ፍልሰታ ለማርያም፤
“ፍልሰታ” የሚለው ቃል ፈለሰ - ተሰደደ(ተገለጠ)፣ መከፈት፣ መገለጥ፣ የመዝጊያ የመጋረጃ ከሚለው የግእዝ ስርወ ቃል የተገኘ ሲሆን የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤ ያመለከታል፡፡
“ፍልሰት” የሚለው ቃል ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር መሔድን ያመለክታል፡፡“ፍልሰታ ለማርያም”ሲል ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መወሰዷን (ማረጓን)፥ በኋላም ሥጋዋ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትውፊትና ቀኖና መሠረት ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንደኛው ጾመ ፍልሰታ ለማርያም ነው። በመሆኑም ከሕጻናት ጀምሮ እስከ አረጋውያን የሚጾሙት ታላቅ ጾም ነው፡፡
እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት በእናት በአባቷ ቤት፥ዐሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ፥ዘጠኝ ወር በቤተ ዮሴፍ፥ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር፥ዐሥራ አምሰት ዓመት በወንጌላዊው በዮሐንስ ቤት ከኖረች በኋላ በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን ዐርፋለች፡፡ቅዱሳን ሐዋርያትም ሊቀብሯት ወደ ጌቴሴማኒ ሲወሰዷት አይሁድ “እርሷንም ቀብረው እንደ ልጇ ተነሣች ብለው እንዳያውኩን፤” በሚል መንፈስ፥በታወፋንያ መሪነት አስከሬኗን ነጥቀው ለማቃጠል ሲታገሉ መልአከ እግዚአብሔር ወርዶ የመሪውን እጆች ቆረጠው።እርሷንም መላእክት ወደ ገነት አሳርገው ከዕፀ ሕይወት ስር አኖሯት።
ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችን ካረፈችበት ከጥር ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ ድረስ ስለ እርሷ ከመጸለይ ባያቋርጡም ከሰው ተለይተው፥ሱባዔ ገብተው፥ጾም ጸሎት የጀመሩት ግን ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምሮ ነው፡፡ሁለት ሱባኤ እንደ ጾሙም ነሐሴ ፲፬ ቀን የእመቤታችን ሥጋ ተሰጥቷቸው በክብር ገንዘው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡በሦስተኛውም ቀን ነሐሴ ፲፮ ቀን ከሙታን ተለይታ በመነሣት ወደ ሰማይ ዐርጋለች።ይኸንንም ቅዱስ ኤፍሬም “ተንሥአት እሙታን፥ማርያም ድንግል፥ከመ ትንሣኤ ወልዳ ዘልዑል፤እንደ ልጇ ትንሣኤ ባለ ትንሣኤ ተነሣች፤” በማለት መስክሯል። ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በመዝሙሩ “ተለዐለት እምድር፥ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ፥በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ፤ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ዐረገች፡፡ በሰማይም ከልጅዋ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች” በማለት ወደ ሰማይ ማረጓንና በክብር መቀመጧን ተናግሯል፡፡ይህ ከመሆኑ ከሺሕ ዓመት በፊትም አባቷ ቅዱስ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” ሲል የተናገረው ትንቢት ይህንኑ የእመቤታችንን ክብር የሚያመለከት ነበር።መዝ፡፵፬፥ ፱፡፡ቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችንን ሥጋ ቀበሩ እንጂ ለጊዜው ትንሣኤዋን ዕርገቷን አላዩም ነበር።
የእመቤታችን ትንሣኤ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤” ያሰኘው:-ልጇ ወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ሞቶ ከተነሣ በኋላ ዳግም ሞት እንደማይገዛው እርሷም እንደዚሁ ሁለተኛ ስለማትሞት ነው። የተነሣችው የክብርና የሕይወት ትንሣኤ ነውና። ሌሎቹ ግን ለምሳሌ አልዓዛር ሞቶ ቢነሣም ሁለተኛ ሞቶ ትንሣኤ ዘጉባኤን እየጠበቀ ነው።ከዐይነ ሞት የተሰወረ ሄኖክና ያረገ ኤልያስም በዓለም መጨረሻ መጥተው፥ሃይማኖታቸውን መስከረው፥በሰማዕትነት ካረፉ በኋላ ትንሣኤ ዘለክብር ይነሣሉ።
ከሐዋርያት ቅዱስ ቶማስ በእመቤታችን ሥርዓተ ቀብር ላይ አልነበረም።ወንጌለ መንግስትን ሲሰብክ ቆይቶ፥ደመና ጠቅሶ፥ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ በጠፈረ ሰማይ ላይ አገኛት፡፡በዚህን ጊዜ “ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ፥ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፤”ብሎ በኀዘን ከደመናው ይወድቅ ዘንድ ወደደ፡፡“ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ፤”ይላል፡፡ እመቤታችንም:-“አይዞህ! አትዘን፥ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን እና ዕርገቴን አንተ አይተሃልና ደስ ይበልህ!”ብላ ለበረከት ሰበኗን ሰጠችው።
ቅዱስ ቶማስ ትእዛዟን ተቀብሎ በክብር ከተሰናበታት በኋላ በደመና እንደ ተጫነ ኢየሩሳሌም ደረሰ።ከዚያም ምንም እንዳልሰማና እንዳላየ መስሎ “ኧረ የእመቤታችን ነገር እንደምን ኾነ?”ሲል ሐዋርያትን ጠየቃቸው፡፡እነርሱም “አግኝተን ቀበርናት፤”ሲሉት “አይደረግም፥ሞት በጥር፥በነሐሴ መቃብር እንደምን ይሆናል?” አላቸው፡፡በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ:-“ከአሁን በፊት ክርስቶስ ተነሣ ብንልህ ተጠራጠርክ፤አሁን ደግሞ የእመቤታችንን ሥጋ አግኝተን ቀበርን ስንልህ ደገምከው፤”አለው። ቀጥሎም ለማሳየት መቃብሯን ቢከፍት የለችም። በዚህን ጊዜ ደንግጦ ቆመ።ቶማስም:-“ወንድሞቼ! አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ፤”ብሎ “ለምልክት ይሁንህ፤”ብላ የሰጠችውን ሰበን አሳያቸው።ይኸውም የመግነዟ ጨርቅ ነው።
በመልክዓ ማርያም ላይ “ሰላም ለግንዘተ ሥጋኪ በእደ ሐዋርያት አርጋብ፣ በአፈወ ዕፍረት ቅድው ዘአሣበ ሤጡ ዕፁብ…እመቤቴ ማርያም ሆይ ዋጋው እጅግ ብዙ በሆነና መዓዛው በሚጣፍጥ ሽቱ በሐዋርያት እጅ ለተገነዘው ንጹሕ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡”የሚል አለ።ይኸንንም ለበረከት ዐሥራ ሁለት ቦታ ተከፋፍለውታል።በእርሱም ሕሙማንን ሲፈውሱበት ኑረዋል።
ከዚህ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት “ትንሣኤዋን፥ ዕርገቷን ቶማስ ብቻ አይቶ እኛ እንዴት ይቀርብናል፤”በሚል መንፈሳዊ ቅናት ተነሣሥተው በዓመቱ ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፮ ሱባኤ ገቡ።ጌታም እመቤታችንን ይዞ ከቅዱሳን መላእክትና ከቅዱሳን ጋር ወረደላቸው።ሊቀ ካህናት በመሆኑ እርሷን መንበር አድርጎ ቀደሰ።ቅዱስ ጴጥሮስ ተራዳኢ ካህን፥ቅዱስ እስጢፋኖስ ደግሞ ሠራዒ ዲያቆን ነበሩ።”ወተቄረበት በዕደ ወልዳ፤”እንዲል እመቤታችን በልጇ እጅ ቆረበች። ቅዱሳን ሐዋርያትም ቆረቡ።ከዚህ በኋላ በይባቤ መላእክት ከልጇ ከወዳጇ ጋር እያዩአት ዐረገች። የፍልሰታ ለማርያም ታሪክ በአጭሩ ይህ ነው።በረከተ ፍልሰቷን ታሳድርብን።ፍልሰተ ሥጋዋን በተመለከተ የመልክአ ማርያም ደራሲ “ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ ደባትረ ብርሃን ኀበ ተተክሉ፤ ለገነተ ጽባሕ በማዕከሉ ፤እመቤቴ ማርያም ሆይ! በምስራቃዊ ተክለ ገነት መካከል የብርሃን ድንኳኖች ወደ ተተከሉበት ለዐረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል፤”ብሏል።
በጾመ ፍልሰታ ወቅት በቤተክርስቲያናችን በየቀኑ በማኅሌቱ፥በሰዓታቱና በቅዳሴው በሚደርሰው ቃለ እግዚአብሔር ነገረ ማርያም በምልዐት ይነገራል። ከተነገረላት ትንቢትና ከተመሰለላት ምሳሌ ጀምሮ ከፅንሰቷ እስከ ዕርገቷ ድረስ ይተረካል።ለአምላክ ማደሪያነት ስለ መመረጧ፥ንጽሕናዋ፥ቅድስናዋ፥ ድንግልናዋ፥ክብሯ፥ርኅርራኄዋ፥ደግነቷ፥አማላጅነቷ፥ ሰውን መውደዷ በስፋት ይሰበካል፡፡እመቤታችንን ከሚያወድሱ ድርሳናት መካከል በተለይም ምሥጢረ ሥላሴን፥ምሥጢረ ሥጋዌንና ነገረ ድኅነትን ከነገረ ማርያም ጋር በማዛመድ የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም፤ እንደዚሁም ነገረ ድኅነትን ከነገረ ማርያም ጋር አዋህዶ የሚያስገነዝበው ውዳሴ ማርያምም በስፋት ይጸለያል፥ይቀደሳል፥ይተረጐማል፡፡
በሰንበታት የሚዘመሩ የቅዱስ ያሬድ መዝሙራት ፥በየዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ለተዋሕዶ መመረጧን፥ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፥ክብሯን፣ ቅድስናዋን፥ንጽሕናዋን የሚያወሱ ናቸው፡፡ የእመቤታችን ንጽሕና የነገረ ድኅነት፥የጌታችን ቤዛነት መነሻ መሠረት ነውና፡፡ቅዱስ ኤፍሬም “አክሊለ ምክሕነ፥ወጥንተ መድኃኒትነ፥ወመሠረተ ንጽሕነ፤መመኪያ ዘውዳችን፥ጥንተ መድኃኒታችን፥ የንጽሕናችን መሠረት፤”ያላት ለዚህ ነው።በረከተ ትንሣኤዋን፥ በረከተ ዕርገቷን ያሳድርብን።በዓሉንም በዓለ ፍስሐ ወሐሴት ያድርግልን።

No comments:
Post a Comment