ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 27 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 27

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ሃያ ሰባት በዚህች ዕለት ኢትዮጵያዊው #ጻድቅ_አባ_በግዑ_ዘሐይቅ ዐረፈ፣ የከበረ ኤጲስ ቆጶስ #አባ_አብሳዲ ሰማዕትነት ዐረፈ።


ታኅሣሥ ሃያ ሰባት በዚህች ዕለት ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አባ በግዑ ዘሐይቅ ዐረፈ፡፡ ይኸውም በመጀመሪያ ሽፍታ የነበረ ሲሆን በመንገድ ላይ ንብረት የያዘን ሰው ማንንም የማያሳልፍ ቀማኛ ሰው ነበር፡፡ ከኃይለኛነቱ የተነሳ ሕዝቡም ሁሉ ይፈራው ነበር፡፡ በእጁ ሰይፍና ጦር ይዞ ሊዘርፍ ወደ ወደደው አገር ይገባል፡፡ እየዘረፈ በሚያገኘው ገንዘብም ራሱን በተለያዩ ምግቦችና መጠጦች ያስደስት ነበር፡፡ ባማሩ ልብሶችም ይዋብ ነበር፡፡ ገንዘቡ የተወሰደበት ሰውም እርሱ እንደወሰደበት ባወቀ ጊዜ ዳግመኛ መጥቶ የተረፈውን ቀምቶ እንዳይወስድበት ምንም አይከሰውም ነበር፡፡ በጉልምስናው ኃይለኛና ብርቱ ስለነበር ወደ እርሱ ማንም አይቀርብ ነበር፡፡
በእንደዚህ ያለ የውንብድና ሥራ ብዙ ዓመታት ከኖረ በኋላ አባ በግዑ በስም ክርስቲያን ነበረና ከዕለታት በአንደኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ አነሳስቶት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደ፡፡ ካህኑም ባየው ጊዜ ከመንገድ ገለል አደረገውና "የሕይወት ዘመንህን ሁሉ በከንቱ አሳለፍክ ዛሬ ስማ ልንገርህ፣ በዘመንህ ፍጻሜ እግዚአብሔር ይጎበኝሃል፣ በመንፈስ ቅዱስም ያድርብሃል፣ ፍጹም መነኵሴ ትሆናለህ፣ በብዙ መከራና ተጋድሎ ትኖራለህ በዚያም የነፍስህ መዳኛ ይሆናል፣ እግዚአብሔርንም ደስ ታሰኘዋለህ" አለው፡፡ ከዚህም የበዛውን ብዙ ነገር ነገረው፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ቁርባን ተቀበለ፡፡ ወደቤቱም ከተመለሰ በኋላ ካህኑ የነገሩትን እያሰበ "እስከ መቼ በስንፍናዬ እኖራለሁ? እስከ መቼስ የነፍሴን መዳኛ ሳላስብ እኖራለሁ? …" እያለ አሰበ፡፡
ከዚህም በኋላ ከዘመዶቹ ተለይቶ ከሀገሩ ወጥቶ ሄደና ወደ ባሕር ዳርቻ ደርሶ የቅዱስ እስጢፋኖስን ቤተ ክርስቲያን እጅ ነሣ፡፡ ከመነኰሳትም ማኅበር ገብቶ እነርሱን ማገልገል ጀመረ፡፡ አባ በግዑ በእግዚአብሔር ጥሪ ወደ ልቡ ተመልሶ ከመነነ በኋላ ግን እስከሞተበት ዕለት ድረስ የላመ እህል ሳይቀምስ ኖረ፡፡ ምግቡን የዛፍ ፍሬና ሜዳ ላይ የሚበቅል ቅጠል አደረገ፡፡ ዓቢይ ጾም ሲመጣም ከሰኞ እስከ ቀዳሚት ሰንበት ምንም ሳይቀም የሚጾም ሆነ፡፡ ውኃንም ሳይጠጣ ኖረ፣ ማንም ሰው ሳያውቅበት ለ5ወር ምንም ውኃ ሳይጠጣ ተቀመጠ፡፡ ከ5ወር በኋላም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደ አባ በግዑ መጣና "የእግዚአብሔር ሰው ሰላም ለአንተ ይሁን! በምን ትታወካለህ? ምንስ ያሳዝንሃል?" አለው፡፡ አባ በግዑም "ጌታዬ ከውኃ ጥም የተነሣ በጣም ስለተጨነቅሁ ነው"አለው፡፡ መልአኩም ነጥቆ ወደ ገነት ወሰደውና ከገነት ቅጠል አንሥቶ አቀመሰው፡፡ ወዲያም የአባ በግዑ ሰውነት ታደሰች፡፡ ከዚህም በኋላ" ውኃ ሳልጠጣ ተጋድሎዬን እፈጽም ይሆን!" የሚለው የኅሊና መታወክ ከእርሱ ጠፋለት፡፡
ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አባ በግዑ ለሚወደው ለአንድ ወዳጁ ለማንም እንዳይናገር በእግዚአብሔር ተስም ካስማለው በኋላ ለ5ወር ምንም ውኃ እንዳልጠጣ ምሥጢሩን ነገረው፡፡ ያ ወዳጁም ይህን ሲሰማ ደንግጦ አለቀሰ፡፡ አባ በግዑም አብሮት አለቀሰ፡፡ ወዳጁም "እስከ ዛሬ ከውኃ የተከለከለ በማን ዘንድ ሰማህ? አሁንም ቅዱሳን መነኰሳትና አበምኔቱ አያምኑህም፡፡ ይህን ምሥጢር ዛሬ ብሸሽግ በመጨረሻ ይገለጣል፡፡ ሕዝቡ፣ ነገሥታቱና መኳንንቱም ይህን ነገር ይሰማሉ ነገር ግን አያምኑም። አሁንም የምነግርህን ስማኝና ትኅርምቱን ትተህ ውኃ ጠጣ" አለው፡፡ አባ በግዑም "የነገርከኝ ሁሉ እውነት ነው ሐሰት የለውም ነገር ግን እኔ ከዚህ በኋላ እስክሞት ድረስ ዳግመኛ ውኃ እንዳልጠጣ ስለ እግዚአብሔር ትቻለሁ፡፡ ሰዎች ባያምኑ እኔ ምን ገዶኝ፣ ነገር ግን፣ በዚህ ገድል እግዚአብሔር ረዳት ይሆነኝ ዘንድ ጸልይልኝ"አለው፡፡
ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሰው አባ በግዑ ብረት አመጣና ሰንሰለቶችን ይሠራለት ዘንድ ለአንጥረኛ ሰጥቶ አሠራ፡፡ ያንን ወዳጁን ጠራውና እጆቹንና እግሮቹን በብረት ችንካር እንዲያስረው አዘዘው፡፡ "አበምኔቱን ጥራልኝ" አለውና ጠራለት፡፡ አባ በግዑም አበምኔቱ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ሲመጣ በፊቱ ሰገደለትና "አባቴ ሆይ! የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እፈጽም ዘንደ በላዬ ላይ ጸልይልኝ" አለው፡፡ "ከዛሬ ጀምሮ ከበዓቴ አልወጣም፣ ሰውም ወደኔ አይገባም" አለው፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐም በላዩ ከጸለየለት በኋላ "ለእኔም ጸልይልኝ" አለው፡፡ አባ በግዑም በቅዱስ ሚካኤል በዓል ቀን በአባ ኢየሱስ ሞዐ እጅ ቅዱስ ቊርባንን ከተቀበለ በኋላ እጆቹንና እግሮቹን በብረት ችንካር ታስሮ ብቻውን ዘግቶ በጽኑ የተጋድሎ ሕይወት ኖረ፡፡ በዓቱንም ዙሪያውን መውጫ መግቢያ እንዳይኖረው መረገው፡፡ ለምግብ የሚሆነውን የዛፍ ፍሬና የሜዳ ቅጠል ማስገቢያ የሚሆን ትንሽ ቀዳዳን አበጃና ያ ወዳጁ ያስገባለታል፡፡ አባ በግዑም ያንን በሦስት ቀን አንድ ጊዜ ብቻ ይመገባል፡፡
የእግዚአብሔር ሰው አባ በግዑ በእንዲህ ዓይነት ጽኑ በሆነ የተጋድሎ ሕይወት ሲኖር ሰውነቱ ላይ ከቆዳውና ከአጥንቱ በቀር የሚታይ ነገር እስኪጠፋ ድረስ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ፡፡ ውኃንም እስከ ሰባት ዓመት ድረስ አልጠጣም፡፡ መቆምም አይችልም ነበርና መነኰሳቶቹ ለቅዱስ ቊርባን በቃሬዛ አድርገው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይወስዱት ነበር፡፡ አባ በግዑ በእንደዚህ ዓይነቱ ለመስማት በሚከብድ እጅ የበዛ ጽኑ ተጋድሎ ካደረገ ከብዙ ድካም በኋላ ታኅሣሥ27 ቀን ዐረፈ፡፡ በዕረፍቱ ጊዜ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከድንግል ማርያምና ከአእላፍ ቅዱሳን መላእክቶቹ ጋር መጥቶ እንዲህ የሚል ቃል ኪዳን ገባለት "ስምህን ለጠራ ፣መታሰቢያህን ላደረገ፣ ወደ ተቀበርክበት ቦታ ሄዶ ለተሳለመ፣ በበዓልህ ቀን ምፅዋት ለሰጠ እስከ ሰባት ትውልድ እምርልሃለሁ ዳግመኛም በጸሎትህ አምኖ ከመልካም ሥራ የሠራ የገድልህን መጽሐፍ የሰማ ሁሉ የእሳቱን ባሕር በግልጽ ይለፍ። ወደ መንግሥተ ሰማያትም ይግባ" አለው።
ለሰው ምንም ውኃ ሳይጠጣ ሰባት ዓመት መኖር ይቻለዋልን!?" በብዙ ሲጋደሉ እንደኖሩ የቅዱሳንን ገድላቸውን ሰምተናል፡፡ ነቢይ ዕዝራ የዱር ዛፍ ፍሬ እየተመገበ ውኃም እየጠጣ በምድረ በዳ እየጾመ ኖረ፡፡ ነቢይ ኢሳይያስም የሜዳ ጎመን እየቆረጠ ከእርሱም እየተመገበ ውኃም እየጠጣ በተራራ እየጾመ ኖረ፡፡ እግዚአብሔር ስሙን "የበረሃ፡ኮከብ" ብሎ የጠራው የመነኰሳት በኩር የሆነ አባ እንጦንስና አባ መቃርስም በደረቅ ኅብስትና በውኃ ብቻ ሲጋደሉ ኖሩ፡፡ እኚህ ምድራዊያን ሲሆኑ ሰማያውያን ሆኑ፡፡ ነቢይ ኤልያስም በኅብስትና በውኃ ብቻ በምድረ በዳ ሲጋደል ኖረ፡፡ ይህ አባ በግዑ ግን ሰባት ዓመት ሙሉ ውኃ ሳይቀምስ ኖረ፡፡ ከመነነ በኋላ እስከ ሞተበት ዕለት ድረስ እህል የሚባል አልቀመሰም፡፡ እርሱ ግን ራሱን በእግዚአብሔር ፊት ዝቅ ያደርግና በትሕትናም ሆኖ ስለ ኃጢአቱ ሁል ጊዜ ያለቅስ ነበር፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ሰው አባ በግዑ ይህን ሁሉ የተጋደለ በራሱ ኃይል አይደለም፤ በእግዚአብሔር ኃይል ነው እንጂ፡፡
"አንተም ወንድሜ ሆይ ራስህን ዕወቅ፡፡ ምንም ተጋድሎን ብታደርግ ጾምኩ፣ ተራብኩ፣ ስለ እግዚአብሔርም ብዬ ራሴን አደከምኩ፣ እግዚአብሔርንም ስላገለገልኩ በሥራዬም እድናለሁ አትበል፡፡ መጨረሻህን አታውቅም፡፡ አንተ ግን ስለ እግዚአብሔር ብለህ ራስህን ኃጥእ አድርግ ያን ጊዜ እግዚአብሔር ያጸድቅሃልና፡፡ ወዳጄ ሆይ በእግዚአብሔር ዘንድ እንድትመሰገን ራስህን አታመስግን፤ ሌሎችም ያመሰግኑህ ዘንድ አትውደድ፡፡ ክብር ታገኝ ዘንድ ትሕትናን ገንዘብ አድርግ መጨረሻውን ሳታውቅ ሰው ሲበድል ብታይ አትጥላው አትናቀውም። አንተ ግን ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር በጸሎትህ ይምረው ዘንድ ጸልይ። የእግዚአብሔር ምሕረት ብዙ ነውና ኃጥአንን ይምራቸዋል። ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረ ጳውሎስንም ሐዋርያ አደረገው። ቀራጭ የነበረውን ማቴዎስንም የወንጌል ጸሐፊ አደረገው። እግዚአብሔር ሽፍታ ሆኖ የሰውን ገንዘብ ሲዘርፍ የኖረ ለአባ በግዑ ምሕረት እንዳደረገለት አስተውል። እግዚአብሔር በቀኙ እንደተሰቀለው ሽፍታ በመጨረሻ ዘመኑ መረጠው የመንግሥተ ሰማያትም ወራሽ አደረገው"።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ዕለት የከበረ አባት ቅዱስ አባ አብሳዲ በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡ ከላይኛው ግብፅ የተገኙት ይህ ጻድቅ ምግባር ሃይማኖታቸው፣ ትሩፋት ተጋድሎአቸው ያማረ ነው፡፡ በዘመናቸው ከሃዲዎች የነገሡበት ዘመን ነበር፡፡ ያን ጊዜ ታላላቆች የሆኑ የላይኛው ግብጽ ኤጲስቆጶሳት አባ አብሳዲና አባ አላኒቆስ የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሆነች በቀናች ሃይማኖት ሕዝቡን እንደሚያጸኑአቸው የአማልክትንም አምልኮ እንደሚሽሩ ዜናቸውን ዲዮቅልጥያኖስ በሰማ ጊዜ መልክተኞችን ልኮ ወደርሱ አስመጥቶ ታላቅ ሥቃይን አሠቃያቸው። የከበረ አባ አብሳዲ ግን አንዲት ቀን እንዲታገሡት መልክተኞችን ለመናቸውና የቊርባን መሥዋዕትን አዘጋጅቶ ቅዳሴ ቀድሶ ለሕዝቡ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው። በቀናች ሃይማኖትም እንዲጸኑ አስተማራቸው ከዚህም በኋላ በሰላምታ ተሰናብቷቸው ከእርሳቸው ዘንድ ወጣ ሰውነቱንም በእግዚአብሔር ላይ ጥሎ ከመልክተኞች ጋር ሔደ ወደ እንዴናው ገዥ ወደ አርያኖስ ወሰዱት።
መኰንኑም አርያኖስም የአባ አብሳዲን ገጽ በአየ ጊዜ ከአርያውና ከግርማው የተነሣ አደነቀ ራራለትም እንዲህም አለው "አንተ የከበርክና የምታስፈራ ሰው ለነፍስህ እዘን የንጉሥንም ቃል ስማ"። አባ አብሳዲም እንዲህ ብሎ መለሰ "እኔ የንጉሥን ቃል ሰምቼ በዚህ በኃላፊው ዓለም ሕይወት መንግሥት ሰማያትን አልለውጥም" በመካከላቸውም ብዙ የነገር ምልልስ ሆነ ከበጎ ምክሪ ባተመለሰ ጊዜ በመንኰራኵር ያሠቃዩትና ከእሳት ማንደጃ ውስጥም ይጨምሩት ዘንድ መኰንኑ አዘዘ ይህን ሁሉ ታገሠ እግዚአብሔርም ያለ ጉዳት በጤና አስነሣው።
ከዚህም በኋላ ራሱን ይቆርጡት ዘንድ አዘዘ አባ አብሳዲም ሰምቶ ደስ አለው ልብሰ ተክህኖ ለብሶ እጆቹንም ዘርግቶ አንገቱን ለሰይፍ ሰጠ የከበረች ራሱንም ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages