መስከረም 11 እንኳን ለቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት እና ቅድስት ታኦድራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, September 21, 2022

መስከረም 11 እንኳን ለቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት እና ቅድስት ታኦድራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
††† በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥሎ አለቅነት ከተሰጣቸው ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ ፋሲለደስ ነው:: እንዲያውም ለዘመነ ሰማዕታት መሪና አስተማሪ እርሱ ነበር:: እስኪ በጥቂቱ ነገሩን ከሥሩ እንመልከተው:: በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን የሮም መንግስት ዓለምን የሚያስተዳድረው በሁለት ከተሞች: ማለትም በራሷ በሮምና በአንጾኪያ ነበር:: የወቅቱ ንጉሥ ኑማርያኖስ ሲሆን የቤተ መንግስቱ ልዑላንና የጦር አለቆች ቅዱሳኑ:- ፋሲለደስ: ገላውዴዎስ: ፊቅጦር: መቃርስ: አባዲር: ቴዎድሮስ (3ቱም): አውሳብዮስ: ዮስጦስ: አቦሊ: ሌሎቹም ነበሩ:: ሴቶቹ ደግሞ ቅዱሳቱ:- ማርታ: ሶፍያ: ኢራኢ: ታኡክልያ: ሌሎቹም ነበሩ:: ለእነዚህ ሁሉ የበላይ ደግሞ ቅዱስ ፋሲለደስ ነበር:: ወቅቱ ከፋርስ: ከቁዝና ከበርበር ጦርነት የሚበዛበት ነበርና ባጋጣሚ ንጉሡ ኑማርያኖስ በሰልፍ መካከል ተመትቶ ወደቀ /ሞተ/:: የሮም መንግስትም ባዶ ሆነች:: ዙፋኑን መያዝ ለቅዱስ ፋሲለደስም ሆነ ለሌሎቹ ቅዱሳን ቀላል ነበር:: ግን እነሱ ዝም ብለው ጠላትን ለመዋጋት ወጡ:: በዘመኑ ደግሞ በግብጽ የፍየል እረኛ የነበረና ከልጅነቱ ሰይጣን የሚያናግረው አንድ አግሪዻዳ የሚሉት ጉልበተኛ ሰው ነበር:: ንጉሡ ከወለዳቸው ልጆች ሁለቱ ሴቶች ክፉዎች ነበሩና ትንሿ አግሪዻዳን ማንም በሌለበት አንግሣ ጠበቀቻቸው:: ስሙንም ዲዮቅልጢያኖስ አለችው:: በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሰይጣን ቀጥሎ እንደዚህ የከፋ ስም የለም:: የዓለም ክርስቲያኖችን የጨፈጨፈ ሰው ነው:: ትልቋ ደግሞ የትንሿን አይታ መክስምያኖስ የሚባል አውሬ አግብታ አነገሠችው:: ዓለምም በእነዚህ ጨካኝ ሰዎች እጅ ወደቀች:: ሠራዊቱ ሁሉ በሚሊየን ይቆጠራሉ:: የተደረገውን ሲያዩ ተበሳጩ:: ይህንን የተመለከተው ቅዱሱ ፋሲለደስ ግን ልዑላኑንና አለቆችን ሰብስቦ:- "ይህ ዓለም ከነ ክብሩ ጠፊ ነው:: ስለዚህ የተሻለውን የክርስቶስን መንግስት እንምረጥ" አላቸው:: ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ ደስ ተሰኝተው ምድራዊ ክብራቸውን ሊተው ወሰኑ:: ቀጥለውም በአንድ ቤት ተሰብስበው ይጾሙ: ይጸልዩ ገቡ:: ወደ ውጪ የሚወጡት ለምጽዋት ብቻ ነበር:: ከሃዲውም ይህንን ሲያይ የልብ ልብ ተሰማው:: ከድሮ ያሰበውንና ክርስቲያኖችን የማጥፋቱን እቅድ ሊፈጽም ምክንያት አገኘ:: አባ አጋግዮስ በሚባል መነኩሴ ምክንያት "አብያተ ክርስቲያናት ይትዐጸዋ: አብያተ ጣዖታት ይትረኀዋ-ቤተክርስቲያኖች ይዘጉ: ቤተ ጣዖቶችም ይከፈቱ" አለ:: አዽሎን: አርዳሚስ የሚባሉ ጣዖቶችንም አቆመ:: በዚህ አዋጅ ምክንያትም የክርስቲያኖች ሰቆቃ ጀመረ:: *ምድር በደም ታጠበች:: *ቅዱሳኑ ቀባሪ አጡ:: *እኩሉ ተገደለ: እኩሉ ተቃጠለ: እኩሉ ታሠረ: እኩሉም ተሰደደ:: በዚህ ጊዜ 'መራሔ ትሩፋት' ቅዱስ ፋሲለደስ ለሰማዕትነት ይበቁ ዘንድ ስለ ራሱና ስለ ወገኖቹ ጸለየ:: ቅዱስ ሚካኤልም በግርማ ወርዶ ቅዱሱን ወደ ሰማይ አወጣው:: ከቅዱሳን ጋር በገነት አስተዋውቆት: ክብረ ሰማዕታትን አሳይቶት: ከጌታ ዘንድ አስባርኮት: ከሕይወት ውሃ ምንጭም አጥምቆ መለሰው::ቅዱስ ፋሲለደስም ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ በንጉሡ ፊት ቆመ:: ንጉሡ ፈራ: እርሱ ግን በፈጣሪው ስም መሞት እንደሚፈልግ ነገረው:: ሊያባብለው ሞከረ: አልተሳካም እንጂ:: ከዚያም አስሮ ወደ አፍራቅያ (አፍሪካ) ላከው:: መጽሩስ የሚባል መኮንንም ቅዱሱን አሰቃየው:: እርሱ የሁሉ የበላይ ሲሆን ስለ ክርስቶስ ሁሉን ተወ:: አካሉ እስኪቆራረጥ ገረፉት: በምጣድ ላይ ጠበሱት: አበራዩት: በወፍጮም ፈጩት:: እርሱ ግን በፈጣሪው ታምኗልና ሁሉን ታገሰ:: ሁለት ጊዜ ገድለውት ከሞት ተነሳ:: በተአምራቱ ምክንያትም ከከተማው ሕዝብ ግማሹ ያህል ከአሕዛባዊነት ተመልሶ ሰማዕት ሆነ:: በመጨረሻም በዚህ ዕለት አንገቱን ሲቆርጡት ደምና ወተት ፈሶታል:: መላእክትም እርሱን ለመቀበል ዐየሩን ሞልተውታል:: ከልዑላኑ ወገንም የቅዱስ ፋሲለደስን ሚስትና ልጆችንጨምሮ አንድም የተረፈ የለም:: ሁሉም በሰማዕትነት አልፈዋል:: ††† እናታችን ቅድስት ታኦድራ ††† ††† ይህች ቅድስት እናታችን የትእግስት እመቤት ናት:: ትእግስቷ: ደግነቷ ፈጽሞ ይደነቃል:: ታሪኳ ደግሞ በሆነ መንገድ ከቅድስት እንባ መሪና ጋር ይገናኛል:: ቅድስት ታኦድራ ግብጻዊት ስትሆን ተወልዳ ያደገችው በእስክንድርያ ነው:: ከሕጻንነቷ ጀምራ ቅን ነበረች:: ምንም እንኳ የምናኔ ሰው ብትሆንም ወላጆቿ ያመጡላትን ባል 'እሺ' ብላ አገባች:: ለተወሰነ ጊዜም በሥጋ ወደሙ ተወስነው ከባሏ ጋር በሥርዓቱ ኖሩ:: ለቤተ ክርስቲያን ከነበራት ፍቅር የተነሳ ጠዋት ማታ ትገሰግስ ነበር:: አንድ ቀን ግን መንገድ ላይ የሆነ ፈተና ጠበቃት::ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በመልኳ ምክንያት ለኃጢአት ተግባር ይፈልጋት የነበረ አንድ ጐረምሳ ድንገት ያዛት:: ታገለችው: ግን ከአቅሟ በላይ ነበር:: ጮኸች:የሚሰማትም አልነበረም:: ሰውየው የሚፈልገውን ፈጽሞ: ከክብር አሳንሷት ሔደ:: ይህንን መቻል ለአንዲት ንጽሕት ወጣት ምን ያህል ከባድ እንደ ሆነ መረዳቱ አይከብድም:: እጅግ መጥፎ ሰው: በቀለኛም ለመሆን ከዚህ በላይ ምክንያት አይኖርም:: ቅድስቷ ግን ከወደቀችበት ተነስታ መሪር እንባን አለቀሰች:: ሕመሟን ችላ ወደ ቤቷ ላትመለስ ወደ በርሃ ተጓዘች:: ወደ ገዳም ገብታ በወንድ ስም 'አባ ቴዎድሮስ' ተብላ መነኮሰች:: በአካባቢው የሴቶች ገዳም አልነበረም:: የሚገርመው በገዳም ውስጥ ሆና ያንን ጨካኝ ሰው ይቅር አለችው:: ቀጥላም ስለ እርሱ ኃጢአት ንስሃን ወስዳ ከባዱን ቀኖና ተሸከመችለት:: ይሔ ነው እንግዲህ ሕይወተ ቅዱሳን ማለት: ራስን አሳልፎ ለጠላት መስጠት:: (ዮሐ. 15:13) ፈተናዋ ግን ቀጠለ:: ወንድ መስለዋት 'በአካባቢው ከምትገኝ ሴት ጸንሰሻል' ብለው ከገዳም አባረሯት:: ያልወለደቺውንም ልጅ ታሳድግ ዘንድ ሰጧት:: አሁንም በአኮቴት ተቀብላ ለ7 ዓመታት በደረቅ በርሃ ተሰቃየች:: ልጁንም አሳደገች:: ከዚያም ከባድ ንስሃ ሰጥተው ተቀበሏት:: ቅድስት ታኦድራ እንዲህ ስትጋደል ኑራ በዚህች ቀን ዐርፋለች:: በዕረፍቷም ቀን ክብሯ ተገልጧል:: ††† ቸር አምላክ የቅዱሳኑን ትእግስትና መንኖ ጥሪት አይንሳን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages