ስንክሳር ዘወርኀ ኅዳር 17 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, March 1, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ኅዳር 17

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ኅዳር ዐሥራ ሰባት በዚህችም ዕለት የከበረ አባት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሥጋው ፍልሰት ሆነ፣ የቅድስት ወለተ ጴጥሮስ እረፍቷ ነው፣ የአቡነ ሲኖዳ ዘደብረ ጽሙና የእረፍታቸው መታሰቢያ ነው።



ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
ኅዳር ዐሥራ ሰባት በዚህችም ዕለት የዓለሙ ሁሉ መምህር የሆነ የከበረ አባት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሥጋው ፍልሰት ሆነ።
ይህም አባት ከእስክንድርያ አገር ሰዎች ወገን ነው የአባቱም ስም አስፋኒዶስ የእናቱም ስም አትናሲያ ነው እሊህም እጅግ ባለጸጎች ነበሩ ይህንንም ልጃቸውን በመልካም አስተዳደግ አሳደጉት ትምህርትንና ጥበብንም ሁሉ አስተማሩት እርሱ ወደ አቴና ሒዶ በመምህራን ቤት ተቀምጦ ትምህርትን ሁሉ ተምሮ በዕውቀቱ ከብዙዎች በላይ ከፍ ከፍ ብሏልና። ከዚህም በኋላ ገና በታናሽነቱ መነኰሰ የዚህንም የኃላፊውን ዓለም ጣዕም ንቆ ተወ ከእርሱም ቀድሞ በዚሁ ገዳም ቅዱስ ባስልዮስ መንኵሶ ነበር በአንድነትም ተስማምተው ብዙ ትሩፋትን ሠሩ ወላጆቹም በሞቱ ጊዜ ከተውለት ገንዘብ ምንም ምን አልወሰደም ለድኆችና ለምስኪኖች ሰጠ እንጂ ከዚያም በምንኵስና ሥራ በመጠመድ ፍጹም ገድልን እየተጋደለ ኖረ።
በዚያም ገዳም ሶርያዊ ጻድቅ ሰው ስሙ ሲሲኮስ የሚባል መነኰስ ነበረ እርሱም ወደፊት የሚሆነውን በመንፈስ ቅዱስ ያይ ነበር በአንዲት ሌሊትም ለጸሎት እየተጋ ሳለ ሐዋርያትን ጴጥሮስንና ዮሐንስን አያቸው ወደ ዮሐንስ አፈወርቅ ገብተው ጴጥሮስ መክፈቻ ሰጠው ወንጌላዊ ዮሐንስም ወንጌልን ሰጠው እንዲህም አሉት በምድር ያሠርከው በሰማይ የታሠረ ይሆናል በምድርም የፈታኸው ደግሞ በሰማያት የተፈታ ይሆናልና በውስጥህ መንፈስ ቅዱስ ያደረብህ አዲስ ዳንኤል ሆይ የክብር ባለቤት ከሆነ ከታለቅ መምህር ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ወደ አንተ ተልከናልና ዕወቅ እኔም የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ የተሰጠኝ ጴጥሮስ ነኝ ።
ሁለተኛውም እኔም በመጀመሪያው ስብከቴ በከበረ ወንጌል ቃል አስቀድሞ ነበረ ያልኩ ይህም ቃል በጠላት ላይ የእሳት ሰይፍ የሆነ ዮሐንስ ነኝ ። ለአንተም ከክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ወገኖችህ ምእመናንን በቀናች ሃይማኖት ታሳድጋቸው ዘንድ ዕውነተኛ አእምሮ ደግሞ ተሰጥቶሃል ።
ጻድቅ ሲሲኮስም ይህን ራእይ በአየ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ቸር ታማኝ እረኛ ሁኖ እንደሚሾም ዐወቀ። ከዚህም በኋላ በቅዱስ ዮሐንስ ላይ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በላዩ ወርዶ አደረበትና ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ ዲያቆን ሁኖ ሳለም የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት ብሉያትንና ሐዲሳትን ተረጐመ ። በአንዲት ሌሊትም ቅዱስ ዮሐንስ ሲጸልይ የእግዚአብሔር መልአክ በድንገት እንደ በረድ ነጭ በሆነ ልብስ ተገለጠለት ቅዱስ ዮሐንስም ሲያየው ደንግጦ በምድር ላይ ወደቀ መልአኩም አርአያውን ለውጦ እንደ ሰው ሁኖ ታየው ወዳጄ አዲስ ዳንኤል ሆይ አትፍራ ተነሣ አለው የቅዱስ ዮሐንስም ልቡ ተጽናንቶ ጌታዬ አንተ ማነህ ግርማህ አስፈርቶኛልና አለው የእግዚአብሔር መልአክም ትሠራው ዘንድ የሚገባህን ልነግርህ ወዳንተ የተላክሁ ነኝ።
አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ያዘዘህን ለመሥራት ልብህን አበርታ ቃልህ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ በአራቱ ማእዘን ይደርሳልና እልፍ አእላፋትም ትምህርትህን ተቀብለው ትእዛዝህን ሰምተው ወደ ፈጣሪያቸው እግዚአብሔር ተመልሰው ይድናሉና በእግዚአብሔር መንግሥትም ውስጥ የጸና የብርሃን ዐምድ ትሆናለህና። እነሆ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አንተ ይመጣል ከእርሱም ጋራ ሁሉም ካህናትና ዲያቆናት በየማዕረጋቸው የሚያዝህንም አድርግ የእግዚአብሐር ትእዛዝ ነውና ልትተላለፍ አይገባህም አለው። ከዚህም በኋላ ያ መልአክ ለአባ ፊላትያኖስ ተገልጦ ቅዱስ ዮሐንስን ቅስና እንዲሾመው አዘዘው በማግሥቱም ሊቀ ጳጳሳቱ መጣ ከርሱ ጋራም ካህናት አሉ ይህን ቅዱስ ዮሐንስንም ይዞ ቅስና ሾመው።
የቍስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳትም በአረፈ ጊዜ ንጉሥ አርቃድዮስ ልኮ አስመጥቶ ቅዱስ ዮሐንስን በቍስጥንጥንያ ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾመው አባቶቻችን ሐዋርያት እንደሚአደርጉት በሊቀ ጵጵስናው ሥራ ላይ ጸና ሕይወትነት በአላቸው ትምህርቶችና ተግሣጾች ሕዝቡን ሁልጊዜ የሚአስተምር ሆነ።
ከኤጲስቆጶሳትም ሆነ ከመንግሥት ወገን ሕግን የሚተላለፉትን ሁሉ ይገሥጻቸዋል ማንንም አይፈራም ፊት አይቶም አያደላም። የንጉሥ አርቃድዮስ ሚስት አውዶክስያም ገንዘብ ወዳጅ ስለሆነች የአንዲት ድኃ መበለት ቦታዋን በግፍ ወሰደች ያቺ መበለትም ወደ ቅዱስ ዮሐንስ መጥታ ንግሥት አውዶክስያ ቦታዋን እንደነጠቀቻት ነገረችው እርሱም የደኃዋን ቦታዋን መልሺላት ብሎ ከብዙ ምክር ጋር እንድትመልስላት ንግሥት አውዶክስያን ለመናት እርሷ ግን እምቢ በማለት አልታዘዘችለትም ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ ሥጋውን ደሙን እንዳትቀበል አውግዞ ለያት።
ቍጣንና ብስጭትንም ተመልታ ስለ ክፉ ሥራቸው ከሹመታቸው እርሱ የሻራቸውን ኤጲስቆጶሳት ሰበሰበች እነርሱም ንግሥቲቱን ስለ ተቃወመ ስደት እንደሚገባው በእርሱ ላይ ተስማምተው ጻፉ እርሷም አጥራክያ ወደ ሚባል ደሴት ሰደደችው ። ከዚያም በደረሰ ጊዜ የዚያች ደሴት ሰዎች በክፉ ሥራ ጸንተው የሚኖሩ ከሀድያን ሁነው አገኛቸው ቅዱስ ዮሐንስም አስተማራቸው ገሠጻቸውም በፊታቸው ስለ አደረጋቸው ድንቆች ተአምራት ወደ ቀናች ሃይማኖት አስገባቸው።
የሮሜ ንጉሥ አኖሬዎስና ሊቀ ጳጳሳቱ ዮናክኒዶስ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ስደት በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ በንጉሥ አርቃድዮስ ላይም በመቆጣት እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጽፈው ላኩ ከዚህ ከክፉ ሥራ ተጠበቅ ትእዛዛችንንም ተቀብለህ የከበረ
ዮሐንስን ከስደቱ ከአልመለስከው በአንተና በእኛ መካከል ሰላም አይኖርም። መልእክታቸውንም በአነበበ ጊዜ እጅግ አዘነ ሚስቱንም አግዶ ልኮ ቅዱስ ዮሐንስን ከስደቱ መለሰው በተመለሰ ጊዜም የቍስጥንጥንያ ሰዎች በመመለሱ ታላቅ ደስታ አደረጉ። ከጥቂት ቀኖች በኋላም ንግሥቲቱ ወደ ክፋቷ ተመልሳ ሁለተኛ ወደ አጥራክያ ደሴት ሰደደችውና በዚያው አረፈ።
ንጉሥ አኖሬዎስና ሊቀ ጳጳሳት ዮናክኒዶስም በሰሙ ጊዜ መልእክትን ላኩ ሊቀ ጳጳሳቱም የከበረ ዮሐንስን ከስደቱ እስከምትመልሰው ድረስ ሥጋውንና ደሙን እንዳትቀበል አውዶክስያን አወገዛት። ከዚህም በኋላ የከበረ ዮሐንስን ይመልሱት ዘንድ ንጉሥ ላከ ግን ሙቶ አገኙት ሥጋውንም ተሸክመው ወደ ቊስጥንጥንያ ከተማ አደረሱት። የከበረ ዮሐንስም በተሰደደበት አገር እንደአረፈና ሥጋውንም ወደ ቍስጥንጥንያ ከተማ እንደአመጡ ወደ አባ ዮናክኒዶስ መልእክት ጽፈው አስረዱት። ሁለተኛም የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ ሥጋውንና ደሙን እንዳትቀበል ልኮ አውድክስያን አወገዛት እየለመነችውም ስምንት ወር ያህል ኖረች በብዙ ልመናም ፈታት።
ነገር ግን ጭንቅ በሆነ ደዌ እግዚአብሔር አሠቃያት ያድኗት ዘንድ ገንዘቧን ለባለ መድኃኒቶች ጥበበኞች እስከ ሰጠች ድረስ ግን አልዳነችም ወደ ቅዱስ ዮሐንስ መቃብርም ሔዳ በእርሱ ላይ ያደረገችውን በደል ይቅር ይላት ዘንድ እየሰገደችና እያለቀሰች ለመነችው እርሱም ይቅር አላት ከደዌዋም ፈወሳት። ጌታችንም ከሥጋው ታላላቅ ድንቆች ታአምራትን ገለጠ።
ስለርሱም እንዲህ ተባለ በአንዲት ዕለትም ከንጉሥ አርቃዴዎስ ጋር ተቀምጦ ሳለ ንጉሡ እንዲህ አለው አባቴ ሆይ ስለ አንድ ቃል እንድታስረዳኝ እለምንሃለሁ። ይህም ቃል ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በልቤ ውስጥ ይመላለሳል ወንጌላዊ ማቴዎስ ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምን የበኵር ልጅዋን እስከ ወለደች ድረስ ዮሴፍ አላወቃትም ስለምን አለ ወንዶች ሴቶችን እንደሚአውቋቸው ዮሴፍ አወቃትን አለው።
የከበረ ዮሐንስም ንጉሥ ሆይ እንዲህ አትበል እንዲህ አንተ እንደምትለው አይደለም የከበረች ድንግል እመቤታችንስ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሆድዋ ውስጥ በነበረ ጊዜ የእርሱ ኅብረ መልክ በሚለዋወጥ ጊዜ ከእርሱ ጋር መልኳ ይለወዋወጥ ነበር። በንጹሕ ብርሌ ውስጥ ውኃ በጨመሩ ጊዜ ውኃ መስሎ እንደሚታይ ወይን ጠጅም ቢጨምሩ ያንኑ መስሎ እንደሚታይ ወይም ከውስጡ በተጨመረው ቀይም ቢሆን ቀልቶ እንደሚታይ ቅጠልያም ቢገባበት ቅጠልያ መስሎ እንደሚታይ ። ድንግልም በሆድዋ ውስጥ የልጅዋ መልክ በሚለዋወጥ ጊዜ ከእርሱ ጋራ መልኳ ይለዋወጥ ነበር። እንደ ሮማን አበባ የምትቀላበት ጊዜ አለ እንደናርዶስም የምታብለጨልጭበት ጊዜ አለ የለመለመ ቅጠል የምትመስልበትም ጊዜ አለ ከወለደች በኋላ ግን አልተለወጠችምና ዮሴፍ በአንድ በቀድሞው ኅብረ መልኳ ተወስናለት መልኳን ተረዳ ማለት ነው አለው። በዚያን ጊዜ በንጉሥ አዳራሽ ውስጥ ከወርቅ የተሠራ የእመቤታችን አምላክን የወለደች የድንግል ማርያም ሥዕል ነበረችና አፈ ወርቅ ዮሐንስ ልሳነ ወርቅ ዮሐንስ አፈ በረከት ዮሐንስ መልካም ተናገርክ የሚል ቃል ከእርሷ ወጣ ።
ንጉሡና ከእርሱ ጋር ያሉት በሰሙ ጊዜ እጅግ አደነቁ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት በዚያን ጊዜ ንጉሥ አዝዞ ወርቅ ሠሪ አስመጥቶ ለከበረ ዮሐንስ የወርቅ ልሳን አሠርቶ ለሚያየው ሁሉ መታሰቢያ ምልክት ሊሆን አምላክን ከወለደች ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ሥዕል ዘንድ ሰቀለው። ቅዱስ ዮሐንስንም ከዚያች ቀን ወዲህ ልሳነ ወርቅ ብሎ ጠራው አፈ ወርቅም ተብሎ እስከዛሬ ተጠራ።
የአርቃዴዎስም ልጅ ታናሹ ቴዎዶስዮስ በነገሠ ጊዜ መልክተኞችን ልኮ የቅዱስ ዮሐንስን ሥጋ ብዙ በመዘመርና በማመስገን በታላቅ ክብር ወደ ቊስጥንጥንያ አፍልሶ አስመጣው ይህም ከዕረፍቱ በኋላ በሠላሳ አምስት ዓመት ነው። በሌላ በቅብጢ መጽሐፍ በግንቦት ወር ሃያ ሁለት ቀን እንደ ደረሰ ይናገራል በሮማውያን መጽሐፍ ግን በየካቲት ወር ሃያ ሁለት ቀን ተባለ የዕንቊ ፈርጾች ባሉት የዕብነ በረድ ሣጥን ውስጥ አድርገው ወደ ቤተ መቅደስ አስገቡት ከሥጋውም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ ።
ሁለተኛም የእስክንድርያ ግጻዌና የሀገረ ቅፍጥ ኤጲስቆጶስ አባ ዮሐንስ የጻፈው ግጻዌ የመለካውያንም ግጻዌ በዚች በኅዳር ዐሥራ ሰባት ቀን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳረፈባት ተባበሩ። ሁለተኛም ደግሞ የመለካውያን ግጻዌ ዮሐንስ አፈወርቅ ዐይሉል በሚባል ወር በዐሥራ አራት እንዳረፈ ይናገራል ይህም በመድኃኒታችን በመስቀሉ በዓል መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን ነው ። ስለዚህም ራሱን ለማስቻል ወደ ኅዳር ዐሥራ ሰባት ቀን ለወጡት። የቀደሙ መጻሕፍት ግን ዕረፍቱ ግንቦት ዐሥራ ሁለት ቀን እንደሆነ ያወሳሉ።

ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ
በዚህችም ዕለት ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ አረፈች። አባቷ ባሕር አሰግድ እናቷ ደግሞ ክርስቶስ አዕበያ ይባላሉ። ትውልዷ ከዳሮ /ምስራቅ ኢትዮጵያ/ ወገን ነው። ወንድሞቿ ዮሐንስና ዘድንግል በንጉሥ ሱስንዮስ ጊዜ ታላላቅ ባለስልጣናት ነበሩ። እናት አባቷ በህግ በስርዓት ካሳደጓት በኋላ ሥዕለ ክርስቶስ የሚባል የስስኑዮስ የጦር አበጋዝ ቢትወደድ አግብታ 3 ልጆች መውለድዋን ገድሏ ይናገራል። ይህ ቢትወደድ ይኖርበት የነበረው ግንብ ቤት ፍራሽ እስከ አሁን ድረስ በጋይንት ስማዳ ይታያል።
ወለተ ጴጥሮስ ከቢትወደድ ሥዕለ ክርስቶስ ጋር በሰላም በመኖር ላይ እያለች ንጉሡ አጼ ሱስንዮስ የተዋሕዶ ሃይማኖቱን ቀይሮ በሮማውያን ሀሰተኛ መምህራን በመታለል ካቶሊክነትን ተቀብሎ የኢትዮጵያ ህዝብም ካቶሊክ እንዲሆን ዐወጀ። በዚህ ዐዋጅ የተነሣ በንጉሡ ደጋፊዎችና የቀደመ ሃይማኖታችንን አንለቅም ባሉት እውነተኛ የተዋህዶ ምዕመናን መካከል ታላቅ ጠብ ሆነ።
የንጉሡ ሠራዊትም በተዋሕዶ ምእመናን ላይ ዘመቱ። ቢትወደድ ሥዕለ ክርስቶስ ከዘመቻ ሲመለስ የጳጳሱን የአቡነ ስምዖንን ልብስ እንደግዳይ ሰለባ ለንጉሡ ይዞለት መጣ። ይህንን የሃይማኖቷን መናቅ የአባቶቿን መደፈር የተመለከተችው ወለተ ጴጥሮስ እንደዚህ ካለው ከሀዲ ጋር በአንድ ቤት አብሮ መኖር አያስፈልግም ብላ ቆረጠች። ከዚህም በኋላ ከቤቱ የምትወጣበትን ዘዴ ያለ እረፍት ማሰላሰል ጀመረች። ከዚያም ወደገዳሙ ለመድረስ እንዲረዷት ከጣና መነኮሳት ጋር መላላክ ጀመረች። የጣና ቂርቆስ ገዳም አበምኔት አባ ፈትለ ሥላሴም ወለተ ጴጥሮስን ይዘዋት እንዲመጡ ሁለት መነኮሳትን ላኩ። በዚያ ጊዜ ልጆቿ ሁሉ ሞተውባት ነበር። ወለተ ጴጥሮስ ከመነኮሳቱ ጋር መጥፋቷን ያወቀው ቢትወደድ ሥዕለ ክርስቶስ ይዘው ያመጡለት ዘንድ አያሌ ሠራዊት ከኋላዋ ሰደደ። ነገር ግን ወለተ ጴጥሮስና ሁለቱ መነኮሳት በእግዚአብሄር ረዳትነት በዱር ውስጥ ተሰዉረዉባቸዉ ሊያገኟቸው አልቻሉም። ይህ ተሰዉረዉበት የነበረዉ ቦታ እስከዛሬ ድረስ "ሳጋ ወለተ ጴጥሮስ" ይባላል። በኋላ ዘመንም በስሟ ቤተ ክርስቲያን ተሰርቶበታል።
ከዚህ በኋላ ወደ ደብረ ዕንቁ ገዳም ገብታ ስርዓተ ምንኩስናን ተምራ መነኮሰች። ታላቁ ገድሏ የተጀመረውም ከዚህ በኋላ ነው። ወለተ ጴጥሮስ ከምንኩስናዋ በኋላ በመላ ሀገሪቱ እየተዘዋወረች ሕዝቡ በተዋሕዶ እምነት እንዲፀና፣ በጸሎተ ቅዳሴም ጊዜ ሃይማኖቱን የለወጠው የንጉሡ የሱስንዮስ ስም እንዳይጠራ ትመክር ጀመር። ብዙ ሰዎችም በምክሯ ተስበው በሃይማኖታቸው እየጸኑ ሰማዕትነትን መቀበል ያዙ።
ይህንን የወለተ ጴጥሮስን ተጋድሎ የሰማው ንጉሥ ሱስንዮስ ተይዛ ለፍርድ ትቀርብ ዘንድ ብዙ ወታደሮች በየአካባቢው አሰማራ። በመጨረሻም በሰራዊቱ ተይዛ በሱስንዮስ ፊት ቀረበች። መሳፍንቱ መኳንንቱና ለእንጀራቸው ሲሉ ሃይማኖታቸውን የለወጡ ሊቃውንት በተሰበሰቡበት ትመረመር ጀመር።
ከሳሽዋ " ንጉሡን ካድሽ፣ እግዚአብሔርን ካድሽ፣ ትዕዛዙን እምቢ አልሽ፣ ሃይማኖቱን ዘለፍሽ፣ ሌሎች ሰዎችም ሃይማኖቱን እንዳይቀበሉ ልባቸውን አሻከርሽ" ሲል ከሰሳት። ወለተ ጴጥሮስ ግን እንደ አምላኳ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በከሳሾቿ ፊት ዝም አለች። ንጉሡም ርቃ እንዳትሄድ ነገር ግን ከቅርብ ዘመዶቿ ጋር እንድትኖር /የቁም እስር/ ፈረደባት።
ሃይማኖት ተንቃ፣ ቤተ ክርስቲያን ተዋርዳ የመና*ፍ*ቃን* መጨዋቻ ስትሆን ማየት የሃይማኖት ፍቅርዋ ያላስቻላት ወለተ ጴጥሮስ በግዞት መልክ ከተቀመጠችበት ቦታ ጠፍታ ዘጌ ገዳም ገባች። አብርዋትም ወለተ ጳውሎስና እህተ ክርስቶስ የተባሉ እናቶች ነበሩ። በዚያም በገዳሙ የነበሩ መነኮሳት እና የአካባቢው ምእመናን በተዋሕዶ ሃይማኖታቸው እንዲጸኑ እየመከረች ጥቂት እንደቆየች የሚያሳጧትና የሚከሷት ስለበዙ ቦታውን ለቃ ወደ ዋልድባ ገዳም ገባች። ዋልድባ ገብታ ሱባዔዋን ከፈጸመች በኋላ በገዳሙ የነበሩትን አባቶችና እናቶች በእምነታቸው ጸንተው እንዲቆዩ ትመክራቸው ጀመር።
አጼ ሱስንዮስ የወለተ ጴጥሮስን ተጋድሎ፣ መነኮሳትንና ምእመናንን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ፣ የካዱትም ከክህደታቸው እንዲመለሱ ማድረጓን ሲረዳ ብዙ ወታደሮችን ይልክባት ነበር። በዋልድባ እያለችም የንጉሡ ሰራዊት ሊያስኖሯት ስላልቻሉ ወደ ጸለምት አመራች። በጸለምት የወለተ ጴጥሮስ ትምህርት እንደ ሰደድ እሳት ተስፋፋ። ምእመናን እየውደዷትና እየተቀበሏት እራሳቸውን ለሰማዕትነት አዘጋጁ። ይህንን የሰማው ሱስንዮስ ይቺ ሴት እኔ ብተዋት እርሷ አልተወችኝም፣ አለና የጸለምቱን ገዥ ባላምባራስ ፊላታዎስን ወለተ ጴጥሮስን ይዞእንዲያመጣለት አዘዘው።
ወለተ ጴጥሮስ በጸለምቱ ገዥ ተይዛ ወደ ሱስንዮስ መጣች። አስቀድመው ሃይማኖቷን እንድትለውጥ ሊያግባቧት ሞከሩ። እርሷ ግን ጸናች። ሦስት የካቶሊክ ቀሳውስት መጥተው ስለሃይማኖትዋ ተከራከሯት። ወለተ ጴጥሮስ ግን የሚገባቸውን መልስ ሰጥታ አሳፈረቻቸው። በየቀኑ የካቶሊክ ቀሳውስት ሃይማኖቷን ትታ ካቶሊክ እንድትሆን በምክርም በትምህርትም ለማታለል ሞከሩ። ይሁን እንጂ ወለተ ጴጥሮስ በተዋሕዶ ዓለት ላይ ተመስርታ ነበርና ፍንክች አላለችም።
በመጨረሻ አንዱ የካቶሊክ ቄስ "እርሷን እቀይራለሁ ማለት በድንጋይ ላይ ውኃ ማፍሰስ ነው" ሲል ለንጉሡ አመለከተ። ሱስንዮስ ይህንን ሲሰማ ሊገላት ቆረጠ። አማካሪዎቹ ግን "አሁን እርስዋን ብትገል ህዝቡ ሁሉ በሞቷ ይተባበራል፣ ስለ ሃይማኖቱ እንደ እርሱዋ መስዋዕት ይሆናል። ደግሞ ሰው ሁሉ ካለቀ በማን ላይ ትነግሣለህ? ይልቅስ ታስራ ትቀመጥ።" ብለው መከሩት። ንጉሡም ገርበል ወደተባለው በርሃ ሊልካት ወሰነ።
መልክዐ ክርስቶስ የተባለው ዋነኛ የካቶሊኮች አቀንቃኝ ወደ ሱስንዮስ ፊት ቀርቦ "ንጉሥ ሆይ በፊትህ ሞገስን ካገኘሁ ክረምቱ እስኪያልፍ ድረስ ከእኔ ጋር ትክረም። እኔ እመክራታለሁ። የፈረንጆቹ መምህር አልፎኑስም ሁልጊዜ መጽሐፉን ያሰማታል። ይህ ሁሉ ተደርጎ አሻፈረኝ ካለች ያንጊዜ ግዞት ትልካታለህ" ሲል ለመነው ንጉሡም ተስማማ።
መልክዐ ክርስቶስ ወለተ ጴጥሮስን የካቶሊኮች ጳጳስ ወደሚኖርበት ጎንደር አዘዞ ወሰዳት። ሁለቱ ተከታዮቿ ወለተ ክርስቶስ እና እኅተ ክርስቶስ አብረዋት ሰነበቱ። ወለተ ጳውሎስ ዘጌ ቀርታለች። አልፎኑስሜንዴዝም ዘወትር እየሄደ የልዮንን ክህደት ያስተምራት ነበር። ንጉሡም የወለተ ጴጥሮስን ወደ ካቶሊክነት መቀየር በየጊዜው ይጠይቅ ነበር፣ የሚያገኘው መልስ ግን ሁልጊዜ አንድ ነው "በፍጹም"። ክረምቱ አለፈ። ኅዳርም ታጠነ። ወለተ ጴጥሮስም በትምህርትም በማባበልም ከተዋሕዶ ሃይማኖቷ ንቅንቅ አልል አለች። ስለዚህ ወደ ስደት ቦታዋ ገርበል በርሃ በሱስንዮስ ወታደሮች ተጋዘች። ወለተ ጴጥሮስ ብቻዋን ገርበል ወረደች። በእርጅና ላይ ያለችው እናቷ ይህንን ስትሰማ አንዲት አገልጋይ ላከችላት። ቆራጧ ተከታይዋ እኅተ ክርስቶስም ወዲያው ወደ እርሷ መጣች።
ገርበል በርሃ ለሦስት አመት ስትኖር ብዙ ጊዜ ትታመም ነበር። ስለዚህ መከራውን ሁሉ ስለሃይማኖቷ ቻለችው። ከግዞቱ ከተፈታች በኋላ ደንቢያ ውስጥ ጫንቃ በተባለ ቦታ ተቀመጠች። በስደቱ ምክንያት ቆባቸውን አውልቀው የነበሩ አያሌ መነኮሳትም ስደቱ መለስ ሲል በዙሪያዋ ተሰበሰቡ፡ በገዳማቸዉም ፀንተዉ እንዲኖሩ ትመክራቸዉ ነበር። በኋላም ወደ ጣና ቂርቆስ ተጉዛለች።ከዚያም ምጽሊ ወደተባለው ደሴት ሄዳ በዙርያዋ አያሌ መነኮሳትን ሰብስባ ለሃይማኖታቸዉ እንዲጋደሉ መከረቻቸዉ።። ነገር ግን መከራ ያልተለያት ወለተ ጴጥሮስ መዝራዕተ ክርስቶስ የተባለው ሰው ካቶሊክ ያልሆኑ ምእመናንን አስገድዶ የሚያስጠምቅበትን ደብዳቤ ይዞ ወደ አካባቢው መምጣቱን ስለሰማች መነኮሳቱን መክራና አስተምራ ወደ እየበረሃው ከሰደደች በኋላ እርሷም እንደገና ስደት ጀመረች። ተመልሳ ወደ ምጽሊ የመጣችው አገር ሲረጋጋ በ፵፱ አመቷ ነው።
ከስደት ስትመለስ መኖርያዋ ያደረገችው መንዞ የተባለውን ቦታ ነው። በዚያ ቦታ ላይ በጸሎትና በስግደት ተጠምዳ ኖረች። በምጽሊ ገዳም አብሯት የነበረው የደብረ ማርያም አበምኔት አባ ጸጋ ክርስቶስም መጽሐፈ ሐዊን ይተረጉምላት ነበር።
አጼ ሱስንዮስ ምላሱ ተጎልጉሎ ከእግዚአብሔር ቅጣቱን ሲቀበልና የተዋሕዶ ሃይማኖት ስትመለስ አቡነ ማርቆስ ግብጻዊ ጵጵስና ተሹመው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከመንገድ ላይ ጠብቃ ቡራኬ ተቀበለች። ስለሃይማኖቷ ብላ ከባሏ መለየትዋ እና መከራ መቀበሏ እስከ ግብጽ ድረስ መሰማቱን ጳጳሱ ነግረዋታል።
ከዚያም በመንዞ ገዳም አቋቁማ በተጋድሎተ ቀመጠች። ያቋቋመችው ገዳም የወንዶችም የሴቶችም ነበር።
የተዋሕዶ ሃይማኖት በዐዋጅ ከተመለሰችና አጼ ፋሲል ከነገሠ በኋላ ንጉሡን ለማግኘትና ወንድሞቿንና ዘመዶቿን ለማየት ወደ ጎንደር መጣች። ንጉሡም በታላቅ ክብር ተቀበላት። በየቀኑም ሳያያት አይውልም ነበር። ወደ እርስዋ ሲገባም አደግድጎ ነበር። ይህም ስለሃይማኖትዋ ጽናትና ስለቅድስናዋ ክብር ነው።
ወለተ ጴጥሮስ በተጋድሎና በምንኩስና ኖራ በ፶ አመቷ በቆረቆረችው ገዳም ዐረፈች። መታሰቢያዋም ኅዳር ፲፯ ቀን ይከበራል። የተከታይዋ ወለተ ክርስቶስ በዓል ደግሞ ኅዳር ፯ ቀን ይውላል። በሃይማኖት ጸንቶ መጋደል ወንድ ሴት አይልም። ቤተ ክርስቲያናችን እንደነ ወለተ ጴጥሮስ ያሉ አያሌ ልጆች አሏት። የዛሬዎቹ እህቶችና እናቶችም በምግባር ታንፆ በሃይማኖት ጸንቶ በእምነት መጋደልን ከእነዚህ እናቶች ሊቀስሙ ይገባል።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን አቡነ ሲኖዳ ዘደብረ ጽሙና የእረፍታቸው መታሰቢያ ነው፡፡ ሲኖዳ ማለት ‹‹ታማኝ›› ማለት ነው፡፡ ትውልድ ሀገራቸው ጎጃም ሲሆኑ የሸዋ ባላባት ልጅ ናቸው፡፡በጎጃም ደብረ ዲማህ አጠገብ ደብረ ፅሞና በተባለው ቦታ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ያመልኩት የነበረውን ትልቅ ዘንዶ አቡነ ሲኖዳ በመስቀል ባርከው ከሁለት ሰንጥቀውታል፡፡ ሰዎቹንም አስተምረው አሳምነው አጥምቀው የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን ሠርተውላቸዋል፡፡ ጻድቁ የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓይነት ገድል አላቸው፡፡ ለዘንዶ ምግብ እንዲትሆን ግብር ሆና የተሰጠችውን ሴት ልጅ ከጫካ አግኝተው ዘንዶውን በመስቀላቸው አማትበው ገድለው ልጅቷን አድነዋታል፡፡
በዘመናቸው ነግሦ የነበረው ‹‹ሕዝበ ናኝ›› የተባለው ንጉሥ በሰዎች ወሬ ‹‹ንግሥናዬ ለሌላ ይሰጣል ትላለህሳ›› በማለት ጻድቁን እጅና እግራቸውን አስሮ ካሠቃያቸው በኋላ እጃቸውን አስቆረጣቸው፡፡ ነገር ግን ለአቡነ ሲኖዳ እመ ብርሃን የብርሃን እጅ ተከለችላቸው፡፡ በጌቴሴማኒ ያለችው ሉቃስ የሳላትና ስርጉት የተባለችው የእመቤታችን ሥዕል በየጊዜው እየተገለጠች ታነጋግራቸው ነበር፡፡ ንጉሡ በስደትና በግዞት ብዙ እያሠቃያቸው ሳለ መልአክ መጥቶ ዕለተ ዕረፍታቸውን ነግሯቸው እሳቸውም ደቀ መዛሙርቶቻቸውን ጠርተው ከተሰናበቷቸው በኋላ ነው ንጉሡ በኅዳር 17 ቀን አንገታቸውን ያሰየፋቸው፡፡ ከአንገታቸው ውኃ፣ ደምና ወተት ፈሷል፡፡
ጻድቁ በሐይቅ ደሴት የተቀበሩ ቢሆንም ቀድሞ በሚያገለግሉበት በድፍን ምስራቅ ጎጃም ድርቅና ርኃብ ስለሆነ በደብረ ፅሞና ገዳም ይኖሩ የነበሩት አባ መቃርስ ዐፅማቸውን አፍልሰው በማምጣት በደብረ ዲማህ አጠገብ በስማቸው በተሰራው በደብረ ፅሞና ቤተ ክርስቲያን በክብር ሲያሳርፉት ወዲያው ዝናብ ጥሎ ድርቁም ጠፍቷል፡፡ ዐፅማቸውን ተሸክማ ያመጣችው በቅሎም ወልዳለች፡፡
ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ሲኖዳ ለማይወልዱ መካኖች እጅግ ልዩ ቃልኪዳን ነው የተሰጣቸው፡፡ መቃብራቸውን እየዞሩ እምነታቸውን እየተቀቡ ገድላቸውን እየታሹ የማይወልዱ መካኖች የሉም፡፡ ከሩቅም ሆነው በስማቸው ተስለው እምነታቸውን ተቀብተው የሚወልዱ በጣም ብዙዎች ናቸው፡፡
የጻድቁ ሌላኛው በስማቸው የተሰየመውና እጅግ ተአምረኛው ታቦታቸው ዛሬም አቡነ ሲኖዳ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከአ.አ 180 ኪ.ሜ ርቆ ከጣርማ በር አልፎ ሞላሌ ከተማ ውስጥ ይገኛል፡፡ በሰሜን ሸዋ በሚገኘው በዚህ ቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ በዘመናችንም በጣም በርካታ ተአምራት ይደረጋሉ፡፡ ለጻድቁ የተሰጠችውን የስዕለት በግ ጅብ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ገብቶ ሊበላ ሲል ቀንዱን ነክሶ ደርቆ ሞቶ ሲገኝ በጉ ግን ምንም አልሆነም፡፡ አቃቢቷም እንዲሁ ከትልቁ ተራራ ሥር በትልቅ ቅል ውኃ ቀድተው ሲመለሱ ገመዱ ተበጥሶ ቅሉ ከነውኃው ከትልቁ ገደል ገብቶ ድንጋይ ላይ ቢያርፍም ቅሉ ሳይሆን ድንጋዩ ነው የተሰበረው፡፡ የአካባቢው ነዋሪም ‹‹በጉ ጅብ ገደለ፣ ቅሉ ድንጋይ ሰበረ›› እያሉ ጻድቁን ያወድሷቸዋል፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages