ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 22 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, July 28, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 22

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም



ሐምሌ ሃያ ሁለት በዚህች ቀን የሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል ቅዳሴ ቤቱ የሚከበርበትና ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል የዕውቀትን ጽዋ ያጠጣበት ዕለት ነው፣ ኢትዮጵያዊው ሰማዕት ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ በሰማዕትነት አረፉ፣ የመነኰሳት ሁሉ አባት የቅዱስ እንጦንስ የከበረች ቤተክርስቲያኑ የከበረችበት (ቅዳሴ ቤቱ) ነው፣ የፋሲለደስ ልጅ ቅዱስ መቃርስ ሰማዕት ሆነ፣ ቅዱስ ልውንትዮስ በሰማዕትነት ሞተ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል
ሐምሌ ሃያ ሁለት በዚህች ቀን ቅዳሴ ቤቱ የሚከበርበትና ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል የዕውቀትን ጽዋ ያጠጣበት ዕለት ነው፡፡ ኢዮር፣ ራማ እና ኤረር የተባሉ ሦስት የመላእክት ከተሞች አሉ፡፡ እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክት ከፈጠራቸው በኋላ በነገድ 100 በአለቃ 10 አድርጎ በሦስቱ ሰማያት አስፍሯቸዋል፡፡ ኢዮርን በ4፣ ራማን በ3፣ ኤረርንም በ3 ከፍሎ ነው በዓሥሩ ከተማ ያሰፈራቸው፡፡
በዚህም መሠረት ኢዮርን ላይና ታች አድርጎ በ4 ከተማ ከፍሏታል፡፡ በእርሷ ያሉትን መላእክትን በ40 ነገድ 4 አለቃ አድርጎ ከፈላቸው፡፡ የመጀመሪያው ነገድ ‹‹አጋእዝት›› ይባላሉ፡፡ አለቃቸው ሣጥናኤል ነበር፤ እርሱም የመላእክትን ሁሉ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ያሳርግ ነበር፡፡ ከክብሩ ሲዋረድ ቅዱስ ሚካኤል በምትኩ ተሹሞበታል፡፡ ሁለተኛው ነገድ ‹‹ኪሩቤል›› ይባላሉ፡፡ እነርሱም መንበረ ሥላሴን ይሸከማሉ፡፡ የቀሳውስት አምሳል ናቸው፡፡ አለቆቻቸው ገጸ ሰብና ገጸ አንበስ ናቸው፡፡ በሦስተኛው ከተማ በኢዮር ያሉት ሱራፌል ይባላሉ፡፡ የዲያቆናት አምሳል ናቸው፡፡ በትንቢተ ኢሳያስ በምዕራፍ 6 ላይ የተገለጹትና ኢሳያስን ከለምጹ እንዲፈወስ ያደረጉት ናቸው፡፡ አለቆቻቸው ገጸ ላህምና ገጸ ንስር ናቸው፡፡ (በነገራችን ላይ ‹‹ከሩቤል›› ወይም ‹‹ሱራፌል›› የሚባሉ የግለሰብ መጠሪያ ስሞች ስህተት ናቸው፡፡ አንደኛ እነዚህ ስሞች የብዙ መላእክት መጠሪያን የሚወክሉ ናቸው፡፡ ለአንዱ ሲሆን ‹‹ኪሩብ፣ ሱራፊ›› ይባላል፡፡ ‹ኪሩቤል› ወይም ‹ሱራፌል› ማለት ግን የብዙ ቁጥራቸው መጠሪያ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የቅዱሳን መላእክትን ስም እንዳለ በቁሙ ወስዶ ለግል መጠሪያ ስም ማዋል ተገቢ አይደለም፡፡ ‹‹ወለተ ሚካኤ፣ ክብፈ ገብርኤል….›› እየተባሉ ይሰየማሉ እንጂ ቀጥታ ‹ሚካኤል›፣ ‹ገብርኤል› እያሉ ሰዎችን መሰየም ስህተት ነው፡፡ 4ኛው ከተማ በኢዮር ያሉት ኃይላት ይባላሉ፡፡ የእሳት ሰይፍ ይዘው በሥሉስ ቅዱስ ፊት የሚቆሙ ናቸው፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት የዛሉና የደከሙ ክርስቲያኖችን የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ አለቃቸውም ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡)
ዳግመኛም እግዚአብሔር በራማ ያሉትን መላእክት በ30 ነገድ በ3 አለቃ አድርጎ ከፈላቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ‹‹አርባብ›› ይባላሉ፡፡ የሥላሴ እልፍኝ አስከልካዮች ናቸው፡፡ የእግዚአብሔርን መንበር በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፡፡
አለቃቸው ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ ሁለተኞቹ በራማ ከተማ ያሉት ‹‹መናብርት›› ይባላሉ፡፡ ለእግዚአብሔርን እጅግ ቅርብ የሆኑ ናቸው፡፡ የመብረቅ ጋሻቸውን የእሳት ጦራቸውን ይዘው የሥላሴ ጋሻ ጃግሬዎች ሆነው በተጠንቀቅ ይቆማሉ፡፡ የሰውን ችግር ለእግዚአብሔር ያቀርባሉ፡፡ መዝ 88፡6፡፡ አለቃቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሦስተኞቹ በራማ ከተማ ያሉት ‹‹ሥልጣናት›› ይባላሉ፡፡ መላውን ፍጥረት ለመጠበቅ ሥልጣን የተሰጣቸውና የምጽአት ዕለት አዋጅ ነጋሪዎች ናቸው፡፡ ዳን 12፡1፡፡ አለቃቸው ቅዱስ ሱርያል ነው፡፡
ዳግመኛም እግዚአብሔር በኤረር ያሉትን መላእክት በ30 ነገድ በ3 አለቃ አድርጎ ከፈላቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ‹‹መኳንንት›› ይባላሉ፡፡ የስላሴ የእሳት ባለ ቀስት ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ልዩ ጠባቂዎች ናቸው፤ በተለይ በአደጋ ጊዜ ሎጥን እንዳዳኑት ፈጥነው ይደርሳሉ፡፡ በዕለተ ምጽዓት የሰውን ሁሉ ዐፅም ሰብስበው ለትንሣኤ ዘጉባኤ ያበቃሉ፡፡ አለቃቸው ቅዱስ ሰዳካኤል ነው፡፡ ሁለተኛዎቹ ‹‹ሊቃናት›› ይላሉ፡፡ የሥላሴ የእሳት ፈረሶች ናቸው፡፡ በእሳት ፈረስ ይመላለሳሉ፡፡ እነዚህም 24ቱ ካህናተ ሰማይ ሲሆኑ አለቃቸው ቅዱስ ሰላታኤል ነው፡፡ በኤረር ከተማ የሰፈሩት ሦስተኛዎቹ ‹‹መላእክት›› ይባላሉ፡፡ ፍጥረትን ሁሉ የሚጠብቁ ናቸው፡፡ አለቃቸው ቅዱስ አናንኤል ነው፡፡ በእነዚህ የማይጠበቅ ፍጥረት የለም፡፡ ከአዝርእት ጀምሮ ሁሉን ይጠብቃሉ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ 7 መላእክትን አየሁ›› (ራዕ 8፡2) እንዳለ ሊቃነ መላእክት በቁጥር 7 ናቸው፡፡ እነርሱም፡- ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ሩፋኤል፣ ቅዱስ ራጉኤል፣ ቅዱስ ዑራኤል፣ ቅዱስ ፋኑኤል እና ቅዱስ አፍኒን ናቸው፡፡ ‹‹ዑራኤል›› የሚለው ስም ‹ዑር› እና ‹ኤል› ከሚሉ ሁለት ቃላት የተመሠረተ ስም ነው፡፡ ‹‹ዑራኤል›› ማለት ትርጉሙ ‹‹የብርሃን ጌታ፣ የአምላክ ብርሃን›› ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ዑራኤል ከ7ቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን ከፍጥረተ ዓለም ጀምሮ በመብረቅና በነጎድጓድ ላይ የተሾመ መልአክ ነው፡፡ በመሆኑም መጽሐፈ ሄኖክ እንደሚገልጸው መባርቅት ለጥጋብና ለበረከት እንዲበርቁ ነጎድጓድም ለሰላም እንዲሆን ያሰማራል፡፡ ምሥጢረ ሰማይንና ሰማያዊውን ዕውቀት ሁሉ ለሄኖክ የገለጸለት መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ የፀሐይን፣ የጨረቃን፣ የከዋክብትንና የሰማይ ሠራዊትን ብርሃንን የሚመራው ይኸው ገናና መልአክ ነው፡፡ መጽሐፈ ሄኖክ 28፡13፡፡ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ ሆኖ በተሰቀለ ጊዜ ክቡር ደሙን በብርሃን ጽዋ ተቀብሎ በብርሃነ መነሳንስ በዓለም ላይ የረጨው ይኸው ገናና መልአክ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡
ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል ጽዋ ጥበብን አጠጥቶ ሰማያዊውን ምሥጢር የገለጠለት መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ ዕውቀት ተሠውሮበት ለነበረው ለኢትዮጵያዊው ሊቅ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም በእመቤታችን ትእዛዝ ጽዋ ጥበብን አጠጥቶ ሰማያዊውን ምሥጢር የገለጠለት ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ ‹‹ዑራኤል የተባለ መልአክ ሊረዳኝ መጣ፡፡›› መጽሐፈ ዕዝራ 2፡1፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር የሕይወትና የይቅርታ ዝናም በምድራችን ላይ ያዘንብ ዘንድ እንዲሁም የእርሻችንን አዝመራ በዝናም አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ ለምግብነት እንዲበቃ ከፈጣሪ ዘንድ ምሕረትን የሚለምን መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡
ሊቁ አባ ጊዮርጊስም በመልአኩ አማላጂነት እጅግ ብዙ ድርሰቶችን የደረሱት መልአኩ ጽዋ ሕይወትን ካጠጣቸው በኋላ ነው፡፡ በመጀመሪያም አባ ጊዮርጊስ የተወለዱት በቅዱስ ዑራኤል አብሳሪነት ነው፡፡ በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ የተመሠረቱ አብዛኞቹ ቅዱሳት ገዳማት በቅዱስ ዑራኤል መሪነት ነው፡፡ ድርሳኑ ላይ የማይጠቅሳቸው የሀገራችን የከበሩ ቅዱሳት ገዳማትና ቅዱሳን ነገሥታት የሉም፡፡
የብርሃን እናቱ ድንግል ወላዲተ አምላክን ከልጇ ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስትሰደድ መንገድ እየመራ ወደ ግብጽ እና ወደ አገራችንን ኢትዮጵያ ያመጣቸው ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ እመቤታችንን ከተወደደ ልጇ ጋር በደመና ጭኖ መላ ኢትዮጵያን ካስጎበኛት በኋላ ቅድስት አገራችንን ለእመቤታችን የዓሥራት አገር እንድትሆን ያደረገው መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል በዓመት 3 ዓበይት በዓላት አሉት፡፡ ጥር 22 በዓለ ሲመቱ ነው፡፡ መጋቢት 27 የጌታችንን ክቡር የሆነ ወርቀ ደሙን ለዓለም የረጨበት ነው፡፡ ሐምሌ 22 ቀን ቅዳሴ ቤቱ የሚከበርበትና ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል የዕውቀትን ጽዋ ያጠጣበት ዕለት ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ኢትዮጵያዊው ሰማዕት ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ
ዳግመኛም በዚህች ዕለት ኢትዮጵያዊው ሰማዕት ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ በሰማዕትነት አረፉ፡፡ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ ሰማዕት የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ በ1875 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ተወለዱ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ በሰማዕትነት እንደሚሞቱ አስቀድመው መምህራቸው በትንቢት ነግረዋቸው ነበር፡፡ ‹‹አለቃ ተጠምቀ›› የተባሉ ቅድስናን ከሊቅነት ጋራ አስተባብረው የያዙ የቅኔ መምህራቸው አንድ ቀን አቡነ ጴጥሮስን ጠርተው «ኀይለ ማርያም አንተ ወደፊት ጳጳስ ትሆናለህ፤ በወቅቱም አረመኔ በዚህች ሀገር ይሠለጥናል፡፡ ታዲያ ያኔ አንተ ለነፍስህ ሳትሳቀቅ በሰማዕትነት እለፍ፤ ሰማዕትነት ክፍልህ ነው፣ አደራ›› ብለዋቸው ነበር፡፡ ይኸውም ትንቢት ደርሶ አቡነ ጴጥሮስ በሰማዕትነት ለማረፍ በቅተዋል፡፡ ብፁዕ አባታችን የጵጵስና ስማቸውን ከማግኘታቸው በፊት መመህር ኀይለ ማርያም ይባሉ ነበር፡፡ በልጅነታቸው ወላጆቻቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ በሃይማኖትና በምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ አድርገዋቸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓተ ትምህርት ከንባብ እስከ ቅኔ ያሉትን ትምህርቶች በሚያስገርም ፍጥነት ከተማሩ በኋላ ወደ ቅኔው አውድማ ጎጃም በመሄድ በሸዋራ የቅኔ ትምህርታቸውን ፈጽመው መምህር ሆነዋል፡፡ የዜማውንም ትምህርት ወደ ጎንደር ሄደው ተምረዋል፡፡ በመቀጠልም ወሎ ቦሩ ሜዳ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጻሕፍትን ምሥጢር ይመግቡ ወደነበሩት ወደ ሊቁ አካለ ወልድ ዘንድ በመሄድ ዋና ዋናዎቹን የመጻሕፍት ትርጓሜ ማለትም ብሉያትን፣ ሐዲሳትንና ሊቃውንትን በሚገባ አሒዱ፡፡ ከዚህ በኋላ በ1900 ዓ.ም ወሎ አምሐራ ሳይንት ሄደው በምስካበ ቅዱሳን ገዳም ገብተው ወንበር ዘርግተው ለ9 ዓመታት ቅኔንና መጻሕፍትን አስተማሩ፡፡ በ1910 ዓ.ም ወደ ደብረ ሊባኖስ መጥተው ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጸሙ፡፡ ከዚያም መምህርነት ተሹመው ደብረ መንክራት ምሁር ኢየሱስ ገዳም ሄደው ለ6 ዓመታት ካስተማሩ በኋላ በ1916 ዓ.ም እንደገና በዝዋይ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም በመምህርነት ተሹመው ለ3 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በ1919 ዓ.ም ወደ አ.አ በመምጣት የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ መምህርና በቤተ መንግሥት የግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ የንስሓ አባት ሆኑ፡፡ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በራሷ ተወላጅ ጳጳሳት ልጆቿ እንድትመራ ከ1600 ዓመታት በኋላ ስለተፈቀደላት ከዚህ በኋላ በሃይማኖታቸውና በስነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው አምስት ደጋግ አባቶች ሲመረጡ አንዱ አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የራሷን ጳጳስ ስትሾም አቡነ ጴጥሮስ ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም ጵጵስና ተሾሙ፡፡ ከዚህም በኋላ ብፁዕ አባታችን ‹‹አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዐ›› ተብለው በያኔው መንዝና ወሎ ሀገረ ስብከት ተሾሙ፡፡
ብፁዕ አባታችንም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንንና ቅድስት ሀገራችን በጸሎታቸው፣ ሕዝቡን በትምህርታቸው እየጠበቁ በተጋድሎ እየኖሩ ሳለ አረመኔው የኢጣሊያ ፋሺስት በ1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነትን አውጆ ሕዝቡን በግፍ ይገድል ቤተ ክርስቲያንን ያቃጥል ጀመር፡፡ በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ካህናትና መነኮሳት ተገደሉ፣ ብርቅዬ የቤተ ክርስቲያን ቅርሶች ተዘረፉ፡፡ አቡነ ጴጥሮስም ይህንን ግፍ በማየታቸው ከሀገራችን አርበኞች ጋር በመሆን በጸሎታቸው ሊዋጉት ተነሡ፡፡ አባታችን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ማይጨው ዘምተዋል፡፡ ፋሺስቱ በማይጨው በመርዝ የተደገፈ ጦርነት ከማድረጉ የተነሣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበታተንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ወደ አ.አ የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለአገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሠላሌ አርበኞች በሚገባ አስተምረዋል፡፡ በደብረ ሊባኖስ ጫካዎች ውስጥ መሽጎ የነበረው የእነ ደጃዝማች አበራ ካሣ አርበኛ ጦር እና በሸንኮራ በኩል መሽጎ የነበረው የእነ ፍቅረ ማርያም አርበኛ ጦር እንደሁም በምዕራብ ይመራ ከነበረው የእነ ደጃዝማች አባ ነፍሶ ጦር ሦስቱም በአንድ ጊዜ ወደ መሐል አ.አ በመግት አ.አ ላይ መሽጎ የነበረውን ፋሽስትን ለመውጋት ታቅዶ የነበረው ዕቅድ በመረጃ ክፍተት ምክንያት ውጤታማ ሳይሆን ቀረ፡፡ በተለያየ ጊዜ መሐል አ.አ እየደረሱ ማለትም በመጀመሪያ የእነ ፍቅረ ማርያም አርበኛ ጦር ለብቻው በኮተቤ አድጎ የካ ሚካኤል ላይ ሲድርስ ተመቶ ተመለሰ፤ ይሄኛው እንዳለቀ ቀጥሎ የእነ አባ ነፍሶ ጦር በባቡር ጣቢያ መጣሁ ቢልም በጠላት ጦር ድካሚ ተመቶ ተመለሰ፤ መጨረሻ ላይ የእነ ደጃዝማች አበራ ካሣ አርበኛ ጦር በእንጦጦ በኩል ቢመጣም እርሱም በጠላት ጦር ተመቶ ተመለሰ፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ሦስቱም የአርበኞች ጦር በመረጃ ክፍተት ምክንያት እየተመታ ወደመጣበት ሲመለስ አቡነ ጴጥሮስ አብረው ከአርበኛው ጦር ጋር መመለሱን አልፈለጉትም ይልቁንም ‹‹ብችል ጠላት በኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ በቅርብ ርቀት ሆኖ የሚመለከተውን ሕዝብ በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሣ አደርገዋለሁ ካልሆነም ደግሞ እዚሁ እሞታለሁ›› በማለት አባታችን ከአርበኞቹ ተነጥለው አ.አ ቀሩ፡፡ ይሁን እንጂ ጠላት በመላዋ ከተማ ያሰማራቸው ባንዳዎች አባታችንን እንዳሰቡት ሊያነቀሳቅሷቸው አልቻሉም ነበር፡፡ በመሆኑም አባታችን ‹‹የሀገሬን ሕዝብ ለጠላት እንዳይገዛ በአደባባይ አውግዤ ጠላትን ረግሜ በሰማዕትነት ባልፍ ይሻለኛል›› ብለው ራሳቸውን ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት ወሰኑና የፋሺስት ኢጣሊያ እንደራሴ ለሆነው ለራስ ኀይሉ ሄደው እጃቸውን ሰጡት፡፡ እርሱም ብፁዕ አባታችንን ወስዶ ለግራዚያኒ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም አሳልፎ ሰጧቸው፡፡ ግራዚያኒም ግማሽ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዲገደሉ ወሰነባቸው፡፡ አቡነ ጴጥሮስ በፈቃዳቸው እጃቸውን አሳልፈው ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ በጠላት የጥይት እሩምታ በሰማዕትነት እስካለፉበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሒደት ኮርየሬ ዴላሴራ የተባለው ጋዜጣ ወኪልና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ፖጃሌ የተባለው ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ ሰኔ 15 ቀን 1936 ዓ.ም በአዲስ አበባ በነበረ ጊዜ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የተሰጠውን ፍርድና የተፈጸመውን የግፍ ግድያ ባየውና በተመለከተው መንገድ እንደሚከተለው ጽፎ ነበር፡-
‹‹ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም አቡነ ጴጥሮስ ተይዘው ወደ ግራዚያኒ ቀረቡ፡፡ በዚህ ጊዜ አቡነ ቄርሎስ የተባሉት ግብፃዊ ጳጳስ ቀርበው ‹ለእስክንድርያው መንበረ ፓትርያርክ ምክር ቤት ሳታሰማ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ እንዳች ነገር ማድረግ አይገባህም››› ሲሉ ለግራዚያኒ ነገሩት፡፡ አቡነ ቄርሎስ ይህን ማለታቸው በዲፕሎማቲክ ደረጃ ለዓለም ለማሰማትና የአቡነ ጴጥሮስን ሕይወት ለማትረፍ አስበው ነበር፡፡ ነገር ግን ግራዚያኒ የአቡነ ጴጥሮስ የሞት ፍርድ እንኳንስ እስከ ግብጽ ከአ.አ ውጭ እንኳ ከመሰማቱ በፊት በግማሽ ቀን እንዲፈጸም መመሪያ አስተላላፈ፡፡ ወደ ምሥራቅ አፍሪካው ዜና መዋዕል አዘጋጁ ወደ ፖጃሌ ዘገባ እንመለስና የአቡነ ጴጥሮስን መልካቸውንና ተክለ ቁመናቸውን እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡- ‹‹ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም፣ ፊታቸው ዘለግ ያለ፣ መልካቸው ጠየም ያለ፣ ዐዋቂነታቸውና ትሕትናቸው ከገጻቸው የሚነበብ ሲሆን በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብሰ ጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ፡፡ ለፍርድ የተሰየሙት ዳኞቸ ሦሰት ሲሆኑ እነዚህም ጣሊያኖችና የጦር ሹማምንቶች ናቸው፤ መካከለኛው ዳኛ ኮሎኔል ነበር፡፡ የቀረበባቸውም ወንጀል ‹ሕዝብ ቀስቅሰዋል፤ ራስዎም አምፀዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምፁ አድርገዋል› የሚል ነበር፡፡ ዳኛውም ‹ካህናቱም ሆኑ የቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የጣሊያንን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?› ሲል ጠየቃቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስም በቆራጥነት የሚከተለውን መለሱ፡- ‹‹አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ፡፡ ሓላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡ ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፡፡ ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ፡፡ እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ ዐውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ» አሉ፡፡ ‹‹ይህንንም ብለው በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ እንዲመለከት ተጋብዞ ለተሰበሰበው ሕዝብ የሚከተለውን ሕያው መልእክት አስተላለፉ፡- ‹አረማዊ የሆነው የፋሺስት መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው፤ እንጂ በጎ ለመሥራት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ፡፡ ስለ ውድ ሀገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከሉ፡፡ ነጻነታችሁ ከሚረክስ ሙታችሁ ስማችሁ ቢቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፤ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን፡፡ በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን› ብለው አወገዙ፡፡ ቀጥሎም ብፁዕነታቸው በፍጥነት ችሎት ላይ እንዳሉ ሕዝቡ ሁሉ ስለ እርሳቸው እያዘነ ሳለ መስቀላቸውን አውጥተው እየጸለዩ ሕዝቡን ባረኩ፡፡ ወዲያው የሞታቸው ፍርድ ሲሰማ ሕዝቡ በኢጣሊያ የእጅ ሰላምታ ዓይነት እጁን እንዲያነሳ ታዘዘ፡፡ በዚያን ጊዜ አቡነ ጴጥሮስ የሞታቸው ሰዓት መድረሱን ዐውቀው ሰዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ፡፡ በዚህን ጊዜ ምንም ፍርሃት አይታይባቸውም ነበር፡፡ የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረው ኢጣሊያዊው ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር፡፡ ታላቅ ፍርሃም በፊቱ ላይ ይታይ ነበር፡፡ የሞታቸው ፍርድ ከተነበበ በኋላ የፈረዱባቸውን ዳኞች ጸልየው በመስቀላቸው ባረኳቸው፡፡
የሀገራቸው በጠላት መወረር፣ የሕዝባቸው መገደልና መታሰር፣ የቤተክርስቲያናቸው መደፈር እስከ ሞት ያደረሳቸው እኒያ እውነተኛ ጳጳስ እንዲገደሉ ሲወሰዱ ጥይት አልፎ ሌላ ሰው እንዳይመታ ግንብ ይፈለግ ጀመር፡፡ ሩቅ ባለመሄድ ከመካነ ፍትሑ ዐሥር ሜትር ርቆ ግንብ ያለው መግደያ ቦታ ተገኘና ወደዚያ ተወሰዱ፡፡ ከገዳዮቹም አንዱ ‹ፊትዎን ለመሸፈን ይፈልጋሉን?› ሲል ጠየቃቸው፡፡ ‹ይህ ያንተ ሥራ ነው› ሲሉ ብፁዕነታቸው መለሱ፡፡
ከመግደያውም ቦታ እንደደረሱ ወንበር ቀረበላቸውና ፊታቸውን ወደ ግንቡ ጀርባቸውን ወደ ሕዝቡ አድርገው እንዲቀመጡ ሆኑ፡፡ ከዚያም በኋላ ስምንት ወታደሮች በስተ ጀመርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተጠንቀቅ ቆሙ፣ ወዲያው አዛዡ ‹ተኩስ!› በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቱዋቸው፡፡ ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ፡፡ መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ፡፡ ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ፡፡ ከዚያም በኋላ አንድ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው፡፡ ብፁዕነታቸው የተገደሉበት ቦታ መሐል አዲስ አበባ ላይ ዛሬ መታሰቢያ ሐውልታቸው ቆሞ በሚገኝበት ቦታ ላይ ነው›› በማለት የጋዜጣ ወኪልና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛው ፖጃሌ ስለ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ‹‹አቡነ ጴጥሮስ እንዴት ሞቱ?›› ሲል በወቅቱ አባታችን ሰማዕትነትን ሲቀበሉ በቦታው ላይ በአካል በመገኘት ሁኔታውን ይከታተሉ የነበሩትን ሙሴ ፓይላክን ጠይቋቸው እርሳቸውውም የሚከተለውን ተናረዋል፡- ‹‹አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ ዕለት እዚያው ነበርኩ፡፡ መጀመሪያ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት፡፡ ቀጥለውም በያዙት መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ፡፡ የኪሳቸውንም ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከኪሳቸው ከተቱት፡፡ ወዲያው ወታደሮቸ በሩምታ ተኩሰው ገደሏቸው፡፡
ይህ እንደሆነ አስገዳዩ ኮሎኔል ተመልካቹን ሕዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ፡፡ ማታ ከአስገዳዩ ኮሎኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወት ‹በዚህ ቄስ መገደልኮ ሕዝቡ ተደስቷል› አለኝ፡፡ ‹እንዴት?› ብለው ‹አላየህም ሲያጨበጭብ?› አለኝ፡፡ ‹ባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባሕል ሲናደድም ያጨበጭባል› አልኩት፡፡ ‹እንዴት?› ቢለኝ እጄን አጨብጭቤ አሳየሁት፡፡ ‹ከዚህ በኋላ የሆነው ቢሆን እኔ ትልቅ ማስታወሻ አግኝቻለሁ› ብሎ አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ ይዘውት የነበረውን መስቀልና መጽሐፍ ቅዱስ የኪስ ሰዓታቸውንም ጭምር አሳየኝ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ መሐል ለመሐል በጥይት ተበስቷል፡፡ መስቀሉም ልክ በመሐሉ ላይ ጥይት በስቶት ወጥቷል፡፡ የኪስ ሰዓታቸውንም እንዳየሁት እንዲሁ ጥይት በስቶታል›› ብለው በወቅቱ የተመለከቱትን መስክረዋል፡፡
ብፁዕ አባታችን በአደባባይ በሕዝብ ፊት የሰማዕትነት ጽዋቸውን ሲቀበሉ ከሕዝቡ ጋር ሆና ትመለከት የነበረች አንዲት ከድጃ የምትባል እስላም ሴት ማንም ሰው ያላየውን ታላቅ ነገር እርሷ ተመልክታለች፤ ይኸውም አባታችን ሰማዕትነትን ሲቀበሉ የብርሃን አክሊል በራሳቸው ላይ ሲቀዳጁ ተመልክታ በዚያው እርሷም ‹‹የእኚህን አባት ሃይማኖት እከተላለሁ›› ብላ በመጠመቅ ክርስቲያን ሆናለች፡፡ የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል በሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ሰማዕቱን አቡነ ጴጥሮስን ገድሎ አስክሬናቸው አደባባይ ላይ ጥሎ ከዋለ በኋላ ቀብራቸው በምሥጢር መፈጸሙን አንዳንዶች ይናገራሉ፡፡ የእኚህን ታላቅ አባት ቀብር በምሥጢር የተፈጸመበት ቦታ ለማግኘት የተለያዩ ምሁራን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የታሪክ ሰነዶችን ሲመረምሩ ቢቆዩም ‹‹ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በምሥጢር ቀበሯቸው›› ከሚል ከመላምት ያለፈ ነገር ምንም ዓይነት የተረጋገጠ ማስረጃ ሳይገኝ ቀርቷል፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ‹‹ፉሪ ለቡ›› ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የሰፈሩ ምዕመናን በአካባቢው ተወልደው ካደጉ አረጋውያን ጋር ባደረጉት ማኅበራዊ ግንኙነት ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ፋሽስቶች በመኖርያነትና በእስር ቤትነት ይጠቀሙበት በነበረው ‹‹ሙኒሳ ጉብታ›› ላይ መቀበራቸውን ከወላጆቻቸው ሲሰሙ እንዳደጉ እየተነገረ ይገኛል፡፡ እንዲሁም የአቡነ ጴጥሮስን ሥጋ በተመለከተ ማንም እንዳይወስደው በአስቸኳይ ከአ.አ ውጭ ማንም በማያውቀው ቦታ በምሥጢር እንዲቀበር መደረጉ በትንሣኤ መጽሔት ቁ.58 1978 ዓ.ም ላይ የተገለጠ ቢሆንም ነገር ግን አንዳንድ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች ቅዱሳን መላእክት የጻድቃንን በድን እያመጡ ወደሚያስቀምጡበትና በውስጡ የሚቀመጥ አስክሬን ወደማይፈርስበት አቡነ መልከ ጼዴቅ ዋሻ ገዳም መላእክት ወስደው እንዳስቀመጡትና በዚያም እንደታየ ይናገራሉ፡፡ ሰሜን ሸዋ ሚዳ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው በአቡነ መልከ ጼዴቅ ዋሻ ውስጥ የቅዳሱኑ አጽም ሳይፈርስና ሳይበሰብስ የአንገት ክራቸው ራሱ ሳይበጠስ እንደዛው እንደነበሩ ስለሚገኝ ቦታውም እጅግ ትልቅ የቃልኪዳን ቦታ ስለሆነ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅም በዚህ በጨረሻው ሀሳብ ይስማማል፡፡
ሰማያዊ ክብርን የሚያስገኝ አኩሪ ገድል በመፈጸም የቤተክርስቲያን ታላቅ አለኝታ አባትና መሪ የሆኑት የዘመናችንን ታላቅ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስን ትውልዱ የግድ ሊያስባቸውና ሊዘክራቸው ይገባል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (united nations) አቡነ ዼጥሮስን "የሺህ ዓመቱ ምርጥ ሰማዕት" ወይም በፈረንጅኛው አፍ (MARTYR OF THE MILLENIUM) በሚል መጠሪያ ሰይሟቸዋል፡፡ ላልተነገረላቸውና ላልተዘመረላቸው ለእኚህ ብርቅዬ የቤተ ክርስቲያናችን ድንቅ አባት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት 12 ቀን 1998 ዓ.ም እኚህን ሰማዕት ‹‹አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ›› ተብለው እንዲጠሩ ወስኗል፡፡ በስማቸውም መቅደስ እንዲታነጽ ፈቅዶ በመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ መሠረት (ኢሳ 56፡4) ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ጻድቁ በተወለዱበት ሥፍራ መታሰቢያ አቁማላቸዋለች፡፡ ግንቦት 1 ቀን 2001 ዓ.ም በስማቸው የተሰየመው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንና መታሰቢያ ሐውልታቸው ሲሠራ የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ የእስልምና እምነት ተከታዮችም ጭምር ለግንባታ የሚሆን አሸዋ ከመርዳት አንስቶ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ድንኳን እስከመትከል ተሳትፈዋል፡፡ በገንዘብም በጉልበትም ተባብረዋል፡፡ ጠላት ድል ተደርጎ ሀገራችን ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ የአባታችንን እጅግ አኩሪ ታሪክ ሲያዘክራቸው እንዲኖር መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት አሳሳቢነት ሐምሌ 16 ቀን 1938 ዓ.ም በአ.አ መሐል ከተማ ላይ ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ እንጦንስ
በዚህች ቀን የመነኰሳት ሁሉ አባት በገዳም ለሚኖር እንደ ኮከብ የሚያበራላቸው አባት እንጦንዮስ የከበረች ቤተክርስቲያኑ የከበረችበት (ቅዳሴ ቤቱ) ነው። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ንፁሀን ክርስቲያን ናቸው እርሱም ከታናሽነቱ ጀምሮ ተንኮል ሽንገላ በልቡ ውስጥ የለውም ከወላጆቹም ጋር ወደ ቤተክርስቲያን ሂዶ በቆረበ ጊዜ ከህፃናት ጋር በመጫወት ከቶ አይሳሳቅም ነበር። ጥቂት በአደገም ጊዜ ራሱን ዝቅ አድርጎ ለወላጆቹ ይታዘዝ ነበር ሰባት አመትም በሆነው ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መፃህፍትን ተማረ ያን ጊዜም የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት አባ ቲዎናስ የተሾመበት ዘመን ነበር የእንጦንዮስንም ወሬውን ሰምቶ መልእክተኞችን ልኮ ወደርሱ አስመጣው ባረከውና ስለርሱ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ ይህ ህፃን በእግዚአብሄር ፊት ታላቅ ይሆናል ዜናውም በአለሙ ሁሉ ይወጣል እጁንም በላዩ ጭኖ ዲቁና ሾመው።
ከዚህም በኃላ ወላጆቹ በሞቱ ጊዜ ታናሽ ብላቴና እኅት ትተውለት ነበር።ከሰባት ወርም በኃላ እንደ ልማዱ ወደ ቤተ ክርስቲያን በሄደ ጊዜ የመንፈስ ቅዱስ ፍቅር በልቡ አደረበትና በኀሳቡ በአለም የሚሰራውን ሁሉ አባቶቻችን ሀዋርያት ሁሉን የአለምን ስራ ትተው ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ተከተሉት በሀዋርያት ስራ መፅሀፍም እንደተፃፈ ጥሪታቸውን እየሸጡ የሽያጩንም ዋጋ በሀዋርያት እግር ስር ያኖሩትን አሰበ እግዚአብሄር በሰማያት ያዘጋጀላቸው ዋጋቸው ምን ያህል ይሆን አለ ይህም ኀሳብ በልቡ ውስጥ የሚመጣ የሚወርድ ሆነ። ከዚህም በኃላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደ የክብር ባለቤት ጌታችን በከበረ ወንጌል ለባለፀጋው የተናገረውን ሰማ እንዲህ ሲል ፍፁም ትሆን ዘንድ ከወደድክ ሂድ ጥሪትህን ሁሉ ሸጠህ ለድኆች ስጥ በሰማይም ላንተ ድልብ አድርገው መጥተህም ተከተለኝ።
ከእግዚአብሄርም ዘንድ ይህን ልዩ ኀሳብ አግኝቶ ይህ ቃል ስለርሱ እንደተነገረ አሰበ በዚያንም ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን ወጣ ለአባቱም ያማረ ሰፊ ምድር ነበረው ለአገሩም ሰዎች ሰጣቸው ለርሱ የተውለትንም ጥሪታቸውን ሁሉ ሸጦ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጣቸው እኅቱንም ወስዶ ከደናግል ገዳም አስገባት።
በዚያንም ወራት የምንኩስና ስርአት አልተገለፀም ነበር እግዚአብሄርንም ለማገልገል የሚሻ ከመንደር ጥቂት ወጣ ብሎ ብቻውን በመቀመጥ በፆም በፀሎት ተወስኖ ይጋደላል የከበረ እንጦንዮስም እንዲሁ አደረገ ሰይጣናትም በስንፍናና በዝሙት ጦር የሚዋጉት ሆኑ በህልሙም የሴት ገፅ በማሳየት አብራውም እንደምትተኛ ያደርጓታል።
ከዚህም በኃላ በባህር ዳርቻ ወዳለች የመቃብር ቤት ሂዶ በዚያ የሚኖር ሆነ በላዩ በአደረ በእግዚአበሄርም ረድኤት በተጋድሎ በረታ ምግቡንም ከዘመዶቹ ወገን ያመጡላት ነበር ሰይጣናትም ሲጋደል አይተው ቀኑበት ታላቅ ዱብደባንም ደብድበው ጥለውት ሄዱ ዘመዶቹም ሲመጡ እንደ ሞተ ሆኖ ወድቆ አገኙት ተሸክመውም ወደ ቤተ ክርስቲያን ወሰዱት ጌታችንም አዳነው በነቃም ጊዜ ወደ ቦታው ተመልሶ ይጋደል ዘንድ ተጋድኖውን ጀመረ። በዚያንም ጊዜ ሰይጣናትን ወደርሱ ሲመጡ አያቸው በአራዊት አምሳል በአንበሶችና በተኩላዎች የተመሰሉ አሉ በእባቦችና በጊንጦችም የተመሰሉ አሉ ያስፈሩትም ዘንድ አንዱም አንዱ በላዩ ተነሳሱ እንጦንዮስም በእኔ ላይ ለእናንተ ስልጣን ካላችሁ ከእናንተ አንድ ያሸንፈኝ ነበር ብሎ ዘበተባቸው ወዲያውኑ እንደ ጢስ ተበተኑ በሰይጣናት ላይ ድልን እግዚአብሄር ሰጥቶታልና ሰይጣናትም ከሚያመጡበት መከራና ስቃይ አረፈ።
ምግቡንም በአመቱ ሁለት ጊዜ ያበስላል በፀሀይም ያደርቀዋል ወደበአቱም ማንም እንዲገባ አያሰናብትም የሚሻውም ሁሉ በውጭ ይቆምና ድምፁን ይሰማል እንጂ ሀያ አመትም እንዲህ ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደለ በገደል ተጠምዶ ኖረ።
ከዚህም በኃላ ፍፁም የሆነ እግዚአብሄርን መፍራትንና አምልኮቱን ለሰዎች ወጥቶ ያስተምር ዘንድ እግዚአብሄር አዘዘው ስለዚህም ወደ ፍዩም አገር ወጥቶ ብዙዎች ደቀ መዛሙርትን ሰብሰቦ አስተማራቸው በእግዚአብሄርም ህግ አፀናቸው ደቀ መዛሙርቶቹ በውስጣቸው የሚኖሩባቸው ብዙዎች ገዳማት ተሰሩለት።
ስለ ሀይማኖትም ስደት በሆነበት ወራት በሰማእትነት መሞት ወዶ ወደ እስክንድርያ ሀገር ሄዶ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመነ ከቶ አልያዙትም በክርስቶስም ስም የታሰሩ እስረኞችን በመጎብኘት ቢአረጋጋቸውና ቢአፅናናቸውም አልያዙትም መኮንኑም እንደማይፈራ ባየው ጊዜ ከፍርድ አደባባይ ውስጥ እንዳይታይ አዘዘው እርሱ ግን ሁልጊዜ መታየቱን አለተወም እንዲአሰቃየውና በሰማእትነትም እንዲሞት የሚያስቆጣውን ነገር ይናገረው ነበር መኮንኑም በእርሱ ላይ ምንም ክፉ ነገር አላደረገም አምላካዊት ኃይል ከልክላዋለችና።
ሊቀ ጳጳሳት ጴጥሮስ ለሰማእታት ፍፃሜ ሆኖ የመከራው ወራት ከአለፈ በኃላ እንጦኒ ወደ ገዳሙ ተመለሰ ይህም በአምላክ ፍቃድ ሆነ የሚለብሰውም ማቅ ነበር በዘመኑ ሁሉ ገላውን በውኃ አልታጠበም ብዙዎች በሽተኞችም ወደርሱ ይመጣሉ በላያቸውም ሲፀልይ ይድናሉ። ብዙዎች ህዝቦችም ትምህርቱን ሊሰሙ ወደርሱ ሲመጡ በአያቸው ጊዜ ብቻውንም ይኖር ዘንድ እንዳልተውት አይቶ ከእርሱ ስለሚደረገው ነገር ልቡ እንዳይታበይ ፈራ እነርሱ ወደሚያውቁት ቦታ ወደላይኛው ግብፅ ይሄድ ዘንድ ወዶ ወደ ባህሩም ወደብ ደርሶ መርከብ እየጠበቀ ተቀመጠ ከሰማይም ወደርሱ ቃል መጣ እንዲህም አለው እንጦንዮስ ሆይ ወዴት ትሄዳለህ ከዚህስ ምን ትሻለህ አለው እርሱም ብዙዎች ወደእኔ ስለሚምጡ እንደምፈልገው ለብቻ መኖር አልተቻለኝም ስለዚህም ወደ ላይኛው ግብፅ እሄድ ዘንድ ወደድኩ አለ ያም ቃል መልሶ እንዲህ አለው ወደ ላይኛው ግብፅ ብትሄድ ድካምህ ደግሞ እጥፍ ይሆናል ብቻህን መኖር ከወደድክ ግን የሶስት ቀን ጎዳና ያህል ወደ ውስጠኛው በረሀ ተጓዝ።
በዚያንም ጊዜ በዚያች ጉዳና ሊጓዙ የሚሹ የዓረብ ሰዋችን አያቸው ወደ እርሳቸውም ሒዶ አብረሮአቸው ይሔድ ዘንድ ለመናቸው እነርሱም በደስታ ተቀበሉት ወደ አንድ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ እስከሚደርስ የሦስት ቀን ጉዳና ተጓዘ በዚያም የጠራና የቀዘቀዘ ውኃ አለ ዳግምም የሰሌን የተምር ዕንጨቶች መቃቃዎችም በብዛት አሉበት እንጦኒዮስም ያንን ቦታ ወደደው ዓረቦችም ምግቡን የሚያመጡለት ሆኑ ብዙዎች የከፋ አራዊትም ነበሩ በጸሎቱም እግዚአብሔር አስወገዳቸው ወደዚያም ቦታ ከቶ አልተመለሱም። አንዳንድ ጊዜም ወደ ባሕሩ ዳርቻ በመውጣት ደቀ መዛሙርቶቹን ጉብኝቶና አረጋግቶ በበረሀ ወስጥወደአለው ቦተው ይመለሳል ።
ከዚህም በኋላ በጸድቁ ንጉሥ ቁስጠንጢስዘንድ ዜናው በተሰማ ጊዜ በጸሎቱያስበው ዘንድ ንጉሡ አየለ መነዉ ደብዳበ ጻፈለት የከበረ እንጦንዮስ ግን ወደ ንጉሥ ደብዳቤ ዘወር አላለም ለወገኖቹ እንዲህ አላቸውእንጂ የንጉሠ ነገሥት ክርስቶስ ደብዳቤ እንሆበላያችን ይነበባል ወንድሞችም እንዲህ ብለው ለመኑት ይህ ንጉሥ የክርስቲያንን ወገኖች የሚወድ ጻድቅ ሰው ነው ደብዳቤ ጽፈህ ልታጽናናው ይገባል ከዚህም በኃላ እያፅናናውና እየባረከው ፃፈለት።
ዳግመኛም በአፍርንጊያ ንጉስ ዘንድ ዜናው በተሰማ ጊዜ ወደ ከበረ እንጦንዮስ እንዲህ ብሎ ፃፈ ወደ እኛ መጥተህ በእኛ ላይ በአገራችንና በሰራዊታችን ላይ በረከትን ታሳድር ዘንድ ስለ ጌታችን ክርስቶስ መከራዎች እኔ ወዳንተ ፈፅሜ እማልዳለሁ።
የከበረ እንጦንዮስም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ ቁሞም እንዲህ ብሎ ፀለየ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እለምንሀለሁ በአፍርጊያ ውስጥ ወዳለ ወደ በርኪኖን አገር እንድሄድ ፈቃድህ ከሆነ ምልክትን ግለጥልኝ ነገር ግን ያንተ ፈቃድ ይሁን ይህንንም ባለ ጊዜ ብርህት ደመና መጣች በዚያችም ሰአት ተሸክማ ወደ አፍርንጊያ አገር አደረሰችው ንጉሱም ደስ አለው ህዝቡና ሰራዊቱም ሁሉ በሽተኞችንም አቀረቡለትና ሁሉንም ፈወሳቸው የፅድቅና የህይወትንም መንገድ እያስተማራቸው ከእነርሱ ዘንድ ስድስት ወር ኖረ። በእሁድም እለት ያቺ ብርህት ደመና ተሸክማ ወደ ገዳሙ ታደርሰውና ከልጆቹ ጋር ተገናኝቶ ያረጋጋቸዋል በማግስቱም ዳግመኛ ተሸክማ ወደ አፍርንጊያ አገር ትመልሰዋለች። ከዚህም በኃላ በእግዚአብሄር ፈቃድ በደመና ተጭኖ ወደ ገዳሙ አንደኛውን ተመለሰ።
በአንዲት እለትም ስንፍና መጣበት እንዲህ የሚለውም ቃል መጣ ታይ ዘንድ ወደ ውጪ ውጣ በወጣ ጊዜም መልአኩን አየው በላዩም የምንኩስና ልብስ አለ መታጠቂያ ቅናት የመስቀል ምልክት ያለው ቀሚስ በወገቡም አስኬማ በራስ ቁር አምሳልም በራሱ ላይ ቆብ አለ እርሱም ተቀምጦ ሰሌን ይታታል ከዚያም ተነስቶ ይፀልያል ዳግመኛም ተቀምጦ ሰሌኑን ይታታል በየሰአቱም እንዲህ የሚል ቃል ወደርሱ መጣ እንጦንዮስ ሆይ እንደዚህ ስራ አንተም ከሰንፍና ከሰይጣናት ጦርነት ታርፋለህ ያንን ያየውንም ተቀብሎ እንዲሁ አስመስሎ የሚሰራ ሆነ ከዚያችም እለት ወዲህ ስንፍናና የሰይጣናት ወጊያ አልመጣበትም።
የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ ተገልፆ አረጋግቶታል አፅንቶታልም። አሁንም እንዲህ አለው የመረጥሁህ እንጦንዮስ ሆይ በእውነት እነግርሀለሁ እኔን ስለመውደድህ በዚች በረሀ ውስጥ ብቻህን በመጋደልህና በማገልገልህ ስለ ድካምህ ስምህን ክፍ ከፍ አደርጋለሁ ስልጣንህንም በአለም ዳርቻ ሁሉ ከፍ አደርገዋለሁ።
ገዳማትንና አድባራትንም መነኩሳትን የተመሉ ሆነው ቅኖች የዋሀን ፃደቃን እንደሚኖሩባቸው አደርጋቸዋለሁ ይልቁንም ያንተ ገዳማት እነርሱ እስከ ፍፃሜ ይኖራሉ። መታሰቢያህንም የሚያደርገውን ሁሉ ለድሆች ምፅዋትን ለቤተክርስቲያን መባ በስምህ የሚሰጠውን ሁሉ እኔ ኃጢአቱን ሁሉ እደመስሳለሁ ከቶ ስቃይን አያያትም በውስጡ ስጋህ የሚቀበርበትንም ገዳም እጅግ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ በውስጡም እንደ መላእክት የሆኑ ደጋጎች መነኮሳት እንዲኖሩበት አደርጋለሁ ከእነርሱም እስከ አለም ፍፃሜ አለቃ የሚሆን አይታጣም የምድር ነገስታት መሳፍንትና ሹማምንት ለገዳምህና ፍለጋህን ለሚከተሉ ልጆችህም እጅ መንሻ ተሸክመው እንዲመጡ አደርጋለሁ ጌታችንም ይህንን ከተናገረው በኃላ ከእርሱ ዘንድ ወደ ሰማያት በታላቅ ክብር አረገ አባ እንጦኒም ፈፅሞ ደስ አለው።
ከዚህም በኃላ ስለ ቤተክርስቲያን መፍረስ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ መናፍቃን በላይዋ ይሰለጥናሉ ከዚህም በኃላ ወደ ቀድሞው ስርዓቷ ትመለሳለች ዳግመኛም ስለ መነኮሳት እነርሱ እጅግ እንደሚበዙ ገዳሞቻቸውንና አድባራቶችን በመተው ወርደው ከአለማውያን መካከል በከተማዎችና በቦታዎች ውስጥ እንደሚኖሩ ስለ አለም ፍፃሜም ትንቢት ተናገረ። ይህም አባ እንጦንዮስ አባ መቃርስን አስኬማንና የምንኩስና ልብስን ያለበሰው ያረጋጋውና ያፅናናው ከእርሱ የሚሆነውንም ያስረዳው ነው ደቀ መዝሙሩና ልጁ ስለሆነ።
ከዚህም በኃላ የገዳማውያን አለቃ ወደሆነ ወደ አባ ቡላ ሄደ እርሱም ለስጋው ያሰበና በሀዋርያዊ አትናቴዎስ ልብስ የገነዘው ነው። እረፍቱም እንደቀረበ በአወቀ ጊዜ በትሩን ለልጁ ለአባ መቃርስ ምንጣፉን ለአባ አትናቴዎስ የፍየል ሌጦ ዐጽፉን ለልጁ ለኤጲስቆጶስ ለአባ ስራብዮን እንዲሰጡ ልጆቹን አዘዛቸው።
ከዚህም በኃላ ከምድር ላይ ጋደም አለ ነፍሱንም በእግዚአብሄር እጅ ሰጠ ወደርሱም ሁሉም የመላእክት ማኅበር መጥተው በክብር በምስጋና ፍፁም ተድላ ደስታ ወዳለበት ዘላለማዊ እረፍት ተቀብለው አሳረጉት።
ስጋውን ግን ልጆቹ እንዳዘዛቸው ሰወሩት እርሱ የቅዱሳን ሰማእታትን ስጋቸውን የሚገልጡትን ይገስፃቸው ነበርና ስለ እነርሱ ስጋ ብዙ ገንዘብ እስከመቀበል ደረሰው አለማዊ ጥሪት ያደርጉታልና። ይህም የከበረና የተመሰገነ አባት እንጢንዮስ እስከ መልካም ሽምግልና ደረሰ እጅግም አረጀ ግን ወደ ወደደውም ክርስቶስ እስከ ሄደ ድረስ መልኩ አልተለወጠም ብርታቱ ፅናቱም መላው እድሜው መቶ ሀያ አመት ነው ጥር ሃያ ሁለት ቀንም ዕረፍቱ በድምቀት ይከበራል።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የፋሲለደስ ልጅ ቅዱስ መቃርስ
ሐምሌ ሃያ ሁለት በዚህች ቀን የጭፍሮች አለቃ የሆነ የፋሲለደስ ልጅ ቅዱስ መቃርስ ሰማዕት ሆነ። ይህንንም ቅዱስ አማልክትን እርሱ እንደማያመልክ በንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ዘንድ ወነጀሉት ንጉሥም ወደ እስክንድርያ ወስደው በዚያም እንዲአሠቃዩት አዘዘ።
እርሱም ወላጆቹን በተሰናበታቸው ጊዜ ለድኆችና ለችግረኞች እንዲአስቡ አደራ አላቸው። ከዚህም በኋላ ወጥቶ ሔደ ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስም ተገልጾለት አጽናናው የሚደርስበትንም ነገረው። ወደ እስክንድርያ ከተማም በደረሰ ጊዜ በመኰንን ኅርማኖስ ፊት ቆመ መኰንኑም የጭፍሮች አለቃ የፋሲለደስ ልጅ እንደሆነ አውቆ ብዙ አባበለው ለመነውም እርሱ ግን አልሰማውም ከመልካም ምክሩም አልተመለሰም።
ከዚህም በኋላ ሰውነቱ እስከምትቀልጥ ድረስ ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው በሥቃይም ውስጥ እያለ ጌታችን የቅዱሳንን ማደሪያዎችንና የአባቱንና የወንድሙን ማደሪያ አሳየው። ከዚህም በኋላ መኰንኑ ወደ ኒቅዮስ ሀገር ሰደደው በዚያም ታላቅ ሥቃይን አሠቃዩት ምላሱንና ክንዱን ቆረጡት በጎኖቹም ውስጥ በእሳት ያጋሉአቸውን የብረት ችንካሮች ጨመሩ ጌታችንም አዳነው ያለ ጉዳትም በጤና አስነሣው። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በእጆቹ ላይ ታላላቅ ድንቆችንና ተአምራቶችን አደረገ ከእነርሱም ብዙ ሰዎች የሞተ ሰው ተሸክመው ሊቀብሩ ሲሔዱ አየ። ሁሉም እያዩት ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን ማለደ። ስለዚያም ምውት ተነሥቶ ያየውን ይነግራቸው ዘንድ ለመነ። ወዲያውኑም ያ ምውት ተነሥቶ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ አምላክና የሁሉ ጌታ እንደሆነ ተናገረ።
ይህንንም ድንቅ ተአምር አይተው ብዙ አሕዛብ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ መኰንኑም ተቆጥቶ ያመኑትን ራሳቸውን አስቆረጠ ሰማዕታትም ሆነው የሰማዕታትን አክሊል ተቀበሉ። በዚያም የእንዴናው ገዥ አርያኖስ ነበረ በተመለሰ ጊዜም ቅዱስ መቃርስን ከእርሱ ጋራ ወሰደው ወደ ሀገረ ሰጥኑፍም በደረሰ ጊዜ መርከቢቱ ቆመች የማትንቀሳቀስም ሆነች እነሆ ጌታችንም ለእርሱ ተገልጦ ተጋድሎውን በዚያ እንደሚፈጽም ነገረው።ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡ። የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማይ ተቀበለ።
ቈስጠንጢኖስም በነገሠ ጊዜ የጣዖታትን ቤቶች እንዲዘጉ አብያተ ክርስቲያናትንም እንዲከፍቱ አዘዘ። ያን ጊዜም ስሙ አውሎጊዮስ የሚባል ምእመን መኰንን አብያተ ክርስቲያናትን ሊሠራ ጀመረ። ቅዱስ መቃርስም ተገለጠለትና ሥጋው ያለበትን ነገረው። መኰንኑም ወደ አመለከተው ቦታ ሔዶ የቅዱስ መቃርዮስን ሥጋ አገኘ ከዚያም ወሰደው ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶ ሥጋውን በውስጥዋ አኖረ። ከእርሱም ታላላቅ ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ልውንትዮስ
በዚህችም ቀን ቅዱስ ለውንትዮስ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ቅዱስ ክርስቲያን ከሀድያን ከሆኑ ሠራዊት ጋር ይኖር ነበር ሀገሩም ጠራብሎስ ነው መልኩም ያማረ በገድሉም ፍጹም የሆነ ነበር። አምላክ ያስጻፋቸው መጻሕፍትንም ያነብ ነበር።ይልቁንም የዳዊትን መዝሙር ሁልጊዜ ያነብ ነበር። ባልንጀሮቹ ለሆኑ ወታደሮችም ያስተምራቸው ይመክራቸውም ነበር።እግዚአብሔርንም እንዲፈሩ ያስገነዝባቸው ነበር። የማይጠቅሙ የረከሱ የአማልክትንም ሸክም ከትከሻችሁ ጣሉ ይላቸው ነበር። ከስሕተትም ተመልሰው ክብር ይግባውና በጌታችን ያመኑ አሉ። ከእነርሱም ወደ መኰንኑ ሒደው ለውንትዮስ አማልክትን አቃለላቸው ሰማይና ምድርን በውስጣቸውም ያለውን ሁሉ የፈጠረ ክርስቶስ ነው ይላል ብለው የከሰሱት አሉ። መኰንኑም በሰማ ጊዜ ወደርሱ አስቀርቦ ጠየቀው እርሱ ግን ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስን እንደሚያመልከው በመኰንኑ ፊት ታመነ ጳውሎስ ከፈጣሪዬ ከክርስቶስ ማን ይለየኛል እንዳለ ከታናሽነቴ ጀምሮ በፍጹም ልቡናዬ አመልከዋሁ ለእርሱም እሰግዳለሁ አለው። መኰንኑም እጆቹንና እግሮቹን አሥረው በወህኒ ቤት ውስጥ እንዲጥሉት አዘዘ እንዲሁም አደረጉበት። በማግሥቱም መኰንኑ አቅርቦ እንዲህ አለው በምን ኃይል የንጉሥን ትእዛዝ ደፍረህ ትተላለፋለህ ሰዎችንም አማልክትን ከማምለክ በምን ኃይል ትመልሳቸዋለህ ቅዱሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት። በእውነት ሰዎች ሁሉ ክብር ይግባውና ወደጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት እንዲገቡ እኔ እሻለሁ አንተም ስሕተትህን ትተህ ክብር ይግባውና ኢየሱስ ክርስቶስን ብታመልከው የረከሱ አማልክትንም ማምለክ ብትተው የዘለዓለም መንግሥትን በወረስህ ነበር። ይህንንም በሰማ ጊዜ መኰንኑ እጅግ ተቆጣ ደሙ እንደ ውኃ እስኪፈስ ድረስም ይገርፉት ዘንድ አዘዘ እርሱም እግዚአብሔርን ፈጽሞ ያመሰግነው ጀመረ። ከወታደሮችም አንዱ አዘነለትና በጆሮው አሾከሾከ እኔ ስለአንተ አዝናለሁ ጉልምስናህንም ላድን እወዳለሁ አንተ ለአማልክትም እንደምትሠዋ ለመኰንኑ አንዲት ቃልን ብቻ ተናገር እኔም እዋስሃለሁ አለው። ቅዱሱም ሰይጣን ከኋላዬ ሒድ ብሎ ገሠጸው። መኰንኑም ጭካኔውን አይቶ ሥጋው እስከ ሚቆራረጥ ደሙም እንደ ውኃ በምድር ላይ እስኪፈስ ድረስ ሥቃዩን እጥፍ ድርብ አደረገበት። ከዚህም በኋላ በውኃ እንዲዘፍቁት በእግሩም እንዲጐትቱትና በወህኒ ቤት እንዲጥሉት አዘዘ በዚያም ነፍሱን አሳለፈ ገድሉንም ፈጸመ። የምታምን ሀብታም ሴት መጥታ ለወታደሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥታ የቅዱሱን ሥጋ ወሰደች በአማሩ ልብሶችም ገነዘችው የወርቅ ሣጥንም አሠርታ በውስጡ አኖረችው። ሥዕሉንም አሣለች በፊቱም ሁልጊዜ የሚያበራ ፋና አኖረች። ለዚችም ሴት ቅዱሱ ያደረገላት የድካም ዋጋዋ ሰኔ አንድ ቀን ተጽፎ አለ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages