አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሰኔ ሃያ ሦስት በዚች ቀን በእስራኤል ሁሉ ላይ የነገሠ የዳዊት ልጅ የጠቢቡ ሰሎሞን የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ በክብር ባለቤት ክርስቶስ የታመነ አባ ኖቭ አረፈ።
ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን (ንጉሠ እሥራኤል)
ሰኔ ሃያ ሦስት በዚህች ቀን በእስራኤል ሁሉ ላይ የነገሠ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።
የዚህ የሰሎሞንም የእናቱ ስም ቤርሳቤህ ነው ዳዊትም ሕግ ተላልፎ ከእሷ ጋራ ስለ መበደሉ ባሏንም ስለ ማስገደሉ ጌታ በገሠጸው ጊዜ ንስሓ ገብቶ መሪር ልቅሶን አለቀሰ ጌታም ንጹሕ ስለሆነ ንስሓው ይቅር አለው። ከዚህም በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ እርሷን አገባትና ሰሎሞንን ወለደችው ንጉሥ ዳዊትም ከእርሱ በኋላ ልጅዋ ሰሎሞን እንዲነግሥና በዙፋኑ ላይ እንዲቀመጥ ቃል ገባላት።
እንዲህም ሆነ ሰሎሞን ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ አዶንያስ እነግሣለሁ ብሎ ተነሣ ምክሩም ሁሉ ከሶርህያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ አብያታር ጋር ሆነ። እነርሱም አዶንያስን ተከትለው ረዱት። አዶንያስም በሮጌል ምድር ምንጭ አጠገብ ባለ በኤልቲ ዘዘኤልቲ ላይ ፍየሎችን በጎችንና ላሞችን አርዶ የንጉሥ አሽከሮች የሆኑ የይሁዳ አርበኞችን ሁሉና የንጉሡን ልጆች ወንድሞቹን ሁሉ ጠራ።
ከዚህም በኋላ አዶንያስ ይህን እንዳደረገ ለቤርሳቤህ በነገሩዋት ጊዜ ወደ ንጉሥ አዳራሽ ውስጥ ገብታ ለንጉሡ ሰገደች ንጉሥ ዳዊትም ምን ሆንሽ አላት። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል በዙፋኔም ላይ ይቀመጣል ብለህ ለእኔ ለባርያህ በፈጣሪህ በእግዚአብሔር ስም አንተ ማልክልኝ እነሆ ዛሬ አዶንያስ ነገሠ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ አንተ ግን አላወቅህም አለችው።
ከንጉሥም ጋራ ገና ስትነጋገር ነቢዩ ናታን መጣ ለንጉሡም ናታን መጣ ብለው ነገሩት። ወደ ንጉሡም ገባ በምድር ላይም በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደ። ነቢዩ ናታንም ከእኔ ቀጥሎ አዶንያስ ይንገሥ በዙፋኔም ላይ ይቀመጥ ያልክ አንተ ነህን ዛሬ ወርዶ በጎችንና ብዙ ፍየሎችን አርዶ የሠራዊቱ አለቆችንና የንጉሥ አሽክሮችን ሁሉ ካህኑ አብያታርንም ጠርቷልና በፊቱም ይበላሉ ይጠጣሉ አንዶንያስ ሽህ ዓመት ያንግሥህ ይሉታል አለው።
ዳዊትም መልሶ ቤርሳቤህን ጥርዋት አለና ጠሩዋት ገብታም በንጉሡ ፊት ቆመች። በእግዚአብሔር ፊት እንደማልኩልሽ አሁንም በዚች ቀን እንደዚሁ እንዳደርግ ሰውነቴን ከመከራዬ ሁሉ ያዳናት የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሕያው ነው ብሎ ማለ። ቤርሳቤህም አንገቷን ደፍታ በግምባርዋ በመሬት ወድቃ ለንጉሡ ሰገደች ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘላለም ኑር አለች።
ንጉሥ ዳዊትም የዮዳሄ ልጅ ብንያስንና ካህኑ ሳዶቅን ነቢዩ ናታንንም ግራዝማቹንና ቀኝ አዝማቹን ጥሩልኝ አለ። ንጉሡም ከእናንተ ጋራ የጌታችሁ አሽከሮችን ይዛችሁ ልጄ ሰሎሞንን በበቅሎዬ ላይ አስቀምጣችሁ ወደ ግዮን አውርዱት። በዚያም ነቢዩ ናታንና ካህኑ ሳዶቅ ቀብታችሁ በእስራኤል ላይ አንግሡት አላቸው።
ቀንደ መለከት ንፉ ሰሎሞን ሺህ ዓመት ያንግሥህ በሉ። ተከትላችሁትም ውጡ ገብቶም በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ እርሱም ስለ እኔ ፈንታ ይንገሥ በሁለቱ ነገድና በዐሥሩ ነገድ ይነግሥ ዘንድ እኔ አዝዣለሁ። ካህኑ ሳዶቅም ከድንኳኑ ቀርነ ቅብዑን ወስዶ ሰሎሞንን ቀባው ቀንደ መለከትንም ነፉ ሕዝቡም ሁሉ ሰሎሞን ሺህ ዓመት ያንግሥህ አሉ ሕዝቡም ሁሉ ተከትለውት ወጡ ከበሮም መቱ ታላቅ ደስታም አደረጉ ከድምፃቸውም የተነሣ ምድሪቱ ተናወጸች።
ሰሎሞንም በመንግሥት ዙፋን ተቀመጠ። የንጉሡም አሽከሮች ጌታቸው ንጉሡ ዳዊትን ሊአመሰግኑ ገቡ። እግዚአብሔር የሰሎሞንን ስም ከስምህ ይልቅ መልካም ያድርገው ዙፋኑንም ከዙፋንህ ይልቅ የበለጠ ያድርገው አሉት። ንጉሡም በዐልጋው ሆኖ ሰገደ። እንዲህም አለ ዐይኖቼ ሲያዩ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጥ ልጅን ለኔ ለባርያው ዛሬ የሰጠ የእስራኤል ፈጣሪ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን አለ። ዳዊትም የሚሞትበት ወራት በደረሰ ጊዜ ልጁ ሰሎሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው። እኔ ሰው ሁሉ በሚሔድበት በሞት ጐዳና እሔዳለሁ አንተ ግን ጽና ብልህ ሰውም ሁን።
በሕጉ ጸንተህ ትኖር ዘንድ የፈጣሪህ የእግዚአብሔርን ትእዛዙን ጠብቅ እኔ እንዳዘዝሁህ እንዴት እንደምታደርግ ታውቅ ዘንድ በሙሴ ሕግ የተጻፈውን ትእዛዙንና ሕጉን ፍርዱንም ጠብቅ ልጆችህ ሕጌን ቢጠብቁ በፊቴም በፍጹም ልቡናቸው በፍጹም ሰውነታቸው በዕውነት ጸንተው ቢኖሩ ከእስራኤል ዙፋን ላይ ሰው አይጠፋብህም ብሎ እግዚአብሔር ለእኔ የነገረኝ ቃሉን ያጸና ዘንድ ጠብቅ ብሎ አዘዘው።
ዳግመኛም በኢዮአብና በሳሚ ወልደ ጌራ ላይ በቀል እንዲአደርግ አዘዘው እነርሱ እጅግ የከፉና ብዙ ክፋት የሠሩ ነበሩና። ከዳዊት ዕረፍትም በኋላ ሰሎሞን በዚያ መሥዋዕትን ይሠዋ ዘንድ ተነሥቶ ወደ ገባዖን ሔደ ገባዖን ፈጽማ ትሰፋ ነበርና ሰሎሞንም በገባዖን በዚያው መሠዊያ ውስጥ ሽህ መሥዋዕትን ሠዋ። እግዚአብሔርም ለሰሎሞን በሌሊት በሕልም ተገለጠለት ለአንተ እሰጥህ ዘንድ ልብህ ያሰበውን ልመናን ለምን አለው።
ሰሎሞንም በቅንነትና በእውነት በንጹሕ ልቡናም ከአንተ ጋራ በፊትህ ጸንቶ እንደኖረ ከአባቴ ከዳዊት ጋራ ታላቅ ቸርነትን አድርገሃል በዚችም ቀን ልጁን በዙፋኑ ላይ ታስቀምጠው ዘንድ ይህን ታላቁን ቸርነት አጽንተህለታል አለው። አሁንም አቤቱ አንተ ፈጣሪዬ ስለ አባቴ ስለ ዳዊት ፈንታ እኔን ባሪያህን አነገሥኸኝ እኔም መግቢያዬንና መውጫዬን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝ።
እኔ ባሪያህ ግን የማይቈጠር ብዙ ሕዝብ በሆነ በመረጥከው ወገንህ መካከል አለሁ። ለዚህ ለብዙ ወገንህ መፍረድ የሚችል የለምና ሰምቶ ለወገኖችህ በእውነት ፍርድን ይፈርድ ዘንድ ከክፉ ነገርም ለይቶ በጎውን ነገር ያውቅ ዘንድ ለባሪያህ ዕውቀትን ስጠው። ሰሎሞን ይህንን ነገር ለምኖታልና ይህ ነገር እግዚአብሔርን በፊቱ ደስ አሰኘው። እግዚአብሔርም ይህንን ነገር ከእኔ ለምነሃልና ለአንተም ብዙ ዘመንንና ባለጸግነትን አልለመንህምና ጠላቶችህንም አጥፋልኝ ብለህ አልለመንህምና ነገር ግን ፍርድ መስማትን ታውቅ ዘንድ ለምነሃልና እነሆ እንዳልህ አደረግሁልህ።
እነሆ ከአንተ አስቀድሞ እንዳልነበረ ከአንተም በኋላ እንዳንተ ያለ እንዳይነሣ አድርጌ ብልህና አስተዋይ ልቡናን ሰጠሁህ። ሰው በመንግሥቱ እንዳንተ እንዳልሆነ አድርጌ ያልለመንኸኝን ባለጠግነትንና ክብርንም በዘመንህ ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው።
ሰሎሞንም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ እውነተኛ ሕልም እንደ ሆነ ዐወቀ ተነሥቶም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደ በጽዮንም በእግዚአብሔር ታቦተ ሕግ አንጻር ባለ በመሠዊያው ፊት ቆሞ የሰላም መሥዋዕትን አቀረበ ለሰዎቹና ለሱም ታላቅ ግብዣ አደረገ።
በዚያን ጊዜም ሁለት አመንዝራ ሴቶች ወደ ንጉሡ መጥተው በፊቱ ቆሙ አንዲቱም ሴት ጌታዬ ስማኝ እኔና ይህች ሴት በአንድ ቤት እንኖራለን በአንድ ቦታም ወለድን እኔ በወለድሁ በሦስተኛው ቀን ይህች ሴት ወለደች በአንድነትም እንኖራለን በዚያም ቤት ከሁለታችን በቀር ከኛ ጋራ ማንም አልነበረም። በላዩ ላይ ተጭናዋለችና የዚያች ሴት ልጅ በሌሊት ሞተ።
በሌሊት እኩሌታም ተነሥታ ተኝቼ ሳለሁ ልጄን ከአጠገቤ ወስዳ በብብቷ አስተኛችው። የሞተውን ልጅዋንም በአጠገቤ አስተኛችው። ልጄን አጠባ ዘንድ በጧት በነቃሁ ጊዜም ያንን የሞተ ልጅ አገኘሁ በነጋም ጊዜ አየሁት እነሆ የወለድሁት ልጄ አይደለም አለች።
ያቺ ሁለተኛዋ ሴትም አይደለም ይህ ደኅነኛው የኔ ልጅ ነው እንጂ ያንቺ ልጅ አይደለም ያንቺስ የሞተው ነው አለች። በንጉሡም ፊት እንዲህ ተባባሉ።
ንጉሡም ሰይፍን አምጡ ደኅነኛውንም ልጅ ከሁለት ቆርጣችሁ እኵሌታውን ለዚች እኵሌታውን ለዚያች ስጡ አለ። ስለ ልጅዋ ማሕፀኗ ታውኳልና ልጅዋ ደኅና የሆነ ያቺ ሴት መልሳ ንጉሡን ጌታዬ አይደለም መግደልስ አትግደሉት ደኅነኛውን ልጅ ለሷ ስጧት አለችው ያቺ ሴት ግን አካፍሉን እንጂ ለእኔም ለእሷም አይሁን አለች።
ንጉሡም መግደልስ አትግደሉት እሱን ለእሷ ስጧት ላለችው ለዚች ሴት ደኅነኛውን ሕፃን ስጧት እርስዋ እናቱ ናትና አለ። እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ የፈረደውን ይህን ፍርድ ሰምተው ቅን ፍርድን ይፈርድ ዘንድ የእግዚአብሔር ጥበቡ በሱ ላይ እንዳለ አይተዋልና በንጉሡ ፊት ፈሩ።
ከዚህም በኋላ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ከወጡ አራት መቶ ሰማንያ አራት ዘመን በሆነ ጊዜ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሊያንፅ ጀመረ።
በዐሥራ አንደኛውም ዘመነ መንግሥቱ ወሩ ባዕድ በሚባል በስምንተኛው ወር ቤቱንና ሥርዓቱን ሁሉ ፈጸመ በሰባት ዓመትም ውስጥ ሠራው የራሱንም ቤት በዐሥራ ሦስት ዓመት ሠርቶ ጨረሰ። ከዚህ በኋላ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤትና የራሱን ቤት በሃያ ዘመን ሠርቶ በጨረሰ ጊዜ የእግዚአብሔርን ታቦተ ሕግ ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ያመጣት ዘንድ ያን ጊዜ የእስራኤልን ሽማግሌዎችና የነገድ አለቆች የአባቶቻቸውንም ቤት አለቆች ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰበሰባቸው።
የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን በሰባተኛው ወር በጥቅምት ተሰበሰቡ። የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ ካህናቱም ታቦትዋንና የምስክሩን ድንኳን በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ያለ ንዋየ ቅድሳቱንም ሁሉ ተሸከሙ። ንጉሡና እስራኤል ሁሉ በታቦትዋ ፊት ሥፍር ቍጥር የሌላቸው በጎችና ላሞችን ይሠዉ ነበር። ካህናቱም ታቦቷን ከኪሩቤል ክንፎች በታች በቤቱ ውስጥ ወዳለው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ቦታዋ አገቧት።
ኪሩቤል በታቦትዋ ቦታ ላይ ክንፋቸውን ጋርደዋልና ኪሩቤልም በስተላይ በኩል በቅድስተ ቅዱሳን ላይ ታቦትዋን ጋርደዋት ነበር። ከቅድስተ ቅዱሳንም ጋራ የተያያዙ ነበሩ። ቅዱሳን ኪሩቤል ከፍ ብለው ከቅድስተ ቅዱሳኑ አንጻር ላይ ሁነው ያያሉ በውጭ ግን አይታይም ነበር። ከግብጽ አገር በወጡ ጊዜ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ጋራ ቃል ኪዳን ከገባባቸው ሙሴም በዚያ በኮሬብ ከአኖራቸው ከሁለቱ ጽላቶች በቀር በታቦቱ ውስጥ ሌላ አልነበረም።
ከዚህ በኋላ ካህናቱ ከቤተ መቅደስ በወጡ ጊዜ ቤተ መቅደሱን ሁሉ ብርሃን መላው። የእግዚአብሔር ብርሃን በማደሪያው ቤተ መቅደስ መልቷልና ከብርሃኑ መገለጥ የተነሣ ካህናቱ ሥራቸውን መሥራትና ከፊቱ መቆም ተሳናቸው።
ያን ጊዜ ሰሎሞን እግዚአብሔር በደመና ውስጥ እኖራለሁ ብሏል። እኔም ለዘላለም የምትኖርበት ማደሪያህ ቤተ መቅደስን በእውነት ሠራሁልህ አለ። ንጉሡም ፊቱን መልሶ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መረቃቸው ወደ እግዚአብሔርም ረዥም ጸሎትን ጸለየ። ሰሎሞንም ይህን ሁሉ ልመና ወደ እግዚአብሔር ለምኖ በጨረሰ ጊዜ በጉልበቱ ተንበርክኮ ከሰገደበት እጆቹንም ከዘረጋበት ከመሠዊያው ፊት ተነሣ።
ቆሞም የእስራኤልን ማኅበር እንደተናገረው ሁሉ ለወገኖቹ ለእስራኤል ዕረፍትን የሰጣቸው እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን ብሎ በታላቅ ቃል መረቃቸው። ከዚህ በኋላ ንጉሡና የእስራኤል ልጆች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕትን ሠዉ።
ንጉሡ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ስለ ሰላም መሥዋዕት የሠዋቸው ሃያ ሁለት ሽህ ላሞችና አንድ መቶ ሃያ ሽህ በጎች ናቸው ንጉሡ ሰሎሞንና የእስራኤል ልጆች ሁሉ ያንጊዜ ለእግዚአብሔር ማደሪያ ለቤተ መቅደስ ቅዳሴ ቤት አደረጉ።
ቀድሞ በገባዖን እንደታየው ዳግመኛ እግዚአብሔር ለሰሎሞን ታየው በፊቴ የለመንኸኝ ልመናህንና ጸሎትህን ሰማሁ። እንደ ልመናህም ሁሉ አደረግሁልህ ስሜ በዚያ ለዘላለሙ ጸንቶ ይኖር ዘንድ የሠራኸውንም ቤተ መቅደስ አከበርሁት ልቡናዬም ዐይኖቼም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ጸንተው ይኖራሉ አለው። ሰሎሞንም አርባ ዘመን ነገሠ ከመንገሡም በፊት ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ መላ ዕድሜውም ሃምሳ ሁለት ዓመት ነበር በሰላም አረፈ።
ይህም ጥበብ የተሰጠው ንጉሥ ሰሎሞን ጥቅም ያላቸው ብዙዎች መጻሕፍትን ደርሶአል። እሊህም ትንቢትና ትምህርት ያለባቸው ምሳሌዎችና መኃልዮች ናቸው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ አባ ኖቭ
በዚህችም ቀን ደግሞ በክብር ባለቤት ክርስቶስ የታመነ አባ ኖብ አረፈ። ይህም ቅዱስ መነኰስ በላይኛው ግብጽ ከሚገኙ ገዳማት በአንዱ ገዳም ውስጥ የሚጋደል ጽሙድ ነበር።
ዲዮቅልጥያኖስም ብዙዎች ሰማዕታትን ሊአሠቃይና ደማቸውን ሊያፈስስ በጀመረ ጊዜ በአንዲት ቀን ሰማንያ ሰማዕታትን አቅርቦ ደማቸውን አፈሰሰ። በዚያን ጊዜ አባ ኖብን አስታወሱት የእንዴናው ገዥ ወደሆነው ወደ አርያኖስ አቀረቡት። እርሱም ለአማልክት ዕጠን ሠዋ ይህንንም የምንኵስና ልብስ ከላይህ አውጥተህ ጣል አለው።
አባ ኖብም ይህ ሥራ ከቶ ከእኔ ዘንድ አይደረግም የክብር ባለቤት ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስንም አልተውም የረከሱ ጣዖታትንም አላመልክም አለ። መኰንኑም በየራሱ በሆነ ሥቃይ እጅግ አሠቃየው ያም አባ ኖብ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ኃይል ታግሦ ተቀበለ።
ከዚህም በኋላ ወደ አምስቱ አህጉር ሰደደው በዚያም በጉድጓድ ውስጥ ጣሉት በውስጡም ጌታችን ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስን አጥፍቶ ደግ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስን እስከሾመው ድረስ ሰባት ዓመት ኖረ።
ቈስጠንጢኖስም በነገሠ ጊዜ ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ የታሠሩትን ሁሉ ፈትተው ወደርሱ እንዲአቀርቧቸውና ከእርሳቸው እንዲባረክ ወደ አገሮች ሁሉ ደብዳቤዎችን ላከ። ለመልእክተኞችም እንዲህ አላቸው ሁሉንም ወደ እኔ ማድረስ ካልተቻላችሁ እጆቻቸውን በራሴ ላይ ጭነው ይባርኩኝ ዘንድ ክብር ያላቸውን ታላላቆችንና መምህራኑን አምጡአቸው።
ከእነርሱም ውስጥ የታወቁ አህናህ ከተባለ አገር አባ ዘካርያስ ከፍዩም መክሲሞስ ከሀገረ ድኂን አጋብዮስ ከሀገረ በላኦስ አባ ኖብ ናቸው የንጉሥ መልእክተኞችም በየአገሮች ሁሉ እየዞሩ የታሠሩ ቅዱሳንን ከእሥር ያወጡአቸው ነበር እነርሱም ደስ ይላቸው ነበር የተመሰገነ እግዚአብሔርንም ያመሰግኑት ነበር ይዘምሩለትም ነበር።
የንጉሥ መልእክተኛም አባ ኖብን ከአምስቱ አገሮች ፈልጎ የአገሩ አንጻር ወደ ሆነች ወደ ሀገረ በሰላ ወሰደው። በዚያም የብረት ልብስ ለብሶ ተቀምጦ ነበር የንጉሡ መልእከተኛም አገኘውና ከእርሱ ጋራ ወሰደው ወደ እንዴናውም እስከ ደረሱ በመርከብ ተሳፈሩ ክርስቲያኖችም ተሰበሰቡ ከውስጣቸውም አራት ኤጲስቆጶሳት ነበሩ አባ ኖብንም ያለ ውዴታው ቅስና ሾሙትና የቊርባን ቅዳሴን ቀደሰ።
በቅዳሴውም ፍጻሜ ቅድሳት ለቅዱሳን ብሎ ጮኸ ይህም ማለት ንጹሕና ቅዱስ የሆነ ከሥጋው ከደሙ ይቀበል ማለት ነው በዚያን ጊዜም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመሠዊያው ላይ ተቀምጦ ንስሐ የገቡትን ኃጢአታቸውን ይቅር ሲላቸው አየው ሥጋውንና ደሙንም ከአቀበላቸው በኋላ ወደ ንጉሡ ለመሔድ ተዘጋጁ ቍጥራቸውም ሰባ ሁለት ነበር ሠላሳ ሰባት ሠረገላም አዘጋጅተውላቸው እየአንዳንዳቸው በሠረገላው ተቀመጡ።
በአለፉም ጊዜ የደናግል ገዳማት ካሉበት ደረሱ ደናግሉም ወጥተው ተቀበሏቸው ቍጥራቸው ሰባት መቶ ነበር ከእነርሱ ጋራም እስከሚሰበሰቡ በቅዱሳን ፊት ይዘምሩ ነበር።
ወደ ንጉሡ ከተማም በደረሱ ጊዜ ወደ ንጉሡ ከመግባታቸው በፊት በውኃ ያጥቧቸውና አዳዲስ ልብሶችን ያለብሷቸው ጀመሩ እንዲሁም ለሁሉ አደረጉ ቅዱስ አባ ኖብ ግን አልታጠበም ልብሱንም አልለወጠም ።
ወደ ንጉሡም በገቡ ጊዜ ከእነርሱ ቡራኬ ተቀበለ ቁስላቸውንም ሳመ እጅግም አከበራቸው ብዙ ገንዘብም ሰጣቸው እነርሱ ግን ለቤተ ክርስቲያን ከሚሆን ንዋየ ቅድሳት በቀር ምንም ምን አልተቀበሉም ከዚህም በኋላ ሰላምታ ሰጥቶ ወደየሀገራቸው በሰላም አሰናበታቸው። አባ ኖብም ወደ ቦታው ተመልሶ አረፈና ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔደ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ
No comments:
Post a Comment