የክርስቶስ ስቅለት በመጋቢት 27 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, April 16, 2020

የክርስቶስ ስቅለት በመጋቢት 27


 

ነገረ ክርስቶስ ክፍል አንድ ከሚለው 622 ገጽ ካለው መጽሐፌ በጥቂቱ የተወሰደ
የነገሥታት ንጉሥ የሕይወት ራስ ኢየሱስ ክርስቶስን ጭፍሮች የእሾኽ አክሊል ጐንጒነው በራሱ ላይ ደፍተውለታል፤ የእሾኽ አክሊል በመቀዳጀቱ በዘፍ ፫፥፲፰ ላይ አዳምን አስቀድሞ “ምድር እሾኽንና አሜከላን ታበቅልብኻለች” ብሎት ነበርና ያነን መርገም ደምስሶለት ለአዳም ክሷል፡፡

ዳግመኛም አዳምና ሔዋን ምክረ ከይሲን ሰምተው የድል ነሺዎች አክሊል ተለይቷቸው ነበርና ያነን ሰማያዊ አክሊል እንደመለሰልን ለማጠየቅ፡፡ ይኽ ለካሳ አምላካችን ስለፈጸመው የድኅነት ምስጢር ቅዱሳት ደናግል በጥልቀት እንዲኽ አብራርተዋል፡-
☞ “አስተቀጸልዎ ከመዝ ለርእሰ ሕይወት አክሊለ ሦክ …” (የሕይወት መገኛ ርሱን የእሾኽ አክሊልን አቀዳጁት፤ መላእክትን የብርሃን ራስ ቁር የሚያቀዳጃቸው የነገሥታት ገዢ የሚኾን ርሱን የሾኽ አክሊል አቀዳጁት፤ በሾኽ አክሊልም ከራሱ ክፍል ያቆሰሉት ሺሕ ናቸው፤ ከራሱም ቊስሎች ደም እንደ ውሃ በዝቶ ፈሰሰ፤ ፊቱም ደምን ለበሰ ሰውነቱም በደም ተጠመቀ፤ የጽዮን ልጆች እናቱ ያቀዳጀችውን አክሊል ተቀዳጅቶ አዩት፤ ተድላ ደስታ የሚያደርግበትና የሙሽርነቱ ቀን ነውና (መሓ ፫፥፲፩) … ነገር ግን የሾኽ አክሊልን በመቀዳጀቱ በምድራችን ላይ የበቀሉትን አሜከላና እሾኽ ርግማንን አጠፋልን (ዘፍ ፫፥፲፰)፤ ራሱንም በዘንግ በመመታቱ የታላቁን እባብ ሰባቱን ራሶቹን ዐሥሩን ቀንዶቹን አጠፋልን (ራእ ፲፫፥፩)) ብለዋል፡፡

ሊቁ ቅዱስ ኤራቅሊስም ስለፈጸመው ካሳ እንዲኽ አስተምሯል፡-
☞ “እንዘ ይትቄጸል አክሊለ ሦክ አብጠለ ኲነኔሁ ለቀኖተ ሞት ወእንዘ ቅንው ዲበ ዕፀ መስቀል ኢተዐርቀ እምነ መንበሩ…” (የእሾኽ አክሊል ደፍቶ የሞትን ሥልጣን ፍርድ አጠፋ፤ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ ሳለ ከዙፋኑ አልተለየም፤ ከባሕርይ አባቱ ከአብ፤ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አልተለየም፤ በምድር አይሁድ እንደ በደለኛ ሲዘብቱበት፤ መላእክት በሰማይ የከበረ ጌትነቱን ይናገሩ ነበር) (ቅዱስ ኤራቅሊስ)

እጆቹና እግሮቹ ስለመቸንከሩ አስቀድሞ በነቢዩ ዳዊት ዐድሮ በመዝ ፳፩፥፲፮ ላይ “ብዙ ውሾች ከብበውኛልና የክፋተኞች ጉባኤም ያዙኝ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ፤ ዐጥንቶቼ ኹሉ ተቈጠሩ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም” በማለት ውሻ ከአፉ ያወጣውን መልሶ ለምግብነት እንዲፈልገው፤ አይሁድም ኦሪትን እለፊ ካላት በኋላ ሲሠሯት በመገኘታቸው በውሻ መስሎ ትንቢት ያናገረባቸው ሲኾን፤ ይኽም ሊፈጸም ንጹሓት እጆቹና እግሮቹ በምስማር ከዕፀ መስቀሉ ጋር አያይዘው ቸንክረውታል፡፡

የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ሔዋን በእግሮቿ ወደ ዕፀ በለስን በማምራቷ በድላ ነበርና ለርሷ ካሳ ሊኾን ንጹሓን እግሮቹ ሲቸነከሩ፤ በእጆቿም በለስን በመቊረጧ ንጹሐ ባሕርይ አምላክ እጆቹ በችንካር ተቸንክረዋል፡፡ በመቸንከሩም ለ፭ሺሕ ፭፻ ዘመን በሰው ልጆች ላይ የሠለጠነ የሞት ችንካር ጠፍቶልናል፡፡
ምስጋና ይግባውና ኢየሱስ ክርስቶስ በመቸንከሩ ስለፈጸመው ካሳ ደናግል ሲተነትኑ፡-
☞ “ወበቅንዋቲሁ ሠበረ ለነ ቀኖተ ሞት …” (በመቸንከሩም የሞት ችንካርን አጠፋልን፤ ሔዋን በእግሮቿ ወደ ዕፀ በለስ ስለ ተመላለሰች እጆቹንና እግሮቹን በመቸንከር ከፍሏልና፤ በእጆቿም የበለስን ፍሬ ስለቈረጠች ፈንታ በእውነት የእግዚአብሔር ቃል በሥጋው ከመስቀል ዕንጨት ጋራ ተቸነከረ) በማለት አስተምረዋል፡፡

መተርጒማን ሊቃውንት እንዳመሰጠሩት ጌታ በዕንጨት መስቀል ላይ መሰቀሉ ስለምን ነው ቢሉ?፤ እሾኽ በሾኽ ይነቀሳል ነገር በነገር ይወቀሳል እንዲሉ በዕፀ በለስ ምክንያት የገባውን ኀጢአት በዕፅ ለማውጣት በዕፀ መስቀል ላይ ተሰቅሏል፡፡
ጌታችን ከምድር ከፍ ከፍ ብሎ ስለምን ተሰቀለ? ቢሉ
“እምከመ ተለዐልኩ እምድር እስሕብ ኲሎ ኀቤየ” (ከምድር ከፍ ከፍ ባልኊ ጊዜ ኹሉን እስባለኊ) ብሎ ነበርና ይኽነን ሊፈጽም ነው (ዮሐ ፲፪፥፴፪)፡፡
ዳግመኛም ከምድር ከፍ ከሰማይ ዝቅ ብሎ መሰቀሉ “ኅሩይ ማእከለ እግዚአብሔር ወሰብእ” እንዲል አምላክ ወሰብእ ኾኖ እንዳስታረቀን ለማጠየቅ፡፡
በመጨረሻም ምድርን በኪደተ እግሩ እየተመላለሰ እንደ ቀደሳት፤ ዐየራትን ደግሞ ሥብ እያጤሱ አስተራኲሰውት ነበርና አየራትን ለመቀደስ ነው፡፡

ንጹሐ ባሕርይ ጌታችንን አይሁድ መስቀሉን አሸክመው ቀራንዮ ወደሚባል ቦታ ከወሰዱት በኋላ ኹለት ወንበዴዎችን በቀኝና በግራ አድርገው ጌታችንን በመኻከል ሰቅለውታል (ማቴ ፳፯፥፴፰፤ ማር ፲፭፥፳፯፤ ሉቃ ፳፪፥፴፫፤ ዮሐ ፲፱፥፲፰)፡፡
ክፉዎች አይሁድ ይኽነን ያደረጉበት ምክንያት በክፋት ነው፤ ይኸውም በቀኝ የሚመጡ ሰዎች በቀኝ የተሰቀለውን ወንበዴ አይተው “ይኽ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ወንበዴ ነው” ይሏቸዋል፤ ከዚያም ጌታን “ይኽስ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ይኽስ ከርሱ ልዩ ነውን አንድ ነው እንጂ” ብለው ሰዎችን ለማሳሳት፤ በግራ የሚመጡ ሰዎች በግራ የተሰቀለውን ወንበዴ አይተው “ይኽ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ወንበዴ ነው” ይሏቸዋል፤ ከዚያም ጌታን “ይኽስ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ይኽስ ከርሱ ልዩ ነውን አንድ ነው እንጂ” ብለው ሰዎችን ለማሳሳት ያደረጉት ነው፡፡
ዳግመኛም አነገሥንኽ ብለውታልና ቀኛዝማች ግራዝማች ሾምንልኽ ለማለት ለመዘበት፡-
በተጨማሪም ነቢዩ ኢሳይያስ በምዕ ፶፫፥፲፪ ላይ “ከዐመፀኞችም ጋር ተቈጥሯልና” የሚለው ትንቢቱን ሊፈጽም ሲኾን ምስጢሩ ግን እኛን ከጻድቃን ጋራ አንድ ያደርገን ዘንድ ርሱ ከበደለኞች ጋር ተቈጥሯል፤ ሌላውም በዕለተ ምጽአት እኛን ኃጥኣንን በግራ ጻድቃንን በቀኝ ታቆማለኽ ሲያሰኛቸው ነበር (ማቴ ፳፭፥፴፫፤ ራእ ፩፥፯)፡፡

በኹለት ወንበዴዎች መኻከል ከሰቀሉት በኋላ ጲላጦስም “የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ጽሕፈት በዕብራይስጥና በሮማይስጥ በግሪክም ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረው፤ (ዮሐ ፲፱፥፲፰-፳፪)፤ የአይሁድ ካህናት አለቆች ጲላጦስን “ርሱ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ እንዳለ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለኽ አትጻፍ” ሲሉት፤ ጲላጦስም “የጻፍኹትን ጽፌአለኊ” ብሎ መልሶላቸዋል፤ ይኽነንም በሕማማት ድርሳኑ ላይ ሲተረጒሙት፡- “ወዝ መጽሐፈ ጌጋይ ዘጸሐፎ ጲላጦስ ወአንበሮ መልዕልተ ርእሱ ይደምስስ ለነ በኲሉ ጊዜ መጽሐፈ ዕዳነ ዘጸሐፉ አጋንንት” (ጲላጦስ ጽፎ ከራሱ በላይ ያኖረው በደሉን የሚናገር ይኽ መጽሐፍ ኹልጊዜ አጋንንት የጻፉትን የዕዳችንን መጽሐፍ ያጠፋልን ዘንድ ነው) በማለት አራቅቀው ገልጠዋል፡፡

ጌታችን በሚሰቀልበት ጊዜ ብርሃን ያለበሳቸውን አምላክ ዕርቃኑን ለመሰወር ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ፀሓይና ጨረቃ ብርሃናቸውን ነሥተዋል (ማቴ ፳፯፥፵፭፤ ማር ፲፭፥፴፫፤ ሉቃ ፳፫፥፵፬-፵፭)፡፡
ይኽ በጌታ ስቅለት ዕለት እንደሚደረግ አስቀድሞ በነቢዩ አሞጽ ኹለት ጊዜ በትንቢት ተነግሯል፡- ይኸውም
“የእግዚአብሔር ቀን ብርሃን ሳይኾን ጨለማ አይደለምን? ጸዳል የሌለውም ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን?” (አሞ ፭፥፳)
በዚያም ቀን ፀሐይ በቀትር እንድትገባ አደርጋለኊ ይላል ጌታ እግዚአብሔር በብርሃንም ቀን ምድሩን አጨልማለኊ” (አሞ ፰፥፱) ተብሎ
በዕለተ ዐርብ በጌታችን ስቅለት ዕለት ስለተደረገው ስለዚኽ ታላቅ ተአምር ሊቃውንት እንዲኽ ይገልጹታል፡-
☞ “ጐየ ፀሓይ ወጸልመ ወርኅ ወከዋክብትኒ ተኀብኡ ከመ ኢያብርሁ ለምእመናን በጊዜ ስቅለቱ ቅዱስ እንዘ ፍጹም በገሃሁ ወርኅ ኢያብርሀ…” (ፀሓይ ብርሃኑን ነሣ ጨረቃም ጨለመ፤ ከዋክብትም በከበረ ስቅለቱ ጊዜ ለምእመናን እንዳያበሩ ብርሃናቸውን ነሡ፤ ጨረቃም በምልአቱ ሳለ አላበራም፤ ፀሓይ ብርሃኑን በነሣ ጊዜ ፍጡራን ኹሉ በጨለማ ተያዙ፤ የፈጠራቸው ፈጣሪያቸው እንደ ሌባ እንደ ወንበዴ በዕንጨት ላይ ተሰቅሎ እንዳያዩ ቀኑ ጨለመ፤ ባለሟሉ መልአክም ከሓድያንን ያጠፋቸው ዘንድ ሰይፉን በእጁ መዝዞ ይዞ ከመላእክት መኻከል ወጣ፤ የክርስቶስም ቸርነት በከለከለችው ጊዜ ያ መልአክ የቤተ መቅደሱን መጋረጃ በሰይፉ መታው ቀደደውም፤ ከላይ እስከ ታችም ወደ ኹለት አደረገው (ማቴ ፳፯፥፶፩፤ ማር ፲፭፥፴፰፤ ሉቃ ፳፫፥፵፭)፤ መላእክትም ኹሉ በሰማይ ኹነው ርሱን አይተው በአንድነት ሲቈጡ የአብ ምሕረቱ፣ የወልድ ትዕግሥቱ፣ የመንፈስ ቅዱስ ቸርነቱ ከለከለቻቸው፤ ፀሓይ ብርሃኑን ነሣ፤ በጨለማ ተይዞ ሲድበሰበስ ዓለምንም ተወው፤ ይኽ ኹሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ከሥጋው ከመለየቱ አስቀድሞ ተደረገ) (ቅዱስ አትናቴዎስ)
☞ “እስመ ሶበ ተሰቅለ ክርስቶስ ጸልመ ሰማይ አሜሃ ወፀሓይኒ ሰወረ ብርሃኖ ወወርኅኒ ደመ ኮነ…” (ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ ያን ጊዜ ሰማይ ጨለማ ኾነ፤ ፀሓይም ብርሃኑን ነሣ፤ ጨረቃም ደም ኾነ፤ ምድርም ተነዋወጠች ደንጊያውም ተከፈለ፤ መቃብራትም ተከፈቱ፤ ስለዚኽም ለፍጡራን ከፈጣሪያቸው ጋር ሊታመሙ ተገባቸው (ማቴ ፳፯፥፵፭-፶፩) (ቅዱስ ሱኑትዩ)

☞ “ፀሓይ ጸልመ ወወርኅ ደመ ኮነ ወከዋክብት ወድቁ ፍጡነ ከመ ኢይርአዩ ዕርቃኖ ለዘአልበሶሙ ብርሃነ” (ፀሓይ ጨለመ፤ ጨረቃም ደም ኾነ፤ ከዋክብትም ፈጥነው ወደቁ፤ ብርሃንን ያጐናጸፋቸውን የጌታን ዕርቃን እንዳያሳዩ) (አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ)
ሊቁ አባ ጊዮርጊስም ምስጢሩን በመጠቅለል በሕማማት ሰላምታው ላይም፡-
“ፀሓይ ብሩህ አሜሃ ጊዜ ቀትር ጸልመ
ወወርኅኒ ጽዱል ተመሰለ ደመ
ትንቢት ከመ ቀደመ፤ ስብሐት ለከ”
(ብሩህ የኾነ ፀሓይ ያን ጊዜ በቀትር (በስድስት ሰዓት) ጨለመ፤ ጽዱል የኾነ ጨረቃም ደምን መሰለ፤ አስቀድሞ ትንቢት እንደተነገረ፤ ጌታ ሆይ ምስጋና ይገባኻል) በማለት ከትንቢተ ነቢያት በመነሣት በዚኽ በስድስት ሰዓት ምስጋናው ላይ በሰዓቱ ከተከናወነው ምስጢር በመነሣት አስተምሯል፡፡

በመስቀል የተሰቀለው የክብር ባለቤት ሰማይን የፈጠረ ነውና በሰማይ ከላይ የተጠቀሱት ተአምራት ሲደረጉ ምድርንም የፈጠረ ነውና በምድር ደግሞ አራት ተአምራት ማለት የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለኹለት ተቀደደ፤ ምድር ተናውጣ ዐለቶች ተሠንጥቀዋል፤ መቃብራት ተከፍተዋል፤ ከ፭፻ በላይ ሙታን ተነሥተዋል (ማቴ ፳፯፥፵፭፤ ፳፯፥፶፩፤ ፳፯፥፶፪-፶፫)፡፡

ከዚኽ በኋላ የተነገረው ትንቢት ኹሉ እንደተፈጸመ አይቶ የሕይወት ውሃ ምንጭ ጌታ ከእኛ ጽምዐ ነፍሳችንን ለማራቅ በፈቃዱ “ተጠማኊ” ባለ ጊዜ ነቢዩ ዳዊት አስቀድሞ በመዝ ፷፰፥፳፩ ላይ “ወወደዩ ሐሞተ ውስተ መብልዕየ ወአስተዩኒ ብሒአ ለጽምእየ” (በምግቤ ሐሞት ጨመሩበት፤ ለጥማቴም ኾምጣጤ አጠጡኝ) በማለት የተናገረው ትንቢት ሊደርስ ሊፈጸም አይሁድ በዚያም ኾምጣጤ የመላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበርና እነርሱም ኾምጣጤውን በሰፍነግ መልተው በሁስጱም አድርገው በአፉ ውስጥ ጨምቀውለታል፡፡
በመጠማቱም ከእኛ ጽምዐ ነፍስን አርቆልናልና፤ መራራ ሐሞትን በመቅመሱ ከሰው ልጆች ላይ መራራው ሞት ጠፍቷል፡፡

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በሰባቱ ጊዜያት የጸሎት መጽሐፉ ላይ፤ ጌታችን ሐሞትንና ከርቤን መጠጣቱ ስለምን እንደኾነ፡-
“ከመ ታስትየነ ለነ ደመ ገቦከ ነባቤ
እንተ አስተዩከ ሐሞተ ወከርቤ
ጸማእኩ በጊዜ ትቤ፤ ስብሐት ለከ”
(ነባቢ የሚኾን የጐንኽን ደም ታጠጣን ዘንድ ተጠማኊ ባልኽ ጊዜ ሐሞትን ከርቤን ያጠጡኽ ጌታ ምስጋና ለአንተ ይገባል) በማለት ገልጦታል፡፡

ቅዱሳን ደናግልም መራራ ሐሞትን ጌታችን በመቅመሱ ለ፭ሺሕ ፭፻ ዘመን የሠለጠነ መራራ ሞት ከሰዎች ስለመወገዱ፡-
“ወሰሪቦ እግዚእ ኢየሱስ ብኂዐ ይቤ ተፈጸመ ኲሉ…” (ጌታችን ኢየሱስ መጣጣውን ቀምሶ በመጽሐፍ የተጻፈው ኹሉ ደረሰ ተፈጸመ አለ፤ በጒረሮው መጠማትና በአንደበቱ መድረቅ ከሥጋና ከነፍስ መጠማት አዳነን፤ በቀትርም ጊዜ የዝኆን ሐሞትና ከርቤ የተቀላቀለበት መጻጻንና የበግ ሐሞትን በመጠጣቱ የጣፈጠ የበለስ ፍሬን ስለ በሉ ስለ አዳምና ስለ ሔዋን ከፈለ፤ ለእኛም መሪር የኾነ ሞትንና ርግማንን አጠፋልን) በማለት ተንትነው ጽፈዋል፡፡
ነገረ ክርስቶስ ክፍል አንድ ከሚለው 622 ገጽ ካለው መጽሐፌ በጥቂቱ የተወሰደ
በመስቀል ተሰቅለኽ ፈያታዊ ዘየማንን ያሰብከው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በቸርነትኽ ዐስበን፡፡
በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages