አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ግንቦት ሃያ ዘጠኝ በዚህችም ዕለት ከአንጾኪያ ገዳም አባ ስምዖን አረፈ፣ ቅዱሳን የሆኑት የአቡነ አፍጼ እና የአቡነ ጉባ መታሰቢያቸው ነው፣የአቡነ መዝራዕተ ክርስቶስ ዕረፍቱ ነው፡፡
አባ ስምዖን
ግንቦት ሃያ ዘጠኝ በዚህችም ዕለት ከአንጾኪያ ገዳም አባ ስምዖን አረፈ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ዮሐንስ የእናቱ ስም ማርታ ነው ስለ ርሱም ድንቆች ተአምራት ሆኑ። ይኸውም እናቱ ገና ሳትፀንሰው መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ እርሷ መጥቶ የዚህን የቅዱስ ስምዖንን መወለድ ነገራት ከእርሱም የሚሆነውን ገለጠላት።
ተወልዶም ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜ በአንጾኪያ ወደአለ ገዳም ሔደ። ራሱንም ወደ ምንኵስና ቀንበር ውስጥ አስገብቶ ታላቅ ገድልን ተጋደለ። መላእክትም አባ ጳኵሚስን እንደ አስተማሩት በየሌሊቱ ሁሉ እየተገለጡለት የምንኵስናን ገድል አስተማሩት።
የማይጠፋ የምንኵስናንም የገድል አሠራር ገለጡለት። እርሱም አጽንቶ ሥጋ ከለበሱ ሁሉ አብዝቶ ተጋደለ መላእክትም ሁልጊዜ መንፈሳዊ ምግብ ያመጡለት ነበረና። ብዙ ከመጋደሉ የተነሣ ከደንጊያ ምሰሶ ላይ ወጥቶ በላይዋ ሰባት ዓመት ቆመ። ከዚህም ወደሌላ ተራራ ሒዶ በሠራው የደንጊያ በዓት ውስጥ እስከ ሃያ ዓመት ፍጻሜ ከእርሷ ሳይወጣ ሃያ ዓመት ኖረ።
ከዚህ በኋላም ደግሞ ከታላቅ ተራራ ራስ ላይ ወጥቶ በላዩ አርባ አምስት ዓመት ኖረ። መላው ዕድሜውም ሰማንያ ስምንት ዓመታት ነው። ይኸውም በአባቱ ቤት ሰባት በአንጾኪያ ገዳም ዘጠኝ ዓመት በምሰሶ ላይ ሰባት ዓመት በደንጊያ ውስጥ ሃያ ዓመት ደግሞ በተራራ ላይ ቁሞ የኖረበት አርባ አምስት ዓመት በጠቅላላ ሰማንያ ስምንት ነው።
ተአምራቱን ግን መቁጠር የሚችል የለም ከእርሳቸውም በገድሉ ተጽፎ አለ። ብዙ የሆኑ ድርሳናትንና ተግሣጽን ደረሰ እነርሱም ለሁሉ የሚጠቅሙ ናቸው። ይልቁንም ለመነኰሳት ከቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትም ብዙዎቹን ተረጐመ። ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አቡነ አፍጼ ወአቡነ ጉባ
አቡነ ጉባ
በዚችም ዕለት ከተሰዓቱ ቅዱሳን የሆኑት የአቡነ አፍጼ እና የአቡነ ጉባ መታሰቢያቸው ነው፡፡ ከተሰዓቱ ቅዱሳን ውስጥ አራቱ በምድር ላይ ሞትን ሳያዩ የተሰወሩ ናቸው፡፡ እነዚህም አቡነ አረጋዊ፣ አቡነ ገሪማ፣ አቡነ ሊቃኖስና አቡነ አፍጼ ሲሆኑ ሁሉም ስውራን ወደፊት በሐሣዌው መሢሕ ዘመን ወደ ምድር ወርደው ከእነ ሄኖክና ኤልያስ ጋር መጥተው ሰማዕት የሚሆኑ ናቸው፡፡
ተሰዓቱ ቅዱሳን ከአብርሃ ወአጽብሐ 6ኛ ንጉሥ በሚሆን በአልሜዳ ዘመነ መንግሥት ከአውሮፓና ከእስያ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው አክሱም ከተማ ካረፉ በኋላ ሀገረ ስብከታቸውን ተከፋፍለው ገዳም እየገደሙ፣ በዓት እያበጁ፣ ከሣቴ ብርሃን አባ ሰላማ የመሠረተውን የክርስትና ሃይማኖት በከፍተኛ ሁኔታ አስፋፍተዋል፡፡ ገዳማትን በከፍተኛ ሁኔታ አስፋፍተዋል፤ የምንኩስና ሕይወትን በሀገራችን በማስፋፋት ሕይወት ዘርተውበታል፤ መጻሕፍትን ወደ ግእዝ ቋንቋ ተርጉመዋል፤ የወንጌልን ብርሃን በሀገራችን ላይ አብርተዋል፤ ድውያንን እየፈወሱ ሙታንን እያስነሡ በተአምራታቸው ቁስለ ሥጋን በትምህርታቸው ቁስለ ነፍስን ፈውሰዋል፡፡
የሮም ነገሥታት ወገን የሆነው አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል) ከነገሥታት ወገን የምትሆን ሚስት አጋብተው ሊያነግሡት ሲያስቡ እርሱ ግን ዓለምን ፍጹም በመናቅ ወደ ታላቁ አባት አባ ጳኩሚስ ገዳም ገብቶ መነኮሰ፡፡ የንጉሡን ልጅ የአቡነ አረጋዊን በሕፃንነቱ ምንኩስና መቀበሉን የሰሙ 8 ደጋግ ሌሎች የነገሥታት ልጆችም ከያሉበት ተሰባስበው አባ ጳኩሚስ ገዳም ገብተው ከአባ ዘሚካኤል ጋር ተገናኙ፡፡ አባ ጳኩሚስን ‹‹እኛንም እንደዚህ ሕፃን አመንኩሰን›› አሉትና አመንኩሶ ባረካቸው፡፡ የሃይማኖትን ምሥጢር ሁሉ ከአባ ጳኩሚስ ጠንቅቀው እየተማሩ ለብዙ ዓመታት ከእርሱ ጋር ተቀመጡ፡፡ እነዚህም ቅዱሳን የቁስጥንጥንያው አባ ሊቃኖስ፣ የሀገረ ቁስያው (ኢጣሊያ) አባ ይምአታ፣ የአንጾኪያው (ሶሪያ) አባ ጽሕማ፣ የቂልቅያው (ግሪክ) አባ ጉባ፣ የእስያው አባ አፍጼ፣ የሮምያው ጰንጠሌዎን፣ የቂሣርያው አባ አሌፍ ሲሆኑ ሁሉም የነገሥታት ልጆች ናቸው፡፡
ከዚህም በኋላ እነዚህ ቅዱሳን ወደ ትውልድ ሀገራቸው ሮም ተመልሰው ሮምን ወደ ቀናች ሃይማኖት መለሷት፡፡ በዚያም ሳሉ በምድረ አዜብ ብሔረ ኢትዮጵያ ስለሚኖሩ ሰዎች ዝና ስለ ነገሥታቶቻቸውም ቅድስናና ሀገሪቱም የእመቤታችን ዓሥራት መሆኗን ከመጻሕፍት ተረዱ፡፡ አባ ዘሚካኤልም ከሁለቱ ደቀ መዛሙርቶቹ ጋር በሌሊት ወጥቶ ወደ ኢትዮጵያ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እየመራው መጥቶ አክሱም ደረሰ፡፡ በዚያም ጥቂት ጊዜ በመቀመጥ ተመልሶ ወደ ሮምያ ሄዶ ስለ ኢትዮጵያ ያየውንና የሰማውን በሙሉ ሁሉ ለሌሎቹ ቅዱሳን ሲነግራቸው እነርሱም ‹‹ይህችን የተቀደሰች ምድርማ ሄደን ማየት አለብን›› ተባበብለው ያላቸውን ሁሉ ይዘው ታቦቶቻቸውን፣ ካህናቶቻቸውን፣ ንዋየ ቅድሳቶቻቸውን፣ መጻሕፍቶቻቸውን ሁሉ ይዘው በዘሚካኤል መሪነት በመምጣት በ460 ዓ.ም ጳጳሱና ንጉሡ ካሉበት አክሱም ከተማ ገቡ፡፡ እነዚህ ቅዱሳን የነገሥታት ወገን ስለሆኑ በሮም ነግሦ የሚገኘውን ወንድማቸውን ይስሐቅን ላኩበት፡፡ ንጉሡ ይስሐቅ ለአባ ዘሚካኤል የእኅት ልጅ ነው፡፡ እርሱም መልእክቱ እንደደረሰው 7 ዓመት በሮም ከነገሠ በኋላ መንግሥቱን ትቶ በሌሊት ተነሥቶ በመውጣት ወደ ሀገራችን በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል መሪነት መጣና ከወንድሞቹ ጋር ተቀላቀለ፡፡ እነርሱም አመነኮሱትና ስሙን ገሪማ አሉት፡፡
ተሰዓቱ ቅዱሳን ቅዱሳን በአንዲት የጸሎት ቤት በምንም ሳይለያዩ በአንድነት እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆነው ለጸሎት ቆመው ውለው ያድሩ ነበር፡፡ የአባ ዘሚካኤልም እናት ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ መጥታ ከሴት መነኮሳት ጋር እነርሱ ባሉበት አካባቢ ትኖር ነበር፡፡ አባ ዘሚካኤልን የበላይ አድርገው ሾሙትና ስሙንም አረጋዊ አሉት፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ድውያንን እየፈወሱና ሙታንን እያስነሱ እጅግ በጣም አስገራሚ የሆኑ ድንቅ ድንቅ ብዙ ተአምራትን ያደርጉ ነበር፡፡ ከሰንበት በቀር እህል የሚባል ነገር የማይቀምሱት እነዚህ ቅዱሳን ኢትዮጵያን በኪደተ እግራቸው ባርከዋታል፣ ጌጦቿ ሆነውላታል፣ በትምህርታቸው የእምነቷን መሠረት አጽንተውታል፣ የልዕልናዋንም ታሪክ ለዓለም መስክረውላታል፡፡
ቅዱሳኑ ለ12 ዓመታት በፍጹም አንድነት አብረው ከተቀመጡ በኋላ ‹‹እርስ በራሳችን እየተያየን ብንኖር ተድላ ደስታ ይሆንብናልና ተለያይተን እንቀመጥ›› ብለው ተማከረው በተለያየ በዓት በተጋድሎ መኖር ጀመሩ፡፡ አባ ሊቃኖስ በደብረ ቁናጽል፣ አባ ጰንጠሌዎንም በእርሱ ትይዩ በሆነ ቦታ፣ አባ ገሪማ በደብረ መደራ፣ አባ ጽሕማ በደብረ ጸድያ፣ አባ ይምአታ በደብረ ገረዓልታ፣ አባ አፍጼ በደብረ ይሐ፣ አባ አሌፍ በደብረ አኅድአ መኖር ጀመሩ፡፡ አባ አረጋዊ ደግሞ በጣም ርቀው በመሄድ በደብረ ዳሞ በዋሻና በፍርኩታ ውስጥ በተራራም ላይ መኖር ጀመሩ፡፡
ከእነዚህም ቅዱሳን ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለአንዳች ሐዋርያ ስብከት አስቀድማ በክርስቶስ እንዳመነችና በዚህም ምክንያት የልዕልናዋን ታሪክ ለዓለም ለማሳወቅ ፈጥነው የሄዱ አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ምድር በእነዚህ የቅዱሳን ኪደተ እግር ተቀደሰች፣ በውስጧም በመመላለሳቸው አውራጃዎቿና አደባባዮቿ ሁሉ ታደሱ፡፡ መዓዛ ትምህርታቸውና ተአምራቶቻቸው በሁሉም አውራጃዎች ተሠራጨ፣ የእምነቷንም መሠረት አጸኑ፡፡
አቡነ አፍጼ የተወለዱት እስያ ውስጥ በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን ወላጆቻቸው አቡሊዲስና አቅሌስያ ይባላሉ፡፡ ገና በሕጻንነታቸው ብሉይ ከሐዲስ ጠንቅቀው በመማር መንኩሰዋል፡፡ አባ አፍጼ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በአልዐሜዳ ዘመን ከ8ቱ ባልንጀሮቻቸው ጋር ነው፡፡ ጻድቁ ጸበል እያፈለቁ ብዙ ድውያንን ፈውሰዋል፡፡ ትግራይ ውስጥ የሓ የተባለው ቦታም ማረፊያቸው ነበር፡፡ ዛሬም ትልቁ ገዳማው በዚያው ይገኛል፡፡ ጻድቁ ከሠሯቸው በርካታ ሥራዎች ውስጥ ከብዙ በጥቂቱ፡- ከ100 ዓመት በላይ አበ ምኔት ሆነው በኖሩበት ገዳማቸው በፍጹም ትጋት በጾምና በጸሎት አገልግለዋል፡፡ሁለተኛ በመጀመሪያ ያስከተሏቸውን 366 ደቀ መዛሙርት ጨምሮ ብዙ መናንያንን አፍርተው በሃገራችን ገዳማዊ ሕይወትን አስፋፍተዋል፡፡ ሦስተኛ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከሱርስትና ከጽርዕ ቋንቋ ወደ ግእዝ ቋንቋ ተርጉመዋል፡፡ ሌላው ጻድቁ በስብከተ ወንጌል ለሀገራችን ብርሃን አብርተዋል፡፡ ሕዝቡ በጣዕመ ስብከታቸው ይገረም ስለ ነበር ‹‹አፍፄ-አፈ ዐፄ›› ብሏቸዋል፡፡ ይኽም የዐፄ/የንጉሥ አንደበት ያለው›› ወይም ‹‹ንግግር አዋቂ›› ማለት ነው፡፡ አቡነ አፍጼ ከ200 ዓመታት በላይ ቤተ ክርስቲያንን አገልግለው ግንቦት 29 ቀን በ684 ዓ.ም በሞት ፈንታ ተሰውረዋል፡፡
እግዚአብሔርም በስማቸው ለተማጸነ፣ ገዳማቸውን ለተሳለመ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡
አቡነ ጉባ
ሌላኛው በዚህች ዕለት ዕረፍታቸው የሆኑት አቡነ ጉባ ናቸው፡፡ እርሳቸውም የተወለዱት ታህሣሥ 29 ቀን 336 ዓ.ም በመንፈቀ ሌሊት ነው፡፡ አባታቸው ጌርሎስ እናታቸው ቴዎዶክስያ የተባሉ ደጋግ ቅዱሳን ናቸው፡፡ አቡነ ጉባ በተወለዱ ቀን ጌታችን ከመላእክቱ ጋር በመውረዱ ቤታቸው ለ7 ቀናት በብርሃን ተሞልቶ ነበር፡፡ ሕጻኑ ጉባም ፈጣሪያቸውን ሃሌ ሉያ ብለው አመስግነዋል፡፡
ጻድቁ በልጅነታቸው መጻሕፍትን አጥንተው ወደ ገዳመ አስቄጥስ ገብተው መንነዋል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ከተጋደሉ በኋላ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ‹‹ወደ ቅድስት ሃገር ኢትዮጵያ ሂድ" ብሏቸው ከ8ቱ ቅዱሳን ጋር ወደ ሀገራችን መጥተዋል፡፡ አባ ጉባ በስብከተ ወንጌል፣ መጻሕፍትን በመተርጎም፣ ገዳማትን በማስፋፋትና አብያተ ክርስቲያናትን በማነጽ ብዙ ደክመዋል፡፡ በተለይም ራማ ኪዳነ ምሕረት እርሳቸው ከመሠረቷት ገዳማት ውስጥ በይበልጥ የምትታወቀው ናት፡፡ ጻድቁ ቅዳሴ ሲቀድሱ ከመሬት ከፍ ብለው ይታዩ ነበር፡፡ ብዙ ጸበሎችን አፍልቀው ድውያንን ፈውሰዋል፡፡ ሙታንንም አንሥተዋል፡፡ እመቤታችን ተገልጣላቸው የብርሃን መስቀል ሰጥታቸዋለች፡፡ ጻድቁ ከብዙ ተጋድሎ በኋላ በሰላም ዐርፈው ማይጨው በሚገኘው ትልቁ ገዳማቸው ተቀብረዋል፡፡ መቃብራቸው ካለበት ዓለት ሥር እጅግ ፈዋሽ ጠበል ፈልቋል፡፡ በተለይም ለዐይን እና ለአእምሮ ሕመም ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አቡነ መዝራዕተ ክርስቶስ
በዚህች ዕለት የአቡነ መዝራዕተ ክርስቶስ ዕረፍቱ ነው፡፡ አባቱ ለባሴ ክርስቶስ የዐፄ ፋሲል የቅርብ ወዳጅ የነበረ የጦር አዛዥ ደጃዝማች ሲሆን እናቱ ሚላንያ ትባላለች፡፡ ጻድቁ ታኅሣሥ 29 ቀን በጎንደር ተወለዱ፡፡ ወቅቱ ዐፄ ሱስንዮስ የረከሰች የሮም ካቶሊክ እምነትን ተቀብሎ የሀገራችንን ክርስቲያኖች በሰማዕትነት የሚገድልበት ዘመን ስለነበር እናቱ ይዛው ፎገራ ወረዳ ቆራጣ ወለተ ጴጥሮስ ገዳም ገባች፡፡ በዚያም ሕፃን ልጇን ክርትስትና የሚያነሳላት ካህን አጥታ ስታለቅስ ደገኛው አባት አባ ስነ ክርስቶስ በስውር መጥተው አጠመቁትና ስሙን መዝራዕተ ክርስቶስ አሉት፡፡
የመዝራዕተ ክርስቶስ እናት ብዙም ሳትቆይ ስለሞተች በዚያው የምትኖር መነኩሲት የሆነች አያቱ አሳደገችው፡፡ እንደ አገሩም ባሕል ፈረስ ግልቢያና ጦር ውርወራ እየተማረ ከፎገራ ልጆች ጋር አደገ፡፡ አያቱም ወላጅ እናቱ ትመስለው ነበር፡፡ አንድ ቀን አብሮት የሚጫወተው ልጅ ወላጆቹ ሲያወሩ የሰማውን ወስዶ ለመዝራዕተ ክርስቶስ እናቱ እንዳልሆነች ነገረው፡፡ እርሱም በሰማው ነገር ደንግጦ አያቱን ስለእውነቱ ጠየቆ ተረዳ፡፡ ከዚህም በኋላ ደጃዝማች አባቱ ወደ ዐፄ ፋሲል ቤተ መንግሥት ወሰደው፡፡ መዝራዕተ ክርስቶስ መልከ መልካም ስለነበር ንጉሡ ዐፄ ፋሲል በወጣቱ ደም ግባት ደስ ተሰኝቶ ድምጹን አሰምቶ ‹‹ለዚህ ልጅ ሴት ልጄን እድርለታለሁ›› ሲል ለመኳንንቱ ሁሉ ተናገረ፡፡ መዝራዕተ ክርስቶስ ግን በልቡ መንኩሶ ስለመኖር የወሰነው በቤተ መንግሥት ይህንን የሰማ ዕለት ነበር፡፡
ከዚኽም በኋላ መዝራዕተ ክርስቶስ ምን ማድረግ እንዳለበት ሲያስብ ቆይቶ ወደ አንዱ ገዳም ጠፍቶ በመሄድ በምንኩስና ለመኖር ወሰነ፡፡ አንድ ቀን አባቱን ተከትሎ ግምጃ ቤት ማርያም ወደምትባለው ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ሳለ አጣኙን አባት ባሕታዊ አባ ቴዎድሮስን ‹‹አባቴ ከዛሬ ጀምሮ በምንኩስና ለመኖር ወስኛለሁና መርቀህ ላከኝ›› አለው፡፡ ባሕታዊውም ‹‹አንተ ገና ልጅ ነህ›› ቢለው የሚቀበለው አልሆንም፡፡ በመጨረሻም መርቆ አሰናበተው፡፡ ወዲያም ጻድቁ በሌሊት ከጎንደር ከተማ ጠፍቶ ወደ ሰሜን አርማጭሆ ቆላ ሄደ፡፡ በዚያም በያዕቆብ ግሙድ ስም በተገደመው ገዳም ገብቶ ከአባ ስነ ክርስቶስ ጋር ተገናኘ፡፡ ያመነኩሰውም ዘንድ ለመነው፡፡ አባ ስነ ክርስቶስ ማንነቱን ከጠየቀው በኋላ ‹‹አንተ ገና ልጅ ስለሆንክ የምንኩስናን ቀንበር መሸከም አይቻልህም›› በማለት ወደ አባቱ እንዲመለስ መከረው፡፡ በሌላም በኩል ከንጉሡና ከመሳፍንቱ ጋር ላለመጣላት ፈርቶ ነበር፡፡ መዝራዕተ ክርስቶስ ግን እያለቀሰ ‹‹የአንተ አምላክ ጽናት ይሆነኛልና አመንኩሰኝ›› በማለት ለመነው፡፡ እርሱም ተግባር ቤት በአርድዕትነት እያገለገለ እንዲቆይ የአመክሮ ጊዜ ሰጠው፡፡
መዝራዕተ ክርስቶስም አባቱ ጭፍሮቹን ልኮ እንደገና ወደ ዓለም እንዳይወስደው ፈርቶ ቶሎ እንዲያመነኩሱት ‹ታመምኩ›› ብሎ ተኛ፡፡ መነኮሳቱም ‹‹ሳይመነኩስ ቢሞት ኩነኔ ይሆንብናል›› ብለው አበምኔቱን ለምነው አመነኮሱት፡፡ ከመነኮሰ በኋላ በሳምንቱ አባቱ ልጁ ያለበትን ገዳም ዐውቆ ታናሽ ወንድሙን ከጭፍሮቹ ጋር በመላክ ለአባ ስነ ክርስቶስ ‹‹ልጄ መዝራዕተ ክርስቶስ አንተ ጋር እንዳለ ሰምቻለሁና ከመመንኮሱ በፊት በአስቸኳይ እንድትልክልኝ›› ብሎ መልእክት ላከበት፡፡ አባ ስነ ክርስቶስም ለመጡት ጭፍሮች መዝራዕተ ክርስቶስ እንደመነኮሰ ነገራቸው፡፡ ጭፍሮቹም ከአባ ጋር ብዙ ስለተጨቃጨቁ መዝራዕተ ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር ለመሄድ ተስማማ፡፡ ከእነርሱም ጋር ሳለ ከጭፍሮቹ አንዱና መሪያቸው የሆነውን ሰውም ‹‹ተሳልሜ ልምጣ፣ ጋቢህን ስጠኝ›› ብሎ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ በምሥራቅ ባለው በር ወጥቶ ጠፍቶ አርማጭሆ ጫካ ውስጥ ገብቶ ጠፋ፡፡ አጎቱና ጭፍሮቹም ፈልገው ቢያጡት ተስፋ ቆርጠው ተመለሱ፡፡ ከዚህም በኋላ አቡነ መዝራዕተ ክርስቶስ ወደ አንገረብ ወንዝ ሄዶ በዚያ ከርኩሳን መናፍት ጋር እየተዋጋ በተጋድሎ በጾም ጸሎት ተወስኖ ኖረ፡፡ ተመልሶ ወደገዳም ቢመጣ አባቱና ዘመዶቹ እንደማያስቀምጡት ስላወቀ አባ ስነ ክርስቶስን አስፈቅዶ ወደላይ አርማጭሆ ደብረ ሙጅና አባ አብሳዲ ገባሬ ተአምር ገዳም ሄደ፡፡ በዚያም 7 ዓመት በተጋድሎ ከኖረ በኋላ ወደ ዋልድባ ገዳም ሄደ፡፡ በዚያም ሥዕለ ማርያምን በጎኑ ታቅፎ ሲያዝን ለብዙ መናንያን የተሰወረችው ደብረሲና የተባለች በዋልድባ የምትገኝ ቅድስት ቦታ ተገለጠችለት፡፡ በደብረ ሲና ተራራ ላይ ወጥቶ 40 ቀንና 40 ሌሊት ሱባኤ ያዘ፡፡ በዋልድ 11 ዓመት እንደተቀመጠ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ‹‹በዚህ ገዳም የምትኖርበት ጊዜ አልቋልና ውጣ›› ብሎ አዘዘው፡፡ ከዚያም ከዋልድባ ወጥቶ ወደ ሰሜን ተራራ ሄዶ ከቅዱስ ያሬድ ገዳም ተባርኮ ወደ ትግራይ ገርዓልታ ሄደ፡፡ ቀጥሎም ወደ ጉንዳጉንዲ ማርያም ገዳም ገብቶ በተጋድሎ መኖር እንደጀመረ አንድ የበቃ ባሕታዊ መጥቶ ‹‹ክፍልህ በዚህ ገዳም አይደልምና ወደ ሌላ ገዳም ሂድ›› አለው፡፡ ወደ መጠራ መቃብረ ጻድቃን ዘንድ ሄዶ ዐጽመ ቅዱሳንን ሲያጥን ‹‹ይህ ገዳም ክፍልህ አይደለም›› የሚል ድምጽ ከሰማይ መጣለት፡፡ ተነሥቶም ወደ ደብረ ቢዘን ሲጓዝ ሌሎች መነኮሳትን አገኘና በመረብ ወንዝ ሸለቆ ውስጥ ብዙ መናንያን እንዳሉ ሲነግሩት በሌላ አቅጣጫ ወደ መረብ ወንዝ አቀና፡፡ በዚያም ሸንፋ በተባለ ቦታ ገዳም መሥርቶ ሲቀመጥ መንፈሰ እግዚአብሔር የጠራቸው 12 መነኮሳት መጥተው አርድእት ሆኑለት፡፡ እነርሱም በወባ በሽታ ታመው ስላረፉ አቡነ መዝራዕተ ክርስቶስ ‹‹ወንድሞቼን አጥቼ በዚህ መኖር ለእኔ አይገባኝም፣ ክፍሌ አይደለም›› ብሎ ወጥቶ ወደ ትግራይ ሄደ፡፡
አድዋ አውራጃ የሐ አቡነ አፍጼ ገዳምን ከተሳለመ በኋላ ገዳሙን ከከበቡት ተራሮች መካከል በአንደኛው ማይ ዱር ወደሚባለው ተራራ ወጥቶ አዲስ ገዳም መሠረተ፡፡ ታቦተ ማርያምን አስገብቶ ሲኖር ከየአቅጣጫው መናንያን መነኮሳት ወደ እርሱ መጡ፡፡ አቡነ መዝራዕተ ክርስቶስም እስከ 93 ዓመቱ ገዳሙን በአበምኔትነት እያስተዳደረ በታላቅ ተጋድሎ ከኖረ በኋላ ግንቦት 29 ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐረፈ፡፡ ‹‹ማይዱር›› በተባለው ገዳሙ ራሱ በሠራት በእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተቀበረ ሲሆን ገዳሙም እስከዛሬ ድረስ ‹‹እንዳ አቡነ መዝራዕተ ክርስቶስ ገዳም›› እየተባለ ይጠራል፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት
No comments:
Post a Comment