሽራ 30 ዓመት በሹመት አገልግለዋል፡፡ ጻድቁ የሚታወቁበት ትልቁ ተጋድሎአቸው በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ሁልጊዜ ዓርብ ዓርብ ያከፍሉ ነበር፡፡ የመድኃኔዓለምን 13ቱን ሕመማተ መስቀሎች በማሰብ አናታቸውን በድንጋይ እያቆሰሉ ቁስሉ ሲተላ ትሉን ለወፎች ይመግቡ ነበር፡፡ በ40 ቀን ውስጥ አንዷን ቀን ብቻ ነው ውኃ ይጠጡ የነበረው፡፡ ጻድቁን የቅኔ ተማሪዎች በዋሸራ ይዘክሯቸዋል፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages