የቅድስና ደረጃዎች(መንፈሳዊ ማዕረጋት) - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 2, 2021

የቅድስና ደረጃዎች(መንፈሳዊ ማዕረጋት)

የቅድስና ደረጃዎች(መንፈሳዊ ማዕረጋት) _______________________________ ቅድስና በአንድ ሌሊት የሚደረስበት ሳይሆን የብዙ ጊዜ መንፈሳዊ ተጋድሎን ንጹህ ልቡናን ትዕግስትን የሚጠይቅ ቅዱሱን እግዚአብሔርን በመምሰል የሚኖሩት ሕይወት ነው። ቅድስና የሚያልፈውን ዓለም መናቅና መተው ልቡናን በሰማይ ማኖር ነው። ቅድስና ሰው ሆኖ ለተፈጠሩበት ዓላማ መኖር ነው። የሰው ልጅ በዚህ ምድር ሲኖር በቅድስናና በንጽሕና እያደገ ሲመጣ የሚደርስባቸው አሥር መንፈሳዊ ማዕረጋት አሉ፡፡ በቤተክርስቲያናችን ብዙዎች ቅዱሳን በእነዚህ መንፈሳዊ ማዕረጋት አልፈው ለክብር በቅተዋል። እነዚህ አሥር መንፈሳዊ ማዕረጋት በሦስት የሚከፈሉ ሲሆን፡- ንጽሐ ሥጋ ፣ንጽሐ ነፍስና ፤ ንጽሐ ልቡና አንድም ወጣኒነት ፣ማዕከላዊነትና ፍጹምነት ይባላሉ፡፡ አሥሩ ማዕረጋት በዝርዝር የሚከተሉት ናቸው:- ፩. ጽማዌ ________ ይህ ማዕረግ የመጀመሪያው ደረጃ ሲሆን ትህትናን፤ ራስን ዝቅ ማድረግን፤መታገሥንና ነገሮችን በውስጥ ይዞ ማሰላሰልን ወዘተ…ይይዛል፡፡እዚህ ደረጃ የደረሰ ሰው የዚህን ዓለም ውጣ ውረድ ከማውራት ይከለከላል በብዙ ነገሮች ላይ ዝምታን ይመርጣል፡፡ ፪. ልባዌ፡- _________ ይህ ማስተዋልና ልብ ማለትን ገንዘብ ያደረጉ ሰዎች የሚገኙበት ደረጃ ነው፡፡እዚህ ማዕረግ ላይ የደረሱ ሰዎች ልናገር ሳይሆን ልስማ ፤ ላስተምር ሳይሆን ልማር ይላሉ፡፡ የመጽሐፉ ቃል የሚለውን ማስተዋልና አብዝተው ኃጢአታቸውን ያሰላስላሉ ማስተዋልን ገንዘብ ያደርጋሉ፡፡ ፫. ጣዕመ ዝማሬ፡- _______________ እዚህ ደረጃ የደረሰ ሰው አንደበቱን ከንባብ ልቡናውን ከምሥጢር ያቆራኛል፡፡እዚህ ደረጃ የደረሱ ቅዱሳን አንደበታቸው ዝም ቢል በልባቸው ግን ዝም ብለው አያውቁም ከሰውነታቸውም ንጽሕና አይለይም፡፡የሚያነቡትን መጽሐፍና የሚጸልዩትን ጸሎት ምሥጢሩን በደንብ እየተረዱት ስለሚያደርጉት አይሰለቻቸውም፡፡ እነዚህ ከ1-3 ያሉት የንጽሐ ሥጋ (ወጣኒነት) ማዕረጋት ናቸው፡፡ ፬. አንብዕ፡- ___________ እዚህ ማዕረግ ላይ የደረሱ ሰዎች የጌታቸውን ፍቅር እያሰቡ እስከ ሞትና መከራ የተጓዘውን ጉዞ እያሰቡ ዘወትር ያለቅሳሉ፡፡ ያለምንም ተጽዕኖ ዕንባቸው እንደ ውኃ ይወርዳል፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ለዚህ ዓለም ፍላጎታቸው መሟላት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ምሕረትና ቸርነት በመናፈቅ ነው፡፡ ፭. ኩነኔ፡- ______ ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ ሥጋዊ ፈቃድ ሁሉ ለነፍስ ፈቃድ ይገዛል ፤ ነፍስ በሥጋ ፍላጎት ላይ ትሰለጥናለች፡፡ ምድራዊ (ሥጋዊ) ፍላጎቶች ይጠፉና ሰማያዊ"(የነፍስ) ፍላጎቶች ቦታውን ይወርሳል፡፡ ፮. ፍቅር፡- _______ ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ ማንንም ሳይመርጡ ወዳጅንም ጠላትንም መውደድ ይጀምራሉ፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ያደረገውን ታላቁን የፍቅር ሥራ እርሱን በመምሰል ሕይወት በመኖር በተግባር ይገልጻሉ፡፡ ፯. ሁሰት፡- ________ ከዚህ ማዕረግ የደረሱ ቅዱሳን ባሉበት ቦታ ሆነው ሁሉን ነገር ማየት ይችላሉ፡፡የቦታ ርቀትና የገዘፉ ቁሶች ሳያግዳቸው ፤ ሁሉን ያያሉ፡፡እነዚህ ከ4-7 ያሉት የንጽሐ ነፍስ (ማዕከላዊነት) ማዕረጋት ናቸው፡፡ ፰. ንጻሬ መላእክት፡- _____________ ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ መላእክትን ሲወጡና ሲወርዱ ማየት ይቻላል፡፡ ፱. ተሰጥሞ፡- __________ ከዚህ ማዕረግ የደረሰ ሰው በብርሃን ባሕር እየተመላለሰ በምድሪቱ ላይ ያለውን ሁሉ ማወቅ መረዳትና መመልከት ከመቻላቸውም አልፈው ሥሉስ ቅዱስ ከመመልከት በስተቀር በሰማያት ያለውንም ምሥጢር ወደ መረዳት ይደርሳሉ፡፡ ፲. ማዕረገ ከዊነ እሳት/ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ/፡- __________________________________ ከዚህ ማዕረግ የደረሱ ሰዎች ሥላሴን በዙፋኑ ላይ ሆኖ እንደ እስጢፋኖስ መመልከት ይጀምራሉ፡፡እንዲሁም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በአካለ ነፍስ ተነጥቀው ወደ ሰማያት በመውጣት ሰማያትን መጎብኘት ወደ መቻል ይደርሳሉ ተሐዋሲያን እንኳን እነሱ ላይ ሲያርፉ እየተቃጠሉ ይወድቃሉ እነዚህ ንጽሐ ልቦና (ፍፁምነት) የቅድስና ማዕረግ የደረሱ ናቸው፡፡ የቅዱሳንን መንገድ እንድንከትል የአምላካችን መልካም ፈቃድ ይሁንልን ከቅዱሳን ረድኤት በረከት ያሳትፈን!

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages