ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 14 ቅዱስ አባ አጋቶን - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 2, 2021

ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 14 ቅዱስ አባ አጋቶን

ቅዱስ አባ አጋቶን ____

መስከረም ፲፬ በዚች ዕለት ታላቁ ቅዱስ አባ አጋቶን እረፍቱ ነው። ከደቡባዊ ግብጽ የተገኘ ታላቅ ጻድቅ ነው፡፡ አባቱ መጥራ እናቱ ማርያ ይባላሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተምሮ በቅስና ሲያገለግል ከኖረ በኋላ መርዩጥ ወደምትባል አገር ሄደ፡፡ ከዚያም ከእግዚአብሔር የታዘዘ ቅዱስ መልአክ በመነኩሴ አምሳል ተግለጦ ወደ መቃርስ ገዳም አስቄጥስ አስገባውና መነኮሰ፡፡ በዚያም አረጋዊያን መነኮሳትን እነ አባ ገዐርጊን እያገለገለ ሥጋው ከቆዳው እስኪጣበቅ ድረስ እየጾመ ያለምንም ምንጣፍ ይተኛ ነበር፡፡ ሁልጊዜም የአባ ስምዖን ዘአምድን ገድል ያነብ ስለነበር ከገዳሙ ተሰናብቶ ወጥቶ ዓምድ ሠርቶ በላዩ ወጥቶ ለ50 ዓመት ቆሞ ሲጸልይ የኖረ ታላቅ አባት ነው፡፡ ጋኔን እያደረባቸው ቅዱሳን ተገለጡልኝ የሚሉ አሳቾችን ወደ እርሱ እያስመጣቸው በውስጣቸው ያደረውን ጋኔን ያወጣላቸው ነበር፡፡ አባ አጋቶን በመላእክት አምሳል ሆነው መልካም ዝማሬን እየዘመሩ ሰይጣናት ተገልጠውለት ሳለ አማትቦ ድል አድርጓቸዋል፡፡ ይህም ጻድቅ እስከ 35 ዓመቱ በዓለም እየኖረ እግዚአብሔርን አገለገለ፤ ለ15 ዓመታት በገዳም በታላቅ ተጋድሎ ኖረ፤ ቀሪውን 50ውን ዓመት ደግሞ በዓምድ ላይ ተተክሎ በጸሎት ሲያመሰግን ኖረ፡፡ እጅግ አስደናቂ ተአምራትን በማድረግና ወንጌልን በማስተማር ብዙ ካገለገለ በኋላ በመቶ ዓመቱ በዚህች ዕለት በሰላም አረፈና ቅድስት ነፍሱን አስረከበ፣ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ አሜን።
አባ ጴጥሮስ ቀዳማዊ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ
_________________________________
አቡነ ጴጥሮስ ቀዳማዊ የተባሉት ጸድቅ ትውልድ ሀገራቸው ሸዋ ቡልጋ ልዩ ስሙ ደብረ ጽላልሽ ነው፡፡ ጻድቁ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ለ48 ዓመታት የቅዱስ ገላውዲዮስን ቤተ ክርስቲያን ሲያጥኑ ኖረዋል፡፡ ከተሰዓቱ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት አቡነ ሊቃኖስ እጆቻቸው እያበሩ ለገዳሙ መብራትነት ይጠቀሙባቸው እንደነበረው ሁሉ የአቡነ ጴጥሮስ ቀዳማዊም እጆቻቸው እንደፋና እያበራ ለጣና ሐይቅ ገዳማት በመብራትነት ያገለግል ነበር፡፡ ጻድቁ ለ31 ዓመታት ከመላእክት ጋር እየተነጋገሩ የኖሩ ሲሆን መናም ከሰማይ እያወረዱ መነኮሳቱን ይመግቡ ነበር፡፡ ድውያንን በመፈወስ፣ ሙታንን በመንሣት ብዙ አስተደናቂ ተአምራት እያደረጉ ወንጌልን በሀገራችን ዞረው በማስተማር እግዚብሔርን ሲያገለግሉ ኖረው በዚህች ዕለት በሰላም ዐርፈው ቅድስት ነፍሳቸውን ቅዱሳን መላእክት በክብር ተቀብለዋታል፡፡
አቡነ ያሳይ ዘማንዳባ
_________________
 አቡነ ያሳይ ‹‹ሰባቱ ከዋክብት›› ከሚባሉት የሀገራችን ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ እነዚህም ‹‹ሰባቱ ከዋክብት›› የተባሉት አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አቡነ ያሳይ ዘማንዳባ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘቆየፃ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘጣሬጣ፣ አቡነ ታዴዎስ ዘባልታርዋ፣ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤ እና አቡነ ዮሐንስ ዘጉራንቄ ናቸው፡፡ እነዚህን የመላእክትን ሕይወት በምድር የኖሩ ታላላቅ የሀገራችንን ቅዱሳን በአንድ ጊዜ አስተምረውና አመንኩሰው ለጽድቅ ያበቋቸው አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ናቸው፡፡ ‹‹ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን›› የተባሉት አቡነ መድኃኒነ እግዚእ የኢትዮጵያ ብርሃኗ በሆኑት በአቡነ ተክለ ሃይማኖት እጅ ከመነኮሱ በኋላ አቡነ መድኃኒነ እግዚእም በተራቸው ያስተማሯቸውና ያመነኮሷቸው መነኮሳት ቁጥራቸው በውል አይታወቅም፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ለአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ‹‹ስፍር ቁጥር የሌላቸው ከዋክብት ቅዱሳንን›› በመንፈስ ቅዱስ እንደሚወልዱ ትንቢት ተናግረውላቸው ነበር፡፡ የተንቤኑን አቡነ ዐቢየ እግዚእን፣ የዞዝ አምባውን አቡነ አብሳዲን ጨምሮ አባታችን መድኃኒነ እግዚእ ብርሃን ሆነው በጣም ብዙ ቅዱሳንን የለኮሱ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ‹‹ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን›› የተባሉት፡፡


አቡነ መድኃኒነ እነዚህንም ሰባቱን ቅዱሳን በአንድ ጊዜ ሲያመነኩሷቸው በዚያው ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ገዳሙን በብርሃን አጥለቅልቆት ታይቷል፡፡ ከሰማይም የምስክርነት ድምፅ ተሰምቷል፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ላይ የመነኮሱት እነዚህ ሰባቱ ቅዱሳን ‹‹ሰባቱ ከዋክብት›› እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ እነዚህም ሰባቱ ከዋክብት የጣናን ባሕር በእግራቸው ጠቅጥቀው ተሻግረው ብዙዎቹን ደሴቱ ላይ ያሉ አስደናቂ የጣና ገዳማትን የመሠረቱት ናቸው፡፡ ከእነርሱም ውስጥ ባሕሩን በእግራቸውም እየረገጡ ጠቅጥቀው የተሻገሩ አሉ፤ በሌላም ቦታ በየብስ የተሰማሩትም ቢሆኑ መጻሕፍቶቻቸውን በአንበሳ ጭነው የተጓዙ አሉ፤ ትልቅ ጠፍጣፋ ድንጋይን እንደጀልባ ተጠቅመው በእርሱ ላይ ሆነው ወደ ደሴት የገቡ አሉ፡፡ አንዱ ዛሬ በዓላታቸውን የምናከብራለቸው አቡነ ያሳይ ናቸው፡፡


ቅዱስ ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው›› (መዝ 67፡35) ብሎ እንደተናገረ ጻድቁ አቡነ ያሳይ ከእግዚአብሔር በተሰጣቸውም ጸጋ ጣና ሐይቅን የሚያቋርጡት በአንድ ትልቅ ጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ድንጋዩን እንደ ጀልባ ተጠቅመው ነበር፡፡ ያ ድንጋይ ዛሬም ድረስ በገዳማቸው ውስጥ በክብር ተቀምጦ ይገኛል፡፡ ጻድቁ ከአቡነ ሳሙኤል ጋር አብረው ወደዚህ ቦታ መጡ፡፡ ከዚያም የቦታው አቀማመጥ የብስ መሬትና ደሴት መሆኑን አይተው ‹‹እግዚአብሔር ፈቅዶ ይችን ደሴት የጸሎት ቦታችን አድርጎ ቢሰጠን በጸሎት እንጠይቀው›› ተባብለው ሁሉቱም ቅዱሳን ሱባኤ ገቡ፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንም ለአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ተገሃድ ተልጦላቸው ‹‹ወዳጄ ሳሙኤል ሆይ ይህ ቦታ የአንተ አይደለም የወንድምህ የያሳይ ቦታ ነው፡፡ እኔ ወዳዘጋጀሁልህ ቦታ ወደ ዋሊ ሂድ›› ብሎ የዋልድባን ምድር አሳያቸው፡፡ አቡነ ሳሙኤልም የጌታችንን ትእዛዝ ተቀብለው ወንድማቸውን አቡነ ያሳይን ተሰናብተው ወደ ዋልድባ ሄደው ገዳማቸውን አቅንተው ተጋድሎቸአውን በዚያ ፈጸሙ፡፡
ጌታችን ዳግመኛም ለአቡነ ያሳይ ተገለጠላቸውና ‹‹ወዳጄ ያሳይ ሆይ የአባትህን መንግሥትና የዓለሙን ክብር ከምኞቱ ጋር ለእኔ ብለህ ስለተውክ ይህንኑ ቦታ በዚህ ዓለም ሳለህ ለአንተ፣ ወደ ዘላለማዊ መንግሥቴ ከወሰድኩህ በኋላም ለልጆችህ ምንዳህ አድርጌ ሰጥቼሃለሁ፤ ምሕረቴንም በቦታህ አዘንባለሁ ቸርነቴም አይለያትም፣ ብዙ የመንፈስ ልጆችንም ታፈራለህ፤ ቦታህም እኔ ለፍርድ እስክመጣ ድረስ ትኖራለች›› በማለት ቃልኪዳኑን አቆመላቸውና ተሰወራቸው፡፡ ‹‹ምንዳህ›› ማለት ደመወዝ ማለት ነውና በዚህም ‹‹ማንዳባ›› ማለት ‹‹የአቡነ ያሳይ ምንዳ-ደመወዝ›› ማለት ነው ሲሉ አባቶች ገዳሙን ‹‹ማንዳባ-ምን እንደ አባ›› ብለው ሰየሙት፡፡
አቡነ ያሳይ የትውልድ ሀገራቸው ሸዋ ተጉለት ነው፡፡ አባታቸው ንጉሡ ዓምደ ጽዮን ቀዳማዊ ነው፡፡ ይኸውም ከ1296-1326 ዓ.ም የነበረው ነው፡፡ አቡነ ያሳይ በልጅነታቸው በንጉሡ አባታቸው ቤት ሲኖሩ የገዳማ መነኮሳት ለመንፈሳዊ ሥራ ወደ ንጉሡ ዘንድ እየመጡ ደጅ ሲጠኑ ያዩአቸዋል፡፡ በዚህም ጊዜ አባታችን ገና በልጅነታቸው የመነኮሳቱን እግር ያጥቡ ስለነበር በዚሁ አጋጣሚ መነኮሳቱን ስለምንኩስና ሕይወት ይጠይቋቸው ነበር፡፡ መነኮሳቱም ሕይወታቸውን ያስረዷቸዋል፡፡ አቡነ ያሳይም ብሉያትንና ሐዲሳትን ከልጅነታቸው ጀምሮ የተማሩ ስለነበር የአባቶችን ትምህርትና የወንጌልን ቃል በማገናዘብ የፈጣሪያቸው ፍቅር በልቡናቸው እንደ እሳት ነደደ፡፡ ይልቁንም ‹‹ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል›› የሚለውን የጌታችንን ቃል አሰቡ፡፡ ማቴ 16፡26፡፡ ከዚህም በኋላ የንጉሡ አባታቸውን የአልጋ ወራሽነት ማለትም የንጉሥነትን ክብር ፈጽመው በመናቅ ‹‹እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር እራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ›› (ማቴ 16፡27) ያለውን የጌታችንን ቃል አስበው ንጉሣውያን ቤተሰቦቻቸውን ጥለው ለምነና ወጡ፡፡
ለምነና እንደወጡም ከሸዋ ተነሥተው ወደ ትግራይ ክፍለ ሀገር በአክሱም አቅራቢያ ከሚገኘው ገዳም ደብረ በንኮል ከሚባለው ከአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ገዳም ደረሱ፡፡ አቡነ መድኃኒነ እግዚእም አቡነ ያሳይ የእግዚአብሔር ጸጋ ያደረባቸው ሰው መሆናቸውንና ወደ እርሳቸውም እየመጡ መሆኑን በመንፈስ ዐውቀውት ስለነበር በደስታ ተቀበሏቸውና በረድእነት ከወንድሞቻቸው ጋር ጨመሯቸው፡፡ አቡነ ያሳይም የገዳም መነኮሳትን በማገልገል በመንፈሳዊ ተጋድሎ ብዙ ደከሙ፡፡ በደብረ በንኮል ገዳምም ብዙ እገራሚ ተአምራትን አደረጉ፡፡ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ ወደ መካነ ገድላቸው በጣና አካባቢ እንደሆነ ነገራቸው፡፡ ‹‹ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን›› የተባሉ አቡነ መድኃኒነ እግዚእም ቀደም ብለን የጠራናቸውን ‹‹ሰባቱን ከዋክብት›› ምግባር ሃይማኖታቸውን፣ ተጋድሎ ትሩፋታቸውንና ገቢረ ተአምራታቸውን አይተው ፈቃደ እግዚአብሔርን ጠይቀው በአንድ ቢያመነኩሷቸው በዚያው ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ገዳሙን በብርሃን አጥለቅልቆት ታይቷል፡፡ ከሰማይም የምስክርነት ድምፅ ተሰምቷል፡፡ ከዚህም በኋላ ከሰባቱ ቅዱሳን ውስጥ ሦስቱ ቅዱሳን አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አቡነ ያሳይ እና አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ሆነው ከደብረ በንኮል ገዳም አባታቸውን አቡነ መድኃኒነ እግዚእን ተሰናብተው ወደ ጣና ደሴት መጥተዋል፡፡
አቡነ ያሳይ በ13ኛው መ/ክ/ዘመን በአባታቸው የዘመነ ንግሥና መጨረሻ ወደ አርባ ምንጭ ሄደው ከዚያው ሱባኤ ገብተው ፈጣሪያቸውንነ ቢማጸኑ እግዚአብሔርም ከዚያው አካባቢ የሚኖር አንድ ባሕታዊን የመድኃነዓለምን ጽላት እንዲወጣቸው አዘዘላቸው፡፡ እርሳቸውም ጽላቱን ተቀብለው በጎጃም በኩል አድርገው ወደ ጣና ተመልሰው በዘጌ አከባቢ ሲደረሱ ከጣና ባሕር ዳር ቆመው በየብስ ያለውን ርቀትና በባሕሩ ያለውን ቅርበት አይተው አሁንም ወደ ፈጣሪያቸው በጸሎት ተማጸኑ፡፡ በዚህም ጊዜ ጌታችን ተገልጦላቸው ‹‹ወዳጄ ያሳይ ሆይ አትጨነቅ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፣ ከጎንህ ያለውን ድንጋይ በባሕሩ ላይ ጫነው፤ ድንጋዩም ለልጅ ልጅ እኔ ዓለምን ለማሳለፍ እስከምመጣበት ሰዓት ድረስ መታሰቢያ ትሁንህ›› አላቸውና ተሰወረ፡፡ አቡነ ያሳይም የመድኃኔዓለምን ጽላት ይዘው በድንጋዩ ላይ እንደተቀመጡ ድንጋዩ እንደታንኳ በባሕሩ ላይ ተንሳፈፈ፡፡ ባሕሩም ከማዕበሉ ብዛት የተነሣ ይታወክ ነበር፡፡ አባታችንም ያለ ምንም ቀዘፋ ልብሳቸውም ውኃ ሳይነካው ቁጭ እንዳሉ ማን እንደአባ ወደ ተባለው ቦታቸው ደረሱ፡፡
ከዚህም በኋላ አቡነ ያሳይ ገዳማቸውን ገድመው ወንድሞቻቸውን ሰብስበው በተጋድሎ በመኖር ብዙ ቅዱሳንን አፍርተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የጌታችንን እግር ያጠቡት አቡነ አብሳዲ፣ እንደ ነቢዩ ኤልያስ ዝናብንና ነፋስን የከለከሉት አቡነ ያዕቆብ፣ እሬትን እንደ ማር ያጣፈጡት አቡነ ገብረ ኢየሱስ፣ እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ጸጋንና ሞገስን የተሞሉት አቡነ ዳንኤል፣ እንደ ንጉሥ ሰሎሞን ጥበብን የተሞሉት አቡነ ፊቅጦርና ሌሎችም ብዙዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በወቅቱም ብዙ የበቁ ቅዱሳን በአካባቢው ነበሩ፡፡ በአጽፋቸውና በእግራቸው በባሕሩ ላይ የሚሄዱ ነበሩ፣ በጸጋ ክንፍ ተሰጥቷቸውም የሚበሩ ነበሩ፡፡ የአቡነ ያሳይ ተአምራቶቻቸው ተነግረው አያልቁም፡፡ በወቅቱ የነበሩት ቅዱሳን ልጆቻቸው ‹‹ከቅዱሳን ማን እንደ አባ ያሳይ በከባድ ድንጋይ ላይ ተጭኖ በባሕር ላይ የተጓዘ አለና..›› ብለው ይገረሙባቸው ነበር፡፡ ቦታቸውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ‹‹ማን እንደ አባ›› ተባለ፡፡ ይህም የአቡነ ያሳይ ገዳም በሰሜን ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት በደንቢያ ወረዳ በጎርጎራ ጣና ሐይቅ አካባቢ ይገኛል፡፡


በጣና ደሴት ላይ ከሚገኙት ታሪካዊ ቦታዎች ውስጥ አንዱ ‹‹አትማረኝ ዋሻ›› ነው፡፡ ይህም ዋሻ ታሪኩ ከአቡነ ያሳይ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ታሪኩም እንዲህ ነው፡- አትማረኝ ዋሻ በጣና ሐይቅ ደሴቶች መካከል ከሚገኙ ገዳማት መካከል ከማን እንደ አቡነ ያሳይ መድኀኔዓለም አንድነት ገዳም በስተ ምእራብ አቅጣጫ የጣና ሐይቅን ጉዞ ከገታው አንድ ተራራ ሥር የሚገኝ ዋሻ ነው፡፡ ይህ ዋሻ ለብዙ ዘመናት አንድ ታላቅ አባት የጸሎት በዓት አድርገውት ‹‹አትማረኝ›› እያሉ የጸለዩበት ቦታ ነው፡፡ አቡነ ያሳይ ወደ ጣና ደሴት ከአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ እና አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ጋር በመሆን በጸሎት ይተጉ እንደነበር ገድላቸው ይናገራል፡፡ ከእግዚአብሔር በተሰጣቸውም ጸጋ በጣና ሐይቅ ላይ እንደ ጀልባ የሚጓዙበት አንድ ትልቅ ጠፍጣፋ ድንጋይ በጣና ደሴት ላይ ለአገልግሎት በመፋጠን ላይ እያሉ ዛሬ አትማረኝ ዋሻ ተብሎ ወደሚጠራው አካባቢ ሲደርሱ አንድ አባት ዋሻው ውስጥ “አትማረኝ፣ አትማረኝ፣ አትማረኝ” እያሉ ሲጸልዩ ያገኟቸዋል፡፡ አቡነ ያሳይም በሰውዬው ጸሎት በመገረም ቀርበዋቸው ‹‹አባቴ ምን ዓይነት ጸሎት ነው የሚጸልዩት?›› አሏቸው፡፡ ያም አባት ‹‹አባቴ እንደ እርስዎ ያሉ አባት መጥተው ‹አትማረኝ› እያልክ ጸልይ ብሎኝ ነው›› በማለት መለሱላቸው፡፡ አቡነ ያሳይም ‹‹እንዲህ ዓይነት ምክር የሚመክር ጠላት ዲያብሎስ ነው፡፡ ከዛሬ ጀምረው ‹ማረኝ› እያሉ ይጸልዩ በማለት አቡነ ዘበሰማያትን አሰተምረዋቸው ይሄዳሉ፡፡ ‹‹አትማረኝ›› እያሉ ይጸልዩ የነበሩት አባትም ‹‹ማረኝ›› እያሉ መጸለያቸውን ቢቀጥሉም ብዙ መግፋት ሳይችሉ ቀሩና ጸሎቱ ይጠፋባቸዋል፡፡ ወደ ሐይቁ ሲመለከቱም አቡነ ያሳይ ድንጋዩን እንደጀልባ ተጠቅመው እየሄዱ ነው፡፡ ጸሎቱን ያስጠኗቸው አቡነ ያሳይ ርቀው ሳይሄዱባቸው ያ አባት በውኃ ላይ በእግራቸው እየተራመዱ በመከተል ይደርሱባቸዋል፡፡ ከኋላቸውም ሆነው ‹‹አባታችን ያስጠኑኝ ጸሎት ጠፋብኝ፤ እባክዎን እንደገና ያስተምሩኝ›› አሏቸው፡፡ አቡነ ያሳይም ሐይቁን በእግራቸው እረገጡ እስኪሄዱ ድረስ ጽድቃቸው የተገለጠውን የእኚህን አባት መብቃት ተመልከተው ‹‹አባቴ እግዚአብሔር የልብ ነውና የሚመለከተው እንዳስለመዱት ይጸልዩ የእርስዎ ይበልጣል›› ብለዋቸው ሔዱ፡፡ በዚህም ምክንያት ቦታው ‹‹አትማረኝ ዋሻ›› ተብሎ ተጠርቷል፡፡ የአቡነ ያሳይ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን አሜን።


ምንጭ: ስንክሳር ዘወርኅ መስከረም

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages