ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 17 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, September 29, 2022

ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 17

#መስከረም_17
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዐሥራ ሰባት በዚህች ቀን #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ የተሰቀለበት የከበረ #መስቀል በዓሉ ነው፣ #የቅድስት_ድንግል_ታኦግንስጣ እና የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ_ዲዮናስዮስ እረፍታቸው ነው።

 
መስከረም ዐሥራ ሰባት በዚች ቀን ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ለከበረ መስቀል በዓሉ ነው። ይህም የጻድቁ ንጉሥ የቈስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ከተሠወረበት የገለጠችው ነው።
የጎልጎታን ኮረብታ በአስጠረገች ጊዜ የከበረ መስቀልን አገኘችው ታላቅ ኮረብታም የሆነበት ምክንያት እንዲህ ነው። ብዙዎች ድንቆች ተአምራት ክብር ይግባውና ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመቃብሩና ከመስቀሉ የሚገለጡ ሁነው ሙታን ይነሡ ነበርና የጎበጡና በሽተኞች ሁሉ ይፈወሱ ነበር።
ስለዚህም አይሁድ ተቆጡ እንዲህም ሥርዓትን ሠርተው አዘዙ በይሁዳ አገር ሁሉና በኢየሩሳሌም ቤቱን የሚጠርግ ሁሉ ወይም አፈር ወይም ጉድፍ የሚጠርግ በናዝሬቱ ኢየሱስ መቃብር ላይ ይጥል ዘንድ እንዲህም እያደረጉ ዕሌኒ ንግሥት እስከ መጣች ድረስ ከሦስት መቶ ዓመት በላይ ኖሩ።
እርሷም በመጣች ጊዜ ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብርን እስከ አሳዩዋት ድረስ አይሁድን ይዛ አሠቃየቻቸው ያንን ኮረብታም እስከ ጠረጉ ድረስ አስገደደቻቸው የከበረ መስቀሉም ከተቀበረበት ተገልጦ ወጣ።
ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያንም ተሠራች በዚች ቀንም አከበሩዋት ለመስቀሉም በዓልን መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን አከበሩለት። የክርስቲያን ወገኖች ሁሉም ከሀገሮቻቸው በመምጣት ክብር ይግባውና ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤውን በዓል እንደሚያከብሩ ለመስቀልም ታላቅ በዓልን የሚያክብሩ ሆኑ።
ክርስቲያኖችም በጎዳና እየተጓዙ ሳሉ ስሙ ይስሐቅ የሚባል አንድ ሳምራዊ ሰው ከእርሳቸው ጋር ነበር ከእርሱም ጋር ብዙዎች ሳምራውያን ነበሩ ይህ ይስሐቅም የክርስቲያን ወገኖችን ለምን በከንቱ ትደክማላችሁ ለዕንጨትስ ልትሰግዱ እንዴት ትሔዳላችሁ እያለ ይሣለቅባቸው ነበር። ከክርስቲያን ወገኖችም ስሙ አውዶኪስ የሚባል አንድ ቄስ አለ ሕዝቡም በጎዳና ሲጓዙ የሚጠጡት ውኃ አላገኙም ነበርና ተጠሙ።
ወደ አንድ ጉድጓድም ሔዱ በውስጡም መሪር የሆነና የገማ ውኃ አገኙ እጅግም በውኃ ጥማት ተሠቃዩ። ይስሐቅም እጅግ ይሣለቅባቸው ጀመረ የቀናች ሃይማኖት ካለቻችሁ ይህ የገማና የመረረ ውኃ ተለውጦ እስቲ ጣፋጭ ይሁን ይላቸው ነበር።
ቀሲስ አውዶኪስም በሰማ ጊዜ መንፈሳዊ ቅናትን ቀንቶ ከዚያ ሳምራዊ ይስሐቅ ጋር ተከራከረ ያ ሳምራዊም በመስቀል ስም የተአምራት ኃይልን ከአየሁ እኔ በክርስቶስ አምናለሁ አለ። ያን ጊዜም ቀሲስ አውዶኪስ በዚያ በገማ ውኃ ላይ ጸለየ ውኃውም ወዲያውኑ ጣፋጭ ሆነ ከእርሱም ሕዝቡ ሁሉ እንስሶቻቸውም ጠጡ።
ሳምራዊ ይስሐቅ ግን በተጠማ ጊዜ በረዋት ከያዘው ውኃ ሊጠጣ ፈለገ ግን ገምቶ ተልቶ አገኘውና መሪር ለቅሶን አለቀሰ። ወደ ከበረ ቄስ አውዶኪስም መጥቶ ከእግሩ በታች ሰገደ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አመነ በከበረ ቄስ በአውዶኪስ ጸሎት ጣፋጭ ከሆነው ከዚያ ውኃም ጠጣ።
በዚያም ውኃ ውስጥ ታላቅ ኃይል የሚሠራ ሆነ እርሱ ለአማንያን የሚጣፍጥ ሲሆን ለከሀዲያንና ለአረማውያን የሚመር ሆነ በውስጡም የብርሃን መስቀል ታየ በአጠገቡም ውብ የሆነች ያማረች ቤተ ክርስቲያንን ሠሩ።
ሳምራዊ ይስሐቅም ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ በደረሰ ጊዜ ወደ ኤጴስቆጶሱ ሒዶ ከቤተሰቡ ጋር የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ። የከበረ መስቀልም ዳግመኛ የተገለጠበት መጋቢት ዐሥር ቀን ነው ዜናውንም በዚሁ ቀን ጽፈናል።
ምእመናንም በታላቁ ጾም መካከል በዓሉን ማክበር ስለአልተቻላቸው በዓሉን ቤተ ክርስቲያኑ በከበረችበት ቀን አደረጉ ይህም መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን ነው በዚህም ቀን አስቀድሞ ከከበረ መቃብር በንግሥት ዕሌኒ እጅ የተገለጠበት ነው።

በዚችም ቀን የከበረች ሮማዊት ታኦግንስጣ አረፈች ። ይቺም ቅድስት በደጋጎች ነገሥታት በአኖሬዎስና በአርቃዴዎስ ዘመን የነበረች ናት። በዚያም ወራት የህንድ ንጉሥ መልእክተኞች እጅ መንሻ ይዘው ወደ ንጉሥ አኖሬዎስ መጡ በሚመለሱም ጊዜ ይችን ድንግል ታኦግንስጣን አገኟት የምታነበውም መጽሐፍ በእጅዋ ውስጥ ነበር ወደ አገራቸውም ነጥቀው ወሰዷት ለህንድ ንጉሥም ሚስቶቹንና ቤተሰቦቹን የምትጠብቅ ሆነች።
በአንዲት ዕለትም የንጉሡ ልጅ አስጨናቂ በሆነ ደዌ ታመመ የከበረች ታኦግንስጣም ወስዳ በብብቷ ታቅፋ በመስቀል ምልክት አማተበችበት በዚያንም ጊዜ ዳነ ከእርሷም ስለ ተደረገው ተአምር የዚች የከበረች ድንግል ታኦግንስጣ ዜናዋ በሀገሩ ሁሉ ተሰማ ከዚያችም ቀን ወዲህ በእነርሱ ዘንድ እንደ እመቤት እንጂ እንደ አገልጋይ አልሆነችም።
ከዚህም በኋላ የህንድ ንጉሥ ወደ ጦርነት በሔደ ጊዜ ጉም ጭጋግ ዐውሎ ነፋስና ጨለማ በላዩ መጣ ንጉሡ ግን የከበረች ታኦግንስጣ ስታማትብ ስለአየ በመስቀል ምልክት ማማተብን ያውቅ ነበርና ያን ጊዜ በጭጋጉ በጉሙ በጨለማውና በጥቅሉ ነፋስ ላይ በመስቀል ምልክት አማተበ። ወዲያውኑ ፀሐይ ወጣ ታላቅ ጸጥታም ሆነ ጠላቶቹንም በዚሁ የመስቀል ምልክት ድል አደረጋቸው እጅግም ደስ አለው።
ንጉሡም ከጦርነት በተመለሰ ጊዜ ለከበረች ታኦግንስጣ። ከእግርዋ በታች ሰገደ እርሱንና ቤተሰቦቹን ሁሉ የሀገሩንም ሰዎች የከበረች የክርስትና ጥምቀትን ታጠምቀው ዘንድ ለመናት ቅድስት ታኦግንስጣም እንዲህ አለችው ይህን አደርግ ዘንድ ለእኔ አይገባኝም የሚያጠምቃችሁን ካህን ይልክላችሁ ዘንድ ወደ ንጉሥ አኖሬዎስ ላኩ።
ያን ጊዜም ከወገኖቹ ጋር የሚያጠምቀውን ካህን እንዲልክለት የህንድ ንጉሥ ወደ ንጉሥ አኖሬዎስ መልእክተኞችን ላከ ንጉሥ አኖሬዎስም ልመናውን ተቀብሎ የሚያጠምቃቸውን ቄስ ላከ ቄሱም አጠመቃቸው መሥዋዕትንም ቀድሶ ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው እግዚአብሔርንም የምትወድ የከበረች ድንግል ታኦግንስጣ እጅግ ደስ አላት ያንንም ቄስ መንፈሳዊ ሰላምታ ሰጠችውና ከእርሱ ቡራኬ ተቀበለች እርሱም ከእርሷ በረከትን ተቀበለ።
ከዚህም በኋላ ለራስዋ ገዳም ሠራች ብዙዎች ደናግልም ተሰበሰቡ የምንኩስና ልብስንም በመልበስ እንደርሷ መሆንን ወደዱ እርሷም እመ ምኔት ሆነች። ያም ባሕታዊ ቄስ የክርስትና ጥምቀትን ከአጠመቃቸው በኋላ ወደ ንጉሥ አኖሬዎስ ተመልሶ የህንድን ሰዎች እንዳጠመቃቸውና ክብር ይግባውና ወደ ክርስቶስ ሃይማኖት እንደገቡ ነገረው። ንጉሥ አኖሬዎስም እጅግ ደስ አለው የሮሜ አገር ሊቀ ጳጳሳትንም ይህን ባሕታዊ ኤጲስቆጶስ አድርጎ እንዲሾምላቸው አዘዘው እርሱም ኤጲስቆጶስነት ሹሞ ከህንድ ሰዎች ላከላቸው እጅግም ደስ አላቸው።
ከዚህም በኋላ ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ሊሠሩ ጀመሩ ምሰሶዎችንም በፈለጉ ጊዜ አላገኙም በዚያም አከባቢ ታላቅ የጣዖት ቤት ነበረ በውስጡም ያማሩ ምሰሶዎች አሉ። ድንግሊቱ ታኦግንስጣም ክብር ይግባውና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ብዙ በማልቀስ ለመነች ያን ጊዜም እሊያ ምሰሶዎች ከጣዖት ቤት ፈልሰው ሐናፂዎች ከሚሹት ቦታ በቤተ ክርስቲያን መካከል ተተከሉ አማንያን ሁሉ ክብር ይግባውና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን አመሰገኑት ጣዖትን ሲያመልኩ የነበሩም ጣዖቶቻቸውን ሰብረው ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት ተመልሰው ገቡ በዚያችም አገር ታላቅ ደስታ ሆነ።
ቅድስት ድንግል ታኦግንስጣም ተጋድሎዋን ከፈጸመች በኋላ እግዚአብሔርንም አገልግላ ደስ አሰኝታ በዚያ ገዳም በደናግሉ መካከል በሰላም በፍቅር አረፈች።

በዚችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ዐሥራ አራተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ዲዮናስዮስ አረፈ። ይህንንም ቅዱስ ንጉሥ ዳኬዎስ ሊገድለው ፈልጎት ነበር ግን እግዚአብሔር ሠወረው ይህም አባት ብልህ አዋቂ ስለነበረ ብዙዎች የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን ተረጎመ።
በዘመኑም በሮም ንጉሥ በከሀዲ ዳኬዎስ እጅ ቅዱስ መርቆሬዎስ በሰማዕትነት አረፈ። ሁለተኛም ሰባቱ ደቂቅ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዓመት አንቀላፍተው ነቁ እሊህም ለጣዖታት ሊአሰግዳቸው በፈለጋቸው ጊዜ ከዳኬዎስ ፊት የሸሹ ከኤፌሶን አገር ከታላላቆች ተወላጆች ወገን የሆኑ ናቸው።
ዳግመኛም በዘመኑ የመነኰሳት አለቃ ገዳማትን የሠራ ግብጻዊው ታላቁ እንጦንዮስ ለመጀመሪያ ጊዜ መነኰስን ሆነ። ይህም ቅዱስ ዲዮናስዮስ በሊቀ ጵጵስናው ሹመት ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ። መንጋዎቹንም በትክክል በፍቅር አንድነት ጠበቃቸው እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።
በመስቀሉ ላዳነን ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages