ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 5 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, April 14, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 5

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሚያዝያ አምስት በዚች ቀን የኢትዮጵያ ብርሃኗ ማኅሌታዊው_ቅዱስ_ያሬድ የተወለደበት ነው፤ የካህኑ የቡዝ ልጅ ታላቅ ነቢዩ_ቅዱስ_ሕዝቅኤል አረፈ።


ሚያዝያ አምስት በዚህች ቀን የኢትዮጵያ ብርሃኗ ማኅሌታዊው ቅዱስ ያሬድ የተወለደበት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ከእናቱ ቅድስት ክርስቲና (ታውክልያ) ከአባቱ ከቅዱስ አብዩድ (ይስሐቅ) በአክሱም በ505ዓ.ም ሚያዝያ 5 ቀን ተወለደ። አባቱ የአክሱም ጽዮን ቄሰ ገበዝ ነበር። በዚያን ጊዜ የብሉያትና የሐዲሳት መምህራንና ተማሪዎች የሚገኙት አክሱም ጽዮን ነውና የአኵሱም ቤተ ቀጢን (ቤተ ጉባኤ) መምህር የነበረው የእናቱ ወንድም አጎቱ መምህር ጌዴዎን ይባል ነበር።
ቅዱስ ያሬድ የሰባት ዓመት ብላቴና በኾነ ጊዜ አባቱ ስለ ሞተ ትምህርት ቤት ከመግባቱ በፊት በዚያ ዘመን አጠራር ለጌታው ዐደረ። ጌታውም የዐፄ ገብረ መስቀል ቢትወድድ አዛዥ ዜና ገብርኤል ይባላል። ያሬድን ዐቅሙ ለጉልበት ሥራ እንዳነሰ አይቶት "አንተ ልጅ ጋሻ ቢያስይዙህ አትችል፤ ሾተል ቢያሸክሙህ አይሆንልህ ለምን ከዚህ መጣህ?" ብሎ መለሰለት። ከዚያ በኋላ ከአጎቱ ዘንድ ሔደ። መምህሩም "ከዚህ የመጣህበት ምክንያት ምንድ ነው?" አለው። እርሱም "መጽሐፍት እማራለኹ ብዬ ነው የመጣኹት" አለው። መምህር ጌድዎንም ዐቅሙንና ዕውቀቱን በመገመት ለተማሪዎች "በሉ ፊደል አስቆጥሩት" አላቸውና ትምህርቱን ጀመረ። ኾኖም ቃለ እግዚአብሔርን የመቀበል ችሎታው ደካማ ስለነበር አብረው የሚማሩትም ሕፃናት "ሰነፍ ያሬድ ዕንጨት ስበር ውሃ ቅዳ" እያሉ አፌዙበት፤ ቀለዱበት። አጎቱ ጌዴዎንም ከትምህርቱ ድክመት የተነሣ በጨንገር (በአለንጋ) ቢገርፈው ሕፃኑ ያሬድም በዚህ ተበሳጭቶና ተስፋ ቆርጦ ከአክሱም ከተማ ወጥቶ ወደ እናቱ መንደር ወደ መደባይ ወለል ደረሰ። ለጥሙ ከምንጭ ውሃ ጠጥቶ ለድካሙ ከዛፋ ጥላ አረፈ። በምን ምክንያት ከጓደኞቹ በታች እንደኾነ ሲያስብና ሲያሰላስል ሲያዝንና ሲተክዝ ከቆየ በኋላ እግዚአብሔር አንድ የሚያጽናና ምልክት አሳየው። ይኸውም አንድ ትል የዛፏን ፍሬ ለመመገብ ፈልጎ ወደ ላይ እየወጣና እየወደቀ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በሰባተኛው ጊዜ ወደ ዛፋ ወጥቶ ፍሬዋን ሲመገብ ተመለከተ ተማሪ ያሬድም ከዚህ ትል ትዕግሥትን፣ ጽናትን፣ ጥረትን፣ ስኬትን ትምህርት ወስዶ እኔም እኮ ተስፋ ሳይቆርጥ ብዙ ጥረት ካደረግኹ እግዚአብሔር ያሳካልኛል ብሎ በተስፋ ተጽናንቶ እንደገና ወደ መምህሩ በመመለስ ትምህርቱን ለመቀጠል ወሰነ። ወደ መደባይ ያደረገው የነበረውን ጉዞ ሠርዞ ወደ አክሱም ከተማ ወደ መምህሩ ጌድዬን ጉባኤ ቤት ተመለሰ። በመጸጸት አጎቱን "አባቴ ስለተቆጣኸኝና ስለገረፍከኝ ተበሳጭቼ ሔጄ ነበር ፤ ነገር ግን በመንገድ ላይ እግዚአብሔር ስላስተማረኝ ተጸጽቼ መጥቻለኹ። ከእንግዲህስ ወዲህ እየተቆጣኽና እየገሠጽህ አስተምረኝ" ሲል አሳቡን ሳይደብቅ ገለጸለት።
አጎቱም ያሬድ ተጸጽቶ በመመለሱ በጣም ተደስቶ ዐይነ ልቡናውን ያበራለት ዘንድ ፈጣሪውን እያለቀሰ በለመነለት ጊዜ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ለያሬድ ዕውቀትን ገለጸለት። የያሬድ ኅሊናው ተከፍቶለት መዝሙረ ዳዊትን፣ ውዳሴ ማርያምን፣ መሓልየ ነቢያት፣ መሐልየ ሰሎሞንን፣ መጻሕፍተ ብሉያትንና ሐዲሳትን ንባባቸውን እስከ አገባባቸው አወቀ።
ቅዱስ ያሬድ ቅዱሳት መጻሕፍትን በቃሉ ይዞ ሲያስተምር ሳለ የትምህርቱን ጥራት፣ የሃይማኖት ጽናት፣ ደግነቱንና ትዕግስቱን፣ ትሕትናውና ተልኮውን በመምህሩና በካህናቱ ተመስክሮለት የአክሱም ጳጳሱ አባ ዮሐንስ ሢመተ ዲቁና ሾመው። ቅዱስ ያሬድ የታላቋ የአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን አጋልጋይ ዲያቆን ኾነ።
ትምህርቱን በስፋት ስለቀጠለበት የመጻሕፍት ብሉያትና ሐዲሳት፣የመጻሕፍት ሊቃውንት ትርጓሜ ሊቅ ኾነ። ቅዱስ ሬድም ለመንፈሳዊ አገልግሎት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት ከዘጠኙ ቅዱሳን ጋራ በቤተ ቀንጢን ጉባኤ ቤት ይውል ስለነበር ገዳማዊ ሕይወት ከእነርሱ በመማር እንደ እነ አቡነ አረጋዊ፣ አባ ገሪማ፣ አባ ጰንጠሌዎን በድንግልና ተወስኖ በንጽሕና ሲያገለግል ቆይቷል።
ለቅዱስ ያሬድ ሰማያዊ ዜማ መገለጽ፦ ኅዳር5 ቀን 527ዓ.ም ከጠዋቱ በሦስት ሰዓት እግዚአብሔር ከኤዶም ገነት ሦስት አዕዋፍን (መላእክት በአዕዋፍ ተመስለው) እርሱ ወዳለበት ላከለት። እነርሱም ያሬድ ባለበት ቦታ አንጻር በአየር ላይ ረብበው በግእዝ ቋንቋ "ብፁዕ ያሬድ ብፅዕት ከርሥ እንተ ጾረተከ ወብፁዕት አጥባት እለ ሐፀናከ (የተመሰገንክና የተባረክ ያሬድ ሆይ፤ አንተን የተሸከመች ማሕፀን የተመሰገነች ናት፤ አንተን ያሳደጉ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው") ብለው አወደሱት። ቅዱስ ያሬድም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ወደ ሰማይ አንጋጦ ሦስቱን አዕዋፍ አየና "እናንተ በሰው አንደበት የምትናገሩ ከወዴት መጣችኹ" አላቸው። ከሦስቱ አዕዋፍ አንዷም "ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ማሕሌትን ሰምተኽ እንድታዜም የተመረጥኽ መኾኑን እነግርህና እናበሥርህ ዘንድ ወደ አንተ ተልከን መጥተናል" አለችው። ከዚያም ቅዱሳን መላእክት በዜማ ወደሚያመሰግኑባት ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በአካል ተነጠቀ።
በዚያም ቅዱሳን መላእክት የሚታየውንና የማይታየውን የፈጠረ እግዚአብሔር በቅኔና በከፍተኛ ደምፅ ያለማቋረጥ በመንበሩ ዙሪያ ኾነው ሲያመሰግኑ እንዲሁም የእንዚራ፣ የበገና የመሰንቆ ድምፅ በሰማ ጊዜ ካለበት ሥፍራ እነርሱ ወዳሉበት ሊገባ ወደደ ነገር ግን አልተቻለውም። በመጨረሻም እነዚያ አዕዋፍ ወደ እርሱ ተመልሰው መጡ። "ያሬድ ሆይ፤ የሰማኸውን አስተውለኸዋል?" ብለው ጠየቁት እርሱም "አላስተዋልኸም" ብሎ መለሰላቸው። እንግዲያውስ አዲሱን የእግዚአብሔር ምስጋና ጥራ፤ እርሱም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። ከእግዚአብሔር መዘምራን ከቅዱሳን መላእክት በየዐይነቱ ዜማ ያለውን ማሕሌት ትማራለኽ፤ ታጠናለኽ" አሉት። ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ማሕሌቱን በየዓይነቱ አውጥቶ "መልካምን ነገር ልቤ ተናገረ" እያለ ከቅዱሳን መላእክት ተማረ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ " ሌሎችን አገልጋዮች ሰዎች ይሾሟቸዋል፤ አንተን ግን እኔ ሢመተ ክህነት (ቅስና) ሾሜኻለሁ" አለው።
ቅዱስ ያሬድም የመላእክት ሥርዓታቸው ዐይቶ፤ ማሕሌታቸውን አጥንቶ ኅዳር6 ቀን 527ዓ.ም በጠዋት ሦስት ሰዓት ወደ ቀድሞ ቦታው ተመልልሷል። ከዚያም ኾኖ ፊቱን ታቦተ ጽዮን ወዳለችበት ወደ ምሥራቅ አዙሮ እጆቹን ዘርግቶ እንዲህ ብሎ ሰማያዊ ዜማን ለመጀመርያ ጊዜ በአኵሱም አደባባይ (ዐውደ ምሕረት) ዘመረ።
"ሃሌ ሉያ ለአብ፣ ሃሌ ሉያ ለወልድ፣ ሃሌ ሉያ ወለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብር ግብራ ለደብተራ። ብሎ በዓራራይ ዜማ አዜመ። ይህም ማለት ዓለም ሳይፈጠር ለነበረ ዓለምን አሳልፎ ለዘለዓለም ለሚኖር አሁንም ላለ ለአብ ምስጋና ይገባል፤ ለወልድም ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል፤ ከጽዮን አስቀድሞ ሰማይን ፈጠረ፤ ዳግመኛም ደብተራ ኦሪትን እንዴት አድርጎ መሥራት እንዳለበት ለሙሴ አሳየው ማለት ነው። ስለምን በዓራራይ ዜማ ጀመረ ቢሉ ቋንቋን የሚያናግር ምስጢር የሚያስተረጉም መንፈስ ቅዱስ የገለጠልኝ ዜማ ነው ሲል ነው። ምክንያቱም ዓራራይ ዜማ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነውና።
ከሰማይ እንደተመለሰ ለመጀመሪያ ጊዜ ጣዕመ ዜማውን ያሰማበት ቦታ "ሙራደ ቃል" (የቃል መውረጃ) እየተባለ ይጠራል። ይኸውም ዜማው ከሰማይ የወረደ ለመኾኑ እውነተኛ ማስረጃ ነው። ይህችንም ዜማ "አርያም" አላት። ይህም ማለት ከመላእክት ወይም ከሰማይ የተገኘች ማለት ነው።
ከዚህም በኋላ ከብሉይና ከሐዲስ፣ ከሊቃውንት መጻሕፍትም ከነአትናቴዎስ፣ ቄርሎስ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ መጻሕፍት ለምስጋናና ለጸሎት የተስማሙትን ቃላት እየመረጠና እያቀና በአራቱ ክፍለ ዘመን፣ በመፀውና በሐጋይ በጸደይና በክረምት እንዲነገር አድርጎ ወስኖ አዘጋጀ። የመጽሐፉ የድርሰቱ ስም ድጓ ተባለ። ድጓ ማለትም በትግርኛ ደጉዓ ማለት መዝሙረ ኃዘን፥ የኃዘን ዜማ፥ ማለት ነው። ሙሾ። የዜማውን ዓይነት በሦስት ክፍል ወስኖ ተናግሮታል። እነርሱም ግእዝ፣ ዕዝል፣ ዓራራይ ይባላሉ። ግእዝ ማለትም አንደኛ በመጀመሪያ የተገኘ ማለት ነው፤ ዕዝል ማለትም ሁለተኛ ሆኖ ከግእዙ ጋር ተደርቦ፣ ተጨምሮ፣ ታዝሎ የሚነገር ማለት ነው። ዓራራይ ማለትም ሦስተኛ ተጨማሪ ሆኖ አራኅራኂ፣ ርኅራኄ፣ አሳዛኝ ልብን የሚመስጥና ደስ የሚያሰኝ ማለት ነው።መንግሥቱን ይህን ድርሰቱን ያዘጋጀበት ዘመን ከ540 ዓ.ም ሲሆን የመጨረሻ ልጁ አፄ ገብረ መስቀል ወረሰ።
አፄ ገብረ መስቀልና አባ አረጋዊ ቅዱስ ያሬድ እነዚህ ሦስቱ በአንድነት እንደነበሩ ታሪከ ነገሥቱና ገድለ አረጋዊ ይገልጽልናል። አቡነ አረጋዊ የደብረ ዳሞን ተራራ አቀማመጥ አይተው ደስ ስላላቸው፣ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀል በዚሁ ተራራ ላይ እንዲኖሩበትና እንዲጸልዩበት ፈቀደላቸው። እርሳቸውም ይህንን ተራራ ከተረከቡ በኋላ በተራራው ላይ የጸሎት ቤት ስለሌለ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀልን አንድ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራላቸው ለመኑት። ንጉሡም ቤተክርስቲያን ልሠራ የምችልበትን ሥፍራ መርጠው ያመልክቱኝ ብሎ ነገራቸው አቡነ አረጋዊም ተነሥተው ዞረው ቦታውን መርጠው አሳዩት።
ከዚህ በኋላ ንጉሡ በአዋጅና በትዕዛዝ ድንጋዩና እንጨቱ እየተሰበሰበ በከብትና በሠረገላ እየተጋዘ ተሰበሰበና ከታች ወደ ተራራው ላይ ወጥቶ ተሠራና የቤተ ክርስቲያኑ ሥራ በሁለት ዓመት አለቀ። ባለቀም ጊዜ የቤተክርስቲያኑ ሥራ ተመልካቾችን አስደነቀ።
ለዚሁም ቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ የሆኑ አልባሳት፣ በወርቅ በብርና የተደጎሱና የተከፈፉ መጻሕፍትን አበረከቱ። ከማኅበረ በኩር የመጣውን የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ላይና አግብተው አቡነ አረጋዊ ባርከውና ቀድሰው ንጉሡና ጳጳሱ ቆረቡ። ከዚያም አፄ ገብረ መስቀል በተራራው ላይና በግርጌ ላሉት ሠራዊት ግብር አብልተው ነዳያን ሁሉ በንጉሡ
ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ በአክሱም ሲያስተምር ሳለ በንጉሡ አፄ ገብረመስቀልና አቡነ አረጋዊ፥ ወደዚህ ተራራ መጥቶ ቤተክርስቲያኑን እንዲጎበኝና እንዲዘምር ተጠርቶ ሲመጣ ከተራራው ሥር ሲደርስ የአቡነ አረጋዊን ደቀመዛሙርት ማትያስና ዮሴፍ የሚባሉትን ከወንዝ ዳር ዓሣ ሲያጠምዱ አግኝቶ "ዳኅንኑ ዝስኩ አረጋዊ አቡክሙ ፤ ይህ አረጋዊ አባታችሁ ደህና ነው?" ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም ደኅንነታቸውን ነገሩት። ከዚያም ቅዱስ ያሬድ ወደ ተራራው ላይ ወጥቶ ከአቡነ አረጋዊ ጋር በመንፈሳዊ አምኃ በፍቅር ተገናኙ ወደ ቤተክርስቲያኑም ሄዶ 3 ጊዜ ሰግዶ ከተሳለመ በኋላ የሕንጻውን ማማር በአድናቆት ተመልክቶ ከፍ ባለ የዜማ ድምፅ እያጉረመረመ እንዲህ ሲል ዘመረ። "ይሄውፅዋ መላዕክት እንተ በሰማያት ይሄውፅዋ መላዕክት እስመ ማኅደረ መለኮት ዖድክዋ ዖድክዋ ዖድክዋ ወርኢኩ ሥነ ሕንፄሃ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ምሥአል ወምስጋድ ወምሥትስራየ ኃጢአት ይዕቲ ቅድስት ደብተራ"።
የሚለውን መዝሙር ከዘመረ በኋላ ስምንት ቀን ያህል ከአቡነ አረጋዊ ጋር ሰንብቶ ተመለሰ።
ከዚህ በኋላ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀልና አቡነ አረጋዊ ከቅዱስ ያሬድበጣና አብረው ወደ ሌላ ጠቅላይ ግዛት ጉብኝት ሄዱ። ከዚያም በጣና በአንዱ ደሴት ላይ የቅዱስ ቂርቆስን ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ተቀመጡ። በዚያም ቦታ ቅዱስ ያሬድ ሁለት ዓመት አስተማረ። እርሱ እራሱ ጻፈው የሚባል ድጓ ምልክት የሌለው ዛሬ በዚሁ ደሴት በጣና ቂርቆስ ይገኛል።
ከዚህም ደሴት ከጣና ቂርቆስ ተነሥተው ንጉሡና አቡነ አረጋዊ ቅዱስ ያሬድም ወደ ደጋው ወደ ጋይንት ወጡ። በዚያም አንድ ትልቅ ተራራ አግኝተው መውጫው ጠፍቶባቸው ሲጨነቁ አንድ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጥቶ አቡነ አረጋዊን "ዑድ አባ መንገለ ምሥራቅ ወዑዳ ለዛቲ ደብር፤ ዙር አባ ወደ እርስዋም ትወጣ ዘንድ በምሥራቅ በኩል ዙር" አላቸው ወደ ምስራቅ ሲዞሩ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነጭ ሐረግ ዘረጋላቸው እርሱን ይዘው ወደ ተራራው ላይ ወጡ። በዚሁ ተራራ ላይ የእመቤታችንንአምባ ክርስቲያን ሠሩ። የተራራውም ስም እስከ ዛሬ ድረስ ዙር አምባ ተብሎ ይጠራል። በዚህ ገዳም ምሥራቃዊ አቅጣጫ ቅዱስ ያሬድን የምትዘክር "ከርሞ አይደርቅ" የምትባል ዛፍ አለች። ቅዱስ ያሬድ በዚች ዛፍ ሥር ተቀምጦ ዝማሬ መዋሥዕት የተባለውን መጽሐፍ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ስላስተማረበት ይህም ቦታ ገዳም እስከ ዛሬ ድረስ የዝማሬና የመዋሥዕት ምስክር ቦታ ሆኖ ይኖራል።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ያሬድ ከአኵሱም ወደ ማይኪራህ አምርቶ እመቤታችን ቅዱስ ኤፍሬምን በአካለ ነፍስ ከሶርያ አባ ሕርያቆስ ከብሕንሳ አምጥታ ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን ንባቡን እየነገሩት በዜማ እንዲደርስላት አድርጋለች። ከዚህም አያይዞ ለሥጋ ወደሙ ጸሎት የሚያገለግሉትን ንባቡ የሌሎች ሊቃውንት ድርሰት የሆኑትን ዐሥራ አራቱን ቅዳሴዎች በዜማ አዘጋጀ።
ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ ሰሜን ተራሮች ጸለምት ሔዶ ምዕራፍ የተባለውን ድርሰቱን ደረሰ። ከዚህ በኋላ አገው፣ ፎገራ እና ወደ ሌሎችም ቦታዎች እየዞረ አስተማረ።
ቅዱስ ያሬድ በቅድስት አኵሰም ወንበር ዘርግቶ፣ ጉባኤ አስፍቶ ደቀ መዛሙርቱን እያስተማረ ሲኖር በጾመ፵ ሱባኤ ላይ ሳለ አንድ ቀን በምኵራብ ሰሞን ስለምናኔው እያስታወሰ በተመስጦ ሲዘምር የዜማው ጣዕም እንኳን ሌላውን ራሱን እጅግ ይመሥጠው ነበር። በጣዕመ ዝማሬው ተመሥጦ ሲያዳምጥ የነበረው ኢትዮጵያዊው ንጉሥ የዐፄ ገብረ መስቀል ዐይን ዐይኑን እየተመለከተ ሳይታወቀው በመስቀል ስላጢኑ (በበትረ መንግሥቱ ዘንግ) ጫፍ የቅዱስ ያሬድን እግር ወጋው። ቅዱስ ያሬድ ግንቀጠለ፤ ከሰማያት የተገኘች ቃለ ማሕሌቱን እስኪፈጽም ድረስ ከቆመበት ሳይንቀሳቀስ ሕመሙ ሳይታወቀው ደሙም ያለማቋረጥ ፈሰሰ።
ቅዱስ ያሬድ የጀመረውን በፈጸመ ጊዜ ንጉሡ ደንግጦ በትሩን ከቅዱስ ያሬድ እግያሬድን ቢነቅለው ደሙ በኃይል ይፈስ ጀመር። ያን ጊዜ ንጉሡ ዐፄ ገብረ መስቀል የቅዱስ ያሬድን ትዕግሥት ባለ ጊዜ በመደነቅ፣ በመገረምና በመደንገጥ ዝም በማለት አፉን ይዞ ቆመና ምድራዊ ዋጋ የሚፈልግ መስሎት "ካህን ያሬድ ሆይ የምትፈልገውን ዋጋ ጠይቀኝ" አለው። ቅዱስ ያሬድ መልሶ "የፈለግኹትን እንዳትከለክለኝ ቃል ኪዳን ግባልኝ" አለው። ንጉሡም የጸና ቃል ኪዳን ለቅዱስ ያሬድ ገባለት። ቅዱስ ያሬድም " ከዚህ ሐላፊ ዓለም ክብር ተለይቼ መናኝ ሆኜ እንድኖር ተወኝያሬድ አሰናብተኝ" ብሎ አሳብን ገለጸለት። ከዚህም በኋላ ንጉሥ ዐፄ ገብረ መስቀል ካህን የጠየቀውን እንዳይከለክለው ከአፉ የወጣውን መሐላ አስቦ በምናኔ አሰናበተው እንጂ ሊከለክለው አልቻለም።
ቅዱስ ያሬድ ካህንም የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ወዳለችበት ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ሁለት እጆቹን በታቦተ ጽዮን ላይ አኑሮ "ቅድስት ወብፅዕት፣ ስብሕት ወቡርክት፣ክብር ወልዕልት አንቀጸ ብርሃን መዓርገ ሕይወት" ብሎ በደረሰው አንቀጸ ብርሃን ጸሎት እመቤታችንን አመሰገ። በዚህ ጊዜ እጁ በታቦተ ጽዮን ላይ ረቦ በመንፈስ ቅዱስ እየተቃኘ ስለነበር ከመሬት አንድ ክንድ ከፍ ከፍ ብሎ ይታይ ነበር። እስከመጨረሻው በከፍተኛ ቃል በዕዝል ዜማ እየዘመረ እግዚአብሔር እና እመቤታችንን ከአመሰገነ በኋላ እመቤታችንበጸሎት መንገድ እንድትመራውና እስከ ፍጻሜ ገድሉ ትረዳው ዘንድ በጸሎት ለመናት። እመቤታችንም መልሳ "ሰማያዊት ጽዮን ያደረግኻት መቅደሴን፣ በመዝሙር በማሕሌት ምስጋና የኪሩቤልና የሱራፌል ወገን ሰማያውያን ያደረግኻቸው ልጆቼ ካህናትን እንዴትድረስ ትተህ ትሔዳለህ" ብላ ቃል በቃል አነጋገረችው። የመንገዱን ስንብት እስክትፈቅድለት በለቅሶና በእንባ ዳግመኛ ለመናት እርሷም እንዲሔድ ፈቀደችለት።
የቅዱስ ያሬድ ምናኔ፦ ወደ ገዳም ሊሆድ ተዘጋጀ በዚህ ጊዜ የሚወዱት ካህናት፣ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ተከትለውት እስከ ተከዜ ወንዝ ድረስ ሸኙት። ከእርሱ በሚለዩበትም ጊዜ "ሰላመ ነሳእነ ወሰላም ኃደግነ ለክሙ ወሰላመ እግዚአብሔር የሀሉ ምስለ ኩልክሙ፤ ሰላምን ከእናንተ ተቀበልን ለእናንተም ሰላምን ተውንላችሁ የእግዚአብሔር ሰላምም ከሁላችሁ ጋራ ይኹን" ብሎ በዜማ ተሰናበታቸው። ዳግመኛ "ወሰላም እግዚአብሔር እንተ ኵሉ ባቲ ተሀሉ ወትረ ምስለ ኵልክሙ፤ ፍቅርና ስምምነት ሁሉ ያለበት የእግዚአብሔር ሰላምታ ሁል ጊዜ ከሁላችሁ ጋራ ትኑር" ብሎ በጣዕ ዜማው መረቃቸው። ካህናቱም ይህን ሰምተው አለቀሱ። እርሱም ከእርሱ ጋራ አለቀሰ። በዚሁ ጣዕመ ዜማው የመጨረሻ ቡራኬውን ሰጣቸውና እርስ በእርሳቸው ተሳስመው ተነሰነባብተው ከእርሱ በመለየታቸው እያዘኑና እየተከዙ ወደ አገራቸው አኵሱም ተመለሱ። እርሱ ግን የተከዜን ወንዝ ተሻገረ። የወንዙ ፏፏቴና ጎርፍ እንሚጮህ አንበሳ ሲጮህ በሰማ ጊዜ "አኅለፍኮሙ በእግር እንተ የብስ ማእከለ ባሕር ተከዜ...፤ በተከዜ ባሕር መካከል በእግር እንደሚሻገር በደረቅ አሻገርካቸው..." እያለ በረቀቀ ምስጢር እግዚአብሔርን በማመስገን እየዘመረ ሲሒድ አንዲት ሴት ውሃ ቀድታ ወደ ቤቶ ስትመለስ ድምፁን ሰምታ ወይ ቃል! ወይ ቃል! እንዴት አንጀት ይበላል! ምንኛስ ያሳዝናል! ብላ ደጋግማ በማድነቅ ስለ ተናገረች ቅዱስ ያሬድ ቆሞ የዘመረባት ቦታ "ወይ ቃል" ተብላ ተጠራች። ዛሬ ይህች ቦታ ጎንደር ክፍለ አገር ደባርቅ አካባቢ "ወይ ቃል" ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ተብላ ትጠራለች።
ቅዱስ ያሬድ ወደ ሰሜን ተራሮች ሔዶ ጸለምት ወጥቶ ብርድ በጸናበት በረዶ በተከማቸበት ሳኔር ተብሎ በሚጠራ በሐዊ ዐምባ ጽመና ይዞ ተቀመጠ። በዚያም በብዙ ትጋት በጾምና በጸሎት ይልቁንም በስብሐት እግዚአብሔር ብቻ ተወስኖ ጉባኤ ዘርግቶ፣ ትምህርት አስፍቶ ከሱራፌል መላእክት እንደተማረው አድርጎ ከጸለምት፣ ከስሜን፣ ከአገውና ከሌላ አገር ወደ እርሱ የሚመጡትን ሰዎች ሁሉ ማሕሌተ እግዚአብሔር እያስተማረ ኖረ።
ቅዱስ ያሬድ ከትውልድ አገሩ አኵሱም መንኖ ከወጣ በኋላ ትዕግሥቱን እያዘወተረ ወደ እርሱ የመጡትን ሁሉ በማስተማር በገዳመ ስሜን ኖረ። ቅዱስ ቍርባን ለመቀበልና ቅዱሳት ገዳማትን ለመሳለም በፈለገ ጊዜ በሠረገላ ብርሃን ተጭኖ አኵሱም ደርሶ ቅዱስ ቍርባን ተቀብሎ ሌሎች ገዳማትንም ይሳለም ነበር።
በመጨረሻ ቅዱስ ያሬድ ካህን ዘመኑን ሁሉ በመላእክት ማኅሌት እግዚአብሔርን በማገልገልና ይህን ማኅሌት ለሚከተሉት ደቀ መዛሙርት በማስተማር ዘመኑን ፈጽሞ ለሃያ ሁለት ዓመታት በላይ በምናኔ ታግሦ በገድሉና በጣዕመ ዜማው ፀላኤ ሠናያትን ድል አድርጎ ከዚህ ዓለም ድካምና መከራ የሚያርፍበት፣ የሚሰወርበት ቀንና ሰዓት መድረሱን በጸጋ በዐወቀ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ሰብስቦ "ይቤ ጳውሎስ ኃላፊ ንብረቱ ለዝንቱ ዓለም አኃውየ አስተፋጥኑ ገቢረ ሠናየ አነሰ በድረየኒ ፈጸምኩ ወሃይማኖትየኒ ሠለጥኩ እንከሰ ጽኑሕ ሊተ አክሊል ዘየዓሥየኒ መኰንነ ጽድቅ" 2ጢሞ4፥7-8 እያለ በሚያራራ ቃል ምክሩን ሰጥቶ ተሰናበታቸው። እነርሱም ምክሩን ተቀብለው "አባ አቡነ፣ አባ መምህርነ አይቴ ተሐውር ወለመኑ ተኀድገነ፤ አባታችን መምህራችን ወደ የት ትሔዳለኽ? ለማንስ ትተወናለኽ? እያሉ ሲያዝኑ ሲያለቅሱ በአንድ ዋሻ ውስጥ ገብቶ ግንቦት11 ቀን በ571ዓ.ም ተሰወረ። (ምንጭ፦ የቤተ ክርስቲያን ብርሃን ቅዱስ ያሬድና የቅዱስ ያሬድ ታሪክ ከሚሉት መጻሕፍት።)
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ቀን የካህኑ የቡዝ ልጅ ታላቅ ነቢይ ሕዝቅኤል አረፈ። ይህም ካህንም ነቢይም ሆኖ ናቡከደነጾር የእስራኤልን ልጆች በማረካቸው ጊዜ ወደ ባቢሎን ተማርኮ ሔደ።
በባቢሎን አገርም ሳለ የትንቢት መንፈስ በላዩ አደረ በትንቢቱ ውስጥ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከከበረች ድንግል እመቤታችን ማርያም ስለ መወለዱና ከወለደችውም በኃላ በድንግልና ጸንታ ስለ መኖርዋ ተናገረ።
እንዲህም ብሎ ትንቢት ተናገረ እኔ ወደ ምሥራቅ ስመለከት የተዘጋች ደጅ አየሁ። ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች አትከፈትም የሚገባባትም የለም። የእስራኤል ፈጣሪ እግዚአብሔር እንደተዘጋች ይገባባታልና ከእርሱ በቀር የሚገባም የሚወጣም የለም አለኝ።
ሁለተኛም ስለ ክርስትና ጥምቀት በንጹሕ ውኃ እረጫችኃለሁ ከኃጢአታችሁም ትነጻላችሁ ከርኲሰታችሁም ሁሉ። አዲስ ልብን እሰጣችኃላሁ አዲስ ዕውቀትንም አሳድርባችኃለሁ ድንቊርና ያለበትንም ልብ ከሰውነታችሁ አርቄ ዕውቀት ያለውን ልብ እሰጣችኃለሁ መንፈስ ቅዱስንም ተቀብለው የእግዚአብሔር ልጆች እንደሚሆኑ ተናገረ።
ሕዝቡንም ማስተማር ስለ መተዋቸው ካህናትን ሲገሠጽ ካላስተማራችኃቸውና ካላነቃችኃቸው የሰዎችን ነፍስ እግዚአብሔር ከእናንተ ይፈልጋል አላቸው።
ደግሞ ስለ ሥጋ መነሣት በሕይወት ለመኖርም ቢሆን ወይም በሥቃይ አስቀድሞ እንደነበሩት በድኖች ተነሥተው ከነፍሶቻቸው ጋራ አንድ ሊሆኑ አላቸው ብሎ ተናገረ። ለሚያነባቸው የሚጠቅሙ ብዙዎች ትምቢቶችን ተናገረ።
እግዚአብሔርም በእጆቹ ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶችን ገለጠ። የእስራኤል ልጆች በባቢሎን ሳሉ ጣዖት ባመለኩ ጊዜ ገሠጻቸው። ስለዚህም አለቆቻቸው በጠላትነት በላዩ ተነሥተው ገደሉት ይህም ሁሉ ትንቢቱ የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ሰው ከመሆኑ በፊት ነው። የትንቢቱም ዘመን ሃያ ዓመት ነው።
ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages