ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር10 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር10

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር አስር በዚህች እለት #የገሃድ_ጾም ነው፣ የከበረ አባት #አባ_ታውብንጦስ_ዘሲሐት ዕረፍቱ ነው፡፡


ጥር አስር በዚህች ዕለት ምንም ምን መብልን ሰይቀምሱ ምእመናን ሁሉ እስከ ምሽት ይጾሙ ዘንድ ከእኛ አስቀድመው የነበሩ ታላላቅ ሊቃውንት የቤተ ክርስቲያን መምህራን ሥርዓትን ሠሩ በምሽትም ቢሆን በታላቁ ጾም ከሚበላው በቀር ጥሉላትን እንዳይቀምሱ። በዚች ዕለት ምእመናን እስከ ምሽት እንደመጾሙን ያዘዙበት ምክንያቱ ይህ ነው የልደትና የጥምቀት በዓል በዓል በረቡዕ ወይም በዓርብ ቀን ቢሆን በበዓለ ኃምሳ የሚበላውን የጥሉላት መብል በጥዋት በመብላት ምእመናን ሁሉ በዓሉን እንዲአከብሩ የከበሩ አባቶቻችን ሐዋርያት አዝዘዋል እሊህ ሁለቱ የእግዚአብሔር ታላላቅ በዓላቶቹ ናቸውና።
እኛ በዚህ በኅላፊው ዓለም ተድላ ደስታ ደስ የሚለን ለሌሎች እንዳይመስላቸው እንደ አይሁድና እንደ አረማውያን በዓል በመብልና በመጠጥ ብቻ እንዳናደርግ ስለዚህ ከልደትና ከጥምቀት በዓል በዋዜማ ያሉትን ሁለቱን ዕለታት እንድንጾም አዘዙን የልደትና የጥምቀት በዓል በረቡዕና በዓርብ ላይ በሚሆን ጊዜ በረቡዕና በዓርብ ፈንታ እንድንጾማቸው ይገባልና በዚህም ሁለት ሥራ ይፈጸምልናል የጾም ሥራና የበዓል ማክበር ሥራ ነው። እንዲሁም በግብፃውያን አብያተ ክርስቲያን የተሠራ ነው።
በይረሙን በእሑድ ወይም በአይሁድ ሰንበት ቀን ቢሆን ይህም ጌታ የተገለጸበት ጥር ዐሥራ ቀን ነው በዋዜማው ዐርብ እስከ ምሽት ይጹሙ አስቀድመን እንደተናገርን ጥሉላት አይብሉ የልደትና የጥምቀት በዓልም ሰኞ ቀን ቢሆን በሰንበት ቀን ይጾም ዘንድ አይቻልም ነገር ግን ጥሉላትን ከመብላት ይጠበቁ።
በጥምቀትም ዕለት ከእኵለ ሌሊት በፊት ተነሥተው በውኃው ላይ ይጸልዩና ይጠመቁ ሕፃናትም በሚጠመቁ ጊዜ በውኃ እንዳይገድፉ ካህናቱም ከመንጋቱ በፊት ቀድሰው ቊርባኑን ያሳርጉ እጅግም ማልደው በጥዋት ከቤተ ክርስቲያን ይውጡ በከበረ ሥርዓታቸው ጌቶቻችን ሐዋርያት እንዳዘዙ።
የመለካውያን ወገኖች ግን የልደትና የጥምቀት ዋዜማ በቅዳሜ ቀን ወይም በእሑድ ቀን ቢሆን በሦስት ሰዓት ይቀድሳሉ ከወደዱም የተባረከ ኅብስት ተመግበው ውኃ ይጠጣሉ ከዚህም በኋላ ካህናቱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁነው በየሰዓቱ በመጸለይ ለበዓሉ የሚገባውን የነቢያትን ትንቢቶች ያነባሉ በዚያች ቀን በምሽት ይኸውም ጥር ዐሥር ነው በውኃው ላይ ይጸልያሉ ይህም አባቶቻችን ሐዋርያት እንዳዘዙት አልሆነም። እርሳቸው የኤጲፋንያን በዓል እንዲአክብሩ አዘዋል ይኸውም መድኃኒታችን የተገለጠበት ካኑን በሚባል በሮም ሁለተኛ ወር በሰባት ይህም ጥር ዐሥራ አንድ ቀን ነው።
መለካውያን ግን የከበሩ አባቶች የቤተ ክርስቲያን መምህራን ያዘዙትን ይተላለፋሉ በልደትና በጥምቀት በዓል ዓርብም ረቡዕም ቢሆን አስቀድመው በርሱ ፈንታ ሳይጾሙ በጥዋት ተነሥተው ይበላሉና። እኛንም ከበደላችን ያነጻን ዘንድ በዮርዳኖስም ወንዝ እንደ ተገለጸ የጌትነቱን ክብር በልቡናችን ይገልጥልን ዘንድ የክብር ባለቤት የሆነ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው ጌትነት ክብር ስግደት ለእርሱ ይገባልና ከቸር አባቱ ጋር ይቅር ባይ ከሆነ መንፈስ ቅዱስም ጋር ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት አባ ታውብንጦስ አረፈ፡፡ ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ አባ ታኡና በሚባል በሮሜው ሊቀ ጳጳሳት ቤት አደገ እርሱም የምንኵስናን ልብስ አለበሰው። መንፈሳዊ ዕውቀትና ኃይል እንደተሰጠው አይቶ ከእስክንድርያ አገር ውጭ ስሙ ጤናዲራን በሚባል ቦታ ኤጲስቆጶስነት ሹሞ የገዳም አበ ምኔት አደረገው ከእርሱ ሥር ያሉ መነኰሳትም ሰባት መቶ ናቸው።
ከዚህም በኋላ ከእርሱ ጋር ላሉ መነኰሳት አለቃ የሆነ ኤጲስቆጶስ ታውብንጦስ ከከሀዲ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ስለሆነው ሁከት በሰማ ጊዜ ሸሽቶ ወደ ደብረ ሲሐት ገዳም ሒዶ እግዚአብሔርን ከምትፈራ ከአንዲት ድንግል ዘንድ ተቀመጠ። በእርሷ ቤትም ብዙ ዘመናት ኖረ በመጀመሪያ ወደርሷ በገባ ጊዜ ግን ንጉሡን ስለ መፍራት ጣዖትን ስታመልክ አገኛትና የክብር ባለቤት ጌታችን ክርስቶስን ወደ ማመን መለሳት።
ከዚያም ተርኑጥና መርኑስ ወደ ሚባሉ ገዳማት ሔደ የአብያተ ክርስቲያናትን ወሬ ይሰማ ዘንድ ፈልጎ በጾም በጸሎት ሌሊትም በመትጋት እያገለገለ በአንዲት ገዳም ውስጥ ሁለት ሦስት ቀን ተሠውሮ ያድር ነበር። የመንፈስ ቅዱስም ጸጋ በላዩ እንዳደረ እግዚአብሔርም በእጆቹ ድንቆች ተአምራቶችን እንዳደረገ ከወንበዴዎችና ከዓመፀኞች ብዙዎችን መነኰሳትን አድርጎ ለክርስቶስ ወደ መገዛት እስከ መላሳቸው ድረስ መነኰሳቱ ሁሉ መሰከሩለት።
ከዚህም በኋላ ፈጽሞ በአረጀ ጊዜ የሚሞትበትን ቀን ዐወቀ ልጆቹንም የክርስቶስ በሆነች በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ ትእዛዙንም እንዲጠብቁ አስተማራቸው ወዲያውኑ በሰላም ዐረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages