እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አባ አጋቶን ወአቡነ ያሳይ ዘመንዳባ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
አባ አጋቶን ዘዓምድ
ታላቁ ጻድቅ በትውልድ ግብጻዊ ሲሆኑ የነበሩበት ዘመንም ከ4ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ እስከ 5ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ አካባቢ ነው:: በእርግጥ 'አጋቶን ' በሚባል ስም የሚጠሩ ብዙ አበው አሉ:: ቅድሚያውን 2ቱ ይወስዳሉ::
አንደኛው አባ አጋቶን ለ30 ዓመታት ድንጋይ ጐርሰው የኖሩት አባት ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ ዛሬ የምናከብራቸው ናቸው:: እኒህኛው 'ዘዓምድ ' ይባላሉ:: ምክንያቱም ለ50 ዓመታት አንድ ምሰሶ ላይ ያለ ዕረፍት ጸልየዋልና ነው::
አባ አጋቶን ገና ከልጅነታቸው መጻሕፍትን የተማሩ ሲሆኑ ምናኔን አጥብቀው ይፈልጓት ነበር:: በዚህም ራሳቸውን በትሕርምት እየገዙ: በዲቁና ማዕርጋቸውም እያገለገሉ እስከ 35ዓመታቸው ቆዩ:: በዚህ ጊዜ ደግሞ 'ይገባሃል' ብለው ቅስናን ሾሟቸው::
የማታ ማታ የለመኑትን የማይነሳ ጌታ ተምኔተ ልባቸውን ፈጽሞላቸው ወደ በርሃ ሔዱ:: ወቅቱ የግብጽ ገዳማት በቅዱሳን ሕይወት የበሩበት ነውና እዚህም እዚያም አበውና እናቶች ይገኙ ነበር::
አባ አጋቶንም የከዋክብቱ አበው አባ ገዐርጊና አባ አብርሃም ደቀ መዝሙር ሆነው ገቡ:: አስፈላጊውን የምንኩስና ፈተና ካለፉ በኋላም ምንኩስናን ከእነዚህ አባቶች ተቀበሉ:: በዚያው በገዳመ አስቄጥስ በጽኑ ገድል ተጠምደው ለ15 ዓመታት አገለገሉ::
ጻድቁ ከእርሳቸው በፊት የነበሩ ቅዱሳንን ተጋድሎ ጠዋት ማታእያነበቡ መንፈሳዊ ቅናትን ይቀኑ ነበር:: በተለይ የታላቁን ስምዖን ዘዓምድን ገድል ሲያነቡ ሕሊናቸውን ደስ ይለው: ይህንኑ ገድል ይመኙ ነበር:: እድሜአቸው 50 ዓመት በሞላ ጊዜ በልቡናቸው እንደ አባ ስምዖን ዘዓምድ ለመጋደል ወሰኑ:: ይህን ለገዳሙ አባቶች ቢያማክሯቸው አበው:- "ይበል! ሸጋ ምክር ነው:: እግዚአብሔር ያስፈጽምህ!" ብለው መርቀው አሰናበቷቸው:: አባ አጋቶን የዳዊትን መዝሙር እየዘመሩ ከገዳሙ ወጡ:: በጣምም ወደ ዓለም ሳይገቡ: ከዓለም (ከከተማም) በጣም ሳይርቁ አንድ ረዥም ምሰሶ አገኙና ከላዩ ላይ ወጡ::
ከዚህች ዕለት ጀምረው ጻድቁ ለ50 ዓመታት ከዚያች ዓምድ (ምሰሶ) ወርደው: ለሥጋቸውም ዕረፍትን ሰጥተውት አያውቁም:: ማዕከለ ገዳም ወዓለም ናቸውና ለምዕመናንም ሆነ ለመነኮሳት አጽናኝ አባት ሆኑ:: ለአካባቢውም የብርሃን ምሰሶ ሆኑ:: የታመመ ቢኖር ይፈውሱታል:: የበደለውን በንስሃ ይመልሱታል:: ሰይጣን የቋጠረውን ይፈቱታል:: ለራሳቸው ግን ከጸሎት: ከጾምና ከትሕርምት በቀር ምንም አልነበራቸውም:: በተለይ እነዚህ ስራዎቻቸው ይዘከሩላቸዋል::
1.አጥማቂ ነን እያሉ ሕዝቡን ያስቱ የነበሩ ሰዎችን እየጠሩ እንዲህ የሚያስደርጋቸውን ጋኔን ከእነሱ አስወጥተዋል::
2.እርሳቸውን ያልሰሙት ግን መጨረሻቸው ጥፋት ሆኗል::
3.ፍጹም ወንጌልን በሕይወትና በአንደበት መስክረዋል::
4.ሕዝቡን በንስሃ አስጊጠዋል::
5.ተግሳጽ የሚገባውን ገስጸዋል::
ጻድቁ አባ አጋቶን ዘዓምድ ከእነዚህ የቅድስና ዘመናት በኋላበተወለዱ በ100 ዓመታቸው በዚህች ቀን ዐርፈው በክብርና በዝማሬ ተቀብረዋል::
አቡነ ያሳይ ዘመንዳባ
እኒህ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ በ14ኛው መቶ ክ/ዘ በጣና ገዳማትውስጥ ያበሩ ኮከብ ናቸው:: ከ7ቱ ከዋክብት (አባ ዮሐንስ፣ አባ ታዴዎስ፣ አባ ያፍቅረነ እግዚእ፣ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አባ ሳሙኤል ዘቆየጻና አባ ሳሙኤል ዘጣሬጣ ) እርሳቸው አንዱ ናቸው:: እነዚህ አበው ከገዳማዊ ሕይወታቸው ባሻገር በምስጉን የወንጌል አገልግሎታቸው የሚታወቁ ናቸው::
ገድላቸው እንደሚለው አቡነ ያሳይ የዐፄ ዐምደ ጽዮን ቀዳማዊ ልጅ ሲሆኑ የተወለዱትም በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ሽዋ: ተጉለት ውስጥ ነው:: ገና በልጅነታቸው ወደ አባታቸው ቤተ መንግስት የሚመጡ መነኮሳትን እግር እያጠቡ ሥርዓተ ምንኩስናን በድብቅ ያጠኑ ነበር::
ብሉይ ከሐዲስ የጠነቀቁ ናቸውና የአባታቸውን ዙፋን (ልዑልነት) ስለ ፍቅረ ክርስቶስ ንቀውት እየዘመሩ ጠፍተው ወደ ትግራይ ተጓዙ:: በዚህም ምክንያት 'መናኔ መንግስት' ይባላሉ:: በዚያም ወደ ደብረ በንኮል ገዳም ውስጥ ገብተው የታላቁ አባት የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ደቀ መዝሙር ሆኑ::
ቀደም ሲል የጠቀስናቸው 7ቱ አበው በዚያ ነበሩና 7ቱም በአንድ ቀን ሲመነኩሱ ገዳሙ የተቃጠለ እስኪመስል ድረስ ብርሃን ወርዶ ነበር:: አቡነ ያሳይ በረድእነት በቆዩበት ዘመን ዛፎችን መትከል ይወዱ ነበር:: ከትሩፋት መልስም በልብሳቸው ውሃ እየቀዱ ያጠጡ ነበር:: በተለይ "ምዕራገ ጸሎት" የሚባለው ተአምረኛ ዛፍ ዛሬ ድረስ አለ ይባላል::
አቡነ ያሳይ ጊዜው በደረሰ ሰዓት ከአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ተባርከው: ከ2ቱ ባልንጀሮቻቸው (አቡነ ሳሙኤል ዘዋሊና አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ) ጋር ወደ ጣና ሐይቅ መጡ:: በዚያም አካባቢ ተአምራትን እየሠሩ ሕዝቡንም እያስተማሩ ከቆዩ በኋላ ጌታ ወደየፈቀደላቸው ቦታ ተለያዩ::
አቡነ ሳሙኤል ወደ ዋልድባ: አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ወደ ገሊላ: ከዚያ ወደ ጉጉቤ ሲሔዱ አቡነ ያሳይ መንዳባ ውስጥ ገቡ:: ጻድቁ ወደ አርባ ምንጭ ሒደው ታቦተ መድኃኔ ዓለምን ይዘው ሲመጡ ጣናን የሚሻገሩበት አጡ:: ጌታን ቢማጸኑት:- "ምነው እሷን ድንጋይ ባርከህ አትቀመጥባትም?" አላቸው:: እሳቸውም በእምነት: ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ጣናን ተሻገሩት:: ይህንን ከርቀት ያዩ የዘመኑ ሰዎች "ብዙ ተአምር አይተናል: ነገር ግን ማን እንደ አባ! ጣናን በድንጋይ የተሻገረ" ሲሉ አድንቀዋቸዋል::
ጻድቁ ጣናን ተሻግረው: ገዳም መሥርተው: ብዙ አርድእትን አፍርተው: በተጋድሎ ሕይወታቸው ቀጥለዋል:: በተለይ ዛሬ ድረስ የሚተረከው የ'አትማረኝ' ታሪክም የሚገኘው እዚሁ ገዳም ውስጥ ነው:: ታሪኩም በየዋህነት "አትማረኝ" ብለው ጸልየው ጣናን ያለ ታንኳ በእግራቸው የረገጡ አባትን የሚመለከት ሲሆን ከአቡነ ያሳይ ጋርም ወዳጅ ነበሩ::
አባታችን አቡነ ያሳይ ለዘመናት በቅድስና ኑረው: ቅዱሳንንም ወልደው መስከረም 14 ቀን ታመሙ:: "ጌታ ሆይ!" ብለው ቢጠሩት መድኃኔ ዓለም መጣላቸው:: ጣና በብርሃን ተከበበች:: ጌታም "ወዳጄ! ስለ ድካምህ: ደጅህን የረገጠውን: መታሰቢያህን ያደረገውን: በስምህ የተማጸነውን ሁሉ ከነትውልዱ እምርልሃለሁ" ብሏቸው ነፍሳቸውን አሳረገ:: አበውም ሥጋቸውን ገንዘው እዚያው መንዳባ መድኃኔ ዓለም ውስጥ ቀበሩት:: ዐጽማቸው ዛሬም ድረስ ይገኛል::
አምላከ ጻድቃን በምልጃቸው የበዛች ኃጢአታችንን ይቅር ይበለን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::
መስከረም 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ አጋቶን ዘዓምድ
2.አቡነ ያሳይ ዘመንዳባ
3.አባ ጴጥሮስ መምሕረ ጻና (ጣና)
4.ቅዱስ ዴግና ቀሲስ
††† ወርሐዊ በዓላት
1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
2.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
3.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
5.አባ ስምዖን ገዳማዊ
6.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
7.እናታችን ቅድስት ነሣሒት
"ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል:: ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል:: ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላቹሃለሁ ዋጋው አይጠፋበትም::"
(ማቴ. ፲፥፵፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment