ስለ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ስናነሣ አፄ ኢያሱ አድያም ሰገድን ማዉሳታችን የግድ ይሆናል፡፡የደብረ ብርሃን ሥላሴን ታሪክ ከአፄ ኢያሱ አድያም ሰገድ ነጥሎ ማየቱ ታሪኩን ያደበዝዘዋል፡፡አፄ ፋሲል ጻድቁ ዮሐንስን፣
ጻድቁ ዮሐንስ ደግሞ ዛሬ ታሪኩን በመጠኑ የምናየዉን አድያም ሰገድ ኢያሱን ይወልዳል፡፡እንግዲህ አፄ ኢያሱ የደጋጎቹ ነገስታት ልጅ መሆኑ ነዉ፡፡
አፄ ዮሐንስ ልጃቸዉን ኢያሱን በትሕርምትና በሥርዓት በገዳም እንዲያድግ በመፈለጋቸዉ አፄ ሠርጸ ድንግል ባቀኑት በአርማጭሆ ወደሚገኘዉ ታላቁ ገዳም ደብረ ሞረና ላኩት፡፡በዚያም በገዳም ዉስጥ የሚሰጠዉን ትምህርት ሥርዓተ ቅዳሴ፣ዜማ ፣ዳዊት አጠናቀዉ ካወቁ በኋላ የገዳሙ ኃላፊዎች ይኼንን አስተምረነዋል ብለዉ ወደ አባታቸዉ ሰደዷቸዉ፡፡አፄ ዮሐንስም‹‹ ሌላስ ምን ተምሯል ብለዉ?››ይጠይቃሉ፡፡ሌላማ ምን እናስተምረዉ ይሏቸዋል የገዳሙ አለቆች፡፡‹‹እንጀራ መጋገር፣የአባቶችን እግርና ልብስ ማጠብ፣ሌላም በገዳሙ ያሉ መነኮሳት የሚፈጽሙትን ተግባር አስተምራችሁታል?››ብለዉ በድጋሚ ቢጠይቁ‹‹ይኼንንማ የጌታችን ልጅ እንዴት እናዛለን ሌላ አርድእት መቼ ታጣና››ይሏቸዋል፡፡ጻድቁ ንጉስም‹‹እንግዲያማ ትዕቢት ነዉ አስተምራችሁ የላካችሁልኝልኝ››ብለዉ መልሰዉ ሰደዷቸዉ፡፡
ከዚያም ኢያሱ በገዳም ያለዉን ሥርዓት አጠናቆ ተምሮ መጣ፡፡አባቱም በቤተ መንግስቱ ዉስጥ ኃላፊነት ይሰጡታል፡፡‹‹‹በገዳሙ የሚሰራዉን ሥራ ሁሉ ንፍሮ በሚበላባቸዉ ቀኖች ንፍሮ፣እንጀራ በሚበላባቸዉ ቀኖች እንጀራ እንዲሆን አድርገህ እንደ ገዳም ሥርዓት ይኼንን ቤተ መንግስት አስተዳድርልኝ›› ብለዉ አባቱ ጻድቁ ዮሐንስ ወራሴ መንግስት ኢያሱን ያዙታል፡፡ኢያሱም እንደታዘዘዉ ቤተ መንግስቱን በገዳም ሥርዓት ማስተዳደር ይጀምራል፡፡በ1674 ዓ.ም ኢያሱ የንግስና መንበሩን ከአባቱ የረከባል፡፡አሁን ኢያሱ ንጉስ ሁኗል፡፡አፄ ኢያሱ በነገሠ በአስራ ሁለተኛዉ ዓመቱ በ1686 ዓ.ም በጎንደር ከተማ የሚገኘዉን የደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተከለ፡፡በዚህ ዓመት መቃረቢያ ተሠርቶ ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ፡፡በበዓሉም ላይ አዲስ ተሹሞ የመጣዉ ግብፃዊ ጳጳስ አቡነ ማርቆስና ለሁለተኛ ጊዜ የተሾመዉ አጨጌ ጸጋ ክርስቶስ ተገኝተዋል፡፡በዓሉ በተከበረበት ዕለት አፄ ኢያሱ በትልቅ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ሻምላ መዝዞ ታቦቱን አጅቧል፡፡ወደ መቃረቢያዉ ሲደርስ ከፈረሱ ወርዶ ታቦቱን አክብሮ ከመቃረቢያዉ አገባዉ፡፡;እዚህ ላይ አፄ ኢያሱ ሥልጣነ ክህነት ይኑረዉ አይኑረዉ የተገኘ ማስረጃ ስለሌለ እንዲህ ነዉ ማለት አልተቻለም፡፡ክህነት ነበረዉ የሚሉ ግን ታላላቅ ሊቃዉንት ቅኔ አበርክተዋል፡፡ዓቃቤ ሰዓት ጥበበ ክርስቶስ መወድስና ኩልክሙ ምናኔ ዓለም የነበረዉ አባ ቀዉስጦስ ዕጣነ ሞገር ተቀኝተዋል፡፡ካእነዚህ ቅኔዎች አንዳቸዉም በዘመን ታሪክ ዉስጥ ተመዝግበዉ አልተገኙም፡፡አፄ ኢያሱ ታቦቱን አክብሮ ስለመግባቱ በዘመኑ ተገጠመ የተባለ የአማርኛ ግጥም ይህንን ይመስላል፡፡
ወዴት ሄዶ ኑሯል ሰሞነኛዉ ቄሱ
ታቦት ተሸከመ ዘዉድ ትቶ ኢያሱ
የተሸሸገዉን የ አባቱን ቅስና
ገለጠዉ ኢያሱ ታቦት አነሳና
አየነዉ ኢያሱን ደብረ ብርሃን ቁሞ
ሰዉነቱን ትቶ መልአክ ሆነ ደግሞ
ሥላሴን ቢሸከም ኢያሱ ገነነ
ከ አራቱ ኪሩቤል አምስተኛዉ ሆነ፡፡
በዚህ ደብር መጀመሪያ የተሸመዉ ቀዉስጦስ ነበረ፡፡የደብሩም የመጀመሪያ የማዕረግ ስም ሊቀ ካህናት ነበር፡፡ወዲያዉ ተለዉጦ መልአከ ብርሃን ሁኗል፡፡ቀዉስጦስ ያረፈዉ በ1716ዓ.ምበ85 ዓመት ዕድሜዉ ነበር፡፡እስከዚያዉ ድረስ በሹመቱ ቆይቶ እንደሆነ የተጻፈ መረጃ አልተገኝም፡፡የተቀበረዉ ግን እዚያዉ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤ/ክ ቅጽር ግቢ ዉስጥ መሆኑ ይታወቃል፡፡ታቦተ ህጉም በመቃረቢያዉ ዉስጥ ለሁለት ዓመት ቆይቶ የዋናዉ ሕንፃ ቤ/ክ ሥራ ጀመረ፡፡በ1688ዓ.ም የህንፃዉ ሥራ ሲጠናቀቅ ወደ አዲሱ ህንፃ ገብቷል፡፡ቤተ ክርስቲያኑ የተሰራበት እንጨት በጣም ትልልቅ ነበር፡፡በዚያን ጊዜ በምን መጓጓዣ እንዳመጡት ላስተዋለ ያስገርማል፡፡እንጨቱ የመጣዉ ግማሹ ከዘጌ ነዉ ሲል የተቀረዉ ደግሞ ከአርማጭሆ እንደሆነ ይነገራል፡፡የቀድሞዉ ህንፃ ክብ ሲሆን ሦስት መቅድስ ነበረዉ፡፡የበሩ ሳንቃዎች ሲከፈቱ አይታዩም ተሸከርክረዉ ወደ ዉስጥ ግድግዳዉ ነበር የሚገቡት፡፡
ስያሜ
አፄ ኢያሱ ቤተ ክርስቲያኑን ካሰሩ በኋላ ታቦተ ጽዮንን ወደ ጎንደር ለማስመጣት ወደ አክሱም ጉዞ አድርገዉ ነበር፡፡በተለያዩ ምክንያቶች ለማምጣት ሳይቻላቸዉ ቀርቷል፡፡በዚህም ቅር ተሰኝተዉ የአክሱም ጽዮን አካባቢ ሕዝብ ሦስት ቀን ግብር ከልክሏቸዋል፡፡ከዚያም አብረዋቸዉ የተጋበዙት አባ ስብሐት ለአብ የሚባሉ ሰዉ ሕዝቡ በርሃብ ሊያልቅ ሲል ታቦተ ጽዮንን ማምጣት ባይሳካልን ለምን ታቦተ ሥላሴን አናስገባም አሏቸዉ፡፡በዚሁ ተስማምተዉ ታቦተ ሥላሴ እንዲገባ አድርገዋል፡፡የአክሱም ታቦተ ጽዮንም ለደብረ ብርሃን ሥላሴ ግብር እንድታስገባ ግብር ጥለዉባት ተመልሰዋል፡፡
አፄ ኢያሱ ወደ ሸዋ ደብረ ብርሃን ተጉዘዉ ሊቃዉንቱንና ባላባቱን ጠይቀዉ ደብረ ብርሃን የሚለዉን ስም ለመሰየም ፈቃድ ሲያገኙ ብዙ ወቄት ወርቅ ሰጥተዉ ተመለሱ፡፡ይኼነን ስያሜ የመረጡበት ምክንያት ቦታዉ ብርሃን የወረደበት በመሆኑ በሁኔታዉ ተማርከዉ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በጠላት ወረራ ጊዜ
ድርቡሽ የጎንደር ከተማን ሲያቃጥል ሕዝቡ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በመሰባሰብ ጸሎተ ምህላ ያደርግ ነበር፡፡ሰማዩም በጉምና በጢስ ይሸፈናል፡፡ቤተ ክርስቲያኑ እንዲጠፋ የፈለጉ ሰዎችም‹‹ደብረ ብርሃን ስላሴ ካልተቃጠለና ካልጠፋ ጎንደር እንዳልጠፋች ይቆጠራል›.በማለት ለድርቡሾች መንገድ እየመሩ የመጡበት ጊዜ እንደነበር የ አካባቢዉ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ድርቡሾች በሩን ለመስበር የተቻላቸዉን ቢያደርጉም ሳይሆንላቸዉ ይቀራል፡፡እንጨት ሰብስበዉ አቃጥለዉ ለመግባት ሲሞክሩ በበሩ ላይ የተሳለዉ የሳንቃዉ ቅ/ሚካኤል ሥዕል ሰይፍ እንደመዘዘ ለህዝበ ክርስቲያኑ ሳይታይ ለእነርሱ ብቻ ይታያቸዋል፡፡በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ያለዉ ከዚህ ቦታ ነዉ እንዳትነኩ ብለዉ ተመልሰዉ ጥለዉት እንደሄዱ የሚነገር ታሪክ አለ፡፡በቤተ ክርስቲያኑ ያሉ አባቶች ይኼንን ሥዕል ቄስ ካልሆነ ዲያቆን እንኳን እንዳይነካ በማለት ተከብሮ በዓመት ዉስጥ ሁለት ጊዜ ብቻ ማለትም የሰኔ እና የኅዳር ሚካኤል ዕለት ብቻ እንዲገለጥ ወስነዋል፡፡
አፄ ኢያሱ የዘመነ መንግስቱ ፍጻሜ በተቃረበበት ወቅት የሥላሴን ቤተ ክርስቲያን በ1685 ዓ/ም በሥዕል ማሰራትና ማስጌጥ ጀምሮ ነበር፡፡ደብሩ በጊዜዉ ከከተማ ወጣ ያለ በመሆኑና በእግዚአብሔር ተአምር ከድርቡሽ ወረራ ከመቃጠል ድኗል፡፡ነገር ግን የዘመኑ ታሪክ እንደሚያወሳዉ በ1699 ዓ.ም መብረቅ ቤተ ክርስቲያኑን እንዳቃጠለዉ ይጠቀሳል፡፡ይህም በከፊል ይሁን በሙሉ የተብራራ ነገር የለዉም፡፡የደብሩ አስተዳዳሪ እንደሚገልጹትም አፄ ኢያሱ ያሰራዉ ቤተ ክርስቲያን ፈርሶ ልጅ ዳዊት/ሣልሳይ/እንደገና እንዳሰራዉም ይገልጻሉ፡፡በዉስጡ የተሳሉ ስዕሎችም በጊዜዉ የተሳሉ መሆናቸዉን ይገልጻሉ፡፡ሥዕሎቹን በጊዜዉ የነበረዉ ጸሐፌ ትዕዛዝ ሐዋርያተ ክርስቶስ ዓለም ከተፈጠረ አንስቶ ወደፊትም እንዲህ ያለ ሥዕል አይኖርም ሲል መስክሯል፡፡ሥዕሎቹም ትልልቅ ዓይኖች ክብ ፊት ያላቸዉ የጎንደር ሥዕሎች መታወቂያ ናቸዉ፡፡ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ የቤተ ክርስቲያኑን አካባቢ ምሽግ አድርጎት ነበር፡፡ጠላት በጎንደር ስድስት ዓመት ያክል ሲቀመጥ ቦምብ ከ አየር ላይ ቢወርድበትም ቤተ ክርስቲያኑ ከቃጠሎ መትረፍ ችሏል፡፡ጣሊያን ይህ ተ አምር ስላስገረመዉ የቤተ ክርስቲያኑን ክዳን ቀድሞ መምህር ገ/እግዚአብሔር በተባሉ የቤተ ክርስቲያኑ አለቃ/በኋላ አቡነ መርቆርዮስ በሐረር በነበሩ ጳጳስ ጠያቂነት በሸክላ አለበሰዉ፡፡በኋላ በ1957 ዓ.ም አፄ ኃይለ ሥላሴ ቆርቆሮ አስቀይረዉ ዙሪያዉን አጠናክረዉ አሠሩለት፡፡በዚህ ሁኔታ እስከ 1964 ዓ/ም ቆየ፡፡ባሕል ሚኒስተርም ጥንታዊነቱን መልቀቅ የለበትም በማለት በቆርቆሮዉ ላይ የቀድሞዉን ሣር አለበሰዉ፡፡
በቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ የ እንቁላል ግንብ በመባል የሚታወቁ ቤቶች አሉ፡፡በ አፄ ኢያሱ ዘመን በ12 ሐዋርያት አምሳያ በዚያዉ ዘወትር የሚቀመጡ ወደ ከተማ የማይወጡ መቁነን በዚያዉ እየተሰጣቸዉ ሰዓቱን እየከፋፈሉ የሚያጥኑ 12 መነኮሳት ይቀመጡበት ነበር፡፡በአሁኑ ሰዓት ብዙዎቹ እየፈራረሱ ይገኛሉ፡፡ቀድሞ በሕል ሚኒስተር ነበር ለጥገናዉ የሚንቀሳቀሰዉ፡፡አሁን ግን የ አካባዉ ነዋሪዎች ለጥገና የሚስፈልገዉን ገንዘብ በመሰባሰብ ኮሜቴ አዋቅረዉ የጥገና ሥራዉን እያንቀሳቀሱት ይገኛሉ፡፡
በደብረ ብርሃን ሥላሴ ቀድሞ 170 በላይ ካህናት ያገለግሉ ነበር ተብሎ ይገመታል፡፡ዛሬ ግን ከ25-30 ቢደርሱ ነዉ፡፡ደሞዛቸዉም ይህንን ያህል በቂ የሚባል አይደለም፡፡ቅዳሴ እሁድ፣በባዓላት ፣በዐብይ ጾም እሑድ፣በጾመ ፍልስታ የ እመቤታችን ክብረ በ ዓል ዕለት ይደርሳል፡፡በቤተ ክርስቲያኑ ያብነት ትምህርት/ቅኔ/ይሰጣል፡፡150-200የሚሆኑ ደቀ መዛሙርት ይማራሉ፡፡ቁጥራቸዉ ከዚህ የሚጨምርበትም የሚቀንስበትም ጊዜ አለ፡፡ይኼንን ጥንታዊና ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን የቀድሞ ይዘቱንና ቅርጹን ሳይለቅ እንደተጠበቀ ለትዉልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ምዕመናን አቅማቸዉ የፈቀደዉን ሁሉ ማድረግ ቢችሉ መልካም ነዉ፡፡ስለ ደብረ ብርሃን ስላሴ ያገኘነዉ መረጃ ይኼንን ይመስላል፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ ታሪክ ሲነሣ ስሙ ስለሚወሳዉ ስለ አፄ ኢያሱ የተነገረለትን ጠቅሰን ብናጠቃልስ፡፡አንድ ጊዜ አፄ ኢያሱ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ሄዶ ሳለ ክፍለ ዮሐንስ የተባለ ሊቅ ሲፀልይ አግኝቶ ከኪሱ ያገኘዉን ወርቅ አዉጥቶ ወረወረና ሊቁን ሳያስበዉ መታዉ፡፡በዚህ ጊዜ ክፍለ ዮሐንስ የሚከተለዉን ጉባኤ ቃና ወዲያዉ ሰጠ፡፡
በእስጢፋኖስ አእባን እመኅልቁ
ዘበጣኒ ኢያሱ በወርቁ/ድንጋዮች በእስጢፋኖስ ላይ ቢያልቁ ኢያሱ መታኝ በወርቁ/
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
It so wonder tanks
ReplyDelete