ምን እንጸልይ? - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 8, 2022

ምን እንጸልይ?

 ምን እንጸልይ?

 



በመደበኛነት ልንጸልያቸው የሚገቡ ጸሎታት /በቤተክርስቲያናችን አባቶች በገዳማቱ በአድባራቱ የሚዘወተሩ እለታዊ ጸሎታት/ እነኚህ ናቸው፡፡
 

1.መዝሙረ ዳዊት

 

መዝሙረ ዳዊት በገዳማት ከሚኖሩ አበው መነኮሳት ባህታውያን ጀምሮ በካህናት፣ምእመናን በሁሉም ዘንድ በየእለቱ የሚጸለይ ጸሎት ነው።አባቶች ከፊደል ቆጠራው ቀጥሎ ዳዊቱን ያጠኑና ከዚህ ጊዜ ጀምረው እየደገሙት፣እየጸለዩበት ይኖራሉ።ዳዊት ሳይደግሙ ወደ ዕለታዊ ተግባራቸው አይሰማሩም።መዝሙረ ዳዊት እንደሌሎች ጸሎታት ሁሉ በየዕለቱ ተለይቶ የሚጸለይ አለው።ቀጥለን እንመልከት
ሰኞ ከ 1 – 30፣ማክሰኞ ከ 31 – 60፣ረቡዕ ከ 61 – 80፣ሐሙስ ከ 81 – 110፣አርብ ከ 111 – 130፣ቅዳሜ ከ 131 – 150
እሁድ- ጸሎተ ነቢያት እና መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ይጸለያል፡፡

 

አንድ ንጉሥ

 
መዝሙረ ዳዊትን ስንጸልይ ለዕለቱ የታዘዘውን ሃያ እና ሰላሳ መዝሙር ማድረስ ባንችል እንኳን አንድ ንጉሥ ማድረስ ይገባናል። አንድ ንጉሥ የሚባለው፡-አስር መዝሙር ነው፡፡ለምሳሌ ሰከኞ አንድ ንጉስ ለማድረስ ከፈቀዱ ከ 1 – 10 ያለውን ያደርሳሉ፡፡ከማክሰኞ ከሆነ ደግሞ ከ 30 -40 ያውን የመጀመሪያውን አስር መዝሙር ያደርሳሉ ማለት ነው፡፡ይህን ሁሉ ማድረስ ያልተቻለው ግን የተወሰኑ መዝሙራትን መርጦ በየእለቱ ያደርሳል፡፡

 

2. ውዳሴ ማርያም

 
ውዳሴ ማርያም ከተቻለ የሰባቱን ዕለታት ካልተቻለ የእለቱን ማድረስ ተገቢ ነው።የዘወትር ጸሎት ካደረስን በኋላ የዕለቱን ውዳሴ ማርያም አድርሰን ይዌድስዋ መላዕክትን ደግመን ከእመቤታችን በረከት ተሳታፊ መሆን ተገቢ ነው፡፡በዋልድባ የሚኖሩ መነኮሳት ውዳሴ ማርያም ከቅዳሴ ማርያም ሳያደርሱ ውለው አያድሩም፡፡በየአብነት ትምህርት ቤቱ የሚገኙ መምህራንና ተማሪዎች እና በየገዳማት ያሉ መነኮሳት ሁሉ ውዳሴ ማርያምን በየዕለቱ ያደርሳሉ፡፡እኛም ከአበው ተምረን ማታ ከመኝታ በፊት ወይም ጠዋት ስንነሳ ይህን ጸሎት ማድረስ ተገቢ ነው፡፡

 

3. ወንጌል ዘዮሐንስ

 
የዮሐንስ ወንጌልን በየምዕራፍ ከፋፍለን በየእለቱ ማንበብ ሌላው ጸሎት ነው፡፡አባቶች ይህንን ጸሎት በየእለቱ እያደረሱ ብዙ ተጠቅመውበታል።

 

4.ሌሎች ጸሎታት

 
ውዳሴ አምላክ፣ ሰኔ ጎለጎታ፣ መልክአ ኢየሱስ፣ መልክአ ማርያም ፣ በመዝገበ ጸሎት እንዲሁም በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍት ላይ ያሉትን ሌሎች ጸሎታት፣እንዲሁም ገድላት፣ተአምራትን፣እንደ ችሎታችን በየዕለቱ እናደርሳለን፡፡ቢያንስ ግን ይህ ሁሉ ባይሆንልን ከላይ የጠቀስነውን የመዝሙረ ዳዊትና ፣ውዳሴ ማርያምን ጸሎት ማድረስ ይገባናል፡፡

 

አጭር ጸሎት

 
በተቻኮልን እና መጻሕፍትን ለማንበብ ጨርሶውን ጊዜ በማይኖረን ሰዓት ይህንን እንድንጸልይ አንዳንድ አባቶች ይመክሩናል።አቡነ ዘበሰማያት፣ጸሎተ ሃይማኖት፣ሰላም ለኪ /ስለ ውዳሴ ማርያም ፈንታ/፣አቡነ ዘመሰማያት፣አንድ ከመዝሙረ ዳዊት/ መዝሙር 150/ በመዝሙረ ዳዊት ፈንታ/በመጨረሻም አቡነ ዘበሰማያት ማድረስ ብንችል መልካም ነው ።ጸሎተ ሃይማኖት የህይማንት መግለጫ በምህኑ እንጸልየዋለን። በመካከል ሰላም ለኪ በመድገማችንም የውዳሴ ማርያም በረከት ይደርሰናል። መዝሙረ ዳዊት 150 ስናደርስ ደግሞ ሁሉንም መዝሙራት የደገምን ያህል ይሆንልንና የዳዊቱን በረከት እናገኛለን፡፡ይህንን ሁሉ ማድረስ ካልተቻለን ግን ቢያንስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን አቡነ ዘበሰማያት ብለን ከቤታችን ልንወጣ ይገባናል።አጭር ጸሎት ከሥፍራ ሥፍራ ሊለያይ ይችላል፡;ዘጠኝ ሰላም ለኪ፣አስራ ሁለት አቡነ ዘበሰማያት በገዳማት ያሉ አበው ያደርሳሉ።

 

የጸሎት ቅደም ተከተል

 
አቡነ ዘመሰማያት: 

አንድ ከመዝሙረ ዳዊት:

ውዳሴ ማርያም: እና ሌሎችም:

ቀጥሎም አቡነ ዘመሰማያት በእንተ እግዘዕትነ ማርያም: ጸሎተ ሃይማኖት በመጨረሻም አቡነ ዘመሰማያት ኪርያላይሶን 41 ግዚ::

 

አጭር ጸሎትን እነደ መደበኛ ማድረግ ለፈተና ያጋልጣል

አጭር ጸሎት የምንጸልየው በጣም በተቸገርንበት፣

ጊዜ ባጣንበት ሰዓት ነው።

ይህንን ጸሎት እንደመደበኛ ይዞ በየእለቱ አንድ አቡነ ዘበሰማያት ብቻ መድገም ግን ስንፍና እንዳይሆን ያስፈራል።ይልቁንም በክርስትና ሕይወት ጅማሬ ላይ ያሉ ምእመናን/ወጣንያን/ክርስትናውን እስኪላመዱ ጸሎታቸው አጭር ሊሆን ይችላል። እየቆዩ ሲሄዱ ግን በጸሎት እየበረቱ ወደ መደበኛው ጸሎት መድረስ አለባቸው።ሁል ግዜ ወተት መመኘት ሁል ግዜ አልበረታውም እያሉ አጭር ጸሎት እያደረሱ መተኛት ተገቢ አይደለም።

ይህ አይነቱ አካሄድ የእግዚአብሔርን ቸርነት ለስንፍና ምክንያት አድርጎ መጠቀምም ነው።ከዚህ ጋር በቤተክርስቲያን አገልገሎት ላይ ያለንም ዳዊት መድገም ውዳሴ ማርያም ማድረስ ይጠበቅብናል።

የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ፣

ዲያቆናት፣

ቀሳውስት፣

ሰባክያነ ወንጌል፣

መዘምራን……እነዚህን ጸሎታት መጸለይ ይጠበቅባቸዋል።አልያ ግን እያወቅን ጸሎት ማድረስ እንዳለብን ብዙ ጊዜ ተምረን እንዳልተምርን ቸል ብንል ለፈተና መጋለጥ ይመጣል።ከእግዚአብሔርም ቸርነት እንድንርቅ ያደርገናል።

አቡነ ዘበሰማያት የጸሎታችን መነሻና መድረሻ ጸሎት ስናደርስ የጸሎታችን መነሻ (መጀመሪያ) አቡነ ዘበሰማያት ነው፡፡በመካከል ጸሎት አቋርጠን ከሰው የምንነጋገርበት ጉዳይ ቢገጥመን በአቡነ ዘበሰማያት ማሰር ተገቢ ነው፡፡በአቡነ ዘበሰማያት አስረን የገጠመንን ጉዳይ ፈፅመን እንመለሳለን፡፡ከዚያም አቡነ ዘበሰማያት ብለን ካቆምንበት እንቀጥላለን።ጸሎታችንን በአቡነ ዘበሰማያት ሳናስር በመሃል እንዳሻን እንዳናቋርጥ አበው ያስተምሩናል፡፡

 

የማህበር ጸሎት

 

በቤታችን ከምንጸልየው ጸሎት በተጨማሪ በቤተክርስቲያን ተገኝተን ጸሎት ማድረስ ተገቢ ነው።ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ቤት እንደመሆና በእርሱአ የሚጸለይ ጸሎት ከጸሎታት ሁሉ የላቀ ነው።በካህናት እየተመራ ፣በሕብረት ሆነን የምናደርሰው በመሆኑ ታላቅ ኃይል አለው።

እግዚአብሔር በቤተ መቅደስ የምንጸልየውን ጸሎት እንደሚሰማ ሲያመለክተን እንዲህ በማለት ነግሮናል። 

”አሁንም በዚህ ሥፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ ፣ጆሮቼም ያደምጣሉ። ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ ቀድሻለሁም ዓይኖቼ እና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።”/2 ዜና መዋ 7-15/ 

ከዚህ አንጻር በቤተ መቅደስ እየተገኘን መጸለይ ተገቢ ነው።

በሰንበት ቀን ኪዳን ማድረስ ፣

ቅዳሴ ማስቀደስ የመጀመሪያው እና ዋነኛው ተግባራችን መሆን አለበት።

በሰንበት ያለ በቂ ምክንያት ቅዳሴ የሚያስታጉል በቀደሙ አባቶች /አባ ሚካኤል ወአባ ገብረኤል/ቃል መወገዙን የተአምረ ማርያም መቅድም ይነግረናል።

ከዚህ ጋር በሰዓታት ፣በማኅሌት ጸሎታት ላይ በመገኘት ቤተ ክርስቲያናችን ካዘጋጀችልን የማይጠገብ ማእድ ልንሳተፍም ይገባናል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች የሃይማኖታችን ፍጹም ፍቅር የሚኖረን ከእነዚህ ጸሎታት ጋር ስንተዋወቅ ነው። አልያ የእንጀራ ልጅ መሆን ይመጣል። የመናፍቃንን አዳራሽ መናፈቅ ይመጣል።

ከላይ በተመለከተው የጸሎት ጊዜ እየተጠቀምን፣

የጸሎት ዓይነቶችንም በምንችለው መልኩ እያደረስን፣

በቤተ መቅደስ እየተገኘን ኪዳን እያደረስን፣

ቅዳሴ እያስቀደስን ከፈጣሪን ጋራ እለት እለት እንነጋገር::

ጸሎት ከሌለ መንፈሳዊነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ከጄነሬተሩ ተቋርጦ ገመዱ ተበጥሶ ብቻውን እንደተንጠለጠለ አምፖል መሆን ይመጣል፡፡ስለዚህ በርቱ  ጸልዩ ፈጣሪ ለሁላችንም ብርታቱን ያድለን፡፡አሜን

1 comment:

  1. በጣም ጠቃሚ ትምህርት አግኝቼበታለሁ እግዚአብሔር ይስጥልኝ በርቱ

    ReplyDelete

Post Bottom Ad

Pages