ስንክሳር ዘወርኀ ኅዳር 18 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, March 1, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ኅዳር 18

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ኅዳር ዐሥራ ስምንት በዚህች ዕለት ሐዋርያው #ቅዱስ_ፊልጶስ#ቅዱሳት_ደናግል_አጥራስስና_ዮና#ቅዱስ_ኤላውትሮስና_እናቱ_እንትያ በሰማዕትነት አረፉ።


ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
ኅዳር ዐሥራ ስምንት በዚህች ዕለት ከአባቶቻችን ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ቅዱስ ሐዋርያ ፊልጶስ በሰማዕትነት የሞተበት መታሰቢያው ነው።
ይህም እንዲህ ነው ዕጣው ወደ አፍራቅያና ወደ አውራጃዋ ሁሉ በወጣ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በውስጧ ሰበከ። ልቡናንም የሚያስደነግጥ ድንቆች ታምራቶችንም አደረገ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ እግዚአብሔርንም ወደ ማወቅ ከመለሳቸው በኋላ ወደሌሎች ብዙ አገሮች ወጣ እያስተማረ ሰዎችን ወደ ሃይማኖት ሲጠራ ኖረ ።
ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ አገር ሒዶ የከበረ ወንጌልን ሰበከላቸው ብዙዎቹም ክብር ይግባውና በጌታችን አመኑ ያላመኑት ግን ይገድሉት ዘንድ ተማከሩ በንጉሥም ዘንድ ተወዳጅነትን ያገኙ ዘንድ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ሐዋርያ ፊልጶስን ይዘው አሠሩት ጽኑዕ ሥቃይንም አሠቃዩት እርሱም ይስቅባቸውና ከዘላለም ሕይወት ለምን ትርቃላችሁ የነፍሳችሁንስ ድኅነት ለምን አታስቡም ይላቸው ነበር እነርሱ ግን ብዙ ካሠቃዩት በኋላ ዘቅዝቀው ሰቀሉት ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።
ሥጋውንም በእሳት ሊአቃጥሉ በወደዱ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ከእጆቻቸው መካከል ነጠቃቸው እነርሱም ወደርሱ እየተመለከቱ ወስዶ ከኢየሩሳሌም አገር ውጭ አግብቶ ሠወረው ይህንንም ድንቅ ተአምር አይተው ሁሉም በታላቅ ድምፅ የቅዱስ ፊልጶስ አምላክ አንድ ነው እያሉ ጮኹ አሠቃይተው ስለገደሉትም ተጸጽተው አዘኑ ክብር ይግባውና በጌታችንም አመኑ ።
የቅዱስ ሐዋርያ ፊልጶስንም ሥጋ ይመልስላቸው ዘንድ ለመኑት ሰውን የሚወድ ቸር ይቅር ባይ ጌታችንም ልመናቸውን ተቀብሎ የሐዋርያ ፊልጶስን ሥጋ መለሰላቸውና እጅግ ደስ አላቸው ሁሉም ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት ገቡ ከሐዋርያውም ሥጋ ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ቀን ቅዱሳት ደናግል አጥራስስና ዮና በሰማዕትነት አረፉ። አጥራስስ ግን ጣዖታትን ለሚያመልክ ንጉሥ እንድርያኖስ ልጁ ናት እርሱም ከሰው ወገን ማንም እንዳያያት አዳራሽ ሠርቶ ለብቻዋ አኖራት እርሷ ግን ስለዚህ ዓለም ኃላፊነት የምታስብ ሆነች አውነተኛውንና የቀናውን መንገድ ይመራት ዘንድ በቀንና በሌሊት እግዚአብሔርን ትለምነው ነበር።
ወደ ፍላጽፍሮን ልጅ ወደ ድንግሊቱ ዮና ላኪ እርሷም የእግዚአብሔርን መንገድ ትመራሻለች የሚላትን ራእይ አየች ከእንቅልፏም ስትነቃ በልቧ ደስ አላት ወደ ዮና ድንግልም ላከች እርሷም ፈጥና መጣች ለዮናም ሰላምታ ሰጠቻትና ከእግርዋ በታች ሰገደችላት የእግዚአብሔርንም ሃይማኖት ታሰተምራትና ትገልጥላት ዘንድ ለመነቻት።
ድንግል ዮናም የእግዚአብሔር ልጅ ሰው የሆነበትን ምክንያት እግዚአብሔር አዳምን ከፈጠረበት ጊዜ በመጀመር ልትነግራት ጀመረች አዳም እንደበደለና ከተድላ ገነት እንደ ወጣ በኖኅም ዘመን የጥፋት ውኃ መጥቶ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንደደመሰሰ የእግዚአብሔርን ሕግ የጠበቁ ስምነት ሰዎች ብቻ እንደ ቀሩ ከዚህም በኋላ ዳግመኛ ሰዎች በምድር ላይ በበዙ ጊዜ እንደበደሉና ጣዖትን እንዳመለኩ እግዚአብሔርም ለአብርሃም እንደተገለጠለትና መርጦ ወዳጅ እንዳደረገው ከእርሱም ጋር ቃል ኪዳንን እንዳጸና እስራኤልንም ከግብጽ አገር እንዳወጣቸው የሰውንም ወገን ጠላት ሰይጣንን ከማምለክ ለእርሱም ከመገዛት ያድነው ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ መምጣቱንና ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው መሆኑን ነቢያት እንደሰበኩ ነገረቻት።
ሁለተኛም ስለ ከበረ ስሙ መከራ በመቀበል ለሚደክሙ ሰማያዊ ሀብት የዘላለም መንግሥትን እግዚአብሔር ስለ ሚሰጣቸው አስረዳቻት። አጥራስስም የዮናን ትምርቷን ሰምታ እጅግ ደስ አላት በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አመነች።
እሊህ ደናግልም ሌሊትና ቀን በተጋድሎ ተጠምደው በአንድነት ተቀመጡ የአጥራስስም አባቷ ይህን አያውቅም ከሌሊቶችም በአንዲቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አዩት እናቱን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንም አዩአት። እመቤታችንም ወደ ልጅዋ እግዚአብሔር እንደ ቁርባን አቀረበቻቸውና እርሱም ባረካቸው።
ከዚህም በኋላ ንጉሥ ወደ ጦርነት ሒዶ በተመለሰ ጊዜ ወደ ልጁ አጥራስስ ገብቶ ልጄ ሆይ ወደ መሞሸሪያሽ ከመግባትሽ በፊት ለአምላክ አጵሎን ዕጣን ታሳርጊ ዘንድ ነዪ አላት። አጥራስስ ድንግልም አባቴ ሆይ ነፍስህና ሥጋህ በእጁ ውስጥ የሆነ የፈጠረህን በሰማይ ያለ አምላክን ትተህ ነፍስ የሌላቸው የረከሱ ጣዖታትን ለምን ታመልካለህ ብላ መለሰችለት።
ንጉሥም እንዲህ ያለ ነገር ከቶ ያልሰማውን ከልጁ አፍ በሰማ ጊዜ አደነቀ በልጁ ላይ ምን እንደደረሰ ልቧንም ማን እንደለወጠው ጠየቀ የፍላጽፍሮን ልጅ ድንግል ዮና የልጁን ልብ እንደ ለወጠች ነገሩት።
ንጉሡም በእሳት ያቃጥሏቸው ዘንድ አዘዘ በወርቅና በብር በተጌጠ የግምጃ ልብሶችን እንደ ተሸለሙ አወጧቸው እነርሱ የነገሥታት ልጆች ስለሆኑ አላራቆቿቸውም ታላላቆችና ታናናሾች ሁሉም ሰዎች ስለ እሳቸው እያዘኑና እያለቀሱ ወጡ ነፍሳቸውንም እንዳያጠፉ ለንገሥ ይታዘዙ ዘንድ ለመኗቸው እነርሱ ግን ከበጎ ምክራቸው አልተመለሱም።
በዚያንም ጊዜ ጉድጓድ ቆፈሩላቸውና በውስጡ እሳትን አነደዱ ነበልባሉም እጅግ ከፍ ከፍ አለ ያን ጊዜ አንዷ ከሁለተኛዋ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ወደ እሳት ውስጥ ተወረወሩ ፊታቸውንም ወደ ምሥራቅ መልሰው በመቆም ረጅም ጸሎትን ጸለዩ ከዚህም በኋላ ነፍሳቸውን በእግዚአብሔር እጅ ሰጡ እሳቱም እንደውኃ የቀዘቀዘ ሆነ ምእመናንም ሥጋቸውን አነሡ ተጠጋግተውም ልብሳቸውንም ቢሆን ወይም የራሳቸውን ጠጉር እሳት ምንም ምን ሳይነካቸው አገኟቸው ። የመከራውም ወራት እስቲፈጸም በታላቅ ክብር በአማረ ቦታ አኖርዋቸው ከዚህም በኋላ ቤተ ክርስቲያን ሠርተውላቸው ሥጋቸውን በውስጥዋ አኖሩ ከእርሳቸውም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ ።

በዚህችም ዕለት ከሮሜ አገር ቅዱስ ኤላውትሮስና እናቱ እንትያ በሰማዕትነት አረፉ። ይህም ቅዱስ እግዚአብሔርን ከሚፈራ አንቂጦስ ከሚባል ኤጲስቆጶስ ዘንድ አደገ ዐሥራ ሰባት ዓመትም በሆነው ጊዜ ዲቁና ተሾመ ደግሞ በዐሥራ ስምንት ዐመቱ ቅስና ተሾመ ከዚህም በኋላ በሃያ ዓመቱ አላሪቆስ ለሚባል አገር ጵጵስና ተሾመ።
በዚያንም ወራት ንጉሥ እንድርያኖስ ወደ ሮሜ አገር መጣ ስለ ኤላውትሮስም ሰምቶ ወደርሱ ያመጣው ዘንድ ፊልቅስን አዘዘው ፊልቅስም በሔደ ጊዜ ቅዱሱን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል ሲያስተምር አገኘው። ፊልቅስም ትምርቱን በሰማ ጊዜ አመነና በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቀ።
ኤላውትሮስንም ወደ ንጉሥ እንድርያኖስ በአደረሱት ጊዜ ለአማልክት ሠዋ አንተ ነጻነት ያለህ ስትሆን ለተሰቀለ ሰው ለምን ትገዛለህ አለው ። ኤላውትሮስም ነጻነትማ ሰማይና ምድርን በፈጠረ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ነው ንጉሡም መንኰራኩር ካለው የእሳት ማንደጃ ውስጥ ጨምረው እንዲአቃጥሉት አዘዘ በጨመሩትም ጊዜ እሳቱ ጠፋ መንኩራኩሩም ተቆራረጠ። ንጉሡም አይቶ አደነቀ የሚያደርገውንም አጥቶ ከወህኒ ቤት ጨመረው ርግብም ከገነት መብልን አምጥታለት በልቶ ጠገበ ። ቆሊሪቆስ የሚባለውም መኰንን አይቶ በቅዱስ ኤላውትሮስ አምላክ አምኖ በሰማዕትነት ሞተ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለ።
ከዚህም በኋላ ፈረሶችን አምጥተው በሠረገላ ላይ እንዲጠምዷቸው ቅዱስ ኤላውትሮስንም ከሠረገላው በታች አሥረው ሕዋሳቱ እስኪሰነጣጠቅ ፈረሶችን እንዲአስሮጡአቸው እንድርያኖስ አዘዘ። በዚያንም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ወረደ ከማሠሪያውም ፈትቶ ወደ ከፍተኛ ተራራ ወሰደው በዚያም እግዚአብሔርን እያመሰገነ ከአራዊት ጋር ተቀመጠ ።
እንድርያኖስም አራዊትን ያድኑ ዘንድ ወታደሮቹን በአዘዘ ጊዜ በዚያ ተራራ ውስጥ ቅዱስ ኤላውትሮስን አግኝተው ከዚያ ወደ ንጉሥ እንድርያኖስ ወሰዱት። ንጉሡም ለአንበሳ እንዲሰጥ አዘዘ አንበሶችም የፊቱን ላብ ጠረጉለትና እግሮቹን ሳሙ ከዚህም በኋላ ተመልሰው ከአረማውያን መቶ ሃምሳ ሰው ገደሉ እንድርያኖስም አይቶ ቁጣን ተመላ ሁለት ወታደሮችን ከእንትያ እናቱ ጋር በጦር እንዲወጉት አዘዘ እርሷንም ብዙ ከአሠቃይዋት በኋላ የልጅዋን አንገት እንዳቀፈች ከእርሱ ጋር ወጓት ነፍሳቸውንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጡ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages