በታላቁ ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የተፈፀመውን ጥቃት አስመልክቶ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በተገኙበት ከመንግሥት አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡
++++++++++++++++++++++++++++++++
በጥንታዊውና ታሪካዊ ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የተፈፀመውን የመነኮሳት ግድያ አስመልክቶ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት በምሥራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ መሪነት ተካሂዷል።
በግፍ የሰማዕትነትን ጽዋ የተቀበሉ አባቶች መርዶ በትናንትናው ዕለት የተሰማ ሲሆን በመላው ዓለም የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ሀዘናቸውን በመሪር እንባ እየገለጹ ይገኛሉ።
የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከትም ከገዳሙ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በትኩረት ጉዳዩን ሲከታተል የቆየ ሲሆን በዛሬ ዕለትም በቢሾፍቱ ከተማ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ አየር ኃይል ግቢ ዐራት ሰዓታትን የፈጀ ሰፊ ውይይት ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በውይይቱ የተቀመጡ የመፍትሔ ሃሳቦች፡-
1ኛ፡- በመንግሥት የፀጥታ አካላት አማካኝነት የሰማዕታቱን አስክሬን ከወደቁበት አንስቶ በክብር ወደ ገዳሙ በማምጣት ሥርዓተ ቀብር እንዲፈፀምላቸው
2ኛ- በቋሚነት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊትና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጸጥታ መዋቅር ገዳሙንና ገዳማውያንን በዘላቂነት መጠበቅ እንዲቻል
3ኛ፡- በመንግሥትና በሀገረ ስብከቱ እንዲሁም በቤተክርስቲያን አባቶች ልባቸው የተሠበረና የተጎዱ የገዳሙ አባቶችና እናቶችን በጋራ ማጽናናት እንዲችል፡፡
የውይይቱ የውሳኔ ሃሳቦች ሲሆኑ ይኼው ግብረ ኃይል ከሀዘኑ በኋላ ዳግም ተገናኝቶ በተሠሩ ሥራዎችና ወደ ፊት አስተማማኝ ሰላም በሚሠፍንበት ጉዳይ ላይ ለመመካከር ቀጠሮ ተይዞ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የዕለቱ ውይይት በጸሎት ተዘግቷል፡፡
ዘገባው የሀገረ ስብከቱ ሐመረ ተዋሕዶ ሚዲያ ነው
ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።
በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሮሜ 8፥37
No comments:
Post a Comment