ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 23 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, October 2, 2022

ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 23

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሃያ ሦስት በዚህች ዕለት የክርስቶስ ሙሽራው የሆነች #ቅድስት_ቴክላ መታሰቢያ በዓሏ ነው፤ ዳግመኛም #ቅዱሳን_አውናብዮስ_እና_እንድርያስ በሰማዕትነት አረፉ፡፡



መስከረም ሃያ ሦስት በዚህች ዕለት የክርስቶስ ሙሽራው የሆነች ቅድስት ቴክላ የመታሰቢያ በዓሏ ነው፡፡
ይህችውም ቅድስት ለሐዋርያው ለቅዱስ ጳውሎስ ረድእ ሆና ያገለገለች ታላቅ ሐዋርያዊት እናት ናት፡፡ የመቄዶንያ ሀገር ባለጸጎች የነበሩት ወላጆቿ ጣዖት አምላኪ ነበሩና በሕጋቸውና በሥርዓታቸው አሳደጓት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደዚህች ሀገር ገብቶ ቅዱስ ወንጌልን ሰበከ፡፡ ቅድስት ቴክላም ትምህርቱን በሰማች ጊዜ በቤቷ ሆና ሳትበላና ሳትጠጣ 3 ቀን ቆየች፡፡ ከዚህም በኋላ ለሚጠብቃት ዘበኛዋ እንዳይናገርባት በማለት የወርቅ ወለባዋን ሰጠችውና ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሄደች፡፡ እርሱም በደስታ ተቀብሎ የክርስቶስን ሃይማኖት አስተማራት፡፡ በማግሥቱም ቅድስት ቴክላን እናቷ ስትፈልጋት ከቅዱስ ጳውሎስ እግር ሥር አገኘቻት፡፡ ከዚያም ወደ መኰንኑ ዘንድ ሄዳ ልጇ ክርስቲያን መሆኗን በመናገር ከሰሰቻትና ለመኰንኑ አሳልፋ ሰጠቻት፡፡
መኰንኑም ሁለቱን ቅዱስ ጳውሎስንና ቅድስት ቴክላን እንዲያመጧቸው ወታደሮቹን ላከ፡፡ ካመጧቸውም በኋላ መጀመሪያ ቅዱስ ጳውሎስን ወደ እሳት ወረወሩት፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በተአምራት አዳነው፡፡ ቅድስት ቴክላን ግን ለሀገሩ ልጆች መቀጣጫ ትሆን ዘንድ መኰንኑ ሰውን ሁሉ ከሰበሰበ በኋላ ወደ እሳቱ እንዲወረውሯት አዘዘ፡፡ እርሷ ግን በመስቀል ሦስት ምልክት ካማተበች በኋላ በራሷ ፈቃድ ማንም ሳይነካት ዘላ ከእሳቱ ውስጥ ገባች፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጥበቃ ልክ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ እርሷም ማንም ሳያያት ከእሳቱ ውስጥ ወጥታ ቅዱስ ጳውሎስ ካለበት ደረሰች፡፡ የራሷንም ጸጉር ቆርጣ በእርሱም ወገቧን ታጥቃ ቅዱስ ጳውሎስን ተከተለችው፡፡
መኰንኑም በሕይወት መኖሯን ሰምቶ ድጋሚ አስፈልጎ አስያዛትና ሃይማኖቷን እንድትለውጥ አስገደዳት፡፡ እሺ እንዳላለችው ባወቀ ጊዜ በተራቡ አንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ጨመራት ነገር ግን አንበሶቹ ሰግደው የእግሯን ትቢያ ሲልሱላት ተመለከተ፡፡ መኰንኑም ይህንን በተመለከተ ጊዜ እርሱና ወገኖቹም ሁሉ አምነው ተጠመቁና የክርስቶስ መንጋዎች ሆኑ፡፡ ቅድስት ቴክላም የጌታችንን ወንጌል በማስተማርና ቅዱስ ጳውሎስንም በማገልገል ብዙ ከተጋደለች በኋላ መስከረም 27 ቀን ዐርፋለች፡፡

ዳግመኛም በዚች ቀን ቅዱሳን ጻድቃን መነኰሳት አውናብዮስና እንድርያስ በሰማዕትነት አረፉ። እሊህ ቅዱሳንም ከልዳ ሀገር ከታላላቆቹ ተወላጆች ናቸው ከታናሽነታቸውም በአምላካዊ ምክር ተስማምተው በሶርያ ውስጥ ከሚገኙ ገዳማት ወዳንዱ ገዳም ሒደው መነኰሳት ሆኑ።
ከዚህም በኋላ ወደ ከበረ ወደ ተመሰገነ አባ መቃርስ ሔዱ ደቀ መዛሙርቱም ሁነው ታዘዙለት ምክሩንም በመቀበል በጾም በጸሎት በገድል ሁሉ ተጠምደው የሚኖሩ ሆኑ በእንዲህ ያለ ሥራም በዚያ ሦስት ዓመት ኖሩ በጎ የሆነ ተጋድሎአቸውና የአገልግሎታቸው ዜና በተሰማ ጊዜ አውናብዮስን መርጠው ኤጲስቆጶስነት፣ እንድርያስን ቅስና ሾሙአቸው በበጎ አጠባበቅም የክርስቶስን መንጋዎች ጠበቋቸው።
ከዚህም በኋላ ሥጋቸውን ፈጽሞ እስከ አደከሙ ድረስ ተጋድሎአቸውንና አገልግሎታቸውን እጅግ አበዙ። ከሀ*ዲ ንጉሥ ዮልዮስም ስለእርሳቸው በሰማ ጊዜ ወታደሮች ልኮ ወደርሱ አስቀርቦ የክብር ባለቤት ክርስቶስን ክደው ወደ ረከሰች አምልኮቱ እንዲገቡ አዘዛቸው ያን ጊዜ እርሱንና የረከሱ ጣዖታቱን ረገሙ እርሱም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው ወደ ብዙ ክፍልም ቆራርጦ ከፋፈላቸውና ነፍሳቸውን በእግዚአብሔር እጅ ሰጡ። እያንዳንዳቸውም ሦስት ሦስት አክሊላትን ተቀበሉ አንዱ በገድል ስለ መጸመድና ስለ ምንኲስና ዋጋ፣ ሁለተኛው ስለ ክህነት አገልግሎት፣ ሦስተኛው ደማቸውን ስለ ማፍሰሳቸው ነው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages