ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 6 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, April 14, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 6

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሚያዝያ ስድስት በዚህችም ቀን የአባታችን_አዳምንና የእናታችን_ሔዋን መታሰቢያቸውን ነው፣ ከአባታችን አዳም ጀምሮ አሥረኛ ትውልድ የሆነ ጻድቁ_ኖኅ ልደቱ ነው፣ ንጉሡ ልበ አምላክ ቅዱስ_ዳዊት ልደቱ ነው፣ በበረሀ የምትኖር ግብፃዊት_ማርያም አረፈች፣ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው ሳምንት ለሐዋርያው_ቶማስ ተገለጠለት፡፡


ሚያዝያ ስድስት በዚህችም ቀን የአባታችን አዳምን የእናታችን ሔዋንን መታሰቢያቸውን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙን። ይህን አባታችን አዳምን ሳይፈጥረው አስቀድሞ በሰማይና በምድር ያለውን አዘጋጀለት። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረ መላእክትንም ስለርሱ ፈጠረ።
ከዚህም በኃላ በኤዶም ተክልን አዘጋጀለት እርሱም የፍሬው ጣዕም በየራሱ ልዩ ነው የሚአሻውን ሁሉ አከናውኖ እነሆ ከምድር መካከል ይኸውም ጎልጎታ ነው አፈር አንሥቶ በሦስት ሰዓት እርሱን ፈጠረው። ከአራት በሕርያት ይኸውም ውኃ እሳት ነፋስና መሬት ነው በአርአያውና በምሳሌው ራሱን አስመስሎ ፈጠረው በፊቱም እፍ ብሎ የሕይወት መንፈስን አሳድሮ የሚናገርና የሚያስተውል የሚያውቅ አደረገው የብርሃንንም ልብስ አልብሶ ንጉሥ ነብይ ካህን አስተዳደሪ አድርጎ በፈጠረው ሁሉ ላይ ሾመው።
ከዚህም በኃላ አይቶ ስማቸውን ይሰይም ዘንድ አራዊትን እንስሳትን የሰማይ ወፎችን ሁሉ ወደርሱ አመጣ። አዳምም መንፈስ ቅዱስ እንዳናገረው ለሁሉም ስም አወጣላቸው። ከዚህም በኃላ በአዳም ላይ እንቅልፍን አመጣበትና አንቀላፋ ከጐኑም አንድ ዐጥንትን ነሣ ቦታዋንም በሥጋ መላው እግዚአብሔርም ሴት አድርጎ አሰምሮ ሠራት በአዳምም በፊቱ አኖራት። አዳምም ነቅቶ ይቺ ከዐጥንቴ ዐጥንት ከሥጋዬ ሥጋ ናት ሚስት ትሁነኝ ብሎ ተናገረ ስሟንም ሔዋን አላት።
አዳምም በጎልጎታ ቁሞ የፈጣሪውን ቃል እየሰማ ሳለ እነሆ ከሚስቱ ከሔዋን ጋራ በፊት በኃላ ሁነው በየነገዳቸው አዳምን ስለ አከበረው መላእክት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ደመና ተሸክማ ወሰደቻቸው በኤዶም ገነትም አኖራቸው።
እግዚአብሔርም አዳምንና ሔዋንን በገነት ካለው ተክል ሁሉ ብሉ ግን ከገነት መካከል ዕፀ በለስን አትቡሉ ከእርሱ በበላችው ቀን ሞትን ትሞታላችሁ አላቸው። አዳምም ገነትን እያረሰና እየቆፈረ ከፍሬዋም እየተመገበ ከመላእክት ጋራ ሲያመሰግን ኖረ።
የበጎ ሥራ ጠላት ሰይጣን ግን ከማዕርጉ በወደቀ ጊዜ በአዳም ጌትነትና ክብር ቀንቶ በእባብ አድሮ ወደሔዋን ሔደ። ያንን ዕፀ በለስንም ትበላ ዘንድ አታለላት አምላክ የመሆንንም ተስፋ አሳደረባትና አሳታት።
ያንን ዕፀ በለስንም በአየችው ጊዜ አማራት በልታ ለባልዋም አበላችው ያን ጊዜ የብርሃን ልብሳቸው ከላያቸው ተገፈፈ። እነርሱም ራቁታቸውን እንደሆኑ አውቀው በበለስ ቅጠል ኀፍረተ ሥጋቸውን ሸፈኑ። እግዚአብሔርም ስሕተታቸውን አውቆ አስቀድሞ እባብን ረገመ በእርሷና በሴቲቱ ዘር መካከል ጠላትነትን አጸና።
በሔዋንም ላይ በፃር በገዐር ውለጂ ወልደሽም መመለሻሽ ወደባልሽ ይሁን እርሱም ይግዛሽ ብሎ ፈረደባት። አዳምንም እንዲህ አለው ስለ አንተ ምድር የተረገመች ትሁን ጥረህ ግረህ እንጀራህን ብላ አንተ አፈር ነህና ወደ አፈርነት ትመለሳለህ።
እግዚአብሔርም የቁርበትን ልብስ አዘጋጅቶ አለበሳቸው ሰባት ዓመት በተድላ ከኖሩ በኃላ በምሽት ጊዜ ከኤዶም ገነት ወጡ። አዳምም በማለዳ ፀሐይ ሲወጣ ነጭ ዕጣን ቀንዓት ሰሊሖት የሚባል ሽቱ ከሎሚ ውኃ ጋር አጠነ። አዳምም በኤዶም ገነት እንደተማረ ምድሪቱን እያረሰና እየቆፈረ ኤልዳ በሚባል ምድር ኖረ።
አዳምም ሔዋንን በግብር አወቃት ቃየልን ከእኅቱ ጋር ወለደችለት ከእርሱም በኃላ አቤልን ከእኅቱ ጋራ ወለደችው ቃየልና አቤልም አድገው አካለ መጠን አደረሱ። ወደ እግዚአብሔርም መሥዋዕት በአቀረቡ ጊዜ ጌታ የአቤልን መሥዋዕት ተቀበለ ስለዚህም ቃየል ተቆጣ በአቤልም ቀንቶ ገደለው።
አዳምም በልጁ በአቤል ሞት እያዘነና እያለቀሰ አራት የዘመን ሱባዔ ኖረ። ከዚህም በኃላ ሴት ተወለደለት በእርሱም መታሰቢያው ጸና ከእርሱም በኃላ ብዙዎች ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ።
እግዚአብሔርም ንስሓውንና ልቅሶውን አይቶ የድኅነት ተስፋ ሰጠው። አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ወደ ዓለም መጥቼ ከልጅ ልጅህ እወለዳለሁ ሕፃንም ሆኜ በሜዳህ ውስጥ እድሀለሁ በመስቀሌና በሞቴም አድንሃለሁ አለው።
አዳምም ከገነት በወጣ ጊዜ የወሰደውን ወርቅ ከርቤና ዕጣን ለልጁ ለሴት ሰጠው እንዲህም አለው በኃላ ዘመን የእግዚአብሔር ልጅ መጥቶ ከድንግል ይወለዳል ያን ጊዜ የጥበቡ ሰዎች ይህን ወርቁን ከርቤውንና ዕጣኑን እጅ መንሻውን ያመጡለታል እርሱም መዝግቦ በዕቃ ቤት አኖረው።
ወደ ኖኅም እስኪደርስ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ኖረ ከኖኅም የምሥራቅ ሰዎች ወደ ሆኑ የጥበብ ሰዎች እስኪ ደርስ ተላለፈ። እነርሱም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በተወለደ ጊዜ አምጥተው ለእግዚአብሔር ልጅ እጅ መንሻ አድረገው አቀረቡለት እመቤታችንም ከእጃቸው ተቀበላ በኃላ ለቅዱስ ጴጥሮስ ሰጠችው ቅዱስ ጴጥሮስም ለቀሌምንጦስ ሰጠው።
አዳምም የሚያርፍበትን ሰዓት በአወቀ ጊዜ ልጁ ሴትን ጠርቶ ከመሞቴ በፊት ልጆችህንና የልጅ ልጆችህን ወደእኔ አቅርባቸው አለው። የአባቱን ቃል ሰምቶ ዕንባው በጉንጩ ላይ እየፈሰሰ ወጣ ወደ አዳምም አቀረባቸው።
አዳምም በአያቸው ጊዜ ከእሳቸው ስለ መለየቱ አለቀሰ። እነርሱም ሲያለቅስ በአዩት ጊዜ ሁሉም በአንድነት ወደ እግዚአብሔር በግምባራቸው ተደፍተው አለቀሱ ምድር እንዴት ትሸፈንሃለች ከዐይኖቻችንስ እንዴት ትሠወራለህ አሉ።
ከዚህም በኃላ አባታችን አዳም ሁሉን ልጆቹን ባረካቸው መረቃቸው። ልጁን ሴትን እንዲህ አለው ይቺ ዓለም ድካምና ችግርን የተመላች ናትና በእግዚአብሔር እየታመንክ ዕውነትን ንጽሕናን ጠብቅ ሰይጣን ወደ ሚያሳይህ ምትሐቱና ወደ ነገሩ አታዘንብል።
በሞትኩ ጊዜም ሥጋዬን ወስዳችሁ ሰሊክ ሚዓ በሚባል ሽቱ ገንዛችሁ በግምጃ ቤት አኑሩኝ የጥፋት ውኃ ይመጣ ዘንድ አለውና ፍጥረት ሁሉ ይሰጥማል ከስምንት ነፍስ በቀር የሚቀር የለም። ልጄ ሆይ ለወገኖችህ ቋሚ ሁነህ እግዚአብሔርን በመፍራት ጠብቃቸው የዕውነት መንገድንም ምራቸው ለስይጣንም እንዳይ ታዘዙና እንዳያጠፋቸው አደራ አስጠብቃቸው።
ልጆችህንና የልጅ ልጆችህን ከቃየል ልጆች ለያቸው አንድ ይሆኑ ዘንድ ከቶ አትተዋቸው ወደ ሥራቸውና ወደ ጨዋታቸውም አይቅረቡ። ከዚህም በኃላ ወደ ልጁ ወደ ሴትና ወደ ሔዋን መለስ ብሎ ያንን ወርቅ ከርቤና ዕጣን ከእርሳቸው ጋራ አኑረው ይጠብቁት ዘንድ አደራ አላቸው። እንዲህም አላቸው የጥፋት ውኃ በመጣ ጊዜ ሥጋዬን ከወርቁ ከከርቤውና ከዕጣኑ ጋራ ወደ መርከብ ያስገቡ ከዚያም በኃላ በምድር መካከል ያኑሩት።
ከብዙ ዘመናት በኃላም ያቺን አገር ይወርዋታል እሊህንም ወርቅ ከርቤና ዕጣን ከብዙ ምርኮ ጋር ይወስዱትና አካላዊ ቃል መጥቶ ሰው እስከሚሆን ድረስ በዚያ ይጠበቃል። ነገሥታትም ይዘው መጥተው ይገብሩለታል ወርቁ ስለ መንግሥቱ ዕጣኑ ስለ ክህነቱ ከርቤውም ማሕየዊት ስለሆነች ሞቱ ነው።
ለአባታችን አዳምም ዘጠኝ መቶ ሠላሳ ዓመት ሲሆን መላልኤልም መቶ ሠላሳ አምስት ዓመት ሲሆነው በተፈጠረባት ዐርብ በዘጠኝ ሰዓት አረፈ ያረፈባትም ሰዓት ከገነት የወጣባት ናት በዚያን ጊዜም የመላእክት ሠራዊት ከልጆቹ ጋራ ተሰበሰቡ። መልካም አገናነዝም ገነዙት በብዙ ሽቱዎችም መዓዛውን አጣፈጡ።
ይህም በገነትና በደብር ቅዱስ ያለ ነው ስጋውንም በፀሐይ መውጫ በኲል በዋሻ ውስጥ አኖሩ የሚያበራ መብራትም አኖሩ ከእርሱም ጋራ ወርቁን ከርቤውንና ዕጣኑን አስቀመጡ ዋሻውንም በአዳምና በሔዋን በሴት ቁልፍ ቆልፈው አተሙት። የጥፋት ውኃም እስከ መጣ ድረስ ሴትና ልጆቹ ለአባታችን አዳም ሥጋ ሲያገለግሉ ኖሩ።
ከዚህ በኃላም ኖኅ በአምላክ ትእዛዝ ደብረ አራራት እስከሚአደርሰው ከእርሱ ጋራ የአባታችን የአዳምን ሥጋ በመርከብ ወሰደው። ከዚያም ሴምና መልከ ፀዴቅ የእግዚአብሔር መልአክ እየመራቸው ይዘውት ሔዱ ከቀራንዮ ቦታ ደርሰው በዚያ ቀበሩት መልከ ጼዴቅም በዕጣንና በቁርባን ሲያገለግል ኖረ።
የእግዚአብሔርም ልጅ መጥቶ ከድንግል ልጁ በተወለደ ጊዜ መድኃኒት በሆነች ሞቱ አድኖ ወደ ቀደመው ርስቱ መለሰው እርሱ ለከበሩ ደጋጎች ነቢያት ለተጋዳዮችም ሰማዕታትና ጻድቃን አባት ነውና ስለ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ ወደ ዓለም መጥቶ ሰው ሁኗልና።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ቀን ከአባታችን አዳም ጀምሮ አሥረኛ ትውልድ የሆነ ጻድቁ ኖኅ ልደቱ ነው፡፡ እርሱም ከታናሽነቱ ጀምሮ ኃጢአት እንደሚበዛና ደጋጎች እንደሚያንሱ ሥጋ የለበሰ ሁሉ በጥፋት ውኃ እንደሚደመሰስ አምላካዊ ምሥጢርን የሚያይ ሆነ፡፡ ስለዚህም ፊቱ የተቋጠረ ሆኖ ፈጽሞ ያለቅስ ነበር፡፡
ጻድቁ ኖኅ ኖኅም የአቡዚር ልጅ የሆነች ሐይከል የምትባል ሴት አግብቶ ወደ እርሷ ሦስት ጊዜ ቢገባ ሦስት ልጆችን ሴም ካም ያፌትን ወለዳቸው፡፡ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ለኖኅ ከደብር ቅዱስ ዕንጨት ቆርጦ መርከብን እንዲያሠራ ካዘዘው በኋላ አሠራሯን በዝርዝርና በጥልቀት አስረዳው፡፡ የቃየል ልጆችም ኖኅን መርከብ ሲሠራ አይተው ዘበቱበት፡፡ የአዳምንም ሥጋ ወስዶ በውስጡ አኖረ፡፡ ሴም ወርቁን፣ ካም ከርቤውን፣ ያፌት ዕጣኑን ወስደው ወደ መርከብ አስገቡ፡፡ ኖኅም ከልጆቹና 500 ዓመት ድንግልናውን ጠብቆ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ለአባታችን አዳም ሥጋ ሲያገለግል ኖረ፡፡ ከዚህም በኋላ ሚስት እንዲያገባ እግዚአብሔር አዘዘው፡፡ ሥጋ የለበሰ ሁሉ እንደሚደመሰስ ከእርሱ ዘር በቀር የሚተርፍ እንደሌለ ነገረው፡፡ ጻድቁ ከሚስቶቻቸው ጋራ ወደ መርከቡ ገባ፡፡ ንጹሐን የሆኑት እንስሳትና አእዋፋት ሴትና ወንድ ሰባት ሰባት፣ ንጹሐን ካልሆኑት ደግሞ ሁለት ሁለት ሴትና ወንድ አስገባ፡፡ ከዚያም ሰማይ ተከፍቶ የምድርም ምንጮች ሁሉ ተነድለው ራጃጅም ተራራዎችም እስኪሸፈኑ ድረስ 40 ቀንና 40 ሌሊት ዘነመ፡፡ ውኃውም በላያቸው 15 ክንድ ከፍ አለና ሥጋ የለበሰ ሁሉ ሞተ፡፡
ከ150 ቀንም በኋላ እግዚአብሔር ኖኅን አስቦ ነፋስን በምድር ላይ አመጣና ውኃውን አጎደለ፡፡ ምንጮች ተደፍነው የሰማይ መስኮት ተዘጋ፡፡ መርከቢቱም በ7ኛው በ12ው ቀን አራራት ተራራ ላይ አረፈች፡፡ ከጊዜም በኋላ እግዚአብሔር ኖኅን ከነቤተሰቡ አንድ ላይ ከመርከቡ እንዲወርዱ አዘዘው፡፡ ኖኅም መሠዊያን ሠርቶ ንጹሕ ከሆኑት ሁሉ ወስዶ መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ እግዚአብሔር መልካም መዓዛን አሸተተ፡፡ ዳግመኛም ምድርን በንፍር ውኃ እንዳያጠፋ ቃልኪዳን ገባለት፡፡ ምድር ፀንታ በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ዘር መከር፣ ቅዝቃዜና ሙቀት፣ በጋና ክረምት፣ መዓልትና ሌሊት እንደማይቋረጥ ቃልኪዳን ገባለት፡፡ እግዚአብሔርም ኖኅንና ልጆቹን ባረካቸው፡፡ ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉዋት ግዟት አላቸው፡፡
ኖኅም ምድርን ያርሳት ይቆፍርራትም ጀመር፡፡ ወይንም ተክሎ ከእርሶ ፍሬውን አድርሶ ወይን ጠጥቶ በሰከረና ራሱን በሳተ ጊዜ የከነዓን አባት ካም የኖኅን ራቁትነት አይቶ ሳቀ፣ ሄዶም ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው፡፡ ያፌትና ሴምም ልብስ ወስደው የአባታቸውን ርቃን ሸፈኑ፡፡ ኖኅም ከስካሩ በነቃ ጊዜ ሁሉም ያደረጉትን ዐወቀ፡፡ ‹ከነዓን የተረገመ ይሁን፣ ለወንድሞቹም ተገዥ አገልጋይ ይሁን› ብሎ ከረገመው በኋላ ‹‹የሴም ፈጣሪ እግዚአብሔር ይመስገን፣ እግዚአብሔርም የያፌትን አገር ያስፋ፣ በሴም ቤትም ይደር›› ብሎ መረቃቸው፡፡ አባታችን ኖኅ ‹‹እግዚአብሔር በሴም ቤት ይደር›› ማለቱ የጌታችንን ሰው መሆን በትንቢት መናገሩ ነው፡፡ እርሱም ከጥፋት ውኃ በኋላ 350 ኖረ፡፡ በአጠቃይ ዕድሜው 950 ዓመት በሆነ ጊዜ በሰላም ዐረፈ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የሰሎሞን አባት ንጉሡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ልደቱ ነው፡፡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ነሐሴ 13 ቀን ተጸነሰ፣ በሚያዝያ 6 ቀን በይሁዳ በቤተልሔም ሀገር ተወልደ። 1ኛ ሳሙ 16፡10-11፡፡
ዳዊት ማለት ‹‹ኅሩይ›› ማለት ነው። አንድም ‹‹ልበ አምላክ›› ማለት ነው። ሐዋ 13፡22፡፡ ትውልዱ ከነገደ ይሁዳ ነው። አባቱ እሴይ እናቱ ሁብሊ ይባላሉ። ሁብሊ መልከ መልካም ሴት ነበረች። ከጎረቤታቸው ያለ ጎልማሳ መልኳን እያየ በሐጸ ዝሙት ተነደፈ። እሴይ የእሷም ፈቃድ እንደሆነ አውቆ መንገድ እሄዳለሁ ብሎ ስንቁን ይዞ ወጣ። የሄደ መስሎ ከዚያው ውሎ ሲመሽ በልብሱ ተሸፋፍኖ ድምጹን ለውጦ ያንን ሰው መስሎ ገብቶ ከእርሷ ጋር አድሮ ጎህ ሳይቀድ ወጥቶ ሄደ። ዳዊት በዚህ ዕለት ተጸንሷል።
በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ” (መዝ 50፡5) ማለቱ ስለዚህ ነው። ቅዱሱም ተወልዶ ጉልበቱ ከጸና በኋላ የአባቱን በጎች ሲጠብቅ አድጓል።
እረኛና ብላቴና የነበረ ቢሆንም የፍልስጤማውያኑን ኃያል ሰው ጎልያድን በ12 ዓመቱ 5 ጠጠርን ከወንዝ ለቅሞ በወንጭፍ ወርውሮ ገድሏል፡፡ 1ኛ ሳሙ 12፡45-51፡፡ ንጉሥ ሳዖል በጌልቦአ ተራራ በራሱ እጅ ከሞተ በኋላ አስቀድሞ በይሁዳ 7 ዓመት በመላው እስራኤል 33 ዓመት ነግሡዋል፡፡ 2ኛ ሳሙ 2፡4፤ 5፡1-5፡፡‹‹እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል” (1ኛ ሳሙ 13፡14) ተብሎ በእግዚአብሔር የተመረጠና ነገረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን፣ ዳግም ምጽዓትን፣ ነገረ ማርያምን፣ ክብረ ቅዱሳንን፣ በስፋትና በጥልቀት የተናገረ የብሉይ ኪዳን ‹‹ወንጌላዊ›› የተባለ ቅዱስ ነቢይ ነው። “ብዙ ውሾች ከብበውኛልና የክፋተኞች ጉባኤም ያዘኝ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ። አጥንቶቼ ሁሉ ተቈጠሩ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም። ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፥ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ…” እያለ የጌታችንን መከራ መስቀል በትንቢት ተናግሯል፡፡ መዝ 21 (22)፡ 16-18፡፡
“አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ።”፣ “ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል። አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም እሳት በፊት ይቃጠላል፥ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ…” እያለ የጌታችንን ዕርገቱንና ዳግመኛ ለፍርድ የሚመጣ መሆኑን በግልጽ ተናግሯል፡፡ መዝ 46(47)፡4-5፣ መዝ 49(50)፡ 1-5፡፡ “የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” እያለ የእመቤታችንን ክብር አይቶ በትንቢት ተናግሯል፡፡ መዝ 44(45)፡9፡፡
ቅዱስ ዳዊት ታላቅና ገናና የከበረ ንጉሥ ከመሆኑ የተነሣ መንግሥቱ የመሢሕ መንግሥት ምሳሌ ሆኗል፤ መሢሑም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዳዊት ስም ብዙ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሶ ይገኛል። (ኢሳ 9፡7፣ ኤር 23፡5-6፣ ኤር 33፡14-17፣ ሕዝ 34፡23፣ ሆሴዕ 3፡5) በሐዲስ ኪዳንም ወንጌላዊያኑ ጌታችንን ‹‹የዳዊት ልጅ›› በማለት ነው መጀመሪያ ነገረ ልደቱን ማውሳት የጀመሩት፡፡ ማቴ 1፡1፡፡ ራሱ ጌታችንም ‹‹እኔ የእሴይ ሥርና የዳዊት ዘር ነኝ›› ብሏል፡፡ ራእ 22፡16፡፡
ቅዱስ ዳዊት 7 ሀብታት የተሰጡት ጻድቅ አባት ነው፡፡ እነዚህም የተሰጡት ሀብታት፡- ሀብተ ክህነት፣ ሀብተ መንግሥት፣ ሀብተ መዊዕ (የማሸነፍ ሀብት)፣ ሀብተ ትንቢት፣ ሀብተ ኃይል፣ ሀብተ በገና (ዝማሬ) እና ሀብተ ፈውስ ናቸው። ቅዱስ ዳዊት 24 ሰዓት ሙሉ የእግዚአብሔር ምስጋና እንዳይቋረጥ መዘምራንን መድቦ እንዲያገለግሉ ያደርግ ነበር፡፡ ራሱም 10 አውታር ባለው በገና ሌት ተቀን በፍጹም ተመስጦ ያመሰግን ነበር፡፡ በመዝሙሩም አጋንንትን ያቃጥል ነበር፡፡ መዝሙረ ዳዊት በውስጡ የያዘው ሚሥጢር እጅግ ጥልቅ ነው፡፡ አባቶቻችን ዛሬም በዱር በጫካ ሆነው መዝሙረ ዳዊትን አብዝተው ይደግማሉ፡፡ እንኳንስ የሰው ልጅ ይቅርና ‹‹መዝሙረ ዳዊትን›› ሰማያውያን ቅዱሳን መላእክትም እግዚአብሔርን ለማመስገኛነት ተጠቅመውበታል፡፡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እድሜ ዘመኑን እግዚአብሔርን በማገልገልና በመፍራት ኖሮ በታኅሣሥ 23 ቀን በሰላም ዐርፎ በኢየሩሳሌም ተቀብሯል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን በበረሀ የምትኖር ግብፃዊት ማርያም አረፈች። ይቺም ቅድስት ከእስክንድርያ አገር ሁና ወላጆቿ ክርስቲያን ናቸው። እድሜዋ አስራ ሁለት አመት በሆናት ጊዜ የመልካም ስራና የሰው ሁሉ ጠላት ሸንግሎ አሳታት በእርሷም የማይቆጠሩ የብዙዎችን ነፍስ አጠመደ እርሱ ሰይጣን ስለ ዝሙት ፍቅር ያለ ዋጋ ስጋዋን እስከ መስጠት አድርሷታልና።
በዚህም በረከሰ ስራ ውስጥ ኖረች በየእለቱም የኃጢአት ፍቅር በላይዋ ይጨመርባት ነበር። ሰውን የሚወድ የእግዚአብሄርም ቸርነት ወደ ክብር ባለቤት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ሊባረኩ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ የሚሹ ሰዎችን ገለጠላት።
ከእሳቸውም ጋራ ትሄድ ዘንድ ልቧ ተነሳሳ ከብዙ ሰዎችም ጋራ በመርከብ ተሳፈረች። ባለ መርከቦችም የመርከብ ዋጋ በጠየቋት ጊዜ ስለ መርከብ ዋጋ ያመነዝሩባት ዘንድ ሰውነቷን ሰጠቻቸው ኢየሩሳሌምም እስከ ደረሰች ይህን ስራ አልተወችም።
የክብረ ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ወደ አለች ቤተ ክርስቲያን ትገባ ዘንድ በወደደች ጊዜ መለኮታዊት ኃይል መግባትን ከለከለቻት። እርሷም ከሚገቡ ሰዎች ጋራ ትገባ ዘንድ ብዙ ጊዜ ደከመች ነገር ግን ከለከላት እንጂ የጌታ ኃይል አልተዋትም።
ከዚህም በኃላ ስለ ረከሰ ስራዋ አሰበች በልቧም እያዘነችና እየተከዘች ወደ ሰማይ ወደ እግዚአብሄር አይኖቿን አቀናች በማንጋጠጥዋም ውስጥ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ስእል አየች።
በፊቷም አለቀሰች ፍጥረቶችን ሁሉ የምትረጅአቸው አምላክን የወለደሽ እመቤቴ ተዋሽኝ ከሁሉ ሰዎች ጋራ ገብቼ የመጣሁበትን ስራዬን የፈፀምኩ እንደሆነ ያዘዝሽኝን ሁሉ እኔ አደርጋለሁ ብላ በማመን ለመነቻት።
ቤተ ክርስቲያን ፈጥና ገባች በገባችም ጊዜ የበአሉን ስራ ፈፀመች። ከዚህም በኃላ አምላክን ወደ ወለደች ወደ እመቤታችን ወደ ከበረች ድንግል ማርያም ስእል ተመልሳ ወደ እርሷ መሪር ልቅሶ እያለቀሰች ረጅም ፀሎትን ፀለየች ነፍሰዋን ለማዳን እርስዋ ወደ ወደደችው ትመራት ዘንድ አምላክን ከወለደች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ስእል ከዮርዳኖስ በረሀ ብትገቢ አንቺ እረፍትንና ድኀነትን ታገኚ አለሽ የሚል ቃል ወጣ።
ከእመቤታችን አምላክን ከወለደች ከቅድስት ድንግል ማርያም ስእል ይህን ቃል ተቀብላ ወድያውኑ ወጣች። በውጪም አንድ ሰው አግኝታ ሁለት ግርሽ ሰጣትና አምባሻ ገዛችሸት።
ከዚያም በኃላ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግራ ፅኑእ ተጋድሎ እየተጋደለች በበረሀው ውስጥ አርባ ሰባት አመት ኖረች ሰይጣንም አስቀድማ በነበረችበት በዝሙት ጦር ይዋጋት ነበር።
እርሷ ግን በተጋድሎ ፀናች ከዚያም ከገዛችው አምባሻ ብዙ ቀን ተመገበች። ሁለት ሁለት ቀን ሶስት ሶስት ቀን ፁማ ከዚያ አምባሻ ጥቂት ትቀምስ ነበር በአለቀም ጊዜ የዱር ሳር ተመገበች።
በዚያችም በዮርዳኖስ በረሀ እየተዘዋወረች አርባ አባት አመት ሲፈፀምላት እንደ ገዳሙ ልማድ የከበረች አርባ ፆምን ሊፈፅም ቅዱስ ዘሲማስ ወደዚያች በረሀ መጣ። በሱ ደብር ላሉ መነኲሳት ልማዳቸው ስለሆነ በየአመቱ ወደ በረሀ ወጥተው የከበረች የአርባ ቀን ፆም እስከ ምትፈፀም በፆምና በፀሎት ተፀምደው በገድል ይቆያሉ ።
ስለዚህም ዘሲማስ ወደ ዮርዳኖስ በረሀ በወጣ ጊዜ የሚፅናናበትን ያሳየው ዘንድ እግዚአብሄርን ለመነው። በበረሀውም ውስጥ ሲዘዋወር ይቺን ቅድስት ሴት ከሩቅ አያት የሰይጣን ምትሀት መሰለችው በፀለየም ጊዜ ከሰው ወገን እንደሆነች ተገለጠለችለት።
ወደርሷም ሄደ እርሷ ግን ከእርሱ ሸሸች ወደርሷም ይደርስ ዘንድ ከኃላዋ በመሮጥ ተከተሉት። ከዚህም በኃላ ዘሲማስ ሆይ ከእኔ ጋራ መነጋገር ከፈለግህ ጨርቅን በምድር ላይ ጣልልኝ እከለልበት ዘንድ ብላ በስሙ ጠራችው።
በስሙ በጠራችውም ጊዜ እጅግ አድንቆ ጨርቁን ጣለላት ያን ጊዜም ለብሳ ሰገደችለት እርሱም ሰገደላት እርስበርሳቸውም ሰላምታ ተሰጣጥተው በላዩዋ ይፀልይላት ዘንድ ለመነችው እርሱ ካህን ነውና ካህን ሰለሆነ።
ከዚህም በኃላ ገድሏን ታስረዳው ዘንድ ቅዱስ ዘሲማስ ለመናት ከእርሷ የሆነውን ሁሉ ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ነገረቸው። እርሷም በሚመጣው አመት የክብር ባለቤት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስጋውንና ደሙን ከእርሱ ጋራ ያመጣላት ዘንድ ለመነችው እርሱም እሺ አላት።
ዓመትም በሆነ ጊዜ ስጋውንና ደሙን በፅዋ ውስጥ ያዘ ደግሞ በለስ ተምርንና በውኃ የራሰ ምስርን ይዞ ወደርሷ ወደ ዮርዳኖስ በረሀ መጣ ቅድስት ማርያምን በዮርዳኖስ ወንዝ ዳር ስትሄድ አያት ወደርሱም ደርሳ እርስበርሳቸው ሰላምታ ተሰጣጡ በአንድነትም ፀለዩ ከዚህም በኃላ ስጋውንና ደሙን አቀበላት።
በለሱን ተምሩንና ምስሩንም አቀረበላትና ትመገብለት ዘንድ ለመናት ስለ በረከት ከምስሩ በእጇ ጥቂት ወሰደች። ደግሞም በሁለተኛው አመት ወደእርሷ ይመለስ ዘንድ ለመነችው ።ሁለተኛ አመትም በሆነ ጊዜ ወደዚያ ወደ ዮርዳኖስ በረሀ መጣ ያቺ ቅድስት ሴት ሙታ አገኛት በራስጌዋም ድኀዪቱን ግብፃዊት ማርያምን ከተፈጠረችበት አፈር ውስጥ ቅበራት የሚል ፅሁፍ አገኘ።ከፅሁፉ ቃልም የተነሳ አደነቀ።
ያን ጊዜም ከግርጌዋ አንበሳን ሲጠብቃት አየ እርሱ መቃብርዋን በምን እቆፍራለሁ ብሎ ያስብ ነበር በዚያም ጊዜ ያ አንበሳ በጥፍሮቹ ምድሩን ቆፈረ የከበረ ዘሲማስም በላይዋ ፀሎት አድርጎ ቀበራት ።
ወደ ገዳሙም ተመልሶ ለመነኮሳቱ የዚችን የከበረች ግብፃዊት ማርያምን ገድሏን እንዳስረዳችው ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ነገራቸው እጅግም አደነቁ ምስጉን ልኡል እግዚአብሄርንም አመስገኑት። መላው እድሜዋም ሰማንያ አምስት ሆኗታል።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው ሳምንት ለሐዋርያው ቶማስ ተገለጠለት በእጆቹና በእግሮቹ ውስጥ የችንካሮቹን ምልክትም አሳየው የቶማስንም እጅ ይዞ በመለኮታዊ ጐኑ ውስጥ አኖረውና በጦር የተወጋበትን ቦታ አሳየው ቶማስም ጌታዬና ፈጣሪዬ መነሣትህን አመንኩ አለ።
ጌታችንም ብታየኝ አመንከኝ የሚመሰገንስ ሳያየኝ የሚአምንብኝ ነው ብሎ መለሰለት። በትርጓሜ ወንጌልም እንዲህ ይላል ቶማስ በመድኃኒታችን ጐን ውስጥ እጁን በአስገባ ጊዜ እጁ በመለኮት እሳት ተቃጠለ በመለኮቱም ደግሞ በታመነ ጊዜ እጁ ከመቃጠል ዳነች።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በሐዋርያቶቹም ጸሎት በታጋዮች ጻድቃንም በድል አድራጊዎች ሰማዕታትም ጸሎት ይልቁንም በእመቤታችን ማርያም በአማልጅነቷ ይምረን ዘንድ ወደርሱ እንለምን ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages