ኦርቶዶክሳዊ የመዳን ትምህርት (ነገረ ድኅነት) ክፍል አንድ - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Monday, September 19, 2022

ኦርቶዶክሳዊ የመዳን ትምህርት (ነገረ ድኅነት) ክፍል አንድ

 be

ድኅነት (መዳን)


በመጽሐፍ ቅዱስ መዳን ተብለው የተገለጹ የተለያዩ ነገሮችን እናገኛለን፡፡ ከእነዚህም ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡


·         ኖኅና ቤተሰቦቹ በመርከብ አማካይነት ከጥፋት ውኃ መዳናቸው፣

·         እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነጻ መውጣታቸው እና በባሕር መካከል በደረቅ መሸጋገራቸውና ሲከተሏቸው ከነበሩት ጠላቶቻቸው እጅ መዳናቸ፣

·         ንዕማን ሶርያዊ ከነበረበት ለምጽ በዮርዳኖስ ውኃ ታጥቦ መዳኑ፣

·         እስራኤላውያን በንጉሡ በሕዝቅያስ ዘመን ከሰናክሬም እጅ በተአምራት መዳናቸው፣


ሆኖም እነዚህ ሁሉ መዳኖች (ድኅነቶች) ለጊዜው ድኅነቱ የተደረገላቸውን ሰዎች ያስደሰቱና ከመከራ ያዳኑ ነገሮች ቢሆኑም ሁሉም ጊዜያዊና ድኅነታቸው በሥጋና በዚህ ዓለም የተወሰነ ነበር፡፡ ይህም ማለት የሰውን ልጅ መሠረታዊ ችግር ያልፈታ፣ ሰውን ከተፈረደበት የሞት ፍርድ ያላዳነ፣ በሰው ልጅ የተጎሳቆለ ሕይወት ላይ ይህ ነው የሚባል መሠረታዊና ተጨባጭ ለውጥ ያላመጣ ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚያ የማዳን ድርጊቶች እግዚአብሔር በልጁ ሰው መሆንና መገለጥ በጊዜው ጊዜ ይፈጽመው ዘንድ ያለውን አማናዊ ድኅነት በጥላነት (በምሳሌነት) የሚያመለክቱ የተስፋ ጭላንጭሎች ነበሩ፡፡


1.1             ድኅነት ማለት ምን ማለት ነው?


ድኅነት ስንል በኃጢአት ምክንያት የወደቀውና የጎሰቆለው የሰው ልጅ ከደረሰበት ድቀትና ሞት ሙሉ በሙሉ ነፃ መውጣቱንና አጥቶት የነበረውን ጸጋ ማግኘቱን፣ መጀመሪያ ከመበደሉ በፊት ወደ ነበረበት ሁኔታ (ከዚያም ወደ በለጠ ደረጃ) መመለሱን ማለታችን ነው፡፡ የመዳን ትምህርት (ነገረ ድኅነት)[1] የቤተ ክርስቲያን ትምህርት መሠረትና የመዓዝን ድንጋይ ነው፡፡ ማንኛውም አስተምህሮና ሐሳብ የሚመዘነውና የሚለካው በነገረ ድኅነት መሠረት ነው፡፡ ከነገረ ድኅነት ጋር የሚጋጭና የሚቃረን ትምህርት ሁሉ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም፡፡ የአንድ ትምህርት ወይም አስተሳሰብ ይዘትና አካሄድ ሲተነተን የሰውን መዳን ከንቱ ወደሚያደርግና “የሰው ልጅ አልዳነም” ወደሚል አቅጣጫ የሚወስድ ከሆነ የተለየና የተወገዘ ነው፡፡ ስለሆነም ከሐዋርያት ጀምሮ ከዚያ በኋላ የተነሡ ቅዱሳን ሊቃውንት የመናፍቃንን አስተሳሰብና ትምህርት ሲመዝኑና ከንቱነቱንና ስህተትነቱን ሲያጋልጡ የኖሩት በነገረ ድኅነት ማንጠሪያነትና መመዘኛነት እያጣሩና እየመዘኑ ነበር፡፡


“የሰው ልጅ ዳነ” ስንል በአጠቃላይ የሚከተሉትን ያካትታል፡፡


1.      ተፈርዶበት የነበረው የሞት ፍርድ ተወገደለት፣ ተነሥቶት (ተወስዶበት) የነበረው ሕይወት ተመለሰለት ማለታችን ነው፡፡


የሰው ልጅ “በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ” ተብሎ አስቀድሞ ተነግሮት የነበረው የሞት ማስጠንቀቂያ በገቢር ተፈጽሞበት፣ በሰውነቱ ላይ ሞት ነግሦበት የሞት ተገዢ ሆኖ ነበር፡፡ ዘፍ. 2:17 በሕይወተ ሥጋ እያለም ኑሮው በጽላሎተ ሞት (በሞት ጥላ ሥር) ውስጥ የወደቀና በሞት በፍርሃት የታጠረ፣ ሲሞትም ነፍሱ በጻዕር ተለይታ ሥጋው ወደ መቃብር ነፍሱ ወደ ሲዖል በመውረድ በጭንቅና በመከራ ይኖር ነበር፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የሚስማማውን የእኛን ሥጋ በመዋሓድ ሞታችንን ሞቶ በሞቱ ሞትን አጠፋልን፣ የእርሱን ሕይወት ለእኛ ሰጠን፣ ሞትን በትንሣኤ ለወጠልን፣ የመቃብርን ይዞ የማስቀረትና ሰውነታችንን የማፍረስና የመለወጥ ኃይል ድል በማድረግ በመቃብር ተይዞ ፈርሶ በስብሶ መቅረትን አጠፋልን፡፡


በብሉይ ኪዳን የነበሩ ወገኖቻችን የሚኖሩት በሞት ፍርሃት ነበር፡፡ ሲሞቱም በጻዕርና በመከራ ነበር፡፡ ነቢዩ ዳዊት ይህን በዚያን ዘመን የነበረውን ፍርሃተ ሞት ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡-


“ወደንገጸኒ ልብየ በላዕሌየ ወመጽአኒ ድንጋፄ ሞት ፍርሃት ወረዓድ አኃዘኒ ወደፈነኒ ጽልመት ወእቤ መኑ ይሁበኒ ክንፈ ከመ ርግብ እስርር ወአእርፍ - ልቤ በላዬ ተናወጠብኝ፣ የሞት ድንጋጤም ወደቀብኝ፣ ፍርሃትና እንቅጥቅጥ መጡብኝ፣ ጨለማም ሸፈነኝ፣ በርሬ ዐርፍ ዘንድ እንደ ርግብ ክንፍን ማን በሰጠኝ?” መዝ. 54:4-7፡፡


ልበ አምላክ የተባለ ዳዊት በመዝሙሩ እንዲህ አድርጎ የገለጸው በዘመነ ኦሪት ሰው ሁሉ ሞትን ከመፍራቱ የተነሣ ፍርሃተ ሞት ሲያስጨንቀውና ልቡ ሲደነግጥበት የነበረ መሆኑንና ከዚያም የተነሣ ከሞት ፊት ለመደበቅ “በርሬ ዐርፍ ዘንድ ክንፍን ማን በሰጠኝ?” እስከ ማለት ድረስ መሄጃ ያጣና የተጨነቀ የነበረ መሆኑን ነው፡፡ ይህን የሰውን ልጅ ሲያስፈራና ሲያስደነግጥ የኖረውን ሞት ከሥሩ ነቅሎ ያጠፋልንና ያስወግድልን ዘንድ ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ ለእርሱ ይሁንና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆነልን፡፡ ሐዋርያው “. . . እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፣ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፣ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነፃ እንዲያወጣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ” አለ፡፡ ዕብ. 2:14-15


ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ የቃልን ሥጋ መሆን በተናገረበት ድርሳኑ ስለዚህ ሲናገር እንዲህ አለ፡-


“በመሞት ካልሆነ በቀር የሰው ሞት ሊወገድ እንደማይችል እግዚአብሔር ቃል ባየ ጊዜ እርሱ በባሕርዩ የማይሞት ስለ ሆነ ስለ ሁሉም መሞት ይችል ዘንድ የሚሞት የእኛን ባሕርይ ተዋሐደ፡፡ የእኛ ባሕርይ ከተዋሐደው ቃል የተነሣ የማይሞት ይሆን ዘንድ፣ መፍረስና መበስበስም በትሣኤ ይጠፋ ዘንድ፡፡ የነሣውን ሥጋ ከበደል ንጹሕ የሆነ መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብና ለሞት በመስጠት ሞትን ከወገኖቹ አስወገደ፡፡ የሞትን ዕዳ ሞትን በመክፈል ከእኛ አስወገደው፡፡ ሞትና ጥፋት የእኛን ሥጋ ከተዋሐደው ከአካላዊ ቃል የተነሣ እኛን ሊገዛና ሊይዝ አልተቻለውም፡፡ የሁሉ ጌታና መድኃኒት መጥቶ ሞትን ድል ባያደርገው ኖሮ የሰው ዘር ጠፊ ነበር፡፡”


ስለሆነም ክርስቶስ በሞቱ ድል ካደረገው ወዲህ ሞት ኃይሉን ያጣ ደካማ፣ የቀድሞ አስፈሪነቱ ቀርቶ በክርስቲያኖች ዘንድ መሳለቂያና ወደ ማያልፈው ዓለም መሄጃ መንገድ ሆኗል፡፡ በዘመነ ክርስትና ሞት ጥፍሩ እንደ ወለቀ፣ ጥርሱ እንደረገፈና ኃይሉ እንደ ደከመ፣ ከዚህም የተነሣ የሕፃናት መጫወቻ እንደ ሆነ አንበሳ፤ እንዲሁም መርዙ እንደ ወጣና ምንም ጉዳት ማድረስ እንደማይችል እባብ ሆኗል፡፡


ሞት በሰው (በአዳም) በኩል መጥቶ በሰው ላይ እንደ ነገሠ በዚሁ መንገድ ሰው በሆነ የእግዚአብሔር ቃል ሞት ተወገደ፡፡ ትንሣኤ ሕይወት ተገኘ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ሞት በሰው በኩል ስለመጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኗልና፡፡ ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና” እንዳለ፡፡ 1 ቆሮ. 15፡21-22


አሁን ሰው የሚሞተው “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” (ዘፍ. 3:20) በሚለው በቀደመው ፍርድ ሳይሆን ለትንሣኤ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ እንደ ቀድሞው ለኩነኔ አንሞትም፤ ነገር ግን ከሞት ተነሥቶ የሁሉን ትንሣኤ እንደሚጠብቅ ሰው በራሱ ጊዜ የሚያደርገውን ትንሣኤ ዘጉባኤን እንጠብቃለን፡፡ 1 ጢሞ. 6፡15


ሐዋርያው “ነገር ግን ሰው፡- ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል፡፡ አንተ ሞኝ፣ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም” በማለት ዘር ካልተዘና በአፈር ውስጥ ካልሞተ ሕያው ሆኖ ለመብቀልና ለማፍራት እንደማይችል ሁሉ የሰው ሞትም እንዲሁ በሐዲስ ሰውነት ለመነሣት መሆኑን አስረዳ፡፡ 1 ቆሮ. 15:35-36 መቃብርም ለዘለዓለም በዚያው ውስጥ ይዞ የሚያስቀረን ሳይሆን እስከ ትንሣኤ ድረስ የምንቆይበትና ከዚያም የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን፣ የሚሞተው የማይሞተውን ለብሶ የሚነሣበት ነው፡፡ በዚያን ጊዜም በኃጢአት ምክንያት ከሰው ተፈጥሮ በኋላ የመጣው “የኋለኛው ጠላት” - “ሞት” - ድል ይነሣል፡፡ 1 ቆሮ. 15:26 እሳት የሚኖረው የሚቃጠል ነገር እስካለ ድረስ ብቻ እንደ ሆነ ሁሉ ሞትም ከትንሣኤ በኋላ የሚሞት ሰውነት ስለማይኖር ራሱ “ይሞታል”፤ ለዘለዓለም ይጠፋል፡፡ ይህን ነው ሐዋርያው በመልእክቱ እንዲህ በማለት የገለጸው፡-


“… ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፣ እኛም እንለወጣለን፡፡ ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ፣ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና፡፡ ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ፣ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ በዚያን ጊዜ፡- ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል፡፡” 1 ቆሮ. 15:51-55


2.      ወደ እግዚአብሔርና ቅዱሳን አንድነት ተመለሰ፣ ሰላምን አገኘ


ሰው ከእግዚአብሔር አንድነት ተለይቶ የተስፋ ቦታውን አጥቶ ከዓለመ መላእክት ወደ ዓለመ እንስሳት ተጥሎ ነበር፡፡ ክብር ምስጋና ይግባውና አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሰው ሆኖ ሰው ወደ ወደቀበት ወደዚህ ዓለም በመምጣትና በእንስሳት በረት በመወለድ የሰውን ልጅ ወደ ራሱ ኅብረትና አንድነት መለሰው፡፡ በዚህም መላእክት ከሰዎች ጋር በአንድነት፡- “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ - ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት ይሁን፣ ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” በማለት ሰው ወደ እግዚአብሔር በመመለሱ ደስታቸውን ገለጹ፡፡ ሉቃ. 2፡14


በመስቀሉ ቤዛነትም በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጠብ ግድግዳ ፈረሰ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በላከው መልእክቱ ይህን እንዲህ ሲል ገልጾታል፡-


“ሁለቱን ያዋሐደ፣ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በሥጋው ያፈረሰ እርሱ ሰላማችን ነውና፡፡ …. ይህም ከሁለታቸው አንድ አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ፣ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፣ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፡፡ መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፣ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምሥራች ብሎ ሰበከ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና፡፡” ኤፌ. 2:14-18


ክርስቶስ ስላማችን ብቻ አይደለም፤ ይህን ሰላም ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት አመጣ እንጂ፡፡ ሰው ከፈጣሪው ጋር ከተጣላበት ጊዜ ጀምሮ ሐዘን የከበበውና የተቅበዘበዘ ነበር፡፡ ነቢዩ በትንቢት “ሜጥከ ላሕየ ወአስተፍሣሕከኒ ሠጠጥከ ሠቅየ ወሐሤተ አቅነትከኒ - ልቅሶዬን በደስታ ለወጥክልኝ፣ ማቄን ቀደድህ፣ ደስታንም አስታጠቅኸኝ” ብሎ እንደ ተናገረ ሐዘኑን አስወግዶ ደስታን ሰጠው፡፡ መዝ. 29:10፡፡ መድኃኒታችን “ሰላሜን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ” አለ፡፡ ዮሐ. 14:27፡፡ ይህንም በመስቀሉ ላይ ባደረገው መሥዋዕትነት አረጋገጠ፡፡


በዚህም ከቅዱሳን አንድነት ደመረን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስ በመስቀሉ ቤዛነት ጥልን ማስወገዱንና ሰላምን ማድረጉን ከገለጸ በኋላ የዚህን ተከታይ ውጤት ሲናገር እንዲህ አለ፡- “እምይእዜሰ ኢኮንክሙ ነግደ ወፈላሴ አላ አንትሙ ሰብአ ሀገሪቶሙ ለቅዱሳን ወሰብአ ቤቱ ለእግዚአብሔር - እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮች እና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም፡፡” ኤፌ. 2:19፡፡ እንዲሁም በዕብራውያን መልእክቱ ይህንኑ በተመለከተ ማለትም የሰውን ወደ ቅዱሳን አንድነት መመለስ ሲናገር እንዲህ አለ፡-


“ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ተራራ ደርሳችኋል፣ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፣ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፣ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፣ የሁሉም ዳኛ ወደ ሆነ ወደ እግዚአብሔር፣ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፣ የአዲስ ኪዳንም መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ … ደርሳችኋል፡፡” ዕብ. 12:22-24


ጌታችንም ሰው አስቀድሞ በመብል ምክንያት ከእርሱ ተለይቶ ነበርና በፍጹም ቸርነቱና ፍቅሩ ራሱን መብልና መጠጥ አድርጎ በመስጠት “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ” (ዮሐ. 6:57) በማለት በራሱ መሥዋዕትነት ከእርሱ ጋር ፍጹም አንድነትን ሰጠን፡፡ ከእርሱ ጋር አንድ የምንሆንበትን የቤዛነት ሥራ በመስቀል ላይ ከፈጸመ በኋላ ይህ እስከ ዕለተ ምጽዓት ድረስ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት እንዲቀጥል አደረገ፡፡ </p>

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages