ነሐሴ 28 ቀን ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ : ቅዱስ ዋርስኖፋ እና አባ ዮሐንስ ዘጐንድ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, August 4, 2022

ነሐሴ 28 ቀን ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ : ቅዱስ ዋርስኖፋ እና አባ ዮሐንስ ዘጐንድ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።

እንኳን ለቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ : ቅዱስ ዋርስኖፋ እና አባ ዮሐንስ ዘጐንድ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ †††
ቅዱሳን ሐዋርያት አባቶቻችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተከተሉበት ሰዓት እድሜአቸው በ3 ደረጃ የተከፈለ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያሳያል:: እንደ ዮሐንስ ወንጌላዊ ያሉት በ20ዎቹ ውስጥ : ቅዱስ ታዴዎስን የመሰሉት ደግሞ በ30ና በ40ዎቹ ውስጥ የነበሩ ሲሆን እነ ቅዱስ ዼጥሮስ ደግሞ በ50ዎቹ ውስጥ የሚገኙ ነበሩ::
ደቀ መዛሙርቱ ከወጣቶችም : ከጐልማሶችም : ከአረጋውያንም የተዋቀሩ ነበሩ ማለት ነው:: ቅዱስ ታዴዎስ በቀደመ ስሙ ልብድዮስ ይባል የነበረ ሲሆን በአንዳንድ መጻሕፍት ውስጥ (በተለይ በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች) ስምዖን እና ይሁዳ እየተባለም ተጠርቷል::
ቅዱሱ ጌታችን ተከትሎ : ከ12ቱ አንዱ ሆኖ በፈጣሪው ተመርጦ : 3 ዓመት ከ3 ወር ከጌታ እግር ተምሮ : በዕርገቱ ተባርኮ : በበዓለ ሃምሳም 71 ልሳናትን ተቀብሎ : ሐዋርያት ዕጣ ሲጣጣሉ የበኩሉን አሕጉረ ስብከት ተካፍሎ ዓለምን ዙሯል::
ቅዱስ ታዴዎስ እስከ እርጅናው ድረስ ለወንጌል ሲተጋ ኑሯል:: ጌታችንም በየጊዜው በአካል እየተገለጸ አጽናንቶታል:: ከብዙ የድካምና የመከራ ዘመናት በሁዋላም ሐምሌ 2 ቀን ዐርፏል::
ቅዱሱ ሐዋርያ ያረፈው ሶርያ ውስጥ ሲሆን ከ250 ዓመታት በሁዋላ ቤተ ክርስቲያኑ ታንጾለት በዚህች ቀን ወደ ቁስጥንጥንያ ፈልሷል:: ይህንን ያደረገው ደግሞ ታላቁ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ነው:: ከሐዋርያው ዘንድም ብዙ ተአምራት ተደርገዋል::
††† ቅዱስ ዋርስኖፋ ሰማዕት †††
††† ቅዱሱ በትውልድ ግብፃዊ ሲሆን ገና ከልጅነቱ ጣዕመ ክርስትና የገባው ነበር:: መጻሕፍትን በማንበብ: ክርስትናንም በመለማመድ ስላደገ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት የመወደድ ሞገስ ነበረው:: በእድሜው እየጐለመሰ ሲሔድ በተጋድሎውም እየበረታ ሔደ::
በወቅቱ እርሱ የነበረባት ሃገር ዻዻስ በማረፉ ሊቃውንቱና ሕዝቡ ተሰብስበው አምላክን ጠየቁ:: እንደሚገባም መከሩ:: በደንብ አስተውለዋልና እንደ አንድ ልብ መካሪ: እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሁነው ሁሉም ቅዱስ ዋርስኖፋን መረጡ::
ዛሬን አያድርገውና በአባቶቻችን ዘመን ሕዝቡም ሆነ ሊቃውንቱ መሪ መምረጥን ያውቁ ነበር:: ተመራጮቹ ደግሞ እንኩዋን እንደ ዘመናችን "ሹሙኝ : ምረጡኝ" ሊሉ በአካባቢውም አይገኙም ነበር::
ቅዱስ ዋርስኖፋ ለዽዽስና እንደ መረጡት ሲያውቅ "ጐየ" እንዲል መጽሐፍ: ጨርቄን ማቄን ሳይል በሌሊት ጠፍቶ በርሃ ገባ:: (እንዲህ ነበሩ አበው) በገባበት በርሃ ውስጥ በዓት ሠርቶ በጾም: በጸሎትና በስግደት በርትቶ ዓመታትን አሳለፈ:: እርሱ በበርሃ እያለ ዘመነ ሰማዕታት ጀምሮ ብዙ ክርስቲያኖች አልቀው ነበር::
እርሱ ግን ከዓለም ርቁዋልና ይህንን አላወቀም ነበር:: አንድ ቀን መልአከ እግዚአብሔር መጥቶ "አንተ በስሙ ደማቸውን ለሚያፈሱ አክሊላት እየታደለ : ሰማያዊ ርስትም እየተካፈለ ነውኮ! አልሰማህም?" አለው::
ቅዱስ ዋርስኖፋም "ለካም እንዲህ ያለ ክብር አምልጦኛል" ብሎ: በርሃውን ትቶ ወደ ከተማ ወጣ:: መልአኩ እንዳለውም ክርስቲያኖች ሲሰቃዩ ደረሰ:: ቅዱሱም ሳያመነታ ስመ ክርስቶስን ሰብኮ: ብዙ ተሰቃይቶ በዚህች ቀን አክሊለ ሰማዕትን በአክሊለ ጻድቃን ላይ ደርቧል::
††† እጨጌ አባ ዮሐንስ ዘጐንድ †††
††† ጻድቁ ተወልደው ያደጉት በኢየሩሳሌም ሲሆን ነገዳቸውም እሥራኤላዊ ነው:: ነገር ግን ተጋድሏቸውን የፈጸሙት በሃገራችን ኢትዮዽያ ውስጥ ነው:: እጨጌ አባ ዮሐንስ ከአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቀጥሎ ባለ ረዥም እድሜ ጻድቅ መሆናቸው ይነገራል::
አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ያረፉት በ562 ዓመታቸው ሲሆን እጨጌ አባ ዮሐንስ ደግሞ በ500 ዓመታቸው ነው:: የሚገርመው ጻድቁ የታላላቁ ጻድቃን ገብረ መንፈስ ቅዱስ : ተክለ ሃይማኖት: ሳሙኤል: ዜና ማርቆስ እና ሌሎችም ባልንጀራ ነበሩ::
በዛ ዘመን ዘረኝነት በቅዱሳኑ ዘንድ አልነበረምና ነጭ ሆነ ጥቁር : ከየትም ይምጣ የሰው ልጅ መሆኑ ብቻ በቂ ነበር:: እጨጌ አባ ዮሐንስ በሃገራችን 5 በዓቶች የነበሯቸው ሲሆን በአንድ በዓት የሚኖሩት ለ50 ዓመት ነበር::
በዚህም በኢየሩሳሌም ለ50 ዓመት : በኢትዮዽያ ደግሞ ለ450 ዓመታት ኑረዋል:: ከበዓቶቻቸው አንዱ ደብረ ሊባኖስ ሲሆን በገዳሙ ለ50 ዓመታት አበ ምኔት(እጨጌ) ሆነው አገልግለዋል:: "እጨጌ" የሚባሉትም በዚህ ምክንያት ነው::
ጻድቁ የመጨረሻ ዘመናቸውን ያሳለፉት በጐንድ (ጉንድ) ተክለ ሃይማኖት ገዳም ነው:: ገዳሙ የሚገኘው በሰሜን ጐንደር ዞን : በለሳ ወረዳ ውስጥ ሲሆን የመሠረቱትም ራሳቸው ናቸው:: ነገር ግን በራሳቸው እንዲጠራ አልፈለጉምና ገዳሙ የሚጠራው በወዳጃቸው በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም ነው::
ጐንድ እኛ ኃጥአን ሳይገባን ያየነው ገዳም ነው:: ዛሬም ድረስ ድንቅ የሆኑ አበው የሚኖሩበት : ተአምራትም የማይቋረጥበት : ፈዋሽ ጠበል ያለው ደግ ገዳም ነው:: ጻድቁ እጨጌ አባ ዮሐንስ ግን አስታዋሽ አጥተው እየተዘነጉ ካሉ ቅዱሳን አንዱ ናቸው:: ምንም ዛሬ አጽማቸው ፈልሶ ወደ ደቡብ ኢትዮዽያ አካባቢ ቢሔድም እርሳቸው በ500 ዓመታቸው ያረፉት በዚህ ገዳም ውስጥ ነው::
††† እግዚአብሔር ከሐዋርያው : ከሰማዕቱና ከጻድቁ ክብርን : በረከትን ያሳትፈን::
ሐምሌ 29 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ፍልሠቱ)
2.ቅዱስ ዋርስኖፋ ሰማዕት
3.እጨጌ አባ ዮሐንስ (ዘጐንድ)
††† ወርኀዊ በዓላት
1.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
2.ቅድስት አርሴማ ድንግል
3.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
4.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
5.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮዽያዊት
6.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)
††† "ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማሕበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ:: የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ:: እንዲሁም ጐበዞች ሆይ! ለሽማግሌዎች ተገዙ:: ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ:: እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና:: ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል::" †††
(1ዼጥ. 5:3)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages