አርባ አራቱ ታቦታተ ጎንደር - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, September 17, 2022

አርባ አራቱ ታቦታተ ጎንደር

መግቢያ
ጎንደር በኢትዮጵያ የመንግሥት ታሪክ ከአክሱምና ላሊበላ ቀጥሎ ትልቋ የመንግሥት ማዕከል ነበረች፡፡ በመንግሥት ማዕከልነት የተቆረቆረችው በአፄ ፋሲል (1624-1660 ዓ.ም) ነው፡፡

FasilCastleGondar
ጎንደር የመንግሥት ማዕከል ብቻ ሳትሆን በጊዜው የመንፈሳዊ ትምህርት ማዕከልም ነበረች፡፡ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የመጻሕፍት እና የአቋቋም ትምህርት ይበልጥ የተስፋፋውና በየሀገሩ ያሉ ሊቃውንት በመናገሻ ከተማዋ ጎንደር በነገሥታቱ አማካይነት በመሰባሰባቸው ሲሆን ከዚያን ዘመን ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ መንፈሳዊ ትምህርት በስፋት የሚሰጥባት የትምህርት ማዕከል ለመሆን ችላለች፡፡
በአሁኑ ሰዓት በሰሜን ጎንደር በሚገኙ 21 ወረዳዎች ከ2117 ያላነሱ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ሲኖሩ በዋና ከተማዋ ደግሞ ከ92 ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡

በአብነት ት/ቤት ረገድም የመጻሕፍት ጉባዔያት፣ የአቋቋም ምስክር፣ የቅኔ አብያተ ጉባዔያት እንዲሁም የዜማ ት/ቤቶች በከተማዋ እና በዙሪያዋ በሚገኙ ወረዳዎች ይገኛሉ፡፡ (ስለአብነት ት/ቤቶች በሚቀጥሉት ጊዜያት እመለስበታለሁ፡፡)

44 የመሆናቸው ምሥጢር
በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ ከ92 ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሩም በአብዛኛው ስማቸው ደጋግሞ የሚነሳው የ44ቱ ብቻ ነው፡፡ በተለያየ ጊዜ በተለይም ጎንደርን ከማያውቁት ሰዎች ጋር ባደረኩት ውይይት 44ቱን ታቦታተ ጎንደርን በተመለከተ የተለያየ ግንዛቤ እንዳለ ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡
አንዳንዶቹ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙት የአብያተ ክርስቲያናት ታቦታት ስያሜ ብዛት ሲመስላቸው ሌሎቹ ደግሞ በጎንደር በጥምቀት በዓል ወደጥምቀተ ባህር የሚወርዱትን ብቻ ስሉ ይደመጣሉ፡፡ ጎንደር ከተማ እየኖሩም የ44ቱን ዝርዝር በውል የማያውቁ ብዙ ሰዎች ገጥመውኛል፡፡
SILASSIE-1
ጎንደር ደብረብርሃን ሥላሴ ቤተክርስቲያን
አርባ አራቱ ታቦታተ ጎንደር ከቤተ መንግሥቶቹ በተጨማሪ ታሪካዊዋ ጎንደር የምትታወቅበት ቅርስ ነው፡፡ ጎንደር ከተማ በአፄ ፋሲል የመንግሥት ከተማ ከመሆኗ አስቀድሞ የአካባቢው ነዋሪዎች ተክለዋቸው የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ቀሐ ኢየሱስ፣ አርባዕቱ እንስሳ፣ አበራ ጊዮርጊስ፡፡

ጎንደር የመንግሥት ከተማ ከሆነችበት እስከ ጎንደር ዘመን ማክተሚያ ፈፃሜ መንግሥት አፄ ተክለ ጊዮርጊስ (1772-1777) ድረስ 18 ነገሥታት የነገሱ ሲሆን እነዚህም አብዛኛዎቹ አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተዋል፡፡

እንግዲህ 44 የሚባሉት አብያተ ክርስቲያናት ጎንደር የመንግሥት ከተማ ከመሆኗ አስቀድሞ የተተከሉበትን ጨምሮ እስከ ፈፃሜ መንግሥት ተክለ ጊዮርጊስ (1772-1777) ድረስ የተተከሉትን ብቻ ሲሆን ቁጥራቸውም 44 ነው፡፡

ከዚያ ወዲህ ከዘመነ መሣፍንት እስከ አሁን የተተከሉ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሩም ከ44ቱ የሚቆጠሩ አይደሉም፡፡ በአጠቃላይ አርባአራቱ ታቦታተ ጎንደር በጎንደር ዘመን በጎንደር ከተማና አካባቢው የሚገኙና የነበሩ 44 አብያተ ክርስቲያናት ጥቅል ስም ነው፡፡
ይህም ማለት አሁን ባለው የጎንደር ከተማ ክልል እና ዙሪያውን በሚገኙ አዋሳኝ የገጠር ቀበሌዎች ለምሳሌ፣ ጠዳ፣ ፈንጠር፣ ብላጅግ፣ ደፈጫ እና በመሳሰሉት ቦታዎች የሚገኙ አጠቃላይ የአድባራት ቁጥር ነው፡፡

በጎንደር ዘመን የነገሡ ነገሥታት
ተ.ቁ
የንጉሡ ስም
ዓመተ ምህረት
የዓመት ብዛት
1
አፄ ሠርጸ ድንግል
1553-1587
34
2
አፄ ያዕቆብ
1587-1594
7
3
አፄ ዘድንግል
1594-1595
1
4
አፄ ሱስንዮስ
1595-1623
28
5
አፄ ፋሲል
1623-1659
36
6
አፄ ዮሐንስ (ፃድቁ)
1659-1674
15
7
አፄ ኢያሱ (አድያም ሰገድ)
1674-1698
24
8
አፄ ተ/ሃይማኖት (ርጉም)
1698-1700
2
9
አፄ ቴዎፍሎስ
1700-1703
3
10
አፄ ዮስጦስ
1703-1708
5
11
አፄ ዳዊት (አድባርሰገድ)
1708-1713
5
12
አፄ በካፋ (መሢህ ሰገድ)
1713-1722
9
13
አፄ ኢያሱ 2
1722-1747
25
14
አፄ ኢዮአስ
1747-1762
15
15
አፄ ዮሐንስ 2ኛ (ዘዋሕድእዴሁ)
1762-1763
1
16
አፄ ተ/ሃይማኖት (መናኔ መንግሥት)
1763-1770
7
17
አፄ ሰሎሞን
1770-1772
2
18
አፄ ተ/ጊዮርጊስ (ፈፃሜ መንግሥት)
1772-1777
5

ተካያቸው
አርባአራቱ ታቦታተ ጎንደር የተተከሉት በነገሥታት፣ በመሣፍንት እና በባላባት ወይም በመንጣሪ ሲሆን በቁጥር ደረጃ በነገሥታት የተሠሩት ይበልጣሉ፡፡
አፄ ፋሲል እና መናኔ መንግሥት ተ/ሃይማኖት ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ሲያሰሩ የሀገሬው ሰው ደግሞ 10 አብያተ ክርስቲያናትን እንዲተከሉ አድርጓል፡፡ የአፄ ፋሲል አባት አፄ ሱስኒዮስ አዘዞ ተ/ሃይማኖትን የተከሉ ሲሆን ዳግሚት ደብረሊባኖስ ተብላ በነገሥታቱ ዘመን የዕጨጌው መቀመጫ ይኽው ደብር ነበር፤ የደብሩ አለቃ የማዕረግ ስምም እንደ ደብረሊባኖስ ገዳም ፀባቴ ነው፡፡ አፄ ፋሲልና አፄ ሱስንዮስ የተቀበሩትም በዚሁ ደብር ሲሆን መቼና እንዴት አጽማቸው ፈልሶ እንደሔደ የጽሑፍ ማስረጃ ማግኘት ባልችልም በአሁኑ ሰዓት ግን ከጣና ገዳማት አንዱ በሆነው በዳጋ እስጢፋኖስ የሁለቱ ነገሥታት አጽም ይገኛል፡፡ (ስለ እጨጌ፣ አዘዞ ተ/ሃይማኖት እና ዳጋ እስጢፋኖስ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡)
fasil-remains
በዳጋ እስጢፋኖስ የሚገኘው የአጼ ሱሲኒዮስ እና የልጃቸው አጼ ፋሲል አጽም

መተዳደሪያቸው
በነገሥታቱ እና በመሣፍንቱ የተሠሩት አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮች ተተክለውባቸው ወይም ተመድበውላቸው ለመተዳደሪያ የአካባቢው ቀበሌ እየተከፋፈለ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህም ሪም ይባላል ይህም ማለት የዚያ አካባቢ ነዋሪ በዓመት እህል እየሠፈረ ለካህናቱ መተዳዳሪያ እንዲያመጣላቸው ነገሥታቱ አካባቢያዎቹን እየከፋፈሉ ይሠጣሉ፡፡ ለምሳሌ የአደባባይ ተ/ሃይማኖት ሪም በበለሳ ወረዳ ሰፊ መሬት፣ የአደባባይ ኢየሱስ ሪም በጐርጐራ፣ በቡቻራ፣ በብችኝ፣ በማንጌ፣ በዋርሄ ነበር፤ የአጣጣሚ ሚካኤል ሪም በደንቢያ ነበር፡፡
አካባቢው ነዋሪ እና በባላባት የተተከሉት አድባራት ግን ምዕመናን አሥራት በማውጣት የመቀደሻ ንዋያተ ቅድሳቱን ፤ዕጣን ፤ ጧፍ እና ሌሎችንም ለቤተክርስቲያን በማበርከት አገልግሎት ይሰጡ ነበር ፡፡ ዛሬ በገጠር እንዳሉት ካህናት አብዛኛዎቹ አራሾች እና ገበሬዎች ስለሆኑ እያረሱ የሚቀድሱ፤ እየቀደሱ የሚያርሱ አገልጋዮች ነበሩ ዛሬም አሉ ፡፡

የአድባራት የማዕረግ ስም
እስከ አፄ አድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን የተሰሩት አብያተ ክርስቲያናት የማዕረግ ስም ሳይኖራቸው በተሰሩበት አካባቢ በሚተከሉበት ወቅት ባጋጠመ ክስተት እና በታቦቱ ስም ይጠሩ ነበር፡፡  ለምሳሌ፡- ቀሐ ኢየሱስ፣ አበራ ጊዮርጊስ፣ አባ እንጦንስ፣ ፊት አቦ፣ ግምጃቤት ማርያም
ከአፄ ኢያሱ አድያም ሰገድ በኋላ ግን ለጎንደር አድባራት ሥርዓተ አስተዳደር ወጥቶ ደብሮችን በደረጃ መለየትና የማዕረግ ስም መስጠት ስለተጀመረ በነገሥታት የተሠሩት የማዕረግ ስም እየተሰጣቸው በነበራቸው ላይ ተጨምሮ ይጠሩበት ጀመር፡፡ ለምሳሌ፡- መካነ ነገሥታት ግምጃ ቤት ማርያም፣ ርዕሠ አድባራት አደባባይ ኢየሱስ እና ሌሎችም ፡፡


የአርባ አራቱ ታቦታተ ጎንደር ዝርዝር

ተ.ቁ
የደብሩ ስም
የተካዩ ስም
የደብሩ አለቃ ስም
1
አዘዞ ተ/ሃይማኖት
አፄ ሱስንዮስ
ፀባቴ
2
ፊት አቦ
አፄ ፋሲል
ሊቀ ዲያቆን
3
ፊት ሚካኤል
አፄ ፋሲል
ሊቀ ዲያቆን
4
አደባባይ ኢየሱስ
አፄ ፋሲል
ጽራግ ማሠሬ
5
ግምጃ ቤት ማርያም
አፄ ፋሲል
ሊቀ ማእምራን
6
እልፍኝ ጊዮርጊስ
አፄ ፋሲል
ሊቀ ማእምራን
7
መ/መ/መድኃኔዓለም
አፄ ፋሲል
ሊቀ ማእምራን
8
አቡን ቤት ገብርኤል
አፄ ፋሲል
መልአከ ምህረት
9
ፋሲለደስ
አፄ ሰሎሞን
ሊቀ ድማህ
10
አባ እንጦንስ
ፃድቁ ዮሐንስ
መልአከ ምህረት
11
ጠዳ እግዚአብሔር አብ
ፃድቁ ዮሐንስ
መልአከ አርያም
12
አርባዕቱ እንስሳ
አቤቶ አርምሐ

13
ቀሐ ኢየሱስ
የአገሬው ትክል

14
አበራ ጊዮርጊስ
የአገሬው ትክል

15
አደባባይ ተክለሃይማኖት
አዲያም ሰገድ ኢያሱ
ቄስ አፄ
16
ደብረ ብርሃን ሥላሴ
አዲያም ሰገድ ኢያሱ
መልአከ ብርሃናት
17
ዳረገንዳ ኤዎስጣቴዎስ
አድባር ሰገድ ዳዊት
ሊቀ ጉባዔ
18
አጣጣሚ ሚካኤል
አድባር ሰገድ ዳዊት
መልአከ ገነት
19
ጐንደር ሩፋኤል
አፄ በካፋ
መልአከ ፀሐይ
   20
ደፈጫ ኪዳነ ምህረት
አፄ በካፋ
መልአከ ህይወት
   21
ቅ.ዮሐንስ መጥምቅ
ራስ ወልደ ልዑል
መልአከ ጽጌ
   22
ጐንደር ልደታ ማርያም
አፄ ዮስጦስ
አለቃ
   23
ሠለስቱ ምዕት
አፄ ቴዎፍሎስ
መልአከ ሰላም
   24
ጎንደር በአታ ለማርያም
መናኔ መንግሥት ተ/ሃይማኖት
መልአከ ኃይል
   25
ወ/ነጐድጓድ ዮሐንስ
መናኔ መንግሥት ተ/ሃይማኖት
መልአከ ተድላ
   26
ጐንደር ቂርቆስ
መናኔ መንግሥት ተ/ሃይማኖት
ሊቀ አእላፍ
   27
ጐንደር ሐዋርያት(ጴጥሮስ ወጳውሎስ )
መናኔ መንግሥት ተ/ሃይማኖት
አለቃ
   28
ፈንጠር ልደታ
መናኔ መንግሥት ተ/ሃይማኖት
አለቃ
   29
ሰሖር ማርያም
መናኔ መንግሥት ተ/ሃይማኖት

   30
ወራንገብ ጊዮርጊስ
መናኔ መንግሥት ተ/ሃይማኖት
አለቃ
   31
ምንዝሮ ተ/ሃይማኖት
አፄ ሠርፀ ድንግል
አለቃ
   32
ደ/ፀሐይ ቊስቋም
እቴጌ ምንትዋብ
መልአከ ፀሐይ
   33
ደ/ምጥማቅ ማርያም
ፈፃሜ መንግሥት ተ/ሃይማኖት
ዐቃቤ ሰዓት
   34
አባ ሳሙኤል
ፈፃሜ መንግሥት ተ/ሃይማኖት
አለቃ
   35
ጐንደሮች ማርያም
የአገሬው ትክል
አለቃ
   36
ጐንደሮች ጊዮርጊስ
የአገሬው ትክል
አለቃ
   37
አባ ጃሌ ተ/ሃይማኖት
ደጃች ወንድወሰን
አለቃ
   38
ዐቢየ እግዚእ.ኪ/ምህረት
ራስ ገብሬ

   39
ብላጅግ ሚካኤል
የአገሬው ትክል

   40
አሮጌ ልደታ
የአገሬው ትክል

   41
ጫጭቁና ማርያም
የአገሬው ትክል

   42
ጋና ዮሐንስ
የአገሬው ትክል

   43
ራ ሚካኤል
የአገሬው ትክል

   44
ዳሞት ጊዮርጊስ
የአገሬው ትክል


SILASSIE-BACK
ጎንደር ደብረብርሃን ሥላሴ ቤተክርስቲያን በስተጀርባ ዕይታ

ከዚህ በላይ ያለው ሠንጠረዥ የ44ቱን ታቦታተ ጎንደር ዝርዝር የያዘ ሲሆን ከ44ቱ አድባራት መካከል በአሁኑ ሰዓት የሌሉ ስድስት ናቸው፡፡
የአድባራቱ የኪነ ሕንፃ ውበት ምን ይመስላል? አድባራቱ ምን ችግር ገጠማቸው? እነዚህ የጠፉት አድባራት እነማን ናቸው? በአሁኑ ሰዓት ባለው የከተማ ክልል የት ቦታ ላይ ይገኙ ነበር ? የሚለውን ጥያቄ ሚቀጥለው ክፍል እንመለከተዋለን፡፡

 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages