ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 19 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 19

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ዐስራ ዘጠኝ ቀን በዚህች ዕለት #ሊቀ_መላእክት_ቅዱስ_ገብርኤል ሠለስቱ ደቂቅን ከእቶን እሳት ውስጥ ያዳነበት ዕለት ነው፣ መልአከ ሞትን ለሦስት ወራት ከበራቸው ላይ ያቆሙት #አቡነ_ስነ_ኢየሱስ ዕረፍታቸው ነው፣#አቡነ_ዮሐንስ_ዘቡርልስ ዕረፍታቸው ነው፡


ታኅሣሥ ዐስራ ዘጠኝ በዚህች ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ሠለስቱ ደቂቅን ያዳነበት ነው፡፡ ንጉሥ ናቡከደነፆር ከአባታቸው ከይሁዳው ንጉሥ ከኢዮአቄም ጋር የማረካቸው አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ እግዚአብሔር በዚህች ዕለት መልአኩን ልኮ ታላቅ ተአምር አድርጎላቸዋል፡፡ ንጉሥ ናቡከደነፆር እነዚህን ወጣቶች በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ጥበብን እያስተማረ ካሳደጋቸው በኋላ በባቢሎን ሀገሮች ሁሉ ውስጥ ሾማቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ንጉሡ የወርቅ ምስል በሠራ ጊዜ መኳንንቱንና በግዛቱ ውስጥ ያሉ ሁሉ ለዚያ ምስል እንዲሰግዱ አዘዘ፡፡ በዚህም ጊዜ ለጣዖቱ ባለመስገድ እግዚአብሔርን ብቻ በማምለክ የጸኑት እነዚህ ሦስት ወጣቶች ብቻ ነበሩ፡፡ ስለ እነርሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲህ ተብሎ ነው የተጻፈው፡-
‹‹ንጉሡ ናቡከደነፆር ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነውን የወርቁን ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው፡፡ ንጉሡም ናቡከደነፆር መኳንንትንና ሹማምቶችን፥ አዛዦችንና አዛውንቶችን፥ በጅሮንዶችንና አማካሪዎችን፣ መጋቢዎችንም፣ አውራጃ ገዦችንም ሁሉ ይሰበስቡ ዘንድ፣ ንጉሡም ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ ይመጡ ዘንድ ላከ፡፡ በዚያን ጊዜም መኳንንቱና ሹማምቶቹ፣ አዛዦቹና አዛውንቶቹ፣ በጅሮንዶቹና አማካሪዎቹ፣ መጋቢዎቹና አውራጃ ገዦቹ ሁሉ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ ተሰበሰቡ፤ ናቡከደነፆርም ባቆመው ምስል ፊት ቆሙ፡፡ አዋጅ ነጋሪውም እየጮኸ እንዲህ አለ፡- ‹ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ ሆይ! የመለከትንና የእንቢልታን፣ የመሰንቆንና የክራርን፣ የበገናንና የዋሽንትን፣ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ፣ ተደፍታችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል እንድትሰግዱ ታዝዛችኋል፡፡ ተደፍቶም የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል፡፡› ስለዚህ በዚያን ጊዜ አሕዛብ ሁሉ የመለከቱንና የእንቢልታውን፣ የመሰንቆውንና የክራሩን፣ የበገናውንና የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ፣ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የተናገሩ ሁሉ ተደፉ፤ ንጉሡም ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቅ ምስል ሰገዱ፡፡
በዚያን ጊዜም ከለዳውያን ቀርበው አይሁድን ከሰሱ፡፡ ለንጉሡም ለናቡከደነፆር ተናገሩ እንዲህም አሉ ‹ንጉሥ ሆይ! ሺህ ዓመት ንገሥ፡፡ አንተ ንጉሥ ሆይ የመለከትንና የእንቢልታን፣ የመሰንቆንና የክራርን፣ የበገናንና የዋሽንትን፣ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ የሚሰማ ሰው ሁሉ ተደፍቶ ለወርቁ ምስል ይስገድ፤ ተደፍቶም የማይሰግድ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል ብለህ አዘዝህ፡፡ በባቢሎን አውራጃ ሥራ ላይ የሾምሃቸው ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም የሚባሉ አይሁድ አሉ፤ ንጉሥ ሆይ! እነዚህ ሰዎች ትእዛዝህን እንቢ ብለዋል፤ አማልክትህን አያመልኩም፥ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል አይሰግዱም፡፡› ናቡከደነፆርም በብስጭትና በቍጣ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም ያመጡ ዘንድ አዘዘ፤ እነዚህንም ሰዎች ወደ ንጉሡ ፊት አመጡአቸው፡፡ ናቡከደነፆርም ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ሆይ! አምላኬን አለማምለካችሁ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን? አሁንም የመለከቱንና የእንቢልታውን የመሰንቆውንና የክራሩን የበገናውንና የዋሽንቱን የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ተደፍታችሁ ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፤ ባትሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው?›› ብሎ ተናገራቸው፡፡ ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም መለሱ ንጉሡን ‹ናቡከደነፆር ሆይ! በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም፡፡ የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፡፡ ነገር ግን ንጉሥ ሆይ! እርሱ ባያድነን አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ› አሉት፡፡
የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም ላይ ቍጣ ሞላበት፡፡ የፊቱም መልክ ተለወጠባቸው፡፡ እርሱም ተናገረ የእቶንም እሳት ይነድድ ከነበረው ይልቅ ሰባት እጥፍ አድርገው እንዲያነድዱት አዘዘ፡፡ ሲድራቅንና ሚሳቅንም አብደናጎንም ያስሩ ዘንድ ወደሚነድድም ወደ እቶን እሳት ይጥሉአቸው ዘንድ በሠራዊቱ ውስጥ ከነበሩት ኃያላን አዘዘ፡፡ የዚያን ጊዜም እነዚህ ሰዎች ከሰናፊላቸውና ከቀሚሳቸው ከመጐናጸፊያቸውም ከቀረውም ልብሳቸው ጋር ታስረው በሚነድድ በእቶን እሳት ውስጥ ተጣሉ፡፡ የንጉሡም ትእዛዝ አስቸኳይ ስለሆነ የእቶኑም እሳት እጅግ ስለሚነድድ፣ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም የጣሉአቸውን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን ገደላቸው፡፡ እነዚህም ሦስቱ ሰዎች ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ታስረው በሚነድደው በእቶኑ እሳት ውስጥ ወደቁ፡፡ የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ፤ አማካሪዎቹንም ‹ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን?› ብሎ ተናገራቸው፡፡ እነርሱም ‹ንጉሥ ሆይ! እውነት ነው› ብለው ለንጉሡ መለሱለት፡፡ እርሱም ‹እነሆ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቈሰላቸውም፤ የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል› ብሎ መለሰ፡፡ የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር ወደሚነድደው ወደ እሳቱ እቶን በር ቀርቦ ‹እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም! ኑ ውጡ› ብሎ ተናገራቸው፡፡ ሲድራቅና ሚሳቅም አብደናጎም ከእሳቱ መካከል ወጡ፡፡
መሳፍንቱና ሹማምቶቹም አዛዦቹና የንጉሡ አማካሪዎች ተሰብስበው እሳቱ በእነዚያ ሰዎች አካል ላይ ኃይል እንዳልነበረው፣ የራሳቸውም ጠጕር እንዳልተቃጠለች ሰናፊላቸውም እንዳልተለወጠ፣ የእሳቱም ሽታ እንዳልደረሰባቸው አዩ፡፡ ናቡከደነፆርም መልሶ ‹መልአኩን የላከ ከአምላካቸውም በቀር ማንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፣ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ፡፡ እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ይቈረጣሉ፣ ቤቶቻቸውም የጕድፍ መጣያ ይደረጋሉ ብዬ አዝዣለሁ› አለ፡፡ የዚያን ጊዜም ንጉሡ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ከፍ ከፍ አደረጋቸው፡፡›› ትንቢተ ዳንኤል 3፡1-30፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚኽች ዕለትም መልአከ ሞት መስከረም 19 ቀን መጥቶ "ጊዜ ዕረፍትህ ደርሷል" ቢላቸው "የቅዱስ ገብርኤልን በዓል ሳላከብር አይሆንም" ብለው መልአከ ሞትን ለ3 ወራት ከበራቸው ላይ ገዝተው ያቆሙት ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ስነ ኢየሱስ ዕረፍታቸው ነው።
አቡነ ስነ ኢየሱስ የትውልድ ሀገራቸው ሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን ልዩ ቦታው ልብሆ ይባላል። ከሽዋ ምድር ተነሥተው ወደ ታች አርማጭሆ በመሄድ በበረሃ ውስጥ በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡ በቅዱስ ገብርኤል መሪነት በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ ሰሜን ጎንደር አርማጭሆ በመሄድ የወርቅ ለብሆ ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ የተባለው ገዳም እንደገና አቅንተው በጽኑዕ ተጋድሎ ለብዙ ጊዜ ኖረዋል። ገዳማቸው ታች አርማጭሆ ከሳንጃ ከተማ የ3 ሰዓት መንገድ ይወስዳል።
መልአከ ሞትን ገዝተው ያቆሙት ጻድቁ ለ300 ዓመት በአንዲት ዐለት ላይ ቆመው ጸልየዋል። አቡነ ስነ ኢየሱስ ብዙ መናንያን አርድእትን ያፈሩ ታላቅ አባት ሲሆኑ በደመና እየተጫኑ ከመጓዝ ጀምሮ በርካታ አስገራሚ ተአምራትን በማድረግም ይታወቃሉ፡፡ ጻድቁ "የቅዱስ ገብርኤልን በዓል ሳላከብር አይሆንም" ብለው መልአከ ሞትን ለ3 ወራት ከበራቸው ላይ ካቆሙትና በዓሉን ካከበሩ በኃላ ታኅሣሥ 19 ቀን በሰላም ዐርፈዋል፡፡
በእርሳቸውም ግዝት መሠረት መልአከ ሞት ከቆመበት ሳይነቃነቅ ከመስከረም 1 ቀን እስከ ታኅሣሥ 19 ቀን ቆመ። ጻድቁም የቅዱስ ገብርኤልን ዝክር ዘክረው እንደፈጸሙ ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታኅሣሥ 19 ቀን ድንግል እናቱን ቅድስተ ቅዱሳን ንጽሕይት ድንግል ማርያምን፣ እልፍ አእላፍ መላእክትን፣ ሐዋርያትን፣ ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ የከበሩ መነኮሳትን አስከትሎ በመምጣት እንዲህ የሚል ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፦ "ቦታህን ሊሳለም የመጣውን ወደ ኢየሩሳሌም እንደሄደ እቆጥርለታለሁ፤ በቦታህ ከወደቀው ፍርፋሪ እንኳን በስምህ የወደቀውን ምግብ ቢመገብ አማናዊውን ሥጋዬን ደሜን እንዲቀበል አደርገዋለሁ፤ የእጀ ሰብዕ ሥራይ የተደረገበት ሰው ከመቃብርህ አፈር አዋሕዶ በውኃ ቢረጨው ሥራዩን እፈታለታለሁ:: በሬም ላምም ቢሆን ቢታመምበት በስምህ ጻድቁ ስነ ኢየሱስ ብሎ ቢማጸን በደልና ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ።" ጻድቁ በዚኽች ዕለት ዐርፈዋል።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚኽች ዕለት በሚቀድስበት ጊዜ ፊቱ እሳት ሆኖ ይታይ የነበረውና በጸሎቱ እሳት ከሰማይ አውርዶ መናፍቃንን ያቃጥል የነበረው አቡነ ዮሐንስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ይኸውም ቅዱስ ቡርልስ በምትባል አገር ኤጲስቆጶስ የነበረው ነው፡፡ በሕፃንነቱ ወላጆቹ እጅግ የከበሩ ስለነበሩ እነርሱ በሞቱ ጊዜ የወላጆቹን የተትረፈረፈ ንብረት ወስዶ ቤተ ክርስቲያን ሠራበት፡፡ የእንግዳ ማረፊያ ሕመምተኞች የሚያርፉበት ቤትም ሠራበትና በውስጡ ብዙ ነዳያንን አስቀምጦ ይንከባከባቸው ነበር፡፡ ገንዘቡንም ሁሉ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጥቶ አባ ዳንኤል ለአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት በነበረበት ወቅት ወደ አስቄጥስ ገዳም ገብቶ በአንድ ዋሻ ውስጥ እየተጋደለ መኖር ጀመረ፡፡ አባ ዳንኤልም አመነኮሱት፡፡ ሰይጣናትም በተጋድሎው ቀንተውበት በብዙ መከራና ሕመማም ፈተኑት፤ ጌታችንም ፈወሰው፡፡ ከዚህም በኋላ አቡነ ዮሐንስ ቡርልስ በምትባ አገር ኤጲስቆጶስ ሆኖ ተሾመ፡፡
በዘመኑም በሀገሮች ውስጥ ኑፋቄ የያዙ ሐሰተኞች የበዙ ነበሩ፡፡ ከላይኛው ግብፅ የተነሣ አንድ ሰው ‹‹ቅዱስ ሚካኤል ምሥጢር ይገልጥልኛል›› በማለት ብዙዎችን አሳታቸው፡፡ አባ ዮሐንስም ይህን አሳች ሰው ይዘው እንዲገርፉት አዘዘ፡፡ በተገረፈም ጊዜ ስህተቱን አምኖ ከሀገር አሳደዱት፡፡ ‹‹ነቢይ ዕንባቆም ይታየኛል ብዙ ምሥጢርም ይገልጥልኛል›› የሚል ሌላ ሰውም ተነሥቶ ነበር፡፡ በሐሰት ትምህርቱም ብዙ ተከታዮችን አፈራ፡፡ አባ ዮሐንስ ይህንንም አሳች ገርፈው እንዲያባርሩት አደረገ:: መጻሕፍቶቹንም አቃጠላቸው፡፡ የሳቱትንም በትምህርቱ መለሳቸው፡፡
አባ ዮሐንስ በሚቀድስበት ጊዜ ፊቱ እሳት ይሆናል፡፡ ሥጋውም ከእሳት ምድጃ ውስጥ እንደወጣ ይሆናል፡፡ የመላእክትን ሠራዊት በመሠዊያው ዙሪያ በግልጽ ያያቸዋልና ዕንባውንም እንደ ዝናብ ያዘንባል፡፡ ኅብስቱን በሚፈትት ጊዜ ጽዋውን ሲባርከው እንደፍሕም የጋለ ሆኖ ጽዋውን ያገኘዋል፡፡ በቀን በልተው የሚቆርቡ ክፉ ሰዎች ተነሥተው ሳለ አስተምሮ ሊመልሳቸው ቢሞክር ፈጽመው እምቢ አሉት፡፡ ባልተመለሱም ጊዜ አወገዛቸው፡፡ በዚህም ጊዜ አቡነ ዮሐንስ ወደ ጌታችን ቢጸልይ እሳት ከሰማይ ወርዳ አቃጠለቻቸውና ለብዙዎች መቀጣጫ ሆኑ፡፡ የአባ ዮሐንስ ጊዜ ዕረፍታቸው ሲደርስ እንጦንስንና መቃርስን ጌታችን ልኳቸው መጥተው የቅዱስ ዮሐንስን ዕረፍቱን ነገሩት፡፡ ሕዝቡንም ሰብስቦ በቀናች ሃይማኖት እንዲኖሩ ካስጠነቀቃቸው በኋላ ታኅሣሥ 19 በሰላም ዐረፈ፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን መላእክት፣ በጻድቃን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages