አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ይህም የአልዓዛር የኤልዩድ ልጅ ኢያቄም በትውልድ ሐረግ እስከ ሰሎሞንና እስከ ንጉሥ ዳዊት የሚደርስ ነው ። ይኸውም በዙፋኑ የሚቀመጥና ለዘላለሙ በእስራኤል ዘሥጋ በእስራኤል ዘነፍስ ነግሦ የሚኖር ከዘሩ ሊሰጠው ጌታ የማለለት ነው።
ሚስቱ ሐናም መካን ሆነች ሁለቱም ወደ እግዚአብሔር አዘ ውትረው ይጸልዩና ይማልዱ ነበር። እግዚአብሔርም ልመናውቸውን ተቀበሎ ይችን ጣፋጭ የሆነች መልካም ፍሬን ዓለሙን ሁሉ ከረኃበ ነፍስ ያዳነች ሰጣቸው።
መሪር የሆነ ተገዢነትንም ከሁሉ በእርስዋ አስወገደ። ለዚህም ጻድቅ ኢያቄም ለክብር ባለቤት ክርስቶስ አያት መሆን ተገባው ድንቅ ስለ ሆነ ሥጋዊው ከልጁ ስለመወለዱ ነው።
እግዚአብሔርም በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም መወለድ ደስ በአሰኘው ጊዜ በልቡናው ደስ ብሎት መስዋዕቱን አቀረበ። ከላዩም ከወገኖቹም ልጆች ኀፍረትን አስወገደ።
አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ጡት ከአስተዋት በኋላ ለእግዚአብሔር እንደተሳሉ ተሸክመው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወስደው አስገቡአት። ጻድቅ ኢያቄም ጥቂት ዘመን ኑሮ በሰላም አረፈ። (ስንክሳር ዘወርኀ ሚያዝያ)
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባታችን ቅዱስ ኢያቄም (ከገድላት አንደበት-የተወሰደ)
ጴጥርቃ እና ቴክታ የሚባሉ ደጋግ ሰዎች በኢየሩሳሌም በአንድነት ተጋብተው ይኖሩ ነበር፡፡ እነዚህም በእግዚአብሔር የሚያምኑ የተወደዱ ጻድቃን ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚህም ሰዎች በእግዚአብሄርም በሰውም ዘንድ የተመሰከረለላቸው ባለጸጎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን መካን ስለነበሩ የሚወርሳቸው ልጅ አልነበራቸውም፡፡
አንድ ቀን ጴጥርቃ ቴክታን እንዲህ አላት፡- ‹‹እኅቴ ሆይ! ይህን ሁሉ የሰበሰብነውን ገንዘባችንን ምን እናደርገዋለን? ልጅ የለን የሚወርሰን አንቺም መካን ነሽ፣ እኔም ካንቺ በቀር ሌላ ሴት አላውቅም›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹ወንድሜ ሆይ! አምላከ እስራኤል ለእኔ ልጅ ቢነሳኝ አንተም እንደኔው ሆነህ ትቀራለህን? ከሌላ ደርሰህ ውለድ እንጂ›› ብላ ብታሰናብተው ‹‹እንደዚህ ያለ ነገር እንኳንስ ላደርገው በልቦናዬም እንዳላስበው አምላከ እስራኤል ያውቃል›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን የሚያውቅ የለም፣ ትላንትና ማታ በህልሜ ነጭ ጥጃ ከማኅፀኔ ስትወጣ ያችም ነጭ ጥጃ ሌላ ነጭ ጥጃ ስትወልድ እንዲሁ እስከ 7ት ትውልድ ሲዋለድ ሰባተኛይቱ ጨረቃን ስትወልድ፣ ጨረቃዋም ፀሐይን ስትወልድ አየሁ›› አለችው፡፡ እርሱም በጠዋት ከህልም ፈቺ ዘንድ ሄዶ የነገረችውን ሁሉ ነገረው፡፡ ያም ህልም ፈቺ ‹‹እግዚአብሔር በምሕረቱ አይቷችኋል በሳህሉ መግቧአችኋል፣ 7 አንስት ጥጆች መውለዳችሁ 7 ሴቶች ልጆችና የልጅ ልጆች ትወልዳላችሁ፣ ከቤታችሁ ሰባተኛይቱ ጨረቃ መውለዷ ከሰው የበለጠች ከመላእክትም የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላችሁ፤ የፀሐይ ነገር ግን አልታወቀኝም›› አለው፡፡ እርሱም የነገረውን ሁሉ ሄዶ ለሚስቱ ነገራት፡፡ እርሷም ‹‹እንጃ አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን ማን ያውቃል!›› ብላ ዝም አለች፡፡ ከዚያም ፀንሳ ሴት ልጅ ወለደች፡፡ ስሟንም ሔሜን ብለው አወጡላት፤ ሔሜንም አድጋ ለአካለ መጠን ስትደርስ ባል አጋብተዋት ሴት ልጅ ወለደች፣ በስምንተኛ ቀኗም ዴርዲ ብለው ስም አወጡላት፡፡ ዴርዲም አድጋ እንዲሁ ሴት ወለደችና ቶና አለቻት፣ ቶናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሲካር አለቻት፣ ሲካርም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሴትና አለቻት፣ ሴትናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሔርሜላ አለቻት፣ ሔርሜላም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ንጽህት ቅድስት ክብርት የምትሆን እመቤታችንን የወለደቻትን ቅድስት ሐናን ወለደች፡፡
ይኽችም ቅድስት ሐና በሥርዓት አድጋ ለአእምሮ ስትበቃና አካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ መንግስት ወገን ከነቅዱስ ዳዊት ወገን ከሆነው ከቅዱስ ኢያቄም ጋር አጋቧት፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ኢያቄምና ሐና በአንድነት ተጋብተው ሲኖሩ ልጅ አጡ፡፡ እነርሱም እጅግ ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ አንድ ልጅ እንኳ ስላልነበራቸው እጅግ ያዝኑ ነበር፡፡ ወደ ቤተ መቅደስ እየሄዱ እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ አጥብቀው ይለምኑት ነበር፡፡ መብዓ ይዘው ለሊቀ ካህኑ ሲሰጡት ሊቀ ካህኑም እንኳ ሳይቀር ‹‹እግዚአብሔር ብዙ ተባዙ ያለውን ሕግ በእናንተ ላይ እንዳይፈጸም አድርጎ ልጅ የከለከላችሁ ኃጢአተኛ ብትሆኑ ነውና መብዓችሁን አልቀበልም›› ብሎ በእጅጉ አሳዝኗቸዋል። በሊቀ ካህኑ እያዘኑና እየተከዙ ሲመለሱ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ዛፍ ሥር ተቀመጠው ሳለ እርግቦች ጫጩቶቻቸውን ሲያጫውቱ ተመልክተው ‹‹ለእነዚህ ወፎች እንኳ ልጆችን የሰጠህ አምላክ ለእኛስ መች ይሆን ልጅ የምትሰጠን?›› ብለው እጅግ አምርረው አለቀሱ፡፡
ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና ሲያዝኑ ሲጸልዩ ውለው ከዘካርያስ ከሊቀ ካህናቱ ሄደው ‹‹አቤቱ ጌታችን ሆይ ወንድ ልጅ ብንወልድ ተምሮ ቤተ እግዚአብሔርን አገልግሎ እንዲኖር እንሰጣለን፤ ሴት ልጅም ብንወልድ ውኃ ቀድታ መሶብ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር እንሰጣለን›› ብለው ስዕለት ገቡ፡፡ ዘካርያስም ‹‹እግዚአብሔር ጸሎታችሁን ይስማችሁ ስዕለታችሁን ይቀበልላችሁ የልቦናችሁን ሀሳብ ይፈጽምላችሁ›› ብሎ አሳረገላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ቅድስት ሐናና ቅዱስ ኢያቄም ዕለቱን ራእይ አይተው ነገር አግኝተው አደሩ፡፡ ራእዩስ እንዴት ነው ቢሉ ኢያቄም ‹‹ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ›› አላት፡፡ ‹‹ወፍ›› የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ነጭነቱ ንጽሐ ባህሪው ነው፤ ‹‹ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ›› ማለቱ የኢያቄምን (የሰውን) ባህርይ ባህርይ እንዳደረገው ዕወቅ ሲል ነው፡፡ ሰባቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን ልዩ ልዩ ባሕርይው ምልአቱ ስፍሃቱ ርቀቱ ልእልናው ናቸው፡፡ ቅድስት ሐናም ‹‹እኔም ደግሞ አየሁ እንጂ›› አለችው፡፡ ‹‹ምን አየሽ?›› ቢላት ‹‹ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማኅፀኔ ስትተኛ አየሁ›› አለችው፡፡ ‹‹ርግብ›› የተባለች እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት፣ ነጭነቱ ንጽህናዋ ቅድስናዋ ድንግልናዋ ነው፡፡ ‹‹ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማኅፀኔ ስትተኛ አየሁ›› ማለቷ ብሥራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን መፀነሷን ነው፡፡ ይህንኑም ራእይ ያዩት ሐምሌ 30 ዕለት ነው፡፡ እነርሱም እንዲህ ያለ ራእይ ካየን ነገር ካገኘን ብለው ዕለቱን በሩካቤ ሥጋ አልተገናኙም ይልቁንም ፈቃደ እግዚአብሔር ቢሆን ብለው አዳምንና ሔዋንን ‹‹‹ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉአት› ብሎ ያበሰረ አምላክ ለእኛስ ይልክልን የለምን!›› ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ ሰባት ቀን ድረስ ለየብቻቸው ሰነበቱ፡፡ ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን ‹‹ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላችሁና ዛሬ በሩካቤ ሥጋ ተገናኙ ብሎሏችኋል ጌታ›› ብሎ መልአኩ ለሐና ነገራት፡፡ በፈቃደ እግዚአብሔር በብሥራተ መልአክ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም ተፀነሰች፡፡
ክብርት እመቤታችን በተፀነሰች ጊዜ ብዙ ተአምራት ተደርጓል፡፡ የሃናን ማሕፀን እየዳሰሱ፡- ብዙ እውራን አይተዋል፣ ድውያን ተፈውሰዋል፣ ምውታን ተነሥተዋል፡፡ ይህንን የተመለከቱ አይሁድ ቅዱስ ኢያቄምን እና ቅድስት ሐናን በድንጋይ ወግረው በእሳት አቃጥለው ሊገድሏቸው በጠላትነት ሲነሡ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ሊባኖስ ወደ ሚባል ተራራ ይዟቸው ወጣ፡፡ በዚያ ሳሉ በግንቦት 1 ቀን ከፀሐይ 7 እጅ የምታበራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደች፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን በመኀልይ በም.4፥8 ላይ እንደተናገረ “ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ነይ…. ከአንበሶች ጉድጓድ ከነብሮችም ተራራ ተመልከች፡፡” እንዳለ ይህ ትንቢት ተፈጸመ በተወለደች በ8ኛው ቀን ስሟን “ማርያም” ብለው አወጡላት ፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእናቷ ማኅፀን እያለች አያሌ ተአምራትን በማድረጓ፥ ለቅዱስ ኢያቄምና ለቅድስት ሐና ከባድ ፈተና ሆኖባቸው ነበር።የበጎ ነገር ሁሉ ጠላት ሰይጣን አይሁድን በምቀኝነት አስነ ሣባቸው። የምቀኝነት ምንጩ ደግሞ ክፉ ልቡና ነው፤ ማር፡፯፥፳፪። የሰው ልጅ መንፈሳዊነቱን ትቶ ፍጹም ሥጋዊ ሲሆን ምቀኝነት ይሰለጥንበታል። ገላ፡፭፥፳፩። ፈቃደ ሥጋው ገዝቶት በክፋትና ነት የሚኖር ሰው ደግሞ ለማንም ፍቅር ሊኖረው አይችልም። ገላ፡፫፥፫። ሰይጣን አዳምን እና ሔዋንን ያሳሳተው በምቀኝነት ነው። ዘፍ፡፫፥፩። ቃየል አቤልን የገደለው በምቀኝነት ነው። ዘፍ ፬፥፰። ዔሳው ወንድሙን ያዕቆብን ለመግደል የዛተው በምቀኝነት ነው። ዘፍ፡፳ ፯፥፵፩። የያዕቆብ ልጆች ወንድማቸውን ዮሴፍን፡- “እንግደለውና በአንድ ጉድጓድ ውስጥ እንጣለው፤” ያሉት፥ በኋላም በሮቤል በጎ ምክር አሳባቸውን ለውጠው ለእስማኤላውያን ነጋዴዎች የሸጡት በምቀኝነት ነው። ዘፍ፡፴፯፥፳፣፳፰። ሄሮድስ፡- ሕፃኑን ኢየሱስ ክርስቶስን ያሳደደው፥ በዚህም ምክንያት አሥራ አራት እልፍ ሕፃናትን ያሳረደው በምቀኝነት ነው። ማቴ፡፪፥፲፮። አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስን እጆቹን እና እግሮቹን በቅንዋተ መስቀል ቸንክረው የገደሉት በምቀኝነት ነው። ማር፡፲፭፥፳፬።
ምቀኝነት የባህርያቸው እስከሚያስመስልባቸው የደረሱ አይሁድ፥ በማኅፀነ ሐና ባለች ፅንስ ምክንያት የሚደረጉት ልዩ ልዩ ተአምራት አላስደሰታቸውም። ተሰብስበውም፡- “ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? ሐና ፀንሳ ሳለች በማኅፀንዋ ታድናለችና፥ የእስራኤልን መንግሥት አጥፍታ በእኛ ላይ ልትነግሥ አይደለምን?” ተባባሉ።
ይኸውም፡- “ከአሁን ቀደም ከእነዚህ ወገን የሆኑት ዳዊት ሰሎሞን፥ አርባ፣ አርባ ዓመት ገዝተውን ነበር፥ ከእነዚህ የሚወለደው ደግሞ ምን ያደርገን ይሆን?” ብለው ነው። ሀገር ያወቀውን፥ ፀሐይ የሞቀውን ምቀኝነታቸውን በሃይማኖት ለመሸፈን፡- “በሙሴ ሕግ መሠረት በድንጋይ ቀጥቅጠን እንግደላቸው፤” ብለው በሌሉበት ሞት ፈረዱባቸው። ይህ የሙሴ ሕግ የሚጠቀሰው ለአመንዝሮች እንጂ፥ ትዳራቸውን አክብረው፥ ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀው፥ በጾም በጸሎት ተወስነው በቅድስና ለሚኖሩ፥ ለቅዱስ ኢያቄምና ለቅድስት ሐና አልነበረም። ዘሌ፡፳፥፲፣ዘዳ፡፳፪፥፳፬።
መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜ፥ የመፀነሷን ነገር አስቀድሞ በሕልም ነግሮአቸው የነበረ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፥ እያዩት ከሰማይ ወርዶ፥ “በዘመድ የከበራችሁ ኢያቄምና ሐና ሆይ፥ ተነሡ፤” አላቸውና ወደ ሊባኖስ ተራራ ወሰዳቸው።
ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ኢያቄምን እና ቅድስት ሐናን ወደ ሊባኖስ ተራራ የወሰዳቸው ያለ ምክንያት አይደለም። “ወዳጄ ሆይ፥ ሁለንተናሽ ውብ ነው፤ (ጥንተ አብሶ የተባለ የአዳም ኃጢአት ያላረፈብሽ ንጽሕተ ንጹሐን ነሽ፤) ነውር የለብሽም። (የአዳም ኃጢአት የለብሽም)።
እኅቴ ሙሽራ ሆይ፥ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤” ተብሎ ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም የተነገረው ቃለ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው። መኃ፡፬፥፯። ሊባኖስ፡- ከገሊላ በስተ ሰሜን እና ከፊንቄ በስተ ምሥራቅ የሚገኝ ተራራማ ሀገር ነው። ዘዳ፡፩፥፯። በዝግባ ዛፍ የተሞላ ተራራ ነው፥ ንጉሡ ሰሎሞን ለቤተ መቅደሱ ሥራ ያስፈለገውን የዝግባ እንጨት ያስመጣው ከዚያ ነበር። ፩ኛ፡ነገ፡፬፥፴፫፤ ፭፥፮። ምሳሌነቱ ጥሩ ነው፥ ከሊባኖስ የተገኘ ዝግባ ለአግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆነ ሁሉ፥ በሊባኖስ የተወለደች ድንግል ማርያምም ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሆና ተገኝታለች። አንድም የሊባኖስ ዝግባ ለቅዱሳን ምሳሌ ነው፤ የዚያ ፍሬው እንዲበዛለት፥ እነርሱ ደግሞ ጸጋና ክብር ይበዛላቸዋል። መዝ፡፺፩፥፲፪።
ቅድስት ሐና የፅንስዋ ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ ግንቦት አንድ ቀን፥ ከፀሐይ ይልቅ የምታበራ ሴት ልጅ ወለደች። ቅዱስ ኢያቄምም እመቤታችንን ስለሰጠው እግዚአብሔርን ካመሰገነ በኃላ በልቡናው ደስ ብሎት መሥዋዕት አቅርቧል፡፡ እመቤታችንንም ጡት ካስጣሏት በኃላ ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና ተሸክመው ወደ ቤተ መቅደስ ወስደው አስገቧት፡፡ ጻድቁ ኢያቄምም ጥቂት ዘመን ኑሮ በዚኽች ዕለት በሰላም ዐረፎ ወደሚወደው እግዚአብሔር ሔደ፡፡
የአባታችን የቅዱስ ኢያቄም ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!
No comments:
Post a Comment