አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ዐሥራ አምስት በዚህች ቀን የሶርያ ሰው ቅዱስ አባት ኤፍሬም አረፈ፣ ቅዱሳን ሐዋርያነት ጴጥሮስና ጳውሎስ በንጉሥ ጰራግሞስ ላይ ተአምራትን አደረጉ፣ የዋልድባው አቡነ ተስፋ ሐዋርያነት የተሰወሩበት ዕለት ነው፡፡
የሶርያ ሰው ቅዱስ አባት ኤፍሬም (አፈ በረከት)
ሐምሌ ዐሥራ አምስት በዚህች ቀን የሶርያ ሰው ቅዱስ አባት ኤፍሬም አረፈ። ይህም ቅዱስ ከዋክብትን ከሚያመልኩ ሰዎች ሀገር ነው አባቱም ክብር ይግባውና የክርስቶስን አምልኮት የሚጠላ የጣዖት ካህን ነበር።
በዚያን ጊዜም የእግዚአብሔር ቸርነት ቀሰቀሰችውና አነሳሥታ የንጽቢን ጳጳስ ወደሆነው ወደ አባ ያዕቆብ ወሰደችው እርሱም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተምሮ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቀው በእርሱም ዘንድ በጾምና በጸሎት ያለማቋረጥ እየተጋደለ ለብዙ ዘመናት ኖረ።
የመንፈስ ቅዱስም ጸጋ አደረበት አሕዛብን ተከራክሮ ይረታቸው ነበር። ኒቅያ በሚባል ከተማ የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት አባቶች ኤጲስቆጶሳት ጉባኤ በተደረገ ጊዜ ይህ ቅዱስ ኤፍሬም ከመምህሩ ከአባ ያዕቆብ ጋራ ወደ ቅዱሳን ጉባኤው ሔደ።
ከሀዲው አርዮስንም አውግዘው ከለዩት በኋላ ይህ ቅዱስ ኤፍሬም በዚያች ሌሊት ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ አየ ከዚህ ራእይም የተነሣ አደነቀ ይገልጽለትም ዘንድ ወደ ጌታ ጸለየ ይህ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ባስልዮስ ነው የሚል ቃል ከሰማይ ወደርሱ መጣ።
ቅዱስ ኤፍሬምም ያየው ዘንድ ወድዶ ወደ ቂሣርያ ሀገር ተጓዘ በደረሰም ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ በማእዘኑ በኩል ቆመ ቅዱስ ባስልዮስንም ወንጌልን ሊያነብ በወጣ ጊዜ ዋጋው ብዙ የሆነ ከወርቅ የተሠራ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ አየው። ሦስት ምልክቶችንም እሰኪያይ ድረስ ተጠራጠረ ምልክቶችም እኒህ ናቸው ነጭ ርግብ መጥታ በራሱ ላይ አረፈች ሁለተኛም በልብሱ ላይ የሚያርፉ ተዋሐስያን ይቃጠሉና ይረግፉ ነበር። ሦስተኛም ከአፉ የእሳት ነበልባል ወጥቶ በምእመናን ላይ ያድር ነበር።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ባስልዮስ ቅዱስ ኤፍሬምን በስሙ ጠራውና እርስ በርሳቸው ሰላምታ ተለዋወጡ። በአስተርጓሚ ይነጋገሩ ጀመሩ። የየራሳቸውንም ቋንቋ ይገልጽላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንዲጸልይ ቅዱስ ኤፍሬም ቅዱስ ባስልዮስን ለመነው። በጸለየ ጊዜም ተገልጾላቸው ያለ አስተርጓሚ ተነጋገሩ።
ከዚህ በኋላም ቅዱስ ኤፍሬምን ዲቁና ሾመው ከጥቂት ወራትም በኋላ ቅስና ሾመው ከእርሱም ብዙ ትሩፋቶች ተገለጡ በመንፈሳዊ ተጋድሎ ሁሉ ተጋደለ። አንዲት በወገን የከበረች ባለ ጸጋ ሴት ነበረች ራስዋንም ለካህን ለማስመርመር ታፍር ነበር ከታናሽነቷ ጀምራ የሠራችውን ኃጢአቷን ሁሉ ጽፋ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ አመጣች። አባቴ ሆይ በዚህ ክርታስ ውስጥ ያሉት ኃጢአቶቼ ይደመሰሱ ዘንድ ተናገር ብላ ለመነችው እርሱም እንዳልሺው ይሁንልሽ አላት።
እርሷም ክርታሱን በገለጠች ጊዜ ከአንዲት ኃጢአትዋ በቀር ኃጢአቷ ሁሉ ተደምስሶ አገኘች ያችም ኃጢአት አስጨናቂና ታላቅ ኃጢአት ነበረች።
ባገኘቻትም ጊዜ ያቺን የቀረች ኃጢአቷን ያጠፋላት ዘንድ አልቅሳ ለመነችው እርሱም ወደ ቅዱስ ኤፍሬም ሒጂ እርሱ ይህችን የቀረች ኃጢአትሽን ያስተሠርይልሻል አላት። ወዲያውም ወደ ቅዱስ ኤፍሬም ሔዳ ከርሷ የሆነውን ሁሉ ነገረችው። እርሱም እንዲህ አላት ፈጥነሽ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ሒጂ ግን ሙቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወስዱት ታገኝዋለሽ ሳትጠራጠሪም ይህችን ክርታስ በላዩ ጣይ ይደመሰስልሻል።
ያቺም ሴት ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ተመለሰች ሙቶ ተሸክመው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወስዱትም አገኘችው። ያንንም ክርታስ በአስክሬኑ ላይ ጣለችው ወዲያውኑም ተደመሰሰላት። ይህም ቅዱስ ኤፍሬም ብዙ ተአምራቶችን አድርጓል በዘመኑም ዲዳን የሚባል አንድ ከሀዲ ተነሣ ይህም አባት ኤፍሬም ተከራክሮ ረታው።
እጅግም ብዙ የሆኑ ዐሥራ አራት ሽህ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ ከእርሳቸውም ውስጥ አምላክን የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ውዳሴዋ ነው። አቤቱ የጸጋህን ማዕበል ግታልኝ እስከሚል ድረስ ድርሳናትን ደርሶአል። መልካም የሆነ ገድሉንም በፈጸመ ጊዜ ወደ ወደደው ወደ እግዚአብሔር ሔደ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱሳን ሐዋርያነት ጴጥሮስና ጳውሎስ
በዚህችም ቀን ለአባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ጴጥሮስና ጳውሎስ በንጉሥ ጰራግሞስ ላይ ተአምራትን አደረጉ። አምላክን ከወለደች ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍልሰት በኋላ ደመና ነጥቆ ወሰዳቸውና በቤተ መንግሥት መካከል አወረዳቸው ንጉሥ ጰራግሞስም በአያቸው ጊዜ ደንግጦ እናንተ ምንድን ናችሁ አላቸው። እነርሱም መንግሥታትን ሁሉ የሚያጠፋ የሚሰሙትንም ማዳን የሚችል የሕያው እግዚአብሔር ልጅ የክርስቶስ ባሮች ነን አሉት።
ንጉሡም ነገራችሁ ትክክለኛ መሆኑን እንዴት ማወቅ እችላለሁ አላቸው። ከዚህ በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ያደረጋቸውን ድንቆችንና ተአምራቶቹን ነገሩት።
የቀኝ ዐይኗን ወፍ ያወጣው አንዲት ልጅ አለችኝ እርሷን ካዳናችኋት በአምላካችሁ አምናለሁ አላቸው ልጅህን ወደ እኛ አምጣ አሉትና ልጁን ወደ እነርሱ አመጣት። ሐዋርያትም ወደ እግዚአብሔር ጸልየው እጆቻቸውን በዐይኗ ላይ አኖሩ። ያን ጊዜም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ዳነች። ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ አይተው ከሐዋርያት እግር በታች ሰገዱ ክብር ይግባውና በጌታችንም አመኑ።
ከዚህም በኋላ ሐዋርያት ክብር ይግባውና ጌታችን እንዳዘዛቸው ወደ ሀገረ ፊልጶስ ሔዱ። ሰይጣንም በእንዶር ንጉሥ ተመስሎ አጋንንትን በጭፍራ አምሳል አስከትሎ ወደ ንጉሥ ጰራግሞስ መጣ በሥራያቸው አገርን ሳያጠፉ እኒህን ሁለቱን ሥራየኞች ፈጥነህ የማታጠፋቸው ለምንድነው አለው።
የንጉሥ ጰራግሞስም ልብ ወደ ክህደት ተመለሰ። ሐዋርያትንም ያመጧቸው ዘንድ ዐሥር ሺህ ጭፋሮችንና ሁለት መቶ ፈረሰኞችን ላከ ጭፍሮችም ሔደው ከተማዋን ከበቧት የከተማዋ ሰዎችም ደንግጠው ለሐዋርያት ነገሩዋቸው። ሐዋርያትም ከከተማው ወጥተው በጭፍሮቹ ፊት ቁመው ርዳታን ይልክላቸው ዘንድ ወደ ጌታችን ጸለዩ።
ያንጊዜም የጭፍሮቹ ፈረሶች ወደ ሐዋርያት ተመለሱ እግሮቻቸውንም አስተካክለው ተንበርክከው ሰገዱ እንደሚያለቅስም በቃጪን ድምጽ ጮኩ። ከፈረሶችም አንዱ ድምፁን ከፍ ከፍ አድርጎ እንዲህ ብሎ እንደ ሰው ተናገረ እናንት ሰነፎች የጰራግሞስ ጭፍሮች ክብር ይግባውና የክርስቶስን ጭፍሮች ጴጥሮስንና ጳውሎስን ለምን ትፈልጓቸዋላቸሁ ሥራየኞችስ ለምን ትሏቸዋላችሁ እነርሱ ግን ሥራይንና የሰይጣንን ሥራ ሁሉ ሊያጠፉ መጥተዋል። ክብር ይግባውና ከንጉሣቸው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በነጫጭ ፈረሶች ተቀምጠው አታዩአቸውምን ለክብር ንጉሥ ለክርስቶስ ጭፍሮቹ ትሆኑ ዘንድ ስሞቻችሁም በሕይወት መጽሐፍ ይጻፍ ዘንድ ስለ እናንተ ይለምናሉ። እኛ እንኳ እንስሳ ስንሆን ለአምላካችው እንሰግዳለን ፈረሱም ይህንን ተናግሮ ዝም አለ።
ከዚህም በኋላ እንዲህ የሚል ቃል ተሰማ ሐዋርያቶቼ ሆይ ሐዲሶች አትክልቶችን ቸለል አትበሏቸው። ያን ጊዜም ሕዝቡ ሁሉ ዐይኖቻቸውን ቀና አድርገው በታላቅ ክብር ወደ ሰማይ ሲዐርግ ጌታችንን አዩት እነዚያም ዐሥር ሺህ ሁለት መቶ ጭፍሮች ክብር ይግባውና በጌታችን በእየሱስ ክርስቶስ አመኑ ለሐዋርያትም ተገዙላቸው።
ሐዋርያትም የምድራዊ ንጉሥ ጭፍራ መሆንን እንዲተዉ ፈረሶቹንና የጦር መሣሪያውንም እንዲመልሱለት ክብር ይግባውና በክርስቶስ በግልጥ እንዲአምኑ አዘዟቸው። እነዚያ ጭፍሮቹም ወደ ንጉሣቸው ጰራግሞስ ሔደው በፊቱ ቆሙ ታመጧቸው ዘንድ የላክኋችሁ እነዚያ ሁለት ባለ ሥራዮት ወዴት አሉ አላቸው። የልጅህን ዐይኗን በማዳን በጎ በሠሩልህ ፈንታ ለምን በክፋት ትፈልጋቸዋለህ አሉት። ከዚህም ጥሩራቸውንና ትጥቃቸውን ፈትተው ገንዘብህን ውሰድ እኛ ግን ከአንተ የተሻለ ንጉሥ አግኝተናል ይኸውም የጴጥሮስና የጳውሎስ አምላክ ነው ብለው ከፊቱ ጣሉለት። በሰማ ጊዜም ደነገጠ ተቆጥቶም እስከሚገድላቸው ድረስ በወህኒ ቤት ይጨምሯቸው ዘንደ አዘዘ።
ከዚህ በኋላም ራሱ ይይዛቸው ዘንድ ተዘጋጀ የጦር መሣሪያውንም አዘጋጀ ወደ ፊልጶስ አገር ሔደው እስከ መሠረቷ ያጠፏት ዘንድ ሃያ ሺህ አራት መቶ እግረኞች ጭፍሮችን አዘዛቸው። ቅድስ ጴጥሮስም በመንፈስ ቅዱስ አውቆ ቅዱስ ጳውሎስን እንዲህ አለው። ወንድሜ ሆይ አገርን እንዳያጠፋ ሳይወጣ ወደ ጰራግሞስ ተነሥ እንሒድ አለው ከዚህም በኋላ ጸሎትን ጸለዩ ወጥተውም በደመና ተጫኑ በቤተ መንግሥት መካከልም አወረዳቸውና በጰራግሞስ ፊት ቆሙ እንዲህም አሉት እነሆ እኛ በፊትህ ነን ስለ እኛ አገርን አታጥፋ። ያን ጊዜም ጭፍሮች እንዲመለሱ አዘዘ።
ሐዋርያትንም እንዲህ አላቸው አገሩን ሁሉ በሥራይ የምታጠፉ ሥራየኞች አናንተ ናችሁን እነርሱም ይህ ሥራ ለእኛ አይገባም አሉት። ሁለተኛም ኃጢአታችሁ ነው ወደዚህ ያመጣችሁ አላቸው።
ችንካር ያላቸው ሁለት የራስ ቁሮችን ከብረት እንዲሠሩ አቃቂርንም እንዲመሉአቸው በእሳትም አግለው በሐዋርያት ራስ ላይ እንዲደፉአቸው አዘዘ እንዲሁም አደረጉባቸው። ያን ጊዜም ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ብሎ ጸለየ አቤቱ ፈጣሪዬ ሆይ የጌትነትህን ኃይል በጰራግሞስ ላይ ግለጽ። ያን ጊዜም ጰራግሞስ ከወገኖቹ ሁሉ ጋር በነፋስ ውስጥ ተዘቅዝቆ ተሰቀለ። በዚያን ጊዜም ጌቶቼ ሆይ ይቅር በሉኝ ከዚህ ፆዕርም አድኑኝ እያለ ጮኸ የእንዶር ንጉሥ አስቶኛልና የተረገመ ይሁን በእናንተም ላይ ክፉ የሚናገር ሁሉ የተረገመ ይሁን አለ። ቅዱስ ጴጥሮስም የታሠሩትን ጭፍሮች ይፈቷቸው ዘንድ እስከምታዝ ከዚህ ስቅላት አትወርድም አለው እርሱም ወደ ልጁ ወደ ሎይ ተጣርቶ ትፈታቸው ዘንድ አዘዛት እርሷም አንዳዘዛት ፈታቻችው።
ቅዱስ ጴጥሮስም ዳግምኛ አለው አሁንም ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም በምድር ላይም እንደእኔ ያለ ርኩስ የለም ብለህ ካልጻፍህ አትወርድም ይህችንም በከተማው መካከል ያነቧት ዘንድ ታዝዛለህ። ንጉሡም ወረቀትንና ቀለምን ታቀብለው ዘንድ ወደ ልጁ ተጣራ እርሷ ብቻዋን ከስቅላት ቀርታ ነበርና ባመጣችለትም ጊዜ ቊልቊል ተሰቅሎ እያለ ጻፈ በከተማውም መካከል ያነቧት ዘንድ ላካት።
ያን ገዜም ጰራግሞስንና ወገኖቹን አወረዷቸው ወደ ሐዋርያትም መጥተው ከእግራቸው በታች ሰገዱላቸው ንጉሡም ጌቶቼ ይቅር በሉኝ እኔ በአምላካችሁ አምናለሁ አለ ሕዝቡም ሁሉ ሕያው በሆነ አምላካችሁ እናምናለን እያሉ ከሐዋርያት እግር በታች ወድቀዉ ሰገዱ።
እነርሱም ሃይማኖትን አስተምረው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው ጭፍሮችንም አጠመቋቸው። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን አንድ ሆኑ። ቤተ ክርስቲያንንም ሠሩላቸው ከአዋቂዎቻቸውም ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾሙላቸው። ነገረ ምሥጢርንም እያስገነዘቡአቸው በእነርሱ ዘንድ ኖሩ። ሃይማኖታቸውንም ይጸና ዘንድ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሰጧቸው። እንዲህም አሏቸው በሃይማኖታችሁ ጽኑ እኛ ካስተማርናችሁ ትምህርት አትናወጹ ወደ እናንተም እንመለሳለን። ከዚህም በኋላ ሰላምታ ሰጥተዋቸው ወደ ፊልጶስ ሀገር ሔዱ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አቡነ ተስፋ ሐዋርያነት
ዳግመኛም በዚህች እለት የዋልድባው አቡነ ተስፋ ሐዋርያት የተሰወሩበት ዕለት ነው፡፡ አባታቸው ተክለ ሐዋርያት ሲባሉ እናታቸው ወለተ ሐዋርያት ይባላሉ፡፡ የአባታቸው የትውልድ ቦታ ሰሜን ጎንደር ሲሆን የእናታቸው ደግሞ ሽሬ ነው፡፡
በዋልድባ ከሳሙኤል ዘዋልድባ ቀጥለው በገዳሙ የተሾሙ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ይኸውም የሆነው በአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ትእዛዝ መሠረት ነው፡፡
አቡነ ተስፋ ሐዋርያት በአቡነ ሳሙኤል መቃብር ላይ የፈለቀውን ፀበል ለአትክልት አንድ ጊዜ ብቻ በማጠጣት ለብዙ ጊዜ ዳግመኛ አያጠጡትም ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ በዋልድባ አካባቢ ያለው የለምነት ምሥጢር ይኸው ነው፡፡
አቡነ ተስፋ ሐዋርያት ልዩ ስሙ አባ ነፅዓ በተባለው ቦታ ገዳማቸውን ከመሠረቱ በኋላ በዋልድባ ያለውን የአንድነት ማኅበሩን በከፍተኛ ሁኔታ አጠናክረውታል፡፡ በጣም ብዙ መነኮሳትንም አፍርተዋል፡፡ ጻድቁ በታላቅ ተጋድሎአቸው በእጅጉ ይታወቃሉ፡፡
በመጨረሻም ሞትን ሳይቀምሱ በዚህች ዕለት ተሰውረዋል፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ
No comments:
Post a Comment