ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 28 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, July 16, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 28

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም



ሰኔ ሃያ ስምንት በዚች ቀን የእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት የሆነው ቅዱስ አባ ቴዎዶስዮስ አረፈ፣ የምሥራቁን ኮከብ ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዳይ መታቢያው ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ አባ ቴዎዶስዮስ
ሰኔ ሃያ ስምንት በዚህች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳ ሦስተኛ የሆነው ቅዱስ አባ ቴዎዶስዮስ የእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት አረፈ። በዚህም ቅዱስ በስሙ በግብጽ ምድር ውስጥ ምእመናን ቴዎዶስዮሳውያን ተብለው ተጠርተውበታል።
ይህም የሆነው እንዲህ ነው ሊቀ ጵጵስና ከተሾመ በኋላ ክፉዎች ሰዎች በእርሱ ላይ ተነሥተው በንጉሥ ምክር ከመንበረ ሢመቱ አሳደዱት በእርሱ ፈንታም አስቀድሞ በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ዲያቆናት የነበረ ስሙ አቃቅያኖስ የሚባለውን አንድ ሰው ሾሙ እርሱም ለአባ ቴዎዶስዮስ ሊቀ ጵጵስና እንዲገባው ከፈረሙት ቁጥር ውስጥ ነበረ።
ይህም አባት ወደ ግርማኖስ አገር ሒዶ ሦስት ወሮች ኖረ በዚያም ወራት በግብጽ አገር ንቡረ እድ አባ ሳዊሮስ ነበረ እርሱም በአባቶቻችን ሐዋርያት እንዲሁም በአትናቴዎስና በዮሐንስ አፈወርቅ የደረሰባቸውን መከራ እያስታወሰ ያጽናናቸው ነበር።
ከዚያም ተነሥቶ መሊግ ወደሚባል አገር ሔደ በዚያም ሁለት ዓመት ተቀመጠ። የእስክንድርያ ከተማ ሰዎችም የጠባቂያቸው የቴዎዶስዮስን መመለስ ሽተው በእስክንድርያው መኰንን ላይ ተነሡበት መኰንኑም ወደ መንበረ ሢመቱ መለሰው አቃቅያኖስንም አባረሩት።
ይህም ነገር በንጉሥ ዮስጣቲያኖስና አምላክን በምትወድ በንግሥት ታዖድራ ዘንድ ተሰማ ንግሥቲቱም አስቀድሞ የተሾመው በሹመት ወንበሩ ይቀመጥ ብላ ጻፈች።
ሃምሳ ስምንት ካህናትም ጉባኤ አደረጉ አስቀድሞ የተሾመ አባ ቴዎዶስዮስ ነው ሲሉም ጻፉ። ያን ጊዜም አቃቅያኖስ በሕዝብ ፊት ቁሞ ክፉዎች ሰዎች ስለ አስገደዱኝ ይህን ሥራ ለመሥራት ሕግን ተላልፌአለሁ አለ። ከዚህም በኋላ አቃቅዮስን ከውግዘቱ እንዲፈታው ነገር ግን ክህነትም ሆነ ሊቀ ዲቁና ለዘለዓለሙ እንዳይኖረው ሕዝቡ አባ ቴዎዶስዮስን ለመኑት። አቃቅያኖስም አዎ እንዲሁ ይሁን አለ ይህም አባት ከግዝቱ ፈታው።
ሃይማኖቱን ያጠፋ ንጉሡ ግን በከፋች ሃይማኖቱ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎዶስዮስ ከእርሱ ጋራ የሚስማማ መስሎት በእስክንድርያ ወዳሉ መኳንንቶቹ እንዲህ ብሎ ጻፈ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎዶስዮስ በሃይማኖት ከእኛ ጋራ የሚስማማ ከሆነ ሹመት ይጨመርለታል። ለእስክንድርያ ከተማ ገዥ ይሆናል። ይህ ካልሆነ ግን ከሹመቱ ይሻር።
ይህም አባት ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ ሰይጣን በበረሀ ጌታችንን ብትሰግድልኝ የዓለም መንግሥታትንና ክብራቸውን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው። ያን ጊዜም ይህ አባ ቴዎዶስዮስ ተነሥቶ ከእስክንድርያ ወጣ ወደ ላይኛው ግብጽም ሔደ በዚያም ሕዝቡን እያስተማራቸው በቀናች ሃይማኖትም እያጸናቸው ጥቂት ቀኖች ኖረ።
ንጉሡም አባ ቴዎዶስዮስ ከእስክንድርያ ከተማ እንደ ወጣ በሰማ ጊዜ እየሸነገለው ወደ እርሱ መልእክት ላከ እንዲህም አለው እኔ ከአንተ ጋራ ልነጋገር ከአንተም ልባረክ እንድትመክረኝም እሻለሁ።
ከዚህም በኋላ ወደ ቍስጥንጥንያ ከተማ ሔደ የጳጳሳት አለቆችና ሕዝቡ ሁሉ ሠራዊቱም ተቀበሉት በከፍተኛ ወንበርም ላይ አስቀመጡት። እርስ በርሳቸውም ስለ ሃይማኖት ተከራከሩ ንጉሡም አብዝቶ ሲሸነግለውና ሲአባብለው ሰነበተ ቅዱስ አባት ቴዎዶስዮስም ከቅዱሳት መጻሕፍት በመጥቀስ ይረታው ነበረ።
ከእርሱም ጋራ ባልተስማማ ጊዜ ከመንበረ ሢመቱ ወደ ላይኛው ግብጽ አሳደደው። በእርሱም ፈንታ ጳውሎስ የሚባለውን ሰው ሾመው። ጳውሎስም ወደ እስክንድርያ ከተማ በመጣ ጊዜ ሕዝቡ አልተቀበሉትም ዓመት ሙሉም ኖረ በእጁም ማንም ቍርባንን አልተቀበለም።
ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ ለመናፍቁ ጳውሎስ እስከሚታዘዙ ድረስ አብያተ ክርስቲያናት እንደዘጉ አዘዘ። ምእመናንም ከእስክንድርያ በመውጣት ወደ ቅዱስ ወንጌላዊ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ቆዝሞስና ድምያኖስ ቤተ ክርስቲያን ይሔዱ ነበር ካህናቱም በዚያ እየቀደሱ ያቈርቧቸው ነበር የአገር ልጆችንም የክርስትና ጥምቀትን ያጠምቋቸው ነበር።
ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲከፍቱላቸው አዘዘ አባ ቴዎዶስዮስም ሰምቶ ንጉሡ እንዳያስታቸው ፈራ ማጽናኛ ቃልን የተመላች መልእክትም ጽፎ በቀናች ሃይማኖት እያበረታታቸው ወደ ምእመናን ላካት እንዲህም አላቸው ለዚያ ከሀዲ ጳውሎስ እንዳትታዘዙ ተጠበቁ። ይህም አባት ሃያ ስምንት ዓመት በስደት ኖረ። መላው የሹመቱ ዘመን ሠላሳ ሁለት ነበር። ይኸውም በእስክንድርያ አራት ዓመት በስደትም ሃያ ስምንት ዓመት ነው።
ይህም አባት ብዙ ድርሳናትን ደርሷል ምእመናንም በያዕቆብ ዘመን ያዕቆባውያን እንደ ተባሉ በስሙ ቴዎዶስዮሳውያን እየተባሉ ሲጠሩ ኖሩ። መልካም ጉዞውንም ፈጽሞ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዳይ
በዚህችም ዕለት የምሥራቁን ኮከብ ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዳይ መታሰቢያው ነው፡፡ "ያዕቆብ" ለሚል ስም ትርጉምን የሰጡ አበው በ2 መንገድ ያትቱታል::
1.አኃዜ ሰኮና:- ነገሩ ከወልደ ይስሐቅ ወርብቃው ርዕሰ አበው ያዕቆብ ጋር የተያያዘ ቢሆንም አበው ግን ለትህትና ይተረጉሙታል::
2.አእቃጺ / አሰናካይ:- ነገሩ ስድብ (አሉታዊ) ይምሰል እንጂ በዚህ ስም የተጠሩ አበው ሁሉ ለአጋንንትና ለመናፍቃን ትልቅ መሰናክል ሆነውባቸው ኑረዋልና አባባሉ ምስጋና እንጂ ነቀፋን አይወክልም::
የ6ኛው መቶ ክ/ዘመን ምሥራቃዊ ኮከብ ቅዱስ ያዕቆብም ለመለካዊ መናፍቃንና ለተዋሕዶ ተገዳዳሪዎች ትልቅ መሰናክል ሆኖባቸዋል:: የቀናችውን ቀርነ ሃይማኖትንም አጽንቷል::
ብዙ ጊዜ "ዘ"-እልበረዲ መባሉን ይዘው በ"ዘ" ምክንያት እልበረዲን እንደ ሃገር የቆጠሯት አልጠፉም:: በረከታቸው ይድረሰንና ትጉሑ ዻዻስ አቡነ ጐርጐርዮስ ካልዕ ግን ለዚሁ
መላምት "የለም!" ባይ ናቸው::
'የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ' በተሰኝ ተወዳጅ መጽሐፋቸው "እል-በረዲ" ማለትን በዓረብኛ ከሠጋር በቅሎ : ከሥሙር ሠረገላ ጋር አነጻጽረው አስቀምጠውታል:: ለምን ቢባል - እንደ ሠረገላ በተፋጠነ አገልግሎቱ ወዳጅንም ጠላትንም አስደምሟልና::
ቅዱስ ያዕቆብ የተወለደው በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ (በ500 አካባቢ) ሲሆን ያረፈው ደግሞ በ578 ዓ/ም እንደሆነ ይታመናል:: ነገሩን ልብ ስንለው ቅዱስ ማኅሌታይ ያሬድን - ወዲህ በዘመን : ወዲያ ደግሞ በአገልግሎት ይመስለዋል:: እርግጥ ነው ለውለታው የሶርያ ቤተ ክርስቲያን "ያዕቆባዊት" ስትባል የእኛዋስ ምናለ "ያሬዳዊት" ብትባል የሚል ቁጭትን ያመጣል::
ጊዜው (5ኛውና 6ኛው መቶ ክ/ዘመን) ወዲህ ወርቃማ : ወዲያ ደግሞ ጨለማ ተብሎ ሊጠራ የሚችል ዘመን ነበር:: በብርሃንነቱ በተለይ በምሥራቁ ዓለም ያበሩ አበው እነ ያዕቆብ ዘስሩግ : ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ : ያዕቆብ ዘእልበረዲን የመሰሉ አበው ተገኝተውበታል:: ሲያልፍ ደግሞ ዘይኑንና አንስጣስዮስን የመሰሉ ደጋግ ነገሥታት በዘመኑ መነሳታቸውን እናስባለን::
በተቃራኒው ግን ዘመኑ ቤተ ክርስቲያን ለ2 የተከፈለችበት : መለካውያን የነገሥታቱ ደጀን አላቸውና ተዋሕዶ ሃይማኖትን ከሥሯ ነቅሎ ለማጥፋት ብዙ የሞከሩበት ዘመን ነውና ጨለማነቱ ይጐላብናል::
በእርግጥም ከመርቅያን እስከ ዮስጢኖስ ዳግማዊ ዘመን ድረስ ለ100 ዓመታት መለካውያኑ የልዮን ልጆች 2 ባሕርይ ማለትን ሊያሰፉ : ተዋሕዶንም ሊያጠፉ የከፈቱት ዘመቻ ሊሳካ ጫፍ የደረሰ ይመስል ነበር::
ግን አማናዊት ቤቱን የማይተው አማናዊው ጌታ መድኃኔዓለም አርመኖቹን ስቦ በ490ዎቹ ወደ መንጋው ቀላቀለ:: በግብጽ አባ ቴዎዶስዮስን : በሶርያ ደግሞ ታላቁን ሊቅ ቅዱስ ሳዊሮስን አስነስቷል:: ከቤተ መንግስትም ስም አጠራሯ ያማረ ንግሥት ታኦድራን ማርኯል:: በእነዚህ ቅዱሳን ትጋት የለመለመችው ተዋሕዶ እንደ ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዲ ያለ አርበኛን ግን ያገኘችው በጭንቅ ቀን ነበር::
ሰው መሆን ሰው በጠፋባቸው ቀናት ነውና : በግብጽና በቁስጥንጥንያ በትምህርትና ምናኔ ላይ የነበረው ቅዱሱ ታጥቆ ለአገልግሎት የተሰለፈው በ530ዎቹ አካባቢ ነበር::
ጊዜው ወዲህ አንበሳው ቅዱስ ሳዊሮስ ከሶርያ ወደ ግብጽ እንደተሰደደ ያረፈበት ነበር:: ወዲያ ደግሞ ሊቁ አባ ቴዎዶስዮስ የግብጹ ለግዞት የተዳረገበት ነበርና የተዋሕዶ ምዕመናን ያለ እረኛ ተቅበዘበዙ:: የቤተ መንግስቱ ተጽዕኖ ደግሞ 2 ባሕርይ በማይሉት ላይ እሥራትና ግድያን ወደ ማወጅ ተሸጋግሯልና የምእመናን ቁጥር እጅጉን መመንመኑ ቀጠለ::
ይህ ዕረፍት የነሳው ቅዱስ ያዕቆብ በበኩሉ ነገሩን በዝምታ ሊያልፈው አልወደደምና አገልግሎቱን አሰፋ:: ሌሊቱን በጸሎት ያድራል:: ቀን በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ማስተማር ባይችል በየቦታው እየዞረ ያስተምር ነበር::
ከትምህርቱ ጣዕምና ከመልእክቱ ሥምረት የተነሳም ምእመናን እንደገና ተነቃቁ:: እርሱም ከግብጽ እስከ ሶርያ : አልፎም እስከ ቁስጥንጥንያ ድረስ ያለ ዕረፍት ሲሰብክ 40 ዘመናትን አሳለፈ:: በተለይ አዲስ አማኞችን ያጠምቅ ዘንድ በእሥረኛው ቅዱስ ቴዎዳስዮስ ኤዺስ ቆዾስነትን ተቀብሏል::
የሶርያ (አንጾኪያ) የፕትርክና መንበሩ ክፍት ሆኖ እርሱን ቢጠብቀውም እርሱ ግን የዚህ (የስልጣን) ፈላጊ አልነበረምና ሌሎች እንዲሾሙበት አድርጉዋል::
ቅዱስ ያዕቆብ በስብከት አገልግሎት ምሥራቁን ዓለም ሲያበራ የተባበሩት ደቀ መዛሙርት ቢኖሩም ያሳለፈው ድካምና መከራ ግን ተወዳዳሪ አልነበረውም:: በተለይ የወቅቱ የአንጾኪያ ኃያላን መኩዋንንትና ሹመኛ መናፍቃን ብዙ አሳደውታል::
እርሱ ግን በጥበብና በፈሊጥ እዚያው ደጃቸው ላይ የነበሩ ምዕመናንን በእረኝነት ጠብቁአል:: ለዚህ ሲባልም ራሱን እየቀያየረ የመሣፍንቱን አጥሮችና ቅጥሮች አልፏል:: ለቤተ ክርስቲያን ክብርም እንደ እብድ : እንደ ሴትም መስሎ የወንጌልን ዘር ዘርቷል::
ከብዙ ፈተናና አገልግሎት በሁዋላም በተወለደ በ78 ዓመቱ (በ578 ዓ/ም) ዐርፎ በክብር ተቀብሯል:: ትልቁ መታሰቢያው የሶርያ ቤተ ክርስቲያን "ያዕቆባዊት" ምዕመኑ "ያዕቆባውያን" መባላቸው ሲሆን እኛ ደግሞ በአንገታችን ላይ እንድናስራት ባስተማረን ማዕተብ (ማኅተም) ዘወትር እናስበዋለን:: ለመጀመሪያ ጊዜ ማዕተብን በአንገት ላይ ስለ ማሰር ያስተማረ እርሱ ነውና::
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages