ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን የሆነ ፈጽሞ መሳተፍ የለበትም!
ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን የሆነ ሰው "ኢሬቻ" በተሰኘው የዋቄፈታ ሃይማኖታዊ የአምልኮ ሥርዓት ላይ ፈጽሞ መሳተፍ የለበትም። ምክንያቱም የኦርቶዶክስ ነገረ-ሃይማኖት አስተምህሮ እና የዋቄፈታ አምልኮ እሳቤ ልዩነታቸው እንደ ሰማይና ምድር የራቀ ነው። የክርስቲያኖች አምላክ እና በዋቄፈታ እምነት "አምላክ" የሚሉት ፈጽሞ አንድ አይደሉም። ስለዚህ ሃይማኖትህ ካልሆነ በኢሬቻ የአምልኮ ሥርዓት ላይ ምን ያንከራትትሃል? ምን ያደክምሃል?
ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ሆኖ በዋቄፈታ ሃይማኖታዊ አምልኮ ላይ የሚሳተፍ ካለ አምላኩን እንደካደ ይቆጠራል። በኢሬቻ የአምልኮ ሥርዓት ላይ የሚሳተፍ ሰው "በዋቄፈታ ሃይማኖት የማመልከው አምላክ የእኔም አምላክ ነው" እያለ ነው። በአንድ ጊዜ "ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ነኝ" እያሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ "የዋቄፈታ ሃይማኖታዊ አምልኮ ተከታይ ነኝ" ማለት አይቻልም።
አንተ ሰው ሆይ፤ ወይ ሰይጣንን ምረጥ ወይም እግዚአብሔርን ምረጥ! እስከመቼስ በሁለት ጌቶች ትገዛለህ? ከክርስትና ውጭ የሆነ የዋቄፈታ ሃይማኖት ተከታይ ነኝ የሚል ሰው እንደፈለገ መሆንና አምልኮውን መፈጸም መብቱ ነው። ነገር ግን ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን የሆነ ምእመን በዚህ ሃይማኖታዊ በአል ላይ ፈጽሞ መገኘትም ሆነ ሥርዓቱን መፈጸም የለበትም። በኢሬቻ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ የሚሳተፍ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ፈጽሞ ሊኖር አይገባም፤ ምክንያቱም ክርስቲያን የሆነ ሰው አምላኩ በማይመሰገንበት የሌላ እምነት ሥርዓት ላይ መገኘት ተገቢ ስላልሆነ። ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን የሆነ ሰው ፈጽሞ፣ ፈጽሞ መሳተፍ የለበትም። አንዳንዶቻችን እስኪ ልብ እንግዛ!
2) በኢሬቻ ሥርዓተ አምልኮ ላይ ካህናት ለምን ይሳተፋሉ?
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቀሳውስት ሆነው ሳለ፣ በኢሬቻ ሥርዓተ አምልኮ ላይ የሚሳተፉ ካህናት አምላካቸው ማን እንደ ሆነ ለይተው ያወቁ አይመስሉም። ምዕመናንን በጎችን እንዲጠብቁ ኃላፊነት የተሰጣቸው እረኞች፣ "ዋቄፈና" በተሰኘው ሃይማኖታዊ አምልኮ ላይ የሚሳተፉ ከሆነ፣ እነሱኑ ራሳቸውን ከገቡበት ማጥ ሊያወጣቸው የሚችል ሌላ እውነተኛ እረኛ ያስፈልጋቸዋል።
ስለሆነም፣ በየሀገረ ስብከቱ የሚገኙና "ሁለት ጌቶችን የሚያመልኩ" ካህናትን በማጣራት መገሰጽ፣ አልፎ ተርፎም በቃልና በጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት ይገባል። የትምህርት ክፍተት ያለባቸውን ካህናት ደግሞ ከስህተታቸው እንዲታረሙ የነገረ መለኮቱን ልዩነት እያነጻጸሩ ማስረዳትና ማስገንዘብ ያስፈልጋል።
ነገሩ ሁሉ የተምታታባቸውን ምዕመናን በኢሬቻ ሥርዓተ አምልኮ ላይ እንዳይሳተፉ መጠበቅ ሲገባ፣ እረኛ የተባለው ካህን ራሱ በሽተኛ ከሆነ ግን የተሸከመውን "መንፈሳዊ ቫይረስ" ለሌላው ከማጋራት ወደኋላ አይልም። በመሆኑም አንድ እግራቸውን በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ ሌላ እግራቸውን ደግሞ በኢሬቻ ሥርዓተ አምልኮ ላይ የሚያደርጉትን አካላት አደብ ማስገዛት ተገቢ ነው።
በነገራችን ላይ ንቁና ጠንካራ የቤተ ክህነት መዋቅር ቢኖረን ኖሮ፣ እንደ ቄስ በላይ መኮንን እና መሰል ካህናትን አደብ ማስገዛት ይቻል ነበር። ስለዚህ "በኢሬቻ ሥርዓተ አምልኮ ላይ ካህናት ለምን ይሳተፋሉ?" ብለን በጽኑ መጠየቅ ይኖርብናል።

No comments:
Post a Comment