ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 10 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, June 16, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 10

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሰኔ ዐሥር በዚህች ዕለት ለክርስቲያን ወገኖች በዓለሙ ሁሉ ታላቅ ደስታ ሆነ መላእክትም በሰማያት ደስ ተሰኙባት፣ ቅዱሳት ደናግል ደባሞንና ብስጣሞን እናታቸውም ሶፍያ በሰማዕትነት ሞቱ።


ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን
ሰኔ ዐሥር በዚህች ዕለት ለክርስቲያን ወገኖች በዓለሙ ሁሉ ታላቅ ደስታ ሆነ መላእክትም በሰማያት ደስ ተሰኙባት። በዚች ቀን ዕውነተኛ ምእመን ከሆነ ከንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ዘንድ የጣዖት ቤቶች እንዲዘጉ አብያተ ክርስቲያናትም እንዲከፈቱ ትእዛዝ ወጥቷልና። ደስታን የተመላች ያች መልእክት ወደ እስክንድርያ ከተማ እንደ ዛሬዋ ቀን በደረሰች ጊዜ ፈጽሞ ደስ ተሰኙ ወደ ግብጽ አውራጃዎችም ሁሉ ላኳት ምእመናን ሁሉ ስለ ቤተ ክርስቲያን ክብር ከፍ ከፍ ማለት ደስ አላቸው። የጣዖታት ቤቶችንም ዘጓቸው አብያተ ክርስቲያናትንም ከፈቱአቸው እንደ ዛሬም በዚች ዕለት በዓል አደረጉ ይኸውም ቈስጠንጢኖስ በነገሠ በዐሥራ አንድ ዓመቱ ነበር እለእስክንድሮስም ሊቀ ጵጵስና በተሾመባት በመጀመሪያ ዓመት ነበር።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅድስት ሶፍያ እና ደናግል ልጆቿ
ዳግመኛም በዚህች ቀን ቅዱሳት ደናግል ደባሞንና ብስጣሞን እናታቸውም ሶፍያ በሰማዕትነት ሞቱ። እንዲህም ሆነ ስሙ ዋርስኖፍ የሚባል አንድ ሰው ነበረ ኤጲስቆጶስነት ሊሾሙት በወደዱ ጊዜ ሸሽቶ ወደ ናባ አውራጃ እሊህ ደናግል ወዳሉበት ወደ ግሕሙን ደርሶ በዚያ አደረ።
በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጦለት ከዚህ ለምን ትተኛለህ ተነሥተህ ተጋደል ለአንተና ሰማዕት መሆን ለሚሹ ሁሉ አክሊል ተዘጋጅቷልና አሁንም ተነሥተህ ወደ መኰንኑ ሒድ በፊቱም ቆመህ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመን አለው።
ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ራእይን እንዳየ ለቅዱሳት ደናግል ነገራቸው። ሲነጋም ተነሥተው ከእርሱ ጋራ ወደ መኰንኑ ሔዱ በመኰንኑ ፊት ክብር ይግባውና በጌታችን ታመኑ። መኰንኑም ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሠቃያቸውና ወደ ወህኒ ቤት ጨመራቸው ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ከዚያ አውጥቶ ከቅዱስ ዋርስኖፍ ጋራ ወደ ስንሑር ላካቸው እናታቸውም ትከትላቸው ነበር።
መኰንኑም ለአማልክት ዕጣን ዕጠኑ አላቸው ባልታዘዙለትም ጊዜ ጽኑ ሥቃይን አሠቃያቸው እግዚአብሔርም መልአኩን ልኮ አጸናቸው ቊስላቸውንም ፈወሰ። ከዚህም በኋላ መኰንኑ ከእርሱ ጋር ወደ ሀገረ ፃ ይዞአቸው ሔደ። የጣዖታቱ ካህናትም ጣዖታቱን እንደምትረግም ስለ ቅድስት ደባሞን ነገሩት እንዲሁም ባልጀራዋ ዮና የምትባል ሴት አንዳለች ነገሩት እነርሱም ኀብራቸው በየራሱ የሆኑ መልካም ልብሶችን እየሠሩ ለምግባቸው ይሸጡ ነበር የተረፋቸውንም ይመጸውቱ ነበር። መኰንኑም የዮናን ዜና ሰምቶ ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጥ ባለሰይፉን ላከው የሰያፊውም ስም አውሎጊስ ነው።
ወደርሷም በቀረበ ጊዜ ፊትዋ እንደ መላእክት ፊት ብርሃንን ተመልቶ አየና ፈራ እርሷንም ወደ መኰንኑ እንዲወስዳት እንጂ እንዳይገድላት የእግዚአብሔር ጸጋ አስገነዘበችው ቤተ ሰቦቿም ተሰነባብተዋት ጸንፋ ከሚባል አገር ወጣች ወደ ሀገረ ፃ ደርሳም መኰንኑን ተገናኘችው ከቅዱስ ወርስኖፍና ከባልንጀሮቹ ጋራ እርስ በርሳቸው ሰላምታ ተሰጣጡ።
ሰያፊው አውሎጊስም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነና ራሱን ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለ እንዲሁም እሊያን ቅዱሳት ደናግልንም ራሳቸውን ቈረጧቸው ገድላቸውንም ፈጽመው የድል አክሊልን ተቀበሉ።
ቅድስት ደባሞንን ግን ጽኑዕ ሥቃይ ያሠቃዩአት ዘንድ በመንኰራኵር ላይ ሰቀሉአት። በዚህ ሥቃይም ውስጥ ለብዙ ቀኖች ኖረች የእግዚአብሔር መልአክም ያጸናት ያስችላትና ቊስሎቿን ይፈውሳት ነበር መኰንኑም ወደ ወህኒ ቤት አስገባት በዚያም ጥቂት ቀን ኖረች ወደ ፍርድ ሸንጎም አስቀርቦ ለአማልክት ሠዊ አላት ባልሰማችውም ጊዜ ራሷን እንዲቆርጡ አዘዘ።
ራስዋንም ሊቆርጡ ከከተማ ወደ ውጭ በአወጧት ጊዜ ሴቶች ሁሉ እያለቀሱ ከብበዋት ነበር እርሷ ግን ፈጽማ ደስ ይላት ነበር። ራስዋንም በሰይፍ ቆረጥዋት እንዲሁም እናቷንና እኅቷን በሰይፍ ቆረጧቸው በመንግሥተ ሰማያትም የድል አክሊልን ተቀበሉ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን። በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages