ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 5 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, July 25, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 5

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም



ሐምሌ አምስት በዚች ቀን የክቡራንና የዐበይት አባቶቻችን ሐዋርያት የቅዱስ ጴጥሮስ እና የቅዱስ ጳውሎስ የሰማዕትነታቸው መታሰቢያ ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የቅዱስ ጴጥሮስ
ሐምሌ አምስት በዚህች ቀን የሐዋርያት የቅዱስ ጴጥሮስ የሰማዕትነት መታሰቢያ ነው። ይህም ጴጥሮስ ከቤተ ሳይዳ ነበር ዓሣ አጥማጅም ነበር ጌታችንም ከተጠመቀባት ዕለት ማግሥት አግኝት መረጠው ከእርሱ አስቀድሞም ወንድሙ እንድርያስን አግኝቶ መረጠው።
መድኃኒታችንንም እስከ መከራው ጊዜ ሲአገለግለው ኖረ ፍጹም ሃይማኖት ለጌታውም ቅንዓትና ፍቅር ነበረው። ስለዚህም በሐዋርያት ሁሉ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው። ጌታችንም ሰዎች ማን እንደሆነ ማንም እንደሚሉት ስለ ራሱ በጠየቃቸው ጊዜ ሌሎቹ ኤርሚያስ ይሉሃል ወይም ኤልያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል አሉት።ጴጥሮስ ግን የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህ አለ።
ጌታችንም የሃይማኖት አለት የቤተ ክርስቲያንም መሠረት ነህ ብሎ ብፅዕና ሰጠው የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻ ቁልፍ ሰጥቼሃለሁ አለው። አጽናኝ የሆነ የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ ከተቀበለ በኃላ ተናጋሪዎች በሆኑ በዚህ ዓለም ተኩላዎች መካከል ገባ በውስጣቸውም ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰበከ ቁጥር የሌላቸው ብዙዎች አሕዛብንም መልሶ የዋሆች ምእመናን አደረጋቸው።
ጌታችንም የማይቁጠሩ ታላላቅ ድንቆችና ተአምራቶችን በእጆቹ አደረገ ጥቅም ያላቸዉ ሦስት መልእክቶችም ጽፎ ለምእመናን ላካቸው ለማርቆስ ወንጌሉን ተርጎሞ አጽፎታል። ከዚያም በሗላ ወደ ሮሜ ከተማ ገባ የከተማው መኳንንት ወደ ሚሰበሰቡበት ወደታላቁ የጨዋታ ቦታም ሔዶ በታላቅ ድምፅ እንዲህ ብሎ ተናገረ የሚራሩ ብፁዓን ናቸው ለርሳቸውም ይራሩላቸዋልና የዚህንም ተከታታይ ቃሎች ተናገሩ በዚያም ከዚያ የነበሩ አራት የድንጊያ ምሰሶዎችም በሚያስፈራ ድምፅ አሜን አሉ የተሰበሰቡትም ይህን ቃል በሰሙ ጊዜ ደነገጡ ከንድ ሰው ነበረ ከእነዚያ ድንጋዮች ቃልን ስለ ሰማ ያን ጊዜ ጋኔኑ ጣለው ከእርሱም ወጥቶ ሔደ መኳንንቱም ፈርተዋልና ስለዚህ ነገር እያደነቁ ወደ ቤታቸው ገቡ።
ከከተማ መኳንንቶችም ቀዉስጦስ የሚባል አንዱ ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ ስሟ አክሮስያ ለምትባል ሚስቱ ዓለምን ስለ መተው ለድኖችም ሰለመራራትና የመሳለለውን ቃል ጴጥርስ እንዴት እንዳስ ተማረ ነገራት እርሷም በሰማች ጊዜ በልቧ ነቅታ ይህ ነገር መልካምና ድንቅ ነው አለች ጴጥሮስ ያስተማረውንም ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በአንድነት ተስማሙ ከዚህም በሗላ ገንዘባቸውን ሁሉ ለድሖች ሰጡ ከዕለት ራት በቀር ምንም አላስቀሩም። ከጥቂት ቀኖችም በሗላ ንጉሡ ስለ መንግሥት ስራ ከርሱ ጋራ ለመማከር በቶሎ እንዲደርስ ወደርሱ መልእክትን ላከ። ቀውስጦስም ይህን በሰማ ጊዜ ገንዘብ ስላልነበረው ፈርቶ ደነገጠ ተጨነቀም ምክንያቱም አመካኝቶ ይሠወር ዘንድ ከሚስቱ ጋራ ተማከረ እሷም ግን ምክንያት አታድርግ ነገር ግን ወደ ንጉሡ ሒድ የጴጥሮስ አምላክ ጎዳናህን ያቅናልህ አለችው።
እርሱም ነገርዋን ተቀብሎ ወደ ንጉሡ ሔደ በመንገድም በእግዚአብሔር የታዘዘ ብዙ በረከትን አገኘ ወደ ንጉሱም ደረሰ ንጉሡም በደስታ እና በክብር ተቀበለው። ከሦስት አመት በሗላም ወደ ቤቱ በተመለሰ ጊዜ ሁለት ልጆቹ የተመረዘ ውኃ ጠጥተው እነሆ ሙተው ነበር ሚስቱም ለእርሱ መንገርን ፈራች ብዙ ምሳሌዎችን ከመሰለቸለት በሗላ ነገረችው በሰማ ጊዜም እጅግ አዝኖ አለቀሰ። ሚስቱም እንዲህ አለችው ጌታዬ ሆይ ልባችን የሚጽናናበትን እርሱ ያደርግልናልን የጴጥሮስ ፈጣሪ እግዚአብሔርን እንለምነው ሊጸልዩም በጀመሩ ጊዜ ቀውስጦስና አክሮስያ ሆይ የደቀ መዝሙሬ የጴጥሮስ ቃል ስለ ሰማችሁና ስለተቀበላችሁት ስለዚህ ልጆቻችሁን በሕይወታቸው እሰጣችሗለሁ የሚል ቃልን ከሰማይ ሰሙ ያን ጊዜም ልጆቻቸው ድነው ተነሡ ቀውጦስና ሚስቱም ደስ አላቸው የተመሰገነ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።
እኝህም ከሞት የተነሡ ልጆች ለቅዱስ ጴጥረስ ደቀ መዝሙሮች ሆኑ የአንዱ ስም ቀሌምንጦሶ ነው እርሱም ቅዱስ ጴጥኖስ ያየውንና ጌታችን በሥጋ ወደ ሰማይ በሚዐርግ ጊዜ የገለጠለትን ምሥጢር ሁሉ የነገረው ነው ሰዎች ሊያዪአቸው የማይገባቸውን መጻሕፍትን አስረከበው። ይህንም ቀሌምንጦስን ሊቀ ጵጵስና ወንድሙንም ዲቁና ሾማቸውከዚህም በሗላ ዳግመኛ ቅዱስ ጴጥሮስ አምላክን የወለደች የንጽሕት ድንግል እመቤታችን ማርያም ክብርዋን በምሳሌ አየ።
በቀስት አምሳል ደመናን አይቷልና በላይዋም የብርሃን ድንኳን ነበር በድንኳኑም ውስጥ አምላክን የወለደች ቅድስት ድንግል ማርያም ተቀምጣለች። በእጆቻቸውስጥ የነበልባል ጦሮችንና ሰይፎችን የያዙ መላእክትና የመላእክት አለቆች በዙሪያዋ ነበሩ እንዲህም እያሉ ያመሰግኗት ነበር ከእርሷ የድኅነታችን ፍሬ የተገኘ የሰመረች የወይን ተክል አንቺ ነሽ።
መሕፀንሽ የእግዚአብሔርን በግ የተሸከመ ንጽሕት አዳራሽ አንቺ ነሽ ሁለተኛውም እንዲህ ይላት ነበር የብርሃን እናቱ ሆይ የምህረት መገኛ ሆይ ደስ ይበልሽ የአማልክት አምላክ የፍጥረት ሁሉ ጌታ የሆነ የመድኅን ዙፋን ሆይ ደስ ይበልሽ ክብርና ምስጋናን የተመላሽ የፍጥረቱ ሁሉ እመቤት ደስ ይበልሽ። መላእክትም ምስጋናዋንና ሰላምታዋን ባደረሱ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእርስዋ ተገልጦ ከእርሷ በቀር ማንም ሊያውቀው የማይቻል ነገርን ነገራት ወዲያውኑም ምድር ተናወጸች ሊነገር የማይቻል ሚስጥራትንም ገለጠላት ።
ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን በሀገሩ ሁሉ ቅዱስ ወንጌልን ዘንድ ጴጥሮስን አዘዘው ጴጥሮስም ወጥቶ ሔደ ኢዮጲ ወደምትባል የባሕር ዳርቻና ልድያ ወደምትባል አገር ደረሰ። በአንዲት ዕለትም በኢዮጲ ሳለ ብርህት ደመና ዞረችው እንሆም ሰፊ መጋረጃ ወደርሱ ወረደች በውስጧም የእንስሳት የምድተ በዳ አውሬዋችና የሰማይ አዕዋፍ አምሳል ነበር ጴጥሮስ ሆይ ተነሥና አርደህ ብላ የሚል ቃል ም ከሰማይ ጠራው ጴጥሮስም አቤቱ አይገባኝም እርኩስ ነገር አልበላም ወደ አፌም ከቶ አልገባም አለ።
ያም ቃል ዳግመኛ ጠራውና እግዚአብሔር ንጹ ያደረገውን እርኵስ ነው አትበል አለው ያም ቃል ሥስት ጊዜ እንዲህ መላልሶ ነገረው በየንግግሩም ወደ እሪያዎች ወደ አራዊትና አዕዋፍ ስእሎች ጣት ያመለክተው ነበር ከዚህ በኋላ ያቺ መጋረጃ ወደ ሰማይ ተመለሰች። ጴጥሮስም ስላየው እራእይ አደነቀ ይህም እራእይ ወደ ፈጣሪያቸወረ እግዚአብሔር የሚመለሱ አሕዛብን ስለመቀበል እንደሆነ አስተዋለ ለወንድሞቹ ሐዋርያትም አሕዛብ የእግዚአብሔር ቃልን እንደተቀበሉ የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስንም ከወገኖቹ ጋር እንዳጠመቀው ነገራቸው ።
ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ ከዮሐንስ ጋራ ጌታችን እንዳዘዛቸው ወደ አንጾኪያ ከተማ ገቡ የአገራቸውን ሁኔታ ይጠይቅ ዘንድ ጴጥሮስ ዮሐንስን ላከው ሰዎችንም ክፉ ነገርን ተናገሩት ሊገድሉትም ፈለጉ እያለቀሰም ተመለሰ ሰውነቱም ተበሳጨች ጴጥሮስም አለው አባቴ ሆይ የእሊህ ጐስቋሎች ክፋታቸው እንዲህ ከሆነ ወደ ነገስታቱና ወደ መኳንንቱ ገብተን በገፀታችን ሰም በሰበክን ጊዜ ምን እንሆን ይሆን እንዴትስ ሃይማኖት እናስተምራለን።
ቅዱስ ጴጥሮስ ወዳጄ ሆይ የሃያውን ቀን መንገድ በአንዲት ሌሊት ያመጣን እርሱ ሥራችንን መልካም ያደርግልናል አትፍራ አትዘንም አለው። ከዚህ በኃላ ወደ ከተማ መካከል ገብተው ክብር ይግባውና በጌታችን ስም ሰበኩ የከተማ ሰዎችና የጣዖታቱ አገልጋዮች በእነርሱ ላይ ተሰበሰቡ ታላቅ ድብደባንም ደበደቧቸ አጐሳቆሏቸውም ግማሽ የራስ ጠጉራቸውን ላጭተው ተዘባበቱባቸው አስረውም በግንብ ወስጥ ጣሏቸው።
ከዚህ በኋላ ይረዳቸው ዘንድወደ እግዚአብሔር ጸለዮ ወዲያውኑም ክብር ይግባውና ጌታችን መዳኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኪሩቤልና ሱራፌል እያጀቡት ተገለጠላቸውና እንደህ አላቸው የመረጥኳቹ ጴጥሮስና ዮሐንስ ሆይ በዘመኑ ሁሉ እኔ ከእናንተጋር እኖራለሁና አትፍሩ አትዘኑም ለመዘባበቻም በራሳቹ መካከል ስለላጩአቹ አታድንቁ ይህም መመኪያና ክብር የክህነት ስርዓትና ምልክትንም ይሆናችኋል ካህን የሚሆን ሁሉ ያለዚህ ምልክት ሥጋዬንና ደሜን ማቀበል አይችልም ።
ይህ ምልክት እያለው የሚሞት ካህንም ኃጢአቱ ይሠረይለታል። ይህን ካላቸው በኃላ ከእርሳቸው ዘንድ በክብር ዐረገ። ከዚህም በኃላ ጳውሎስ መጥቶ ዮሐንስን ተገናኘው የዚህ አገር ሰዎች ያደረጉብህ ምንድነው አለው እርሱም ስለ እኔ አታድንቅ የሐዋርያትንም አለቃ በእኔ ላይ በአደረጉት አማሳል አድርገውበታልና አለው። ጳውሎስም አጽናናቸው እንዲህም አላቸው እኔ በጌታችን ፈቃድ ወደ ከተማው ውስጥ ገብቼ እናንተንም አስገባችኃለሁ።
ከዚህም በኃላ ጳውሎስ ሒዶ ምክንያትን ፈጠረ ጣዖተቸውንም እንደሚአመልክ መስሎ ሐዋርያትን እንዲአቀርቡለትና ስለ ሥራቸውም እንዲጠይቃቸው የከተማውን መኳንንት አነጋገራቸው። መኳንንቱም ወደ ጳውሎስ እንዲአቀርቧቸው አዘዙ በቀረቡም ጊዜ ጳውሎስ ስለ ሥራቸው ጠየቃቸው። እነርሱም ድንቆችንና ተአምራቶችን ለሚአደርግ ለክርስቶስ ደቀ መዝሙሮቹ እንደሆኑ ነገሩት።
ዳግመኛም እናንተ እንደርሱ ማድረግ ትችላላችሁን አላቸው እነርሱም አዎ በእርሱ ስም ሁሉን ሥራ መሥራት እንችላለን አሉት። ከዚህም በኃላ ከእናቱ ማሕፀን ዕውር ሆኖ የተወለደውን ዐይኑን አበሩ። የንጉሡንም ልጅ ከሞተ በሦስት ወሩ ሥጋውም ከተበላሸ በኃላ ከመቃብር አስነሡት። ንጉሡና የከተማ ሰዎች ሁሉ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ።
ጴጥሮስም ምድሩን ረግጦ ውኃን አፈለቀ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱሰወ ስም አጠመቋቸው በቀናች ሃይማኖትም እንዲጸኑ አደረጓቸው። ከዚህም በኃላ በሎዶቅያ ያሉ ምእመናን የቂሳሮስ ባሕር ከወሰኑ አልፎ ብዙ ሰዎችን ከአትክልት ቦታዊቻቸውና ከከብቶቻቸው ጋራ እንዳሠጠማቸው ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ላኩ ጴጥሮስም ተወዳጅ ዮሐንስን ወደ እነርሱ ላከ።
ዮሐንስም ወደ እነርሱ ሲጓዝ በጎዳና በግ አገኘ በጉንም እንዲህ ብሎ ላከው ወደ ቂሳሮስም ወንዝ ሒድ የክርስቶስ ደቀ መዝሙሩ ወደ አንተ ልኮኛል ወደ ቀድሞው ወሰንህ ተመለሰህ ትገባ ዘንድ አንተ በእግዚአብሔር ቃል የታሠርክ ነህ ብሎሃል በለው። ያን ጊዜ በጉ ሒዶ እንዳዘዘው አደረገ ወንዙም ሸሽቶ ወደ ቦታው ተመለሰ ቁጥር የሌላቸው ብዙዎች የከተማ ሰዎችም ይህን አይተው በጌታ አመኑ።
ከዚህም በኃላ ቅዱስ ጴጥሮስ አልፎ ወደ ሮሜ ከተማ ገባ በዚያም ሥራ መሠሪው ሲሞን ተቃወመው እርሱንም ከአየር ላይ አውርዶ ጥሎ አጠፋው ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው ብዙዎች ሕዝቦች አመኑ። የከተማው ገዥ የአክርጶስ ቁባቶችም የቅዱስ ጴጥሮስን ትምህርት ተቀበሉ ሌሎችም የከበሩ ብዙዎች ሴቶች ትምህርቱን በመቀበል ከባሎቻቸው ርቀው ንጽሕናቸውን ጠበቁ።
ስለዚህም ነገር ቅዱስ ጴጥሮስን ሊገድሉት የሮሜ መኳንንት ተማከሩ። የአልታብዮስ ሚስትም እንዳይገድሉት ከሮሜ ከተማ ወጥቶ እንዲሔድ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ላከች ምእመናን ወንድሞችም ውጣ አሉት እርሱም ቃላቸውን ተቀበለ ትጥቁንም ለውጦ ከከተማው ወጣ። በሚወጣበትም ጊዜ መስቀል ተሸክሞ ወደ ከተማ ሲገባ ጌታችንን አገኘውና አቤቱ ጌታዬ ወዴት ትሔዳለህ አለው።
ጌታም ልሰቀል ወደ ሮሜ ከተማ እሔዳለሁ ብሎ መለሰለት ቅዱስ ጴጥሮስም አቤቱ ዳግመኛ ትሰቀላለህን አለው። ያን ጊዜም ጎልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ እጅህ ታጥቀህ ወደ ወደድከው ትሔዳለህ በሸመገልክ ጊዜ ግን እጅህን ታነሣና ሌላ ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል ያለውን የጌታችንን ቃል አሰበ አስተዋለውም። ያን ጊዜም ወደ ከተማው ተመልሶ ክብር ይግባውና ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የሆነውን ለወንድሞች ነገራቸው እነርሱም እጅግ አዘኑ።
ንጉሥ ኔሮንም ቅዱስ ጴጥሮስን እንዲሰቅሉት አዘዘ ሊሰቅሉትም በያዙት ጊዜ ወታደሮችን እንዲህ ብሎ ለመናቸው የክብር ንጉሥ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደላይ ሆኖ ስለተሰቀለ እኔ ቁልቁል ልሰቀል ይገባኛል። ወዲያውኑም እንደነገራቸው ሰቀሉት። ተሰቅሎ ሳለም ለምእመናን የሕይወትን ቃል አስተማራቸው በቀናች ሃይማኖትም እንዲጸኑ አዘዛቸው ከዚህም በኃላ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የቅዱስ ጳውሎስ
በዚህችም ቀን ዳግመኛ ልሳነ ዕረፍት የክርስቶስ አንደበት የዕውቀት አዘቅት የቤተ ክርስቲያን መብራት የቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ የሰማዕትነቱ መታሰቢያ ነው። እንደ ስሙም ትርጓሜ መሪ አመስጋኝ ወደብ ጸጥታ ነው። ይህም ጳውሎስ አስቀድሞ በክርስቶስ ያመኑትን የሚያሳድድ ነበረ እርሱም ከብንያም ወገን የፈሪሳዊ ልጅ ነው።ወላጆቹም ሳውል ብለው ስም አወጡለት ትርጓሜውም ስጦታ ነው።
ቁመቱ ቀጥ ያለ መልኩ ያማረ ፊቱ ብሩህ ቅላቱ እንደ ሮማን ቅርፍት ደበብ ያለ ዐይኑም የተኳለ የሚመስል አፍንጫው ቀጥ ያለ ሸንጎበታም ጉንጩ እንደ ጽጌ ረዳ ነበረ። እርሱም ሕገ ኦሪትን አዋቂ ነበረ ለሕጉም ቀናተኛ ሆኖ ምእመናን አስዳጅ ነበረ። ወደ ሊቀ ካህናቱም ሔዶ በመንገድ የሚያገኘው ሰው ቢኖር ወንዶችንና ሴቶችን እንደ ታሠሩ ወደ ኢየሩሳሌም ይመልሳቸው ዘንድ ለደማስቆ ከተማና ለምኮራቦች የፈቃድ ደብዳቤ ለመነ።
ሲሔድም ወደ ደማስቆ ከተማ አቅራቢያ በደረሰ ጊዜ ድንገት ከሰማይ መብረቅ ብልጭ አለበት በምድር ላይም ወደቀ ወዲያውም ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ የሚለውን ቃል ሰማ። ሳውልም አቤቱ አንተ ማነህ አለው አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ በሾለው ብረት ላይ ብትረግጥ አንተን ይጎዳሃል አለው። ከርሱ ጋራ ቁመው: የነበሩ ሰዎችም ንግግሩን ይሰሙ ነበር ነገር ግን የሚያዩት አልነበረም። ሳውልም ከምድር ተነሣ ዐይኖቹም ተገልጠው ሳሉ አያይም ነበር እየመሩም ወደ ደማስቆ አስገቡት በዚያም ሳያይ ሳይበላና ሳይጠጣ ሦስት ቀን ሰነበተ።
በዚያም በደማስቆ ከደቀ መዛሙርት ወገን ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው ነበረ ጌታም በራእይ ተገለጠለትና ሐናንያ ብሎ ጠራው እርሱም አቤቱ ጌታዬ እነሆኝ አለ። ጌታም ተነሥና ቀጥተኛ ወደምትባለው መንገድ ሒድ በይሁዳ ቤትም ጠርሴስ ከሚባል አገር የመጣ ሳውል የሚባል ሰው ፈልግ እርሱ አሁን ይጸልያልና አለው። ሐናንያ ግን መልሶ እንዲህ አለ አቤቱ ስለዚያ ሰው በኢየሩሳሌም በቅዱሳኖችህ ላይ የሚያደርገውን ክፉ ነገር ሁሉ ከብዙ ሰዎች ሰምቻለሁ ወደዚህም ከካህናቱ አለቃ አስፈቅዶ የመጣ ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ሊአሥር ነው። ጌታችንም ተነሥና ሔድ በአህዛብና በነገሥታት በእስራኤልም ልጆች ፊት ሰሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ አድርጌዋለሁና ።
እኔምሰ ስለ ስሜ መከራ ይበቀል ዘንድ እንዳለው አሳየዋለሁ። ያን ጊዜም ሐናንያ ሔደ ወደ ቤትም ገባ ወንድሜ ሳውል በመንገድ ስትመጣ የታየህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታይ ዘንድ የመንፈስ ቅዱስም ጸጋ ይሞላብህ ዘንድ ወደ አንተ ልኮኛል አለው። ያን ጊዜም የሸረሪት ድር የመሰለ ከዐይኖቹ ላይ ተገፎ ወደቀ ዐይኖቹም ተገለጡ።
ወዲያውም አየ ተነሥቶም ተጠመቀ እህልም በልቶ በረታ። ከደቀ መዛሙርትም ጋር በደማስቆ ጥቂት ቀን ሰነበተ። በዚያው ጊዜ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ብሎ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰበከ አስተማረም። የሰሙትም ሁሉ አደነቁ እንዲህም አሉ በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ሁሉ ያሳድድ የነበረው ይህ አልነበረምን ወደዚህስ የመጣው እያሠረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሊወስዳቸው አይደለምን።
አጽናኝ መንፈስ ቅዱስም አደረበት ዕውነተኛውንም ሃይማኖት ግልጽ አድርጎ አስተማረ። ለኦሪት ሕግ የሚቀና እንደ ነበረ እንዲሁ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሠራት ሕገ ወንጌል ዕጽፍ ድርብ ቅንዓትን የሚቀና ሆነ ከዚህም በኃላ በአገሮች ሁሉ ዞሮ ሰበከ በጌታችንም ስም ሰበከ። ድንቆችንና ተአምራትንም አደረገ። ቁጥር የሌላቸው ብዙዎች አሕዛብንም አሳመናቸው ነገር ግን ብዙ ጊዜ በመገረፍ በመደብደብና በመታሠር ብዙ መከራ ደረሰበት መከራውንም ሁሉ ታግሦ በሁሉ ቦታ ዙሮ አስተማረ።
በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔርን ሥራ ሲሠሩ ሲጾሙና ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ እኔ እነርሱን ለመረጥሁለት ሥራ ሳውልንና በርናባስን ለዩልኝ አላቸው። ከዚህም በኃላ ጾመውና ጸልየው እጃቸውንም በራሳቸው ላይ ጭነው ሾሙአቸው ከመንፈስ ቅዱስም ተሹመው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ። በደሴቱም ሁሉ ሲዘዋወሩ ጳፉ ወደ ምትባል አገር ደረሱ።
በዚያም ሐሰተኛ ነቢይ የሆነ ስሙ በርያሱስ የሚባል አንድ ሥራየኛ አይሁዳዊ ሰው አገኙ እርሱም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባል ብልህ ሰው ከሆነ አገር ገዥ ዘንድ የነበረ ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ወደ በርናባስንና ሳውልን ጠራቸው። የስሙ ትርጓሜ እንዲህ ነበርና ኤልማስ የሚሉት ያ ሥራየኛ ሰው ይከራከራቸው ነበረ ገዥውንም ማመንን ሊከለክለው ወዶ ነበር። ጳውሎስ በተባለው ሳውል ላይም መንፈስ ቅዱስ መላበት።
አተኲሮም ተመለከተው ኃጢአትንና ክፋትን ሁሉ የተመላህ የሰይጣን ልጅ የፅድቅ ሁሉ ጠላት ሆይ የቀናውን የእግዚአብሔርን መንገድ እያጣመምኽ ተው ብትባል እምቢ አልኽ እነሆ አሁን የእግዚአብሔር ልጅ በአንተ ላይ ተቃጥታለች ትታወራለህም እስከ እድሜ ልክህም ፀሐይን አታይም አለው። ወዲያውኑም ታወረ ጨለማም ዋጠው የሚመራውንም ፈለገ አገረ ገዢውም የሆነውን አይቶ ደነገጠ በጌታችንም አመነ።
ከዚህ በኃላ ሒደው ወደ ሊቃኦንያ ከዚያም ወደ ልስጥራንና ደርቤን ከተማ ወደ አውራጃውም ሁሉ ገብተው አስተማሩ። በልስጥራን ከተማም ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ እግሩ ልምሾ የሆነ አንድ ሰው ነበረ ተቀምጦ ይኖር ነበረ እንጂ ለምሾ ከሆነ ጀምሮ ቆሞ አልሄደም። ጳውሎስንም ሲያስተምር አደመጠው ጳውሎስም ተመልክቶ ሃይማኖት እንዳለው እንደሚድንም ተረዳ።
ድምፁንም ከፍ አድርጎ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥና ቀጥ በልኽ ቁም እልሀልሁ አለው ወዲያውኑ ተነሥቶ ሔደ። አሕዛብም ጳውሎስ ያደረገውን አይተው በጌታችን አመኑ። እርሱም በዚያ ሳለ አይሁድ ከአንጾኪያና ከኢቆንያ መጥተው ልባቸውን እንዲአስጨክኑባቸው አሕዛብን አባበሏቸው።
ጳውሎስንም በድንጊያ ደበደቡት ጎትተው ወደ ውጭ አወጡት። በማግስቱም ከበርናባስ ጋራ ወደ ደርቤን ከተማ ሄዱ። በዚያችም ከተማ አስተማሩ ብዙ አህዛብንም ወደ ሃይማኖት አስገቡ ለቤተ ክርስቲያንም ቀሳውስትን ሾሙላቸው ከዚያም ወደ መቄዶንያ አልፈው ሔዱ ጋኔን ሟርት የሚያሠራትን አንዲት ልጅ አገኙ ከምታገኘው ዋጋ ለጌቶቿ ብዙ ትርፍን ታስገባ ነበር።
እንዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው የሕይወትንም መንገድ ያስተምሯችኋል ብላ እየጮኸች ከጳውሎስ ኋላ ተከተለች ብዙ ቀንም እንዲሁ ታደርግ ነበር። ጳውሎስንም አሳዘነችው መለስ ብሎም መንፈስ ርኩስን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንድትወጣ አዝዤሃለሁ አለው ወዲያውኑም ተዋት።
ከዚህ በኃላም ሐለብ ከሚባል አገር ደረሰ የጢሞቴዎስንም እናት ስሟ በድሮናን ከሞት አስነሣት። በዚያም ያዙት ለዚያች አገር ጣዖትም ሊሠዉት ወድደው በሚነድ እሳት ውስጥ ጨመሩት። ስለእነርሱም እየማለደ እጆቹን በመስቀል ምልክት አምሳል ዘረጋ። አሕዛብም በአዩት ጊዜ ስለዚህ ድንቅ ሥራ አደነቁ።
ከእሳት መካከልም እንደወጣ ማለዱት ምንም ምን ሳይነካው ወጣ ሰገዱለትም ክብር ይግባውና በጌታችንም አመኑ የአገሩ ሹም አርስጦስም አመነ። ሰባቱ የጣዖት ካህናቶች ግን ሸሽተው ተሠወሩ። ቅዱስ ጳውሎስም በጭላት አምሳል የተቀረጸውን ምስል ጠራው ምስሉም በአንበሳ ምሳሌ መጥቶ በምኩራቡ መካከል በጳውሎስ ፊት ቆመ።
ቅዱስ ጳውሎስም የሚያመልኩህ ካህናቶችህ ወዴት አሉ አለው አንበሳውም ያሉበትን እስክነግርህ ድረስ ጌታዬ ጥቂት ታገሠኝ አለው። ካህናቱም ወሰተሸሸጉበት ሔዶ አንዱን አንገቱን በአፉ ይዞ እየጎተተ አምጥቶ እንደ በድን በአደባባዩ መካከል ጣለው። ሰባቱንም እንዲሁ እየአንዳንዱን እየጎተተ አመጣቸው።
ሕዝቡም ሊገድሏቸው ወደዱ። ጳውሎስም ዛሬ በዚች ከተማ ማዳን እንጂ መግደል አይገባም አለ ከዚህም በኃላ ሁሉንም አጠመቃቸው ሃይማኖትንም አስተማራቸው። ያንንም አንበሳ የሆነ የጭላት ምስል አንበሳ ሆይ አትፍራ ስለ አገለገከኝ እስከ ምሻህ ድረስ ኑሮህ በበረሀ ይሁን አለው። ያን ጊዜም ወደ በረሀ ሔደ።
ጳውሎስም ከዚያ ተነሥቶ አካ ወደ ሚባል ከተማ ሔደ ስክንጥስ ከሚባል ደቀ መዝሙርም ጋራ ተገናኘ አይሁድም ዜናውን ሰምተው ከአሕዛብ ጋራ ተሰበሰቡ ይዘውም ጭንቅ የሆነ ሥቃይን አሠቃዩት ዳግመኛም ሁለት በሮችን አመጡ ከስክንጥስ ጋራም አሥረው በከተማው ጥጋጥግ በስለታም ድንጋይ ላይ አስጐተቷቸው ደማቸውም እንደ ውኃ ፈሰሰ ዐጥንታቸውም እስከሚታይ ድረስ ሥጋቸው ተቆራረጠ።
ወደ ጌታም ጸለዩ ያን ጊዜም በሮቹ ከሚነዳቸው ጋራ ደንጊያ ሆኑ። ሕዝቡም በአዩ ጊዜ ለመኮንኑ ነገሩት እርሱም ተቆጣ ወደርሱም እንዲአቀርቧቸውና በደንጊያ እንዲወግሩአቸው አዘዘ በቅዱስ ጳውሎስም ላይ እጅግ ተቆጥቶ አንተ የሥራይ ሰው እነሆ አሠቃይሃለሁ አለው በበሬ ቅርጽ የተሠሩ ሁለት የናስ ቀፎዎችንም ያመጡ ዘንድ አዘዘ።
ዝፍት ሙጫና ድኝ አምጥተው በውጭ ቀላቅለው ሁለቱን የናስ ቀፎዎች በውስጥም በውጭም ቀቧቸው። ሐዋርያትንም በውስጥ ጨምረው በእሳት ምድጃ ውስጥ አስገቧቸው ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊትም እሳት አነደዱባቸው።
መዳኒታችንም ክርስቶስም ከመላእክቶቹ ጋር መጣ እሳቱንም ከዚያ ፈልሶ ወደ ከተማው ውስጥ ገብቶ የከተማውም ሰዋችሁሉ እንዲከባቸው አደረገው በተጨነቁም ጊዜ ጮኹ አለቀሱም መዳን ከፈለጋቹ ፈጥናቹ በአደባባዩ በአንድነት ተሰብሰቡ የሚል ቃል ከሰማይ ጠራቸው ጳውሎስም ወደ በረሀ አሰናብቶት የነበረውን አንበሳ መጣ ጳውሎስ በስሙ በሚያስተምርበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እመኑ እያለ ጮኸ።
ከዚህም በኋላ ወደ እሳቱ ምድጃ ተመልሶ ጳውሎስንና ስክንጥስን ከእሳቱስ ውስጥ ወጡ አላቸው ያንጊዜም የራሳቸው ጠጉር እንኳ ሳይቀነብር ወጡ በላያቸውም ላይ የቃጠሎ ሽታ የለም። ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው በጌታችን በናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን እያሉ ጮኹ ከዚህም በኋላ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸው ስክንስንም ቅስና ሾመላቸው። ከዚሁ በኋላም ከሐዋርያ ፊልጶስ ጋራ ወደ ሁለት አገሮች በአንድነት ሔዱ በዚህም በጌታችን ስም ሰበኩ የአገሩ አለቆችም ያዙአቸው እጆቻቸውንና እግሮቻቸውንም አሠሩአቸው በአንገቶቻቸውም የብረት ሰንሰለቶችን አስገቡ ራሳቸውንም የሚሸፍን የሚሸፍን የብረት ቆብን ሠሩላቸው በእጅና በመሐል አጆቻቸውና በክንዶቻቸው እያንዳንዱን የብረት አጅ ጨመሩ ከብረቶችም ጋር ቸነከሩአቸው።
ሁለተኛም እስከ አንገት የሚደርስ በትከሻ አምሳል ሠሩ በፉትና በኋላም ቸነከሩአቸው ደግሞም መላ አካላቸውን የሚከብና ከአካላቸው ምንም እንዳይታይ የሚሸፍን የብረት ሠሌዳ ሠሩ ከወገቦቻቸውም ጋራ ቸነከሩት ችንካሮችም ተረከዛቸውን ነድለው ወደ ጭኖቻቸው እስከሚደርሱና እስከ አቈሳሏቸው ድረስ የብረት ጫማ ሠርተው እግሮቻቸውን ቸነከሩ። ደግሞ በመሸፈኛ አምሳል የብረት ሰናፉል ሠሩ ቀማሚዋችም መጡ አንድ መክሊት የሚመዝን እርሳስንም አመጡ ታላቅ የብረት ጋንንም ሰባት ልጥር የሰሊጥ ቅባትን አመጡ ሰቡንና አድሮ ማሩን የእሳቱንም ኋይል አብዝቶ የሚያነደውን ቅመሙን ከሙጫውና ከድኙ ጋር ቀላቀሉ ከዋርካና ከቁልቋል ከቅንጭብም ደም ሰባት ልጥር አንድ የወይን አረግንና ቅባት ያላቸውን ዕንጨቶች ሁሉ አመጡ።
በጋን ውስጥ ያበሰሉትንና ያሟሙትንም ልዩ ልዩ ቅመማ ቅመም አምጥተው ከስጋቸው ጋር እስከሚጣበቅ በቅዱሳን ሐዋሪያት ሥጋ ላይ ባሉት ሠሌዳዎች ውስጥ ጨመሩት በእግራቸው እስከ ራሳቸውም ከፍ ከፍ እስከሚል ድረስ በእሳት ያቀለጡትን ያንን እርሳስ ጨመሩ ርዝመቱ ዐሥራ አምስት ክንድ በሆነ ወፍራም የጥድ ምሰሶ ላይም አቆሟቸውና ከበታቻቸው ፍሬ በሌለው በወይን ሐረግና በተልባ እሳቱን አቀጣጠሉ አንዳንዱ የእሳቱ ነበልባል ከሥጋቸው በላይ ከፍ ከፍ አለ ሐዋርያት ግን ወደ እግዚአብሔር ይፀልዩ ነበር።
ከመኳንንቱም በአንድ ልብ ርኅራኄን አሳደረና እንዲፈቷቸው አዘዘ ፈቷቸው በፈቷቸውና ሠሌዳውን ከስጋቸው ላይ በአስወገዱ ጊዜ ቆዳቸው ተገፈፈና ከብረቱ ሰሌዳዋች ጋር ወጣ ብዙ ደምም ከስጋቸው ፈሰሰ። ሰይጣንም በከተማው ሰዎች ለብ አደረና ሐዋርያትን ወደ እሳት ውስጥ መለሱአቸው ያን ጊዜ ጌታችን ወርዶ የእሳቱን ነበልባል አጠፋው ዝናምን የተመላች ብርህት ደመናም መጥታ ቅዱሳን ሐዋርያትን ከበበቻቸው ከዚያችም አገር አንድ ጊዜ በደንጊያ በመወገር አንድ ጊዜም በፍላጸ በመንደፍ ብዙ ተሠቃዩ ከዚህም በሗላ ሙታንን በአነሡ ጊዜ የከተማው ሰዎች ሁሉ አመኑ አጠመቋቸውም ቤተ ክርስቲያንንም ሰሩላቸው ካህናትንም ሾሙላቸው በቀናት ሐይማኖትም እስቲጸኑ አስተማሩአቸው ከዚያም ወጥተው ጌታችን ወደ አበዘዛቸው ወደ ሌላ አገር ሔዱ።
ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለጳውሎስ ተገለጸለትና የመረጥኩህ ጳውሎስ ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን። መታሰቢያህ የሚያደርገውን በውስጧ የሚጸልየውን ስለትንና መባንም የሚሰጠውን በመታሰቢያህም ቀን ለድኇች የሚመጸውተውን ሁሉ ከአንተ ጋራ በመንግሥተ ሰማያት አኖራቸዋለሁ አለው።
በስምህ የታነፁትንም አብያተ ክርስቲያናት መላእክቶቼን እንዲጠብቋቸው አደርጋቸዋለሁ ብዙ ቃል ኪዳንም ሰጠው በመለኮታዊ አፉ አፉን ሳመውና ከእርሱ ዘንድ ወደ ሰማያት በክብር ዐረገ። ከዚህም በሗላ እልዋሪቆስ ወደምትባል ታላቅ ሀገር እስከ ሚደርስ በብዙ አገሮች ውስጥ ተመላለሰ በዚያም የብርሃን እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገልጻለት አረጋጋችው ረዳችውም በመጋቢት ሃያ ዘጠኝ እንደጻፍነው የአገሩን ሰዎች እንዲአጠምቃቸውና እንዲአስተምራቸው አዘዘችው።
ከዚህም በሗላ ወደ ሮሜ ከተማ ገብቶ በውስጧ ሰበከ ከበስብከቱም ብዙዎች ሰዎች አምነው የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው በመጻሕፍትነት የታወቁ ዐሥራ አራት መልእክቱም ለሮሜ የተጻፈችው ናት። መልካም ሩጫውንም ከፈጸመ በሗላ ንጉሥ ኔሮን ይዞ ድኑ ሥቃይን አሠቃየው እራሱንም በሰይፍ እድቆርጢት ለሰያፊ ሰጠው ከሰያፊውም ጋራ አልፎ ሲሔድ ከንጉሥ ኔሮን ዘመዶች የሆነች አንዲት ብላቴና አገኘችው እርሷም ክብር ይግባውና በጌታችን ያመነች ነበረች ስለርሱም አለቀሰች።
እርሱ ግን መጎናጸፊያሽን ስጨኝ እኔም ዛሬ እመልስልሻለሁ አላት እርሷም መጎናጸፊያዋን ሰጠችውና ራስ ወደ ሚቆርጡበት ቦታ ሔደ ለሰያፊውም ራሱን በአዘነበለ ጊዜ በመጎናጸፊያዋ ፊቱን ሸፈነ ሰያፊውም የቅዱስ ጳውሎስን ራስ ቆርጦ በዚያች ብላቴና መጎናጸፊያ እንደገደለው ለንጉሥ ሊነግረው በተመለሰ ጊዜ ያቺ ብላቴና አገኘችው ያ ጳውሎስ ወዴት አለ አለችው ራስ የሚቆረጥበት ቦታ ወድቋል ራሱም በመጎናጸፊያሽ ተሸፍኗል አላት።
እርሷም እንዲህ ብላ መለሰችለት ዋሽተሃል እነሆ ጴጥኖስና ጳውሎስ በእኔ ዘንድ አልፈው ሔዱ እነርሱም የመንግሥት ልብሶችን ለብሰዋል በራሳቸውም ላይ በዕንቁ የተጌጡ ዐይንን የሚበዘብዙ አክሊላትን አድርገዋል መጎናጸፊያዬንም ሰጡኝ እርሷም እነሗት ተመልከታት ብላ ለዚያ ሰያፊ አሳየችው ከርሱ ጋራ ለነበሩትም አሳየቻቸው አይተውም አደነቁ ስለዚህም ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ።
የዚህም ሐዋርያ ጳውሎስ ተአምራቶቹ ቁጥር የሌላቸው እጅግ የበዙ ናቸው።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳት ሐዋርያት ጸሎት ይማረን በረከታቸው የቅዱሳት ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages