አባ ሕርያቆስ - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, May 24, 2020

አባ ሕርያቆስ

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! 

 ሊቁ አባ ሕርያቆስ 

ሊቁ አባ ሕርያቆስ እመቤታችንን እንዲህ ይላታል
" ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ዘሠምረ ኪያኪ ወቅዱስ ወልድ ዋሕድ ዘኅደረ ውስተ ከርሥኪ ወቅዱስ ጰራቅሊጦስ መንፈሰ ጽድቅ ዘአጽንዐኪ"
ትርጓሜውም፦
" አንቺን የወደደ እግዚአብሔር አብ ቅዱስ ነው በማኅጸንሽ ያደረ ወልድ ዋሕድም ቅዱስ ነው ያጸናሽ የጽድቅ መንፈስ ጰራቅሊጦስም ቅዱስ ነው።"
በተጨማሪም እንዲህ አለ፦" እግዚአብሔር አብ በሰማይ ሆኖ ምሥራቅንና ምዕራብን ሰሜንንና ደቡብን ዳርቻዎችንም ሁሉ በእውነት ተመለከተ ተነፈሰ አሻተተም እንደ አንቺ ያለ አላገኘም የአንቺን መዓዛ ወደደ ደም ግባትሽንም ወደደ የሚወደውን ልጁንም ወደ አንቺ ሰደደ።"
፨ ከሞት ወደ ሕይወት፣ከሲኦል ወደ ገነት የተሸጋገርንባት ድልድያችን ምክንያተ ድኂን ወላዲተ አምላክ ርኅርኅተ ኅሊና ናት፤ አባ የጽጌ ድንግል በድርሰቱ " አኮ ለሰብእ ባሕቲቱ ማርያም ሠናይት እመ ርኅርኅተ ልብ አንቲ ለኩሉ ፍጥረት፤ እመቤታችን ማርያም ሆይ ርኅራኄሽ ለሰው ልጅ ብቻ አይደለም። ይልቁንም ለፍጥረት ሁሉ ርኅርኅተ ልቦና ነሽ " አላት ድንግል ማርያም እናታችን ውሃን ለተጠማ ውሻ በወርቅ ጫማዋ አጠጥታዋለች።
እንዲሁም ታላቁ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በአርጋኖን ድርሰቱ እንዲህ አለ፦ " ለቅድስት ድንግል ምን ያህል ጸጋ ክብር ተሰጣት የማያመሰግናትስ ፍጥረት እንደምን ያለ ነው ክብሯንስ የማይናገር ምን አንደበት ነው፡፡ የማይቀድሳትስ ምን አፍ ነው፡፡ ለክብሯስ የማይገዛ እንደምን ያለ ሰውነት ነው፡፡"
በእውነት ለእርሷ የማይገዛ ትውልድ ምን ዓይነት ትውልድ ነው? አምላክን በማሕጸኗ የተሸከመች ንጽህት አዳራሽ እመቤታችን ምስጋና ይገባታል።
ወላዲተ አምላክ ፍቅሯን በልቦናችን ጣእሟን በአንደበታችን ታሳድርብን+++

 ክርስቲያን ሆኖ እመቤታችንን የሚወድ ሰው ሁሉ ይህንን አባት ያውቀዋል::           አባ ሕርያቆስ ተወልዶ ያደገው በምድረ ግብጽ ሲሆን አካባቢው ብህንሳ (ንሒሳ) ይባላል:: ይህቺ ቦታ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ጨምሮ በርካታ ቅዱሳንን ያፈራች ናት::
አባ ሕርያቆስን በዚህ ዘመን ነበረ ብየ ትክክለኛውን ዓ/ም ለመናገር ይከብደኛል:: ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት መረዳት እንደሚቻለው ግን የነበረበት ዘመን 4ኛው: ወይ 5ኛው መቶ ክ/ዘመን እንደ ሆነ መገመት ይቻላል::
ቅዱሱ በዘመኑ የተለየ ማንነት የነበረው ሰው ነው:: ገና ከልጅነቱ እመ ብርሃንን የሚወዳት በመሆኑ ቅን: የዋህና ገራገር ነበረ:: መቼም እመቤታችንን ይወዳል ሲባል እንደ ዘመኑ በአፍ ብቻ እንዳይመስለን:: ቀንና ሌሊት ለፍቅሯ የሚተጋ: ማዕበለ ፍቅሯ የሚያማታው ሰው ነበር እንጂ::
የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ስም ሲጠራ ምስጥ ብሎ ልቡናው ይሰወርበት ነበር:: ዘወትር የእርሷን ፍቅር ከማሰብ በቀር ሌላ ሥራ አልነበረውም:: የልጅነት ጊዜው ሲያልፍም ድንግልንና ቸር ልጇን ያገለግል ዘንድ መነነ::
ዘመኑ ዘመነ ሊቃውንት እንደ መሆኑ ሁሉም ለትምሕርት ሲተጉ እርሱ ግን ለጸሎትና ለደግነት ብቻ ነበር የሚተጋው:: ከትምሕርት ወገንም የሰሞን ጉዋዞችን: አንዳንድ ቅዳሴያትንና የዳዊትን መዝሙር ተምሮ ነበር::
በተለይ ግን የዳዊትን መዝሙር እየጣፈጠው መላልሶ: መላልሶ ያመሰግንበት ነበር:: ከዳዊት መካከል ደግሞ መዝ. 44ን ፈጽሞ ይወዳት ነበር:: ይህቺ ጥቅስ የምትጀምረው "ጐስዐ ልብየ ቃለ ሠናየ" ብላ ነው:: የውስጧ ምሥጢርም ስለ ድንግል ማርያምና ስለ ክርስቶስ ነው::
አባ ሕርያቆስ ይህቺን መዝሙር በቃሉ አጥንቶ: ቁሞም ተቀምጦም: ተኝቶም ተነስቶም ያለ ማቋረጥ ይላት ነበር:: እየጣፈጠችው "ልቡናየ በጐ ነገርን አወጣ" እያለ ይዘምር ነበር:: በወቅቱ ታዲያ የብህንሳ ኤዺስ ቆዾስ በማረፉ ምትክ ሲያፈላልጉ መንፈስ ቅዱስ አባ ሕርያቆስን መረጠ::
ምንም አለመማሩ ቢያሰጋቸውም "በጸሎቱ: በደግነቱ ሃገር ይጠብቃል" ብለው ሾሙት:: ነገር ግን ምንም በሥልጣን የበላያቸው ቢሆን ተማርን የሚሉ ሰዎች ይጠሉት: ይንቁትም ነበር:: እርሱ ግን እንደ ጠሉኝ ልጥላቸው: እንደ ናቁኝ ልናቃቸው ሳይል በፍቅር ያገለግል ነበር::
አንድ ቀን ታዲያ መንገድ ይወጣል:: በበርሃ ብቻውን እየተራመደ: "ጐሥዐ ልብየ ቃለ ሠናየ" እያለ እየዘመረ: ተመሥጦ ቢመጣበት መንገድ ሳተ:: እርሱ በምስጋናው ሲደሰት እግሩ ግን ከገደል ጫፍ ደርሶ ነበር:: ገደሉን ልብ አላለውም ነበርና ሳይታወቀው ወደ ገደሉ ውስጥ ተወረወረ::
በዚህ ጊዜ ደንግጦ ቢመለከት እጅግ ጥልቅ በሆነ ገደል ውስጥ ራሱን አገኘው:: ነገር ግን አንድም አካሉ አልተነካም:: ልብሱም አልቆሸሸም:: ለራሱ ተገርሞ ዙሪያ ገባውን ሲመለከት እርሱ ቁጭ ያለበት ብርሃንን የተሞላ የልብስ ዘርፍ ነበር::
"እመ ብርሃን!" ብሎ ሲጮህ የሰማይና የምድር ንግሥት የሆነች እመቤታችን ከፊቱ ቁማ ታየችው:: እመ አምላክን በገሃድ ቢያያት እንደ እንቦሳ ዘለለ::
የሚገርመው ደግሞ የተቀመጠበት የድንግል ማርያም የቀሚሷ ዘርፍ ነበር:: እመቤታችን አነጋገረችው: ባረከችው:: ፍቅሯ ቢመስጠው ከሰው ሳይገናኝ: ምግብም ሳይበላ: እዚያው ገደሉ ውስጥ ለ1 ዓመት ያህል በተመስጦ ቆይቷል::
በኋላ እመ ብርሃን መጥታ ከገደሉ አውጥታ ወደ ሐገሩ መለሰችው:: ከጥቂት ጊዜ በኋላም አንድ ፈተና ገጠመው:: አንድ ቀን እመቤታችን በተወለደችበት ግንቦት 1 ቀን ቅዳሴ "ማን ይቀድስ" ሲባል ሰዎቹ "አባ ሕርያቆስ ይሁን" አሉ::
እርሱ ግን "እኔ አይቻለኝም: እናንተ ሊቃውንት ቀድሱ" አላቸው:: "አይሆንም" ብለው እርሱኑ አስገቡት:: ይህንን ያደረጉት ለተንኮል ነበር:: ልክ ወንጌል ተነቦ ፍሬ ቅዳሴ ሲመረጥ እርሱ "እግዚእን (የጌታ ቅዳሴን) ልቀድስ" ቢል እነርሱ "የሚቀደሰው የሊቅ ቅዳሴ ነው" አሉት::
ይህንን ያሉት እርሱ የሊቃውንቱን ቅዳሴ አያውቅምና በሰው ፊት እንዲዋረድ ነው:: እንዲህም ብለው ባለመማሩ ተሳለቁበት:: አባ ሕርያቆስ ግን እያዘነ ወደ መንበሩ ዞረ:: ድንግልንም "እመቤቴ መናቄን: መገፋቴን ተመልከች" አላት::
ወዲያው ግን ድንግል ማርያም ወርዳ ቀጸበችው (ጠራችው):: በዘርፋፋው ቀሚሷ ላይም ረቂቅ የሆነ ቅዳሴን አሳየችው:: ደጉ ሰው ደስ ብሎት "ጐሥዐ ልብየ" ሲል ሁለቱ እግሮቹ ከመሬት ከፍ አሉ:: እርሱም "ወአነ አየድእ ቅዳሴሃ ለማርያም" ብሎ እስከ ኃዳፌ ነፍሱ ድረስ አደረሰው::
ሕዝቡና ካህናቱ በሆነው ነገር ሲደነቁ: አንዳንዶቹ "ዝም ብሎ ነው የቀባጠረ" አሉ:: ቅዱሱ ግን ቅዳሴ ማርያምን በብራና ጠርዞ በሕዝቡ መካከል ድውይ ፈወሰበት:: እሳት ሳያቃጥለው: ውሃ ሳይደመስሰው ቀረ::
መጽሐፈ ቅዳሴው ሙትንም አስነስቷል:: ከዚህች ሰዓት ጀምሮ በዘመኑ ቁጥር 1 ሊቅ ሆነ:: ብዙ መጻሕፍትን ሲተረጉም አጠቃላይ ድርሰቶቹም እልፍ (10,000) ናቸው:: ሊቁ እንዲህ በንጹሕ ተመላልሶ ዐርፏል::  ጥቅምት ሁለት ቀን ለቅዱሱ የልደቱና ዕረፍቱ መታሰቢያ ናት::

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages