ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 8 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, March 16, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 8

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ስምንት በዚህች ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት የአንዱ የሐዋርያ_ቅዱስ_ማትያስ የእረፍቱ መታሰቢያ ሆነ፣ የእንዴናው መኰንን ቅዱስ_አርያኖስ በሰማእትነት አረፈ፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ_አባት_አባ_ዮልዮስ አረፈ።

መጋቢት ስምንት በዚህች እለት በአስቆሮቱ ይሁዳ ፈንታ የተሾመ ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት የአንዱ ሐዋርያ የማትያስ የእረፍቱ መታሰቢያ ሆነ። ይህም ሰውን ወደሚበሉ ሰዎች አገር ወንጌልን ይሰብክላቸው ዘንድ በሄደ ጊዜ ወዲያውኑ ይዘው አይኖቹን አውልቀው አሰሩት፡፡ ምግባቸው የመጻተኛ ሰው በድን ስለሆነ ልማዳቸውም እንዲህ ነው።
መጻተኛ ሰው ሲይዙ አይኖቹን አውልቀው በእስር ቤት ያኖሩታል። የያዙበትንም ቀን ይጽፋሉ፡፡ ሠላሳ ቀንም እስኪፈጸም ሳር ያበሉታል፡፡ ከዚያ በኋላም አውጥተው አርደው ይበሉታል።
ሐዋርያ ማትያስም ታስሮ ሳለ ሠላሳው ቀን ሳይፈጸም በጌታችን ትእዛዝ ሐዋርያው እንድርያስ ወደርሱ ደረሰ፡፡ የአገሩ ሰዎች የሚሰሩትን ክፉ ስራ አይቶ አደነቀ፡፡ እጅግም አዘነ፡፡ እስረኞችንም ሁሉ አውጥቶ የአገር ሰዎች ወደማያገኙአቸው ቦታ አኖራቸው። እነርሱ ግን ሁለቱ ሐዋርያት እንድርያስና ማትያስ ተገለጡላቸው፡፡ የአገሩም ሰዎች ያዙአቸው፡፡ በዘንገታቸውም ገመድ አስገብተው እስከ ሦስት ቀን በሀገሩ ጥጋጥግ ጎተቱአቸው፡፡ ሐዋርያት ስለዚያች አገር ሰዎች ስለድኅነታቸው ወደ እግዚአብሄር ጸለዩ፡፡ ያንጊዜ ከወህኒ ቤቱ ምሰሶ ስር ውኃን አፈለቁ፡፡ ውኃውም ከፍ ከፍ ብሎ በሀገር ውስጥ እሰከሚአጥለቀልቅና ወደ ሰዎች አንገት እስከ ደረሰ እየበዛ ሄደ።
በተጨነቁና የህይወታቸውን ተስፋ በቆረጡ ጊዜ ወደ ሐዋርያት መጡ፡፡ በፊታቸውም ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ አለቀሱ፡፡ ሐዋርያትም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመኑ እናንተም ትድናላችሁ አሉአቸው፡፡ ሁሉም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ።
ሐዋርያትም አስተማሩአቸው፡፡ ገሰፁአቸውም፡፡ የአንድነትን የሶስትነትን የመድኃኒታችን ሰው የመሆኑን ምስጢር ገለጡላቸው፡፡ ደግሞም ይህን የአራዊት ጠባይ ጌታችን ከእነርሱ ያርቅ ዘንድ ጸለዩላቸው፡፡ ከዚህ በኃላ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው፡፡ ያ የአውሬ ጠባይ ከእነርሱ ርቆ ሰው የሚመገበውን የሚመገቡ የዋሆችና ቅኖች ሆኑ።
ኤጲስቆጶሳትን ቀሳውስትንና ዲያቆናትንም ሾሙላቸው፡፡ በቀናች ሃይማኖትም እያጸኑአቸውና እያስተማሩአቸው ሠላሳ ቀኖች ያህል ከእሳቸው ጋራ ኖሩ፡፡ ከዚያም ወጥተው ሄዱ፡፡ የአገር ሰዎች ግን በሌላ ጊዜ ወደ እነርሱ እንዲመለሱላቸው ሐዋርያትን ለመኑአቸው።
ሐዋርያ ማትያስ ግን ወደ ደማስቆ ከተማ ገብቶ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰበከ። የአገርም ሰዎች ይዘው በብረት አልጋ ላይ አስተኝተው በበታቹ ስድስት ቀን ስድስት ሌሊት እሳት አነደዱ፡፡ ሊያዩትም ወደርሱ በመጡ ጊዜ ፊቱ እንደ ፀሀይ ሲበራ አገኙት፡፡ ስጋውንም ሆነ የራስ ጠጉሩን ወይም ልብሶቹን ምንም ምን እሳት አልነካውም እጅግም አደነቁ። አሁንም ዳግመኛ ሀያ አራት ቀን እስኪፈጸም ድረስ ሐዋርያ ቅዱስ ማትያስ በተኛበት በዚያ የብረት አልጋ በታች እሳትን አነደዱ።
ከዚህ በኋላም ከእሳቱ ባወጡት ጊዜ ያለ ምንም ጉዳት ጤነኛ ሆኖ አገኙት፡፡ እጅግም አደነቁ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ። እርሱም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸው፡፡ ካህናትንም ሾመላቸው፡፡ በቀናች ሃይማኖትም እያጸናቸው ከእነርሱ ጋራ ኖረ።
ከዚያም ተነስቶ ስሟ ፊላዎን ወደሚባል ከአይሁድ አገሮች ወደ አንዲቱ ሄደ፡፡ በዚያም በጎ እረፍትን አረፈ፡፡ ስጋውንም በመልካም ቦታ አኖሩ፡፡ ከስጋውም በሽተኞችን በመፈወስ ታላላቅ የሚያስደንቁ ተአምራት ተገለጡ።

በዚህች እለት የእንዴናው መኰንን ቅዱስ አርያኖስ በሰማእትነት አረፈ። ይህም እንዲህ ነው፡፡ የከበሩ ፊልሞንና አብለንዮስ በእርሱ እጅ በሰማእትነት ከሞቱ በኃላ እርሱም በስቃይ ውስጥ ሳለ ከአማንያን አንዱ ከቅዱሳን ከደማቸው ወስደህ አይንህን ብትቀባ በዳንክ ነበር አለው፡፡ ያን ጊዜም ከደማቸው ወስዶ አይኑን ቀባ ወዲያው ድኖ ፈጥኖ አየ።
ከዚያም በኋላ በቅዱሳን ላይ በአደረገው ክፉ ስራ ሁሉ በድንቁርናውም ምህረት የሌለው ስቃይ ስለአሰቃያቸው ታላቅ ጸጸት ተጸጽቶ አዘነ፡፡ ተነስቶም ጣኦታቱን ሰበረ፡፡ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አምኖ ምእመናንን ማሰቃየቱንም ተወ።
ዲዮቅልጥያኖስም ወሬውን በሰማ ጊዜ ጭፍሮቹን ልኮ ወደርሱ አስመጣው፡፡ በምን ምክንያት አማልክትን ማምለክ እንደ ተው ጠየቀው። እርሱም በቅዱሳን ሰማእታት እጅ እግዚአብሔር የሚሰራቸውን አስደናቂዎች ተአምራት ሊነግረው ጀመረ፡፡ ሕዋሳታቸውን እንዴት እንደሚቆራርጡአቸው፤ በየአይነቱ በሆነ ስቃይም ሲያሰቃዩአቸው፤ ያለምንም ጉዳት ጤነኞች ሆነው ተመልሰው እንደሚነሱ።
ዲያቅልጥያኖስም የተአምራትን ነገር ስለ ነገረው ተቆጣ፡፡ ጽኑ የሆነ ስቃይም እንዲአሰቃዩት አዘዘ። ሁለተኛም ከጉድጓድ እንዲጨምሩትና እስኪሞትም የጉድጓዱን አፍ እንዲዘጉ አዘዘ እንዲሁም አደረጉ።
የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልአኩን ልኮ ከጉድጓዱ አውጥቶ በንጉስ ዲዮቅልጥያኖስ መኝታ ላይ አቆመው። ንጉሱም በነቃ ጊዜ አይቶ ደነገጠ፡፡ ፈራ፡፡ ማነህ አንተ አለው። እርሱም እኔ የእንዴናው ገዥ አርያኖስ ነኝ ብሎ መለሰለት፡፡ ንጉሱም ደንግጦ እየተንቀጠቀጠ፤ በማቅ ጠቅልለው ከባህር እንዲአሰጥሙት አዘዘ፡፡ በባህሩም ውስጥ ነፍሱን በጌታችን እጅ ሰጠ።
እንዲህም ሆነ ቅዱስ አርያኖስ ዘመዶቹንና አገልጋዮቹን ሲሰናበታቸው እንዲህ ብሎ ነገራቸው፡፡ ለስጋዬ እርሱ እንደሚአስብና ወደአገሬ ወደ እንዴናው እንደሚመልሰው በሌሊት ራእይ እግዚአብሔር አስረድቶኛልና እናንተም በእስክንድርያ ወደብ ስጋዬን ጠብቁ አላቸው።
በአሰጠሙትም ጊዜ ጌታችን አሳ አንበሪን አዘዘ፡፡ አንበሪውም ተሸክሞ ወስዶ በእስክንድርያ ወደብ አውጥቶ በየብስ ላይ አኖረው። አሽከሮቹ ከዚያ እየጠበቁት ነበር ወደ አገሩ ወደ እንዴናው አድርሰው ከቅዱሳን ሰማእታት ከፊልሞንና ከአብላንዮስ ከስጋቸው ጋራ በአንድነት አኖሩት።

በዚችም ቀን ደግሞ በእስክንድርያ ለተሾሙ አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አስራ አንደኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት አባ ዮልዮስ አረፈ። ይህም አባት አስቀድሞ በእስክንድርያ ቄስ ሆኖ ነበር፡፡ እርሱም ባለበት ዘመን በግብፅ አገር እንደርሱ ያለ የሌለ አዋቂ ብልህ የሆነ ምሁር ነበር።
የክብር ባለቤት በሆነ በእግዚአብሔርም ፈቃድ በእስክንድርያ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ፡፡ ብዙዎች ድርሳናትንና ተግሳፃትን ደረሰ። የሹመቱም ዘመን ሠላም የሰፈነበት ነበር፡፡ በቀናች ሀይማኖትም ይጸኑ ዘንድ ህግና ስርአትንም ሁሉ እንዲጠብቁ ህዝቡን ሁልጊዜ ይመክራቸውና ያስተምራቸዋል።
በወንጌላዊው ማርቆስ ወንበር አስር አመት ከኖረ በኋላ በሠላም በፍቅር አረፈ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን፡፡ በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages