❖ ይኽ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ የአባቱ ስም ቊንስጣ የእናቱ ስም እሌኒ ነው፤ ከሓዲው መክስምያኖስ በሮሜ በአንጾኪያ እና በግብጽ ነግሦ በነበረ ጊዜ አባቱ በራንጥያ ለሚባል ሀገር ንጉሥ ነበር፤ እሌኒ ከርሱ ቆስጠንጢኖስ ከወለደችው በኋላ አባቱ ቊንስጣ እነርሱን ሮሐ (ሶርያ) ላይ ትቷቸው ወደ በራንጥያ ተመለሰ፡፡ “ወይእቲ ነበረት እንዘ ተሐጽኖ ለወልዳ ወመሀረቶ ትምህርተ ክርስትና ወኮነት ዘትዘርዕ ውስተ ልቡ ምሕረተ ወሣሕለ ላዕለ ሕዝበ ክርስቲያን” ይላል፤ ርሷም ልጇን የክርስትና ትምህርትን አስተማረችው፤ ይቅርታንና ርኅራኄን በክርስቲያን ወገኖች ላይ እንዲያደርግ በልቡናው መልካም ዘርን ትዘራበት ነበር፡፡
❖ ከዚያም ቈስጠንጢኖስ አካለ መጠን ሲያደርስ ወደ አባቱ ሰደደችው፤ አባቱም የጥበቡን ብዛት አይቶ በመደሰት ከበታቹ መስፍን አድርጎት በመሾም በመንግሥቱ ሥራ ላይ ኹሉ ሥልጣንን ሰጥቶታል፤ “ወእምድኅረ ክልኤቱ ዓመት አዕረፈ አቡሁ ወተመጠወ ቈስጠንጢኖስ ኲሎ መንግሥተ ወገብረ ፍትሐ ርቱዐ” ይላል፤ ከኹለት ዓመት በኋላ አባቱ በማረፉ ቈስጠንጢኖስ መንግሥቱን ኹሉ ተረክቦ የቀና ፍርድን የሚፈርድ ኾነ፤ ከርሱ በፊት የነበሩ ነገሥታት የጫኑባቸውን ጽኑ አገዛዝ ከሰዎች ላይ የሚያስወግድ ኾነ፤ በዚኽ ምክንያት ኹሉም ወደደው፤ ዝናውም በብዙ ሀገሮች ላይ ተሰማለት፡፡
❖ በአንጾኪያ ያሉ ክርስቲያኖችም የቈስጠንጢኖስን ፍርድ መጠንቀቁን፣ ድኻ መጠበቁን እየሰሙ ከከሓዲው ከመክስምያኖስ አገዛዝ እንዲያድናቸው የልብሰ ተክህኖውን ቅዳጅ፣ የመስቀሉን ስባሪ ይልኩለት ነበር፤ ርሱም ስለደረሰባቸው መከራ በእጅጉ እያዘነ እንዴት አድርጎ እንደሚያድናቸው ያስብ ነበር፤ “ወእንዘ ይነብር ውስተ ዐውድ ወናሁ አስተርአዮ በመንፈቀ መዓልት መስቀል ዘሕብሩ አምሳለ ከዋክብት ወዲቤሁ ጽሑፍ በልሳነ ዮናኒ ኒኮስጣጣን ዘበትርጓሜሁ በዝንቱ ትመውዕ ጸረከ ወአንከረ ብርሃኖ ለመስቀል ሶበ ርእየ እንዘ ይከድኖ ለብርሃነ ፀሓይ” ይላል ከዕለታት ባንዳቸው በአደባባይ በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ከቀኑ በስድስት ሰዓት ጊዜ ሕብሩ እንደከዋክብት የኾነ መስቀል በጸፍጸፈ ሰማይ ላይ ሲታየው፤ በላዩም በዮናኒ ቋንቋ ኒኮስጣጣን የሚል ጽሑፍ ነበረው፤ ትርጓሜውም በዚኽ ጠላትኽን ድል ታደርጋለኽ ማለት ሲኾን፤ ርሱም የመስቀሉ ብርሃን የፀሓይን ብርሃን ሲሸፍነው አይቶ ተደንቋል፡፡
❖ ይኽነንም ያየውን ለሊቃውንቱ በጠየቃቸው ጊዜ አውስግንዮስ የሚባል ሕጽው በዚኽ መስቀል አምሳል ጠላትኽን ድል ታደርጋለኽ ማለት ነው ብሎ ተረጐመለት፤ መልአኩም ሌሊት በራእይ ታይቶት አስረዳው፤ “ወነቂሆ እምንዋሙ ጸንዐ ልቡ ወገብረ መስቀለ ዘወርቅ ወረሰዮ መልዕልተ አክሊለ መንግሥቱ ወአዘዞሙ ለኲሎሙ መኳንንቲሁ ወሐራሁ ከመ ይግበሩ መስቀለ በኲሉ ንዋየ ሐቅሎሙ” እንዲል ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ልቡ ጸናና የወርቅ መስቀልም አሠርቶ በነገሠበት ዘውድ ላይ አደረገው፤ መኳንንቱንና ወታደሮቹን ኹሉ መስቀል አሠርተው በጦር መሣሪያቸው ላይ ያደርጉ ዘንድ አዘዛቸውና እንዳላቸው አደረጉ፡፡
❖ ከዚያም በክርስቲያኖች ጠላት በከሓዲው መክስምያኖስ ላይ ዘመተበት፤ ከዚያም መክስምያኖስ ሰምቶ ጦሩን ይዞ መጣበት፤ በመክስምያኖስ ጦር ላይ ዐድረው ድል ያደርጉ የነበሩ አጋንንት በቈስጠንጢኖስ ጦር ላይ ያለውን ትእምርተ መስቀል ባዩ ጊዜ ተለይተውት በኼዱ ጊዜ ድል ተነሣ፤ ርሱም ከጥቂቶች ጋር ራሱን ለማዳን “ወተጽዕኑ ዲበ ተንከተም ወተንከተምኒ ንህለ ወተሠጥመ መክስምያኖስ ምስለ ሰራዊቱ” ይላል ወደ ሮሜ ለመሻገር በድልድይ ላይ ሲወጡ ድልድዩ ፈርሶ ከሰራዊቱ ጋር ሰጥሟል፡፡
❖ ከዚያም በድል አድራጊነት ንጉሥ ቈስንጢኖስ ወደ ሮሜ በገባ ጊዜ ካህናቱ ሕዝቡ መብራት ይዘው፤ “መስቀል ኀይልን መስቀል ጽንዕነ መስቀል መዋዔ ጸር” እያሉ እየዘመሩ ተቀበሉት፤ ርሱም እናቱ ቅድስት እሌኒ እያስተማረች ያሳደገችው፤ በኋላም ምእመናን ይልኩለት የነበረው፤ በሰሌዳ ሰማይ ላይ የተመለከተው፤ አኹንም በአንጾኪያ ምእመናን ይዘው የተቀበሉትን አይቶ ትክክለኛውን ሃይማኖት በመረዳት ከሀገሩ ሶልጴጥሮስን አምጥቶ ተጠምቋል፡፡
❖ ከዚያም ዐዋጁን ባዋጅ በመመለስ “አብያተ ጣዖታት ይትዐጸዋ አብያተ ክርስቲያናት ይትረኀዋ” (አብያተ ጣዖታት ይዘጉ አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ) የሚል ታላቅ ትእዛዝን አዘዘ፤ የጌታችንንም መስቀል እንድታወጣ እናቱ እሌኒን ወደ ኢየሩሳሌም ላካት፨
❖ ይኽስ እንደምንድ ነው ቢሉ የጌታችን መስቀል ከጌታችን ዕርገት በኋላ ሙት እያነሣ፣ ደዉይ እየፈወሰ ለክርስያኖች ታላቅ ክብር በመኾኑ፤ አይሁድ በዚኽ ቀንተው ጒድጓድ ቈፍረው በይሁዳ እና በኢየሩሳሌም ኹሉ ቤቱን የሚጠርግ ጒድፉን አምጥቶ እንዲያፈስስበት በማዘዛቸው ቦታው የቆሻሻ መጣያ ኾኖ ዕሌኒ ንግሥት እስከ መጣችበት ድረስ ለ፫፻ ዓመታት ያኽል ተቀብሮ ኖረ፡፡
❖ ልጇ ቆስጠንጢኖስም በመስቀሉ ኀይል የክርስቲያኖች ጠላት የኾነውን መክስምያኖስን ድል ከነሣ በኋላ በሶል ጴጥሮስ ተጠምቆ ክርስቲያን ኾነ፤ ርሷም ልጄ ክርስቲያን ከኾነ ኢየሩሳሌም ኼጄ የፈረሱትን አብያተ ክርስቲያናት አሠራለኊ፤ የጌታዬ መስቀልን ከተቀበረበት አስወጣለኊ ብላ ስዕለት ተስላ ነበርና ያ በመፈጸሙ ደስ ተሰኝታ፤ ለልጇ ነገረችው፤ ርሱም በደስታ ብዙዎች ሰራዊትን ስንቅ አስይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ላካት፤ በደረሰችም ጊዜ ሱባኤን አድርጋ የመስቀሉ ጠላቶችን በጽኑ እስራት አሰረቻቸው፤ በኋላም አሚኖስና ኪራኮስ የሚባሉ በዕድሜ የጠገቡ ሽማግሌዎችን ብትጠይቃቸው ሊነግሯት ፈቃደኛ አልኾኑምና በጽኑ እስራት ብታስጨንቃቸው፤ ታሪኩን ነገሯት፤ ቦታውንም ጠቈሟት፡፡
❖ ከዚያም በጸሎቷ ላይ ቅዱስ መልአክ ተገልጾላት በዕጣን ጢስ አማካይነት እንደምታገኘው ተረድታ፤ መስከረም ፲፮ ደመራን አስደምራ በእሳት እንዲቃጠል አድርጋ እጅግ ብዙ ዕጣንን ብታስጨምር ጢሱ ወደ ሰማያት ወጥቶ መስቀሉ ካለበት ቦታ ላይ ተተክሎ ሰገደ፤ ርሷም ፈጣሪዋ እግዚአብሔርን በፍጹም ደስታ አመስግና ቊፏሮውን ከመስከረም ፲፯ ዠምሮ እስከ መጋቢት ፲ ድረስ እንዲቈፈር አስደርጋለች፤ በቊፋሮው ወቅትም የፈያታዊ ዘየማንና የፈያታዊ ዘጸጋም መስቀል ቢገኙም ዕውር አላበሩም፣ ሕሙማንን አልፈወሱም፡፡
❖ ከዚያም መጋቢት ፲ ጌታችን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት ቅዱስ መስቀሉ ተገኘ፤ በዚኽ ጊዜ ከሕሙማን ላይ ቢያደርጉት ኹሉንም ፈወሳቸው፣ ዕዉራን በሩ፣ ሙታንም ተነሡ፡፡ ከዚኹም ጋር የተወጋበት ጦሩ፣ የተቸነከረባቸው ቅንዋት ኹሉ ተገኝተዋል፤ ርሷም በፈረሷ ልጓም ላይ የመስቀል ምልክትን አስቀርጻበታለች፡፡
❖ ርሷም ጌታችን ተአምራት በሠራባቸው ቦታዎች አብያተ ክርስቲያናትን በማሠራት፤ በተለይም በጎልጎታ የተሠራው ቤተ ክርስቲያን መስከረም ፲፯ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምእመናን በተገኙበት ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያኑ ተከብሯልና፡፡ ርሷም ለድኾችና ለጦም አዳሪዎች ብዙ መልካም ነገርን በማድረግ ግንቦት ፱ በሰላም ዐርፋለች፡፡
❖ ሊቁ አርከ ሥሉስም ስለ ቅድስት እሌኒ በዐርኬው ላይ፡-
“ሰላም ለእሌኒ ውስተ ምድረ ሕይወት ኤልዳ
ምክረ መንፈስ ቅዱስ አመ ወሰዳ
ለዘሐይወ በድን በለኪፈ መስቀል ቅድመ ዐውዳ
እምአይቴ አንተ ትቤሎ ወእምአይ አንግዳ
ዘተረከብከ ግዱፈ በበዳ”
(የመንፈስ ቅዱስ ምክር በወሰዳት ጊዜ ኤልዳ ወደ ተባለች የሕይወት ምድር የኼደች ለኾነች ለዕሌኒ ሰላምታ ይገባል፤ በአደባባይዋ ፊት መስቀልን በመንካት የዳነውን በድን በበረሓ ወድቀኽ የተገኘኽ አንተ እንግዳ ከወዴት ነኽ አለችው) በማለት መስቀሉ ከወጣ በኋላ ስለተደረገላት ተአምር ጽፏል፡፡
"ስብሐት ለመስቀለ ክርስቶስ ዕፀ መድኀኒት ኀይልነ ወጸወንነ"
(ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ)
No comments:
Post a Comment