ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 3 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 3

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር ሦስት በዚች ቀን #የቤተልሔም_ሕፃናት በኄሮድስ ተገደሉ፣ የከበረ አባት #የአባ_ሊባኖስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡


ጥር ሦስት በዚች ቀን ኄሮድስ ከሰብአ ሰገል እንደ ተረዳው ዘመን ልክ ሁለት ዓመት የሆናቸው ከዚያም በታች የሆኑ በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ ሁሉ ያሉ ሕፃናት ተገደሉ። ቊጥራቸውም ዐሥራ አራት እልፍ ከአራት ሺህ ነው እነርሱም ከሴቶች እንደ ተወለዱ ንጹሐን የሆኑ ናቸው።
በከበረ ወንጌል እንደተነገረ ሰብአ ሰገልም ከሔዱ በኋላ እነሆ ኄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻዋልና ተነሣ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ምድረ ግብጽ ሽሽ ተመለስ ብዬ እስከምነግርህም ከዚያ ኑር ብሎ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ነገረው። እርሱም በሌሊት ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ ግብጽ ሔደ ኄሮድስ እስቲሞት ድረስም በዚያ ኖረ ከእግዚአብሔር ዘንድ ልጄን ከግብጽ ጠራሁት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ።
ከእነዚህ ውስጥ የክብር ባለቤት ጌታችን ክርስቶስ አንዱ እንደሚሆን ኄሮድስ አስቧልና። ጌታችንም ሥራውን ሁሉ ከብቻዋ ከኃጢአት በቀር ሠራ በረቀቀ ጥበቡም ከኄሮድስ ፊት ሸሸ ኄሮድስ አግኝቶት ሊገድለው ቢአስብ ያለ ጊዜው መግደል ባለተቻለውም ነበርና ሰነፎች ሰዎች ሰው መሆኑን ምትሐት ነው ብለው በአሰቡ ነበር ስለዚህ የክብር ባለቤት ጌታችን ሸሸ ሁለተኛም እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ ወደ ግብጽ ይወርዳል ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ዳግመኛም ከክፉ ነገር እንድንሸሽ ለእኛ ሊአስተምረን የግብጽንም ጣዖታት ያጠፋቸው ዘንድ ነው።
ይህን ያህል ብዛት ያላቸውን ሕፃናት መሰብሰብና መግደል ለኄሮድስ እንዴት ተቻለው ተንኰለኛ ኄሮድስ ምክንያት ፈጥሮ የሁለት ዓመትና ከዚያም ያነሱ ሕፃናትን አሳድገን ጭፍራ እንሠራለት ዘንድ የሚያዝ የንጉሠ ነገሥት ቄሣር ደብዳቤ ከእኔ ዘንድ ደርሷል ወርቅ ብር ቀለብ ልብስም እንሰጣለን ብሎ ወደ ሀገሩ ሁሉ ላከ። ስለዚህም ከእናቶቻቸው ጋር ተሰበሰቡ ያን ጊዜ ከእርሱ ዘንድ አንድ ሽህ ሁለት መቶ ወታደሮችን አውጥቶ በተራራ ላይ አረዱአቸው። ነቢይ ኤርምያስም የተናገረው ተፈጸመ ራኄል ስለ ልጆቿ ስታለቅስ ብዙ መከራ ጩኸት ሙሾ ልቅሶ ዋይታ በራማ ተሰማ ልቅሶ መተውን መጽናናትን እምቢ አለች ልጆቿ ልጆችን አልሆኗትምና።
ዮሐንስም በራእዩ እንዲህ አለ በታላቅ ቃል ጮኹ የተመሰገንህ እውነተኛ አቤቱ እስከ መቼ ነው ስለ ደማችን ተበቅለህ በምድር ላይ በሚኖሩ ሰዎች አትፈርድባቸውምን አሉ። ከእነርሱም ወገን ለየአንዳዱ ብሩህ ልብስ ሰጥተው እንግዲህ ጥቂት ቀን ዕረፉ አሉዋቸው። እንደነርሱ ላሉ ለእግዚአብሔር ባለሟሎች እንደነርሱ ይሞቱ ዘንድ ያላቸው ወንድሞቻቸው እስከሚፈጸሙበት ቀን ድረስ እንዲህ የእሊህን ሕፃናት ነፍሳቸውን አይቷልና።
ዳግመኛም እንዲህ አለ በዙፋኑ ፊት በአራቱ እንስሶችና በሃያ አራቱ አለቆች ፊት አዲስ ምስጋና ያመሰግናሉ ከግብጽ ምድር ከተዋጁ ከዐሥራ አራት እልፍ አራት ሽህ ሕፃናት በቀር ያቺን ምስጋና ሊያውቃት የሚቻለው የለም። እነርሱም ከሴቶች እንደ ተወለዱ ንጹሐን የሆኑ ናቸው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት ዳግመኛ የከበረ አባት የአባ ሊባኖስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው ይኸውም መጣዕ ነው። የዚህ ቅዱስ የአባቱ ስም አብርሃም የእናቱም ስም ንግሥት ነው እነርሱም በወርቅና በብር እጅግ የበለጸጉ ሮማዊ ናቸው:: ልጃቸውን አባ ሊባኖስን በሃይማኖት በምግባር ኮትኩተው ካሳደጓቸው በኋላ ዕድሜያቸው ሲደርስ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ያጋቧቸው ዘንድ ከቁስጥንጥንያ አገር ሚስት ባመጡለት ጊዜ እርሱ ግን ፈጽሞ እምቢ አለ፡፡ ወደጫጉላቤትም መግባትን እምቢ አለ፡፡ በዚህም ጊዜ ነቢዩ ሳሙኤልን እንደጠራው አባታችንንም እግዚአብሔር ሦስት ጊዜ በስማቸው ጠራቸውና ‹‹ከአባትህ ተለይ አንተ የመንግሥተ ሰማያት ሙሽራ ነህ እንጂ የዚህ ምድራዊ ዓለም ሙሽራ አይደለህም›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹ወዴት እሄዳለሁ? ምንስ ላድርግ?›› ባሉ ጊዜ ወዲያው የታዘዘ መልአክ በሌሊት መጥቶ ከአባታቸው ቤት አውጥቶ ታላቁ አባት አባ ጳኩሚስ ዘንድ አደረሳቸው፡፡ ታላቁ አባት አባ ጳኩሚስም ለአባ ሊባኖስ በዓት በመስጠት ገዳመ ሥርዓትን፣ አስኬማ መላእክትን፣ ቅናተ ዮሐንስን አስተምረዋቸው አመነኮሷቸውና ከ8ቱ ቅዱሳን ጋር እንዲገናኙ አደረጓቸው፡፡
ከዚህም በኋላ ያ ከአባታቸው ቤት ወስዶ አባ ጳኩሚስ ገዳም ያደረሳቸው ያ መልአክ ድጋሚ ተገለጠላቸውና ‹‹ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ሂድና ተጋድለህን በዚያ ፈጽም ዝናህ በስፋት ይነገራል፣ ለብዙዎችም አባት ትሆናቸዋለህ›› አላቸው፡፡ ቀጥሎም ራሱ መልአኩ ወደ ኢትዮጵያ አመጣቸውና በአክሱም ተቀመጡ፡፡ በዚያም ብዙ ከተጋደሉ በኋላ ወደ ሸዋ መጡና ወንጌልን ዞረው አስተምረው ብዙ ድውያንን ፈውሰው ከዓመታት ቆይታ በኋላ ተመልሰው አክሱም ሄዱ፡፡ በአክሱምም 7 የተለያዩ ጸበሎችን ከድንጋይ ላይ በተአምራት አፍልቀው ድውያንን ፈውሰው ዕውራንን አበሩ፡፡ በዓታቸውንም ከአክሱም ጽዮን ፊት ለፊት አድርገው ሲኖሩ ከዕለታት በአንደኛው ቀን አባታችን በተአምራት ከጭንጫ ካፈለቁት ጸበል ‹‹ተራ ውሃ ነው›› ብላ አንዲት ሴት ልጇን አዝላ ልትቀዳ መጣች፡፡ ወዲውም ከቦታው ስትደርስ አድጧት ወደቀችና ልጇም አምልጥጧት ልቡን ድንጋይ መቶት ሞተ፡፡ ሴትዮዋም ስትጮህ አባ ሊባኖስ ፈጥነው ወጡና በልጁ ላይ ጸልየው በመስቀል ምልክት አማትበው ከሞት አስነሥተውታል፡፡ ሕፃኑ ልጅ ከሞት እንደተነሣ ‹‹አምላከ አባ ሊባኖስ›› ብሎ አመሰገነ፡፡
ይህንንም ደግ ሥራቸውንና ተአምራታቸውን ያዩ አንዳንድ እኩይ ካህናት በቅናት ተመልተው ‹‹ምትሃት ነው የሚያሳየው›› ብለው በጻድቁ ላይ ሕዝቡን አሳደሙባቸው፡፡ አባታችንም ካህናቱን ለመምከር ቢሞክሩም አላስቀምጥ አሏቸው፡፡ ይልቁንም ጦር ጦራቸውን ይዘው አሳደዷቸው፡፡ አባታችንም በዚህ እጅግ አዝነው ከአክሱም ተነሥተው ደርቃ ወደምትባል ቦታ ሄዱ፡፡ በዚያም በጾም በጸሎት እየተጋደሉ ሲኖሩ በእነዚያ በጠሏቸውና በክፋት በተነሡባቸው ካህናት አገር ግን ለ3 ዓመት ምንም ዝናብ ሳይዘንብ ቀረ፡፡ አባታችን በተሰደዱባት በደርቃ አገር ግን ብዙ ዝናብ ይዘንብ ነበር፡፡ አባታችን በዚያችም አገር እንደልማዳቸው ከዐለት ላይ ውኃ አፍልቀው በውኃው ብዙ ድውያንን ፈውሰውበታል፡፡ በዚያም ትልቅ በዓት መሥርተው በተጋድሎ ሲኖሩ በክፉ የተነሡባቸው እኩይ የሆኑ ካህናት መጥተው ‹‹አባታችን በከንቱ አምተንሃል በድለንሃልና ይቅር በለን፣ በድርቅ ማለቃችን ነውና ዝናብም እንዲዘንብልን ጸልይን›› ብለው ከእግራቸው ሥር ወደቁ፡፡ አባታችንም ይቅር ብለው ከፈጣሪ አማለዷቸው፡፡ ዝናቡም ወዲያው ዘነበላቸውና በአገሪቱ ጥጋብ ሆነ፡፡
ከዚህም በኋላ አባታችን አስቀድመው ወዳዩአት ወደ ሸዋ ምድር ግራርያ መጡና በዓታቸውን በአሰቦት ጫካ አደረጉ፡፡ ነገር ግን መልአኩ ተገልጦላቸው ‹‹ሊባኖስ ሆይ! ከዚህ ቦታ የአንተ መኖሪያ አይደለም፣ በዚህ ቦታ ላይ እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያገናኝ የሚያስታርቅ ታላቅ ጻድቅ ይወጣበታልና ይህ ቦታ የእርሱ ርስት ነው፣ የብዙ መነኮሳትም መንደር ይሆናል ነገር ግን የቦታው ስም በአንተ ስም ይጠራልሃል›› አላቸው፡፡ በኋላ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ተወልደው በዓታቸውን በዚያ ቦታ ላይ ሲያጸኑ ቦታው ግን ‹‹ደብረ ሊባኖስ›› ተብሎ በመጀመሪያው አባት ስም ተሰየመ፡፡ መልአኩም በሌሊት እየመራ ወደ አክሱም ወሰዳቸው፡፡
ከዚያም ‹‹ታሪክ ወደምትሠራበት ዕጣ ክፍልህ ወደሆነው ቦታ አደርስሃለሁ›› አላቸውና ወደ ኤርትራ አካለ ጉዛይ አውራጃ ልዩ ስሙ መጣዕ ወደተባለው ቦታ ወሰዳቸው፡፡ በዚያም አባታችን ድውያንን እየፈወሱ፣ ለምፃሞችን እያዳኑ፣ ሙታንን እያስነሡ ብዙ ተአምራትን እያደረጉ ወንጌልን እየሰበኩ ‹‹ሊባኖስ ዘመጣዕ›› የሚባለውን ትልቁን ገዳማቸውን መሠረቱ፡፡ በወቅቱ የነበረው ዐፄ ገብረ መስቀልም የመጀመሪያውን ቤተ ክርስቲያን አሠራላቸው፡፡
ቅዱስ ላሊበላ 23 ዓመት ሙሉ ካነጻቸው እጅግ ድንቅ 11 ቤተ መቅደሶች ውስጥ አንደኛውን በአባ ሊባኖስ ስም ሰይሞላቸዋል፡፡ በዐፄ ገብረ መስቀል ያሠራላቸው ሌላኛው ገዳማቸው ትግራይ ተንቤን ውስጥ ይገኛል፡፡ እጅግ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ የሚታወቁት አባታችን እንደ ተስዓቱ ቅዱሳን ከሮም በመምጣት በሀገራችን ላይ ብርሃንን አብርተዋል፡፡ በመጨረሻም ጥቅምት 2 ቀን ተፀንሰው ሐምሌ 3 ቀን ተወለደው ጥር 3 ቀን ባላቅ ክብር ዐርፈዋል፡፡ ቅዳሴ ቤታቸው ደግሞ ሐምሌ 3 ቀን ነው፡፡ ይኸውም ለመጀመሪያ ጊዜ በዐፄ ገብረ መስቀል ጊዜ በስማቸው ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ የተመረቀበት ዕለት ነው፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages