አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥር አንድ ቀን የዲያቆናት አለቃ የሰማዕታት መጀመሪያ የሆነ የከበረ #ቅዱስ_እስጢፋኖስ ምስክር ሆኖ ሞተ፣ #ቅዱስ_ለውንድዮስ በሰማዕትነት ሞተ፣ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት #አባ_መቃርስ አረፈ፣ #ቅዱሳን_ዲዮስቆሮስ_እና_ሰከላብዮስ (#ቅዱሳን_ሰማዕታተ_አክሚም) በሰማዕትነት አረፉ፡፡
በዚህችም ጥር አንድ ቀን የዲያቆናት አለቃ የሰማዕታት መጀመሪያ የሆነ የከበረ እስጢፋኖስ ምስክር ሆኖ ሞተ። ለዚህም ለከበረ እስጢፋኖስ የእግዚአብሔርን ኃይልና ጸጋ የተመላ ሰው እንደነበረና በሕዝቡም መካከል ታላላቅ ተአምራትንና ድንቅ ሥራን ይሠራ እንደነበረ የሐዋርያት ሥራ የተባለ መጽሐፍ ስለርሱ ምስክር ሆነ።
ከዚህም በኋላ አይሁድ ቀኑበት የሐሰት ምስክሮች የሚሆኑ ሰዎችንም አስነሡበት ይህን ሰው በሙሴና በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃልን ሲናገር ሰምተነዋል እንዲሉ ሐሰትን አስተማሩአቸው። ሕዝቡንና ሽማግሌዎችን ጸሐፊዎችንም አነሣሡአቸው አዳርሱን ብለው ከበው እየጐተቱ ወደ ሸንጎ ወሰዱት።
የሐሰት ምስክሮችንም አቆሙበት እነርሱም ይህ ሰው በቤተ መቅደስ ላይ በኦሪትም ላይ ስድብን ሲናገር ተው ብንለው እምቢ አለ። የናዝሬቱ ኢየሱስ ቤተ መቅደሳችሁን ያፈርሰዋል ሙሴ የሰጣችሁን ኦሪታችሁንም ይሽራል ሲል ሰምተነዋል አሉ።
በአደባባይ ተቀምጠው የነበሩት ሁሉ ተመለከቱት ፊቱንም የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ሁኖ አዩት። ሊቀ ካህናቱም እውነት ነውን እንዲህ አልክ አለው። እርሱም እንዲህ አለ ወንድሞቻችንና አባቶቻችን ስሙ ወደ ካራን ከመምጣቱ አስቀድሞ በሶርያ ወንዞች መካከል ሳለ ለአባታችን ለአብርሃም የክብር ባለቤት እግዚአብሔር ተገለጠለት። ካገርህ ውጣ ከዘመዶችህም ተለይ እኔ ወደማሳይህ ሀገርም ና አለው።
ከዚህም በኋላ ከከላውዴዎን ወጥቶ በካራን ተቀመጠ አባቱም ከሞተ በኋላ ዛሬ እናንተ ወደ አላችሁባት ወደዚች አገር አመጣው። ከዚህም በኋላ የግዝረትን ሥርዓት ሰጠው ይስሐቅንም በወለደው ጊዜ በስምንተኛው ቀን ገዘረው እንዲሁ ይስሐቅም ያዕቆብን ገዘረው ያዕቆብም ዐሥራ ሁለቱን ነገድ አባቶችን ገዘረ።
የቀደሙ አባቶቻችንም በዮሴፍ ላይ ቀንተው ወደ ግብጽ አገር ሸጡት እግዚአብሔር ግን አብሮት ነበር። ከመከራው ሁሉ አዳነው በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ፊትም ዕውቀትን መወደድን ሰጠው በግብጽ አገር ሁሉና በቤቱ ሁሉ ላይ ሾመው። ነገርም በማስረዘም በሰሎሞን እጅ እስከተሠራችው ቤተ መቅደስ ያለውን ተረከላቸው።
ከዚህም በኋላ ድምፁን ከፍ ከፍ አድርጎ እናንተም እንደአባቶቻችሁ ዘወትር መንፈስ ቅዱስን የምታሳዝኑት ዐይነ ልቡናችሁ የታወረ ዕዝነ ልቡናችሁ የደነቈረ አንገተ ደንዳኖች አላቸው። አባቶቻችሁ ከነቢያት ያላሳደዱት ያልገደሉት ማን አለ እናንተ ክዳችሁ የገደላችሁትን የአምላክን መምጣት አስቀድመው የነገሩዋችሁን ገደላችኋቸው።
በመላእክት ሥርዓት ኦሪትን ተቀብላችሁ አልጠበቃችሁም። ይህንንም ሰምተው ተበሳጩ ልባቸውም ተናደደ ተነሣሣ ጥርሳቸውንም አፋጩበት። በእስጢፋኖስም መንፈስ ቅዱስ አደረበት ሰማይም ተከፍቶ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ የእግዚአብሔርን ክብር አየ። እነሆ ሰማይ ተከፍቶ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ አያለሁ አለ።
ጆሮአቸውን ይዘው በታላቅ ድምፅ ጮኹ በአንድነትም ከበው ጐተቱት። እየጐተቱም ከከተማ ወደ ውጭ አውጥተው በደንጊያ ወግረው ገደሉት የገደሉትም ሰዎች ልብሳቸውን ሳውል ለሚባል ጐልማሳ ልጅ ያስጠብቁ ነበር። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል እያለ ሲጸልይ እስጢፋኖስን በደንጊያ ወገሩት።
ዘለፍለፍ ባለ ጊዜም ድምፁን ከፍ አድርጎ አቤቱ ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው በደልም አታድርግባቸው ይህንንም ብሎ አረፈ። ደጋግ ሰዎችም መጥተው የእስጢፋኖስን ሥጋ ወስደው ቀበሩት ታላቅ ልቅሶም አለቀሱለት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ዕለት በከሀዲው መክስምያኖስ ዘመነ መንግሥት ከሶርያ አገር የከበረ ለውንድዮስ በሰማዕትነት ሞተ። የዚህንም ቅዱስ ዜና እግዚአብሔርን የሚያመልክ ተጋዳይ እንደሆነ ንጉሥ መክስምያኖስ በሰማ ጊዜ ልኮ ወደርሱ አስመጣው ሃይማኖቱንም ትቶ አማልክቶቹን ያመልክለት ዘንድ ብዙ ገንዘብ አቀረበለትና ይሸነግለው ጀመረ የከበረ ለውንድዮስ ግን ዘበተበት ስጦታውንም በማቃለል ክብሩን አጐሳቈለ የረከሱ አማልክቶቹንም ረገመ።
ያን ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ በመንኰራኲር ውስጥ ሰቅለው ጽኑዕ የሆነ ሥቃይን እንዲአሠቃዩት አዘዘ። ንጉሥ እንዳዘዘ አደረጉበት የክብር ባለቤት ጌታችን ግን ያለ ጥፋት በጤና አወጣው።
ዳግመኛም በብረት ዘንጎች ይደበድቡት ዘንድ ቅባትና ስብንም በታላቅ ድስት አፍልተው ቅዱስ ለውንድዮስን ከውስጡ ይጨምሩት ዘንድ አዘዘ ይህን ሁሉ ሥቃይንም አሠቃዩት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያጸናውና ያስታግሠው ያለ ጉዳትም በጤና ያስነሣው ነበር።
ማሠቃየቱንም በደከመው ጊዜ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ። ከሥጋውም ድንቆች የሆኑ ብዙዎች ተአምራቶች ተገለጹ ዜናውም በሶርያ አገር ሁሉ ተሰማ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ተሠሩለት ከገዳማቱም በአንዲቱ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት የሆነው የከበረ ሳዊሮስ በሕፃንነቱ ተጠመቀባት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት አባ መቃርስ አረፈ፡፡ እርሱም ለአባቶች ሊቃነጳጳሳት ስልሳ ዘጠነኛ ነው። ከእርሱ በፊት የነበረ አባ ሚካኤልም በአረፈ ጊዜ ኤጲስቆጶሳትና ሊቃውንቱ የግብጽም ታላላቆች ሁሉም ወደ አስቄጥስ ገዳም ወጥተው ለዚች ለከበረች ሹመት ስለሚገባ ከዋሻ ውስጥ ከሚኖሩ ደጋጎች ገዳማውያን ሲጠያየቁና ሲመረምሩ ኖሩ። ከዚህም በኋላ አንድ ጻድቅ ሰው ስለዚህ አባት ነገራቸው እንዲህም አላቸው በአባ መቃርስ ገዳም የሚኖር ቀሲስ አባ መቃርስ እርሱ ለዚች ሹመት ይገባል።
በዚያንም ጊዜ ፈልገው ያዙት እርሱም እኔ ለዚች ሥራ የማልጠቅም በደለኛ ነኝ እያለ ሲጮህ ያለ ፈቃዱ አሥረው ወሰዱት ሊቀ ጵጵስና ሾሙት እንጂ እርሱ የሚላቸውን ቃሉን አልሰሙትም።
ከዚህም በኋላ የሊቀ ጵጵስናውን ሥራ መሥራት ጀመረ በግብጽ አገር በሁሉ ቦታ ኤጲስቆጶሳትን ካህናትን ሾመ ብዙዎች አብያተ ክርስቲያናትንም አደሰ ጊዜውም ያለ ኀዘን የጤንነትና የሰላም ጊዜ ነበር። ሹመቱም ሃያ ሰባት ዓመት ከአርባ አንድ ቀን ኖረ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የከበሩ የአክሚም ሰማዕታት የምስክርነታቸውን ተጋድሎ ፈጸሙ ዜናቸውም እንዲህ ነው። አክሚም በሚባል አገር ሹም የሆነ አንድ ሰው ነበረ በወርቅ በብር ባለጸጋ ነው ስሙም አልሲድማልዮስ ይባላል ስማቸው ዲዮስቆሮስና ሰከላብዮስ የሚባል ሁለት ልጆችን ወለደ እነርሱም ከመጾምና ከመጸለይ ጋር እግዚአብሔርን በመፍራት አደጉ።
አባታቸውም በሞተ ጊዜ ምንኲስናን ተመኙ የእግዚአብሔርም መልአክ ተገልጦላቸው ወደ ገዳማዊ አባ ሙሴ ገዳም እንዲሔዱ አዘዛቸው ሒደውም በዚያ መነኰሱ ድንቆች ተአምራቶችንም እያደረጉ በብዙ ተጋድሎ ኖሩ።
ከጥቂት ወራትም በኋላ ዲዮስቆሮስ ቅስና ሰከላብዮስም ዲቁና ተሾሙ። ዲዮቅልጥያኖስም የክብር ባለቤት ክርስቶስን በካደው ጊዜ ለጣዖታት የማይሰግዱ ክርስቲያኖችን ሁሉ ይገድል ዘንድ የእንዴናው ገዥ አርያኖስን አዘዘው።
አርያኖስም አክሚም ከተማ በደረሰ ጊዜ ኤጲስቆጶሱን አባ ብኑድያስን ያዘውና አሥሮ ወደ አገር ውስጥ ገባ። የእግዚአብሔር መልአክ ሚካኤልም ለዲዮስቆሮስና ለሰከላብዮስ ተገለጸላቸው ወደ መኰንኑም ሒደው የምስክርነት አክሊልን እንዲቀበሉ ነገራቸው እነርሱም ታኅሣሥ ሃያ ስምነት ቀን ሃያ አራት መነኰሳት ሁነው ሔዱ።
ወደ አክሚም ከተማም ሲደርሱ በመድኃኒታችን ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የከበረ የልደትን በዓል ለማክበርና ስለ ከበረ ስሙም ይሞቱ ዘንድ የክርስቲያን ወገኖችን ከሴቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ተሰብስበው አገኙአቸው ኤጲስቆጶሱ አባ ብኑድያስም ከእርሳቸው ጋር ገባ። በማግሥቱም አባ ብኑድያስ ቀደሰ አግዮስ ወደሚለው በደረሰ ጊዜ መላእክት እንዲህ ብለው በታላቅ ድምጽ አመሰገኑ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር አሸናፊ ፍጹም የጌትነትህ ምስጋና በሰማይና በምድር የመላ ነው።
ያን ጊዜ መድኃኒታችንን በመሠዊያው ታቦት ላይ ተቀምጦ መላእክትም በዙሪያው ቁመው ቊርባኑን እያነሣ በካህኑ እጅ ላይ በማድረግ የተሰበሰቡትን ሲያቆርባቸው ቅዱሳኑ አዩት።
በዚያንም ጊዜ መኰንኑ አርያኖስ ደረሰ ተቆጥቶም ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ስማቸው ብሕዋፋና ውኒን የሚባሉ ሁለት የሀገር አለቆችን ይዞ ራሳቸውን በሰይፍ ቆረጠ ከእነርሱም በኋላ ዲያቆናትን ንፍቀ ዲያቆናትን መዘምራንን የቤተ ክርስቲያን ሹሞችን ደማቸው ከቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ወጥቶ ሃያ ክንድ ያህል እስቲጎርፍ ሴቶችና ልጆችንም ሳያስቀር አረዳቸው።
ከዚህም በኋላ ኤጲስቆጶሱን አባ ብኑድያስን ዲዮስቆሮስን ሰከላብዮስን ከእርሳቸውም ጋር ያሉ መነኰሳትን ከእርሱ ጋር ወሰዳቸው ለጣዖትም ይሰግዱ ዘንድ ሸነገላቸው እምቢ በአሉትም ጊዜ ዐጥንቶቻቸው እስከሚለያዩ ድረስ ይደበድቧቸው ዘንድ አዘዘ የእግዚአብሔርም መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ተገልጾላቸው አዳናቸው የአርያኖስም የጭፍሮቹ ታላላቆች ኮርዮንና ፊልሞና ከጭፍሮችም አርባ ሰዎች ይህን ድንቅ ተአምር አይተው በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ወደ እሳት ማንደጃም እንዲጥሏቸው አዘዘ። ተጋድሏቸውንም ታኅሣሥ ሠላሳ ቀን ፈጸሙ ከተሰበሰቡትም ውስጥ ብዙዎች የሚያሰገድዳቸው ሳይኖር በእውነተኛ አምላክ በክርስቶስ እናምናለን እያሉ ወደ እሳቱ ማንደጃ ራሳቸውን ወረወሩ ምስክርነታቸውንም እንደዚህ ፈጸሙ።
ከዚህም በኋላ ጥር አንድ ቀን ዲዮስቆሮስና ሰከላልብዮስ ታሥረው ሳሉ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ተገለጠላቸውና ምስክርነታቸውን እንዲፈጽሙ አበረታቸው በነጋም ጊዜ ለአማልክት ስለ መስገድ አርያኖስ ተናገራቸው አይሆንም በአሉትም ጊዜ የዲዮስቆሮስን ዐይኖቹን ያወልቁ ዘንድ አዘዘ ቅዱሱም የወለቁ ዐይኖቹን አንሥቶ ወደ ቦታቸው መለሳቸው መኰንኑ ሉክዮስም አይቶ ከሠራዊቱ ጋር በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ ወደ እሳትም ወርውረዋቸው ምስክርነታቸውንም ፈጸሙ።
ከዚህም በኋላ የከበሩ ሰማዕታትን ይገድሏቸው ዘንድ አርያኖስ አዘዘ ሲጸልዩም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸው ስማቸውን ለሚጠራ መታሰቢያቸውንም ለሚያደርግ ገድላቸውንም ለሚጽፍ ከቅዱሳን አንድነት ይቈጥረው ዘንድ ቃል ኪዳን ሰጣቸው። ከዚህም በኋላ ወታደሩ ቀርቦ የቅዱስ ዲዮስቆሮስን ራስ ቆረጠ ሰከላብዮስንም ከወገቡ ላይ ቆረጡት ሃያ አራቱን መነኰሳትም ከቁመታቸው ሠነጠቋቸው በዚች በጥር አንድ ቀን ሁሉም ተቆረጡ ከዘመዶቻቸው የሆነ ሳሙኤልም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በከበረች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቀበራቸው በሀገረ አክሚም የተገደሉ ሰማዕታትም ቊጥራቸው ስምንት ሺ አንድ መቶ አርባ ሆነ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment