ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 29 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 29

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን መፃተኛ የሆነ የከበረች #ቅድስት_አክሳኒ አረፈች፣ተጋዳይ የሆነ #አባ_እስጢፋኖስ አረፈ፣ #አቡነ_ታዴዎስ_ዘጽላልሽ በሰማእትነት አረፉ፣ የጻድቃን #ቅዱሳን_ማኅበረ_ዶጌ #ከመድኃኔዓለም ጋር ማኅበር የጠጡ ቅዱሳን መታሰቢያቸው ነው፣ የከበሩ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ #አቡነ_ገብረ_ናዝራዊ_ዘቀወት አረፉ፡፡


ጥር ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን የስሟ ትርጓሜ መፃተኛ የሆነ የከበረች አክሳኒ አረፈች፡፡ እርሷም ከሮሜ አገር ለከበሩ ሰዎች ልጅ ናት ወላጆቿም ከርሷ በቀር ልጅ የላቸውም እርሷም የምትጋደል ሆነች በቀንና በሌሊትም ትፆማለች ትፀልያለች በሮሜ አገር ወዳለ የደናግል ገዳም በመሄድ ከእነርሱ ጋር ታገለግላለች ከአባቷ ቤት የሚያመጡላትን ምግብ ለድሆችና ለምስኪኖች ሰጥታ እርሷ ከደናግል ምግብ ትመገበለች የደናግል መነኮሳያትንም ጋር አንድ ያደርጋት ዘንድ እግዚአብሄርን አብዝታ ትለምን ነበር።
ከዚህም በኃላ ወላጆች ሊአጋቧት አስበው ከሮሜ አገር ታላላቆች ለአንዱ አጭዋት የወርቅ ልብሶችን ከወርቅና ከብር የተሰሩ የከበሩ ሽልማቶችንና ጌጦችንም አዘጋጁላት።
የጋብቻውም ቀን ሲደርስ እናቷን እናቴ ሆይ በምትጋቡኝ ጊዜ ወደ ደናግሉ መሄድ አይቻለኝም እኔ ዛሬ ሄጄ በረከታቸውን ተቀብዬ በረከታቸውን ተቀብዬ ሰላምታ ሰጥቻቸው ፈጥኜ መመለስ እሻለሁ አለቻት። እናቷም የነገስታት የሆነ የወርቅ ልብሶችን አልብሳ ሴቶች አገልጋዮችን ከእርሷ ጋር አድርጋ አሰናባተቻት።
እርሷ ግን ወደ ባህር ወደብ ተጉዛ መርከብንም አግኝታ ተሳፈረችና ወደ ቆጵሮስ ደሴት ሄደች።ወደ ከበረ ኤጲፋንዮስም ደርሳ ኀሳቧን ሁሉ አስረዳችው የከበረ ኤጲፋንዮስም ወደ እስክንድርያ አገር ሰደዳት ወደዚያም በደረሰች ጊዜ በህልሟ የከበረ ሀዋርያ ጳውሎስ ተገልፆ ስሙን ነገራትና የምትሰራውን ሁሉ አስተማራት።
በማግስቱም ወደ ሊቀ ጳጳሳት ቴዎፍሎስ ገባች የራሷንም ጠጉር ተላጭታ የምንኩስና ልብስን ለበሰች ከርሷ ጋር ያሉ ሽልማቶችንና ጌጦችን የወርቅ ልብሶችንም ሸጠችና በሰማእታት መጀመሪያ በከበረ እስጢፋኖስ ስም ቤተ ክርስቲያን ሰራች አባ ቴዎፍሎስም ብዞዎች ደናግል መነኮሳይያትን ሰበሰበላትና በዚያ ገዳም ከርሷ ጋር የሚኖር ሆኑ።
ይቺም ቅድስት አክሳኒ ታላቅ ተጋድሎን ጀመረች እርሷ ከጥሬ ባቄላ በቀር በእሳት ያበሰሉትን አትቀምስና በምትተኛም ጊዜ ያለ ምንጠፍ በምድር ላይ ትተኛ ነበር እንዲህም እየተጋደለች ሀያ አመት ያህል ከዚያም የሚበዛ ኖረች ከዚህም በኃላ ጥቂት ታመመችና አረፈች።
ልኡል እግዚአብሄርም የሰጣትን ልእልና ሊገልጥ ወደደ። በአረፈችበትም አለት ሰዎች በቀትር ጊዜ የብርሀን መስቀል በሰማይ ውስጥ አዩ ብርሀኑም የፀሀይን ብርሀን ሸፍኖ ነበር የሚያበሩ ከዋክብትም አክሊላትም በዙሩያው ሆነው ስጋዋን ከደናግል ስጋ ጋር እስከ አኖሩ ድረስ የሚያበሩ ሆኑ ከዚያም በኃላ ተሰወረ ይህም ስለርሷ እንደተገለጠ ህዝቡ አወቁ።
በዚያንም ጊዜ እነዚያ ሁለቱ አገልጋዮቿ የዚችን ቅድስት አክሊኒ ከመጀመሪያው እስከ አረፍቷ ያለ ገድሏን ለሊቀ ጳጳሳቱና ለህዘቡ ሁሉ ስማቸውንም ለውጣ እህቶቿ እንዳለቻቸው እርሷንም እመቤታችን ማለት ሳይሆን እኅታችን እንዲሏት ምስጢሯንም ሁሉ እንዲሰውሩ እንዳማለቻቸው ተናገሩ። ሊቀ ጳጳሳቱና ህዝቡም ሁሉ አደነቁ ገድሏንም እስከመጨረሻ ፃፉ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን ተጋዳይ የሆነ አባ እስጢፋኖስ አረፈ፡፡ ይህም ቅዱስ ቅዱሳን ገዳማውያንን በመፈለግ በበረሀ ውስጥ ሲዞር የወደቀች የሰው ራስ አገኘ እርሷም ስጋ የሌላት አጥንት ብቻ ናት።
ስራዋንም ያስረዳው ዘንድ ወደ እግዚአብሄር ለመነ በዚያንም ጊዜ ከዚያች ራስ ውስጥ እንዱህ የሚል ቃል ወጣ እኔ በብዝበዛ ጭምር የማተርፍ ነጋዴ ነበርኩ መመፅወትንም አላውቅም በእኔ ዘንድ ካለው የገንዘብ ብዛትም አልጠግብም ነበር በአንዲትም እለት ወደ ንግድ ሩቅ ወደ ሆነ አገር ስጓዝ ውኃ ወደ ሌለበት በረሀ ደረስኩ የቀን ሀሩርም በፀና ጊዜ ግመሎቼ ሞቱ ባሮቼም ሸሹ ብቻዩንም ቀረሁ።
በሶስትኛውም ቀን አይኖቼ ከበዱኝ እንደፉጨትም ያለ ሰማሁ ያንጊዜ ነፍሴ ወጣች እንደስራዬም ቅጣቴን ልቀበል ወደ ስቃይ ቦታ ወሰዱኝ አንተም በለመንክ ጊዜ ስራዬን እነግርህ ዘንድ ወዳንተ አመጡኝ አሁንም ወደ ስቃይ ቦታ እንደይመልሱኝ እግዚአብሄርን ስለ እኔ ምህረትን ትለምነው ዘንድ እማልድሀለሁ አለው።
ቅዱሱም ወደ እግዚአብሄር ስለርሱ ለመነለት በዚያንም ጊዜ ስለአንተ ምሬዋለሁ የሚል ቃልን ሰማ ይህንንም ሰምቶ ወደ በዓቱ ሄደ እስከ አረፈ ድረስም እያለቀሰና ደረቱን እየደቃ ኖረ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች እለት አቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ በሰማእትነት አረፉ፡፡ አባታቸው ካህኑ ሮማንዮስ የደብረ ሊባኖሱ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አጎት ሲሆኑ እናታቸው ማርታ ይባላሉ፡፡ የትልድ ቦታቸው ጽላልሽ ዞረሬ ነው፡፡ ሲወለዱ ዓምደ ብርሃን ተተክሎ የታየ ሲሆን እርሳቸውም በብርሃን ልብስ ተጠቅልለው ታይተዋል፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ለሊቀ ካህናቱ ለሕይወት ብነ በጽዮን ተሰጥተው ሃይማኖትን በሚገባ ተምረዋል፡፡
አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዳሞት ተሻግረው ሞተሎሚን አስተምረው ካሳመኑት በኋላ አቡነ ታዴዮስን ወደ እርሳቸው እንዲመጡ ልከውባቸው ሄደው አቡነ ተክለ ሃይማኖትን እያገለገሉ ዘጠኝ ዓመት ተቀመጡ፡፡ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ግን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል ሲሄዱ አቡነ ታዴዎስም ወደ ጽላልሽ ተመልሰዋል፡፡ ሁለቱም ከ32 ዓመት በኋላ ተመልሰው በጽላልሽ ተገናኘተው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለአቡነ ታዴዎስ ማዕረገ ምንኩስናን ሰጥተዋቸዋል፡፡
አቡነ ታዴዎስም በሥጋ ዕድሜ ታላቅ ቢሆኑም እንደታናሽ ብላቴና አቡነ ተክለ ሃይማኖትን እያገለገሉ በደብረ ሊባኖስ ተቀምጠዋል፡፡ ከዚህ በኋላ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አቡነ ታዴዎስን ወደ ጽጋጋ እንዲሄዱ ነገሯቸው ምክንያቱም አቡነ አኖሬዎስ በዚያ ሲያስተምሩ ከሃዲያን ደብድበው አስረዋቸው ነበር፡፡ እሳቸውም ታስረው ሳለ ወደ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘንድ የሚላካቸው ሲያስቡ ቁራ መጥቶ ‹‹እኔ እላክሃለሁ›› ቢላቸው ‹‹ክፋትህ እንደ መልክህ ነው›› ብለው እምቢ አሉት፡፡ ርግብ መጥታ ‹‹እኔ እላክሃለሁ›› ብትላቸው ‹‹መጥተህ አድነኝ›› ብለው በክንፏ ላይ ጽፈው ልከዋት እርሷም መልእክቱን ለተክለ ሃይማኖት አድሳ ነበር፡፡ ስለዚህም ነው አቡነ ታዴዎስን ሕዝቡን ከኃጢአት ግዞት አኖሬዎስን ከእስራት እንዲያስፈቱ የላኳቸው፡፡
አቡነ ታዴዎስም በፋስ ሠረገላ ተጭነው መዩጥ ከተባለውና አኖርዮስን ካሰራቸው ንጉሥ ፊት ቢደርሱ ንጉሡ በግንጋጤ መልአክ የመጣበት መስሎት ሲፈራ ከሰው ወገን መሆናቸውን ነግረው ክርስትናን አስተማሩት፡፡ ጋኔን ከእሳት ጥሎት ሲሠቃይ የሚኖርና ሊሞት የደረሰ ልጁን ቢፈውሱለት በትምህርታቸውና በተአምራታቸው አምኖ ሕዝቡ ክርስትናን እንዲቀበል በአዋጅ አስነገረ፡፡ አፍጃል የሚባለው ባለጸጋ ወደ አቡነ ታዴዎስ ቀርቦ ሲማር ‹‹ባለጸጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል›› (ማቴ 19፡24፣ ማር 10፡25፣ ሉቃ 18፡25) የሚለውን የወንጌል ቃል ሲሰማ ለአእምሮው ረቆበት ‹‹እስቲ አድርገህ አሳየኝ?›› አላቸው፡፡ አቡነ ታዴዎስም እናቲቱን ግመል ከነጇ ቀጥሎም 28 ግመሎችን በየተራ በመርፌ ቀዳዳ እያሾለኩ አሳይተውታል፡፡ ሕዝቡ ሁሉ በእጅጉ ሲገረምና ‹‹በአምላከ ታዴዎስ ስም አምናለሁ›› ሲል የባለጸጋው ልጅ ሙሳ ግን ‹‹በምትሃት አሳይቶን ነው እንጂ የእውነት አይደለም›› በማለት አባቱንም እንዳያምን ይናገር ጀመር፡፡ ይህንንም ሲናገር በመጀመሪያ ያለፈችው እናቲቱ ግመል እረግጣ ገደለችው፡፡
አቡነ ታዴዎስም ንጉሡን፣ አባቱን አፍጃልንና ሕዝቡን የሞተ እንደሚነሣ ሲያስምሯቸው ‹‹የሞተ ይነሣልን? እስኪ ይህ የሞተው ልጅ ይነሳና ሁሉም አይቶ ይመን›› አሏቸው፡፡ እሳቸውም ‹‹ዛሬ ተቀብሮ ይዋልና ነገ በሦስተኛው ይነሣል›› ብለዋቸው ተቀብሮ ዋለ፡፡ በማግሥቱም አፍጃልን ጠርተው ‹‹‹አልዓዛርን ከሞት ባስነሣው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ልጄ ሆይ ና ውጣ› ብለህ ከልጅህ መቃብር ላይ አኑረው› ብለው ዘንጋቸውን ሰጡት፡፡ ሄዶም እንዳሉት ቢያደርግ ልጁ አፈፍ ብሎ ተነሥቷል፡፡ ይህንን ያዩ የሀገሩ ሰዎች ሁሉም አምነው ተጠምቀዋል፡፡ እሳቸውም 12 አብያተ ክርስቲያናትን አሳንጸው ሞቶ የተነሳውን ሙሳን ሙሴ ብለው ሰይመው አስተምረው ሊቀ ካህናት አድርገው ሾመውት አቡነ አኖሬዮስን ይዘው ወደ ጽላልሽ ዞረሬ ተመልሰዋል፡፡
አቡነ ተክለ ሃይማኖት ካረፉ በኋላ አባ ያዕቆብ የተባሉ ጳጳስ ከግብፅ መጡ፡፡ የአቡነ ታዴዎስን ዜና ሲሰሙ ተደስተው ከአቡነ ፊሊጶስ ጋር ሆነው አስጠርተዋቸው ‹‹የአባታችሁን ዜና ገድል ንገሩኝ›› አላቸው፡፡ አቡነ ታዴዎስም ‹‹ጨዋታ በአስተርጓሚ አይሰምርም›› ብለው ወደ ጌታችን ቢጸልዩ የጳጳሱ ቋንቋ ለታዴዎስ፣ የታዴዎስም ቋንቋ ለጳጳሱ ተገልጦላቸው የመሸ የነጋ ሳይመስላቸው 40 ጾምን ሲጨዋወቱ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ጳጳሱ ከንጉሡ ተማክረው ‹‹ሊቀ ካህናት ዘጽላልሽ›› ብለው ሾመዋቸዋል፡፡
በነግህና በሰርክ ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ፣ ቀን ወንጌልን እየሰበኩ፣ ሌሊት ከባሕር ገብተው ሲጸልዩ እያደሩ በታላቅ ተጋድሎ እየኖሩ ሳለ ከ10 ዓመት በኋላ ሰይጣን በንጉሡ በዓምደ ጽዮን ፍቅረ ዝሙት አሳድሮበት በክፉዎችም ምክር አታሎት የአባቱን ቅምጥ አገባ፡፡ አቡነ ታዴዎስም ይህን ሲሰሙ እንደ ነቢዩ ኤልያስና እንደ መጥምቁ ዮሐንስ በቀጥታ ሄደው ንጉሡን ገሥጸው አወገዙት፡፡ ገሥጸውና አውግዘው አቡነ ማትያስን አስከትለው ሲመለሱ ቅምጧ የንጉሡ ሚስት በፈረስ ተከትላ ደርሳ የኋሊት አሳስራ ዛሬ ‹‹ማርያም ገዳም›› ከሚባለው ቦታ ፊት ለፊት ካለው ትልቅ ገደል ውስጥ ሁለቱንም ጣለቻቸውና ጥር 29 ቀን በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡
በሰማዕትነት ዐርፈው ደማቸው ከፈሰሰበት ከገደሉ ስር በፈለቀው ጸበላቸው ‹‹ታዴዎስ ወማትያስ›› እያለ ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እያለ የተጠመቀ ሰው እንደ 40 ቀን ሕፃን እንደሚሆን ጌታችን ቃልኪዳን ገብቶላቷቸዋል፡፡ ይህ ሰማዕትነት በተቀበሉበት አካባቢ የተሠራው ቤተ ክርስቲያናቸው በጠላት ወረራ ጊዜ ፈርሶ ቦታው ጠፍ ሆኖ የኖረ ቢሆንም የአካባቢው ሕዝብ ቦታውን ከልሎ በክብር ሲጠብቀው ስለኖረ ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ የአቡነ ታዴዎስ ታቦታቸው በ2005 ዓ.ም ከኢቲሣ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ወጥቶ ጻድቁ ሰማዕትነት በተቀበሉበት አካባቢ በተሠራው መቃኞ ቤተ ክርስቲያናቸው በታላቅ ክብር ገብቷል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑም ከኢቲሣ በእግር የአንድ ሰዓት ተኩል ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች እለት የጻድቃን ቅዱሳን ማኅበረ ዶጌ አክሱም አካባቢ በቁጥር ወደ 3000 የሚሆኑ ከመድኃኔዓለም ጋር ማኅበር ይጠጡ የነበሩ በአንድ ላይ የተሰወሩ ቅዱሳን መታሰቢቸው ነው፡፡ እነዚህም ጌታችን መድኃኔዓለም ክርስቶስ በመካከላቸው ተገኝቶ የጽዋ ማኅበራቸውን አብሯቸው የጠጣ ሦስት ሺህ ቅዱሳን ‹‹ማኅበረ ጻድቃን ወይም ማኅበረ ደጌ›› እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ ማኅበሩን ያቋቋመው ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ነው፡፡ በኋላም ከመድኃኔዓለም ክርስቶስ ጋር አብረው ማኅበር የጠጡ እነዚህ ሦስት ሺህ ቅዱሳን አክሱም አካባቢ ባለው በአቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ገዳም ጥር 29 ቀን በዓመታዊ መታሰቢያ በዓላቸው ይከብራሉ፡፡ ማኅበረ ዴጌ ማለት የደጋጎች ሀገር ማለት ነው፡፡ የደጋጎች ሀገር የተባለበት ምክንያት ብዙ ሺህ ቅዱሳን ተሰብስበው ስለሚኖሩበት ነው፡፡ ገዳሙ የሚገኘው በትግራይ ክልል በአክሱም አውራጃ ከአክሱም ከተማ ወደ ደቡብ ምዕራብ በሚወስደው መንገድ አስራ ሁለት ኪሎሜትር ያህል ርቀት ላይ ነው፡፡
በቦታው ላይ ጥንት መሥዋዕተ ኦሪት ይሠዋበት ነበር፡፡ በኋላም በ40 ዓ.ም ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ወደ አገራችን በመጣ ጊዜ በቦታው ላይ ወንጌልን ሰብኮ ብዙዎችን አጥምቋል፡፡ በወቅቱ የነበረችው ንግሥትም በቅዱስ ማቴዎስ እጅ ተጠምቃለች፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም ንግስቲቱን ካጠመቀ በኋላ ቀጥሎ መኳንንቱን፣ መሳፍንቱንና የጦር ሠራዊቱን ሁሉ አጥምቋቸዋል፡፡ ከዚህም በኋላ የጻድቃንን ማህበር አቋቁሞ በጌታችን ስም በየወሩ በ29 ቀን እየተሰበሰቡ ጽዋ እንዲጠጡ አድርጓቸው ወደ ኢየሩሳሌም ሄዷል፡፡
በ365 ዓ.ም በአስፍሕ ወልደ አብርሃም ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ዘመነ መንግስት ‹‹ሮምያ›› ከምትባል መንደር ቅዱሳን ‹‹ስለ ጽድቅ ብለው የሚሰደዱ ብፁአን ናቸው መንግስተ ሰማያት የነርሱ ናትና›› ያለውን ዳግመኛም ‹‹አባቱንና እናቱን ሚስቱንና ልጆቹን ያልተወ ሊያገለግለኝ አይችልም›› ብሎ ጌታችን የተናገረውን አስበው ቅዱሳን የዚህም ዓለም ጣዕም ጥቅም ንቀው ሀገራቸውን ትተው መንነው ወደ ኢትዮጵያ የመጡትን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ እነዚህም ቅዱሳን በአክሱም ከተማ በስተሰሜን በሐውልቱ ጀርባ ቤተ ቀጠንት በሚባል ስፍራ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ያህል እንደ ተቀመጡ በዚያም ምቾትና ድሎት ስለተሰማባቸው ‹‹ለዚሁ ለዚሁማ ሀገራችንን ለምን ትተን መጣን? ስለዚህ ሱባዔ ገብተን በጾም በጸሎት ተወስነን የምንሄድበትን ቦታ በረከተ ነፍስ የምናገኝበትን ስፍራ እግዚአብሔር እንዲያሳየን እናመልክት›› ብለው ሱባዔ ገቡ ጾም ያዙ፡፡
ከሱባዔውም በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገልጻላቸው ግማሾቹን እያንዳንዳቸው የሚኖሩበትን በዓት አመልክታቸው፣ በዚያም በጾምና በጸሎት ጸንተው እንዲኖሩ ነገረቻቸው፡፡ ሦስት ሺህ ያህሉን ደግሞ ከላይ ወደጠቀስነው ሥፍ ሄዱ፡፡ ከእነርሱ የተቀሩት ደግሞ ወደ ቆየፃ ሓባር፣ ተድባ፣ አኮርየን፣ ተንስሓ፣ ደብረ አንሳ ወደ ተባሉ ቦታዎች ሄደዋል፡፡ ተጨማሪ ሥስት ሺህ የሚሆኑት ደግሞ እዚያ ከነበሩት ጋር ተደመሩ፡፡ ከዚህም በኋላ እነዚህ ቅዱሳን ‹‹ከሁሉ ፍቅር ይበልጣል›› የሚለውን ጠብቀው በእምነት በፍቅር በአንድነት ጸንተው በየሳምንቱ እሁድ እሁድ ተዝካረ ሰንበትን ጠብቀው ማኅበር ይጠጡ ጀመር፡፡ በዚህም ጊዜ የማኅበረ ዴጌ ታሪክ ተቀየረ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአምሳለ ነዳይ ድሀ መስሎ በመካከላቸው ተገኘ፡፡ ግን ማንም አላወቀውም ነበር፡፡ ጌታችንም ከእነርሱ ጋር አንድ ማኅበርተኛ ሁኖ እንዲታወቅ ጠየቃችው፣ እነርሱም ፈቀዱለትና አንዱ የማኅበሩ አባል ሆነ፡፡ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ያህልም ከእነርሱ ጋር ሳይለይ ቆየ፡፡ በዚሁ ጊዜ ‹‹እስቲ ለእኔም ተራ ስጡኝ እንደአቅሜ ዝክር ላውጣ›› አላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ድህነቱን አይተው ‹‹አይሆንም አንተ ድሀ ነህ፣ ከኛ ጋር ሁነህ በዓሉን አክብር እንጂ ምን አለህና ነው የምትደግሰው? ይቅርብህ›› አሉት፡፡ እርሱም ‹‹አይሆንም ስጡኝ እንጂ›› ብሎ ግድ አላቸው፡፡ እነርሱም ካልክማ ብለው ቀን ወስነው ሰጡት፡፡ ቀኑም ጥር 29 ነበር፡፡
ከማኅበርተኞቹ መካከል ‹‹ሳይዳ›› የሚባል ሰው ነበር፡፡ ይህም አሳላፊ ወይም ሙሴ ነበር፡፡ ይህም ሰው እንግዳና ድሀ ሰው ፈጽሞ አይወድም ነበርና ጌታችንም ከማኅበርተኞቹ መካከል ሲገኝ ድሀ መስሎ ስለነበር በጣም ይጠላው ነበር፡፡ ጌታችን አንድ ዓመት ከስድስት ወር ከእነርሱ ጋር ሲቀመጥም አንድ ቀን እንኳን አንድ ዋንጫ የወይን ጠጅ ሰጥቶት አያውቅም ነበር፡፡ የሆኖ ሆኖ መድረሱ አልቀረም የጌታችን ማኅበር ደረሰ፡፡ እንደማህበሩ ስርዓት የወይን ጠጅ የሚጠመቅባቸውን ጋኖች የሚያጥበው ሙሴው ወይም አሳላፊው ነው፡፡ ስለሆነም በሥርዓቱ መሠረት ጌታችን ሙሴውን ጠርቶ ጋኖችን እጠብልኝ አለው፡፡ አሳላፊውም በቁጣ ‹‹አንተ ቤትህ የማይታወቅ፤ ከየት አምጥተህ ማኅበር ልታደርግ ነው?›› አናንቆ አልታዘዝህም ብሎ ሄደ፡፡ ይህን የተመለከተው ጌታችንም አንድ እረኛ ጠርቶ ‹‹አንተ ልጅ ከብቶችህን እኔ እጠብቅልሃለሁና በዚህ ውሀ አምጣልኝ›› አለው፡፡ ትንሹ እረኛ ልጅም ገምቦውን ይዞ ትንሽ ወጣ እንዳለ ጌታችን ዘወትር በሚቀመጥበት ድንጋይ ላይ ሆኖ ዘንጉን ወደ ልጁ አቅጣጫ ወረወረው፣ ዘንጉንም ከልጁ ፊት ሂዶ ተተከለ፡፡ ልጁንም ጠርቶ ዘንጉንም እንዲነቅለው አዘዘው፡ ልጁም እንደታዘዘው ዘንጉን ቢነቅለው ውሀ ፈለቀ፡፡ ጌታችንም ‹‹ከእርሱ ቀድተህ አምጣልኝ›› አለው፡፡ ልጁም ከዚያ ውሀ ቀድቶ አመጣለትና ጋኖቹን አጠባቸው፡፡
በበዓሉ ቀን ማኅበርተኞቹ ‹‹ምን ሊያበላን ነው! ምንስ ሊያጠጣን ነው!›› ሳይሉ ሁሉም ተሰበሰቡ፡፡ ጌታችንም በፊታቸው ጋኖቹን ቢባርካቸው በተአምራት የወይን ጠጅ ሞልተው ተገኙ፡፡ ቀድቶ ቢሰጣቸውና ቢቀምሱትም በጣም ግሩም ጣፋጭ ስለነበር እጅግ አደነቁ፡፡ እነርሱም ጌታችንን ከጻድቃን አንዱ ስለመሰላቸው ከእግሩ ላይ ወድቀው ‹‹እስካሁን ድረስ ሳንበድልህ አልቀረንምና ይቅር በለን›› ብለው ለመኑት፡፡ እርሱም ‹‹ተነሱ›› ብሎ ካስነሣቸው በኋላ ‹‹እናንተ ምንም አልበደላችሁም፣ የጠየኳችሁን አድርጋችኋል የበደለኝ ግን አሳላፊያችሁ ነው፣ አንድም ቀን እንኳን አንድ ዋንጫ የወይን ጠጅ አልሰጠኝምና አፈራርዱኝ›› አላቸው፡፡ ነገር ግን ሙሴው ወይም አሳላፊው የማያፍር ደፋርና ርጉም ስለነበር ‹‹‹ይህ ሰው በልቶ አልበላሁም፣ ጠጥቶ አልጠጣሁም› የሚል ስለሆነና ስለማይጠግብ ነው እንጂ እንዲያውም ለእናንተ አንድ አንድ ዋንጫ ሲሰጣችሁ ለእርሱ ሁለት ሁለት ነበር የሚሰጠው›› ብሎ የሐሰት ቃል መለሰ፡፡ ጌታችንም በዚህ ጊዜ ‹‹እንግድያስ እኔ የጠጣሁበት ዋንጫ ትቅረብና ትመስክርብኝ›› አለው፡፡ በዚሁ ተስማምተው ሙሴው ሄዶ አንድ ሸራፋ ዋንጫ አምጥቶ ‹‹በዚህ ነበር የሚሰጠውና የሚጠጣው›› ብሎ አቀረበ፡፡ በዚህም ጊዜ ዋንጫዋ ከተቀመጠችበት አንድ ክንድ ከስንዝር ወደላይ ተነሥታ በሰው አንደበት በመመስከር ‹‹ዓለማትን የፈጠረ አምላክ ምስክሬ ነው እኔ የያዝኩትን የወይን ጠጅስ እርሱ በከንፈሩ አልነካኝም በሌሎቹ ሰዎች እጅ ግን ተይዤ ያየኝ ነበር›› አለች፡፡ ያንጊዜም ሙሴውን ሳይዳን እንደ ዳታንና እንደ አቤሮን ምድር ተከፈተችና ዋጠችው፡፡ ማኅበረ ጻድቃንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ዐውቀው እንደገና ከእግሩ ወድቀው ይቅርታ እንዲያደርግላቸው ለመኑት፡፡ ጌታችንም ‹‹ይቅር ብያችኋላሁ›› ካላቸው በኋላ ‹‹ስማችሁን የጠራ፣ በስማችሁ ተዝካር ያወጣ፣ ድኆችን የረዳ፣ ያለበሰ፣ ያጎረሰ፣ የመጸወተ፣ ቤተ ክርስትያን የሠራ ያሠራ እሰከ 14 ትውልድ ድረስ ምሬላችኋለሁ›› የሚል ድንቅ ቃል ኪዳን ገባላጣቸው፡፡ ዳግመኛም ‹‹ይህችን የተቀደሰች ቦታችሁን መጥቶ የተሳለመ ቢኖር ኢየሩሳሌምን እንደተሳለመ እቆጥርለታለሁ›› አላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ‹‹እንደነ ሄኖክና ኤልያስ ከሞት ተሰወሩ›› ብሏቸው በማግሥቱ ጥር 30 ቀን ከዚህ ዓለም ሠውሯቸዋል፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች እለት የከበሩ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ገብረ ናዝራዊ ዘቀወት አረፈ፡፡ ጻድቁ አቡነ ገብረ ናዝራዊ በሰሜን ሸዋ ይፋትና ጥሙጋ ደብረ ሲና ውስጥ ቀወት በምትባለው ቦታ በ13ኛው መ/ክ/ዘ ተወለዱ፡፡ አባታቸው ስቡሐ አምላክ እናታቸው ክርስቶስ ክብራ የሚባሉ የነገሥታት ወገን ናቸው፡፡ የአባታችን የስማቸው ትርጉም ‹‹በስዕለት ለእግዚአብሔር የተሰጠ ልዩና የተቀደሰ ማለት ነው፤ ይህም የበኩር ልጅ ስለሆኑና በስዕለት የተሰጡ ስለሆነ ነው፡፡ ወላጆቻቸውም ፈሪሃ እግዚአብሔርንና የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በሚገባ እያስተማሩ በምግር በሃይማኖት ኮትኩተው አሳደጓቸው፡፡ ዲቁናን ከተወበሉ በኋላ በሸዋ አካባቢ እየተዘዋወሩ ወንጌልን መስበክ ጀመሩ፡፡ ነገር ግን በዚህ በሐዋርያዊ አገልግሎታቸው ጊዜ ብዙ ፈተና ገጠማቸው ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ከላይ በአቡነ ታዴዎስ ገድል ላይ እንዳየነው ሰይጣን በንጉሡ በዓምደ ጽዮን ፍቅረ ዝሙት አሳድሮበት በክፉዎችም ምክር አታሎት የአባቱን ሚስት በማግባቱ ምክንያት አቡነ ገብረ ናዝራዊም ይህን ሲሰሙ እንደ ነቢዩ ኤልያስና እንደ መጥምቁ ዮሐንስ በቀጥታ ሄደው ንጉሡን ገሥጸው አወገዙት፡፡ በዚህም ምክንያት ንጉሡ በማሠር ብዙ አሠቃያቸው፡፡ ጳጳሱ አባ ያዕቆብን ጨምሮ ብዙ ቅዱሳንም ለስደት ተዳረጉ፡፡
አቡነ ገብረ ናዝራዊም አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ከእሥር እንደተፈቱ ወደ ላሊበላ በመሄድ 12 ዓመታት በተጋድሎ ኖሩ፡፡ ወደ ሐይቅ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ገዳምም በመሄድ ካገለገሉ በኋላ ወደ ትግራይ ሄዱ፡፡ ከዚያም ግብፅን አቋርጠው ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ከጳጳሱ አባ ያዕቆብ ጋር ሲነሡ አባ ያዕቆብ ‹‹በዓትህ ኢትዮጵያ ብቻ ናት›› ብለው ስለነገሯቸው ሀሳባቸውን ትተው የጳጳሱን ምክራቸውን ተቀበሉና ከጉዞአቸው ቀሩ፡፡
ከዚህም በኋላ ወደ አዲግራት በመሻገር ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ፈጽሙ፡፡ መጀመሪያ እንደመጡ ያረፉባት አጋዝና በተባለቸው ተራራማ ቦታ ነበር፡፡ የአባታችን ሁለተኛ ቤተ ክርስቲያናቸው በዚህ ቦታ ላይ ታንጾ ይገኛል፡፡ በቦታውም ላይ 8 ዓመት ኖረውበታል፡፡ ወደሸለቆመም ዘቅዝቀው ወርደው ወደ ማየ ኢየሱስ በመሄድ ሓባ በምትባለው ተራራ ላይ የቁፋሮ ሥራ ጀምረው ባለ ሁለት ዓምድ የሆነ አንድ በር ያለው ቤተ ክርስቲያን አንጸው ሲያበቁ አሁን ወዳለው ገዳማቸው ደብረ ኀረይክዋ መጡ፡፡
አቡነ ገብረ ናዝራዊ ደብረ ኀረይክዋ ዓምባ ላይ ከወጡ በኋላ በመጀመሪያ የተለያየ መጠንና መጠሪያ ስም ያላቸውን ከዓለት ላይ የተፈለፈሉ አስደናቂ የሆኑ ከ44 በላይ የውኃ ጉድጓዶችን አንጸዋል፡፡ ከጉድጓዶቹም በተአምራት ጸበሎች ፈልቀውላቸዋል፡፡ እነዚህንም ጸበሎች እስከዛሬ ድረስ መጠናቸው ምንም ሳይጎድል ገዳማውያኑ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ ጻድቁ በዚሁ ቦታ ከዓለት ላይ ፈልፍለው ያነጹት አስደናቂ ቤተ መቅደስ ይኛል፡፡ መካነ መቃብራቸውም በዚሁ ገዳማቸው ውስጥ በክብር ተቀምጦ ይገኛል፡፡
አቡነ ገብረ ናዝራዊ በጾምና በጸሎት ተወስነው ሕዝቡን በማስተማር ብዙ አስገራሚ ተአምራትን በመፈጸም ላይ እንዳሉ የቀድሞ ጓደኛቸው የነበሩትና በኋላም የነገሡት ዐፄ ዓምደ ጽዮን በትግራይ ከፍለ ሀገር አጋሜ አውራጃ ዓምባ ጽዮን በተባለው ተራራ ላይ ሽፍቶች ተነሥተው መሽገው ነበር፡፡ ንጉሡም እነዚህን የተነሡባቸውን ሽፍቶች ለመያዝ ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት ብለው 10 ሺህ ሠራዊት ይዘው ወደ አካባቢው ዘመቱ፡፡ ንጉሡም በአካባቢው እንደደረሱ አቡነ ገብረ ናዝራዊ በዚያ እንዳሉ ስለሰሙ መልእክተኞችን ልከው አስመጧቸውና የመሸጉትን ሽፍቶች በምን ዓይነት ዘዴ ድል ማድረግ እንደሚችሉ የጠቋቸው፡፡ አቡነ ገብረ ናዝራዊም ‹‹ለሦስት ቀናት ያህል በቤተ ክርስቲያን ጸሎትና ምህላ ይደረግ፣ ሕፃናት የእናቶቻቸውን ጡት እንዳይጠቡ ይከልከሉ፣ የሚጠቡ የቀንድ ከብቶችም ከጥጃዎቻቸው ጋር እንዳይገናኙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይደረግ›› ብለው ነገሯቸው፡፡ ንጉሡም ጻድቁ እንዳሏቸው ቢያደርጉ በሦስተኛው ቀን ሽፍቶቹን በቀላሉ ማረኳቸውና አገሪቱ ሰላም ሆነች፣ ንጉሡም እጅግ ደስ አላቸው፡፡ አቡነ ገብረ ናዝራዊንም በማስጠራት ‹‹ያልከው ተፈጸመ፣ ድል አድርጌያለሁና ደስ ብለኛል፡፡ የትኛውን አካባቢ ርስት ጉልት አድርጌ ልስጥህ?›› አሏቸው፡፡ ጻድቁም ለመነኮሳት ልጆቻቸው የእርሻ ቦታ የሚሆን ርስትን ተቀበሉ፡፡
አቡነ ገብረ ናዝራዊ ገዳማቸው ደብረ ኀረይክዋ በቁና በነጹ መነኮሳት እንዲገለገል ካላቸው ፍላጎት አኳያ መነኮሳቱንም ከዓለማዊ ፈተና ለመታደግ ሲሉ ሴቶች ወደ ገዳሙ እንዳይወጡ ከልክለዋል፡፡ አንዲት ሴት የጻድቁን ቃል በመተላለፍና በመደፋፈር ወደ ተራራው በመውጠቷ አፋፉ ላይ እንደደረሰች ከያዘችው ድፎ ዳቦ ጋር ድንጋይ ሆና ቀርታለች፡፡ ይህ ምስሏ አሁንም ድረስ ከነሙሉ የሰውነቷ ቅርጽ በግልጽ ይታያል፡፡
ሴቶች አንዳንድ ገዳማት ላይ እንዳይገቡ ገዳሙን የገደሙት ቅዱሳን የከለከሉበትን በቂ የሆነ መንፈሳዊ ምክንያት ስላላቸው ነው እንጂ እንዲሁ ያወጡት ሕግ አይደለም፡፡ ለዚህም ተጨማሪ ማሳያ ይሆን ዘንድ የእመ ምዑዟ እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ የወንዶችና የሴቶች ገዳም የተለያየ እንዲሆን ያደረገችበት ምክንያት ከገድሏ ላይ እንይ፡- ‹‹እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ቤተ መቅደሷን በአንዲት ቀን ብቻ ሠርታ እንደጨረሰች ጌታችን ከመንበሩ ሆኖ ተገለጠላትና በቦታው ላይ ትልቅ ቃልኪዳን ሰጣት፡፡ ተአምራቶቿንና የትሩፋቷን ዜና የሰሙ ሁሉ ወደ እርሷ እየመጡ ተሰብስበው በተጋድሎ መኖር ጀመሩ፡፡ ቅድስት እናታችንም ትመክራቸውና ታስተምራቸው ነበር፡፡ በመንፈስ ቅዱስም ኃይል ተገልጾላት የበጎ ሥራ ጠላት የሆነው ሰይጣን በማኅበሩ ልቡና እርሻ ላይ እንክርዳድ ሽንገላን እንደዘራ ባየች ጊዜ ከዚህ በኋላ የወንዶቹንና የሴቶቹን ቦታ ለየች፡፡ ለወንዶቹ ለብቻ፣ ለሴቶቹም ለብቻ ገዳም መሥርታ ዘወትር እንዳይተያዩ አደረገች፡፡ ልጆቿንም ሁሉ የእግዚአብሔር መልአክ ይጠብቃቸው ነበር፡፡ እርሷም የአርባውን ጾም ስትጾም ምንም ሳትቀምስ በምድር ላይም ሳትቀመጥ ቆማ ትጨርሳለች፡፡ እንደዚሁም በሌሎች አጽዋማት እንዲሁ ታደርግ ነበር፡፡ በስግደትና በግርፋትም ብዛት ሰውነቷን እጅግ ትጎዳና ታደክም ነበር፡፡ መላእክትም ምግቧን ከሰማይ ኅብስትና ወይን ያመጡላት ነበር፡፡ ውዳሴ አምላክንና አርጋኖንን በጸለየች ጊዜ ጌታችንና እመቤታንም በየጊዜው እየመጡ እየባረኳት ይሄዳሉ፡፡ የዕረፍት ጊዜዋም ከመድረሱ በፊት መላእክትም በብርሃን ሠረገላ ወደ ብሔረ ሕያዋን ወስደው ሥጋ ወደሙን እንትድቀበል አድርገዋታል፡፡››
አንዳንድ አላዋቂ ሰዎች በተለይም ከእኛ እምነት ውጭ ያሉ ሰዎች የሴቶችን ወደ አንዳንድ ገዳማት መግባት አለመቻል በዘመኑ የእኩልነት ስሌት ያሰሉታል፡፡ ይህን ሀሳብ የሚጋሩ አንዳንድ ኦርቶዶክሳውያን እኅቶችና እናቶችም አይጠፉም፡፡ እውነታው ግን ይህ ነው፡- ቅዱሳን አባቶቻችንና ቅዱሳት እናቶቻችን ይህን ሕግ የሠሩበት ምክንያት ግን ከላይ እንዳየነው በውል የታወቀና የተረዳ እውነት ነው፡፡ ‹‹ገዳማቸው በቁና በነጹ መነኮሳት እንዲገለገል ካላቸው ፍላጎት አኳያ መነኮሳቱንም ከዓለማዊ ፈተና ለመታደግ ሲሉ ሴቶች ወደ ገዳሙ እንዳይወጡ ከልክለዋል፡፡›› ፤ ‹‹ለቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስም ኃይል ተገልጾላት የበጎ ሥራ ጠላት የሆነው ሰይጣን በማኅበሩ ልቡና እርሻ ላይ እንክርዳድ ሽንገላን እንደዘራ ባየች ጊዜ ከዚህ በኋላ የወንዶቹንና የሴቶቹን ቦታ ለየች፡፡ ለወንዶቹ ለብቻ፣ ለሴቶቹም ለብቻ ገዳም መሥርታ ዘወትር እንዳይተያዩ አደረገች፡፡››
ሌላው የአቡነ ገብረ ናዝራዊ ደብረ ኀረይክዋ ገዳማቸውን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች ውስጥ ጻድቁ በዘንዶ አማካኝነት ወደ ተራራው ሲወጡ መጀመሪያ የረገጡት ዓለት የእግር ጣታቸው ምልክት ያለበት መሆኑ ነው፡፡ እናቶች ምጥ ሲይዛቸው ወይም ሰዎች ሲታመሙ ድርቅና ቸነፈር ሲከሰት የሚፈውስና ምሕረት የሚያወርድ እንዲሁም የተጣሉ ሰዎች የሚታረቁበት ነባኢ መስቀል (የሚያነባ መስቀል) በገዳሙ ይገኛል፡፡ በየዓመቱ ጥር 29 ቀን የዕረፍታቸው በዓል በድምቀት ይከበራል፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages