አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥር ሁለት በዚች ቀን ደሙ በግፍ የፈሰሰ #ጻድቁ_አቤል አረፈ፣ የከበረ አባት #ቅዱስ_አላኒቆስ ኤጲስቆጶስ በሰማዕትነት ሞተ፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት #ቅዱስ_ቴዎናስ አረፈ።
ጥር ሁለት በዚች ቀን ደሙ በግፍ የፈሰሰ ጻድቁ አቤል አረፈ እርሱም ወንድሙ ቃየል የገደለው የሙታን በኵር የሆነ ነው።
ምክንያቱም አዳም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተላልፎ እንዳይበላው የታዘዘውን ዕፅ በላ ያን ጊዜ በእርሱና በልጆቹ ላይ ሞት ሠለጠነ ለኃጢአትም ተገዥ ሆነ። ሰይጣንም ሰውን ለማሳት ሠለጠነ ከዚህም በኋላ አዳም ከገነት ወጥቶ ወደታችኛዋ ምድር ወረደ ስለ በደሉና የፈጣሪውንም ትእዛዝ በመተላለፉ ፈጽሞ እያዘነና እያለቀሰ መቶ ዓመት ኖረ።
ከዚህም በኋላ አዳም ሔዋንን በግብር አወቃት ፀንሳ ቃየልንና እኅቱን ኤልዩድን ወለደች ሁለተኛም ዐወቃት አቤልንና እኅቱን አቅሌማን ወለደቻቸው አዳምም ሔዋንን እነሆ ልጆችሽ አካለ መጠን አደረሱ ጐለመሱ ቃየል የአቤልን እኅት አቅሌማን ያግባት አቤልም የቃየልን እኅት ኤልዩድን ያግባት አለ።
ቃየልም እናቱን ሔዋንን እንዲህ አላት ለእኔ ከእኔ ጋር የተወለደች እኅቴን ማግባት ይገባኛል አቤልም ከእርሱ ጋር የተወለደች እኅቱን ያግባ ቃየል ከእርሷ ጋር የተወለደ ኤልዮድም እናቷ ሔዋንን የምትመስል እጅግ የምታምር መልከ መልካም ናትና።
አዳምም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እጅግ ጭንቅ ሆነበት ቃየልንም አብራህ የተወለደች እኅትህን ታገባት ዘንድ አይገባህም አለዚያም ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቅርቡና መሥዋዕቱን ለተቀበለው ይሁን አለው።
መሥዋዕትንም በአቀረቡ ጊዜ የአቤልን መሥዋዕት እግዚአብሔር ተቀበለ የቃየልን ግን አልተቀበለም ስለዚህም ቃየል ፈጽሞ አዘነ ሰይጣንም ተገናኘውና ምን ያሳዝንሃል አለው ቃየልም ለወንድሜ ለአቤል እኅቴን እተውለት ዘንድ አባቴ አዘዘኝ አለው። ሰይጣንም ምክርን ከኔ ስማ ወንድምህን ወደ ውኃ ምንጭ ይዘኸው ሒድ ውኃንም ሲጣጣ ራሱን በደንጊያ ምታው በሞተ ጊዜ ሁለቱንም ታገባቸዋለህ የሚከለክልህ ማነው አለው ለቃየልም የሰይጣን ምክር ደስ አሰኘው ልቡም በዝሙት እሳትነት ነደደ ሰይጣን እንዳስተማረውም ወንድሙን አቤልን ገደለው ለሴት ስለ መቅናትም ጻድቁ አቤል በወንድሙ እጅ ሞተ እንዲህም ሞት ወደ ዓለም ገባ።
እግዚአብሔርም ቃየልን ወንድምህ አቤል ወዴት ነው አለው። ቃየልም አላውቅም በውኑ እኔ የአቤል ጠባቂው ነኝን አለው። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው ቃየል ምን አድርገሃል የወንድምህ የአቤል ደም ጩኸት ከምድር ወደኔ ደርሷል። አሁንም በእጅህ የፈሰሰውን የወንድምህን ደም ትጠጣ ዘንድ አፍዋን የከፈተች ምድር የተረገመች ትሁን አንተ ታርሳታለህና በረከቷን ትሰጥህ ዘንድ አትጨምርም በምድር ላይ ፈሪ ተቅበዝባዥ ሁን።
ይህም መርገም ዘሩ በጥፋት ውኃ ከምድር ገጽ እስከ ሚደመሰስ በቃየል ላይ የበዛ ሆነ። የክብር ባለቤት ጌታችንም ጸሐፍት ፈሪሳውያንን ሲዘልፋቸው እንዲህ አላቸው ስለዚህ ነቢያትን ሊቃውንትን ጥበበኞችን ወደናንተ እልካለሁ ከነርሱ የምትገድሉት አለ የምትሰቅሉትም አለ በምኵራባችሁ የምትገርፉት አለ ካንድ አገር ወዳንድ አገር ታሳድዷቸዋላችሁ።
ከጻድቁ ከአቤል ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በዓለም የፈሰሰው የጻድቃን ደም ሁሉ በእናንተ ላይ ይደርስ ዘንድ።
ጳውሎስም አለ ቃየል ካቀረበው መሥዋዕት ይልቅ አቤል በሃይማኖት ለእግዚአብሔር ያቀረበው መሥዋዕት ተሻለ ስለ እርሱም ደግ እንደሆነ መሰከረለት መሥዋዕቱንም በመቀበሉ ምስክሩ እግዚአብሔር ነው ደግ እንደሆነም ከሞተ በኋላ ተናገረ።
ከዚህም በኋላ አዳም ልጁን በአጣው ጊዜ ወንድምህ አቤል ወዴት አለ ብሎ ቃየልን ጠየቀው ቃየልም በቁጣ አላውቅም እኔ የአቤል ጠባቂው ነውኝን ብሎ መለሰ አዳምም ልጁን ይፈልግ ዘንድ ወደ ዱር ሮጠ በወንዝ ዳርም በድኑን አገኘና አንገቱን አቅፎ ማን ገደለህ አለው ከበድኑም ወንድሜ ቃየል ገደለኝ የሚል ቃል ወጣ። አዳምና ሔዋንም በልጃቸው በአቤል ሞት ሃያ ስምንት ዓመት ያህል ሲያለቅሱ ኖሩ።
ከዚህም በኋላ መላእክት ወደ አዳም መጥተው የዓለሙ ሁሉ አባቶች አባት አዳም የምሥራች እነሆ ልጅህ አቤል የገነትን ዛፎች ተሳለመ ነፍሱም እንደ ተወደደ መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ዐረገች አሉት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የከበረ አባት አላኒቆስ ኤጲስቆጶስ በሰማዕትነት ሞተ። እርሱ ጣዖታቱን እንዲአቃልሉ ለሰዎች እንደሚያስተምራቸው ከሀዲው ንጉሥ በሰማ ጊዜ ይዘው ጽኑ ሥቃይን ያሠቃዩት ዘንድ መልእክተኞችን ላከ።
የንጉሥ መልክተኞች መላካቸውን የተመሰገነ አላኒቆስ ሰምቶ በሀገረ ስበከቱ ያሉትን ሕዝቦች ሰበሰባቸውና የቁርባን ቅዳሴን ቀድሶ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው። ከዚህም በኋላ በቀናች ሃይማኖት ጽኑ ከእንግዲህ ፊቴን አታዩኝም አላቸው። እነርሱም አለቀሱ ሊአስተዉትም አልተቻላቸውም ወጥቶም ራሱን ለንጉሥ መልክተኞች አሳልፎ ሰጠ እነርሱም ወስደው ለእንዴናው አገር መኰንን ሰጡት። እርሱም ወደ ሀገረ እንድኩ ወስዶ በዚያ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው ማሠቃየቱም በሰለቸው ጊዜ ትከሻውን በሰይፍ ይሠነጥቁ ዘንድ ራሱንም ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ መሞቱን አውቆ አማንያን ከሆኑ መርከበኞች አንዱን እንዲህ ብሎ አዘዘው ወደ ወደቡ ስትደርሱ ሥጋዬን በኮረብታ ላይ አድርግ እርሱም እንዳዘዘው አደረገ።
ከዚህም በኋላ ምእመናን ሰዎች መጥተው ሥጋውን ወስደው ገነዙት የስደቱም ወራት እስቲያልፍ በእነርሱ ዘንድ አኖሩት ቤተ ክርስቲያንም ሠርተው ሥጋውን በውስጧ አኖሩ ከእርሱም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራቶች ተደረጉ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት ቴዎናስ አረፈ። እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ዐሥራ ስድስተኛ ነው። ይህም ቅዱስ አዋቂ ብልህ በቀናች ሃይማኖትም የጸና በሥራው ሁሉ ያማረ ስለ ዕውቀቱም ሰዎች ሁሉ የሚወዱትና የሚሹት ሆነ።
በዚያም ወራት ከሀዲያንን በመፍራት በሥውር ከዋሻ ውስጥ በቀር በግልጥ ሊጸልዩና ሊቀድሱ ለክርስቲያኖች አልተቻላቸውም ነበር ይህም አባት አብያተ ክርስቲያናትን እስከሠሩ ድረስ አግባባቸው በእመቤታችንም በቅድስት ድንግል ማርያም ስም ያማረች ቤተ ክርስቲያን ሠሩ ከከሀዲያንም ብዙዎችን መልሶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃችው።
በተሾመባት በመጀመሪያ ዓመት ተፍጻሜተ ሰማዕት የሆነ ሊቀ ጳጳሳት ጴጥሮስን ያጠመቀው እርሱ ነው። በተሾመ በአምስተኛ ዓመቱም አናጒንስጢስነት ሾመው በዐሥራ ሁለተኛም የሹመቱ ዓመት ቅስና ሾመው።
በዚህም አባት ዘመን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ ገጽ ነው የሚል ከሀዲ ሰባልዮስ በእስክንድርያ አገር ተነሣ ይህም አባት አውግዞ ለየው የከፋች ሃይማኖቱንም አጠፋት። ዳግመኛም በዘመኑ ቆዝሞስና ድምያኖስ ወንድሞቻቸው እናታቸው ቴዎዳዳም በሰማዕትነት ሞቱ ይህም አባት ያማረ ጒዞውን በመጓዝ እግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment