አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, May 24, 2020

አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ


ልደቱ :- የወርቃማው ዘመን ወርቃማ ደራሲ፣ መናኝ፣ ጻድቅ፣ ሊቅ፣ የሕዝብ መምህር እና የሥነ ምሕንድስና ባለሙያ የሆነው አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ የተወለደው በ1357 ዓመተ ምሕረት በወሎ ክፍለ ሀገር በዛሬው ቦረና በጥንቱ ወለቃ ወረዳ ሸግላ በተባለ ቦታ ነው፡፡ አባቱ ሕዝበ ጽዮን እናቱ እምነ ጽዮን ይባላሉ፡፡ ስለ አባቱ ሕዝበ ጽዮን ሁለት የተለያዩ ታሪኮች ይተረካሉ፡፡ የሰኔ ድርሳነ ዑራኤል ምንባብ አባቱ በመጀመሪያ የትግራይ በማስከተል የሰግላ /ጋሥጫ/ አገር ገዢ እንደነበር ይወሳል፡፡ ገድሉ ደግሞ /ጠቢብ ወማእምረ መጻሕፍት ወአቡሁኒ መፍቀሬ እግዚአብሔር አምኁልቈ ካህናተ ደብተራ ዘውሳጤ ዓጸደ ቤተ ንጉሥ/ አባቱም የእግዚአብሔር ወዳጅና በቤተ መንግሥት በነበረችው ድንኳን /ሥዕል ቤት/ ከሚያገለግሉ ካህናት ወገን ነበረ ይላል፡፡ እንደ ገድሉ ገጸ ምንባብ ትርጉም ሕዝበ ጽዮን ከንጉሡ ሥዕል ቤት በቅዳሴ ወይም በማሕሌት ከሚያገለግሉ ካህናት አንዱ ነው፡፡ /. . . ወእሙኒ እም ሥዩማነ ወለቃ/ እናቱም ከወለቃ ሹማምንት ወገን ነች ይላታል፡፡ ይኸውም የጥንቱ ወለቃ /የዛሬው ደቡብ ወሎ፣ ቦረና ከላላ/ ከነበሩ መኳንንት ወገን መሆኗን ያመለክታል፡፡      የአባ ጊዮርጊስ ወላጆች ልጅ ሳይወልዱ ለረጅም ዓመታት ቆይተዋል፡፡ የልጅ ፍላጎታቸው እንዲሠምር ለሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተሳሉ፡፡ ስእለታቸውም ሥምሮ በመልአኩ ቀዱስ ዑራኤል አብሣሪነት ወንድ ልጅ ወለዱ፡፡ ልጃቸውን ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመማጸን ስለወለዱ ስሙን ጊዮርጊስ ብለው ጠሩት፡፡ ወላጆቹ የታላቁን ሰማዕት ስም ለልጃቸው ያወጡት ወደ ፊት በዓላውያን ነገሥታት ፊት ምስክር፣ አፅራረ አምነትን አሳፋሪ፣ ካህናትንና ምእመናት በየዘመናቱ ከሚነፍሱ የኑፋቄና የክህደት ነፋሳት በወንጌል ብርሃን ነፃ የሚያወጣ ሲሉ ይህን ስም እንዳወጡለት ድርሳነ ዑራኤል እንዲህ ይተርካል፡፡ ‹‹ዘይከውን መምህረ ኵሉ ዓለም ወበጸሎቱ ዘያድኅን አሞተ ሲኦል ፍቁረ ድንግል ማርያም ወላዲቱ ለአማኑኤል፡፡ ወመገሥጾሙ ለነገሥት፡፡ ወፀሮሙ ለዐላውያን ሃይማኖት በሰይፈ ቃሎሙ ለሐዋርያት ዘያጠፍኦሙ እም ብሔረ ኢትዮጵያ፤ ወለካህናተ ጽድቅ ዘይመርሆሙ እምጽልመተ ኑፋቄ መንገለ ብርሃን ቃለ ወንጌሉ ለክርስቶስ በትምህርተ ሕጎሙ ለሐዋርያት›› ይላል፡፡
ትምህርት :-አባ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ደረጃ መንፈሳዊ ትምህርቱን ከወላጅ አባቱ ሕዝበ ጽዮን እንደተማረ ይገመታል፡፡ አባቱ የመጀመሪያ ደረጃ ተምህርቱን ካስተማሩት በኋላ መዐርገ ዲቁና እንዲቀበል ማድረጋቸውን  ገድሉ ይነግረናል፡፡ ወሶበ ልህቀ ሕቀ ወሰዶ ኀበ ጳጳስ ወሴሞ ዲያቆነ፡፡ ባደገም ጊዜ ከጳጳስ ዘንድ ወሰደው ጳጳሱም በዲቁና አሾመው ይላል ገድሉ፡፡ ዲቁና መቀበሉን እንዲ መዓርገ ዲቁና የሰጡትን ጳጳስ ስም አይገልጽም፡፡ ዳሩ ግን መዓርገ ዲቁናን በ1341 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እስከ ዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ አካባቢ ከነበሩት ብፁዕ አቡነ ሰላማ መተርጉም እንደተቀበለ ይገመታል፡፡
መዓርገ ዲቁና ከተቀበለ በኋላ የአባ ጊዮርጊስ ወላጆች ለታላቅ ሐላፊነት የተመረጠውን ልጃቸውን በዘመኑ የታወቀ የነገረ ሃይማኖት ትምህርት ሊያስተምሩት ለሚችሉ መምህራን መስጠት እንዳለባቸው ወሰኑ፡፡ በወቅቱ ጥልቀት ያለው የነገረ ሃይማኖት ትምህርት ለመማር የሚመረጠው ትምህርት ቤት ሐይቅ እስጠፋኖስ ነበር፡፡ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ በዐፄ ዳዊት /1385 - 1395/ ዘመነ መንግሥት እንደገባ ገድሉ ይገልጣል፡፡ ሐይቅ እስጢፋኖስ የተለያየ ሊቃውንት የሚገኙት፣ በብዙ መጻሕፍት የተሞላውና ዙሪያውን በሐይቅ በመከበቡ የተማሪን ሐሳብ ለማሰባሰብ አመቺ የሆነ ቦታ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርት አልገባው ብሎ ለሰባት ዓመታት ተቀምጦ ነበር፡፡ የትምህርት ቤት ሕይወቱም ከቅዱስ ያሬድ ይመሳሰላል፡፡ ቀዱስ ያሬድ ትምህርት አልገባው ብሎ ሰባት ዓመት እንደተቸገው እንደዚሁ አባ ጊዮርጊስም አብረውት የሚማሩት ተማሪዎች ይህ ትምህርት የማይገባው ስለ ምንድን ነው? በእርሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ? ብለው እስከ ሚጠይቁ ድረስ ትምህርት አልገባ ብሎት ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ የሐይቁ መምህር የነበረው ዐቃቤ ሰዓት ሠረቀ ብርሃን ለአባቱ ‹‹ልጅህ ትምህርት አይገባውምና የቤተ መንግሥት ነገር አስተምረው›› ብሎ መለሰው፡፡ አባቱ ሕዝበ ጽዮን ግን ‹‹ አንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ አልቀበልህም እዚያው ገዳሙን ያገልግል›› ብሎ እንደገና ላከው፡፡በዚህ ዓይነት መምህሩ ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ መልሶ ወሰደውና በጥበብ እድ ሥራ ላይ ተመደበ፡፡ በጥበበ እድ ባከበተው ዕውቀትም እንደ ቅዱስ ላሊበላ ከዐለት ፈልፍሎ ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ ችሏል፡፡ ዛሬ ከዘመን ርዝማኔ የተነሣ ጥገና ባይደረግለትም አባ ጊዮርጊስ ፈልፍሎ ያሠራው ዋሻ ቅኔ ማኅሌት፣ ቅድስት እና መቅደስ ያለው ቤተ ክርስቲያን ብዙ የትሩፋት ሥራ በሠራበት በጋሥጫ ገዳም ይገኛል፡፡ የወለቃን ወንዝ ለመሻገር ያገለግል ዘንድ ከዓለት ፈልፍሎ የሠራው ድልድይም የሥነ ምሕንድስና ሙያው የታየበት አሻራ ነው፡፡አባ ጊዮርጊስ ዕውቀት ስለ ተሠወረው ሁል ጊዜ በሥዕለ ማርያም ሥር እየተንበረከከ ይጸልይ ነበር፡፡ የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምንም እህል በመፍጨት ያገለግል ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ይፈጭበት የነበረው የድንጋይ ወፍጮ አሁንም በገዳሙ ውስጥ ይገኛል፡፡ አንድ ቀን እመቤታችን ተገለጠችለትና አይዞህ ዕውቀት የተሠወረብህ ትምህርት ስለማይገባህ ሳይሆን የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ እንዲገለጥ ነውና ታገሥ አለችው፡፡ ከዚያም ጽዋዐ ልቡና አጠጣችው፡፡ከዚህ በኋላ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርቱን በሚገባ ተምሮ አጠናቀቀ፡፡ በዕውቀቱም ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ይደነቁበት ጀመር፡፡

አባ ጊዮርጊስ የያሬድንም ዜማ ተምሯል፡፡ የተማረውም ከአቡነ ሳሙኤል ዘጋርማ እንደሆነ ገድሉ ይገልጣል፡፡ ሊቁ በዚያ መን በዐፄ ዳዊት አማካኝነት በሰሜን ኢትዮጵያ የያረድ ድጓ ዋና ማዕከል በሆነው በደብረ ነጎድጓድም ተሹሞ አስተምሯል፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ የድጓ ሊቃውንት ዝርዝር አባ ጊዮርጊስ ይጠቀሳልና፡፡በትርጓሜ መጻሕፍትና በቅኔ የጠለቀ ዕውቀት እንዳለውም ድርሰቶቹ ይመሰክራሉ፡፡የማስተማር ሥራውን የጀመረው በዚያው በሐይቅ እስጢፋኖስ መሆኑን ገድሉ በሚከተለው መልኩ ይገልጠዋል፡፡ ‹‹ወአብርሃ ለቤተ ክርስቲያን እንተ ተሐንጸት በሐይቅ ባሕር፣ ወእመ አምሃ አኀዙ ይስእሉ አምኀቤሁ ኵሎሙ ሰብአ ሀገር ቃለ መጻሕፍት ወትርጓሜሆሙ፣ ወኵሉ  ቃለ ማሕሌት፤ በሐይቅ የታነጸችውን ቤተክርስቲያን እንድታበራ አደረጋት /አደመቃት/ ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከእርሱ ዘንድ የአገሪቱ ሰው ሁሉ የመጻሕፍትን ቃል ትርጓሜና ሁሉንም የማሕሌት ቃል ይጠይቁ ጀመር፡፡ ››ከሐይቅ በኋላ በዚያ ዘምን ሸግላ በመባል ትጠራ ወደ ነበረችው ወደ ትውልድ ሀገሩ ወደ ጋሥጫ ተጓዘ፡፡ በዚያ ጊዜ የነገሥታቱ መቀመጫ በዚያ የነበረ ይመስላል፡፡ ለዚህ ሦስት ምልክቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው በነገሥታቱ መቀመጫ አካባቢ አብያተ ክርስቲያናት እንደሚገዙት ሁሉ /አክሱምን፣ ላስታን፣ ጎንደርን፣ አንኮበርንና አዲስ አበባን በምሳሌነት ማንሣት ይቻላል፡፡/ በጋሥጫም በዚያ ዘመን ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በገድሉ ላይ አባ ጊዮርጊስ ወደ ሽግላ በመጣ ጊዜ ወደ ቤተመንግሥት እንዳስገቡት የሚገልጥ ታሪክ መኖሩ ነው፡፡ ሦስተኛው መረጃ ጋሥጫ የዐፄ ይስሐቅ የክረምት ጊዜ ማረፊያ እንደነበረች ገድሉ መግለጡ ነው፡፡አባ ጊዮርጊስ ወደ ሽግላ ሲመጣ አባቱ በጣም አርጅቶና መንኩሶ ነበር፡፡ ስለዚህም በአባቱ እግር ተተክቶ በቤተመንግሥት ያለችውን ሥዕል ቤት እንዲያገለግል ወደዚያው አስገቡት፡፡ አባ ጊዮርጊስ በቤተመንግሥቱ የንጉሡን ልጆች ከማስተማሩም በላይ በቤተ መንግሥቱ ዙርያ ከነበሩት ሊቃውንት መካከል አንዱ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ግብፃዊው ጳጳስ አቡነ በርተሎሜዎስ ሥላሴን አንድ ገጽ ብለው ያምናሉ፡፡ ተብለው በተከሰሱ ጊዜ ነገሩን እንዲያጣሩ ከተመረጡት ከቄስ ሐፄ ተከሥተ ብርሃንና ከሐይቁ መምህር ከዐቃቤ ሰዓት ዮሴፍ ጋር አብሮ ተልኮ ነበር፡፡ እነዚህ ሦስት አበው ጳጳሱን ካነጋገሩ በኋላ ክሱ ሐሰት መሆኑን በማረጋገጥ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ የሚገልጠውን የጳጳሱን እምነት በጽሑፍ ይዘው መጡ፡፡በቤተ መንግሥቱ በነበረ ጊዜ የንጉሡን ልጆች ይስሐቅን፣ ቴዎፍሎስን፣ እንድርያስን፣ ሀብተ ኢየሱስን፣ ሕዝቅያስን፣ ኢዮስያስን፣ ዘርዐ ያዕቆብንና ሴት ልጁን ዕሌኒን በምግባርና በሃይማኖት ቀርጿቸዋል፡፡ ወደ ዙፋን ከመጡት ቴዎድሮስ፣ ይስሐቅ፣ ዘርዐ ያዕቆብና እንድርያስ በስተቀር ሌሎች ታዋቂ አይደሉም፡፡ በእነዚህም የአባ ጊዮርጊስ የሕይወት ፍልስፍና ተንጸባርቋል፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ በድርሰቱ ሲመስለው ቴዎድሮስ ደግሞ ለቅድስና ማዕረግ በቅቶ በሕይወት መስሎታል፣ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ተብሎ ጽላት ተቀርፆለታል፣ በዓሉ ሰኔ 29 ቀን ይከበራል፡፡ ይስሐቅም በዘመኑ ፖለቲካዊና ባህላዊ እመርታ አሳይቷል፡፡
ምንኵስናና ተጋድሎ:-      ዐፄ ዳዊት የአባ ጊዮርጊስን ሊቅነትና መልካም ሥነ ምግባር በሚገባ ስላወቀ በጋብቻ ሊዛመደው ወዶ ስለ ነበር ልጁን እንዲያገባ ዘወትር ይጠይቀው ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን በድንግልና ጸንቶ ለመኖር እንደ ሚገልግ ከመግለጽ አልተቆጠበም ነበር፡፡ የዐፄ ዳዊት ጥያቄ ስለበዛበት ከአካባቢው በመሸሽ ከአባ በጸሎተ ሚካኤል መቃብር ደረሰ፡፡ አባ በጸሎተ ሚካኤልን ከልጅነቱ ጀምሮ ይወዳቸው ስለነበር እርሳቸው በመሠረቱት ገዳም በመልካም ሥነ ምግባራቸው ከታወቁት የአባ ቴዎድሮስ ዘንድ የምንኵስና ልብስ ለብሶ መነኮሰ፡፡
ከመነኮሰ በኋላ ወደ ሸግላ በመምጣት ‹‹ወእምድኀረዝ ኮነ አቡነ ጊዮርጊስ መምህር ለነገሥት ወለካህናት ዘደብተራ ወለኩሉ ዐበይተ ቤተ መንግሥት፣ ለንቡራነእድ ወለመኳንንት፣ ለመሳፍነት ወለኩሉ ተዐይነ ቤተ መንግሥት ከዚህ በኋላ ለነገሥታትና በቤተ መንግሥቱ ለነበሩ ካህናት እንዲሁም በቤተ መንግሥቱ ታላላቆች ለነበሩ፣ ለንቡራነእድ ለመኳንንት፣ ለመሳፍንትና በቤተ መንግሥቱ ለነበሩ ባለሟሎች ሁሉ መምህር ሆነ፡፡››
አባ ጊዮርጊስ በሸግላ በነበረ ጊዜ በወባ በሽታ ታምሞ ሊሞት ደርሶ እንደ ነበር ገድሉ ይናገራል፡፡ታምሞ በነበረ ጊዜ አንድ ሌሊት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ተገልጠውለት ከእኛ ጋር ትኖር ዘንድ ልንወስድህ መጣን አሉት፡፡ እርሱም የድርሰት ሥራዬን ሳልሠራና እግዚአብሔርንም አብዝቼ ሳላመሰግነው አሁን አትውሰዱኝ ሲል ለመነ፡፡ እነርሱም ልመናውን ተቀብለውት ከሕመሙ ፈውሰውት ሔዱ፡፡ ለዚህም ይመስላል ከበሽታው እንደ ተፈወሰ ወዲያው የድርሰት ሥራውን የጀመረው፡፡
የመጀመሪያ መጽሐፉን ጽፎ እንደ ጨረሰ ጠፍቶበት እንደ ነበር ገድሉ ይተርካል፡፡ በቤቱ ውስጥ የነበሩትን መጻሕፍት ሁሉ እያገላበጠ ቢፈልገውም ሊያገኘው አልቻለም፡፡ አንድ ቀን በቤተክርስቲያን ሌሊት በአገልግሎት ላይ እያለ እመቤታችን ተገልጣ ‹‹ለምን አስቀድመህ ሳትነግረኝ ጻፍክ?›› ስትል ጠየቀችው፡፡ እርሱም ‹‹አንቺን ደስ ያሰኘሁ መስሎኝ ነውና ይቅር በይኝ›› ሲል መለሰላት፡፡ ከዚህ በኋላ የድርሰት ሥራውን ፈቅዳለት ተሰወረች፡፡
የድርሰት ሥራው አባ ጊዮርጊስ በበርካታ ሃይማኖታዊ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እንዲኖረው አድርጓል፡፡  ይህ በጎ አገልግሎቱ ለበርካታ ጊዜያት ለመከራ አጋልጦት ነበር፡፡ በተለይም ለተራው ሕዝብና  ለመኳንንቱ የሚሰጠው ከበሬታ አንድ አይነት በመሆኑ ይህ አድራጎቱም በሹማምንቱ ዘንድ አልተወደደለተም፡፡
በመምህርነት እንደተሾመ እቴጌዎች /የነገሥታት ባለቤቶች/ ቁጭ እንዳሉ ሥጋ ወደሙ የመቀበላቸውን ልማድ ማስቀረት ፈለገ፡፡ ‹‹የነገሥታት ንጉሥ የሆነው የክርስቶስ ሥጋና ደም ነውና እቴጌዎቹ ወደ ቁርባኑ ቦታ መጥተው መቀበል አለባቸው እንጂ እነርሱ ወንበር ላይ ቁጭ ብለው ቁርባኑ ወደ እነርሱ ሊሔድ አይገባም›› ብሎ በመጽናቱ ንግሥቲቱ ወደ ካህናቱ ቀርበው መቁረብ ጀመሩ፡፡
ይሁን እንጂ ንግሥቲቱ አባ ጊዮርጊስ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ይከበር ማለቱን እንደ ድፍረት ስለቆጠሩት ጉዳዩን ወደ ንጉሡ ዘንድ አቅርበው ከሰሱት፡፡ ንጉሡም በጉዳዩ ውሳኔ ለመስጠት አጣብቂኝ ውስጥ ገቡ፡፡ንጉሡ የአባ ጊዮርጊስ ተማሪ እንደ መሆናቸውና እንደ መንፈሳዊ ሰውነታቸው የአባ ጊዮርጊስ ውሳኔ ትክክል እንደሆኑ ልቦናቸው ቢያውቀውም ለንግሥቲቱ ያሳየውን አመለካት ስላልወደዱለት እርሱን የንቡረ እድገት መዓርግ ሰጥተው ዳሞት ውስጥ ለሚገኝ ቤተክርስቲያን አለቃ አድርገው ላኩት፡፡  ይህን በማድረግ ንጉሡ ጉዳዩን በፈሊጥ በፊቱም፡፡ ውሳኔው ግን ለንግሥቲቱ ፍላጎት ያደላ ነበር፡፡
አባ ጊዮርጊስ እና አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ የተገናኙት አባ ጊዮርጊስ ወደ ዳሞት በሚጓዝ ጊዜ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ የአባ ጊዮርጊስ ዋናው ትኩረት በድርሰቱ ላይ ሆነ፡፡ ወደ ጳጳሱ ወደ አቡነ በርተሎሜዎስ ዘንድ በመሔድ የቅዳሴ ድርሰት ለመድረስ እንዲፈቀድለት ከጠየቀ በኋላ የቅዳሴ ድርሰት ማዘጋጀሩን ገድሉ ይገልጻል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ቅዳሴያት ደራሲያቸው ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ፍንጭ የሚሰጠን ይሆናል፡፡ገድሉ እንደሚተርከው አንዳንድ ካህናት የአባ ጊዮርጊስን ቅዳሴ ተቃውመው ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር አርዮስን በቀጣበት መንገድ ተጥቷቸዋል፡፡
አባ ጊዮርጊስ ነገረ ሃይማኖትን ጠንቅቆ የተረዳና የሚያስረዳ ስለነበር በዘመኑ የተነሡ የሃይማኖት ክርክሮች ሁሉ እርሱ ከሌለ አይሳኩም ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ በሸዋ በይፋት ራሳቸውን ቤተ እስራኤል እያሉ የሚጠሩ አይሁድ ነበሩ፡፡ ከአቡነ ዜና ማርቆስ ጀምሮ ብዙ መምህራን ወደ እነዚህ ሕዝቦች እየተሠማሩ ወንጌልን አስተምረዋል፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ክርስትና ለተመለሱት ቤተ እስራኤላውያን በእመቤታችን፣ በቅዱስ ሚካኤል፣ በአባ ኖብና በሰማዕቱ በጊርጋ ስም አራት አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተው ነበር፡፡ ሁለቱ የመጀመሪያዎቹ አሁንም አሉ፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም ቤተ እስራኤላዊያኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ክርስትና አልተመለሱም ነበር፡፡
ከእነዚህ አይሁድ ማካከል አንዱ ከክርስቲያኖች ጋር በነገረ ሃይማኖት ለመከራከር ጥሪ አቀረበ፡፡ ‹‹ክርስቲያኖች ከረቱኝ ወደ እነሱ ሃይማኖት እገባለሁ እኔ ከረታኋቸውም ወደ እኔ ሃይማኖት ይገባሉ›› ሲል ነገሩን ጥብቅ አደርገው፡፡ ዐፄ ዳዊት ይህን ጉዳይ ሲሰማ በጣም ስለ ተናደደ ሊቃነ ካህናቱን፣ ንቡራነእዱንና የመጻሕፍት ዐዋቂዎችን ሁሉ ከየሀገሩ እንዲሰባሰቡ አዘዘ፡፡ አይሁዳዊው በአንድ ወገን መምህራኑ በአንድ ወገን ሆነው ክርክሩን ጀመሩ፡፡ የመጀመሪያው እድል የተሰጠው ለአይሁዳዊው በመሆኑ ቀጥሎ ያለውን ጥያቄ አቀረበ፡- ‹‹እናንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የምትሉ ይኸ ክርስቶስ እውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፣ ወደ ቢታኒያ በመጣ ጊዜ አልዓዛር የተቀበረበትን ቦታ ሳያውቅ ቀርቶ አልዓዛርን የተ ቀበራችሁት? ብሎ እንደ ጠየቀ በወንጌላችሁ ተጽፏል፡፡ ለዚህ መልስ ስጡኝ፣ እኔንም ከመጽሐፈ ኦሪት ጠቅሳችሁ ጠይቁኝ?›› ሲል የመከራከሪያ ነጥቡን አቀረበ፡፡
በዚህ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ ታሞ አልጋ ላይ ነበር፡፡ ሊቃውንቱም እንዲህ ያለው ነገር ያለ እርሱ አይሆንምና አባ ጊዮርጊስ ይምጣ ሲሉ ለዐፄ ዳዊት አመለከቱት፡፡ አባ ጊዮርጊስም በአልጋ ላይ እያለ እንዲመጣ ተደረገ፡፡ ሊቁም በአልጋም ላይ ሆኖ በጉባኤው ላይ ተገኘ፡፡ ጉባኤተኞቹ የቀረበውን ጥያቄ ነገሩት፡፡ አባ ጊዮርጊስ የሰጠውን መልስ ገድሉ በሚከተለው መንገድ ይገልጥልናል፡፡ ‹‹እኔ ግን በወንጌል ሳይሆን በኦሪት እከራከርሃለሁ፡፡ የምኵራብ መጻሕፍት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን የታወቁ ናቸውና፡፡ ምኵራብ ዘራች ቤተክርስቲያንም አጨደችው፤ ምኵራብ ፈተለችው ቤተክርስቲያን ለበሰችው፤ አዳምን በገነት ሳለ አዳም ሆይ! ወዴት ነህ ብሎ የጠየቀው ማነው? አብርሃምንስ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት ብሎ የጠየቀው ማነው? እስቲ መልስልኝ፤ ሰይጣንንስ ከወዴት መጣህ ብሎ የጠየቀው ማነው? እግዚአብሔር አብ አይደለምን?›› በዚህ ጊዜ አይሁዳዊው መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡ ንጉሡ፣ ሊቃውንቱና መኳንንቱም እጅግ ተደሰቱ፡፡
አባ ጊዮርጊስ ሌላው ያጋጠመው ክርክር ቢቱ ከተባለው ሰው ጋር ያደረገው ክርክር ነበር፡፡ ቢቱ በምጽአት ጊዜ የሚመጣው ወልድ ብቻውን እንጅ አብና መንፈስ ቅዱስ አይመጡም የሚል ኑፋቄ ማስተማር ጀምሮ ነበር፡፡ ቢቱ ከዚህ ኑፋቄው በተጨማሪ የጥንቆላ ሥራም ይሠራ ነበር፡፡ ቢቱ በጥንቆላ ሥራው የተነሣ በቤተ መንግሥቱ ተቀባይነት የነበረው ሰው እንደ ነበረ ገድሉ ይናገራል፡፡ይህን መሰሉን ተግባር አጥብቆ የተዋጋው ዘርዐ ያዕቆብ እስኪ መጣ ድረስ ነገሥታቱ ምንም ክርስቲያኖች ቢሆኑ በዚህ መሰሉ ስንኩል ሕፀፅ ይዋጡ ነበር፡፡
ተንኮለኛው ቢቱ እና አባ ጊዮርጊስ ወደ ዐፄ ዳዊት ቀርበው በጉዳዩ ላይ መነጋገር እንደሚፈልጉ ገለጡ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ጳጳሱና ሊቃውንቱ ባሉበት እንዲነጋገሩ ስለወሰነ ጳጳሱ እንዲመጡ አዘዘ፡፡ በዚህ ጊዜ ተንኮለኛው ቢቱ ከአባ ጊዮርጊስ ጋር ከተከራከረ እንደሚረታ ስላወቀ ንጉሡ የአባቶቻችንን ሃይማኖት ክዷልና አትምጣ የሚል ደብዳቤ በአባ ጊዮርጊስ ስም ጽፎ ጳጳሱን ሊጠሩ በሔዱት መልእክተኞች እጅ ላከ፡፡ ወዲያውም ለዐፄ ዳዊት ይህንን ነገር አሳበቀ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ፈጣን መልእክተኞች ልኮ የፊተኞቹ መልእክተኞች እንዲመለሱ አደረገና ደብዳቤው ተነበበ፡፡ የቢቱ ተንኮል ያልገባው ዐፄ ዳዊት ይህን ደብዳቤ ሲመለከት አባ ጊዮርጊስ በደም እስኪነከር ድረስ እንዲደበደብ አድርጎ ወደ እስር ቤት አስገባው ፡፡ ቅዱስም ዐፄ ዳዊት እስኪሞትና ልጁ ቴዎድሮስ እስኪነግሥ ድረስ በዚያ ቆየ፡፡ ቢቱ ግን በመልአክ ተቀስፎ ሞተ፡፡
በአባቱ ዙፋን በተተካ ጊዜ አባ ጊዮርጊስን ከውኅኒ ቤት አውጥቶት በጥንቱ ቦታው አስቀመጠው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን የቤተ መንግሥትን ነገር ለመሸሽ ስለ ፈለገ በጋሥጫ ከመቀመጥ ይልቅ ርቆ ጥንት ወደ ነበረበት ወደ ዳሞት በመሔድ ማስተማር ጀመረ፡፡ ወደ ዳሞት ሲሔድ እግረ መንገዱን ወደ ደብረ ሊባኖስ ገብቶ የአቡነ ተክለሃይማኖትን መቃብር ተሳልሟል፡፡ በዚያ ጊዜ የደብረ ሊባኖሱ አበምኔት ዕጨጌ ዮሐንስ ከማ /ሰባተኛው የደብረ ሊባኖስ ዕጨጌ/ እንደ ነበሩ ገድሉ ይናገራል፡፡
ነገር ግን በዕውቀቱ የሚቀኑበት፣ በችሎታው የሚመቀኙት ሰዎች ነገር ሠርተው ከንጉሡ ቴዎድሮስ ጋርም ስላጣሉት ሰው ሊኖርበት ወደ ማይችል በረሃ እንዲጋዝ ተደረገ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ከዚህም ግዞት የወጣው ዐፄ ቴዎድሮስ ሲሞት ነበር፡፡
የአባ ጊዮርጊስ ሌላው ተማሪ የነበረው ዐፄ ይስሐቅ በ1399 ዓ.ም መንግሥቱን ሲይዝ አባ ጊዮርጊስ ከግዞት አውጥቶ ወደ ጋሥጫ መለሰው፡፡ በዚያ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ ዕድሜው 42 ዓመት ሲሆን በስደትና በጤንነት መታወክ የተነሣ ጉዳት ደርሶበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜውን በጾም፣ በጸሎትና በድርሰት ያውለው ነበር፡፡
አባ ጊዮርጊስ መከራ ያልተለየው አባት ነበር፡፡ ገድሉ እንደሚተርከው በቤተ መንግሥቱ የነበሩ ሰዎች የርሱን መከበርና መወደድ አይፈልጉትም ነበር፡፡ በተለይም ፍካሬ ሃይማኖት የተሰኘውን መጽሐፍ በመጻፉ የተነሣ መከበሩ አልተዋጠላቸውም፡፡ ስለዚህም ነገር ሠርተውም ከዐፄ ይስሐቅም ጋር አጣሉት፡፡
ከዕለታት በአንድ ቀን የአባ ጊዮርጊስ በሥጋ ዘመዱ የሚሆን አባ ጊዮርጊስ በሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ ያለውን ክብርና ሞገስ አይቶ በመቅናት ወደ ንጉሡ በመሔድ በሐሰት ከሰሰው ዐፄ ይስሐቅ አባ ጊዮርጊስን አሳስሮ ውሃ ወደ ማይገኝበት አለታማ ቦታ አጋዘው፡፡ በዚያም በመከራ ለብዙ ጊዜ ኖረ፡፡ በዚያ እያለ ዘወትር በጸሎት አብዝቶ ይተጋ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ዐፄ ይስሐቅ ወደ ልቡናው እንዲመለስ አደረገ፡፡ ንጉሡም በአባ ጊዮርጊስ ላይ የፈጸመው ነገር ሁሉ ፀፀተው፡፡ አገልጋዮቹንም ጠርቶ አባ ጊዮርጊስን እንዲያመጡለት አዘዘ፡፡ ነገር ግን እነዚያ ተንኮል ሠሪዎች የአባ ጊዮርጊስ መምጣት ተንኮላቸውን ስለሚያጋልጠው አባ ጊዮርጊስ ሞቷል ብለው አስወሩ፡፡ ይህንን ሲሰማ ዐፄ ይስሐቅ ፈጽሞ አዘነ፡፡
አባ ጊዮርጊስ ሞቷል እየተባለ መወራቱን ከደቀ መዝሙሩ ስለሰማ በሕይወት የመሆሩን ዜና ጽፎ ለዐፄ ይስሐቅ እንዲያደርስለት አውሎ ነፋስን ላከው፡፡ አውሎ ነፉሱ ደብዳቤውን ተሸክሞ በመሔድ ዐፄ ይስሐቅ በድንኳን ተቀምጦ ሳለ ጉልበቱ ላይ አስቀመጠው፡፡ ንጉሡ ምትሐት የተሠራበት ስለመሰለው ደነገጠና መኳንንቱንና ሕዝቡን ሰብስቦ ጉዳዩን ገለጠ፡፡ ወዲያውም እሳት አስነድዶ ቢጥለው ሊቃጠል አልቻለም፡፡ ወደ ውሃው ቢጨምረው አልጠፋም፡፡ በዚህ ተደንቆ ወረቀቱን ከፍቶ አነበበው፡፡ ደብዳቤው ከአባ ጊዮርጊስ የተላከ መሆኑን ሲያውቅ ዐፄ ይስሐቅ ደነገጠ፡፡ አነዚያን መልእክተኞች ይዞ ወደ ወኅኒ ጨመራቸው፡፡ አባ ጊዮርጊስንም ከግዞት ያወጡት ዘንድ ላከ፡፡
አባ ጊዮርጊስ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሲመጣ ንጉሡ በደስታ ተቀበለው፡፡ ደብዳቤውን በማን አጅ እንደ ላከውም ጠየቀው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ደብዳቤውን በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ በነፋስ እንደ ላከው አስረዳ፡፡
ዐፄ ይስሐቅ ለአባ ጊዮርጊስ ምድረ ሰዎን የተባለውን የጳጳሳት መቀመጫ የነበረውን ሀገር በርስትነት ሰጥቶት ነበር፡፡ ይህ ቦታና ጋሥጫ ቅርብ ይመስላሉ፡፡ ምክንያቱም ገድለ አባ ጊዮርጊስ ስለ ምድረ ሰዎን ሲናገር በዚያ የአባ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም እንዳለ ይተርካል፡፡ የአባ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ያለው ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ገዳም ሥር ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ በግዞት በነበረ ጊዜ በራእይ እመቤታችን ተገልጣ ዕረፍቱ በአባ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም እንደሚሆን እንደነገረችው ገድሉ ይተርካል፡፡ አባ ጊዮርጊስ በምድረ ሰዎን ንጉሥ ይስሐቅ ክረምቱን ያሳልፍበት በነበረው ቦታ ላይ ቤተክርስቲያን ሠራ፡፡ በዚያም በማስተማርና በጾም በጸሎት ይተጋ ነበር፡፡ በጋሥጫ እያለ ዐፄ ይስሐቅ አስጠራው፡፡ በዚያ ጊዜ ንጉሡ የመናገሻ ማርያምን ቤተክርስቲያን አሠርቶ ስለነበር እንዲባርክለት ፈልጎ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ምንም እንኳን በዚያ ጊዜ ታምሞ የተኛም ቢሆን ወደ ንጉሡ ተጓዘ፡፡ እዚያ ሲደርስ በጣም ተዳክሞ ነበር፡፡ ሥርዓቱን ለመፈጸምም ዐቅም አልነበረውም፡፡ ስለዚህም ንጉሥ ይስሐቅ በአልጋ ተሸክመውት እንዲዞሩ ቤተክርስቲያኗን እንዲባርካት አደረገ፡፡
ቡራኬውን ከፈጸመ በኋላ ደቀመዛሙርቱን ሰብስቦ ከሞትኩ አባቴ በጸሎተ ሚካኤል መከራ ወደ ተቀበለባትና እኔም ቤተ ክርስቲያን ወደ አነጽኩባት ቦታ ወስዳችሁ ቅበሩኝ ሲል አዘዛቸው፡፡ ለደቀ መዛሙርቱ የመጨረሻ የስንብት ትምህርቱን እያስተማራቸው እነርሱም በአልጋ ተሸክመውት ወደ ጋሥጫ እያመሩ ሳለ በመንገድ ላይ ሐምሌ ሰባት ቀን 1426 ዓ.ም በ 69 ዓመቱ ዐረፈ፡፡
በገድሉም ላይ ዘመዶቹና በደቀመዛሙርቱ መካከል የት ይቀበር በሚለው ጉዳይ ላይ ክርክር መነሣቱናና ንጉሡ በገዳሙ እንዲቀበር መወሰኑን ይገልጣል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ ክርክሩ አልቆ ዐፅሙ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እስኪገባ ድረስ በሌላ ቦታ ዐፅሙ ዐርፎ መቆየቱን ገድሉ ጨምሮ ይገልጣል፡፡ በመሆኑም ያረፈበት ቦታ ጉንደ መስቀል ሳይሆን አይቀርም፡፡
የጻድቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን፡፡
ሥራዎቹ:-      በርካታ የድርሰት ሥራዎችን በማበርከት አባ ጊዮርጊስን የሚተካከል ሰው በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረ መሆኑ ያጠራጥራል፡፡ በዚህም የተነሣ የኢትዮጵያ ብርሃን የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ የመጽሐፎቹ ብዛት በትክክል ባይታወቅም በገድሉ ውስጥ የተጠቀሱት ዘጠኙ በሌሎች የጥናት ወረቀቶች የሰፈሩት የሚከተሉት ናቸው፡፡
      ሀ. አርጋኖን
      አርጋኖን የተሰኘው መጽሐፍ ሊቁ እመቤታችንን በቅኔ ያመሰገነበት መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ እንደ ውዳሴ ማርያምና እርሱ እንደጻፈው ኆኅተ ብርሃን በሰባት ቀን የተከፋፈለ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ አብዛኛውን ጊዜ በነግህ ጸሎት የሚደርስ ነው፡፡ ገዳማውያን አባቶች በስፋት ይገለገሉበታል /ይጸልዩበታል/ በዚህ መጽሐፍ እምቅነት እና ይዘት የተደሰቱት ዐፄ ዳዊት መጽሐፉ በወርቅ ቀለም እንዲጻፍ አዘው እንደነበር ይነገራል፡፡
      ስለ አርጋኖን ድርሰቱ እንደሚከተለው በገድሉ ተጽፏል፡፡ ‹‹ወሰመዮ በሠለስቱ አስማት ዘውእቶሙ አርጋኖን ውዳሴ ወመሰንቆ መዝሙር ወእንዚራ ስብሐት፤ በሦስት ሰዎችም ሰየማቸው እነርሱም አርጋኖነ ውዳሴ፣ መሰንቆ መዝሙርና እንዚራ ስብሐት ይባላሉ፡፡›› ይህ አገላለጥ አርጋኖን አንድ ሆኖ ሦስት መድብሎች ያሉት እንደሆነ ያሳያል፡፡
      ለ. እንዚራ ስብሐት
      እንዚራ ስብሐት የተሰኘው መድብል ከአርጋኖን ጋር በአንድ ጥራዝ የተዘጋጀ ሲሆን ከ‹‹ሀ›› እስከ ‹‹ፓ›› ያሉትን ፊደላት በመክፈያነት በመጠቆም የተዘጋጀ ነው፡፡ ‹‹ወሰመዮ ሠለስቱ አስማት ዘውእቶሙ አርጋኖን ውዳሴ ወመሰንቆ መዝሙር ወእንዚራ፣ በሦስት ስሞች ሰየማቸው እነርሱም አርጋኖን ውዳሴ፣ መሰንቆ መዝሙርና እንዚራ ስብሐት ይባላሉ፡፡›› ይላል ገድሉ፡፡ ይህ አገላለጥ ሁለት ነገሮችን ይጭራል፡፡ አንደኛው ስለ አርጋኖን ይዘት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሊቁ በዝርውና በግጥም የሚደርሳቸው መጻሕፍት ከዜማ መሣሪያዎች ጋር ለማጣጣም ጥረት ማድረጉን ያመላክታል፡፡
      ሐ. ውዳሴ ሐዋርያት
      ይህን መጽሐፍ አባ ጊዮርጊስ በእስር ቤት ሳለ እንደጻፈው ይነገራል፡፡ በተለይ በወኅኒ ተጥሎ ሳለ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ እያመጡ ያጽናኑት ስለ ነበረ ‹‹ውዳሴ ሐዋርያት›› የሚለውን መጽሐፉን ስያሜ ከግብራቸው አያይዞ የሰጠው ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በሌላ አጠራሩ ገድሉ ይህን መጽሐፈ ፍጽሞ ብሎ እንደጠራው ይናገራል፡፡
      መ. ሕይወተ ማርያም
      ከሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬምና ከኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ ለጥቆ እንደ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በእመቤታችን ሕይወት ዙሪያ በስፋት የጻፈና የተቀኘ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ምንጮቻችንም አይጠቁሙም፡፡ በጥቅሉ ሕይወተ ማርያም ስለ ክብረ ድንግል ከቀደምት ነቢያት ትንቢትና ምሳሌ ጀምሮ እስከ ሐዋርያት ስብከት ድረስ የተጻፈ መጻሕፍትን መሠረት ያደረገና የሊቁ የጽሑፍ ክሂሎት የታየበት መጽሐፍ እንደ ሆነ ለመገመት አያዳግትም፡፡
      ሠ. ተአምኖ ቅዱሳን  
      የዚህም መጽሐፍ ቅጂ በአሁኑ ጊዜ አልተገኘም፡፡ ስለይዘቱ ግን ከስያሜው ተነሥቶ ግምት መስጠት ይቻላል፡፡ መጽሐፉ ‹‹ተአምኖ ቅዱሳን›› ተብሎ እንደመሰየሙ የቅዱሳንን የገድል እና የትሩፋት ሕይወት የሚያሳይ መሆኑን መጠቆም ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የሊቁ ሕይወት በገድልና በትሩፋት የተመላ እንደመሆኑ የሌሎችን ቅዱሳን ሕይወት ያሳየበት መጽሐፍ ሳይሆን አይቀርም፡፡
      ረ. ጸሎት ዘቤት ቤት
      ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነ አልአዛር በምእመናን ቤት በመገኘት ያስተምር እንደነበር ሐዋርያትም ይህንን አብነት አድርገው በምእመናን ቤት ትምህርትና ጸሎት ያደርጉ ነበር አባ ጊዮርጊስም ይህንን ትውፊት በመጠበቅ ካህናት በምእመናን ቤት ለማስተማርና ለማጥመቅ በሚዘዋወሩበት ጊዜ በምእመናን ቤት የሚጸልዩትን ጸሎት አዘጋጅቷል፡፡ ይህም መጽሐፍ ካህናት ለማጥመቅ ለማስተማር በሚዘዋወሩበት ጊዜ በየሰዓቱ የሚጸልዩት እና በምእመናን ቤት የሚያደርሱት የጸሎት መጽሐፍ ሊሆን እንደሚችል ከስያሜው ተነሥቶ መገመት ይቻላል፡፡
      ሰ. ፍካሬ ሃይማኖት
      ገድሉ ላይ እንደተጻፈውና ከመጽሐፉ ስም መረዳት እንደሚቻለው ይህ መጽሐፍ የተዘጋጀው የዐፄ ዳዊት ጦር አዛዥ የነበረው ቴዎድሮስ ስለ ቀናች ሃይማኖት /ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ/ በጠየቀው ጊዜ መልስ ይሆን ዘንድ የጻፈው መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ንጉሡን ዐፄ ዳዊትን በዘመኑ የነበሩትን ሊቃውንት እጅግ ማስደሰቱን ከገድሉ መረዳት ይቻላል፡፡
      ሸ. ሰዓታት ዘመዓልት ወዘሌሊት
      መጽሐፈ ሰዓታት ከስያሜው መረዳት እንደሚቻለው የሌሊት ምስጋና የቀን ምስጋና ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ሌላኛው ስሙ ‹‹መጽሐፈ ስብሐት›› እንደሚባል በሊቁ ሥራ ላይ ጥናት ያደረጉት ዶ/ር ሥርገው ሀብተ ሥላሴ ያስረዳሉ፡፡ በብራና ላይ በሚገኙ ቅጂዎች ደግሞ ‹‹መዝሙር›› እየተባለ ይጠራል፡፡ መጽሐፈ ሰዓታት የተባለበት ምክንያት በየሰዓቱ የሚጸለይ ምስጋና የያዘ በመሆኑ ነው፡፡
      ቀ. ቅዳሴያት
      አባ ጊዮርጊስ እመቤታችን ልጇን ይዛ ወደ ግብፅ በተሰደደች ጊዜ በወርኀ ጽጌ የሚቀደስ የእመቤታችንን ቅዳሴ መድረሱ ይነገራል፡፡ ይህ ቅዳሴ በወርኀ ጽጌ በአንዳንድ ገዳማት ይቀደሳል፡፡ ሌሎችም ያልታተሙ ወይም በብራና የተዘጋጁ ስድስት የቅዳሴ ቅጂዎች እንዳሉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትውፊትና መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ጥናት ያደረጉ ስዊዛዊቷ ክርስቲን ሻዮ ያስረዳሉ፡፡
      በ. ውዳሴ መስቀል
      በመጽሐፉ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን እንደሚያስረዱት መጽሐፉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ መስቀልን የሚያወድስ ነው፡፡ የአጻጻፍ ስልቱም ከሊቁ ሌሎች ሥራዎች ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ አለው፡፡
      ተ. ኆኅተ ብርሃን
      በዚህ መጽሐፍ አባ ጊዮርጊስ የመጽሐፍ ቅዱስ ምጡቅ ዕውቀቱ እንዳንጸባረቀበት ከሥራው መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ትንቢተ ሕዝቅኤልን መሠረት አድርጎ ‹‹ርኢኩ ኆኅተ በምሥራቅ ኅቱም፤ በምሥራቅ የተዘጋ በር አየሁ›› ‹‹ኆኅትሰ ድንግል ይእቲ እንተ ወለደት ለነ መድኅነ፤ ደጂም መድኅንን የወለደችልን ድንግል ማርያም ናት›› ብሎ እንዳመሰገነ አባ ጊዮርጊስም በጠቀሰው ሊቅ አደራረስ መሠረት ለድንግል ማርያም አጠር ያለ ውዳሴ ያቀረበበት መጽሐፍ ነው፡፡
      ይህ መጽሐፍ በሰባት ዕለታት የተከፋፈለ ነው፡፡ በይዘቱም ከውዳሴ ማርያም አንቀጸ ብርሃንና ቅዳሴ ማርያም ጋር ይዛመዳል፡፡
      ቸ. መጽሐፈ ብርሃን
      አባ ጊዮርጊስ ይህን መጽሐፍ የእግዚአብሔርን መንገድ እና ክብረ ድንግልና ለመግለጽ ያዘጋጀው መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ ‹‹መጽሐፈ ብርሃን›› ብሎ የሰየመበትን ምክንያት በገድሉ ላይ በዚህ መልኩ ተጽፎ ይነበባል፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር የምስጋናውን መንገድ አብርቶ ያመለክታልና የእመቤታችንንም የምስጋናዋን ጣዕም ይገልጣልና ›› ይላል፡፡ ከእርሱ በኋላ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ በዘመኑ ሥር ሰዶ የነበረውን ባዕድ አምልኮ /አጉል እምነት/ ለመዋጋት ያዘጋጀው መጽሐፍም ‹‹መጽሐፈ ብርሃን›› የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
      ነ. መጽሐፈ ምሥጢር
      ይህ መጽሐፍ የአባ ጊዮርጊስ የነገረ ሃይማኖት ዕውቀት በስፋትና በጥልቀት የተንጸባረቀበት መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፈ ምሥጢር የትርጓሜ ዕውቀቱ መለኪያ ነው የሚሉም አሉ፡፡ መጽሐፉን ኢትዮጵያዊ ትምህርተ ሃይማኖት የተንጸባረቀበትና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ጥበብ ብለውታል፡፡
ምንጭ ፡- መጽሐፈ ምሥጢር
ደራሲ፡- አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages