የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, April 16, 2020

የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት


   

በጲላጦስ ዘመን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት፤ ትንቢቱም ይፈጸም ዘንድ መከራን ተቀበለ፤ ጲላጦስ በ፫ ሰዓት ይሰቅል ዘንድ ሲፈርድበትም፤ ‹‹መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው ቀራንዮ ወደሚባል ቦታ ወጣ›› (ዮሐ.፲፱፥፲፯) የራስ ቅል ስፍራ ቀራንዮ-ጎልጎታ አዳም ዐጽም የተቀበረበት ቦታ ነበር፡፡ በዚያም የአዳም መቃብር የሆነች ዋሻ አለች፤ የመስቀሉንም እንጨት በዚያ በምድር መካከል አይሁዶች ተከሉት፡፡ የአዳም አጽም ቀድሞ ከአዳም ትውልዶች ሲተላለፍ ከኖኅ ደርሷል፤ ኖኅም ወደ መርከብ እንደታቦት አስገብቶት በኋላ መልከጼዴቅ ቀብሮታል፡፡ ጌታችንም ከአዳም የራስ ቅል በላይ ሊያድነው መስቀል ተሸከሞ ተንገላታ፤ አይሁዶችም የቀራንዮን ዳገት  እየገረፉ ከወደ ጫፍ አደረሱት፤ሁለቱንም እንጨት አመሳቅለው ዐይኖቹ እያዩ እጆቹንና እግሮቹን ቸነከሩት፤ በዕለተ ዐርብ ቀትር ፮ ሰዓት ላይም ተሰቀለ፡፡

ጌታችን የተሰቀለበት ሰዓት ፀሐይ በሰማይ መካከል በሆነ ጊዜ የጥላ መታየት በሚጠፋበት፤ ወደ ሰው ተረከዝም በሚገባበት ነበር፡፤ ከ፮ ሰዓት ጀምሮ እስከ ፱ ምድር ጨለመች፤ ፀሐይ፤ጨረቃ፤ከዋክብት ብርሃናቸውን ከለከሉ፤ ምክንያቱም የፈጣሪያቸውን ዕርቃኑን ይሸፍኑ ዘንድ ነበር፤ ‹‹ቀትርም በሆነ ጊዜ ፀሐይ ጨለመ፤ምድርም ሁሉ እስከ ፱ ሰዓት ድረስ  ጨለማ ሆነ›› ማር.፲፭፥፴፫፡፡

በ፱ ሰዓት በቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ስለ ጌታችን በሰማይ ፫ት በምድር ፬ት ተአምራትን ሲያደርጉ አይቶ በእውነት አምላክ እንደሆነ አመነ፤ ‹‹አቤቱ በመንግሥት በመጣህ ጊዜ አስበኝ›› ባለ ጊዜ በግራ የተሰቀለው ዳክርስ ግን ‹‹እስቲ አምላክ ከሆነ እራሱን ያድን›› ብሎ ተዘባበተ፡፡ ፍያታዊ ዘየማን ግን ‹‹እኛስ በበደላችን ነው የተሰቀልን፤ እርሱ ግን ምንም ሳይበድል ነው፤ እንዴት በአምላክ ላይ ክፉ ነገርን ትናገራለህ›› ብሎ ገሰጸው ፤ፍያታዊ ዘየማንም ጌታችን በጌትነት መንበረ ጸባዖት(መንግሥት) ሆኖ ታየው፤እርሱንም አይቶ ‹‹ተዘከረኒ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ›› ቢለው ጌታችን ‹‹ዮም ትሄሉ ምስሌየ ውስተ ገነት›› ብሎ ደመ ማኅተሙን ሰጥቶታል፤ በኋላ ገነት ሲገባም መልአኩ አንተ ማነህ፤ አዳም ነህ፤ አብርሃም ወይንስ ይስሐቅ? እያለ ጠይቆታል፡፡ መልአኩ ሳያውቅ የጠየቀ ሆኖ አይደለም፤እንኳን በመጨረሻ የጸደቀ ፍያታዊ ቀርቶ በዘመናቸው የኖሩ ጻድቃንን ያውቃል፤ አዳምን ፤አብርሃምን፤ይስሐቅን ሳያውቅ ቀርቶም አይደለም፡፡ ነገር ግን ሊቃውንት ሲተረጉሙት ‹‹አዳም ነህ›› ማለቱ የአዳምን ያህል ሥራ አለህን? አብርሃም ነህ ሲለው ደግሞ የአብርሃምን ያህል ሥራ አለህን? ለማለት ነው፡፡ ‹‹በጌታችን ኢየሱስ መስቀል አጠገብም እናቱ፤ የእናቱም እኅት፤ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፤መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር›› (ዮሐ.፲፱፥፳፭) ‹‹እነርሱም ማርያም መግደላዊት፤ የታናሹ ያዕቆብ እና የዮሳ እናት ማርያም፤ የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ሰሎሜም ነበሩ›› (ማር.፲፭፥፵)፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከተናገራቸው የአደራ ቃላት አንዱ እመቤታችን ለቅዱስ ዮሐንስ መሰጠቷ ነው፤ ለወዳጁ ዮሐንስ ከስጦታ ሁሉ ስጦታ የሆነች እናቱን እናት ትሁንህ ብሎ ሰጠው፤‹‹እነኋት እናትህ፤ እነሆ ልጅሽ›› (ዮሐ.፲፱፥፳፮)፡፡ በኋላ ወደ ቤቱ ወስዷት ፲፭ ዓመት ኖራለች፤ በዚህም የዮሐንስ ቤት በአቢዳራ ቤት ተመስላለች፤እመቤታችንም የሚያጽናናትን ወዳጁ ዮሐንስን ሰጥቷታል፡፡ የእመቤታችን ለዮሐንስ መሰጠት ቀድሞ በሙሴ አንጻር ጽላቷ ለሕዝቡ ሁሉ እንደተሰጠች፤በዮሐንስ አንጻርም እመቤታችን ለሁላችን ለምእመናን ተሰጥታናለች፡፡

፱ ሰዓት በሆነ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ፤አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ›› ብሎ በታላቅ ቃል ተናገረ፤(ማር.፲፭፥፴፬)፡፡ በዚያም ቆመው የነበሩት ‹‹አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ፤›› የሚለውን ድምጽ የሰሙ ኤልያስን ይጣራል እያሉ አሙት፤ ክህደትንም ተናገሩ፤ ያንጊዜ አንዱ ወታደር ሮጦ ሆምጣጤ የመላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበርና  በሰፍነግ መልቶ በሂሶጽም አድርጎ በአፉ ውስጥ ጨመረለት፡፡

 በመስቀል ላይ ሳለ ጌታችን ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ሁሉ ተፈጸመ አለ፤ (ማር. ፲፭፥፴፯)፤ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በፈቃዱ ለየ፡፡ አይሁድም እኒህ ሰዎች እንደተሰቀሉ አይደሩ፤ ምክንያቱም ቀጣዩ ቀን ሰንበት ነውና ጭናቸውን ሰብረው ያወርዷቸው ዘንድ ጲላጦስን ጠየቁት፤ እርሱም ፈቀደላቸው፡፡ የሁለቱ ወንበዴዎች፤ ፈያታይ ዘየማንንና ፈያታይ ዘጸጋምን አብረው አወረዷቸው፤ ከጌታችን ዘንድ ቢቀርቡ ፈጽሞ ሞቶ አገኙት፤ በዚህም ጭኑን ሳይሰብሩት ቀሩ፡፡ ሌላው ግን የተመሰለው ምሳሌ ፍጻሜ ሲያገኝ ነው፤ የፋሲካውን በግ ‹‹አጥንቱን ከእርሱ አትስበሩ›› የተባለው አሁን ተፈጸመ፤(በዘፀ.፲፪፥፲)፡፡ ከጭፍሮቹም አንዱ ቀኝ ጎኑን በጦር ወጋው እንዲል ከወታደሮቹ አንዱ የሆነው ለንጊኖስ የጌታችንን ጎን ቢወጋው ትኩስ ደምና ቀዝቃዛ ውኃ ፈሷል፡፡ ለንጊኖስ ጥንተ ታሪኩ አንድ ዐይኑ የጠፋ ሲሆን ጌታችን በተሰቀለበት ጊዜ ወደ ጫካ ሸሽቶ ርቆ ነበር፤ ምክንያቱም ከዚህ ሰው ሞት አልተባበርም በማለት ነው፡፡ አመሻሹ ላይ የአይሁድ አለቆች ሲመለሱ ከመንገድ አገኘቱ፤ስለምን ከመሢሑ ሞት አልተባበርክም አሉት? እርሱም ምንም ስላላገኘሁበት አላቸው፡፡ ከዚያም በኋላ እንደሕጋቸው እንደሚቀጡት ቢነግሩት እየሮጠ ሔዶ የጌታችንን ጎን ሲወጋው ደሙ በዐይኑ ላይ ፈሰሰ፤ ያን ጊዜ ዐይኑ በራለት፤ከጌታችን ጎን የፈሰሰው ደም እንደ ለ ቅርጽ ሆኖ በሁለት ወገን ደምና ውኃ ሆነ፡፡ ከጌታችንም የፈሰሰውን ትኩስ ደም መላእክት በጽዋ ቀድተው በዓለም ላይ ረጩት፤ ይህ መሠረት ሆኖ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የሚታነጸው የጌታችን ደም የነጠበበት  ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ›› ያለው (ሐዋ.፳፥፳፰)፡፡ ከጌታ ጎን የፈሰሰው ውኃ ደግሞ ምእመናን የልጅነት ጥምቀትን ስንጠመቅ ውኃውን ካህኑ ሲባርከው ማየ ገቦ ይሆናል፡፡

ቅዳሜ ከቀድሞው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረችው ቅዳሜ ትባላለች፤ ይህ ቅዳሜ ጌታችን ሥጋው በመቃብር የዋለበት በመሆኑ እኛም እንደ ሐዋርያት የትንሣኤውን ብርሃን ሳናይ እህል አንቀምስም በማለት በጾም ስለምናሳልፈው ነው፡፡ ቄጠማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤው ሌሊት በራሳቸው ላይ ያሰሩታል፤ የቄጠማው አመጣጥና ምሥጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፤ ምድር በጥፋት ውኃ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሠረችው ቄጠማ ይዛ በመግባት ነው፡፡ ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ኃጢአት ጠፋ፤ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነፃነት ተሰበከና ታወጀ በማለት ካህናቱ ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበስሩበታል፡፡

በዚህች ቅድስት ቅዳሜ፤ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ፤ በዚህች ዕለት ከሥራው ሁሉ ያረፈባት ዕለት ናት፡፡ ጌታችን የተቀበረበትም ስፍራ ለተሰቀለበት ቦታ አቅራቢያ ነበር፤ ዮሴፍ ከኒቆዲሞስ ጋር ሆኖ ጌታችንን እንደፍጡር በሐዘንና በልቅሶ ሲገንዙት የጌታችን ዐይኖች ተገለጡ ‹‹እንደፍጡር ትገንዙኛላችሁን? በሉ እንዲህ እያላችሁ ገንዙኝ፤ ቅዱስ እግዚአብሔር፤ ቅዱስ ኃያል፤ ቅዱስ ሕያው›› አላቸው፡፡
ምንጭ ማሕበረ ቅዱሳን

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages