ኒቆዲሞስ፣ የዐብይ ጾም ሰባተኛ ሰንበት - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, April 23, 2021

ኒቆዲሞስ፣ የዐብይ ጾም ሰባተኛ ሰንበት


 ኒቆዲሞስ ቃሉ የግሪክ ሲሆን ድል ማድረግን ወይም አሸናፊነትን ያመለክታል፡: ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ፥ ከአይሁድ አለቆችና መምህራን አንዱ ነው። በወንጌለ ዮሐንስ ምዕራፍ ሦስት ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ አንድ ሰው እንደነበረና እርሱም በሌሊት ወደ ጌታችን መጥቶ እንደተማረ ተጠቅሷል።
በአይሁድ አለቆች ፊትም ”ሕጋችን አስቀድሞ ሳይሰማ የሠራውንም ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” በማለት ስለ መድኃኔዓለም ክርስቶስ የተናገረ እሱ ነው። እነርሱ ግን በክርስቶስ እግዚአብሔርነት ያመኑበት ኦሪትን የማያዉቁ ስሑታን እንደሆኑ ያስቡ ስለ ነበር ”አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ከገሊላ ነቢይ እንደማይነሳ መርምርና እይ“ አሉት እንጂ አልተቀበሉትም። ዮሐ ፯፥፵፰-፶፪። ኒቆዲሞስ የአርማትያስ ሰው ከሚሆን ከዮሴፍ ጋር በመሆን የጌታችንን ቅዱስ ሥጋ በንጹሕ በፍታ ገንዞ በአዲስ መቃብር ቀብሯል። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ”ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ሄዶ የነበረዉ ኒቆዲሞስም መጣ፤ ቀብተውም የሚቀበርበትን መቶ ወቄት የከርቤና የሬት ቅልቅል ሽቶ አመጣ።” እንዳለ። ዮሐ ፲፱፥፴፱። በዚህም ኒቆዲሞስ ከምክረ አይሁድ ያልተቀላቀለ መሆኑ ይታወቃል።
++የሌሊት ተማሪው ኒቆዲሞስ የሌሊቱን ጊዜ ለትምህርት ለምን መረጠ
የሌሊት ተማሪው ኒቆዲሞስ ዮሃ ፫፤፪
ከፈሪሳዊያን ወገን የሆነ የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው በሌሊት ወደ ጌታ እየሄደ ይማር ነበር ኒቆዲሞስ ከቀኑ ክፍለ ጊዜ ይልቅ የሌሊቱን ጊዜ ለትምህርት ለምን መረጠ ?
፩. ኒቆዲሞስ መምህር ስለነበር ስማር ሰዎች ቢያዩኝ ውዳሴ ከንቱ መምህር መባል ይቀርብኛል ብሎ ነው እኛስ ዛሬ የዘላለም ህይወት የሚሰጠንን ቅዱስ ቃል ብትህትና መማር ሲገባን ለምድራዊ ክብር ብለን በቀን ጊዜያችን መማር ያልቻልን ስንቶቻችን ነን ስለዚህ ቀን ጊዜአችንን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል::
‹ማንም ሊሰራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለችና › ዮሃ ፱፤፬
፪.ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ስለነበር እንዳያዩት ፈርቶ ሌሊት እየመጣ ይማር ነበር እኛስ ዛሬ ልባችን የተረዳውን እውነት በግልጥ እንዳንፈጽም በፍራቻ በይሉኝታ የምንሰውር ስንቶቻችን ነን
‹ፍጹምፍቅር ፍርሃት የለውም ፍርሃት ቅጣት አለውና› ፩ዮሃ ፬፤፲፰ ፍርሃትን አስወግደን ለእውነት ልንቆም ይገባል::
፫ ኒቆዲሞስ ከቀን ልብ ይልቅ የሌሊት ልብ የተካተተ ስለሆነ በሙሉ ልቡ በማስተዋል ለመማር ስለፈለገ ከቀኑ ክፍለ ጊዜ ይልቅ የማታውን መረጠ ዛሬስ ስንቶቻችን ነን ቅዱስ ቃሉን በማስተዋል ከልብ ሆነን የምንማር የሰማነው ቅዱስ ቃል በህይወታችን ፍሬ እንዲያፈራ ቅዱስ ቃሉን ከልብ ሆነን በማስተዋል ልንሰማ ይገባናል ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ልብ መልካም መሬት ተብⶀል::
‹ በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው› ማቴ ፲፫፡፳፫
አንዳንዶቻችን ጸሎት እያደረግን እንኳን አንደበታችን የእግዚአብሄርን ቃል ይነዳል ልባችን ሌላ ቦታ ይንጎዳጎዳል በማህበር ጸሎትም አብረን እየጸልይን በመሃል ሳይን አውት አርገን ልክ ሲፈጸም አለቀ እንዴ ብለን ሳይን ኢን የምናደርግ አንጠፋም::
፬ ሌሊት ጨለማ ነው ብርሃን የለም ይህም የኃጢአት ምሳሌ ነው ኒቆዲሞስ በሌሊት መምጣቱ በኃጢአት እንዳለ ንስሃ እንደሚፈልግ ያስረዳናል:: ዛሬስ ስንቶቻችን ነን ቅዱስ ቃሉን ስንሰማ በተአምኖ ኃጢአት በንስሃ ውስጥ ሆነን የምንሰማ ያለንስሃ የምንሰማው ቃል በህይወታችን ፍሬ የማፍራት እድሉ ጠባብ ነው ምክንያቱም በንስሃ ከልባችን ያልጸዱት ክፉ ምኞቶች እንደ እሾህ ሆነው ያንቁታልና::
‹ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ እሾህም ወጣና አነቀው› ማቴ፲፫፤፰ ተብሎ የተጻፈው ለዚህ ነው
፭ ሌሊት የቆየው ኪዳን ወይም የብሉይ ኪዳን ምሳሌ ነው ኒቆዲሞስም እኔ ምሁረ ኦሪት እንጂ ምሁረ ወንጌል አይደለሁም ወንጌልን ካንተ እማር ዘንድ ያስፈልገኛል ሲል በሌሊት ይመጣ ነበር ብሉያት ከሓዲሳት ጋር ተዋህደው ሲተረጎሙ ሰሙና ወርቁ ተጣምሮ የሕይወት ትምህርት ያስገኛል አንዳንዶች ዛሬ ብሉያት ጭራሽ አያስፈልጉም ሲሉ ይደመጣሉ ነገር ግን እንደ ኒቆዲሞስ ሁለቱን ኪዳናት አዋህዶ መጓዝ ትክክለኛው መንገድ ነው ለዚህም ነው ጌታ ሲያስተምር‹እውነት እላችኋለው ሰማይና ምድረስኪያልፍ ድረስ ከህግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ አታልፍም› ማቴ፭፤፲፰ በማለት አበክሮ የተናገረው ኒቆዲሞስ ምንም እንኳን የቀኑ ክፍለ ጊዜ ባይመቸውም በሌሊቱ ሰአት ለመማር ችⶀል እኛም ከሱ ተምረን ከልብ ካለቀሱ እንባ አይጠፋምና ምንም ስራ ቢበዛብን ለቅዱስ ቃሉ ጊዜ አይጠፋምና ህይወት ለሚገኝበት ትምህርት ጊዜ ልንሰት ይገባል።
ምስባክ
_______
ሐወጽከኒ ለሊተ ወፈተንኮ ለልብየ
በሌሊት ጎበኘህኝ ልቦናየንም ፈተንከው
አመከርከኒ ወኢተረክበ ዓመፃ በላዕሌየ።
ፈተንከኝ በላየ ምነም በደል አልተገኘም
ከመ ኢይንብብ አፋየ ግብረ ዕጓለ አመሕያው
የሰው ልጅ ስራን አፌ እንዳይናገር
ወንጌል (ዮሐ ፫ ፣፩-፲፪)
_________________
 '' ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ። መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው። ኢየሱስም መልሶ። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ኒቆዲሞስም። ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው። ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ። ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው። ኒቆዲሞስ መልሶ። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን? እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም። ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?"
የዕለቱ ቅዳሴ
___________
ቅዳሴ ዘእግዝትነ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages