ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 29 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, July 16, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 29

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምሰኔ ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን ከቆና ገዳም ሰባት ቅዱሳን ሰማዕታት ሆኑ፣ቅዱሳን አባ ሖር አባ፤ አባ በሶይና እናታቸው ይድራ በሰማዕትነት ሞቱ፣ የንጉሥ ዳዊት ልጅ የኢትዮጵያ ንጉሥ ቅዱስ ቴዎድሮስ አረፈ፣ ጻድቅ የሆነ ለሮሜ ንጉሥ ለቅዱስ ማርቆስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ፣ የወሎው ሰማዕቱ አቡነ ዓምደ ሚካኤል ፍልሠተ ዐፅማቸው ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ሰባቱ ቅዱሳን
ሰኔ ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን ከቆና ገዳም ሰባት መስተጋድላን ሰማዕታት ሆኑ። እሊህም አባ አብሲዳ፣ አባ ኮቶሎስ፣ አባ አርድማ፣ አባ ሙሴ ፣ አባ እሴይ፣ አባ ኒኮላስና አባ ብሶይ ናቸው የእግዚአብሔርም መልአክ ተገለጾ እንዲህ ብሎ አዘዛቸው ክብር ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ግለጡ።
ያን ጊዜም ወደ መኰንኑ ሊሔዱ ተነሡ መርከብንም አገኙ በመርከቧም ውስጥ አምስቱን መስተጋድላን አገኙአቸውና ከእነርሱ ጋር ተስማሙ ወደ መኰንኑም ደርሰው በፊቱ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ታመኑ።
መኰንኑም ከእርሳቸው አንዱን ስለ ሀገራቸው ጠየቀው እርሱም ቆና ከሚባል አገር እንደሆኑ አስረዳው መኰንኑም ያሥሩዋቸው ዘንድ አዘዘ። ከዚህም በኋላ ደግሞ ከእሥር ቤት አውጥተው ጽኑ ሥቃይን ያሠቃዩአቸው ዘንድ ደግሞም በአንገቶቻቸው ከባድ ደንጊያዎችን አንጠልጥለው እንዲአሥሩዋቸው አዘዘ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በውህኒ ቤት ውስጥ ተገለጠላቸው አጽናናቸውም ቃል ኪዳንም ገባላቸው። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ወደ እስክንድርያ ከተማ ላካቸው በዚያም ጽኑ ሥቃይን አሠቃዩአቸው።
ከዚህም በኋላ ዝፍትና ድኝ በተመሉ ከሁለት የብረት ምጣዶች ውስጥ ጨመሩአቸው ነበልባሉም ሃያ ክንድ ከፍ ከፍ እስከሚል ድረስ ከታች እሳትን አነደዱባቸው ከምጣዶችም ውስጥ አውጥተው በእሳት ምድጃ ውስጥ ጨመሩአቸው ጌታችንም ዳግመኛ ተገልጾ ያለ ምንም ጉዳት አዳናቸው።
ከዚህም በኋላ ወደ መኰንኑ ቀርበው ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው መቶ ሠላሳ ሰዎች በጌታችን አምነው በሰማዕትነት ሞቱ።
ከዚህም በኋላ አስጨናቂ የሆነ ሥቃይን አሠቃያቸው ወደ እነርሱም አጵሎን የሚሉትን ጣዖት በወንበር እንደ ተቀመጠ አምጥቶ እንዲሰግዱለት አዘዛቸው እነርሱ ግን በእግሮቻቸው ረገጡትና ከመንበሩ ወድቆ ተሰበረ። መኰንኑም አይቶ እጅግ ተቆጣ እግሮቻቸውንም እንዲቆርጡ አዘዘ የቅዱስ ቀሲስ አብሲዳንን ግን ራሱን በሰይፍ ቆረጡትና ምስክርነቱን ፈጸመ እንዲሁ ደግሞ እሊያ አምስቱንም ራሶቻቸውን ቆረጡ ቅዱስ ኮቶሎስን ግን በእሳት አቃጠሉት ሁሉም የሰማዕትነትን አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀዳጁ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱሳን አባ ሖር አባ፤ አባ በሶይና እናታቸው ይድራ
ዳግመኛም በዚህች ቀን ደግሞ ቅዱሳን አባ ሖር፣ አባ ብሶይና እናታቸው ይድራ ከአንጾኪያ ንጉሥ ሠራዊት ውስጥ የሆነ አባ ሖርሳም በሰማዕትነት ሞቱ። እሊህም ወደ እስክንድርያ በደረሱ ጊዜ በመኰንኑ ፊት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ታመኑ መኰንኑም አባ ብሶይን ይዘው ቀኝ እጁንም አሥረው በከተማዎች ሁሉ በበሬዎች እንዲጐትቱት አዘዘ።
ከዚህም በኋላ የተዘረጉ ብረቶችን በእሳት አግለው በሥጋው ውስጥ አደረጉ የግራ እጁንም ቆረጡ እርሳስም አቅልጠው በአፉ ጨመሩ ጊንጦችና እባቦች ወደ ተከማቹበት ውስጥ ጣሉት እነርሱ ግን ከቶ አልቀረቡትም።
ከዚህም በኋላ በብረት በትሮች ይደበድቡት ጀመር እርሱም ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ርዳኝ ከዚህ ሥቃይም አድነኝ ብሎ ጮኸ ጌታችንም አጸናው እንደቀድሞውም ያለ ምንም ጉዳት ጤነኛ አድርጎ አስነሣው።
ከዚህም በኋላ እናቱ ወደርሱ መጥታ አረጋጋችው በመጋደሉም ደስ ተሰኘችበት። ስለ እርሷም ለመኰንኑ ነገሩት እርሱም ወደ እርሱ አስቀርቦ እያስፈራራ ለአማልክት ሠዊ አላት። እርሷ ግን አልፈራችውም ትእዛዙንም አልሰማችም የብረት በትሮችንም አግለው በጎኖቿ ውስጥ እንዲአደርጉ አዘዘ ይህንም በእርስዋ ላይ በአደረጉ ጊዜ ደስ ብሏት ዘመረች ስለ ቅዱስ ስሙም መከራ እንድትቀበል ያደረጋት እግዚአብሔርን አመሰገነችው ከዚህም በኋላ ነፍሷን ሰጠች የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀዳጀች።
ቅዱስ አባ ሖርንም ከቅባትና ከተቀመመ የነዳጅ ቅመም ጋራ በብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት እርሱም ያለ ሕማም ሁኖ እግዚአብሔርን ያመሰግን ነበር ይህንንም ለመኰንኑ ነገሩት እርሱም እጅግ አደነቀ ደነገጠም። ንጉሡ ግን ተቆጣ በእጁም ጦር እንደያዘ ወደ ብረት ምጣዱ ሒዶ ቅዱስ ሖርን ወጋው ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ። እንዲሁም ወንድሙ አባ ብሶይን ብዙ ሥቃይን ካሠቃዩት በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡት። ሁሉም በመንግሥተ ሰማያት የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጁ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ቴዎድሮስ
በዚችም ቀን የንጉሥ ዳዊት ልጅ የኢትዮጵያ ንጉሥ ቴዎድሮስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ በዕውቀትና በተግሣጽ አደገ የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍት የተማረ ደግሞም ቀስት ማፈናጠርንና ፈረስ ግልቢያን ተማረ ኃይል ያለውም ብርቱ ሰው ሆነ።
ከታናሽነቱም ጀምሮ በእግዚአብሔር ፍቅር ታሠረ ገንዘቡን ለድኆችና ለችግረኞች ይመጸውት ነበር። አብያተ ክርስቲያንንም እጅ መንሻ ከመያዝ ጋራ ይጐበኝ ነበረ በጸሎትና በጾምም ይጋደል ነበረ። ካንዲት ሴት በቀር አላገባም በማንም ላይ ዐመፅና ግፍ ከቶ አልሠራም።
ወደ ኢየሩሳሌም ለመሔድ በአሰበ ጊዜ አባ ማርቆስን አማከረው እርሱም በመንፈስ ቅዱስ ያውቅ ነበረና ክፍልህ አይደለም አለው። ከዚህም በኋላ ባረፈ ጊዜ በክረምት ወራት በድኑን ሲወስዱ ሞልቶ የነበረው ወንዝ ወዲያና ወዲህ ተከፍሎ ተሻገሩ በቀበሩበትም ቦታ ሕይወትነት ያለው ውኃ መነጨ እስከ ዛሬም አለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ለቅዱስ ማርቆስ
ዳግመኛም በዚህች ዕለት ንጹሕ ጻድቅ ለሆነ ለሮሜ ንጉሥ ለማርቆስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ። ይህም ቅዱስ በድንግልናው አምስት ዓመት ነገሠ ሕዝቡንም እግዚአብሔርን በመፍራትና በቅን ፍርድ ጠበቀ።
እርሱንም ከመውደዳቸው የተነሣ ሚስትን እንዲአገባ መኳንንቱ አስገደዱት እርሱ ግን በሌሊት ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ፊት ቁሞ ጸለየ እመቤቴ ሆይ ላንቺና ለማይሻር ንጉሥ ልጅሽ እገዛ ዘንድ ወደ ምሔድበት ምሪኝ አላት። እርሷም ወደ ቶርማቅ ተራራ ሒድ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋራ ይኑር አለችው።
ከዚህም በኋላ በሌሊት ወጥቶ ሔደ ወደ ባሕር ወደብም በደረሰ ጊዜ ያለ መርከብ ተሻግሮ ወደ ቶርማቅ ተራራ ደረሰ ያም ቦታ ደረቅ ነበረ ከአጋንንት ጋራም እየተጋደለ በውስጡ ስልሳ ዓመት ኖረ። በአረፈ ጊዜም መላእክት በክብር ቀበሩት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ሰማዕቱ አቡነ ዓምደ ሚካኤል
ዳግመኛም በዚህች ዕለት ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ሰማያዊ መና ሲመግባቸውና የጌታችንንም ቅዱስ ሥና ደም በሰንበት እያመጣለቸው ያቆርባቸው የነበሩት የወሎው ሰማዕቱ አቡነ ዓምደ ሚካኤል ፍልሠተ ዐፅማቸው ነው። ጻድቁ ኅዳር ሦስት በሰማዕትነት ካረፉ በኋላ መጀመሪያ በንጉሥ እስክንድር ዘመነ መንግሥት ወደ አባቶቹ መቃብር ዳግመኛም በንጉሥ ልብነ ድንግል ዘመን በዐረፉ በ40 ዓመታቸው ፈለሰ።
ዐፄ ልብነ ድንግል በነገሠ ጊዜ ዐፅማቸውን አፍልሶ ወደ አትሮንስ ማርያም ወሰደውና በቅዱሳን ነገሥታት መቃብር በክብር አኖረው። (የዕረፍታቸውን ዕለት ኅዳር ሦስትን ይመለከቷል።) አቡነ ዓምደ ሚካኤል ትውልዳቸው ወሎ ቦረና ነው። ወላጆቻቸው ገላውዲዮስና ኤልሳቤጥ ሁለቱም በሃይማኖትና በዓለም ገንዘብ የበለጸጉ ናቸው።
ይህንንም ጻድቅ ልጃቸውን የአርባዕቱ እንስሳ በዓል ዕለት ወለዱትና ስሙን ዓምደ ሚካኤል ብለው ጠሩት። ለዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ፣ ለዐፄ በእደ ማርያምና ለዐፄ እስክንድር የሠራዊት አለቃ የነበረ ጻድቅ ነው። በአንድ ዓመቱ ወላጆቹ ወደ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ይዘውት እንደሄዱ ከወላጆቹ ተለይቶ ጠፍቶ ሳይገኝ ቀረ። መልአክም ከቤተ መቅደስ አግብቶ እየመገበው 3 ቀን አቆይቶታል። በ3ኛው ቀን ቄሱ ሊያጥን ሲገባ በከርሰ ሐመሩ ውስጥ ሕፃኑን አገኘውና ወስዶ ለወላጆቹ ሰጣቸው። ባደገም ጊዜ በመመጽወትና አብያተ ክርስቲያናትን በማደስ የሚተጋ ሆነ። ለድኆችም በቅንነት በመፍረድ በታላቅ ተጋድሎ የሚኖር ሆነ።
ለነገሥታም ገዥ ከሆነ በኋላ በጸሎቱና በበረከቱ በሀገራችን ላይ ሁሉ ሰላም ሆነ። ጠላቶችም ሁሉ ለነገሥታቱ ተገዝተው ይገብሩ ነበር። በበጎ ምግባሩ የቀኑ ዐመፀኞችም በክፋ ተነሡበት። ጻድቁ በመንፈስ አድጎ መንኩሶ በታላቅ ተጋድሎ ሲኖር ነገር ሠሪዎች በሐሰት ወንጅለው ከሰሱት። ንጉሡም እጅግ ስለሚወደው የራራለት ቢሆንም በነገራቸው ባስጨነቁት ጊዜ ወደ ሩቅ አገር አስሮ አጋዘው።
አባታችንም በግፍ ታስረው ሳሉ በእስር ቤቱ ውስጥ ብርሃን ወረደላቸው፣ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልም ሰማያዊ መና እያመጣ ይመግባቸው ነበር። የጌታችንንም ሥና ደም በሰንበት እያመጣለቸው ያቆርባቸው ነበር። ነገረ ሠሪዎቹ ይገድሏቸው ዘንድ ንጉሡን ለመኑት። በዓመፃቸውም ብዛት ወደ ፍርድ ሸንጎ አምጥተው ገደሏቸው። አንድ ጻድቅ መነኩሴ የቅዱስ ዓምደ ሚካኤልን ሥጋ ሦስት ቅዱሳን መላእክት ሲያጥኑ አገኛቸውና ያየውን ለሕዝቡ ተናገረ። በሌላም ጊዜ የብርሃን ፋና ከሰማይ ሲወርድላቸው ብዙ ቀን የተመለከቱ ብዙ ቅዱሳን ምስክርነታቸውን ሰጡ።
ንጉሡም ይህንን ሁሉ ሲሰማ በአሳቾቹ ልበ ደንዳናነትና ክፋት እጅግ ተጸጽቶ በሞት ቀጣቸው። ቅዱስ ዓምደ ሚካኤልንም በአባቶች መቃብር በክብር አስቀበራቸው። ስማቸውንም በበጎ እንጂ በክፋ ማንም እንዳያነሳቸው በአዋጅ አስነገረ። መታሰቢያም አቆመላቸው። ከዚህም በኋላ ዐፄ ልብነ ድንግል በነገሠ ጊዜ የአባቱን የበእደ ማርያምን ቃል ኪዳን ሰምቶ ዐፅማቸውን አፍልሶ ወደ አትሮንስ ማርያም ወሰደውና በቅዱሳን ነገሥታት መቃብር በክብር አኖረው። ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋም ጻድቁ ሲያርፉ በደብረ ሊባኖስ ገዳም የተቀበሩ ቢሆንም ከብዙ ዘመን በኋላ ዐፅማቸውን አፍልሰው በተድባበ ማርያም እንደቀበሯቸው ጽፈዋል።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages