ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 21 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 21

 ታኅሣሥ ሃያ አንድ ይህችን ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን #ኖላዊ_ሔር ብላ ታከብራለች፣ #የሐዋርያው_ቅዱስ_በርናባስ ዕረፍቱ ነው::ታኅሣሥ ሃያ አንድ ይህችን ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን "ኖላዊ ሔር" ብላ ታከብራለች:: ይሕንንም ለሳምንት ያህል ታዘክራለች:: መሠረታዊ መነሻዋም (ዮሐ. 10፥1) ነው:: "ኖላዊ" ማለት በቁሙ "እረኛ" ማለት ሲሆን "ሔር" ደግሞ "ቸር፣ርሕሩሕ፣አዛኝ" እንደ ማለት ነው:: ገጥመን ብንተረጉመው ደግሞ "ቸር እረኛ" የሚል ትርጉምን ይሰጠናል:: ከአባታችን አዳም ስህተት በኋላ ተፈጥረው ከነበሩ ችግሮች አንዱ ቸር እረኛ ማጣት ነው። እግዚአብሔር አዳምን ፈጥሮ: ቸር እረኛ ሆኖ በገነት አሰማርቶት ነበር።
ኤዶም ገነት የለመለመች: ፈሳሾች የሞሉባት መልካም መስክ ናትና:: አባታችን ቅዱስ አዳም ደግሞ እንደ አቅሙ የጸጋ እረኝነት ተሰጥቶት ነበር:: ድቀት ካገኘው በሁዋላ ግን ከነፍስ እረኛው ጋር ተጣልቶ ከመልካሟ መስክ ገነት ወጣ:: እርሷንና የነፍሱን እረኛ ሲሻም አለቀሰ:: ተስፋ ድኅነት ሲሰጠውም ለልጆቹ ነገራቸው:: ከዚያም በመንጋው ላይ በአዳም ሴት ተተካ:: ከሴት ኄኖስ፣ ከኄኖስ: ቃይናን . . . እያለ ከኖኅ ደረሰ።
ከኖኅም በሴም ከአብርሃም: ከአብርሃምም በይስሐቅና በያዕቆብ ወርዶ ከሙሴ ደረሰ:: ከሙሴም በኢያሱ አልፎ ከነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ደረሰ:: እነዚህ ሁሉ እረኞች ምንም እንኩዋ ለእግዚአብሔር ሕዝብ በትጋት ቢሠሩም ሕዝቡን ከሲዖል ማዳን አልቻሉም:: ከሲዖል የሚያድን የነፍስ እረኛ ነውና ያን ጊዜ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት የራሱን: የአባቶቹንና የልጆቹን ጩኸት ባንድ አድርጐ ጮኸላቸው:: "ኖላዊሆሙ ለእሥራኤል አጽምዕ - የእሥራኤል እረኛ ሆይ ስማን!" አለ:: (መዝ. 79:1)
ጩኸቱም ቅድመ እግዚአብሔር ደረሰ:: ይህንን የሰማ ጌታም በጊዜው ከድንግል ማርያም ተወለደ:: በየጥቂቱ አድጐ ቸር እረኝነቱን ገለጠ:: መድኃኒታችን እንዳስተማረን እርሱ ቸር እረኛ ነው:: ከእርሱ በፊት የተነሱት ቴዎዳስ ዘግብጽና ይሁዳ ዘገሊላ (ሐዋ. 5:36, ዮሐ. 10:8) ሐሰተኛ እረኞች ነበሩ:: እርሱ ግን እውነተኛው የበጐች በር ነውና (ዮሐ. 10:7) በእርሱ የሚገቡ ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛሉ:: እርሱ እውነተኛ እረኛ ነውና (ዮሐ. 10:11) ለመንጋው ራሱን አሳልፎ ይሰጣል:: በእሥራኤል ባሕል እረኞች ከፊት: መንጋው (በጐቹ) ከሁዋላ ሆነው ይሔዳሉና ገዳይ ቢመጣ መጀመሪያ የሚገድለው እረኛውን ነው::
መድኃኒታችን ክርስቶስ በሞቱ ሕይወትን: በመራቆቱ የጸጋ ልብስን: በውርደቱ ክብርን: በድካሙ ኃይልን ይሰጠን ዘንድ ስለ እኛ ራሱን አሳልፎ ሰጠ:: የማይሞት ንጉሥ ስለ መንጋው ሞተ:: ሰማይን ከነግሡ ምድርንም ከነልብሱ የፈጠረ ጌታ (ዘፍ. 1:1, ዮሐ. 1:2) ስለ በጐቹ ይህንን ሁሉ ታግሦ ከሲዖል አዳነን:: በሚያርግ ጊዜም በእርሱ ፈንታ ባለ ሙሉ ስልጣን እረኞችን: ሐዋርያትን (ዮሐ. 21:15) ሊቃነ ዻዻሳትን (ሐዋ. 20:28) ካህናትን (ማቴ. 18:18) ሾመልን:: እነርሱን እረኞች አሰኝቶ እርሱ "ሊቀ ኖሎት-የእረኞች አለቃ" ተባለ:: እነርሱም እስከ ዓለም ፍጻም የክርስቶስን መንጋ ሊጠብቁ ስልጣኑም ኃላፊነቱም አለባቸው:: (ማቴ. 28:19)
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ዕለት ሐዋርያው ቅዱስ በርናባስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ይህም ቅዱስ ሐዋርያ ከሊዊ ነገድ የሆነ አገሩ ቆጵሮስ ነው የቀድሞ ስሙ ዮሴፍ ነው ክብር ይግባውና ጌታችን ከመከራው በፊት ይሰብኩ ዘንድ ከላካቸው ከሰባ ሁለት አርድእት ጋር መረጠው ስሙንም በርናባስ ብሎ ጠራው። ከጌታ ዕርገትም በኋላ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ እርሱም ከሐዋርያት ጋር የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ተቀብሎ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አስተማረ። የእርሻ ቦታ ነበረውና ሽጦ ዋጋውን አምጥቶ ከሐዋርያት እግር በታች አኖረው።
ቅዱስ ጳውሎስም በጌታችን አምኖ ወደ ሐዋርያት በመጣ ጊዜ ክብር ይግባውና ለክርስቶስ እርሱ ደቀ መዝሙሩ እንደሆነ ሐዋርያት አላመኑትም ነበር። ይህ በርናባስ ጌታችን በመንገድ እንደ ተገለጸለትና እንደአነጋገረው እርሱም በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በደማስቆ እንደ አስተማረ ነገራቸው። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔርን ሥራ ሲሠሩ ሲጾሙ ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ "ሳውልና በርናባስን እኔ እነርሱን ለመረጥኩት ሥራ ለዩልኝ" አላቸው።
ከዚህም በኋላ ጹመው ጸልየው እጆቻቸውን በራሳቸው ላይ ጭነው ሾሟቸው። ከመንፈስ ቅዱስም ተሹመው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ ከዚያም ወደ ቆጵሮስ ሔዱ የእግዚአብሔርንም ቃል በአገሩ ሁሉ አስተማሩ። ልስጥራን በተባለ አገርም ልምሾ የነበረውን ሰው በአዳኑት ጊዜ የልስጥራን ሰዎች መሥዋዕትን ሊሠዉላቸው ወደዱ። ሐዋርያት ቅዱስ ጳውሎስና በርናባስም በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀድው ወደ ሕዝቡ ሔዱ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንዲህ አሏቸው "እናንት ሰዎች ይህ ነገር ምንድን ነው እኛማ እንደናንተ የምንሞት ሰዎች አይደለንምን ይህን ከንቱ ነገር ትታችሁ ሰማይና ምድርን ባሕርንም በውስጣቸው ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደሕያው እግዚአብሔር ትመለሱ ዘንድ እናስተምራችኋለን" አሏቸው እንዲህም ብለው መሠዋትን በጭንቅ አስተዋቸው።
ከዚያም ብዙ አገሮችን ከአስተማሩ በኋላ ቅዱስ በርናባስ ከቅዱስ ጳውሎስ ተለይቶ ቅዱስ ማርቆስን ይዞ ወደ ቆጵሮስ ሔደ በዚያም አስተማረ ብዙዎችን ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ማመን መለሳቸውና የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው።
በቆጵሮስ አገር የሚኖሩ አይሁድም ቀኑበት በመኳንንትም ዘንድ ወነጀሉት በእግር ብረትም አሥረው ጽኑ ግርፋትን ገረፉት ከዚህም በኋላ በደንጊያ ወገሩት ዳግመኛም ወስደው ከእሳት ጨመሩት ምስክርነቱንም ፈጸመ። ቅዱስ ማርቆስም ከርሱ ጋር አለ ግን እግዚአብሔር ጠብቆ አተረፈው። እርሱም ቅዱስ በርናባስን ከእሳት ውስጥ አወጣው ሥጋውንም እሳት ከቶ አልነካውም በአማሩ ልብሶችም ገንዘውና ተሸክሞ ወስዶ ከቆጵሮስ ከተማ ውጭ በዋሻ ውስጥ አኖረው።
የመድኃኔዓለም ቸርነቱ የድንግል እናቱ ምልጃዋ ከእኛ ጋር ይሁን፤ በሐዋርያ ቅዱስ በርናባስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages