እግዚአብሔር እንዴት ይፈርዳል? - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, October 26, 2022

እግዚአብሔር እንዴት ይፈርዳል?

Posted ጥቅምት ፲፭ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
(ጊዜ ወስደው ያንብቡት አያጥር ነገር ታሪክ ሆኖ ነው)
አንድ ግብፃዊ መነኩሴ ለገዳሙ መርጃ የእጃቸው ሥራ የሆኑትን ቅርጫቶች ሊሸጡ ወደ እስክንድርያ ለመጓዝ በጠዋት ተነሡ፡፡
በመንገድ ላይ ታዲያ ትልቅ የቀብር ሥነ ሥርዓት ለማድረግ የሚጓዝ ሕዝብ ገጠማቸው፡፡ ሟቹ ዝነኛ አረማዊ ገዢ ሲሆን በዘመነ ሰማዕታት በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን የገደለ ሰው ነበር፡፡ አሁን ዕድሜ ጠግቦ ሞቶ ነው፡፡ ቀኑ ውብ ፀሐያማ ቀን ነበርና የሀገሩ ዜጎች በነቂስ ወጥተው ገዢያቸውን እየቀበሩ ነው፡፡
ይህንን ያዩት መነኩሴ ጉዳያቸውን ፈጽመው ወደ ገዳም ሲመለሱ አሳዛኝ ዜና ሰሙ፡፡ ለስድሳ ዓመታት በበረሃ በብሕትውና ቅጠልና የበረሃ ፍሬ ብቻ እየበላ የኖረ ባሕታዊ በዚያች ዕለት በጅብ ተበልቶ ሞቶ ነበር፡፡
መነኩሴው እጅግ ጥልቅ ኀዘን ውስጥ ሆነው እንዲህ ሲሉ አሰቡ ፦
‘በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን የገደለው አረማዊ ሰው በታላቅ ክብር ታጅቦ ሲቀበር ሕይወቱን ሙሉ በጾምና በጸሎት ፈጣሪውን ያገለገለው ባሕታዊ በጅብ ተበልቶ የተዋረደ አሟሟት ሞተ፡፡ይህ እንዴት ዓይነት ፍርድ ነው? እግዚአብሔር ከመልካምነቱ ሁሉ ጋር ኢፍትሐዊ ነገሮች ሲሆኑ ዝም ብሎ ይፈቅዳል፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ሰዎች የፈጣሪን መኖር ይጠራጠራሉ፡፡ እኔም ፍርዱን እንዲገልጽልኝ መጸለይ ይኖርብኛል’ አሉ፡፡
ከዚያች ቀን ጀምሮ መላልሰው ወደ ፈጣሪ ‘’ፍርድህን ግለጽልኝ’ ብለው ደጋግመው ጸለዩ፡፡ ብዙም ሳይቆይ እግዚአብሔር ፍርዱን እንዲህ ገለጠላቸው፡፡
ከሳምንታት በኋላ እንደተለመደው ወደ እስክንድርያ የሦስት ቀን ጉዞ ሊሔዱና ቅርጫታቸውን ሊሸጡ ተነሡ፡፡መንገዱን እንደጀመሩ ድንገት አንድ ወጣት መነኩሴ ወደ እርሳቸው ሲመጣ ተመለከቱ፡፡
‘’አባቴ ይባርኩኝ’
‘እግዚአብሔር ይባርክህ ልጄ’
‘አባቴ ወዴት ይሔዳሉ?’ አለ ወጣቱ መነኩሴ
‘ወደ እስክንድርያ ቅርጫቴን ልሸጥ እየሔድኩ ነው’ አሉት
‘ጥሩ አጋጣሚ ነው አባ እኔም ወደዛ እየሔድኩ ነው’ አለ በትሕትና
‘ጎሽ አብረን እንጓዛለና’ አሉ አባ፡፡ ወጣቱ መነኩሴ ከእጃቸው ሸክማቸውን ተቀበለ፡፡ ጥቂት እንደሔዱ እንዲህ አላቸው፡፡
‘አባ ያው እንደሚያውቁት እንደ መነኮሳት ሥርዓት ጉዞ ስንጓዝ በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር አለብን አይደል?’’ አላቸው፡፡
‘ልክ ነው ልጄ’ አሉት
‘እንግዲያውስ ለሦስት ቀን አብረን ስንጓዝ እስክንድርያ እስክንደርስ ድረስ አንዲትም ቃል አንነጋገር ፤ ምናልባት በሦስቱ ቀን ጉዞአችን ለማየት የሚከብድ ነገር እንኳን ሳደርግ ቢያዩኝ ላይናገሩኝ ላይፈርዱብኝና የአርምሞ ቃልኪዳንዎን ላያፈርሱ ቃል ይግቡልኝ’ አላቸው፡፡
አባ እየተገረሙ ‘እሺ በሕያው አምላክ እምላለሁ ልጄ አንዲትም ቃል አልተነፍስም’ አሉት፡፡
ሁለቱ አባቶች በጠዋቱ የአርምሞ ጉዞአቸውን ጀመሩ፡፡ ቀትር ላይ ወደ አንዲት መንደር ደረሱ፡፡
ሁለት ወጣቶች እነዚህን መነኮሳት አዩአቸው፡፡ ከሁለቱ አንዱ ‘ቅዱሳን አባቶች’ እያለ ወደ እነርሱ ሮጠ ‘ቅዱሳን አባቶቼ ፀሐዩ እስኪበርድ ድረስ እባካችሁን እኛ ቤት አረፍ በሉ’ አላቸው፡፡ ፀሐይዋ እየከረረች ስትመጣ በበረሃማዋ ግብፅ ጉዞ በጠዋትና ማታ እንጂ በቀትር ስለማይታሰብ ጉዞአቸውን ማቋረጥ ነበረባቸው፡፡ ስለዚህ ሁለቱ ወጣቶች እነዚህን መነኮሳት በክብር ተቀብለው ከቤታቸው አስገቧቸው፡፡እግራቸውን አጠቧቸው፡፡ በቤታቸው ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረ የከበረ እጅግ ውድ የብር ሰሐን ላይ ምግብ አቀረቡላቸው፡፡ መነኮሳቱ በዝምታ ተመገቡ፡፡ ከዚያም ትንሽ አረፍ የሚሉበት ክፍል ተሠጣቸው፡፡
ትንሽ እንደቆዩ ወጣቱ መነኩሴ ቀስ ብሎ ወደ ምግብ ማብሰያው ክፍል ገብቶ ይበሉበትን ውድ የብር ሳህን በልብሱ ደብቆ ይዞት መጣና አባን ጠቅሶ ጠራቸው፡፡ ተሰናብተው ከወጡ በኋላ አባ በቀሚሱ ውስጥ የደበቀውን የብር ሳህን ሲያዩ ደነገጡ፡፡ መናገር ባይችሉም በልባቸው እንዲህ አሉ ፦
‘እነዚያ ደግ ወጣቶች በክብር ተቀበሉን ፤ እግራችንን አጥበው መገቡን፡፡ እውነት ለውለታቸው ምላሹ ውዱን ንብረታቸውን መስረቅ ነው?’’ ብለው አዘኑ፡፡
ጥቂት እንደተጓዙ የመስኖ ውኃ ወደተከማቸበት አንድ ድልድይ ጋር ደረሱ፡፡ ውኃውን ሲሻገሩ ታዲያ ወጣቱ መነኩሴ በብር ሳህኑ ላይ ካማተበበት በኋላ ወደ ወንዙ ወረወረው፡፡
አባ እንዲህ ብለው አልጎመጎሙ ፦
‘’እንዴት ያለ ነገር ነው? ሳህኑን የሰረቀው ሊወረውረው ነው? እዚያው አይተውላቸውም ነበር?’’ አሉ አርምሞአቸውን ሊያፈርሱ አይችሉምና ዝም አሉ፡፡
ሲመሽ ወደ አንድ ወጣት ባልና ሚስት ቤት ደረሱ፡፡ እንደ ቀኖቹ ወጣቶች እነዚህም በክብር እግር አጥበው አስተናገዷቸውና ማረፊያ ሠጧቸው፡፡ ባልና ሚስቱ የሁለት ወር ሕፃን ልጅ ነበራቸው፡፡ በጠዋት ሲነሡ ወላጆች ሳይነሡ ወጣቱ መነኩሴ ቀስ ብሎ ሔዶ የተኛውን ሕፃን ገደለው፡፡ አባ ሊያስጥሉት ቢሉም አልቻሉም፡፡ እየጎተተ ይዞአቸው ወጣ፡፡ ‘ጌታ ሆይ ምን ዓይነት ርጉም ነው ንጹሑን ሕፃን ገደለው እኮ’ እያሉ እንባቸው ወረደ፡፡ ምንም እንኳን አንጀታቸው በኀዘን ቢኮማተርም በመሓላ የገቡበትን አርምሞ አፍርሰው ከግዝት ላለመግባት አንዲት ቃል ግን አልተናገሩም፡፡
በቀጣዩ ቀን ሁለቱ መነኮሳት ወደ አንድ መጠጥ ቤት ደጅ ደረሱ ፤ የጭፈራው ድምፅ ከሩቅ ይሰማል ፤ ሰካራሞቹ መነኮሳቱን ሲያዩ ‘ቅዱሳን’ እያሉ ተሳለቁ፡፡ በሰካራም አንደበት የሚናገረው ዲያቢሎስ ነው ብለው ዝም አሉ፡፡
ወጣቱ መነኩሴ ግን ወደ መጠጥ ቤቱ አቅጣጫ በግንባሩ ተደፋና ሦስት ጊዜ ሰግዶ ተሳለመው፡፡
ጥቂት እንደሔዱ አንድ ያረጀ ፤ መስቀሉ ከጉልላቱ የተነቀለ በርና መስኮት የሌለው ቤተ ክርስቲያን አዩ
ወጣቱ መነኩሴ ድንጋዮች ለቀመና አማተበባቸው ወደ ፈረሰው መቅደስም ወረወረው
አባ ይሄን ጊዜ ፦ መጠጥ ቤቱን ተደፍቶ ተሳለመ ፤ ወደ ቤተ መቅደሱ ድንጋይ ወረወረ ! ብለው በዝምታ ተንጨረጨሩ ::
አሁን ሦስተኛው ቀን ሞላ በጠዋቱ ወደ አንድ በሸንበቆ የተሠራ ቤት ደረሱ እናታቸው የሞተችባቸውና በአጎታቸው እርዳታ ብቻ የሚኖሩ አምስት ሕፃናት ተቀምጠው ያለቅሳሉ፡፡ አባ በርኅራኄ ለሕፃናቱ ምግብ ሠጧቸው፡፡ እሳቸው ከሕፃናቱ ጋር ሲነጋገሩ ወጣቱ መነኩሴ ደሞ የሸንበቆውን ቤት በእሳት እያያያዘ ነበር፡፡ ሕፃናቱ ከሚነደው ቤት ሮጠው አመለጡ፡፡
‘ይህን ነፍሰ ገዳይ እስከመቼ እታገሰዋለሁ’ ሲሉ የቆዩት አባ እስክንድርያ ደርሰዋልና በምሬት መናገር ጀመሩ
‘’እስቲ ንገረኝ ከዚህ በኋላ ዝም ልልህ አልችልም፡፡ መልስልኝ አንተ ሰው ነው ወይስ ሰይጣን ነህ?’
‘ምነው አባ ምን አጠፋሁ?’ አለ መነኩሴው
‘በዚህ ሦስት ቀን ውስጥ ምን ያላደረግከው ነገር አለ? በበረሃ አክብረው የተቀበሉንን ሰዎች የብር ሳህን ሰርቀህ ወንዝ ውስጥ አልጨመርህም? እነርሱም መነኩሳት በቤታችን ተቀብለን ሰርቀውን ሄዱ እያሉ ይሆናል’
መነኩሴው መለሰ :- ‘አባ ትልቅ ነገር ነው እኮ ነው ያደረግሁላቸው፡፡ ያቀረቡልን የብር ሳህን ቅድም አያታቸው ከጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን የሰረቀው ጻህል /የቅዱስ ቁርባን ማቅረቢያ/ ነበር፡፡ መላው ቤተሰብ ይህንን ሳያውቅ በዚያ ቤት ለብዙ ዘመን ሲቀባበሉት ነበር፡፡በላዩ ላይም በላቲን ቋንቋ ይህ ጻህል ለቅዱስ ኒቆላዎስ ቤተ ክርስቲያን የተሠጠ የሚል ጽሑፍ አለበት፡፡ በዚህ ምክንያት ያንን ቅዱስ ንዋይ የሚጠቀሙ ሁሉ እስካልተመለሰ ድረስ በእግዚአብሔር ላይ ድፍረት ይሆንባቸዋል፡፡ የሞቱት ወላጆቻቸውም በዚያ ቅዱስ ንዋይ የተነሣ ነፍሳቸው ትታወካለች፡፡ እነዚያም ወጣቶች በጻሕሉ እኛን በማስተናገዳቸው ነፍሳቸው እንዳትጎዳ አዘንኩላቸው፡፡ ስለዚህም ሰረቅኋቸው፡፡ የሰረቅሁት ፈልጌው አይደለምና ውኃው ውስጥ ወረወርሁት፡፡
በማግሥቱ የደብሩ ዘበኛ ሊታጠብ ወደ ውኃው ይመጣል፡፡ በውኃው ውስጥም ያገኘዋል፡፡ የላቲን ቋንቋ ስለሚያውቅ የተጻፈውን ያነበዋል፡፡ ወስዶም ለካህኑ ይሠጠዋል፡፡ ፃህሉ ከብሮ ድጋሚ ሲቀደስበት የሞቱትም ያርፋሉ የቆሙትም ከጥፋት ይድናሉ፡፡ ’ አላቸው፡፡
አባ ተደነቁ ፤ ‘እሺ ሕፃኑንስ የገደልከው ለመልካም ብለህ ነው?’
‘አባ የእግዚአብሔርን ፍርድ አይመዝኑ ፤ ሕፃኑ የተፀነሰው በኃጢአት ነው ፤ ለወደፊት ደግሞ እጅግ ጨካኝ ወንጀለኛ ሆኖ ወላጆቹን የሚገድል ብዙዎችን የሚያሰቃይ ነው፡፡ ስለዚህ ልጁን በመግደሌ ሦስት መልካም ነገሮች አደረግሁ፡፡ ሕፃኑ ከንጽሕናው ጋር ወደ ሰማይ እንዲሔድ አደረግሁት ፤ ወላጆቹንም በልጃቸው እጅ ከመሞት አዳንኋቸው፡፡በዚህ ልጅ ኀዘን ምክንያት ወላጆቹም ልባቸው በመሰበሩ የቀደመ ኃጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል’
‘እሺ መጠጥ ቤቱ ደጃፍ ላይ የሰገድከው ምን ሆነህ ነው?’
‘ሦስት ሰዎች በዚያ መጠጥ ቤት ውስጥ ሆነው የፈረሰውን የከተማችንን ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንሥራ እያሉ እየተጨነቁ ይነጋገሩ ነበር፡፡ ምንም እንኳን የተሰበሰቡበት ቦታ መጥፎ ቢሆንም በልባቸው ያለው ሃሳብ ቅን ስለሆነ እግዚአብሔር እንዲረዳቸው ወድቄ ሰግጄ ለመንሁት’’
‘ታዲያ ወደ ፈረሰው ቤተ መቅደስ ድንጋይ ለምን ወረወርህ?’
‘በፈረሰው መቅደስ ላይ እየተሳለቁ አጋንንት ሲጨፍሩ አየሁ፡፡ በመስቀል ምልክት አማትቤ ድንጋይ ወረወርሁ ፤ በዚህም ምክንያት አጋንንቱ በንነው ሸሹ’ አለ መነኩሴው፡፡
አባ ቀጠሉ ‘የእነዛን የሙት ልጅ የሆኑ ሕፃናት ቤትስ ለምን አቃጠልከው?’
‘’እነዚያ ሕፃናት እንደሚያውቁት ወላጆቻቸው ሞተውባቸዋል ፤ የቀራቸው ንብረትም ቤቱ ብቻ ነው፡፡ ቅድመ አያታቸው የቀብሩት እጅግ ብዙ ሀብት ግን ከዚያ ቤት በታች አለ፡፡ ከቃጠሎው በኋላ በቀረው ክፍል ለማደር ልጆቹ ሲገቡ የተቀበረውን ሀብት ያዩታል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ጠባቂነት ለሚያገለግል አጎታቸውም ሔደው ይነግሩታል፡፡ በረሃብ መሞታቸው ቀርቶ በጥሩ ሁኔታ ያድጋሉ’’ አለ መነኩሴው፡፡
አባ ምንም እንኳን ነገሩ ቢያስደንቃቸውም አንድ ወጣት መነኩሴ ይህንን ሁሉ እንዴት ሊያውቅ ይችላል የሚል ጥርጣሬ አደረባቸውና ‘አንተ ማን ነህ?’ አሉት፡፡
‘የእኔ ማንነት ይቆይና እርስዎ በዚህ ሰሞን መላልሰው ፈጣሪን የጠየቁት ነገር ካለ ይንገሩኝ’ አላቸው
‘እኔማ እግዚአብሔር ሆይ ፍርድህን አሳየኝ ብዬ በምድር ላይ ስለሚደረጉ ኢፍትሐዊ ነገሮች ጠይቄው ነበር’ አሉት፡፡
‘እግዚአብሔር ‘ሰማይ ከምድር እንደሚርቅ መንገዴ ከመንገዳችሁ ሃሳቤም ከሃሳባችሁ የራቀ ነው’ ብሏልና ፍርዱ አይመረመርም፡፡ ለመላእክት እንኳን ያልተገለጸውን የእግዚአብሔርን ፍርድ እንዴት እርስዎ በሰው አቅም ሊመረምሩ ይፈልጋሉ፡፡ ጸሎትዎን ሰምቶ እግዚአብሔር ያዩትን ሁሉ እንዳደርግና ፍርዱን እንዳሳይዎት ላከኝ’’ አላቸው፡፡
ቅዱስ ዑርኤል ለዕዝራ እንዲህ አለው፦
‘የምትፈርስ የምበሰብስ አንተ የማይፈርስ የማይበሰብስ የሕያው እግዚአብሔርን ፍርዱን ልትመረምር አትችልም’
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሚያዝያ 24/ 2012 ዓ ም

 

 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages