ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 15 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 15

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር ዐሥራ አምስት በዚህች ዕለት የከበረ ሕፃን #ቅዱስ_ቂርቆስና_ቅድስት_ኢየሉጣ በሰማዕትነት አረፉ፣ #ነብዩ_ቅዱስ_አብድዩ አረፈ፣ በሶርያ ክርስቲያን ወገኖች #የቅዱስ_ጎርጎርዮስን የዕረፍቱን መታሰቢያ በዓል ያከብራሉ።


ጥር ዐሥራ አምስት በዚህች ዕለት የከበረ ሕፃን ቂርቆስ እናቱ ብፅዕት ኢየሉጣ ዳግመኛ ለከበረ ሕፃን ቂርቆስ ማኅበር የሆኑ ዐሥራ አንድ ሺህ አራት ሰዎች በሰማዕትነት ሞቱ።
በዚያንም ወራት የክብር ባለቤት የሆነ ክርስቶስን በሚያምኑ የክርስቲያን ወገኖች ላይ ታላቅ መከራና ስደት ሆነ። ስሟ ኢየሉጣ የሚባል አንዲት ሴት ነበረች እርሷም ከታናሽነቷ ጀምራ ደግ ናት ስደትም እንደሆነ በሰማች ጊዜ መኰንኑን ከመፍራት የተነሣ ሕፃኗን ይዛ ከሮም ከተማ ተሰዳ የኪልቅያ አውራጃ ከሆነ ከጠርሴስ ደርሳ ከዚያም በሀገሮች ውስጥ እየተዘዋወረች ተቀመጠች።
ወደዚያች አገርም ያ ከእርሱ የሸሸችው መኰንን እለእስክንድሮስ መጣ ጭፍሮቹም ክርስቲያኖችን ፈለጓቸው። ይቺንም ቅድስት ኢየሉጣን አግኝተው ያዝዋትና ወደ መኰንኑ አደረሷት የክርስቲያን ወገንም እንደሆነች ነገሩት።
መኰንኑም ሴትዮ ተናገሪ ከወዴት ሕዝብ ወገን ነሽ ነገድሽ ምንድን ነው ሀገርሽስ ወዴት ነው አላት። የከበረች ኢየሉጣም እንዲህ ብላ መለሰችለት የአንጌቤን ሰው ለሆንኩ ለእኔ ወገኖቼ ለኢቆንዮን አገር አለቆች የሆኑ ኤሳውሮሳውያን ናቸው እኔም በአንተ ምክንያት ሸሽቼ ነበር እነሆ ዛሬ ግን በእጅህ ውስጥ ነኝ አለችው።
መኰንኑም በእጄ ውስጥ እንደተገኘሽ ታውቂያለሽን አላት አሁንም የሚሻልሽን ምረጪ ስምሽንም ተናገሪ እኔንም እሺ በይኝና ለአማልክት ሠዊ የከበረች ኢየሉጣም ለረከሱ አማልክት እኔ አልሰዋም አለችው መኰንኑም ስምሽን ስጪ ተናገሪ አላት እርሷም የኔ ስም ክርስቲያን መባል ነው አለችው። መኰንኑም ይህስ ስንፍና ነው የሚጠቅምሽ አይደለም እንዳትሞቺ ስምሽን ስጪ ተናገሪ አላት። የከበረች ኢየሉጣም የኔ ስም ክርስቲያን መባል እንደሆነ ነገርኩህ ሞት የሚሽረው በሰዎች ዘንድ የምጠራበትን ከፈለግህ ስሜ ኢየሉጣ ነው ብላ መለሰችለት።
መኰንኑም ጽኑ የሆኑ ሥቃዮችን በላይሽ ሳይመጣ ተነሥተሽ መሥዋዕትን ለአማልክት አቅርቢ አላት። የከበረች ኢየሉጣም ዕወነት ነገርን ለመሥራት የምትሻ ከሆነ ዕድሜው ሦስት ዓመት የሆነ ሕፃን ልጅ ይፈልጉ ዘንድ ወደ ሀገሩ መንደር ላክ ወዳንተም ያምጡትና የምንገዛለትንና የምናመልከውን እርሱ ይንገረን አለችው።
ያን ጊዜም የሦስት ዓመት ልጅ ይፈልጉ ዘንድ መኰንኑ ወታደሮችን ላከ የሀገር ሰዎችም ልጆቻቸውን ሠውረዋልና አላገኙም ከዚያም ከከተማው ቅጽር ውጭ በፀሐይ መውጫ ወዳለው በረሀ በኩል ወጡ የቅድስት ኢየሉጣንም ልጅ አገኙት ይህ ሕፃን የስንት ዓመት ልጅ ነው ብለው ስለርሱ ጠየቁ ሰዎችም ይህ ሕፃን የሦስት ዓመት ሲሆን የክርስቲያናዊት መበለት ልጅ ነው አሏቸው።
ያንንም ሕፃን ይዘው ወደ መኰንኑ ወሰዱት መኰንኑም መልኩ የሚያምርና ደም ግባት ያለው እንደሆነ በአየው ጊዜ ደስ የምትል ደስተኛ ሕፃን ሰላምታ ይገባሃል አለው። ሕፃኑም እኔን ደስተኛ ማለትህ መልካም ተናገርክ ላንተ ግን ደስታ የለህም እግዚአብሔር ለዝንጉዎች ደስታ የላቸውም ብሏልና ብሎ መለሰለት መኰንኑም ሕፃኑን ሳልጠይቅህ ይህን ያህል ትመልስልኛለህን አለው። ሕፃኑም ገና ከዚህ የሚበዛ ነገርን እመልስልሃለሁ አለው።
መኰንኑም ሕፃኑን ስምህ ማን ነው አለው ከንጹሕ ዐዘቅትና ከማይለወጥ ከማይጠፋ ውኃ የተገኘ ሕፃን ስሜ ክርስቲያን መባል ነው ብሎ መለሰለት። መኰንኑም ዳግመኛ እንዳትሞት ስምህን ንገረኝ አለው የከበረ ሕፃንም ስሜ ክርስቲያን መባል እንደሆነ ነገርኩህ ሞክሼ ስም የምትሻ ከሆነ እናቴ የሰየመችኝ ቂርቆስ ነው።
መኰንኑም ሕፃን ቂርቆስን እሺ በለኝና ለአማልክት ሠዋ በሥጋህም ስታድግ እሾምሃለሁ በብዙ ወርቅና ብርም አከብርሃለሁ አለው። ሕፃኑም የሰይጣን መልእክተኛ ለዕውነትም ጠላቷ የሆንክ ከእኔ ራቅ አለው።
መኰንኑም ሰምቶ ተቆጣ ደሙ እንደ ውኃ እስከሚፈስ ቆዳውን እንዲጨምቁትና እንዲገፉት አዘዘ። የከበረች ኢየሉጣም የልጅዋን ትዕግሥት ባየች ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነችው።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ ጨውና ሰናፍጭ አምጡ አለ የሁለቱንም አፍንጮቻቸውን ከፍተው ያንን ጨውና ሰናፍጭ እንዲጨምሩባቸው አዘዘ ያን ጊዜ ሕፃኑ ትእዛዝህ ለጕረሮዬ ጣፋጭ ሆነ ከማርና ከስኳርም ለአፌ ጣመኝ ብሎ ጮኸ።
ሁለተኛም መኰንኑ እንዲህ ብሎ አዘዘ የረዘሙና የተሳሉ በእሳትም እንደ ፍም የጋሉ ዐሥራ አራት የብረት ችንካሮች አምጡ ሰባቱን በእናቱ አካላት ውስጥ ጨምሩ በሕፃኑም ሁለት በጆሮዎቹ ሁለት በዐይኖቹ ሁለት በአፉና በአፍንጫው አንድ በልቡ ጨምሩ እንዲህ ሲጨመርበት ጆሮዎቹ እንዲአሩ ዐይኖቹም ይጠፉ ዘንድ አንደበቱም ይቃጠል ዘንድ ወደ ልቡም ጽኑ ሕማም ገብቶ እርሱ ከዚህ ዓለም በሞት እንዲለይ ለእናቱም እንዲሁ አድርጉ ችንካሮችም በቅዱሳኑ በሥጋቸው ሁሉ ተጨመሩ።
የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ትእዛዝ የብረቶቹ ግለት ጠፍቶ እንደ በረዶ ቀዘቀዘ ጤነኞችም ሆኑ መኰንኑም ወደ ወህኒ ወስዳችሁ በዚያ አሥራችሁ ዝጉባቸው አለ።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ የሥቃይ መሣሪያ ይሠራ ዘንድ አንዳዝዘው ብረትን የሚያቀልጥ ሰው አምጡልኝ አለ። በአመጡለትም ጊዜ ሰይጣኑ ወደ መኰንኑ ልብ ገብቶ አንደበቱን ዘጋውና መናገር ተሳነው ሕፃኑ ፈጥኖ አክሊልን ለመቀበል እንደሚተጋ ሰይጣን ስለ አወቀ ስለዚህ ዘጋው።
ከዚህም በኋላ ሕፃኑ ሠራተኛውን ጠርቶ እኔንና እናቴን የሚያሠቃዩበትን የሥቃይ መሣሪያ መሥራት ትችላለህን ይህ መኰንን ግን ምንም የሚያውቀው ነገር የለም አለው ሠራተኛውም እንደምትሻው በል ንገረኝ እንደምታዝዘኝ እኔ መሥራት እችላለሁ አለው።
ሕፃን ቂርቆስም ሊአዝዝ ጀመረ እንዲህም አለ ሁለት መላጫዎች ስፋታቸው አራት ክንድ የሆነ ለእኔና ለእናቴ ሥራ። ዳግመኛም የሚያስጨንቅ ራስን የሚመታና የሚሰብር አንገትንም የሚያሥር የሚዝቅም ሹካ ዐይንንም የሚያወልቅ አካልንም የሚበሳሳ አፍንጫንም የሚያጣምምና የሚሰብር ጆሮንም የሚልጥ ሕዋሳትን የሚፈታና የሚለያይ እንደ ልጓም ሁኖ ምላስን የሚቆርጥ በሰውነትም ውስጥ ገብቶ የሚንቀሳቀስ ቆላፋ ጉጠትን ጐኖችንም የሚፍቅና የሚቆለምም አስጨናቂ የሆነ ጉልበቶችንና ጭኖችን የሚሰብር ጅማቶችንም የሚቆራርጥ ሥሮችንም የሚመዝ በዚችም አስጨናቂ መሣሪያ ጅማቶችን የሚታታ አድርግ።
ዳግመኛም በላም አምሳል ሰፊ መቀመጫ ከናስ ሥራ ሦስት ቀዳዳዎችንም በዚያ መቀመጫ ውስጥ ቅደድ። በቁመቴም ልክ ሦስት ችንካሮችን ሥራ የችንካሮቹንም ራስ ከናስ አድርገህ በውስጡ ከሚጠሩት ዘንድ ፈጽሞ የማይለይ ልዩ ሦስት ብለህ ጻፍ።
ዳግመኛም ጠምዝዞ ወደ ላይ የሚያወጣ ሁለት መሣሪያ ሁለት መጋዞችን ሁለት የብረት ምጣዶችን ሥራ አሁንም አንድ ታላቅ ጋን ሠርተህ በውስጡ አንገትን የሚጠመዝዝና የሚሠነጥቅ ተሽከርካሪ መሣሪያ አድርግ።
በውስጥ የተሸሸገ የሆድ ዕቃን የሚመረምር እጅን ከብረት ሥራ እኔ የጻዕር ስቃይን የምሠቃይበት ይህ ነው አለ። ብረት ሠሪውም ሰምቶ እጅግ አደነቀ የሚረዱትንም ከሀገር ውስጥ መቶ ሠራተኞችን ሰብስቦ መሥራት ጀመረ በአርባ ቀንም ጨረሰ።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ እለእስክንድሮስ ቂርቆስንና እናቱን ወደ አደባባይ ያመጡአቸው ዘንድ አዘዘ ያን ጊዜ አንደበቱ ተፈትቶ ነበርና እንዲህም አለ ሕፃኑንና እናቱን ከቆዳቸው ጋር ራሳቸውን ላጩአቸውና በላያቸው የእሳት ፍሞችን ጨምሩ እርር ብለው እንዲቃጠሉ ዳግመኛም አራት ችንካሮችን ከትከሻዎቹ እስከ ተረከዙ ድረስ እንዲተክሉበት አዘዘ የእግዚአብሔርም መልአክ መጥቶ ሥቃዮችን ከርሱ አራቀ።
ዳግመኛም ከጥዋት እስከ ማታ ከሥቃይ መሣሪያዎች ውስጥ ጨምረው አዋሏቸው ግን ማሠቃየት ተሳናቸው። ከዚህም በኋላ ከማምጠቂያው ውስጥ ጨምረው መገዙአቸውና አመድ እስከሆኑ ከቅባትና ከጨው ጋር በብረት ምጣድ ውስጥ ቆሉአቸው ጌታችንም ከሞት አስነሥቶ አዳናቸው።
ወደ መኰንኑም በገቡ ጊዜ እንዲህ አላቸው በእውነት ከሙታን ተለይታችሁ የተነሣችሁ ከሆነ ይህ ጫማዬ ከእግሬ ወጥቶ እንደ ቀድሞው ሕያው እንዲሆን አድርጉ ሕፃን ቂርቆስም በጸለየ ጊዜ ያ ጫማ ታለቅ በሬ ሆነ ከአንገቱም ፍየል ወጣ።
በዚያንም ሰዓት ለዐሥራ አንድ ሽህ አራት ሰዎች በሬውንና ፍየሉን አርደው ምሳ እንዲያደርጉላቸው መኰንኑ አዘዘ እንዲህም አለ ይህ በቅቷቸው ከጠገቡ ከዚህም ሌላ ምግብ ካልፈለጉ የተሠራው ሁሉ ዕውነተኛ ነዋሪ ነው። ከዚህም በኋላ አርደው ምሳ አደረጉላቸውና ከፍየሉ ሥጋ ስድስት እንቅብ ከበሬው ሥጋ አራት እንቅብ አተረፉ መኰንኑም የተረፈውን ሥጋ አይቶ ወደ ባሕር እንዲጥሉት አዘዘ።
መኰንኑም ቢያፍር የሕፃኑን ምላስ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ጌታችንም ምላሱን መለሰለት ዳግመኛም በታላቅ ጋን ውኃ እፍልተው ሕፃን ቂርቆስንና እናቱን ኢየሉጣን ይጨምሩአቸው ዘንድ አዘዘ እናቱም አይታ ፈረች። ልጅዋም ወደ እግዚአብሔር በጸለየላት ጊዜ አምላካዊ ኃይልን አሳደረባትና ከልጅዋ ጋር ወደ ጋኑ ገባች። እንደ ውርጭም ቀዝቀዛ ሆነ ደግሞም በውስጡ መንኰራኲር ወዳለበት የብረት ምጣድ እንዲጨምሩአቸውና ሥጋቸው እሰከሚቦጫጨቅ እንዲስቡአቸው አዘዘ የእግዚአብሔርም መልአክ በሕይወት አወጣቸው።
መኰንኑም እነርሱን ማሸነፍ በተሳነው ጌዜ ቸብቸቧቸውን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ በዚያን ጊዜ ለስም አጠራሩ ስግደት የሚገባው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወረደ ሕፃን ቂርቆስንም የምትሻውን ለምነኝ አለው።
ሕፃኑም ሥጋዬ በምድር አይቀበር ስሜን ለሚጠራ መታሰቢያዬን ለሚያደርግ ቤተ ክርስቲያኔን ለሚሠራ የተጋድሎዬን መጽሐፍ ለሚጽፍና ለሚያጽፍ ወይም ለሚያነበው ለቤተ ክርስቲያኔ መባ ለሚያገባ በውስጧም ለሚጸልይ ለሁሉም ፍላጎታቸውን ስጣቸው ኃጢአታቸውንም ይቅር በል ስሜም በሚጠራበት በዚያች ቦታ የከብት ዕልቂት አይምጣ በሰውም ላይ እባር ቸነፈር በእህልም ላይ ድርቅ የውኃም ማነስ አይሁን።
መድኃኒታችንም የለመንከኝን ሁሉ እሰጥሃለሁ አንተም በቀኜ ትኖራለህ ሥጋህንም ኤልያስ በዐረገበት ሠረገላ ውስጥ አኖራለሁ አለው ሕፃን ቂርቆስም በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ ብሎት ጌታችንን አመሰገነው። ከዚህም በኋላ በሌሊቱ እኩሌታም ከእናቱ ጋር አንገቱን ተቆረጠ መድኃኒታችንም በማይጠፋ አክሊል ጋረደው ነፍሶቻቸውንም በታላቅ ክብር ከእርሱ ጋር አሳደገ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን ዕውነተኛ ነብይ አብድዩ አረፈ። ይህም ነብይ የሐናንያ ልጅ ነው። በንጉሥ ኢዮሳፍጥም ዘመን ትንቢት ተናገረ እግዚአብሔርም ስለ ትንሣኤና ስለ ፍርድ ቀን በቃሉ ነገረው።
ሁለተኛም ከእስራኤል ልጆች የሚሆነውን ከአሕዛብም ለቀሩት አጸናቸው አብዝቶ መከራቸውም ገሠጻቸውም። ይህም ንጉሥ አካዝያስ ይጠሩት ዘንድ ወደ ኤልያስ ከላካቸው ሦስተኛ መስፍን ነው። ከእርሱ አስቀድመው የመጡ እነዚያን ሁለት መስፍኖች በኤልያስ ቃል እሳት ከሰማይ ወርዳ ከእነርሳቸው ጋር ካሉ ወታደሮች ጋር በላቻቸው።
ይህ ግን ወደ ኤልያስ በመጣ ጊዜ በፊቱ ተንበርክኮ ሰግዶ ተገዛለት እንዲህም አለው የእግዚአብሔር ሰው ተገዛሁልህ የእሊህ የባሮችህ ሰውነትና የኔ ሰውነት በፊትህ ትክበር በእግዚአብሔር ነቢይ ላይ ፈጽሞ አልታበየምና ነቢዩ ኤልያስም ራራለት ወርዶም ከርሱ ጋር ወደ ንጉሡ ሔደ።
ይህም አብድዩ ከምድራዊ ንጉሥ አገልግሎት የኤልያስ አገልገሎት እንደምትበልጥ የኤልያስም አገልገሎት ለሰማያዊ ንጉሥ አገልገሎት ታደርሳለችና ይህን በልቡ ዐወቀ ስለዚህ ምድራውያን ነገሥታትን ማገልገል ትቶ ነቢይ ኤልያስን ተከተሎ አገለገለው በላዩም ከእግዚአብሔር ሀብተ ትንቢት አደረበትና ትንቢትን የሚናገር ሆነ የትንቢቱም ወራት ሃያ ዓመት ነው ከጌታችን ሥጋዌ በፊት በዘጠኝ መቶ ዓመት በሰላም በፍቅር አንድነትም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን ዳግመኛ በሶርያ አገር ያሉ የክርስቲያን ወገኖች የቅዱስ ጎርጎርዮስን የዕረፍቱን መታሰቢያ በዓል ያከብራሉ። ይህም አባት በነፍስ በሥጋ በበጎ ሥራ ሁሉ ከወላጆቹ ጋር ፍጹም ነው። እርሱ እግዚአብሔርን መፍራትንና ትምህርቶችን ተምሮ ዐውቋልና የቋንቋም ትምህርት እጅግ የሚያውቅ የዮናናውያንንም ቋንቋ የሚያነብና የሚተረጒም ለቀና ሃይማኖትም የሚቀና ሆነ በውስጡም በጎ ሥራ በጎ ጠባይ ተፈጸመለት ኑሲስ በምትባል አገርም ላይ ሳይወድ በግድ መርጠው ኤጲስቆጶስነት ሾሙት እርሷም ደሴት ናት የእግዚአብሔርንም መንጋዎች ጠበቀ በትምህርቱና በድርሰቶቹም ልቡናቸውን ብሩህ አደረገ የብሉያትንና የሐዲሳትንም መጻሕፍት ተረጐመ።
ጳጳስ ሁኖ ስለነበረው ስለ ከሀዲው መቅዶንዮስ በንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዘመን በቊስጥንጥንያ ከተማ የመቶ ሃምሳ ኤጲስቆጶሳት የአንድነት ስብሰባ በሆነ ጊዜ ይህ ጎርጎርዮስ ከአባቶች ኤጲስቆጶሳት ጋር ሁኖ የሰባልዮስን ወገኖች መቅዶንዮስንና አቡሊናርዮስን ተከራከራቸው መልስ አሳጥቶም አሳፈራቸው። ስሕተታቸውንም ገለጠ። ይህም የካቲት አንድ ቀን ተጽፎአል የእነዚህንም ክህደት አስወገደ በቃሉ ሰይፍነትም የንባባቸውን የስሕተት ሐረግ ቆራርጦ አጠፋ ከተሰበሰቡትም ጋር በሰላም ተመለሰ እነርሱ በድል አድራጊነት እነዚያም ከሀ**ድያን በኀፍረት ሆነው ተመለሱ ።
ወደ መልካም እርጅና ደርሶ እግዚአብሔርንም ደስ አሰኝቶ አገልገሎ በሰላም አረፈ እነሆ በዚህ ወር ጥር ሃያ አንድ ቀን ከገድሉ ጥቂት ጽፈናል ይኸውም በግብጻውያን ዕረፍቱ ነው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages